የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና፤ የኢትዮጵያ ዕድሎችና ሥጋቶች

Wednesday, 28 March 2018 12:14

 

የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በቅርቡ በሩዋንዳ ኪጋሊ ባደረጉት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ 44 ሀገራት የነፃ ገበያ ቀጠናን ለማቋቋም ስምምነት ፈርመዋል። በአህጉሪቱ 54 ሀገራት የሚገኙ ሲሆን በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚን ያንቀሳቅሳሉ ተብለው ከሚጠቀሱት ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችውን ናይጄሪያን ጨምሮ አስር ሀገራት ስምምነቱን አልፈረሙም።


ኢትዮጵያም ስምምነቱን በመቀበል ፊርማዋን አኑራለች። ይሄው የአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጠና (African Continental Free Trade Area) ተብሎ የሚጠቀሰው አህጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ሥርዓት በዋነኝነት በሀገራት መካከል የተሳለጠ የንግድ ግንኙነት እንዳይኖር የሚያደርጉትን መሰናክሎች ያስወግዳል ተብሏል። በዚህም የፊርማው አካል የሆኑ ሀገራት በስምምነቱ መሰረት በገቢ በአፍሪካዊያኑ ሀገራት ገቢ ሸቀጦች ላይ የሚጥሏቸው ምንም አይነት የጉምሩክ ታሪፎች አይኖርም ማለት ነው። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስ የሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ከአስር በመቶ አይበልጥም።


የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ በአንፃሩ 25 በመቶ የደረሰ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ይህ ሰፊ የንግድ ቀጠና እውን የሚሆን ከሆነ ለ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን አፍሪካዊያን የተሻለ ህይወትና ብልፅግናን ያመጣል። ይህ የአሁኑ የአፈሪካዊያን የነፃ ገበያ ቀጠና በቀጣይ ህብረቱ ለመሄድ ያሰበባቸውን በርካታ መንገዶች አመላካች ነው ተብሏል። ከእነዚህም ቀጣይ ተግባራት መካከል አንዱ የህብረቱ አባል ሀገራት አንድ አይነት መገበያያ ገንዘብን እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው።


የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠናን ለማቋቋም 44 ሀገራት ፊርማቸውን ቢያኖሩም ስምምነቱን እውን በማድረጉ ረገድ ግን ከባድ ፈተናዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከእነዚህም ፈተናዎች መካከል አንዱ ሀገራቱን እርስ በእርስ የሚያገናኝ እንደ መንገድና ባቡር ያሉ መሰረተ ልማት አለመኖራቸው ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሀገራት ያላቸው የምርት አይነት ተመሳሳይነት የሚታይበት መሆኑ፣ እንደዚሁም ሀገራቱ ምርቶችን የሚያመርቱበት ሂደት ኋላቀር መሆኑ ሌላኛው ምክንያት የንግድ እንቅፋት ተደርጎ ይጠቀሳል። ምርቶቹ ከሌሎች ከአህጉሪቱ ውጪ ካሉ ሀገራት አንፃር ሲታይ በውድ የአመራረት ዘዴ መመረታቸው የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ ከማድረግ ይልቅ እንደ ቻይና እና ሌሎች መሰል ሀገራት ጋር የበለጠ የንግድ ትስስር እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይህም ሁኔታ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን ከመመስረቷ ቀደም ብሎ የአመራረት ቴክኖሎጂዋን ማሻሻል ይገባት ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ።


የጋራ ገበያን ለመፍጠር አህጉራዊ ትስስርን ለማምጣት የሚያስችሉ በርካታ የጋራ መሰረተ ልማቶች መገንባት ግድ ይላቸዋል። ሆኖም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህ የልማት ትስስር በአፍሪካ የለም። ይህንን ሁኔታ የተመለከቱ የኢኮኖሚ ተንታኞች የአሁኑ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን የጋራ የንግድ ቀጠና ሥምምነት “ከፈረሱ ጋሪው” የሚል ትችትን እንዲያቀርቡ እያደረጋቸው ነው።

