ያለፉት ጊዜያት የጋራ መኖሪያ ቤት ችግሮች አሁንም ተመልሰው እየመጡ ነው

Wednesday, 07 February 2018 12:47

 

ከሰሞኑ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባን አቶ አባተ ስጦታውን ያካተተ የከፍተኛ ኃፊዎች ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ በግንባታ ላይ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመዘዋወር ተመልክቷል። በዚህ የመስክ ጉብኝት ወቅትም እንደተመለከተው በያዝነው በጀት ዓመት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም 32ሺህ የ20/80 እና የ40/60 ቤቶች መጠናቀቅ ያለባቸው መሆኑ ተመልክቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀደም ባሉት ጊዜያት በዘርፉ የሚታዩት ተመሳሳይ ችግሮች አሁንም መልሰው እየታዩ መሆኑን መረዳት ችለናል። ባለፉት ጊዜያት ከፕሮጀክቶች መጓተት፣ ቤቶቹን በዕጣ ለማስተላለፍ ባሉት ሂደቶች ይታዩ የነበሩ ችግሮችና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች በቀጣይም መልሰው የሚደገሙ መሆኑን የሚያሳዩ ጠቋሚ ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህም ጠቋሚ ማሳያዎች ውስጥ የሚከተሉትን ነቅሰን በማውጣት ተመልክተናቸዋል።

 

ለውጫዊ ገፅታ ዕይታ የሚደረግ ሩጫ

በቤቶቹ አሰራር ቅደም ተከተል ያለው ሂደት ከሀቀኝነት ይልቅ ዕይታ ላይ ትኩረት ያደረገ ሆኖ ይታያል። አንድ ብሎክ ውጫዊ ቀለም የሚቀባው የህንፃው ቁመናዊ ግንባታ ተጠናቆ ጣሪያው እንደተመታ ነው። ሆኖም ይህ ሥራ የሚሰራው በብሎኮቹ ውስጥ መሰራት የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች ሳይሰሩ ነው። ህንፃዎቹ ቀለም ተቀብተው ለሚያይ ማንም አላፊ አግዳሚ የቤቶቹ ግንባታ የተጠናቀቀ ይመስለዋል።  

 

ሆኖም ህንፃዎቹ ውስጥ ተገብተው ሲታዩ ግን በሚገባ ያልተለሰኑ፣የኤሌክትሪክና የቧንቧ መስመሮቻቸው ያልተጠናቁ፣ በርና መስኮቶች ያልተገጠሙላቸው፣ የመፀዳጃ ቤት ሥራዎቻቸው ያልተሰሩ፤ አለፍ ሲልም የውስጥ ክፍልፋይ ግንባታቸው እንኳን ያልተጠናቀቁ ሆኖ ይታያል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ለቤቶቹ ውጫዊ ቀለም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ለታይታ የሚደረገው ሩጫ ከምን የመነጨ ነው የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው። ከሰሞኑ በተካሄደው የቤቶች ግንባታ የመስክ ጉብኝት በዚሁ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን የሚከተለውን መልዕክት ነበር ያስተላለፉት፡-

 

ቀለምተቀብተውባየናቸውቤቶችደስብሎናል።አንዳንድጊዜግንባለፈውስንጎበኝቀለምተቀብተው፤ነገርግንውስጣቸውምንምለውጥሳናይአሁንምስንጎበኝቀለምተቀብተውያገኘናቸውቤቶችአሉ።አሁንቀለምየተቀቡትንቤቶችገብተንብናያቸውየሚቀርነገርሊኖርይችላል።ስለዚህውስጣቸውንእናሟላ።የምንሰራውየታይታሥራአይደለም።አላፊአግዳሚውእንዲያያቸውአይደለም።ቤቶቹደርሰውለተጠቃሚውእንዲተላለፉናአገልግሎትእንዲሰጡነውየሚፈለገው።

በነገራችን ላይ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት በግንባታ ላይ የነበሩት የሰንጋ ተራና የክራውን አካባቢ የአርባ ስልሳ ቤቶች ግንባታ የውጫዊ ቀለም ሥራ ያለቀው ቀደም ብሎ ነበር። ይህ ሁኔታ በርካቶችም ቤቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕጣ ይወጣባቸዋል የሚል ጉጉት እንዲያድርባቸው አድርጎም ነበር። በስተመጨረሻ ግን ከቀለሙ በስተጀርባ ያልተጠናቁትን ቀሪ የግንባታ ስራዎች ለማጠናቀቅ ረዥም ጊዜን ውስዷል።

 

ወጥነት የማይታይበት የግንባታ ሂደት

ቤቶቹ በኮንትራክተሮችና በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲገነቡ ይደረጋል። በአሰሪው አካል በኩል ያለው በጀትን በጊዜ አለመልቀቅ የግንባታው ሂደት ሙሉ በሙሉ እስከመቋረጥ ደርሶ እንደገና የሚጀመርበት ሁኔታ አለ። በዚህ ዙሪያ አሁን በግንባታ ላይ ያሉት የቦሌ አራብሳና የኮየ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤት የግንባታ ሂደት በቂ ማሳያዎች ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው።

