የፕላስቲክ ጠርሙሶች፤ ከአካባቢ ብክለት ወደ ቤት ግንባታ ግብዓትነት

Wednesday, 14 February 2018 11:27- ሥራው በኢትዮጵያ ተጀምሯል

 

በሀገራችን የቤቶች ግንባታ ሂደት ጊዜንም ሆነ ገንዘብን በመቆጠብ ብሎም፤ አሁን ካለው የድንጋይ፣ የብረት፣ የሲሚንቶና የመሳሰሉት ግብዓቶች ባሻገር እንደሌሎች ሀገራት ብዙም ሌሎች አማራጭ ግብዓቶችና የግንባታ ቴክኖሎጂዎች ያልተሞከሩበት ነው። በርካታ ሀገራት ከመደበኛውና የተለምዶ የቤት ግንባታ ባሻገር የተለያዩ የቤት ግንባታ ዘዴዎችን ሲጠቀሙ ይታያል። እንደምሳሌ ያህልም የቤቶቹን አካላት ሌላ ቦታ በማምረትና ወደ ግንባታ ቦታው ወስዶ ተገጣጣሚ ቤቶችን መገንባት አንዱ አማራጭ ነው። ይህ አይነቱ አሰራር በግንባታ ቦታ የሚባክነውን ግብዓት ለመከላከል ብሎም ጊዜን ለመቆጠብ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል።
ይህንንና ሌሎች አማራጭ የቤት ግንባታ ግብዓቶችንና ቴክኖሎጂን በመጠቀሙ ረገድ በሀገራችን ያለው ልምድ “ዜሮ ነው” ሊባል የሚያስችል።


ኢትዮጵያ በዓለማችን ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ሀገራት መካከል የምትመደብ እንደመሆኗ መጠን መሰረታዊ የሆነው የሰዎች መጠለያን በመገንባቱ ሂደት ሀገሪቱ በየዓመቱ ቢሊዮን ብሮችን ማፍሰስ ግድ ይላታል። አሁን ባለው ሁኔታ ፍላጎትና አቅርቦቱ ከመቀራረብ ይልቅ ይበልጡኑ እየሰፋ በሄደበት ሁኔታ አንድ ሌላ አማራጭ የቤት ግንባታ ቴክኖሎጂ መኖሩን የሚያሳይ የቤት አሰራርን ተመልክተናል። ይህ አማራጭ የቤት አሰራር ዘዴ መደበኛውን ቤት ለመገንባት የሚያገለግሉትን እንደ ድንጋይ፣ ብረትና ብሎኬት ያሉ ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ በማስቀረት እነዚህን ግብዓቶች ተጠቅመን ከምንሰራቸው ቤቶች ጥንካሬን ጨምሮ በብዙ መልኩ የተሻሉ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ነው።


እነዚህ መደበኛ ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ ከቀሩ በኋላ በቤቶቹ ግንባታ ጥቅም ላይ የሚውለው ዋነኛ ግብዓት፤ በተለምዶ በህብረተሰባችን ዘንድ “ሃይላንድ” ተብሎ የሚጠራው ያገለገለ የፕላስቲክ ጠርሙስ ነው። ይህ የፕላስቲክ ጠርሙስ በብዛት ከተሰበሰበ በኋላ እያንዳንዱ ጠርሙስ ውስጥ አፈር እየተሞላ ለግንባታ ዝግጁ እንዲሆን ይደረጋል። በየአካባቢው ተበትነው የሚጣሉ እነዚህ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ሲምኮን ቴክኖሎጂ በተባለ ኩባንያ አማካኝነት ለቤት ግንባታ ሥራ የሚውሉበት አሰራር ተነድፎላቸዋል።


አንድ ሰው ቤቱ ሲሰራ በአይኑ ካላየ በስተቀር እንዴት አንድ ቤት ከፕላስቲክ ጠርሙሶች ብቻ ተገንብቶ መኖሪያ ቤት ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ በአዕምሮው ሊመላለስ ይችላል። በዚህ ዙሪያ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ያደረገው ሲምኮን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ቤቱ በምን መልኩ እውን እንደሚሆን ለማሳየት አንድ ሞዴል ቪላ ቤትን በአዳማ ከተማ ገንብቶ ለዕይታ አቅርቧል። ይሄነኑ ቤትም ከሰሞኑ ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል። እኛም በቦታው ተገኝተን አፈር ከተሞሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ተገንብቶ በአንድ መቶ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ዘመናዊ ቪላን ተመልክተናል።


