ከራስ ያለፈ በጎ ተግባር

Wednesday, 18 April 2018 12:50

 

በኢትዮጵያ ትምህርትን ለማዳረስ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎች መሰራታቸው ቢታወቅም ከትምህርት ጥራት አኳያ ግን አሁንም በርካታ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን የሚያመላክቱ ብዙ ማሳያዎች አሉ። የትምህርት ጥራት ለመማር ማስተማር ከሚያስፈልጉ ቁሳዊ ግብዓቶች ጀምሮ እስከ መሰረተ ልማቶችና ሰብዓዊ ሀብትን ጭምር አጠቃሎ የያዘ ነው። ከሶስቱ የአንዱ መጓደል በትምህርት ጥራት ላይ የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ ነው።

 

እኛም ከሰሞኑ በአዲስ አበባና በዱከም መካከል በምትገኝና አቃቂ ወረዳ ተብላ በምትጠራ የሚገኝን ኦዳ ነቤ የተባለ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በጎበኘንበት ወቅት የተመለከትነው ይህንን እውነታ ነው። የትምህርት ቤቱ ግንባታ የተከናወነው በ1997 ዓ.ም መሆኑን ከመምህራኑ ገለፃ መረዳት ችለናል።

 

አሁን ባለው ሁኔታ ትምህርት ቤቱ በቂ መማሪያ ክፍሎች የሉትም። የተገነባው በእንጨትና በጭቃ ሲሆን አንዳንዶቹ ክፍሎች የቆይታ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ይመስላል። የጭቃ ምርጊታቸው እየረገፈ ነው። የመዝመምና የመውደቅ አዝማሚያም ይታይባቸዋል። አንዳንዶቹ ክፍሎች እንደውም መጪውን ክረምት የሚሻገሩ አይመስሉም። በአካባቢው መብራትና ውሃ የማይታሰብ ነው። በቂ አጥርም የለውም።

 

ከትምህርት ቤቱ ግንባታ ከደረጃ በታች መሆን ባሻገር በውስጡም ቢሆን በቂ የማስተማሪያ ቁሳቁሶችንና ሌሎች ተጓዳኝ ግብዓቶችን ያሟላ አይደለም። የተማሪዎች ቤተመፃህፍት የለውም። ቤተሙከራ የማይታሰብ ነው። እንኳን ሌላ የተማሪዎች መቀመጫና ወንበር እንኳን በበቂ ሁኔታ የተሟላበት ሁኔታ የለም። የመምህራን ማረፊያ ክፍልንም በበቂ ሁኔታ ያሟላ አይደለም።

 

ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ሰዓት በሁለት ፈረቃ በጠቅላላው 360 ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑን ከመምህራኑ ገለፃ መረዳት ችለናል። ተማሪዎቹ የትምህርት አገልግሎቱን የሚያገኙት ከአንደኛ እስከ አራተኛ በመጀመሪያ ፈረቃ፤ ከዚያም ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ በሁለተኛው ፈረቃ ነው። ይህ እንዲሆን የተደረገው በቂ መማሪያ ክፍል እንደዚሁም መምህራን ባለመኖራቸው ነው። ተማሪዎቹ ከቀያቸው ወደ ትምህርት ቤቱ ለመድረስ በቀን እስከ ሁለት ሰዓት በእግራቸው መጓዝ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ከተደረገልን ገለፃ መረዳት ችለናል።

 

ይህ ትምህርት ቤቱ አሁን ያለበትን ደረጃ ለመለወጥ አንድ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ምሁር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተመልክተናል። ምሁሩ ዶክተር ገዛኸኝ ሆርዶፋ ይባላሉ። ተውልደው ያደጉትና የልጅነት የትምህርት ጊዜያቸውን ያሳለፉት በዚያው ትምህር ቤቱ በሚገኝበት ኦዳ ነቤ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ሲሆን በጊዜው ከቀበሌው እስከ ዱከም ብሎም እስከ ደብረ ዘይት በእግራቸው በመጓዝ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩ መሆኑን ነግራውናል። ዶክተር ገዛኸኝ በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ስኮላርሺፕ አግኝተውተምረዋል። ከዚያም በሥራው ዓለም በተባበሩት መንግስታት የበጎ ፈቃደኛ ሰራተኛ ሆነው ስደተኞችን በልዩ ልዩ ድጋፎች ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ይህም አጋጣሚ በርካታ ሀገራትን የመመልከት እድሉን ፈጥሮላቸዋል። በአሁኑ ሰዓትም ነዋሪነታቸው በካናዳ ነው።

