ለቢዝነስ የፈጠራ ሥራ የሚያነሳሳው መድረክ

Wednesday, 17 January 2018 13:14

 

ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በስፋት በፈጠራ የቢዝነስ ሥራ መሰማራት የሚያስችላቸውን ፍላጎት ለማነሳሳትና እርስ በእርሳቸውም ትስስርን እንዲፈጥሩ ለማድረግ የሚያስችል አንድ መድረክ ባለፈው ቅዳሜ ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም ተካሂዷል።  መድረኩም ለሦስተኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑ ታውቋል።

 

 በዚህ በሞርኒግ ስታር ሆቴል በተካሄደው ዝግጅት ላይ ከ 2 መቶ ያላነሱ ወጣቶች ተገኝተዋል። በዕለቱ ወጣቶቹን የቢዝነስ ፈጠራ ለማነሳሳት የሚያስችል ልምድ የማካፈል ሥራም ተከናውኗል። ከልምድ ማካፈሉ በተጨማሪም ከህግ አንፃር ያሉ ሁኔታዎችም አጠር ባለ ሁኔታ ተቃኝተዋል።

የዚህ መድረክ አዘጋጆች ኤክስ ሃብ (xHub) እና ሴንተር ፎር ሊደርሽፕ የተባሉ ሁለት ኩባንያዎች ናቸው። ኤክስ ሃብ  ትኩረቱን ወጣቶች ላይ በማድረግ፣በፈጠራ፣አዲስ ሀሳብን በማፍለቅና የፈለቀውንም ሀሳብ በተግባር እውን እንዲሆን በማድረጉ ረገድ የተለያዩ ሥራዎችን የሚሰራ መሆኑን የኩባንያው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪው አቶ መላኩ ተኮላ ገልፀውልናል። ወጣቶቹ በዚህ መድረክ ላይ ለመገኘት የበቁት በማህበራዊ ሚዲያ በተፈጠረው ትስስርና የሀሳብ ልውውጥ መሆኑን ከተደረገልን ገለፃ መረዳት ችለናል።

 

 በዕለቱም የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል መስራችና ባለቤት አቶ ዳዊት ኃይሉ ለወጣቶቹ የቢዝነስ ስኬት ተሞክሯቸውን ሰፋ ባለ ሁኔታ አካፍለዋል። የእሳቸውንም ልምድ ማካፈል ተከትሎ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ማብራሪዎችንም ሰጥተውበታል።

 

በዕለቱ የቢዝነስ ሥራ አጀማመር ሂደታቸውን ለታዳሚው በሰፊው ያካፈሉት   አቶ ዳዊት ኃይሉ ወደ ቢዝነሱ ዓለም ሲገቡ የነበራቸውን የአነሳስ ሂደት፣ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶችና ለስኬት ያበቋቸውን ልምዶች በማብራሪያቸው ለታዳሚው አጋርተዋል። አቶ ዳዊት ትምህርታቸውን ከቀድሞው ኮሜርስ ኮሌጅ በአካውንቲግ የትምህርት ዘርፍ ካጠናቀቁ በኋላ ተቀጥረው ደመወዝተኛ ከመሆን ይልቅ የራሳቸውን ሥራ ለመስራት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር፤ በሂደትም በድንገት ከአሁኗ የትዳር አጋራቸው ጋ ተገናኝተው የፍቅር ግንኙነት መጀመራቸውን በዕለቱ ለነበሩት ታዳሚዎች በትረካ መልክ አካፍለዋል።

 

ከዚያም ከፍቅረኛቸው ጋር ትዳር ለመመስረት በነበራቸው ሂደት ለሰርግ የሚሆን ገንዘብ መቆጠብ እንዳለባቸው በጥንዶቹ መካከል መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ እሳቸው በተባራሪ ከሚያገኙት ገንዘብ በወር ስድስት መቶ ብር እንዲቆጥቡ ፤በሌላ መልኩ ደግሞ እጮኛቸው ደግሞ በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ከሚያገኙት ስምንት መቶ ብር ወርሃዊ ደመወዝ ውስጥ ሁለት መቶ ብሩን እንዲቆጥቡ መግባባት ላይ ተደረሰ።

