በአማራ ክልል የመጀመሪያው የመድሃኒት ፋብሪካ ተከፈተ

Wednesday, 06 December 2017 13:00

 

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ማሪያም ወረዳ በክልሉ የመጀመሪያው የሆነ የመድሃኒት ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል። ፋብሪካው ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባው ሂውማን ዌል በተባለ የቻይና ኩባንያ ሲሆን በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አማካኝነት ባለፈው ዕሁድ ህዳር 24 ቀን 2010 ዓ.ም ተመርቋል። የመድሃኒት ፋብሪካው የተገነባው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ ከተማ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቱለፋ በተባለች ከተማ ነው።

 

የመድሃኒት ፋብሪካው ባለቤት የሆነው ሂውማን ዌል ፋርሲማዩቲካል ኢትዮጵያ የአለም አቀፉ ሂውማን ዌል ሄልዝ ኬር ግሩፕ አካል ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ለገነባው የመድሃኒት ፋብሪካ ወጪ ያደረገው አጠቃላይ የኢንቨስትመንት መጠን 20 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ታውቋል። ኩባንያው በቀጣይ በሶስት ዙር በሚያካሂደው የማስፋፊያ ሥራ የኢንቨስትመንቱን መጠን ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል። ኩባንያው ወደ ምርት የገባው የፋብሪካውን መሰረት ድንጋይ በጣለ ከአንድ ዓመት ብዙም ባልራቀ ጊዜ ወስጥ ሲሆን፤ በዚህም ፋብሪካው ከ30 በላይ መድሃኒቶችን የሚያመርት መሆኑ ታውቋል።

 

 ከእነዚህም የመድሃኒት አይነቶች መካከል በታብሌት መልኩ የሚዋጡ፣በመርፌ የሚሰጡና በሽሮፕ መልኩ የሚጠጡ መኖራቸውን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሥራ ሲገባ እስከ 3 መቶ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

 

ፋብሪካው በምርቶቹ ከኢትዮጵያ ባለፈ የምስራቅ አፍሪካ ገበያንም ለማስፋት እቅድ ይዟል። ኩባንያው ከቻይና ባለፈ በበርካታ በአውስትራሊያና እስያ ሀገራት እንደዚሁም በሰሜን አሜሪካ አድማሱን እያሰፋ ሲሆን በአፍሪካም ኢትዮጵያን ጨምሮ በማሊ እና ቡርኪናፋሶ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል። ሂውማን ዌል ኩባንያ በጥቂት ኮሌጅ ተማሪዎች እ.ኤ.አ በ1939 የተመሰረተ መሆኑን የኩባንያው ታሪክ ያመለክታል። ከዚያም ራሱን በማሳደግ ዛሬ በዓለማችን አሉ ከሚባሉት መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች መካከል አንዱ ለመሆን የበቃ መሆኑን ከራሱ ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ ይገልፃል።

 

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር የሰሜን ሸዋ ዞን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ካለው የኢንቨስትመንት ፍስት አኳያ የነበረው ተጠቃሚነት ያን ያህል የነበረ መሆኑን አስታውሰው፤ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን የዞኑ የግል ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እየጨመረ መሄዱን አመልክተዋል። እንደ አቶ የሺጥላ ገለፃ በዞኑ ከአጠቃላይ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ ውስጥ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ብቻ ከ34 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው 646 ፕሮጀክቶች ፈቃድ ወጥቶባቸዋል። 301 ያህል ፕሮጀክቶች ደግሞ 526 ሄክታር የለማ መሬት የወሰዱ መሆኑን ያመለከቱት ዋና አስተዳዳሪው፤ከእነዚህም ውስጥ ሃያ ስምንቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት የገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል። 84 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች ደግሞ በግንባታ ላይ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው ጨምረው አመልክተዋል።

 

ከእነዚህም በግንባታ ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከልም ብዙዎቹ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ምርት ሥራ ይገባሉ ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ 112 አዳዲስ ፕሮጀክቶች የመሬት ጥያቄ አቅርበው ውሳኔ እየተጠባበቁ መሆኑን አቶ የሺጥላ ገልፀዋል።

 

በኢትዮጵያ የቻይና ኢምባሲ የኢኮኖሚና ንግድ አማካሪ የሆኑት ሚስስ ሊዩ ባደረጉት ንግግር የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ መሆኑን ገልፀው፤ በኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትም ቻይና ቁጥር አንድ ሀገር መሆኗን አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቻይና የኢትዮጵያ ዋነኛ አለም አቀፍ የንግድ ሸሪክ (Trade Partner) መሆኗን በመግለፅ፤ ኢትዮጵያና ቻይና ካላቸው የሁለትዮሽ  ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ባሻገር በጤናው ዘርፍም የቆየ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆኑን አስታውሰዋል።

 

 በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ቻይናዊያን የጤና ባለሙያዎች ወደ  ኢትዮጵያ በመመጣት የተለያዩ ሙያዊ እገዛዎች ያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል። ቻይና ለኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ እያደረገችው ካለው እገዛ ጋር በተያያዘ የጥሩነሽ ቤጂግ ሆስፒታል አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚታይ መሆኑን ሚስስ ሊዩ ጨምረው አመልክተዋል።

 

እ.ኤ.አ በ2015 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው አስረኛው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ቻይና ከአፍሪካ ጋር ካላት ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ባሻገር በጤናውም ዘርፍ ከአፍሪካዊያን ጋር በጋራ ለመስራት ሰፊ እቅድ ያላት መሆኑን በቻይና ፕሬዝዳንት በኩል ተገልፆ እንደነበር ሚስ ሊዩ ጨምረው በማስታወስ፤ በኢትዮጵያ ያለው የዘርፉ ኢንቨስትመንትም የዚሁ አቅጣጫ አካል መሆኑን አመልክተዋል።

 

ቻይና በቀጣይም በኢትዮጵያ ያለውን የጤናውን ዘርፍ ኢንቨስትመንትም ለማበረታታት በብዙ መልኩ በስፋት የምትሰራ መሆኗን በአማካሪዋ በኩል  ተገልጿል። የመድሃኒት ማምረቻና ማቀነባባሪያ ኢንዱስትሪያቸውን ያላዳበሩ ታዳጊ ሀገራት የውጭ መድሃኒት አቅርቦት ጥገኛነታቸው ለበርካታ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እያጋለጧቸው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም ችግሮች መካከል ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችና ፈዋሽነት የሌላቸው የውሸት መድሐኒት ምርቶች ማራገፊያ መሆን ተጠቃሽ ነው። እነዚህን ችግሮች ለመከላከልም ሀገራት ሰፊ የሆነውን የመድሃኒት አቅርቦት ድርሻ በራሳቸው የምርት አቅርቦት እንዲሸፍኑ ይመከራል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው መድሃኒትን በሀገር ውስጥ ማምረቱ ምርቱን በቅርበት ለማግኘት ከማስቻሉም ባሻገር ፋብሪካው ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚኖረውንም የላቀ ጠቀሜታ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ የመድሃኒት ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ብሎም ሀገሪቱ ለመድሃኒት ግዢ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማዳንም በኩል መሰል ፋብሪካዎች የሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በቀላሉ የማይታይ መሆኑን አመልክተዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
130 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 230 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us