ዳሸን ባንክ 980 ሚሊዮን ብር ትርፍን አስመዘገበ

Wednesday, 06 December 2017 12:53

 

ዳሸን ባንክ ህዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው የባለአክስዮኖች 23ኛ መደበኛና 21ኛው መደበኛ ዓመታዊ ስብሰባ በ2016/17 በጀት ዓመት 980 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ። ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲታይ የ29 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ያሳየ መሆኑ ተመልክቷል።

 

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት በዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተካ አስፋው አማካኝነት የቀረበ ሲሆን በዕለቱም በቀረበው ሪፖርት እንደተመለከተው በ2016/17 በጀት ዓመት የባንኩ ዓመታዊ የሃብት መጠን በ 6 ቢሊዮን ብር እድገት በማሳየት 34 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል። ዓመታዊ የተቀማጭ ገንዘቡ መጠንንም በ22 በመቶ በማሳደግ 27 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ማድረሱ ተገልጿል።

 

 በሪፖርቱ አጠቃላይ ዳሰሳ በዓመቱ በዓለም አቀፍ፣ በሀገር አቀፍና በባንኩ ሴክተር ያለው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አጠር ባለ ምልከታ ለተሰብሳቢው ቀርቧል። በዚህም አጠቃላይ የአለም አቀፉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ቀደም ካሉት ዓመታት የተሻለ መሆኑ ተመልክቷል። ይሁንና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት አጠቃላይ እድገት ከታሰበው በታች እንደነበር በዚሁ ሪፖርት ላይ ተካቶ ቀርቧል። የኢትዮጵየን የኢኮኖሚ እድገት በተመለከተም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የታየውን ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል አለመቻሉ የተመለከተ ሲሆን፤ በተለይ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር በኢኮኖሚው ላይ የራሱን የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑን በዚሁ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል።

 

ሪፖርቱ የዳሰሳ አድማሱን በማጥበብ የባንኩ ዘርፍ አጠቃላይ ሁኔታም ተመልክቷል። እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ በሀገሪቱ ዘርፉን የተቀላቀለ አዲስ ባንክ ባይኖርም በሀገሪቱ ያሉት ባንኮች ግን በከፍተኛ ሁኔታ ቅርንጫፎቻቸውን የማስፋትና ተደራሽነታቸው ላይም በሰፊው ሰርተዋል። ዳሸን ባንክም የዚሁ ቅርንጫፍን የማስፋት ሥራ አንዱ አካል መሆኑን ያመለከቱት አቶ ተካ፤በዚህም ባንኩ ባለፈው ዓመት ብቻ 83 ቅርንጫፎችን  የከፈተ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

ይህም የባንኮች ቅርንጫፍ መስፋፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውንም የተቀማጭ (ቁጠባ) መጠንንም ከፍ እያደረገው የሄደ መሆኑ ተመልክቷል። የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አስፋው አለሙ በበኩላቸው ከባንኩ አጠቃላይ ሀብት ውስጥ 51 በመቶ የሚሆነው በብድር መልክ ወጪ የተደረገ መሆኑን ለጉባኤተኛው ገልፀዋል።  ባንኩ የተቀማጭ ገንዘቡን ከፍ በማድረጉ ረገድ የቅርንጫፎቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ፤ ብሎም ሀብትን ለማሰባሰብ በተሰራው ሥራ (Deposit Mobilisation) ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው በፕሬዝዳንቱ ገለፃ ተመልክቷል።

 

ይህ ብቻ ሳይሆን ባንኮች የሚለቁት የብድር መጠንም ከፍ እንዲል ያደረገ መሆኑንም ሪፖርቱ ጨምሮ ያመለክታል። ዳሸን ባንክ ከዚህ አንፃርም ሂሳብ ከተዘጋበት ባለፈው ዓመት የሥራ ዘመን ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ያሰራጨ መሆኑን ይኸው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ይገልፃል። ይሁንና ከወጪ ንግድ መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘ በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ባንኩ ደንበኞቹ የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ፤ በመጠንም ሆነ ጊዜውን በጠበቀ መልኩ ማቅረብ አለመቻሉን አቶ ተካ አመልክተዋል።

 

 ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር አሁንም ድረስ በተባባሰ ሁኔታ ቀጥሏል ተብሏል። እንደ አቶ ተካ ገለፃ በእነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥም ቢሆን ባንኩ 980 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍን አግኝቷል። ባንኩ ካለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ለሰራተኞቹ 70 ሚሊዮን ብር የሁለት ወር ተኩል የማበረታቻ ቦነስ የሰጠ መሆኑን ያመለከቱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፤ ይህም የገንዘብ መጠን ከባንኩ ገቢ ላይ ባይቀነስ ኖሮ የባንኩ የትርፍ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ይሆን ነበር።

 

ይህም የተመዘገበው የትርፍ መጠን እ.ኤ.አ በ2015/16 ዓ.ም ከተመዘገበው የትርፍ መጠን ጋር ሲነፃፀር የ 3 በመቶ ወይንም በብር በ29 ነጥብ 1 ሚሊዮን እድገት ማሳየቱን ሪፖርቱ ጨምሮ ያመለክታል። ባንኩ ካገኘው አጠቃላይ ትርፍ ውስጥም 212 ሚሊዮን ብር በታክስ መልኩ ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ማድረጉንም ተገልጿል።

 

 እንደ አቶ አስፋው ገለፃ የተቀማጭ ሂሳብ ደንበኞች ቁጥር 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ደርሷል። ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር በንፅፅር ሲታይ የ23 በመቶ  እድገት የታየበት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጨምረው አመልክተዋል። የባንኩ ተበዳሪ ደንበኞች ቁጥርም የ19 በመቶ እድገትን በማሳየት 12 ሺህ 8 መቶ 48 የደረሰ መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ገለፃ ጨምሮ ይገልፃል።

 

 የባንኩ የክፍያ ካርድ ተጠቃሚዎችም ቁጥር በ 29 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑ በፕሬዝዳንቱ ሪፖርት የተጠቀሰ ሲሆን በቁጥር ደረጃም 557 ሺህ የደረሰ መሆኑን ነው ፕሬዝዳንቱ የጠቀሱት። የኤቲኤም ማሽኖችንም በተመለከተ ከተገዙ የተወሰኑ ዓመታትን ያሳለፉና የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት ማሽኖችን በአዲስ ኤቲኤም ማሽኖች የመተካቱ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የቀረበው ሪፖርት ያመለክታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
108 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 229 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us