ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ኢትዮጵያ ግንኙነት ሂደቶች

Wednesday, 20 December 2017 12:40

 

የዓለም አቀፉ የገንዘብ (IMF) ማኔጂግ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ጉብኝት አድርገዋል። ይህ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የቤኒንና የጂቡቲ የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝታው አካል መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

 

 በዚሁ ጉብኝታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደዚሁም ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር ቆይታም አደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ የኢስት ኢንዱስትሪ ዞንንም የጉብኝታቸው አካል አድርገዋል። ላጋርድ ከጉብኝታቸው መልስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አወድሰው በተለይ በማምረቻው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተመለከቷቸው የቻይና እና የኔዘርላንድስ ኢንቨስትመንቶች ያስደሰቷቸው መሆኑን አመልክተዋል። ይህም እሰቴን በመጨመር የዓለም አቀፉን የጥራት ደረጃ በሟላ መልኩ ምርቶቹን የማምረቱ ሂደት የኢትዮጵያን የኤክስፖርት ገበያ በማጠናከሩ በኩልም ሰፊ ሚና የሚኖረው መሆኑንም ማኔጂግ ዳይሬክተሯ ጨምረው አመልክተዋል።

 

 ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት አባል የሆነችው ድርጅቱ ከተመሰረተበት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ ነው። ሆኖም ሀገሪቱ የድርጅቱ መስራች አባል ሀገር ከሚባሉት ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም ሌሎች ሀገራት ከተቋሙ የሚያገኙትን ጥቅም ያህል ተጠቃሚ ናት ብሎ መናገር ያስቸግራል። በተለይ የደርግ መንግስት በነበረው የፀና ኮሚኒስታዊ አቋም የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ጨምሮ ከበርካታ መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የነበረው ግንኙነት በእጅጉ የተበላሸ ነበር። ሆኖም አገዛዙ የማክተሚያ ጊዜው እየተቃረበ በነበረበት ወቅት በነበረው የለውጥ ሂደት የአለም ባንክን እና የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ምክረ ሀሳቦች የመቀበል አዝማሚያን ያሳየበት ሁኔታ ነበር።

 

በዘመነ ኢህአዴግ ያለው አካሄድ ዥንጉርጉር የሆነ ግንኙነት የሚታይበት ነው። ኢህአዴግ የስልጣን መንበሩን እንደተቆጣጠረ ሀገሪቱ ከዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ በብዙው ኢኮኖሚያዊ ማገገም ውስጥ መግባት ስለነበረባት መንግስት ከእነዚህ አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ ከመስራት ባሻገር በብዙ መልኩ ታዛዥነቱን ማንሳትም ጭምር ነበረበት። በዚህም በተለይ ብር ከዶላር አንፃር ያለው የምንዛሪ ዋጋ በተከታታይ እንዲወርድ በማድረጉ ረገድ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሰፊ ምክረ ሀሳባዊና የተፅዕኖ ሚና ነበረው።

 

ገዢው ፓርቲ  ከነበረው ኮሚኒስታዊ ተፈጥሮ አንፃር ከድርጅቶቹ ጋር አብሮ ለመስራት ያሳየው መለሳለስ ከነበረው መሰረታዊ ችግር አንፃርም ነበር። ሆኖም በሂደት በስልጣን የመጠናከር፤ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ማገገሞች ሲታዩ ሁኔታዎች በሂደት እየተለወጡ መሄድ ጀመሩ። በተለይ ከ1997 ሀገራዊ ምርጫ ቀውስ በኋላ የወጡ በርካታ አነጋጋሪ ህጎች የገዢውን ፓርቲና የምዕራባዊያኑን ግንኙነቶች ይበልጥ ከማሻከር ባሻገር ኢህአዴግ የመንግስት ቁጥጥር ያየለበትን የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚከተል መሆኑን በግልፅ ማሳየት ጀመረ። የገንዘብ ተቋማት ከምዕራቡ ዓለም የሊብራል የፖለቲካ ፍልስፍና ጋር በተያያዘ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ያለምንም መንግስት ጣልቃ ገብነት በራሱ ህግጋቶች እንዲመሩ የሚፈልጉ በመሆናቸው ልዩነቶቹ ይበልጥ በግልፅ መንፀባረቅ ጀመሩ።

 