ቤቱ ካገለገሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች የተገነባ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ በአንድ ጎኑ ውጫዊ ክፍል ብቻ የልስንና የማጠናቀቂያ ሥራ (Finishing) እንዲሰራለት አልተደረገም። ከዚህ ውጪ በሌላኛው የቤቱ ዙሪያም ሆነ ወደ ውስጥ ሲገባ ቤቱ “በፕላስቲክ ጠርሙስ የተገነባ ነው” ብሎ ለማመን እስኪከብድ ድረስ የቤቱ የማጠናቀቂያ ሥራ (Finishing) በእጅጉ የተዋጣለት ሆኖ ተመልክተነዋል። የጂፕሰሙ ሥራ፣ የመብራቶቹ፣ የበርና የመስኮቶቹ አሰራርና የመሳሰሉት ሲታዩ በውበት ደረጃ ቤቱ ከተለምዶ መደበኛ ቤቶች ባልተለየ መልኩ ውበትን የተላበሰ ሆኖ አይተነዋል። ይህንን ሞዴል የፕላስቲክ ጠርሙስ ቤት ጋዜጠኞችና የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጎብኝተውታል። ከጉብኝቱ በኋላ የሲምኮን ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አዲል አብደላ በቤቱ አሰራርና ጠቀሜታ ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት በበርካቶች አዕምሮ ውስጥ ሲብላሉ ለነበሩት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።


እንደ ዶክተር አዲል ገለፃ በፕላስቲክ ጠርሙሶቹ የሚገነቡ ቤቶች በአገልግሎት ረገድ የሚሰጡት ጥቅም በመደበኛ ግንባታ ከሚሰሩት ቤቶች በብዙ መልኩ የላቁ ሆኖ ይታያል። ይህንንም የተለየ ጠቀሜታ ለማሳየት ዶክተር አዲል የተለያዩ ማሳያዎችን በማብራሪያቸው አካተዋል። በዚህም ገለፃ መሰረት በፕላስቲክ ጠርሙሶች የሚገነቡ ቤቶች በመደበኛ የግንባታ ግብዓት ከሚገነቡ ቤቶች የተለየ የሚያደርጋቸው ጥንካሬያቸው ነው። አንድ ቤት በሸክላ፣ በተለያዩ የጡብ አይነቶችና በብሎኬት ምርቶችና በመሳሰሉት ግብዓቶች ሊገነባ ይችላል። ከሁሉም ግብዓቶች የተሻለ ጥንካሬ አለው የሚባላው ግን ሸክላ ነው። ዶክተር አዲል በሰጡት ማብራሪያ ግን አፈር በተሞሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች የሚገነቡ ቤቶች የጥንካሬ ደረጃ ግን ከመደበኛው የሸክላ ቤት ጋር ሲነፃፀሩ ከ20 እጥፍ የሚልቅ ጥንካሬ አላቸው።


ይህም የጥንካሬ ደረጃ በሸክም ደረጃ ሲለካ በአንድ ካሬ ሜትር 438 ሺህ 977 ኪሎ ግራም ክብደትን መሸከም የሚችል መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ ቤቱ ጥይት የማይበሳው እንደዚሁም እሳት ቢነሳ እንኳን ፕላስቲኮቹ በአፈር የተሞሉ በመሆናቸው ቤቱን በራሱ እሳትን ማጥፋት የሚችል መሆኑን አመልክተዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የመሬት መንቀጥቀጥ ቢነሳ እንኳን እነዚህ ቤቶች መደበኛ ቤቶችና ህንፃዎች ለአደጋ ከሚጋለጡበት ሬክተር በላይ ርዕደ መሬትን መቋቋም የሚችሉ መሆናቸውም ተመልክቷል። በዚህም ቤቶቹ እስከ 9 ነጥብ 8 ሬክተር የሚደርስ የምድር መንቀጥቀጥን መቋቋም ይችላሉ ተብሏል። በመሬት መንቀጥቀጥ የሚደርሰው ጉዳት እንደየአካባቢውና የመሬት ሁኔታ ቢለያይም በርዕድ መሬት ሬክተር ስኬል መለኪያ ከባድ ጉዳት ያደርሳል የሚባለው 6 ነጥብ 3 ሬክተር ስኬል የሚደርስ የምድር መንቀጥቀጥ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ በሬክተር ስኬል መለኪያ 9 ሬክተር ስኬል የደረሱ ርዕደ መሬቶች በቁጥር እጅግ ውስን ናቸው። ከዚህ አንፃር ሲታይ በአፈር በተሞሉ የፕላስቲክ ቤቶች እስከ 9 ነጥብ 8 ሬክተር ስኬል የሚለካ የምድር መንቀጥቀጥን መቋቋም ከቻሉ እጅግ ጠንካሮች ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል።


