የግዙፉ ቻይናዊ ኩባንያ አንድ እግር በኢትዮጵያ

Wednesday, 02 May 2018 12:27

 

ባለፈው ቅዳሜ ሎንቶ በመባል የሚታወቅ አንድ የቻይና ኩባንያ የሹራብ ፋብሪካን በዱከም ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን አስመርቋል። የኩባንያው አጠቃላይ የኢንቨስትመንት መጠን 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን አሁን ባለበት ደረጃም በዓመት አምርቶ ወደ ውጭ የሚልከው የሹራብ ብዛት ግማሽ ሚሊዮን መሆኑ ተመለክቷል። ኩባንያው ከመነሻው የራሱ የሆኑ የገበያ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን አሁን በኢትዮጵያ የሚያመርታቸው የሹራብ ምርቶችም ወደ እነዚሁ አለም አቀፍ መዳረሻዎች የሚገቡ መሆኑ ታውቋል። የምርቶቹ መዳረሻ ሀገራት ናቸው ከተባሉት ሀገራት መካከልም ጣሊያን፣ ፖላንድ፣ ራሺያ፣ ብራዚልና የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል። ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት ለ4 መቶ ሰራተኞች የሥራ ዕድል የከፈተ ሲሆን ይህ ቁጥር ከኩባንያው የኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር በተያያዘ በቅርቡ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ቁጥር ወደ አንድ ሺህ ያድጋል ተብሏል።

 

የግዙፉ ኩባንያ ቅምሻ

ይህ ሎንቶ ጋርመንት ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በሌላ አንድ ግዙፍ የቻይና ኩባንያ ሥር የሚገኝ ድርጅት ነው። ዋናው ቻይናዊ ኩባንያ ሻንጋይ ድራጎን ኮርፖሬሽን በመባል የሚታወቅ ነው። ሻንጋይ ድራጎን ኮርፖሬሽን በራሱ በሌላኛው ሻንቴክስ ተብሎ በሚጠራው ግዙፍ ቻይናዊ ኩባንያ ሥር የሚገኝ ነው። ሻንቴክስ ኩባንያ በስሩ ከስድስት መቶ በላይ ኩባንያዎችን የያዘ ሲሆን ከፋይናንሱ ዘርፍ ጀምሮ እስከ ሪልስቴት ባሉት በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ ተሰማርቶ ይገኛል። የሎንቶ ጋርመንት ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባት ግዙፉን የቻይና ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት መንገድ ጠራጊ ነው ተብሏል። ሎንቶ ጋርመንት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውጤታማ የሚሆን ከሆነ በዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማራው ሻንቴክስ ኩባንያ በቀጣይ ወደኢትዮጵያ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ይህ ኩባንያ በቻይና ካሉት አንድ መቶ ምርጥ ኤክስፖርተሮች መካከል አንዱ ሲሆን በ27 ሀገራት የማምረቻ ፋብሪካዎችን የተከለ፤ እንደዚሁም ከአንድ መቶ ሀገራት ጋር የንግድ ግንኙነትን የፈጠረ መሆኑ ታውቋል። ከንግድ ግንኙነት አንፃር ሲታይ በአፍሪካ እንደ ደቡብ አፍሪካና ግብፅን ከመሰሉ ሀገራት ጋር ጠንካራ የንግድ ግንኙነትን የመሰረተ ሲሆን የማምረቻ ኩባንያን በመገንባቱ ረገድ ግን ይህ በየኢትዮጵያ የተገነባው ጨርቃጨርቅ ኩባንያ በአፍሪካ የመጀመሪያው መሆኑ ታውቋል።

 

