የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የኳታር ጉብኝት ፖለቲካዊ ወይንስ ኢኮኖmiያዊ?

Wednesday, 15 November 2017 12:38

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኳታር ኦfiሴላዊ ጉብኝት ለማድረግ ዶሃ ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒሰትሩና ልዑካን ቡድናቸው በዶሃ ሀማድ አለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ የኳታር  የኢኮኖሚና የንግድ ሚኒስትሩ ሼክ አህመድ ቢን ጃሲም ቢን ሞሃመድ አልጣሃኒ በቦታው በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኳታር ጉብኝት ቀደም ብሎ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር የኳታሩ ኤሚር ሼክ ቢን ሀማድ አልጣሃኒ በአዲስ አበባ ቆይታ በማድረግ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከእሳቸው ጉብኝት በኋላ ግን ከኳታር ጋር በተያያዘ የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ብዙ ግልፅ የሆነ ለውጦች ታይቶበታል።

ኳታር በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች እንደዚሁም አለም አቀፍ አሸባሪዎችን በገንዘብና በቴክኒክ ታግዛለች በሚል በሳዑዲ፣ በግብፅና በአጋሮቻቸው ዘርፈ ብዙ እገዳ የተጣለባት መሆኑ ይታወሳል። በዚህ ወቅት ኤርትራ ከሳዑዲ ጎራ በመሰለፍ አጋርነቷን ለማዕቀብ ጣዮቹ ሀገራት በግልፅ ያሳየች ሲሆን ይህንንም የኤርትራ አቋም ተከትሎ ኳታር በሠላም አስከባሪነት በኤርትራና ጂቡቲ ድንበር የነበራትን ጦር እስከማስወጣት ደርሳለች። ይህ ብቻ ሳይሆን መቀመጫውን በዚያው በኳታር ዶሃ የሆነው የአልጀዚራ ቴሌቭዥን ጣቢያም ኤርትራን በተመለከተ ከምንግዜውም በላይ አሉታዊ ዘገባዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል። ውዝግቡ እንደተፈጠረ  በገለልተኛነት ሀገራቱ ልዩነቶቻቸውን በድርድር እንዲፈቱ ኩዌት ሀሳብ ማቅረቧ የሚታወስ ሲሆን ኢትዮጵያም ቢሆን ጊዜው የኩዌትን ሀሳብ የምትደግፍ መሆኗን በመግለፅ በውዝግቡ ዙሪያ ገለልተኛ አቋምን መያዝን መርጣለች። ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በነበራቸው ፖለቲካዊ አለመግባባት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቻቸውን እስከማቋረጥ የደረሱበት ሁኔታ ነበር።

የኳታር ባለሀብቶች ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ በሆቴልና በሪል ስቴት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ከማሳየት ባለፈ በመሀል ከተማ መልሶ ማልማት ቦታ የተረከቡበት ሁኔታም አለ። ከዚህም በተጨማሪ ኳታራዊያን በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የገለፁት ሁኔታም ነበር። የሁለቱ ሀገራት የጋራ ልማት የሚከታተል “የኳታር ኢትዮጵያ የጋራ ቴኪኒካል ኮሚቴ” የተቋቋመበት ሁኔታም አለ። ይህም ኮሚቴ ከከፍተኛ የሁለቱ አመራሮች የእርስ በእርስ ጉብኝት ባሻገር የራሱን የሆነ የዕለት ሥራዎችን በመሥራት መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ወደ መሬት በሚወርዱበት ዙሪያም የሚሰራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ አለመግባባት ከ8 ዓመታት በፊት የተቋረጠውን ግንኙነታቸው እንዲመለስ ካደረጉ በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ብዙም ወደፊት ሳይገፋ በዚያው  ባለበት የቆየ ሲሆን የተሻሉ ለውጦች መታየት የጀመሩት ግን ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ነው።

ኳታር በኢኮኖሚ ካላት አቅም ባሻገር በመካከለኛው ምስራቅ ብሎም በአፍሪካው ቀንድ የራሷ የሆነ ፖለቲካዊ ሚና አላት። በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የተፈጠረውን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ተከትሎ የተከሰተውን ወታደራዊ ፍጥጫ ለማብረድ ኳታር ሁለቱን ሀገራት ለማሸማገል ጥረት ከማድረግ ጀምሮ በአወዛጋቢው ቦታ የራሷን ሠላም አስከባሪ ጦር ለዓመታት እስከማስፈር ደርሳም ነበር። ሀገሪቱ በሶማሊያ ፖለቲካም ውስጥ የራሷን ሚና ትጫወታለች። እነዚህ እስከ ምስራቅ አፍሪካ የዘለቁ የኳታር ፖለቲካዊ እጆች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ከኢትዮጵያ ጋርም የሚገናኙ ይሆናል። ኳታር ከኤርትራ ጂቡቲ አወዛጋቢ ድንበር ጦሯን ማስወጣቷን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ውጥረት የተከሰተበት ሁኔታ ነበር።

 በጊዜው የኤርትራ ጦር የተለቀቀውን ክፍት ቦታ በጦር ኃይሉ ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የወጪ ገቢ ንግድ እስትንፋስ የሆነው የኢትዮ ጂቡቲ መስመር “አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል” የሚል ስጋት ያደረባት ኢትዮጵያ፤ ጉዳዩን በቅርበት ከመከታተል ባሻገር በአካባቢው የራሷን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እሰከማድረግ የደረሰችበት ሁኔታም ነበር።

 ኳታር በኢኮኖሚ እንቅስቃሴም በኩል ኤርትራን በብዙ መልኩ ስታግዝ የቆየች ቢሆንም በመካከለኛው ምስራቅ የኳታርንና የቀድሞው ወዳጀቿን ውዝግብ ተከትሎ ኤርትራ አጋርነቷን ለሳዑዲው ወገን በማሳየቷ የሁለቱ ሀገራት የቀደመ የሞቀ ግንኙነት  ባለበት ለመቆም ተገዷል። የኢትዮ-ኤርትራ ባላንጣነት እንደተጠበቀ ሆኖ ኳቷር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከሩን ፍላጎት ከማሳየት ባሻገር ወደ ተጨባጭ ተግባራዊነቱ የገባቸው ሀገሪቱ ከመካከለኛው ምስራቅ የቀድሞው ወዳጆቿ ጋር ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ ከመግባቷ ቀደም ብሎ ነው። የኳታሩ ኤሚር ከወራት በፊት ለኦፊሴላዊ ጉብኝት በአዲስ አበባ ቆይታ ያደረጉት ኳታርን በማዕቀብ ለማንበርከክ ሳዑዲና አጋሮቿ ድንገተኛ ማዕቀባቸውን ይፋ ከማድረጋቸው ቀደም ብሎ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ሲታዩ የሁለቱ ሀገራት የግንኙነት ከፖለቲካዊ አንደምታው ይልቅ ኢኮኖሚያዊ ሚዛኑ የሚያደላ ይመስላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶሃ ሲደርሱ አቀባበል ያደረጉላቸው የሀገሪቱ የኳታር የኢኮኖሚና የንግድ ሚኒስትሩ ሼክ አህመድ ቢን ጃሲም ቢን ሞሃመድ አልጣሃኒ መሆናቸው ጉብኝቱ በአብዛኛው ኢኮኖሚያዊ አንደምታ ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
218 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 144 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us