ከየትኛውም የኢትዮጵያ ከተሞች በላይ ሰፊ እምቅ የመልማት እድል ያላት ሞጆ

Wednesday, 13 December 2017 12:15

 

ሞጆ ከተማ ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በተለየ ሁኔታ በርካታ እምቅ የእድገት ዕድሎች ያሏት ከተማ ናት። ከተማዋ ሰፊ የእድገት እድሎች እንዲኖሯት ያደረጓት ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ፣ በሀገሪቱ ትልቁ የሆነው ደረቅ ወደበን የያዘች መሆኗ፣ ከአዲስ አበባ አዳማ የተዘረጋው የፍጥነት መንገድ አካል መሆኗ፣ በአሁኑ ሰዓት በግንባታ ላይ ያለው የሞጆ-ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት መነሻ ሆኗ ማገልገሏ በዋነኝነት የሚጠቀሱ የከተማዋ የእድገት ዕድሎች ናቸው።

 

 ከዚህም በተጨማሪ ከአዲስ አበባ አዳማ ከተገነባው የፍጥነት መንገድ ጎን ለጎን እያገለገለ ያለው መሃል አገርን ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኘው ነባሩ መንገድም ሞጆ ከተማን አቋርጦ የሚያልፍ ነው። ሞጆ ይህ ብቻ ሳይሆን አራት የመግቢያ በሮችን የያዘች ከተማም ጭምር ናት።

 

 ከኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ከአዲስ አበባ አዳማ ከተገነባው የፍጥነት መንገድ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የሞጆ የፍጥነት መንገድ ነው። ይህ መንገድ 202 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። መንገዱ ከአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ሞጆ 52 ኪሎ ሜትር በመነሳት በደቡብ አቅጣጫ የመቂ፣ የዝዋይ (ንባቱ) አርሲ ነገሌ ከተሞችን በማገናኘት ሀዋሳ የሚገባ ነው።

 

 የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ከደቡብ አፍሪካ-ኬፕታውን እሰከ ግብፅ -ካይሮ የሚዘረጋው አህጉራዊ ሰፊ የመንገድ ኔትወርክ አካል እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ እየተገነባ ያለ መንገድ ሲሆን በሀዋሳ በኩል ኢትዮጵያን ከኬኒያ ጋር በማገናኘት የሞምባሳን ወደብ ለመጠቀም የሚያስችል ነው።

 

ሞጆ ከተማ ካላት ዘርፈ ብዙ እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም አንፃር የሚገባትን ያህል የኢንቨስትመንት ፍሰት አግኝታለች ባይባልም ከተማዋ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩና ከ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታልን ያስመዘገቡ 199 ባለሀብቶችን እያስተናገደች መሆኗን ከከተመዋ አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ይህም የኢንቨስትመንት ፍሰት ከ9 ሺህ ላላነሱ ዜጎች  ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ይሄው መረጃ ጨምሮ ያመለክታል።

 

ከተማዋ ራሷን የበለጠ በማስተዋወቅ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ በቅርቡ አንድ የንግድ ባዛርና ኤግዚብሽን የምታካሂድ መሆኑ ታውቋል። ይህም “ሞጆ የትራንዚትና ሎጅስቲክስ የልማት አገናኝ የንግድ ባዛር እና ኤግዚብሽን በሎጂስቲክስ ከተማ” በሚል የሚካሄደው ኤግዚብሽን ከታህሳስ 15 እስከ 28 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

 

 ይህም ባዛርና ኤግዚብሽን የከተማዋን እምቅ የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት አቅም የበለጠ ለማስተዋወቅ እገዛ ያደርጋል ተብሏል። 16 የሚደርሱ የቆዳ ፋብሪካዎች አሉ። በሞጆ ከተማ በህብረተሰቡ ከሚነሱት ችግሮች መካከል አንዱ ከቆዳ ፋብሪካዎች የሚለቀቀው የተበከለ ኬሚካል ፍሳሽ ነው።

 

 በከተማዋ 16 የሚሆኑ የቆዳ ፋብሪካዎች ያሉ ሲሆን ከፋብሪካዎቹ የሚወጣው ፍሳሽ ኬሚካል በነዋሪው ብሎም በአርሶ አደሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ መሆኑን በቅሬታ መልክ ይነሳል።

 የሞጆ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እልፍነሽ ቤቻ  ከፋብሪካዎቹ የሚለቀቀው ኬሚካል በአካባቢ ብሎም በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸውን ገልፀው፤ይሁንና ችግሩን በመፍታቱ ረገድ በአሁኑ ሰዓት ጅምሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።

 

ሌላው በእነዚሁ ቆዳ ፋብሪካዎች ላይ የሚነሳው  ቅሬታ ከሰራተኞች ደህንነት ብሎም ተገቢውን ክፍያ ካለመክፈል ጋር በተያያዘ ነው። ወይዘሮ እልፍነሽ ችግሩ መኖሩን ገልፀው ይሁንና የሚታየው ችግር በሁሉም ድርጅቶች ሳይሆን በተወሰኑ ድርጅቶች መሆኑን ገልፀውልናል። ይህም ችግር ከቅጥር ጀምሮ እስከ ሰራተኛ ደህንነት (Safety) የሚዘልቅ መሆኑንም አመልክተዋል።

 

 አንድ የቆዳ ፋብሪካ ከሀገሪቱ የአሰሪና ሰራተኛ ህግ ውጪ ሰራተኞቹን በሙሉ በቀን ስራ ብቻ ቀጥሮ ሲያሰራ የነበረ መሆኑን በዋቢነት ያመለከቱት ከንቲባዋ፤ በዚህም ፋብሪካው “ሰራ የለኝም” ካለ ሰራተኞቹ እዚያው ውለው ምንም አይነት የክፍያ ሂሳብ ሳይታሰብላቸው እንዲሁ ወደቤታቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንደነበር ገልፀውልናል።

 

 መስተዳድሩ የእነዚህን አንድ ሺህ ሰባት መቶ የሚሆኑ ሰራተኞች  ቅሬታንም በመስማት የከተማ መስተዳድሩ ከባለሀብቱ ጋር ባደረገው ውይይት 60 በመቶ የሚሆኑት ሰራተኞች በቋሚነት፤ እንደዚሁም 40 በመቶ የሚሆኑትን ደግሞ በጊዜያዊነት የቅጥር ውል እንዲፈፅሙ የተደረገ መሆኑን ወይዘሮ እልፍነሽ ጨምረው አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሰራተኞች በሥራ ላይ ሳሉ ተገቢው ደህንነትን እንዲያገኙ ብሎም በምሽት ሥራ ወቅትም ተገቢው የመኝታ ቦታ እንዲኖርም ከባለሀብቶቹ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን በከንቲባዋ ተገልጿል።

 

 የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ካለመጠቀም ጋር በተያያዘ ከፋብሪካዎቹ የሚወጡት የተበከሉ ኬሚካሎች በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱበት ያለበት ሁኔታ መኖሩን በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን ወይዘሮ እልፍነሽ አመልክተዋል። ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውን ገልፀውልናል። እነዚህም ሥራዎች ፋብሪካዎቹ የራሳቸው የሆነ የፍሳሽ ኬሚካል ማጣሪያ (Treatement Plant) እንደኖራቸው ማድረግ ነው ተብሏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
141 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 198 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us