የናይል ቀን በኢትዮጵያ

Wednesday, 21 February 2018 11:14

 

የናይል ተፋሰስ ሀገራት ትብብር “የናይል ቀን” በሚል በየዓመቱ ያከብራሉ።ይህ በየዓመቱ የሚታሰበው ዝግጅት በዚህ ዓመትም በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ Shared River, Collective Action በሚል መሪ ቃልፌብሩዋሪ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይከበራል።

 

በዕለቱም የተለያዩ የጥናት ወረቀቶች በበርካታ ምሁራን የሚቀርብ መሆኑ ይሄንኑ ጉዳይ አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት በዋሽግንተን ሆቴል የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ያመለክታል። በናይል ተፋሰስ ስር አስር የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ሲሆን እነዚህ ሀገራት ወንዙን በፍትሃዊና በትብብር በመጠቀሙ ረገድ ምንም አይነት የጋራ መድረክ ኖሯቸው አያውቅም።

 

ሆኖም ውሃውን በትብብር በመጠቀሙ ረገድ የተለያዩ ቅድመ ሥራዎች ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በስተመጨረሻ የናይል ተፋሰስ ሃገራት ትብብር (Nile Basin Initiative) እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም እንዲቋቋም ተደረገ። ይህም ትብብር በስሩ አስር የተፋሰሱ ሀገራትን የያዘ ሲሆን የናይል ቀንም በየዓመቱ እንዲከበር የሚደረገው ትብብሩ ይፋ የሆነበትን ቀን ለማሰብ ነው። ተፋሰሱ ኢትዮጵያን፣ ብሩንዲን፣ሩዋንዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን፣ ኡጋንዳን፣ ግብፅን፣ ሱዳንን፣ ደቡብ ሱዳንን ኬኒያን፣ ታንዛኒያን በአባልነት የያዘ ነው።

 

የናይል ተፋሰስ ትብብር ሲቋቋም ካሉት በርካታ አላማዎች መካከል አንደኛው የናይልን ውሃ የተፋሰሱ አባል ሀገራት ፍትሃዊ በሆነ ክፍፍል እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው። ይህንን ጉዳይ እውን እንዲሆን በማድረጉ ረገድ የተፋሰሱ አባል ሀገራት ዓመታትን የፈጀ ውይይቶችንና ድርድሮችን ማድረግ ግድ ብሏቸዋል።

 

ከአስር ዓመታታ ያላነሱ ተከታታይ ድርድሮች በኋላ የመጨረሻ እ.ኤ.አ በ2010 መግባባት ላይ ተደርሶ ሀገራቱ የጋራ ትብብር ሰነድን መፈረሚያው ጫፍ ላይ ሲደርሱ ግብፅና ሱዳን ራሳቸውን አገለሉ። በጊዜው ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በሰነዱ ላይ ፊርማቸውን አኖሩ። በቅኝ ግዛት ዘመን እ.ኤ.አ ግብፅና እንግሊዝ በደረሱበት ስምምነት መሰረት በእንግሊዝ ቅኝ ሥር የነበሩ ሀገራት የናይል ውሃን ለመጠቀም የግድ የግብፅን ፈቃድ መጠየቅ ይጠበቅባቸው ነበር።

 

ሆኖም አዲሱ በግብፅ የተገፋው ሥምምነት ይህንን የቀደመ ሥምምነት በአዲሱ በጋራና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሥምምነት የሚተካ በመሆኑ ነው። ግብፅ ስምምነቱን ጥላ ብትወጣም በተደረሰው ሥምምነት መሰረት ውሃውን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ሀገራት ሥምምነቱን ከፊርማ ባለፈ ተቀብለው በህግ አውጪ አካላቸው በማፅደቅ ወደ ሥራ በመግባቱ ረገድ የሄዱበት ርቀት እጅግ ውስንነት የሚታይበት የሚሉ ተደጋጋሚ ትችቶች ሲቀርቡ ይሰማል። ኢኒሼቲቩ እውን ከሆነ እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ ሁለት አስርት ዓመታት ቢቆጠሩም በተጨባጭ መሬት ላይ የወረደ ተግባር የለም የሚሉ ተደጋጋሚ ትችቶች ሲቀርቡ ቆይተዋል።

 

