አረንጓዴ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ፤ ቀላል ወይስ ከባድ የቤት ሥራ?

Wednesday, 21 March 2018 12:29

 

 

በሽዋፈራው ሽታሁን

 

ለልማት ሊቃውንትና ለአካባቢ አጥኚዎች “አረንጓዴ” የቀለም አይነት ብቻ አይደለም። የአካባቢ ክብካቤ ሥራዎችንም ይጠቀልላል - ከእልፍ የመሬት ሀብት ጥንቁቅ አጠቃቀም ጋር።

እርግት ላለ የኢኮኖሚ መንገድ ይሽን መስሉ መንገድ እንዲቀናበር አረንጓዴ አመራር ለአረንጓዴ ኢንዱስትሪአዊነት እንዲውል -አዋዋሉ ደግሞ ከአንድ በጎ ካልሆነ ማህበረ ኢኮኖሚ ጫፍ ወደ ሌላ በጎ ወደሆነ ማህበረ ኢኮኖሚ ሽግግር እንድናታደርግ እጀታ ይሆናታል- ኢትዮጵያ። ሰንሰለታዊ እሴት አካይ ምርት ወ አገልግሎት ከጥሬው ሀብት ተፈልቅቆና ተበጅቶ ለገበያ እንዲቀርብ አረንጓዴ ኢንዱስትሪአዊነት የሀገሪቱ ፖሊሲ ከሆነ ሰነበተ።

 

የአረንጓዴ ውትወታ (Green Advocacy) ልብ የሚገኘው በሰው ወደ አየር በሚለቀቀው የካርቦንዳይኦክሳይድ ላይ ነው። 87 በመቶውን የሚሸፍነውን እሱው ነው። የነዳጅ ቁፋሮና ንግድን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያኖረው እሱ ነው ካርቦንዳይ ኦክሳይድ።

 

የተፈጥሮ ጋዝ፣ የድንጋይ ከሰልና የነዳጅ ዘይት ጭስ የካርቦን፣ ሚቴንና የውሃ ትነት ያመነጫሉ ተመንጭተው ወደ ከባቢ አየር ሲበተኑ የዓለም ሙቀትን ያባብሳሉ። ማባባሳቸው የሰው ልጅ ሕይወት እንዲጠይም ምክንያት ይሆናሉ።

 

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ይኸን ፈተና በደህና ውጤት ለማለፍ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪአዊነት መንገዷ ላይ ያጋጠማትን ከባቢያዊ ጽድቅና ኩነኬ እንዴት እየተወጣች ነው?

ያለፍንበት መንገድ በ2025 መካለኛ ገቢ አገር ለመሰኘት ውጥን የዘረጋችው ኢትዮጵያ በ2011 ገነን ያለ በጉጉትና ተስፋ የተሞላ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራተጂ አጽድቃ ነበር። በዘላቂ የግብርና ሥራ አተገባበር ላይ መሰረቱን ያደረገ የማህበረሰብ አቀፍ ልማትን ከግሉ ዘርፍና ከዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ጋር በመደጋገፍ ስትራተጂውን ለማንቀሳቀስ በጥረት ላይ ነች ሀገሪቷ።

 

በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP)ና ግሎባል ኢንቫይሮመንት ፋሲሊቲ ድጋፍ አራት ፕሮጀክቶችን እየሰራች ነው። እነሱም፡- የጥብቅ አካባቢዎች የዘላቂ ልማት ፕሮጀክት፣ የግብርና ብዙሀነትን የማስናኘት ፕሮጀክት፣ የራስ አገዝ የመቋቋም ፕሮጀክትና የአየር ንብረት ለውጥና ድርቅን መከላከል ፕሮጀክቶች ናቸው። 

 

የፕሮጀክቶቹ ዛላና አረማመድ የግል ዘርፍ የሚያቀርባቸውን ምርትና አገልግሎት ከህብረተሰቡ ተግባራዊ የህይወት ፍላጎቶች ጋር የውሃ ልኩን ጠብቆ የአስተማማኝ ገበያ እያገኘ እንዲዘልቅ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተስፋ ያደርጋል።

 

የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ዓመታዊ መፅሔት “ፕሮጀክቶቹ የአየር ንብረት ለውጥ መልከ ጥፉ መልኮችን በማስተንፈስ ሻገር ሲልም ለማፈን እንድንችል ፕሮጀክቶቹ ተቋማዊ ቁመናችንን የሚሞርድ ቅንጅታዊ ሥራን እያቀረበልን ነው” ሲል የተነበበው ቃል አካባቢ ተኮር የገበያ ቁስ ለማቅረብ መጣጣር ትርፍን ይመግባል የሚል ምክር ለግሉ ዘርፍ የተፃፈለት አድርጎ መተርጎም ፍልሰት (fallacy) የለበትም።

 

በርግጥ የአየር ንብረት ለውጥ የኢትዮጵያ ቡና አምራችና ነጋዴ የሆነው የግሉን ዘርፍ አካል እየፈተነው ይገኛል። የአየር ጠባይ ለውጡ ለኪሳቸው ቢጫ መብራት እያሳየም ነው። ቀንና ሌሊቱ ይሞቃል። አንድ ሰሞን ሲቀዘቅዝ ይሰነብትና ደሞ በወዲያኛው በግልባጩ ይሆናል። ምርት ተገማችና አስተማማኝ እንዳይሆን በምርቱ ላይ እድገት ላይ ጫናውን ይምላል። እንዲህ ሲሆን ከግሉ ዘርፍም የሀገር ኢኮኖሚ ሆድ እንዳይብሰው የ15 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሕይወት የቡና ጥገኛ ነው። ቡናን ለተቀረው ዓለም በመላክ በአፍሪካ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ነን። ቡና ብቻ ሳይሆን የቅባት እህሎች አበባና ሌሎች ምርቶቻችን የውጪ ንግዳችን ምሰሶዎች ናቸው። ድርቅ ሲያጋጥም ማለት መኖን ውሃ ሲያጡ ከብቶቻችን በበሽታ ይጠቃሉ። እናም ወደ ውጭ ልከናቸው ዶላር እንዲላክልን አንበቃም።

 

በተገቢው ጊዜና በተገቢው አቅም ከተጠቀምንባቸው አዳዲስ አለም አቀፍና ብሔራዊ ፖሊሲዎች የግሉን ዘርፍ የአየር ንብረት ለውጥን የሚላመዱ ቁሶችን ማቅረቢያ የፋይናንስ አቅርቦት በተለይም በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ መርሃ ግብር ሲቀርብ እያየን ነው። ከስምምነት አኳያ።

 

በሌላ ወገን ደግሞ የግሉ ዘርፍ የአየር ጠባይ ለውጥን በተመለከተ ሃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በማልማት ትኩረት ያደርግበት ጀምሯል። ግን የዘላቂነት መርሕ ጋር ግብብ መሆኑ የተገባው ነው ደሞ ዘላቂነት ምንድነው?

ዘላቂነት

ጋዜጠኞች ለአየር ያበቁታል- የአካባቢ ሰዎች ይጠቅሱታል ግን የተባበሩት መንግስታት ጠቅልሎታል። በሀገረ ብራዚል በከተማ ሪዮዲጂኔሪዬ በ1992 ዓመት ብይን ሰጥቶበታል በ“ዘላቂነት” ትርጓሜ ላይ። ከትርጓሜው ትክክል መጪው ትውልድ የሚዘምርበት ቅኔ በውስጡ አለ።

 

ሀሳብና ተግባር የተቀላቀሉበት ተስፈኛው ትርጓሜ እንዲህ ነው። “የመጪውን ትውልድ ያለው የዝሬ ቁጠባዊና ሥርዓታዊ የአኗኗር አድራጎት አኗኗር ሥርዓት ነው” ይለዋል።

 

የሩሲያ ፌዴሬሽን ዜጎቹ ለመጪው ዘመን እንዲኖሩበት የማይነካ “ነዳጅና ወርቅ” ከልሎ አስቀምጦላቸዋል። አሜሪካኖቹም የቀጣዩ ትውልድ ተስፋ እንዲለመልም እንዲሁ አድርገዋል። ኢትዮጵያውያን ከልሎ ማስቀመጥ ባይችሉ እንኳ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና አያያዛቸው የመጪውን ትውልድ ህልውና የሚያደበዝዝ እንዳይሆን ማድረግ አይቻላቸውምን? ይህን ለመከወን ልዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ይጠይቃቸዋልን? ይቻላቸዋል -ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ ነው። ኧረ እንደውም ለሁለተኛው። ወሳኙ ነገር በእውነት የቆረጠ አመራርና በእውነት የተሰራ ፖሊሲ ናቸው።