ይሄው ሎንቶ ጋርመንት በመባል የሚታወቀው ቻይናዊ የጨርቃጨርቅ ኩባንያ ከህዳር ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወራት ያህል ኩባንያው በኢንዱስትሪ ዞኑ ውስጥ በተረከበው ሼድ ውስጥ ወደ ማምረት ሥራው ሊያስገቡት የሚያስችሉትን ቅድመ ሥራዎች ሲሰራ ከቆየ በኋላ ሥራው በወራት ጊዜ ውሰጥ ወደ ምርት ሥራው ገብቷል። ቀደም ባለው አሰር ቢሆን ኖሩ ከኩባንያው የኢንቨስመንት ፈቃድን ለማውጣት ረዘም ያለ ጊዜን መውስድ ይጠበቅበት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የኢንቨስትመንት መሬቱንም ለማግኘት ሌላኛው ፈተና ነበር።ከመሬቱ ማግኘት ባሻገር እንደ ኤሌክትሪክና ውሃ ያሉ መሰረተ ልማቶችን የተሟሉ ለማድረግ ከባድ ፈተናን የሚጠይቅበት ሁኔታ ነበር። እነዚህ ሁሉ ውጣ ውረዶች ሲደማመሩ አንድ ባለሀብት ከኢንቨስትመንት ፈቃድ እስከ ምርት ለመድረስ ረዥም ጊዜያትን የሚወስድበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መገንባት ኢንቨስተሮች ለመሰል ቅድመ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ሳይጨነቁ ማሽኖቻቸውን ብቻ አስገብተው ሰራተኛ በማሰልጠን በቀጥታ ወደ ሥራ እንዲገቡ አስችሏቸዋል።

 

ሎንቶ ጋርመንትም ከአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት ሥራ እንዲገባ ያደረገው በቀጥታ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በመግባቱ ነው። የሽመና፣ የማጠቢያ፣የመተኮሻ፣ የሰራተኞች መመገቢያ፣ የቢሮና ሌሎች ክፍሎችን የመከፋልና የማሽን ተከላ ሥራው የተከናወነው ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው። የሰራተኛ ስልጠናም ጭምር የተከናወነው በዚሁ አጭር ጊዜ ውስጥ ነው።

 

ኩባንያው አሁን በዱከም ኢስት ኢንዱስትሪ ዞን ካለው ኢንቨስትመንት በተጨማሪ በኮምቦልቻም አራት ሄክተር መሬትን ወስዶ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል። በተረከበው አካባቢ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋነኛ ዓላማ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ራዕይ እውን እንዲሆን ማድረግ ብሎም የኤክስፖርቱን አቅም ማሳደግ ነው።

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባለሀብቶቹ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሲመቻችላቸው እነሱም በበኩላቸው የሚወጧቸው ግዴታዎችም አሉ። ከእነዚህ ግዴታዎች መካከልም በፓርኩ ውስጥ የሚመረቱ ምርቶቻቸውን በሙሉ ለኤክስፖርት ገበያ ማቅረብ ነው። ይህም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርገው ይሆናል። መንግስት ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ሲያደርግ በርካታ ማበረታቻዎችን አድርጎ ነው። ሆኖም ኤክስፖርቱ ገበያ ለምርታማነት ከሚደረገው ድጋፍ ባሻገር ሌሎች ተጨማሪ የተሳለጡ ሥራዎችን ጭምር የሚጠይቅ ነው። ይህ ሥራ በአጭሩ ሎጂስቲክስ ተብሎ የሚጠራ ነው።

 

ይህም የምርቱ ጥሬ እቃ ሀገር ውስጥ ከሚገባበት ሂደት ጀምሮ ከተመረተ በኋላም ለዓለም አቀፉ ገበያ እስከሚደርስበት ድረስ ያለው የቢሮክራሲ ሰንሰለት ነው። በዚህ ረገድ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የጉምሩክ ክሊራንስ፣ የብሄራዊ ባንክ ሥራና የመሳሰሉት በዋነኝነት የሚጠቀሱ የሎጂስቲክሱ አካላት ናቸው። የዚህ ሂደት ቀልጣፋና የተቀናጀ አለመሆን አምራች ባለሀብቱን የሚያማርር ከመሆኑም ባሻገር ሀገሪቱንም የውጭ ምንዛሪን እንዳታገኝ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ።

 

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ዶክተር በላቸው መኩሪያ በዚህ ዘርፍ ያለው የተንዛዛ አሰራር ባለሀብቶች ያመረቷቸውን ምርቶች ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብን እንዲመርጡ የሚያደርጋቸው መሆኑን አመልክተዋል። ይህንንም ችግር ለማቃለልና ለመፍታትም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ላሉ ባለሀብቶች የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በመስጠት በዋነኛ መፍትሄነት እየተሰራበት መሆኑን ዶክተር በላቸው ጨምረው አመልክተዋል።