 

ዶክተር ገዛኸኝ በሥራቸው መሃል ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም ለቤተሰባቸው ብሎም ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ እገዛዎችን ያደርጉ ነበር። ከእገዛዎቹም መካከል የታመሙ ሰዎችን ማሳከምና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በተለያዩ ጊዜያትም በርከት ያሉ የአካባቢው ሰዎች በራሳቸው ወጪ ህክምና እንዲያገኙ ያደረጉ መሆኑን ከእሳቸው ገለፃ መረዳት ችለናል።

 

በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ጉዳት ላይ የሚገኘውን የኦዳ ነቤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትንም በራሳቸው ወጪ በማገዝ ላይ ናቸው። ቀደም ባሉት ጊዜያት ትምህርት ቤቱ የብረት መቀመጫ ዴስኮች እንዲኖረው አድርገዋል። ባሳለፍነው ቅዳሜም በቦታው በመገኘት ማልያና ታኬታ ጫማዎችን ባካተተ መልኩ የስፖርት ትጥቆችን፣ ኳሶችን፣ እንደዚሁም አጋዥ መፃህፍትን በልገሳ መልክ አበርክተዋል። በቀጣይም ለትምህርት ቤቱ የቤተ መፅሐፍት ህንፃን፣ ጤና ጣቢያን እና የውሃ ጉድጓድን ለማስቆፈር ከአካባቢው የስራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ በመሆን የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል። በተቀመጠውም የፕሮጀክት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንባታዎቹ በሶስት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል። ዶክተር ገዛኸኝ እንደ አካባቢው ተወላጅነታቸው የበጎ አድራጎት ሥራውን እያከናወኑ ያሉት በግላቸው ወጪ መሆኑን ገልፀው፤ ዋና አላማውም ለመሰል የልማት እገዛ በሌሎች አስተሳሰብ ውስጥ ተነሳሽነት እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ዶክተር ገዛኸኝ ሌሎች በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በቻሉት ሁሉ መሰል እገዛን ቢያደርጉ ለሀገር ልማት በተለይም ለትምህርት ጥራት የራሳቸውን አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ መሆኑን በመግለፅ ጥሪያቸውንም አስተላለፈዋል።

 

በወረዳው ባሉ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡን የወረዳው የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጫላ ዳዲ በአቃቂ ወረዳ በአጠቃላይ 53 ትምህርት ቤቶች ያሉ መሆኑን ነግረውናል። ትምህርትን በማዳረሱ ረገድ አሁን ያሉት 53 ትምህርት ቤቶች የተደረሰውም ከሰባት ትምህርት ቤቶች በመነሳት ነው። ሆኖም ትምህርት ከማዳረስ ባሻገር በትምህርት ጥራት ደረጃ በአካባቢው ብዙ የሚቀር ነገር መኖሩን አቶ ጫላ አመልክተዋል። እንደሳቸው ገለፃ በወረዳው ካሉት 53 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተገቢውን የጥራት ደረጃ የሚያሟሉት አራቱ ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው። ኦዳ ነቤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ቀሪዎቹ 49 ትምህርት ቤቶች ከጥራት አኳያ ሲታዩ ከደረጃ በታች ናቸው።

 

የህዝብ ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፤ በዚህ ረገድ ወረዳው ሊሰራቸው ካሰባቸው ስራዎች መካከልም አንዱ ዲያስፖራውን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የድጋፍ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥረት ማድረግ ነው።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
237 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1027 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us