በኢኮኖሚ ትስስር ያልታሸው የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት የአቋም ለውጥ እየታየበት ይሆን?

Wednesday, 14 March 2018 12:37

 

የኢትዮጵያን የውስጥ ፖለቲካ ትኩሳት ተከትሎ አሜሪካ ያላትን አቋም በግልፅ አሳውቃለች። በተለይ ሁለተኛውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምትቃወም መሆኗን ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ በኩል በኋላም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሬክስ ቴለርሰን በኩል ገልፃለች። ሁኔታው የቀደመው የኢትዮጵያ መንግስትና የአሜሪካ የሞቀ ወዳጃዊ ግንኙነት የተለየ መልክን እየያዘ መምጣቱን የሚያሳይ ሆኗል።

 

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የስልጣን ዓመታት ወቅት አልቃይዳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሽብር ሥጋት የነበረበት ጊዜ ነበር። በተለይ ከምርጫ 97 ቀደም ብሎ በነበሩት ጥቂት ዓመታትና ከዚያ በኋላ በነበሩት ተከታታይ ዓመታት አሜሪካና አጋሮቿ የአልቃይዳን አለም አቀፍ የሽብር መረብ ለመበጣጠስ በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል።

 

በዚህ ረገድም የዓለም አቀፉ የፀረ ሽብር ዘመቻ አጋር ተደርገው ከተወሰዱት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ልትሆን በቅታለች። ኢትዮጵያ በጊዜው የዚህ ዘመቻ አጋር እንድትሆን ከተደረገባቸው ምክንያቶች መካከል ዋነኛው አልቃይዳ ከአልሸባብ ጋር በመጣመር መረቡን በሶማሊያ ምድር በመዘርጋቱ ነበር። ይህንንም ኃይል ለመምታት የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ጦሩን ወደ ሶማሊያ በመላክ ቀደም ብሎ ከእስላማዊ ፍርድ ቤት ኃይሎች በኋላም ከአልሸባብ ጋር የፊት ለፊት ፍልሚያ አድርጓል። ከአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ጦር(AMISOM) ጋር በጋራ ሰርቷል።

 

በጊዜ ሂደት እስላማዊ ፍርድ ቤት ከነአካቴው በሶማሊያ ምድር መጥፋቱ እንደዚሁም እሱን የተካው አልሸባብ እየተዳከመ መሄድ ግድ ብሎታል። በተለይ የአልቃይዳ አለም አቀፍ እንቅስቃሴ እየደበዘዘ መሄድና በአይ ኤስ አይ ኤስ መተካት፤ አልሸባብ የበለጠ የተነጠለ ቡድን እየሆነ እንዲሄድ አድርጎታል። አሜሪካም ብትሆን በሳተላይት የስለላ መረጃ በመደገፍና የአልሸባበብ አመራሮችን ኢላማ ባደረገ መልኩ ተደጋጋሚ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ማድረሷ አልሸባብ ክፉኛ እንዲዳከም አድርጎታል። ይህ ጥቃት በተለይም የአልሸባብን የዕዝ ማዕከላትና አመራሮችን ዋነኛ ኢላማው ማድረጉ ቡድኑ የበለጠ እየተዳከመ ያደረገው መሆኑ ይነገራል። የአልቃይዳና የአልሸባብ መዳከም በአሜሪካ መንግስት የዓለም አቀፉ የፀረ ሽብር አጋር ተብለው የተለዩ መንግስታት የግንኙነት ሁኔታም የሚወስነው ይሆናል። የቀደመው በአሜሪካ የሽብር ስጋትና ደህንነት ላይ መሰረት አድርጎ የተቀረፀው ግንኙነት እየደበዘዘ ለመሄድ ይገደዳል። ፓኪስታን የአፍጋኒስታን ጎረቤት አንደመሆኗ መጠን አሜሪካ በአፍጋኒስታን አልቃይዳን እንደዚሁም ታሊባንን ስትዋጋ በብዙ መልኩ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቅኝት መሰረት ያደረገው እነዚህን ኃይሎች በመደምሰሱ ላይ ነበር።