 

ይህም የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሀብቶች ከጉምሩክ የክሊራንስ አገልግሎት ጀምሮ እስከባንክና የትራንስፖርት አገልግሎት ድረስ የሚሰሩት ሥራዎችን በዚያው በፓርኩ ባሉ ማዕከላት ብቻ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። እንደ ዶክተር በላቸው ገለፃ ለምሳሌ የጉምሩክ ክሊራንስን በተመለከተ በአንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያለ አምራች ኩባንያ ከውጭ እቃን ሲያስገባ ከወደብ ጀምሮ ፓርኩ እስኪገባ ድረስ መንገድ ላይ በተደጋጋሚ ፍተሻ ጊዜውን እንዲያጠፋ የሚደረግበት ሁኔታ አይኖርም። የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎትን በተመለከተ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ወደ ሥራ በመግባቱ ቀደም ሲል በተሽከርካሪዎች በኩል የነበረውን የተንዛዛ አሰራር በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ተብሏል።

 

ከመሰል የተንዛዙ አሰራሮች ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶች ወደ ዓለም አቀፉ ገበያ ከገቡ በኋላ በበቂ ሁኔታ መወዳደር እንዳይችሉ የሚያደርግበት ሁኔታ ሲኖር፤ አሁን ከሎጂስቲክስ እስከ አንድ መስኮት እየተሰጠ ያለው አገልግሎት የአምራቾችን የማምረቻ ዋጋ በመቀነስ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ በዋጋቸው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል ተብሏል። እንደ ዶክተር በላቸው ገለፃ ወጪ ምርቶችንና የምርት ግብዓቶችን በማጓጓዙ በኩል ከባቡሩ ባሻገር የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። አየር መንገዱ ለዚሁ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚውል አቅሙን በመገንባት በአሁኑ ሰዓት ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ ሸቀጠን ማከማቸት የሚያስለው አቅም ላይ የደረሰ መሆኑን ዶክተር መኩሪያ ጨምረው አመልክተዋል፡

 

የፍተሻና ሌሎች የጉምሩክ ሥራዎች የሚከናወኑት በኢንዱስትሪ ፓርኩ የጉምሩክ ማዕከል ውስጥ ብቻ ነው። የኢንቨስትመንቱንም ውጤታማነት የበለጠ ለማቀላጠፍ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ሎጂስቲክስ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ዶክተር በላቸው አመልክተዋል።

    

ግዙፉ ኢስተርን ኢንዱስትሪያል ዞን

ሎቶ ጋርመንት የሚገኝበት የዱከሙ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ዞን ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን በመባል ይታወቃል። ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የኢንዱስትሪ ዞን ሲሆን በስሩም በርካታ የቻይና ኩባንያዎችን እያስተናገደ ይገኛል። በዚሁ አንዱስትሪ ዞን ውስጥ ካሉት የቻይና አምራች ኩባንያዎች መካከል ሁጁዋን ሹ በመባል የሚታወቀው ግዙፉ የቻይና ጫማ አምራች ኩባንያ እንደዚሁም ሊፋን ሞተርስ ይገኙበታል። የዚህ ኢንዱስትሪ ዞን እውን መሆን የበርካታ ቻይናዊያንን ባለሀብቶች ትኩረት ኢትዮጵያ ላይ እንዲያርፍ አስችሏል። ኢንዱስትሪ ዞኑ ወደ 13   ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞችን በውስጡ ይዟል። 125 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልም ተፈቅዶለታል።

 

እስከአሁን ባለው ሂደት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ ያለው መንግስት ሲሆን ባለሀብቶች ወደዘርፉ እንዲገቡ መንግስት ከየትኛው ዘርፍ በተለየ ሁኔታ ለዚህ ዘርፍ ልዩ ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል። እንደ ዶክተር በላቸው ገለፃ ከመንግስት ለዘርፉ ከሚሰጡት ማበረታቻዎች መካከል አንደኛው የግብር የእፎይታ ጊዜ ሲሆን ለዚህ ዘርፍ የሚሰጠው የግብር የእፎይታ ጊዜ 15 ዓመት ነው። ይህ የእፎይታ ጊዜ እንዲረዝም የተደረገባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ።

