የዓለም አቀፉ የሙስና ደረጃና ኢትዮጵያ

Wednesday, 28 February 2018 12:15

 

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየዓመቱ የየሀገራቱን የሙስና ተጋላጭነት ዝርዝር በማውጣት ሀገራትን ነጥብ እየሰጠ በደረጃ ያስቀምጣል። ባለፈው 2016 የፈረንጆች ዓመት የነበረውን ዓለም አቀፍ የሙስና አመላካች ሁኔታ በያዝነው 2018 የፈረንጆች ዓመት ይፋ አድርጓል። ሪፖርቱ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ያለው የሙስና ሁኔታ እየተባባሰ መሄዱን ያመለክታል። ኢትዮጵያም በዚሁ ሪፖርት የተዳሰሰች ሲሆን በ180 ሀገራት ዝርዝር ውሰጥ ተካታ ደረጃ ተሰጥቷታል። የሙስናን መስፋፋትና ዝንባሌን በተመለከተ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሚያወጣውን ሪፖርት በተመለከተ አንዳንዶች ሪፖርቱ በትክክል የየሀገራቱን የሙስና ደረጃ አያመለክትም በሚል የሚተቹ አሉ። “መነሻ የጥናት ሀሳቡንም ቢሆን በርቀት የሚሰበሰብ ወይንም በሶሰተኛ ወገን የሚሰጥ መረጃ ነው” በማለት የትችት ሃሳባቸውን የሚሰነዝሩ ቢኖሩም ድርጅቱ ግን በየዓመቱ መረጃውን ማውጣቱን ቀጥሎበታል።

አጠቃላይ የሪፖርቱ ይዘት


ሪፖርቱ በአጠቃላይ 180 ሀገራትን በዚሁ የሙስና ማነፃፀሪያ ሰንጠረዥ ውስጥ አካቷል። በዚህ ረገድም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት የሚገኙበትን ሁኔታ ዘርዝሮ በቅደም ተከተል ያስቀመጠ ሲሆን በጠቃላይ ባስቀመጠው ደረጃም ሀገራት ባለፉት ስድስት ዓመታት ሙስናን ለመዋጋት ያደረጉት አስተዋፅኦ አነስተኛ መሆኑን አመልክቷል።


ሙስናን በመዋጋቱ ረገድ በሀገራት ያለው የፕሬስ ነፃነትና የተቋማት ጠንካራነት እንደዚሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በወሳኝነት ተቀምጠዋል። ሪፖርቱ በዚህ ረገድ ደካማ የፕሬስ ነፃነት ያለባቸው ሀገራት የሙስና ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱን ያመለክታል።


ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ለሀገራት የሙስና ደረጃ ውጤት የሚሰጠው ከአንድ እስከ መቶ ባለው አሃዝ ነው። በዚህም መሰረት በ2017 የሙስና ደረጃ ሪፖርት 89 ውጤት በማስመዝገብ የአንደኝነት ደረጃን የያዘችው ኒውዚላንድ ናት። ዴንማርክ ከኒውዚላንድ በአንድ ነጥብ በማነስ 88 አምጥታ የሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ከካናዳ ውጪ ከአንድ እስከ አስር ያለውን ደረጃ የያዙት የአውሮፓ ሀገራት ናቸው። ሴኔጋል 45 ነጥብ በማምጣት በአፍሪካ የአንደኝነትን ደረጃ ስትይዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ 66ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ደቡብ አፍሪካ በ43 ነጥብ ከአፍሪካ የሁለተኛ ደረጃን እንደዚሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ 71ኛ ደረጃን ስትይዝ፤ ጋና 40 ነጥብን ይዛ በአፍሪካ በሶስተኝነት ደረጃ ተቀምጣለች። ጋና በዓለም አቀፉ የንፅፅር ሰንጠረዥ ያላት ቦታ 81ኛ ነው። ሞሮኮም በተመሳሳይ መልኩ 81ኛ፣ ቤኒን 85ኛ ደረጃን ሲይዙ ኮትድቯርና ታንዛኒያ ተመሳሳይ 36 ነጥብን በማምጣት በዓለም አቀፉ የንፅፅር ሰንጠረዥ ሁለቱም ሀገራት በእኩል 103ኛ ደረጃ ላይ ተገኝተዋል።