ሌላኛው የቤቶቹ ልዩ ባህሪ ተደርጎ የተጠቀሰው ያለምንም ተጨማሪ ማሽን እገዛ የሙቀት መጠንን በራሳቸው መቆጣጠር መቻላቸው ነው። ዶክተር አዲል በሰጡትን ማብራሪያ ቤቶቹ ውጪው ሲሞቅ የሚቀዘቅዙ እንደዚሁም ውጪው ሰቀዘቅዝ ደግሞ የሚሞቁ መሆኑን ገልፀውልናል። በዚህም የቤቶቹ ሙቀት ከ18 ዲግሪ ሴልሸስ የማይበልጥ መሆኑም በጥናት የተረጋገጠ መሆኑም ተመልክቷል። ከዚህም በተጨማሪ ቤቶቹ ጎርፍን እስከ 1 ነጥብ 5 ሜትር ድረስ ከመቋቋሙም በተጨማሪ 2 መቶ ኪሎ ሜትር በሰዓት የሚፈጥንን የነፋስ ኃይልንም የመቋቋም አቅም ያላቸው መሆኑንም ከገለፃው መረዳት ችለናል።


ሌላው የቤቶቹ ጥቅም ተደርጎ የተወሰደው ከግንባታ ወጪ አንፃር ከመደበኛው ቤት አኳያ የሚጠይቁት ወጪ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ነው። አንዳንድ ጥናቶች በፕላስቲክ ጠርሙሶች ግብዓትነት የሚገነቡ ቤቶች ከመደበኛ ቤቶች አንፃር ሲታዩ የሚጠይቁት ወጪ በአራት አጥፍ ያንሳል። ዶክተር አብዲል ቤቱ የሚጠይቀውን አጠቃላይ ወጪ ከመደበኛው ቤት ወጪ አንፃር በንፅፅር ለማወቅ በተግባር የተሰራ የጥናት ውጤት መኖሩን ገልፀውልናል። አሁን ለማሳያነት የተገነባው የፕላስቲክ ጠርሙስ ቤት ከመገንባቱ በፊት ከፕላስቲክ ጠርሙስ ቤቱ ተመሳሳይ የሆነ ስፋት እና ደረጃ ያለው ቤት በመደበኛው አሰራር ዋጋው እንዲሰራ ተደረገ።


በዚህም መሰረት በአንድ መቶ ካሬ ሜትር ላይ አርፎ ሶስት መኝታ፣ አንድ ሳሎን፣ ሁለት መፀዳጃ እና አንድ ማዕድ ቤት ያለው ቪላ ቤትን ለመገንባት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ መሆኑን በተደረገው የግንባታ ዋጋ አወጣጥ አሰራር ሂደት የታወቀ መሆኑን ዶክተር አዲል አመልክተዋል። በተመሳሳይ መልኩ የክፍሎቹ ይዘትና ስፋት ሳይቀየር በፕላስቲክ ጠርሙሶቹ አማካኝነት ያንኑ ቤት መገንባት የተቻለው በ345 ሺህ ብር ብቻ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል። ይህም የዋጋ ልዩነት በንፅፅር ሲታይ በፕላስቲክ ጠርሙሶች የተገነባው ቤት በመደበኛ መልኩ ከሚገነባው ቤት የ855 ሺህ ብር ቅናሽ ያለው መሆኑ ነው።


ይሄንንም ሞዴል ቤት ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሶስት ሳምንታት ብቻ የወሰደ መሆኑን ከኃላፊው ገለፃ መረዳት ችለናል። የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ለቤት ግንባታ አገልግሎት ማዋል ያለው ጥቅም ከግንባታ ዋጋም አንፃር ብቻም ሳይሆን የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ብክለትንም ጭምር ለመከላከል ነው። ጥናቶች እንሚያመለክቱት አንድ ፕላስቲክ ጠርሙስ አፈር ውስጥ ገብቶ ሙሉ በሙሉ በስብሶብሶ ከአፈሩ ጋር ለመዋሃድ ከ5 መቶ በላይ ዓመታትን ይፈጃል። ፕላስቲኮቹ በተለይ የውሃ አካል ውስጥ ሲገቡ በአካባቢው ሥነ ምህዳር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ነው። ከፕላስቲክ ማሸጊያዎች፣ እንደዚሁም ከፕላስቲክ ጠርሙስ ውሃ ምርት መበራከት ጋር በተያያዘ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በርካታ ሀገራት መፍትሄ ማፈላለግ ግድ ሆኖባቸዋል።


ከእነዚህም መፍትሄዎች መካከል አንደኛው ፕላስቲኮቹን ወደ ሌላ ምርት መቀየር (recycle) ሲሆን ሁለተኛው በፕላስቲክ ጠርሙስ መሰል የቤት ግንባታን ማከናወን ነው። ይህ በፕላስቲክ የቤት ግንባታን የማከናወን ሥራ በህንድና በናይጄሪያ በስፋት በተግባር ላይ እየዋለ መሆኑን መረጃዎች መለክታሉ። በሀገራችንም ይህ ሥራ መጀመሩ ከብዙ አቅጣጫ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
979 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 831 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us