በዚህ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡን የናይል ቤዝን ኢኒሼቲቭ ኤግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ኢኒሼቲቩ ከተቋቋመበት ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን የሰራ መሆኑን ገልፀውልናል። እንደእሳቸው ገለፃ የጋራ ትብብሩ ከስምምነቱ እውን መሆን በኋላ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል። ከሰራቸው ሥራዎች መካከልም ሀገራት ወንዙን በጋራ በመጠቀሙ ረገድ የጋራ ደንበር ተሻጋሪነት ጥቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ ነው። የጋራ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት እንዲኖር እንደዚሁም የተፋሰሱን ሀገራት ውሃውን በአግባቡ የመጠቀም አቅም መገንባቱ ላይም ሥራዎች ሲሰሩ የቆዩ መሆኑ ተገልጿል። እ.ኤ.አ ከ1999 በፊት የተፋሰሱ ሀገራት በናይል ዙሪያ የሚወያዩበት ምንም አይነት የጋራ መድረክ ያልነበራቸው መሆኑን ያመለከቱት አቶ ፈቅአህመድ፤ ሆኖም በ1999 ኢኒሼቲቩ ከተቋቋመ በኋላ ሀገራት በውሃው አጠቃቀም ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት እየተገናኙ እንዲወያዩ ማስቻሉ በራሱ ትልቅ እድገት ነው ብለዋል።

 

አቶ ፈቅአህመድ ሀገራት እነዚህን የጋራ ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ በማድረጉ ረገድ ኢኒሼቲቩ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ፋይናንስ እንዲያገኙ በማድረጉ ረገድ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀውልናል። በዚህ ረገድም ኢትዮጵያንና ደቡብ ሱዳንን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርገውና በባሮ ላይ የሚገነባው ባሮ-አኮቦ-ሶባት ዘርፈ ብዙ የውሃ ሀብት ልማት እውን እንዲሆን በማድረጉ ረገድ አማካሪዎችን በማስተባባርና በሌሎች ተግባራት ሰፊ ሥራ የሰራ መሆኑን ገልፀውልናል። የኢትዮ-ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ትስስርም በተመለከተ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ኢኒሼቲቩ ሰፊ ሥራ የሰራ መሆኑን በመግለፅ፤ ይሄው ፕሮጀክት በስኬት ተምሳሌትነት ተጠቅሷል። የናይል ቤዝን ኢኒሼቲቭ የልማት ፕሮግራሞች በኢነርጂና በመሳሰሉት ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው ተብሏል። ሀገራቱ የበለጠ በኢኮኖሚ የተሳሰሩ በማድረጉ በኩል የመሰረተ ልማት ትስስር እንዲኖራቸው ማድረግ ዋነኛው ተግባር ተደርጎ እየተሰራ ነውም ተብሏል። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ እምቅ የኤሌክትሪክ አቅም ስላላት አካባቢውን በኃይል ለማስተሳሰር ያላት ሚና ከፍተኛ መሆኑም በጋዜጣዊ መግለጫው ተመልክቷል።

 

በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ከሚታዩት መሰረታዊ ችግሮች መካከል አንደኛው መተማመን አለመቻል ነው። በዚህ ረገድ በተለይ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የሚታየውን ሥጋት ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች የተሰሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። አቶ ፈቅአህመድም ይሄንኑ ሀሳብ በመጋራት ኢኒሼቲቩ በዋነኝነት እየሰራባቸው ካሉት ሥራዎች መካከልም አንዱ ሀገራት በውሃው አጠቃቀም ዙሪያ መተማመን መፍጠር ይችሉ ዘንድ ያለውን የመረጃ ክፍተት የመሙላት ሥራን መስራት ነው። በዕለቱ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ግጭቶች ቢነሱ የትብብሩ ሚና ምን ይሆናል? የሚለው ይገኝበታል። ትብብሩ ወደ ኮሚሽንነት ካላደገ በስተቀር በአባል ሀገራት መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ተጠቅሞ መፍትሄ ለመስጠት የሚቸገር መሆኑ ተመልክቷል።

 

የናይል ቀን እ.ኤ.አ በ2007 መከበር የጀመረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህም ዓመት ጀምሮ በነበረው የናይል ቀን፤ በናይል ዙሪያ በርካታ የጥናት ወረቀቶች የሚቀርቡ ሲሆን የየሀገራቱ የውሃ ሀብት፣ የግብርና እና የኢነርጂ ሚኒስትሮች በመድረኩ ላይ ይገኛሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የየሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የአካዳሚክ ሰዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የፓርላማ አባላትና የሚዲያ ሰዎችም የዚሁ በዓል ታዳሚዎች መሆናቸውን በትላንትናው ዕለት የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ያመለክታል።

 

ሩዋንዳ በ2007 የመጀመሪያውን የናይል ቀን ያስተናገደች ሀገር ናት። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳና ሌሎች የተፋሰሱ አባል ሀገራት በተከታታይ ይህንኑ ቀን ለማሰብ ፕሮግራሙን ያዘጋጁ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
978 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 654 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us