 

በሂደትም አልቃይዳ ተዳከመ፣ መሪው ቢላደንም ተገደለ። የታሊባንና የሌሎች እስላማዊ ታጣቂዎችም እጣ ፈንታ በተመሳሳይነት የሚታይ ሆነ። ይህ ሁኔታ የቀደመውን የአሜሪካን-ፓኪስታን ግንኙነት በነበረበት የሞቅታ ድባብ እንዳይቀጥል አድርጎታል። አሜሪካ ዛሬ የተጠናከረ ግንኙነት ያላት ከፓኪስታን ይልቅ ሰፊ የተጠናከረ የኢኮኖሚ አቅም ካላት የራሷ የፓኪስታን ጎረቤት ከሆነችው ህንድ ጋር ነው።

 

ነገሩን ወደ ኢትዮ አሜሪካ ግንኙነት ስንመልሰው የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፀረ ሽብር ዘመቻ አጋርነት ከሚለው እሳቤ እየወጣ ይመስላል። ለዚህ ደግሞ ከሶማሊያ አንፃር ሲታይ ሁለት መሠረታዊ ሚዛን የሚደፉ ጭብጦች ይታያሉ። አንደኛው ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው የአልሸባብ መዳከም ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከብዙ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥረት በኋላ የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት በራሱ መቆም መቻሉ ነው። የዚህ ማዕከላዊ መንግስት መጠናከር የሶማሊያ ጉዳይ በሶማሊያዊያን ብቻ መፍትሄ እንዲሰጠው በማድረግ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በሶማሊያ ጉዳይ ስትጫወተው የነበረውን ዓለም አቀፍ ሚና የሚቀንሰው ይሆናል። የሚታየውም ነባራዊ ዕውነታም ይህ ነው።

 

የኢትዮጵያ መንግስት በአካባቢው ጠንካራ የፀረ ሽብር አጋርና የሰላም ኃይል ተደርጎ በአሜሪካዊያንና በሌሎች የአሜሪካ አጋሮች እንዲወሰድ ያደረጉት ሌሎች አካባቢያዊ ምክንያቶችም እንዳሉ ሊዘነጋ አይገባም። አንደኛው ምክንያት ሱዳን በአሜሪካ ፀረ ሽብር መዝገብ ውስጥ ገብታ በማዕቀብ ስትማቅቅ የቆየች ሀገር መሆኗ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የኤርትራ መንግስት ከምዕራባዊያን ጋር እጅግ በሻከረ ግንኙነት ውስጥ መገኘቱ ነው።

 

ይህ ብቻ ሳይሆን ደቡብ ሱዳንም በከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ መግባቷ የኢትዮጵያ መንግስት አካባቢያዊ ሚና የበለጠ የጎላ እንዲሄድ አድርጎታል። በዚህ መሃል ግን የሱዳንና የአሜሪካ ግንኙነት አዎንታዊ መልክን ይዟል። አሜሪካ ሱዳንን በሽብር ስጋትነት ከማየት ተቆጥባለች። በሀገሪቱ ላይ ለሁለት አስርት ዓመታት የጣለችውንም የኢኮኖሚ ማዕቀብ አንስታለች። ይህ የአሜሪካ-ሱዳን ግንኙነት ቢሆንም የሁለቱ ሀገራት የቀደመ የጥርጣሬ ግንኙነት እየለዘበ መሄዱ የኢትዮጵያ መንግስትን በአካባቢው ብቸኛ አጋርና የኃይል ሚዛን ጠባቂ ተደርጎ የመወሰዱን ሁኔታ ግን በተወሰነ ደረጃ የሚቀንሰው መሆኑ ጥርጥር የለውም። እነዚህ ሁኔታዎች የቀደመውና ከ1990ዎቹ ጀምሮ በፀረ ሽብር አጋርነት የተቃኘውን የኢትዮ- አሜሪካ ግንኙነት ሌላ መልክ እንዲይዝ የሚያደርጉት ይሆናል።

 

