የኢየሩሳሌም ጉዳይ የኢትዮጵያን የገንዘብ እርዳታ አደጋ ላይ ይጥል ይሆን?

Wednesday, 27 December 2017 12:18

 

የትራምፕ አስተዳደር ኢየሩሳሌምን በእስራኤል ዋና ከተማነት እውቅና በመስጠት የአሜሪካንን ኢምባሲ አሁን እስራኤል ከዋና ከተማነት እየተገለገለችበት ካለው ቴላቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም ለማዛወር መወሰኑን ተከትሎ ሰፊ ዓለም አቀፍ ውዝግብ ተቀስቅሶ ሰንባብቷል። ውዝግቡ ከተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤት እስከ ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ዘልቆ የኢትዮጵያንም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳይቀር የሚነካካ ሆኖ ታይቷል። አሜሪካ ይህንን አወዛጋቢ ውሳኔ ይፋ ከማድረጓ ቀደም ብሎ ውሳኔዋ ሰፊ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን እንደሚያጣ አስቀድማ ተረድታለች። ይህንንም እውነታ ተከትሎ  የሷን ቀጥተኛ እርዳታና እገዛ በሚያገኙ ሀገራት ላይ ተፅዕኖን በማሳደር ድጋፍን ለማሰባሰብ ሙከራን ስታደርግ የከረመችበት ሁኔታም ታይቷል። ሆኖም ይህ ተፅዕኖ ምንም አይነት ውጤት ሳያመጣ የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤትም ሆነ በጠቅላላ ጉባኤው በኩል ድጋፍን አጥቷል። ድርጅቱ ባለው አሰራር መሰረት የፀጥታው ምክር ቤትን ውሳኔ አሜሪካ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷ ተጠቅማ ውድቅ ብታደርገውም ጉዳዩ ወደ ጠቅላላ ጉባኤው አምርቶ የትራምፕ አቋም ተቀባይነትን ማጣት ግድ ሆኖበታል።

 

የትራምፕ አስተዳደር ጉዳዩ ለፀጥታው ምክር ቤት ከመቅረቡ ቀደም ብሎ የአሜሪካንን የገንዘብ እገዛ እያገኙ የአሜሪካንን ሀሳብ ውድቅ ለማድረግ ድምፅ የሚሰጡ ሀገራትን ጉዳይ በጥንቃቄ የሚመረምሩ መሆኑን አስታውቀው ነበር።

 

ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት፡- ከእኛ በመቶ ሚሊዮኖች ብሎም በቢሊየን ዶላሮች የገንዘብ እገዛን እያገኙ ሀሳባችንን ውድቅ ለማድረግ ድምፅ የሚሰጡ ሀገራትን ጉዳይ በጥብቅ እንከታተላለን። ግድ የለም! የእኛን ሀሳብ ውድቅ በሚያደርግ መልኩ ድምፅ መስጠት ይችላሉ። እኛም ገንዘባችንን ለመቆጠብ ይረዳናል።

 

የገንዘብ እርዳታ እቀባውን በተመለከተ ፕሬዚዳንቱ ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ የሪፐብሊካን ባለስልጣትም ሳይቀሩ ይህንን ማስጠንቀቂያ አዘል ዛቻን በማጠናከር የሀገሪቱን የእርዳታ ገንዘብ እየተቀበሉ ከአሜሪካ በተቃራኒ ድምፃቸውን በሚሰጡ ሀገራት ላይ ሀገራቸው የእርዳታ እቀባ የምታደርግ መሆኑን ገልፀዋል።

 

ከዚህ ሁሉ ማስጠንቀቂያ በኋላ መንግስታቱ ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ኢየሩሳሌምን በተመለከተ ድምፅ የሚሰጥበት ወሳኙ ቀን ደረሰ። በእለቱም ከ193 የድርጅቱ አባል ሀገራት ውስጥ 128 የሚሆኑት ሀገራት ድምፃቸውን የሰጡት የአሜሪካንን የኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት ሀሳብ ውድቅ በማድረግ ነበር። 9 ሀገራት ከአሜሪካ አንፃር በመቆም ድምፃቸውን የሰጡ መሆኑ ታውቋል። 35 ሀገራት ደግሞ አወዛጋቢውን የውሳኔ ሀሳብ ባለመደገፍና ባለመቃወም በድምፀ ተአቅቦ ማለፍን መርጠዋል። 21 ሀገራት በአንፃሩ በድምፅ መስጫው እለት በቦታው አለመገኘትን መርጠዋል።