ኢትዮጵያና የንግድ ሥምምነቱ ሁኔታ


ይህንን ግዙፍ ኢኮኖሚን የሚፈጥር ነፃ የአፍሪካ የንግድ ቀጠናን ለማቋቋም ፊርማቸውን ካስቀመጡት ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ ይህንን ፊርማዋን ስታስቀመጥ በእድልም በስጋትም የሚታይበት ሁኔታ አለ። እንደ መልካም እድል ተደርገው ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነፃውን ገበያ መቀላቀል በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሀብቶች ሰፊ የገበያ መዳረሻ እድልን የሚፈጥር መሆኑ ነው። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ይህ ከግብፅ ካይሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን የሚዘረጋው ሰፊና ግዙፍ ነፃ የንግድ ቀጠና 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሰዎችን በስሩ የሚያቀፍ በመሆኑ እጅግ ሰፊ የገበያ መዳረሻ የሚሆን ነው።


የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ዋና ፀሃፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ ይሄንን ሀሳብ ይጋራሉ። ሰፊ ገበያን መፍጠሩ ያንን ገበያ ለመጠቀም የሚፈልጉ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያበረታታ መሆኑን ይገልፃሉ። በዚህም በአፍሪካ ግዙፍ ገበያ መኖሩን ይጠቅሳሉ። ኢትዮጵያን በተመለከተም አቶ እንዳልካቸው የአምራች ኢንዱስትሪዋ ካለው ውስን አቅም አንፃር በተወዳዳሪነቱ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። ኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪውን የበለጠ ለማጠናከርና ተወዳዳሪ ለማድረግ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና መሰረተ ልማቶች እየገነባች መሆኑን የገለፁት አቶ እንዳልካቸው፤ በነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ግን በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በርካታ ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች መኖራቸውን ገልፀውልናል። ከዚህ አንፃርም አሁን በአፍሪካ ሀገራት መካከል የተደረሰውን ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት እንደ መልካም አጋጣሚም እንደዚሁም እንደ ስጋትም የሚያዩት መሆኑን ገልፀዋል። ሆኖም ሀገሪቱ እድሉን በአግባቡ መጠቀም የምትችልበትን አሰራር መፍጠር ከቻለች ግን ከስጋቱ ይልቅ መልካም አጋጣሚው የሚያመዝን መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ጨምረው አመልክተዋል። የንግድ ሚኒስትሩ ዶክተር በቀለ ቡላዶ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የዚህ ነፃ የንግድ ቀጠና አባል ለመሆን የሚያስችሏት ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።


አንደኛው ኢኮኖሚያዊ ሲሆን ሌላኛው ፖለቲካዊ ነው። ኢኮኖሚያው አቅጣጫ የገበያ እድሉ ማስፋት መቻሉና አፍሪካም የተሻለ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ ሲሆን ፖለቲካዊ አቅጣጫው ደግሞ ኢትዮጵያ በህብረቱ ውስጥ ካላት ሚና አንፃር የሚታይ ነው። ዶክተር በቀለ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መስራችና ፣የህብረቱ ዋና ፅህፈት ቤት መቀመጫ በመሆኗ አርባ አራት ሀገራት ፊርማቸውን ካስቀመጡበት ስምምነት ውጪ መሆን እንደሌለባት ያለውን ፖለቲካዊ አንድምታ በማሳየት የመንግስትን ውሳኔ ትክክለኛነት አመላክተዋል። ሆኖም ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖውን በተመለከተም ኢትዮጵያ በፊርማው ማግስት ገበያዋን ክፍት ለማድረግ የማጥሯሯጥ በመሆኑ ሥጋት ሊኖር የማይገባ መሆኑን ነው የገለፁት።


ሚኒስትሩ “እኛ ስምምነቱን ስለፈረምን በቀጣዩ ዓመት ገበያውን ከፈትን ማለት አይደለም። እኛ በየዓመቱ እንከፍታለን ብለን አልፈረምንም። ሌሎች ሀገራት ግን በየዓመቱ አስር በመቶ ገበያቸውን ለመክፈት ተስማምተዋል። እኛ ግን በፈለግን ጊዜ ነው ገበያችንን የምንከፍተው።” በማለት እየተነሳ ያለውን ቀለል አድርገውታል።


ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ለዚሁ ነፃ የንግድ ገበያ የሚከፈቱ፣ በሂደት እየተከፈቱ የሚሄዱና ጭራሽኑ ሊከፈቱ የማይችሉ በማለት ሊይታ አስቀመጣለች። ሆኖም እነዚህ በሶስት የተከፈሉ የገበያ ዘርፎች በዝርዝር ተቀምጠው ግልፅ የተደረጉበት ሁኔታ የለም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
86 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1037 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us