 

አንዘንጋው! መቶ ሚሊዮን ሆነናል። በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ህዝብ አለ ማለት መሰረታዊ የኑሮ ፍላጎቶች ምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳትና ኃይልን ማሟላት በተፈጥሮ ሀብታችን ትከሻ ላይ ይወድቃል ማለት ነው። በማሟላት ቅስቃሴ ወቅት የካርቦን ወደ አየር መለቀቅን የሚያስከትሉ መሆናቸው እውቅ ነው።

 

የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የኦዞን (O3) ንጣፍ መሳሳት፣ የብዝሁ ህይወት መቀነስ፣ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን፣ የመሬት መንሸራተት፣ የውሀና የአየር መበከል፣ አካባቢያዊ መገለል የሃይል ቀውስ፣ ጎጂ ኬሚካሎች ስጋት፣ የተረፈ ምርት አያይዝ ችግር በመጨረሻም የህዝብ ቁጥር መጨመር (ወደ በረከት ካልተመነዘረ) ለመጪው ዘመን ያለ መኖር ፍርሃትን ኮትኩተው የሚያሳድጉ ብስል ተቀሊል ዝርዝር ውስጥ ያሉ ስንክሳሮች ናቸው። የፍርሀቱ ምንጭ የስንክሳሮቹ መዘዝ የሚያስከትሉት የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች ናቸው። ከወዲሁ ጠቃሚ ውይይቶች፣ ሥራዎች፣ ሌላም ሌላም ከፖሊሲ አውጭዎች፣ ከተመራማሪዎች፣ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አካላትና ከግሉ ዘርፍ ሁሉን አቀፍ ርብርብን ጠያቂ ነው።

ድምፅ ከ “ኢኮኖሚክስ”

 

የኢኮኖሚ ሀኪሞች፣ ኢኮኖሚስቶች አንድ ኪኒን ያዛሉ ፖሬቶ-ኦፕቲማሊቲ የተባለ አንድ ሰው ጥቅም ለማግኘት አስቦ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሌላውን ወገን ጥቅም ሳይጎዳ እንዴት ቢንቀሳቀስ እንደሚበጅ ሀሳብ የሚመግብ ጽንሰ ሀሳብ ነው። በጽንሰ ሀሳቡ ማህጸን ውስጥ ሌላ ሀሳብ ውልደትን ያገኛል- ተወላጅ ሀሳብ “ውጭአዊነት” /Externality/ ይሰኛል።

 

ውጭአዊነት አምራች ወይም ተጠቃሚ በማምረቱና በመጠቀሙ ለሌላ ወገን የሚያስገኘው ጥቅም ወይም በሌላ ወገን ላይ የሚያደርስበት ኪሳራን በተመለከተ የሚተርክ ነው። ነገሩን በሁለት ድርጅቶች መሀል የሚያጋጥም ይኽን መሰል ሁኔታ በአብነት ጠቅሰን እንየው። ሁለቱም የንግድ ተቋማት በወንዝ ዳር ይገኛሉ እንበል። አንደኛው ብረት የሚያመርት ሁለተኛው ከወንዙ ታች ሆኖ የሆቴል አገልግሎት የሚሰጥ ሪዞርት። የብረት ፋብሪካው ቧንቧ ዘርግቶ ንፁህ ውሃ በመሳብ ማቅለጫ ጋኖቹን ያጥብና እጣቢውን ወደ ወንዙ ይለቀዋል። ቅሪቱ ምርቱንም አያይዞ ይጥልበታል። ሪዞርቱ ግን ከወንዙ ዳር ከወንዙ ውሃ በሚመጣው አየርና የተፈጥሮውን ገፀ አቀማመጥ እያደነቁ ለሚዝናኑ ቱሪስቶች አገልግሎት ለመስጠት እክል ይጥልበታል።

 

የሁለቱም ድርጅት ባለቤት የተለያዩ ሰዎች ከሆኑ የፍላጎት ተቃርኖ መከሰቱ አይቀርም ወንዙ ለወደፊት ሊሰጥ የሚችለው በረከት ዕድሜው ያጥራል። በአሁኑ እይታ ደግሞ ባለ ሪዞርቱ ተጎጂ ይሆናል በዚህ እንቆቅልሽ ኢኮኖሚክስ ለመንግስት የሚያቀርበው የፖሊሲ መላ አለ?