 

ለአሜሪካ ድጋፋቸውን በድምፃቸው ከሰጡ ሀገራት መካከል ብቸኛዋ ከሰሀራ በታች ያለች ሀገራት ቶጎ ናት። ኬኒያ በእለቱ በቦታው ባለመገኘት ጉዳዩን በዝምታ ማለፉን መርጣለች። ከሰሀራ በታች ካሉት የአፍሪካ ሀገራት መካከል የአሜሪካንን ከፍተኛ እርዳታና እገዛ በማግኘት ድምፃቸውን በተቃራኒው የሰጡ ሀገራት ተብለው በየመገናኛ ብዙሃኑ ስማቸው ሲጠራ የከረሙ ሀገራት አሉ። ከእነዚህ ሀገራት መካከልም ኢትዮጵያ የግንባር ቀደሙን ስፍራ ይዛለች።

 

ይህን ዘገባ በሰፊው ካሰራጩት የሚዲያ ተቋማት መካከል አንዱ NBC የአሜሪካንን ከፍተኛ የእርዳታና እገዛ ገንዘብ እየተቀበሉ ድምፃቸውን ከአሜሪካ ሀሳብ በተቃራኒ የሰጡ ሀገራትን ዝርዝር ይፋ አድርጓል። ይህ ዝርዝር ሀገራቱ ከአሜሪካ የሚያገኙትን ዓመታዊ የገንዘብ መጠንንም ሳይቀር በዝርዝር አስቀምጧል። በዚህም ዝርዝር መሰረት የአሜሪካን ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ በማግኘት በዚሁ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከአሜሪካ በተቃራኒ ከቆሙ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ 938 ሚሊዮን ዶላርን በማግኘት ከአፍጋኒስታን ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጣለች። ይሄው ዘገባ ድምፅ አሰጣጡ ሊያስከትል የሚችለውን የገንዘብ እቀባ በተመለከተ ሀገራቱ ከሚያገኙት ዓመታዊ እገዛ ጭምር Financial consequences በሚል በሚከተለው መልኩ በዝርዝር አስቀምጧቸዋል።

 

አፍጋኒስታን                    977 ሚሊዮን ዶላር

ኢትዮጵያ                       938 ሚሊዮን ዶላር

ዮርዳኖስ                       813 ሚሊዮን ዶላር

ናይጀሪያ                       681 ሚሊዮን ዶላር

የመን                          573 ሚሊዮን ዶላር

ኢራቅ                         530 ሚሊዮን ዶላር

ፓኪስታን                      485 ሚሊዮን ዶላር

ሶማሊያ                        416 ሚሊዮን ዶላር

ኮንጎ                           393 ሚሊዮን ዶላር

ደቡብ አፍሪካ                   354 ሚሊዮን ዶላር  

 

የትራምፕ አስተዳደር የእርዳታና እገዛው የገንዘብ ቅጣት ከሚጠብቃቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት እንዲያስቀምጣት ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል አንደኛው፤ ሀገሪቱ ከአሜሪካ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍን የምታገኝ መሆኗ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ሀገሪቱ ድምጿን የሰጠችው ከአሜሪካ በተቃራኒ ቆማ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ የአሜሪካን ሀሳብ ውድቅ ያደረገችው ሁለት ጊዜ ነው። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤት ተለዋጭ አባል በመሆኗ በዚያ በነበራት ተሳትፎ የአሜሪካንን ሀሳብ ውድቅ አድርጋለች። በሁለተኛ ደረጃ ከአሜሪካ በተቃራኒ የቆመችው ጉዳዩ ወደ ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ካመራ በኋላ ነበር።

 

