ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝን ለመላክ የሚያስችላትን የቧንቧ ዝርጋታ ልታካሂድ ነው

Wednesday, 24 January 2018 13:53

 

በኢትዮጵያ በርከት ላሉ ዓመታት ስታካሂድ የነበረው የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ሂደት ተጠናቆ ጋዙን ወደ ውጪ ለመላክ የሚያስችለውን ቧንቧ ለመዘርጋት ሥምምነት ተፈርሟል። ስምምነቱ በማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴርና በቻይናው ፖሊ ጂ ሲ ኤል ኩባንያ (Poly-GCL) መካከል ከሰሞኑ ተፈርሟል። በዚህ ስምምነት መሰረት የቻይናው ፖሊ ጂ ሲ ኤል ኩባንያ (Poly-GCL) ከኦጋዴን አካባቢ እስከ ጂቡቲ የሚደርስ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧን መዘርጋት ይጠበቅበታል። እንደ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ መረጃ ከሆነ የጋዝ ፍለጋውን ሥራ ለማከናወን 360 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን አጠቃላይ የሚጠይቀው የኢንቨስትመንት  መጠን ግን 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ነው።

 

ኩባንያው በኦጋዴን ካሉብ ሂላላና በገናሌ አካባቢ የፔትሮሊየም ፍለጋን ለማከናወን በ2013 ከኢትዮጵያ ከመንግስት ጋር ውል አስሮ የተፈራረመ ሲሆን በዚህም በአካባቢው የምርመራና የተፈጥሮ ሀብቱን መጠን ግመታ (Reserve Estimation) ሲሰራ የቆየ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። እንደ ማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ማብራሪያ ከሆነ የተረጋገጠ የተፈጥሮ ጋዙን ለማግኘት 11 ጉድጓዶች እንዲቆፈሩ የተደረገ ሲሆን በዚህም ሂደት ከአምስት እስከ ስድስት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችትን ማገኘት የተቻለ መሆኑ ታውቋል።

 

የጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ የመዘርጋቱን ሂደት ለመጀመር ረዘም ያሉ ጊዜያት የወሰደ ሲሆን ለዚህም አንዱ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው መስመሩ ከኢትዮጵያ ግዛት ባሻገር የጂቡቲ ግዘትንም ጭምር አካቶ ወደብ ድረስ የሚደርስ በመሆኑ ነው። ይህንንም ረዘም ያለና ውስብስብነት የታየበት ድርድር ብሎም የጥናት ጊዜ የጠየቀ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የቧንቧ ዝርጋታው ከኢትዮጵያ ድንበር ባሻገር በጂቡቲ ግዛትም 84 ኪሎ ሜትር ርዝመትን የሚያካትት መሆኑ ታውቋል። ይህ ፕሮጀክት በተያዘው የፈረንጆች ዓመት አጋማሽ ተጀምሮ እ.ኤ.አ በ2020 አገልግሎት መስጠጥ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። በኦጋዴን አካባቢ በርካታ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋዎች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን አሁን ከተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ በተጨማሪ ሌሎች መሰል ምርቶችም የሚገኙ ከሆነ አሁን የሚገነባው ጋዝ ማስተላፊያ ቱቦ ለሌሎችም የሚያገለግልበት ሁኔታ ይኖራል።

 

የጋዝ ምርቱ ወደ ቻይና የሚላክ ሲሆን ኢትዮጵያም በዓመት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የምታገኝ መሆኑ ታውቋል። እንደ አቶ ሞቱማ ገለፃ ሀገሪቱ በቀጣይ ዓመታት ውስጥ ከምርቱ የምታገኘው የገቢ መጠን ወደ 7 ቢሊዮን ይድርሳል። በኢትዮጵያ ሶማሌ፤ ኦጋዴን አካባቢ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ሲካሄድ ከአርባ ዓመታት በላይ ጊዜያት ተቆጥረዋል። በአካባቢው በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት በ1960ዎቹ የመጀመሪያውን የፍለጋ ሥራ ያከናወነው የአሜሪካው ቴኔኮ ኩባንያ ነበር። ሆኖም ኩባንያው በማዕድኑ ምርመራና ፍለጋ ላይ እያለ የመንግስት ለውጥ በመካሄዱ የደርግ መንግስት አሜሪካዊውን ኩባንያ ከሀገር እንዲወጣ በማድረጉ ፍለጋው እንዲቋረጥ የተደረገ መሆኑን የቀደሙ መዛግብት ያስረዳሉ።

 

የቴኔኮን መባረር ተከትሎ በቀጣይ ሥራውን የተረከበው የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ነዳጅ ፈላጊ ኩባንያ ነበር። ኩባንያው በዚሁ የነዳጅና ጋዝ ፍለጋ ሥራው ብዙ ቢገፋበትም የመጨረሻ ውጤት ላይ ደርሶ ወደ ምርት የገባበት ሁኔታ ግን አልነበረም። በዚሀ መሃልም የእርስ በእርስ ጦርነቱ እየበረታ በመሄዱ ሙሉ የመንግስት ትኩረት ጦርነቱ ላይ በማረፉ የአካባቢው የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ሥራም መቆም ግድ ብሎታል። የኢህአዴግ መንግስት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ቢሆን በአካባቢው ብዙም መሰል እንቅስቃሴዎች የታዩበት ሁኔታም አልነበረም።

 

 የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታም አስተማማኝ ስላልነበር ሥራውን ማከናወን አስቸጋሪ ነበር። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂ ኃይሎች በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ከማስጠንቀቅና ከማስፈራራት ባለፈ በ2000 ዓ.ም  በነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ላይ የነበሩ 65 ኢትዮጵያዊያንና 9 ቻይናዊያንን በመግደል ንብረትም ጭምር ያወደሙበት አጋጣሚም እስከመፈጠር ደርሷል። ይህ አይነቱ የታጣቂዎች እርምጃ በአካባቢው የነበረው ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀዛቀዝ አድርጎት የቆየ ሲሆን  በሂደት ግን የተለያዩ በዘርፉ  የካበተ ልምድና ከፍተኛ የካፒታል አቅም ያላቸው የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ፈላጊ ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው የምርመራ ሥራዎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ይህ የተፈጥሮ ጋዝ ሙሉ በሙሉ ወደ ኤክስፖርቱ ገበያ ሲገባ የኢትዮጵያን በውስን የግብርና ምርቶች ላይ የተንጠለጠለ የኤክስፖርት ገቢ ስብጥር ከፍ የሚያደርገው ይሆናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
132 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 806 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us