“አሜሪካ ቀደም ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች ሲካሄዱ ሰምታ እንዳልሰማች፤ አይታ እንዳላየች በመሆን ጉዳዩን በቸልታ ማለፍን እንድትመርጥ ያደረጋት የብሄራዊ ደህንነቷ ዋነኛ ማዕከል የሆነው የፀረ ሽብር አጋርነት ዘመቻዋ እንዳይበላሽ ነው” በማለት በተደጋጋሚ ወቀሳ ሲያሰሙ የነበሩ ወገኖች በርካቶች ናቸው። በዚህም በዜጎቻቸው ላይ ሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈፅሙትን መንግስታት ከመገሰፅ ይልቅ እሽሩሩ ማለትን መርጣለች በማለት ተደጋጋሚ ወቀሳዎች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።

 

በዚህ በኩልም አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀስ የነበረው የኢትዮ- አሜሪካን ግንኙነት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች እንደዚሁም እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች ያሉ አካላት በዚህ ረገድ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን በመሰንዘር የሚታወቁ ናቸው። አሁን ባለው ሁኔታ ያሉት የምስራቅ አፍሪካና አፍሪካ ቀንድ አካባቢ የፖለቲካ መልክአ ምድራዊ (Geopolitical landscape) መለዋወጥ አሜሪካ በዋነኝነት በቀደመው የፀረ ሽብርተኝነት አጋርነት ላይ ብቻ በተመሰረት የፖለቲካ ግንኙነት የአካባቢውን ሀገራት የፖለቲካ ቁመና የምትለካበት አካሄድ እየተቀየረ እንዲሄድ አድርጎታል።

 

ይህም በተለይ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው የአልሸባብ መዳከም፣ የአልቃይዳ ህልውና እያከተመ መሄድ፣ አዲሱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሥጋት የሆነው አይኤስአይኤስ ከመካከለኛው ምስራቅና ከሰሜን አፍሪካ ባለፈ ወደ ምስራቅ አፍሪካ አድማሱን ማስፋት አለመቻሉ ናቸው። እነዚህ አጠቃላይ ሁኔታዎች የኢትዮ-አሜሪካን በፀረ ሽብር አጋርነት ላይ የተመሰረተውን የሞቀ ወዳጃዊ ግንኙነት ሌላ መልክ እንዲይዝ የሚያደርግ ይሆናል።

 

ግንኙቱ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ብቻ ትኩረቱን የሚያደርግ ከሆነ አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግስት በተመለከተ የሚኖራት መለኪያ ከቀደመው የፀረ ሽብር አጋርነት የተለየ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የፓኪስታንና የአሜሪካ የሞቀ ወዳጃዊ ግንኙነት የቀጠለው አልቃይዳና ታሊባን ጠንካራ ሆነው እስከቀጠሉ ድረስ ብቻ ነበር። ፓኪስታን ያንን ግንኙነት ዘለቄታዊነት ባለው መልኩ ጠብቆ ለማቆየት ወደ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መቀየር ባለመቻሏ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜያዊ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።

 

በሌላ መልኩ የፓኪስታን ጎረቤት የሆነችው ህንድ ጠንካራ ኢኮኖሚን ከመገንባት ባለፈ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት የበለጠ ማስፋት በመቻሏ የአሜሪካ-ህንድ ግንኙነት እንደየሁኔታው በሚለዋወጥ የፖለቲካ የሙቀት መጠን የሚወሰን ሆኖ አልታየም። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሠረቱ በዋነኝነት ኢኮኖሚያዊ በመሆኑ በሁኔታዎች የፀና (All-weather partnership) ሆኖ ይታያል።

 

እንደ ኢኮኖሚክ ታይምስ ዘገባ ከሆነ በዓለም አቀፉ የንግድ ግንኙነት መሰረት ህንድ የአሜሪካ ዘጠንኛ የንግድ አጋር(9th largest trading partner) ሆና ተቀምጣለች። በ2015 ህንድ ወደ አሜሪካ የላከችው የሸቀጥ መጠን 44 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ሲደርስ አሜሪካ በአንፃሩ ወደ ህንድ የላከችው 21 ነጥብ 5 ዶላር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሁለቱ ሀገራት በጨርቃጨርቅ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በኬሚካል ምርቶች ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እጅግ ጠንካራ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትም ቢሆን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የአሜሪካንን የውጭ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ከሚያስተናግዱት ሀገራት መካከል ህንድ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በህንድ ካለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ውስጥ አሜሪካ ወደ 9 በመቶውን ድርሻ ትይዛለች።