ኢትዮጵያ በዚህ ሪፖርት ከ180 ሀገራት ውስጥ 107ኛ ደረጃ የያዘች መሆኗን ሪፖርቱ ያመለክታል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የተቀመጠችው 103ኛ ደረጃን ከያዘችው ታንዛኒያ ቀጥሎ ነው። አርሜኒያ እና ቬትናም ከኢትዮጵያ ጋር እኩል 35 ነጥብ በማገኝት በተመሳሳይ የ103ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


ሪፖርቱ አ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ የሀገራት የሙስና ሰንጠረዥ ሲታይ በርካታ ሀገራት ደረጃቸውን ሲያሻሽሉ፤ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሀገራት ደግሞ ከነበሩበት ደረጃ ተንሸራተው የታዩ መሆኑን የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ጨምሮ ያመለክታል። የተሻለ መሻሻል ታይቶባቸዋል ከተባሉት ሀገራት መካከልም ኮትዲቯር፣ ሴኔጋልና ዩናይትድ ኪንግደም በቀዳሚነት ተጠቅሰዋል።


አካባቢያዊ ንፅፅሮሽ


ሪፖርቱ ሀገራትን በዝርዝር ከማስቀመጥ ባሻገር አካባቢያዊ (Regional) በሆነ መልኩም የራሱን የንፅፅር ዳሰሳ አስቀምጧል። በዚህም ንፅፅሮሽ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በድምሩ በአማካይ 32 ነጥብን በማስመዝገብ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ይታያሉ። ምስራቅ አውሮፓና መካከለኛው እስያም በአካባቢያዊ ደረጃ 34 አማካይ ነጥብን በማስመዝገብ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ብዙም ባልራቀ ውጤትን ያስመዘገበ ነው። የተሻለ ውጤትን ያስመዘገበው ምዕራብ አውሮፓ ነው። አማካይ ነጥቡ 66 ነው።


አፍሪካ አሁንም በሀገራት ዝርዝር ደረጃ ሲታይ ሙስናን በመዋጋቱ ረገድ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኑ ዝርዝሩ ያመለክታል። አፍሪካ በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና ተጋላጭነት የንፅፅር ሰንጠረዥ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የተገኘች አህጉር ብትሆንም በቅርቡ ከወር በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ሙስና የአህጉሪቱ ዋነኛ ተግዳሮት በመሆኑ መፍትሄ ይፈለግለት ዘንድ የተመከረበት ሁኔታ ነበር።

 

የሚዲያ ነፃነት ገደብና የሙስና ተጋላጭነት


ሪፖርቱ የሚዲያ ነፃነት የተገደበባቸው ሀገራት ለሙስና ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱን ያመለክታል። ነፃ ሚዲያ ከዲሞክራሲ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መሆኑን ያተተው ይሄው ሪፖርት የሙስና መስፋፋትና የሚዲያ ነፃነት እጦት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን አትቷል።

 

የሀገራት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት


ባለመረጋጋት ውስጥ ያሉ ሀገራት ለሙስና ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። እነዚህም በከፋ ደረጃ ለሙስና ተጋላጭ ተደርገው ከተዘረዘሩት ሀገራት መረጋጋት ከማይታይባቸው ሀገራት መካከል ሶሪያ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን በግንባር ቀደምትነት ተጠቅሰዋል። ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው ሀገራቱ ካሉበት የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ልዩ ልዩ ተቋሞቻቸው የፈራረሱ ወይንም ክፉኛ የተዳከሙ መሆናቸው ነው።

በምክረ ሀሳብ ደረጃ የተቀመጡ ነጥቦች


ጥናቱ በምክረ ሃሳብ ደረጃ ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል መንግስታት ሙስናን ለመዋጋት ገለልተኛ ሚዲያን እንዲያበረታቱ፣ የመናገር ነፃነት እንዲኖር የሲቪል ሶሳይቲ ሚና እንዲጠናከር እንዲያደርጉ ይጠይቃል። ጋዜጠኞች ያለምንም መሸማቀቅ ሙያዊ ሥራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ የግድ መሆኑን የሪፖርቱ ምክረ ሀሳብ ይጠይቃል። የመንግስታት አሰራር ግልፅነት ኖሮት ተጠያቂነት መስፈን የሚችለውም የሚዲያ ነፃነት ሲኖር መሆኑን ይሄው ምክረ ሀሳብ ይተነትናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
3538 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 645 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us