 ገዢው ፓርቲ የነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓት (Free Market)  አካሄድን የሚቀበል መሆኑን ከገለፀ በኋላ፤ ገበያው ያለምንም መንግስት ጣልቃ ገብነት በራሱ የጨዋታ ህጎች ብቻ ይመራ የሚለውን አሰራር ግን የማይቀበል መሆኑን በሊቀመንበሩ በአቶ መለስ በኩል በተደጋጋሚ መግለፁን በስፋት ተያያዘው። የዚህ አስተምህሮ ጠንሳሽና አቀንቃኝ የነበሩት አቶ መለስ የቀደመውን የምዕራቡን አለም የሊብራል አስተሳሰብና አካሄድ በኒኦሊብራል የገበያ አክራሪነት ስም የበለጠ በማውገዝ በየመድረኩ ጎልተው መታየት የጀመሩት ከዚህ በኋላ ነበር።

 

 መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ የማረጋጋትን ሥርዓት ማስያዝን ብሎም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ የግሉ ዘርፍ ሊገባባቸው በማይችሉ የተመረጡ ኢኮኖሚ ዘርፎች መዋዕለ ነዋይን በማፍሰስ በኢኮኖሚው ውስጥ የራሱን የሆነ ጉልህ ተሳትፎ ሊኖረው እንደሚገባ በገዢው ፓርቲ በኩል የተያዘ ጥብቅ የፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ አቋም ሆኖ በግልፅ የታየውም ከዚህ በኋላ ነበር። ባለሁለት አሀዝ የተባለው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትም በምሳሌነት እየተጠቀሰ ማሳያ እንዲሆንም ተደርጓል።

 

 አቶ መለስ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ የውይይት መድረኮች ለመሳተፍ ባገኙባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ይሄንኑ ፍፁም ገበያ መር የሆነውን የምዕራቡን ዓለም ፖለቲካዊ የኢኮኖሚ ፍልስፍና ብዙም የማስኬድ መሆኑን በተደጋጋሚ ሞግተዋል።

 

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊዜው ከኢትዮጵያ ባለፈ መላው ታዳጊ ሀገራት በተለይም አፍሪካዊያን ከምዕራቡ ዓለም ኢኮኖሚያዊ አካሄድ በተለየ መልኩ የራሳቸውን አዲስ የኢኮኖሚ ዕቅድና ሥልትን ነድፈው በነፃ ገበያና በግሉ ዘርፍ ከሚመራ የኢኮኖሚ አካሄድ ይልቅ፤ የግሉን ዘረፍ በስፋት ባሳተፈ መልኩ በመንግስት ቁጥጥር ባልራቀና በእሱም የበላይነት የሚመራ የኢኮኖሚ ሥርዓትን እንዲከተሉ የራሳቸውን ምክረ ሀሳብ በአፅንዖት ይሰጡ ነበር።

 

በተለይም እ.ኤ.አ በ2008 የተከሰተው ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የምዕራቡ ዓለም መንግስታት ግዙፍ የፋይናስ ተቋማቶቻቸውን ከለየለት ክስረት ለመታደግ በጊዜው በመንግስት ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጋቸው አቶ መለስ ሀሳባቸውን በተጨባጭ ምሳሌ እያስደገፉ እንዲያስረዱም አስችሏቸው ነበር። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ የሚለውን የፓርቲውን የፖለቲካ መስመርና ባህሪ ከቀደሙት የልማታዊ መንግስታት አስተምህሮ ጋር አዳቅሎ “ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ”  የሚል የራሱን የፖለቲካ ኢኮኖሚ አካሄድ ቀይሶ ሀገሪቱን መምራት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።

 

አሁንም ቢሆን ይህ አይነቱ ጥብቅ የኢህአዴግ ፖለቲካዊ የኢኮኖሚ ዶግማ በምዕራቡ ዓለም ሊብራል አስተሳሰብ ተቀባይነት ያለው አይደለም። የዚህ የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተፅዕኖ መፍጠሪያ ዋነኛ መሳሪያዎች የሆኑት ደግሞ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ ናቸው። መንግስታት ከእነዚህ ተቋማት ጋር ለመስራት ግዴታ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች መካከል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው በብድር መልኩ የሚለቁት ጠቀም ያለ የብድር ገንዘብ ነው።

 

ይህ የሚለቀቀው የብድር ገንዘብ አንድ ሀገር ስላስፈለገው ወይንም የመበደር አቅም ስላለው ብቻ የሚበደረው ገንዘብ ሳይሆን በብዙ ቅድመ ሁኔታዎች የሚፈቀድና የሚለቀቅ ነው። ከአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት በኋላ በኢትዮጵያ በርካታ ነበራዊ ለውጦች ተከስተዋል። ባለፉት ዓመታ የተከሰቱት ተከታታይ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ኢኮኖሚው በነበረበት አካሄድ እንዳይቀጥል አድርጎታል። ባለሁለት አሃዝ የተባለው እድገት ወደ ነጠላ አሀዝ መውረዱ ተመልክቷል። እንደ ቻይና ያሉ አበዳሪ ሀገራት ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ በስፋት የሚለቁትን ብድር ማቀዘቀቀዝን መርጠዋል። የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ክፉኛ በማሽቆልቆሉ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመስፋት ላይ ነው።