 

በአንፃሩ የፓኪስታንና የአሜሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ከህንድ አሜሪካ ግንኙነት አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ሆኖ አይታይም። እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ትሬድ ሪፕረዘንታቲቭ ድረገፅ መረጃ ከሆነ በ2016 አሜሪካ ወደ ፓኪስታን የላከችው የሸቀጥ መጠን 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ነው። ፓኪስታን በአንፃሩ ወደ አሜሪካ የላከችው ዓመታዊ የሸቀጥ መጠን 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። ይህም ከህንድ ጋር ሲነፃፀር በብዙ እጥፍ የሚያንስ ሆኖ ይታያል። ፓኪስታን በአሜሪካ በኩል በፀረሽብር አጋርነት የተሰጣትን እድል ወደ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መቀየር ባለመቻሏ ዛሬ ከአሜሪካ ጋር ባላት ግንኙነት ከባላንጣዋ ህንድ እኩል ከአሜሪካ ፊት መቆም አልቻለችም።

 

የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነትም ቢሆን ከዚሁ የተለየ ሆኖ አልታየም። ከንግድ ግንኙነት አንፃር ኢትዮጵያ በንግድ አጋርነቷ ከሌሎች የአሜሪካ የንግድ አጋሮች ጋር ስትተያይ በ92ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኗን የሀገራትን የንግድ ግንኙነት የሚተነትነው Office of the United States Trade Representative ድረገፅ ያመለክታል። አብዛኛውም የንግድ ግንኙነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ያለው የአውሮፕላን ግዢ ላይ ያተኮረ ነው። ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ላሉ ሀገራት በአሜሪካ መንግስት በኩል ተሰጠውን ከቀረጥና ከኮታ ነፃ የገበያ እድልን እንኳን በሚገባ መጠቀም ያልቻለች ሀገር ናት። እነዚህ አጠቃላይ ሁኔታዎች ሲታዩ የኢትዮ አሜሪካ ግንኙነት በቀጣይም በእርዳታ ላይ ተንጠልጥሎ የሚቆይ መሆኑን ያሳያል። ግንኙነቱ ኢኮኖሚያዊ መሰረት እስከሌለው ድረስ በተለዋዋጩ የሀገር ውስጥና የአካባቢው ፖለቲካ መመራት ግድ ሆኖበታል። ይህም በመሆኑ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሀገር ውስጥ ተቃውሞዎች ሲበረቱ ብሎም የምስራቅ አፍሪካ የአካባቢ ፖለቲካ መለዋወጥ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የነበራትን የቀደመ ግንኙነት በተለየ መልኩ ለመቃኘት ፍላጎት ያላት መሆኑን በተግባር እያሳየች ትገኛለች። ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በግልፅና በማያሻማ ቋንቋ ለመቃወም አሜሪካን የቀደማት ሀገርና ተቋም የለም።

 

ይህ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ በኩል የተገለፀው ግልፅ የሀገሪቱ አቋም በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴለርሰንም ይሄንኑ የኢምባሲውን መግለጫ በተጠናከረና በተብራራ መልኩ ደግመውታል። ነፃነትን በመገደብ ሳይሆን ነፃነትን በማስፋት መፍትሄ እንደሚገኝ፣አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተቻለ ፍጥነት የሚነሳበት ሁኔታ እንዲኖርና የመሳሰሉትን የመንግስታቸውን ጠበቅ ያለ አቋምን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። አሜሪካ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከኢህአዴግ መራሹ መንግስት ጋር ባላት ግንኙነት እንደዚህ አይነት የተለየ አቋምን ስታራምድ ምን አልባትም ይህ የመጀመሪያዋ ነው ሊያስብል የሚያስችል ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1306 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 984 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us