የቤቶቹ ግንባታ ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠርም ከጊዜ አንፃር የግንባታቸው ሂደት ሲታይ ግን ወጥነት የሚታይበት ሆኖ አይታይም። አንድ ሰሞን ሳይቶቹ ከፍተኛ የግንባታ ጥድፊያ ይታይባቸዋል። ጥቂት ቆየት ብሎ ደግሞ አካባቢዎቹ የተወረረ ከተማ እስኪመስሉ ድረስ ጭር ብለው ይታያሉ። በዚህ ወቅት ከሳይት ጥበቃዎች ውጪ በአካባቢው ዝር የሚል ሰው አይታይም። ይህ ሁኔታ ለወራት ከዘለቀ በኋላ ሌላ ዙር ግንባታ እንደገና ይጀመራል። በዚህ መልኩ ግንባታው በመሃል እየተቋረጠ እንደገና እየተጀመረ የሚካሄድባቸው ሁኔታዎች የፕሮጀክቱን ጊዜ የበለጠ እያራዘመው ብሎም የሚጠይቀውንም ወጪ እያናረው የሚሄድበት ሁኔታ ይታያል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የግንባታ ፕሮግራሞቹ እየተቋረጡ እንደገና እንደ አዲስ ለሚጀመሩበት ሁኔታ ምክንያት ተደርጎ የሚነሳው በመንግስት በኩል ለግንባታ የሚያስፈልገው በጀት በጊዜው መልቀቅ አለመቻል ነው። መንግስት ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ተፅዕኖ እያደረገበት መሆኑን ሲገልፅ ቆይቷል። ሆኖም ዶክተር አምባቸው በዚህ በጀት ዓመት መንግስት ለቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት 20 ቢሊዮን ብር በጀት መደበ መሆኑን ገልፀው የግንባታዎቹ መዘግየት ችግር ከኮንትራክተሮቹ አቅም ማነስ ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክተዋል።

 

ዕዳ ማስተላለፍ ወይንስ የቤት ዕድለኛ ማድረግ?

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ የሚናወነው አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ ቢሆንም ወደ ማጠናቀቂያው አካባቢ ሲታይ ግን ከፍተኛ ጥድፊያ ይታያል። በቅርቡ በግንባታ ላይ ያሉትን የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ከሆነ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት የቤቶቹ ግንባታ ጥድፊያ በተሞላበት አኳኃን በመካሄድ ላይ ነው። በቦሌ አራብሳ ያሉ በርካታ ቤቶችና በየካ አባዶ ግንባታቸው በጊዜው ተጠናቆ በመጨረሻው ዙር እጣ ያልወጣባቸው ህንፃዎች የግንባታ ሂደት የዚህ ማሳያዎች ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው። 

 

ወደ መጨረሻዎቹ አካባቢ ህንፃዎቹን የሚገነቡት ተቋራጮች ስራቸውን በአስቸኳይ አጠናቀው እንዲያስረክቡ ጫና ይደረግባቸዋል። በዚህ ወቅት የሚታየው ጥድፊያ ቀላል አይደለም። ከግንባታ ጥራት ጋር ተያይዞ ብዙ ግድፈቶች የሚታዩትም በዚሁ ሰሞን ነው። ያም ሆኖ ቤቶቹን በተባለው ጊዜ የማያጠናቀቁ ኮንትራክተሮች በርካቶች ናቸው።

 

በቤቶቹ ላይ እጣ የሚያወጣው አካል ቤቶቹን ለመረከብ ዝግጅት ሲያደርግ ለእጣ ዝግጁ መሆናቸውን የመለየቱ ሥራ ላይ የሚሰራቸው ሥራዎች ግን አግባብነት የጎደላቸው ናቸው። በርካታ ህንፃዎች በተገቢው መንገድ ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ “ለእጣ ዝግጁ ናቸው” ተብሎ እንዲያልፉ ይደረጋል። እጣም እንዲወጣባቸው ይደረጋል። እጣ የወጣለት ግለሰብም ቤቱን ለማየት ሲሄድ ግን ቤቱ በርና መስኮት የሌለው፣ የመፀዳጃ ቤት ሥራው ያልተጠናቀቀና ሌሎች በርካታ ሥራዎች የሚጎድሉት ሆኖ ይመለከታል።

 

ዕጣው የወጣለት ግለሰብ ውል ከፈረመበት እለት ጀምሮ የእዳ ኃላፊነቱን መወጣት የሚያስችለውን ግዴታ ውስጥ ይገባል። ውል ከፈረመበት ዕለት ጀምሮ በሚቆጠረው አንድ ዓመት ውስጥ የእፎይታ ጊዜ እንዳለው ይነገረዋል። ሆኖም ይህ የእፎይታ ጊዜው ግለሰቡ ቀሪውን የቤቱን 80 በመቶ እዳ ለማጠናቀቅ ለአንድ ዓመት ያህል ክፍያ እንዳይከፍል እድልን የሚሰጥ እንጂ ከቤቱ ዕዳ ወለድ ግን ነፃ የሚያደርግ አይደለም። ሆኖም ቀላል ቁጥር የሌላቸው ቤቶች እጣ የሚወጣባቸው በተገቢው መንገድ ሳይጠናቀቁ በመሆኑ ቀሪ ግንባታቸው የሚከናወነው በዕጣ ከተላለፉ በኋላ ነው።