አሜሪካዊያኑ እነሱን በመደገፍ ድምፅ የሰጠውን ሀገር ብቻ ሳይሆን በእለቱ በቦታው ባለመገኘት አቋሙን ማሳወቅን ያልፈለገውን ሀገር ሳይቀር ምስጋናቸውን በመቸር የወዳጅነት ግብዣንም አድርገዋል። በዚህ ረገድ በአሜሪካ የኬኒያ አምባሳደር የዚሁ ግብዣ አካል ሆነው ለሀገሪቱ ምስጋና የተላከ መሆኑን ዴይሊ ኔሽን ከሰሞኑ ባሰራጨው ዘገባ አመልክቷል። ፕሮግራሙ የተካሄደው በዋሽንግተን እስራኤል ኢምባሲ ውስጥ ሲሆን በእለቱም በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሀሊ ምስጋናቸውን ለሀገራቱ የገለፁ መሆኑን ይሄው ዘገባ ያመለክታል።

 

ይህ የምስጋና መልዕክት ከምስጋናነት ባለፈ ለሌሎች ሀገራት የተገላቢጦሽ መልዕክትን ያዘለ ነው ተብሏል። የትራምፕ አስተዳደር ከዚህ ቀደም “አሜሪካ ትቅደም” በሚለው መርህ የሀገሪቱን ወጪ ለመቆጠብ ሲነሳ የእርዳታና እገዛ ቅነሳ ከሚደረግባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን አንዷ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

 

ይህ አወዛጋቢው የኢየሩሳሌም ጉዳይ የሚያሻክረው የኢትዮ- አሜሪካንን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የኢትዮ እስራኤልም ግንኙነት ጭምር ነው። እስራኤል ካለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማሻሻል ሰፊ ስራን መስራት የጀመረችበት ሁኔታ ነበር። በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ በር ተደርጋ በእስራኤል እስከመወሰድ የደረሰችበት ሁኔታም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ ባሳለፍነው ክረምት አዲስ አበባ በመገኘት ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው። በዚህም በተለይ በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዲፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን የጎበኙት 60 የእስራኤል ኩባንያዎችን በማስከተል ነበር። በዚህም ወቅት የኢትዮ እስራኤል የቢዝነስ ፎረም ተካሂዷል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያው ጉብኝት የኬኒያ፣ ሩዋንዳና ኡጋንዳ ጉብኝት አካል ነበር።

 

ኢትዮ እስራኤል ግንኙነት ከድምፅ አሰጣጡ ሂደት በኋላ በምን መልኩ ሊቀጥል እንደሚችል እስከአሁን ግልፅ የሆነ ነገር ባይኖርም ከሁኔታው አንፃር ሲታይ ግን ቢያንስ ጊዜያዊ መቀዛቀዝን አይፈጥርም ብሎ መናገር አይቻልም። የአሜሪካንን የገንዘብ ድጋፍን ማቋረጥንም ሆነ ከኢትዮ እስራኤል ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ ሂደቱንና ጊዜ እያጠራው የሚመጣ ይሆናል። ለጊዜው ግን በአንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ይቻላል። የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካንን ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ እየተቀበሉ አሜሪካንን በመቃወም ድምፃቸውን የሰጡ ሀገራትን ለመቅጣት ጥብቅ ዛቻን አሰምቷል። ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ በአሜሪካዊያኑ ሚዲያዎች በግንባር ቀደምትነት ስሟ ተጠቅሷል። ይህ ዛቻ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ግን ኢትዮጵያ የምታጣው እገዛ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። ኬኒያ በድምፅ መስጫው እለት በቦታው ተወካዩዋን ባለመላክ ባዶ መቀመጫ ማድረጓ በማንም ወገንተኝነት ውስጥ እንዳትፈረጅ አድርጓታል። ኢትዮጵያ አሜሪካንን በመደገፍ ድምጿን ብትሰጥ በአረቡ አለምና በአንዳንድ ሙስሊም ሀገራት የሚኖረው አሉታዊ እይታም ሌላኛው የሳንቲሙ ገፅታ ነው። አንዳንዶቹ ግን ኢትዮጵያ የኬንያን አቋም ብትይዝ ወይንም ድምፅ ተአቅቦ ብታደርግ የተሻለ ማምለጫ ዘዴ ይሆናት ነበር በማለት ሀሳባቸውን ሲገልፁ ተሰምቷል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
157 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 193 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us