 

ገንዘቡንም ለማጠራቀም የጋራ የባንክ  ሂሳብ ከተከፈተ በኋላ የመቆጠቡ ሥራ ተጀመረ። በመጨረሻ የገንዘቡ መጠን 11 ሺህ ብር ደረሰ። በዚህም ገንዘብ ሰርግ እንዲደገስ ተወሰነ። ሆኖም ከሰርጉ ድግስ ባሻገር እሳቸውም ቋሚ ገቢ ሊኖራቸው የሚገባ መሆኑ ከእጮኛቸው ጋ መግባባት ላይ ተደረሰ። የሰርጉ ድግስ በሂደት ባለበት ሁኔታም ወደ ቢዝነስ ስራ የሚገባበት እንቅስቃሴ ተጀመረ። ከዚያም ያዩትን ክፍት ቦታ ባለቤቶቹን በማናገር በአሮጌው ፖስታ ቤት አካባቢ አንድ የባህል ዕቃ መሸጫ ሱቅ ከፈቱ።

 

ሆኖም ከሱቁ መከፈት በኋላ የነበረው ፈተና ሰፊውን ሱቅ በተገቢው እቃ በመሙላት የሽያጭ መጠንን ማስፋት አለመቻል፤ ብሎም ለደንበኞች እይታ ሳቢ ማድረግ አለመቻል ነበር። ለዚህ ደግሞ ከሰርግ ተርፎ ለኢንቨስትመንቱ ከዋለችው አነስተኛ ገንዘብ በተጨማሪ ሌላ ገንዘብ መኖር ነበረበት። ይህንንም ክፍተት ለመሙላት ሁለት የገቢ ምንጮች ታሳቢ ተደረጉ። አንደኛው እቅድ እቁብ በመሰብሰብ የመጀመሪያውን የዕቁቡ ገንዘብ መውሰድ ሲሆን ሁለተኛው እቅድ ደግሞ ከዘመድና ከወዳጅ ብድር ማፈላለግ ነበር። ሁለቱም እቅዶች ተሳኩ። በተገኘው ገንዘብም ተጨማሪ እቃዎች ወደ ሱቁ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ የገበያው ሁኔታ እየደራ ሄደ።

 

የሽያጩን መድራትም ተከትሎ በዓመቱ ሁለተኛው ቅርንጫፍ ተከፈተ። ከዚያም ተጨማሪ ተመሳሳይ ሱቆችን ከመክፈት ባሻገር የመጀመሪያው ባለድረገፅ የባህል ዕቃዎችና አልባሳት መሸጫ እና የኦንላይን ግብይትንም የሚያከናውን ድርጅት መሆኑን አቶ ዳዊት በትረካቸው ገልፀዋል። ከዚህም ባለፈ ድርጅቱ ለሱቁ የሚያገለግሉትን ሸቀጦች ወደ ማምረት ብሎም ወደ ኤክስፖርቱ ሥራም ተሰማራ።

 

ቢዝነሱ እየሰፋና እየደራ ባለበት ሁኔታ ግን በአንድ አጋጣሚ እስራኤል ሀገር ይኖሩ ከነበረ አንድ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው ስለስራቸው ሀሳብ መለዋወጥ  ጀመሩ። በዚህም መሃል ከእስራኤል የመጡት ጓደኛቸው የሲቲ እስካን ባለሙያ መሆናቸውን ይንግሯቸዋል። በጊዜው ሲቲ ስካን የህክምና ማሽን በኢትዮጵያ የሚታወቅ ስላልነበር አቶ ዳዊት ስለማሽኑ እየደጋገሙ ይጠይቃሉ።

 