 

የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ግለሰቦቹን “እጣ ወጣላችሁ” ብሎ ዕድለኞቹ ከባንክ ጋር እንዲዋዋሉ ካደረገ በኋላ በስተመጨረሻ ወደ ተግባር ሲገባ “ቤቶቹ ግንባታቸው አልተጠናቀቀም” በማለት እድለኞች የቤቶቹን ቁልፍ የሚያገኙበትን ጊዜ ያራዝማል። በዚህ መልኩ ለባዕድለኛው የተሰጠው የእፎይታ ጊዜ ይገባደዳል። ቁልፍ አለመረከብ ማለት በሌላ አቅጣጫ የውሃና የመብራት ውል አለመዋዋል ማለት ነው። በእነዚህ የባለዕድለኛው የእፎይታ ጊዜያት ውስጥ ግን ኮንትራክተሮች ያጠናቀቁትን ሥራዎች እንዲያጠናቀቁ ይደረጋል።

 

እነዚህ ሁኔታዎች ሲታዩ የቤት ዕጣ የወጣለት ሰው፤ እዳ ነው የተላለፈለት? ወይንስ እጣ ነው የወጣለት? የሚል ጥያቄን ያስነሳል። ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር በቀበሌ ቤት የሚኖሩ ሰዎች ቁልፍ ባልተረከቡበት ወይንም ቢረከቡ እንኳን በቅጡ ቤታቸውን ማደስ ባለችላሉበት ሁኔታ “የኮንደሚኒየም ዕጣ ወጥቶላችል” በሚል ቤቶቹን በአፋጣኝ እንዲለቁ የሚደረጉበት ሁኔታም መኖሩ ነው። ከሰሞኑም የዶክተር አምባቸው፣ የአቶ አባተ ስጦታውና የሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በግንባታ ላይ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉብኝት ጋር በተያያዘ ቤቶቹ ይጠናቀቃሉ ተብሎ የተቀመቀጠው የጊዜ ሰሌዳና የቤቶቹ የግንባታ ደረጃ ሲታይ ባለፉት ጊዜያት ሲሰሩ የነበሩት ስህተቶች መልሰው ላለመደገማቸው ምንም ዋስትና የለም። የቤቶቹ የግንባታ ሁኔታ ወጥነት አይታይበትም።

 

የተወሰኑ ኮንትራክተሮች የስራ ሂደት ሲታይ በተቀመጠላቸው የዓምስት ወራት እድሜ በአግባቡ አጠናቀው የሚያስረክቡ ይመስላል። በሌላ መልኩ በርካታ ቤቶች የግንባታ ሂደት ሲታይ ግን በተሰጡት ጥቂት ቀሪ ወራት መጠናቀቅ ይቅርና በመጪው በጀት ዓመት ሳይቀር ተጨማሪ ጊዜያትን የሚወስዱ መሆናቸው ከወዲሁ ያስታውቃል። ሆኖም ቀደም ሲል በተለመደው አካሄድ እነዚህ ግንባታቸው የተጓተቱ ቤቶች በጥድፊያ ግንባታ ርክክባቸው ተፈፅሞ ዕጣ ይውጣባቸው የሚባል ከሆነ የመጨረሻ ተጎጂው የሚሆነው ዕጣ ወጣለት የተባለው ዜጋ ነው።

 

ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር በተያያዘ ሌላው የሚነሳው አነጋጋሪ ጉዳይ የቤቶቹ ዋጋ ሁኔታ ነው። የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች እየተገነቡ ያሉት በሁለት መልኩ ነው። አንደኛው በ20/80 የቤቶች ፕሮግራም ያለው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ መካከለኛ ገቢ አላቸው ተብሎ ለሚታሰቡት ነዋሪዎች በአማራጭነት የቀረበው የ40/60 የቤቶች ፕሮግራም ነው። አሁን ባለው የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ ንረት አንፃር ሲታይ፤ በቀጣይ ዕጣ የሚወጣባቸው ቤቶች አዲስ የዋጋ ለውጥ ይታይባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

በተለይ ከወራት በፊት የተካሄደው የብር ምንዛሪ ለውጥ የዋጋ ንረት ካስከተለባቸው ዘርፎች ውስጥ ግንባር ቀደም ሆኖ የታየው የኮንስትራክሽን ግብዓቶች የገበያ ሁኔታ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ሲታዩ በቀጣይ ዕጣ ይወጣባቸዋል የተባሉት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ የሚደረግባቸው ከሆነ በርካታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችን አቅም ክፉኛ የሚፈታተን ይሆናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
554 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 832 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us