 

ወጪ ቆጣቢ -‘መላ መጋቢ’ የብክለት ፖሊሲ

 

1.ብክለት ለቃቂ አካል የሚለቀው ብካይ ፈሳሽ ወይም ቁስ መጠን በሕግ የተወሰነ ማድረግ “የለቀቃ ደረጃ” /Emission standard/ ማውጣት አንደኛው የፖሊሲ መላ ነው።

ተቆጣጣሪው አካል የተለመደውን የሕግ አሰራር በመጠቀም በእያንዳንዱ የብካይ ምንጭ ላይ የተለያየ ልቀት መፍቀድ “ፍቀድና ተቆጣጠር” /Command and control/ አሰራር ሊተገብር ይችላል።

 

አንዳንድ የፖሊሲ መገልገያ ዘዴዎች ተቆጣጣሪዎች ብካይ ለቃቂው ድርጅት ብከላውን ለመከላከል የሚያወጣው ወጪ ምን ያህል እንደሆነ መረጃ ባይኖራቸውም እንኳ ወጪ ቆቢ የብከላ ብልሀት እንዲጠቀሙ ይፈቅዳሉ። ይኽ የፖሊሲ ውሳኔ ተፈላጊው ምርት ለገበያ እንዲቀርብ ኢኮኖሚያዊ ማበረታቻ ተደርጎ ይቆጠራል።

2. ለእያንዳንዱ የብክለት ዩኒት በመንግስት የሚሰበሰብ የብክለት ክፍያ /Emission charge/ መተግበር ነው። የተለቀቀው ዩኒት ብዛት በአንድ ዩኒት ክፍያ ዋጋ ተባዝቶ በሚገኘው ስሌት ክፍያው ሊፈፀም ይችላል። ክፍያው በድርጅት ባለቤቶች ላይ ወጪ ስለሚያበዛ የብክለት መጠን እንዲወርድ የሚያደርግ የፖሊሲ አማራጭ ነው- የብክለት ክፍያ ወይም /Emission charge/።

 

3.የግብይት ለቃቂ ሥርዓትን የሚፈቅደው ተሸጋጋሪ የለቀቃ ፍቃድ /Transferable emission permits/ ሌላው የፖሊሲ አማራጭ ነው። ይህን ያህል ዩኒት በአጠቃላይ በተገደበ ጊዜ (ገደቡ እንደ ሁኔታወ ሊሻሻል ይችላል) እንዲለቀቅ የሚፈቀድበት ብልሀት ነው። ስለሆነም ለእያንዳንዱ ተቋም በካይና ውሁድ ነገርን እንዲለቅ ተመጥኖ የሚሰጥ መብት ነው። ተቋማት በዚህ አድራጎታቸው ክፍያ አይጠየቁም። ተቆጣጣሪው አካል በሀገሪቱ ሊለቀቅ የሚገባውን የብክለት ጥቅል ዩኒት ይወስናል። ሲሆን ሲሆን ከተቀመጠው ዩኒት በታች ቢሆንለት መንግስት ይወዳል። ካልሆነ ግን ከተሰመረበት መጠን በላይ እንዳይሆን ይመክራል። ከገደቡ አልፎ የለቀቀ አካል ቢያጋጥም ከፍ ያለ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል።

 

ተሸጋጋሪ የግብይይት ለቀቃ የተሰኘው ድርጅቶቹ ለብክለት ለቀቃ ሊከፍሉ የሚችሉትን ገንዘብ ለመንግስት ከመክፈል ይልቅ ለራሳቸው ምርት ማበልፀጊያ ማስፋፊያ እንዲያውሉት የታለመ ሀሳብ በመሆኑ ነው።

 

መንግስት ከግሉ ዘርፍ፣ ከሲቪል ማህበረሰብና የምርምር ተቋማት ጋር ህብረት ፈጥሮ ሶስቱን ፖሊሲዎች አንዳቸውን ከሌላኛው ጋር በማቀላቀል ከክልልና የከተማ ነዋሪዎች ማህበረ ኢኮኖሚ ሁናቴ ጋር እያስማማ ቢሰራበት ጥቅም ይገኝበታል። እንዲህ ስናደርግ አረንጓዴ ኢንዱስትሪአዊት እራሱ “እኔ ቀላል የቤት ሥራ ነኝ” ማለቱ አይቀርም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1193 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 719 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us