 

ከእነዚህም ምክንያቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ኢንዱስትሪ ፓርክን መገንባት ከፍተኛ ካፒታልን የሚወስድ በመሆኑ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሀብቶች ወደ ትርፍ ለመግባት በርካታ ዓመታትን የሚወስድባቸው መሆኑ ነው። ይህንንም ጊዜ ለማሳጠር መንግስት የታክስ የእፎይታ ጊዜውን ረዘም ያለ ዓመት እንዲሆን ያደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ አመልክተዋል። በኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ ለሚሰማራ ባለሀብት የተመቻቸለት የማበረታቻ ድጋፍ ይህ ብቻ አይደለም። ባለሀብቶች መሬት በነፃና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገኙ ይደረጋል። በአሁኑ ሰዓት በመቀሌ፣ በኮምቦልቻ፣ በአረርቲና በመሳሰሉት አካባቢዎች የግል ባለሀብቶች የራሳቸውን የኢንዱስትሪ ፓርክ የገነቡበት ሁኔታ መኖሩ ታውቋል።

 

ከዚህም በተጨማሪ መንግስት በራሱ ለተያዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያቀርባቸውን የመሰረተ ልማትና የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችንም በራሱ ወጪ በግል ለሚገነቡት ፓርኮች እንዲቀርብላቸው ያደርጋል። ይህም አንዱ ሀገሪቱን የማስተዋወቂያ መንገድ ነው ተብሏል። ዶክተር በላቸው፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሀገሪቱ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እያደረገ ባለው ጥረትም “በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ የኢንቭስትመንት ፕሮሞሽን ኤጀንሲ” በሚል በያዝነው ዓመት በዱባይ በተካሄደ የሽልማት ሥነስርዓት ኮሚሽኑ ተሸላሚ እንደነበር አስታውሰዋል።

የሰራተኞች ደመወዝ ጉዳይ

በሎንቶ ጋርመንት 4 መቶ የሚሆኑ ሰራተኞች መኖራቸው ተመልክቷል። ሰራተኞቹን ተዘዋውረን በመጠየቅ በሰበሰብነው መረጃ መሰረት በምርት ስራ ላይ ያሉ ሰራተኞች የሚከፈላቸው ወርሃዊ የደመወዝ መጠን ከአንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር ይደርሳል።

 

“ይህ የደመወዝ መጠን አሁን ካለው የኑሮ አንፃር እንዴት ይታያል?” የሚል ጥያቄን ለዶክተር በላቸው አንስተን ነበር። ዶክተር በላቸው ለዚህ ጥያቄ በሰጡን ምላሽ፤ ሀገሪቱ የሰለጠነ የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ የሌላት መሆኑን ገልፀው ባለሀብቶች የሚቀጥሯቸውን ሰራተኞች ለማሰልጠን ብዙ ገንዘብ ወጪ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልፀውልናል። ከዚህም በተጨማሪ ሰራተኞች የትራንስፖርት ሰርቪስን በነፃ የሚያገኙበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀው፤ ነፃ የምሳ አገልግሎትንም የሚያገኙት ሁኔታ መኖሩንም አመልክተዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ኢንቨስትመንቱ ወራትን ያስቆጠረ በመሆኑ የደመወዙን ሁኔታ ለመነጋገር ጊዜ መሆኑን ገልፀውልናል።

 

የሰራተኞቹ ክህሎትና ምርታማነት እያደገና እየዳበረ ሲመጣም የደመወዝ ማስተካከያም የሚኖርበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀውልናል። ከቀጥተኛው ክፍያ ይልቅ ሰራተኞች ከሚያገኙት ነፃ የምሳና የትራንስፖርት አገልግሎት ባሻገር በቀጣይ በዚያው በየፓርኮቹ ውስጥ ሰራተኞች በቅናሽ ዋጋ መሰረታዊ ሸቀጦችን የሚያገኙበት አሰራር የሚተገበርበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀውልናል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
636 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 906 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us