ጓደኛቸውም የተጠየቁትን ለማስረዳት ሙከራ ቢያደርጉም አቶ ዳዊት ግን ማሽኑን የተረዱበት መንገድ ሌላ ነበር። አቶ ዳዊት በጊዜው ሲቲ ስካን ሲባል በሄሊኮፕተር አማካኝነት ከሰማይ ላይ የከተማን ፕላን የሚያነሳ ማሽን አድርገው ነበር የተረዱት። ሀሳቡን በዚህ ቢረዱትም ግንዛቤያቸውን የበለጠ ለማጠናከር በጎግል የመረጃ ቋት አማካኝነት ተጨማሪ መረጃዎች ማፈላለጉን ተያያዙት።

 

 ከጎግል ያገኙት መረጃ በርካታ ቢሆንም ከእነዚህ መረጃዎች ውስጥ ሲቲ ስካን የህክምና መሳሪያ መሆኑን የሚገልፀው መረጃ ላይ አይናቸው አረፈ። በዚሁ ዙሪያም የተለያዩ መረጃዎችን በማፈላለግ ካነበቡ በኋላ ነጋ አልነጋ ብለው በበነጋታው  ከጓደኛቸው ጋር ተገናኙ። ሲቲ ስካን ሲባል የተረዱበት መንገድ ሌላ መሆኑን በመግለፅ፤ በመጨረሻም ዘግይተውም ቢሆን በኢንተርኔት መረጃ በመደገፍ የህክምና መሳሪያ መሆኑን የተገነዘቡ መሆኑን ለጓደኛቸው ይነግሯቸዋል።  በሁኔታው ከጓደኛቸው ጋር ከተሳሳቁ በኋላ ጉዳዩ የምር ውይይት ይካሄድበታል።

 

 በመጨረሻ ይህ ማሽን በሀገር ውስጥ የህክምና ማዕከላት መኖር አለመኖሩ ጥናት ይደረግበት ጀመር። የግልና የመንግስት ሆስፒታሎች አንድ በአንድ እንዲታሰሱ ተደረገ። ሆኖም የተባለው ማሽን አንድም ቦታ ሊገኝ አልቻለም። ይህ ሁኔታ የአቶ ዳዊትን ማሽኑን ከውጭ የማስገባት ፍላጎት አናረው። ሆኖም እሳቸው ከህክምና ጋር በተያያዘ ሙያው የሌላቸው የመሆኑ ጉዳይ ደግሞ ሌላ ስጋትን  ፈጠረ። ያም ሆኖ ሀሳቡ ባለበት አልቆመም። በመሆኑም የመጀመሪያው የዲያግኖስቲክ ማዕከል ተቋቋመ። በአንድ የሲቲ ስካን ማሽን  ውዳሴ የዲያግኖስቲክ ማዕከል ወደ ሥራ ገባ። በዓመቱም አንድ አልትራ ሳውንድና ኤክስሬይ ማሽን በማካተት ሥራው በስፋት ቀጠለ። ቢዝነሱም እየሰፋ ሄደ፣ አምቡላንሶች ተጨመሩ። እንደዚሁም ኤም አር አይ የተባለ የህክምና ማሽን ግዢ ተከናውኖ ሥራው በስፋት ቀጠለ።

 

 ከአቶ ዳዊት ገለፃ መረዳት እንደቻልነው ከባለቤታቸው ወይዘሮ ውዳሴ ጋ በጋራ በመሆን ዛሬ ቢዝነሳቸውን ከህክምና እስከ ትምህርት ቤት በማስፋት በርካታ ሥራዎችን በመስራት ላይ ናቸው። በቀጣይም የቢዝነሳቸውን አይነትና ስብጥርን የማስፋት እቅድ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ መሆናቸውን በመግለፅ አንድ ሰው ቢዝነስ ከማቋቋም ጀምሮ የቢዝነሱን ቀጣይነት እስከሚያረጋግጥ ድረስ መከተል ያለበትን መርህ በሰፊው አካፍለዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
118 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 826 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us