ቻይና ከአሜሪካ ጋር የገባችበት የንግድ ውዝግብ እንዲበርድ እያደረገች ነው

Wednesday, 11 April 2018 14:05


ቻይና እና አሜሪካ የገቡበትን የንግድ እሰጣ ገባ ተከትሎ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ፒ ግ ውጥረቱን ሊያረግብ የሚችል ንግግር አደረጉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ በዚያው በቻይና እየተካሄደ ባለው የቢዝነስ ኮንፍረንስ ላይ እንደገለፁት፤ ቻይና ኢኮኖሚዋን የበለጠ ክፍት በማድረግ ከቀሪው ዓለም ጋር በጋራ የምትሰራ መሆኗን አሰታውቀዋል፡፡ “ቻይና ለበርካታ ዓለም አቀፍ የንግድ ህጎች አትገዛም፣ቴክኖሎጂዎችን የባለቤትነት መብትን ሳታከብር አባዝታ ለገበያ ታውላለች፣ ገበያዋን በተገቢው መንገድ ክፍት አታደርግም” በሚልና በመሳሰሉት በአሜሪካ በኩል ክስ ሲቀርብባት ቆይቷል፡፡ ይህ ውዝግብ ተካሮ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በወሰዱት እርምጃ በበርካታ የቻይና ምርቶች ላይ የገቢ ምርት ታሪፍ እስከመጣል መድረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡

 

ቻይናም በአሜሪካ ገቢ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ እርምጃዎችን በመውሰድ ውጥረቱ የበለጠ እንዲባባስ እስከማድረግ ደርሳ ነበር፡፡ ሆኖም ከሰሞኑ ፕሬዝዳንቱ ያደረጉት ንግግር ቻይና በያዘችው አቋም እንደማጥቀጥል የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡ እንደ ኤቢሲ ኒውስ ዘገባ ከሆነ፤ ፕሬዝዳንቱ “ቻይና በሯን አትዘጋም እንደውም የበለጠ እያሰፋች ትሄዳለች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የቻይና እና የአሜሪካ የንግድ ውዝግብ የበለጠ ውጥረት ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ቻይና በውጭ ተሽከርካሪዎች ላይ የያዘችው ጠንካራ አቋም ነው፡፡


ሀገሪቱ የውጭ ባለሀብቶች ከቻይና መኪና አምራች ኩባንያዎች ጋር በሽርክና እንዳይሰሩ ብዙም ፍላጎት የሌላት ከመሆኑም ባሻገር በገቢ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለችው ታሪፍም ቢሆን ሌላኛው የአለመግባባቱ መንስኤ ነው፡፡ በዚህም የቻይና መንግስት በሁለቱም አቅጣጫዎች ይዟቸው የነበሩትን አቋሞች የቀየረ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ ትራምፕ ከቀደሙት አስተዳደሮች በተለየ ሁኔታ በቻይና የንግድ ግንኙነት ላይ በወሰዱት እርምጃ እስከ 50 ቢሊዮን በሚደርሱ የቻይና ልዩ ልዩ ሸቀጦች ላይ ታሪፍ እንዲጣል ማድረጋቸውን ተከትሎ ቻይናም አፀፋዊ እርምጃን ውስዳለች፡፡


ሆኖም ይህ የሁለቱ ግዙፍ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሀገራት እርምጃ በሁለቱንም ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖን እንደሚያሳድር የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ቻይና ውዝግቡን የበለጠ ከማጦዝ ይልቅ ነገሩን እያቀለሉ መሄዱን የመረጠች መሆኑን የኤቢሲ ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ውዝግብ በአለም አቀፉ የንግድ እንቅስቃሴም ላይ የራሱን የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖን በማሳደር ላይ ነው፡፡ ውዝግቡ እየተካረረ መሄዱን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ እንደዚሁም የአክስዮን ገበያዎች የመቀነስ ሁኔታ ታይቶባቸው ነበር፡፡ ሆኖም ከፕሬዝዳንቱ ንግግር በኋላ በተፈጠሩት ተስፋዎች በሁለቱም ገበያዎች የመረጋጋት አዝማሚያ መታየቱን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
303 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 155 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us