 

እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች የገዢው መንግስት ባለስልጣናት በአቶ መለስ አስተምህሮ ፀንተው የግዙፎቹን የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት እጅ ጥምዘዛ የሚቋቁበት አቅም እንዳይኖራቸው አድርጓል። ይህም በመሆኑ መንግስ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ምክረ ሀሳብ በመተግበር በቅርቡ ብር ከዶላር አንፃር ያለው የምንዛሪ መጠን እንዲወርድ ማድረግ ግድ ሆኖበታል። በቀጣይም ከኢትዮጵያ መንግስት ባህሪ ውጪ የሆኑ በተፅዕኖ የሚታዩ ለውጦች ይኖራሉ ተብሎ ይታሰባል። በተለይም የፋይናሱንና የቴሌኮም ዘርፉን ከመንግስት መዳፍ የሚወጣበት አካሄድ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 እነዚህ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከመንግስታት ጋር አብረው ለመስራት በበርካታ ቅድመ የታጠሩ ናቸው። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ደግሞ የምዕራቡን ዓለም የኢኮኖሚ ፍልስና መሰረት ባደረገ መልኩ የተቃኙ በመሆናቸው በመንግስታት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

 

እነዚህ ሁኔታዎች ዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅትንም ሆነ ዓለም ባንክን በሰፊው ሲያስወቅሷቸው ቆይተዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ታዳጊ ሀገራትን ሳይቀር በአባል ድርጅትነት ሳይቀር አቅፈው ይዘዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በአጠቃላይ እስከ 189 የሚደርሱ አባል ሀገራትን በውስጡ አቅፎ የያዘ ሲሆን በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም የዚሁ ተቋም አባላት ናቸው።

 

ሀገራቱ በአባልነታቸው ከባንኩ ቀጥተኛ ገንዘብ ብድር ከማግኘት ባለፈ የፖሊሲ ምክርና ደጋፍም ጭምር የሚያገኙበት ሁኔታ አለ። ሀገራት በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብተው የክፍያ ሚዛን ችግር ሲገጥማቸው የመታደጊያ ገንዘብ የሚለቅበት አሰራርም አለ።

 

የብድሩም ሁኔታ በተመለከተ ለታዳጊ ሀገራት በልዩ ሁኔታ በረዥም ጊዜ የሚፈቀድና  በአነስተኛ ወለድ የሚታሰብ የብድር አይነትን የሚፈቅድበት አሰራር አለ። ሆኖም ቅድመ ብድር መመዘኛውና የፖሊሲ ተፅዕኖው ፈተኛው የሆነው ይህ ድርጅት በተለይ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ያመጣው ተጨባጭ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሲፈተሽ ግን ብዙም አመርቂ ሆነው አልታዩም።

 

በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉት የአፍሪካ ሀገራት በዚህ ረገድ ውጤታማ ተጠቃሚነት አልታየባቸውም። በክርሲቲያን ላጋርድ የአዲስ አበባ ቆይታ የተንፀባረቀውም ይህ እውነታ ነው። ማኔጂግ ዳይሬክተሯ በዚሁ አዲስ አበባ ቆይታቸው ከሰሃራ በታች ያሉ 17 የአፍሪካ ሀገራት አጠቃላይ ኢኮኖሚ ክፉኛ እያሽቆለቀለ መሆኑን ገልፀው፤ ለዚህም ጉዳይ መፍትሄ ማፈላለጉ ግድ መሆኑን አመልክተዋል።

 

 የተባበሩት መንግስታት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በመሆን በጋራ በሰጡት መግለጫ በአፍሪካ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ አድገትን ለማምጣት በአህጉሪቱ አዲስ የልማት ሞዴል የሚያስፈልግ መሆኑን አመልክተዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በዚህ ደረጃ አፍሪካን በተመለከተ የመለሳለስ ሁኔታን በማሳየት በይፋ መግለጫ ሲሰጥበት ይሄው የአዲስ አበባው መረጃ የመጀመሪያው ነው ማለት ያስችላል። በቀጣይ ድርጅቱና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ በጥናት የተደገፈ የመፍትሄ ሀሳብን ይዘው የሚመጡ መሆኑን አስታውቀዋል። ምን አይነት መፍትሄና መቼ? የሚለው ጉዳይ ግን ጊዜው ሲደርስ የሚመልሰው ይሆናል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
125 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 194 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us