ኢትዮጵያ፤ “የቻይና የአፍሪካ በር?”

Wednesday, 09 May 2018 13:13

 

ባሳለፍነው ሳምንት የቻይና የንግድ ሳምንት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። ይህ የቻይና የንግድ ሳምንት የተካሄደው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በርካታ የቻይና ባለሀብቶች ተሳታፊ ሆነውበታል። ቻይና በኢትዮጵያ በብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተሳታፊ የሆነች ሀገር ናት። ቻይና በኢትዮጵያ ባላት ሰፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በርካቶች “ኢትዮጵያ የቻይና የአፍሪካ መግቢያ በር ናት” ይሏታል። ይህ ሁኔታ ለአሜሪካ ጭምር ሥጋትን በመፍጠር አሜሪካ ፊቷን ወደ አፍሪካ እንድታዞር ምክንያት ሆኗል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። ፕሬዝዳንቱ በጊዜው ሁለት ጉዳዮችን በመሰረታዊነት ያነሱበት ሁኔታ ነበር።

 

የመጀመሪያው አፍሪካን ከመርዳት ይልቅ በአፍሪካ መዋዕለ ነዋይን ማፍሰስ መሰረት ያደረገ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአፍረካ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንዲስፋፉ በተለያየ መልኩ የእገዛ ሥራን መስራት ነው። በወቅቱም ከዚሁ ጋር በተያያዘ አፍሪካን በኢነርጂ ኢንቨስትመንት ለማገዝ ፓወር አፍሪካ በመባል የሚታወቀው የአሜሪካ ኢኒሼቲቭ ይፋ የሆነበት ሁኔታ ነበር። አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ትከተል የነበረውን የቆየ አቋም እንድትለውጥ ምክንያት የሆነው የቻይና በአፍሪካ ምድር በስፋት ሥር እየሰደደ የመሄድ ጉዳይ ነው።

 

ሆኖም “አሜሪካ ትቅደም” (America First) የሚለው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መርህ በቀድሞው ፕሬዝዳት ኦባማ የስልጣን ዘመን መጨረሻ የነበረውን ለአፍሪካ ትኩረት የመስጠት አካሄድ ባለበት እንዲቆም አድርጎታል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለአፍሪካዊያን ያላቸው አመለካከት የተዛባ መሆኑን መላ አፍሪካዊያንን በአንድ ወቅት በመዝለፍ አሳይተዋል። ይህም ሁኔታ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የስልጣን ዘመን አሜሪካ በአፍሪካ ምድር የቻይና ተወዳዳሪ ሆና የምትሰራበት ሁኔታ እንደማይኖር ግልፅ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

 

ቻይና በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ያላት ኢኮኖሚያዊ ሚና በብዙ መልኩ ሊገለፅ የሚችል ነው። በአፍሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ አንዱ የቻይና ተፅዕኖ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰደው ሀገሪቱ ለአፍሪካ ሀገራት የምትለቀው ከፍተኛ መጠን ያለው የብድር ገንዘብ ነው። ሀገራት ባላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ከሌሎች ሀገራት እንደዚሁም ከአበዳሪ ዓለም አቀፍ ተቋማት የብድር ገንዘብ ሊያገኙ ይችላሉ።

 

እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ አይነቶቹ አበዳሪዎች ለአፍሪካዊያኑ ሀገራት የብድር ገንዘብን ለመልቀቅ የሚያስቀምጧቸው መመዘኛዎች ውስብስብ ናቸው በሚል ይተቻሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የድርጅቶቹን የብድር ገንዘብ ተጠቅመው የልማት ሥራቸውን ለማከናወን የቻሉት የአፍሪካ ሀገራት ውስን ናቸው። ሆኖም ቻይና ወደ አፍረካ አህጉር በሰፊው መግባቷ በብድር አቅርቦቱ በኩል ቀላል አማራጭ ሆና እንድትታይ አድርጓታል። እንደ ኤይድ ዳታ ፕሮጀክት መረጃ ከሆነ ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት ከ 2000 እስከ 2014 ባሉት ዓመታት የለቀቀችው አጠቃላይ የብድር መጠን 86 ቢሊዮን ዶለር ነው። የብድሩ መጠን ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታትም እየጨመረ ሄዷል።

 

ይህም የብድር መጠን በዓመት ሲሰላ ሀገሪቱ ለአፍሪካ ሀገራት በአማካይ 6 ቢሊዮን ዶላር ትለቃለች ማለት ነው። ቻይና ከፍተኛ ብድር ከምትሰጣቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ናት። ቻይና ለኢትዮጵያ የምትለቀው ብድር በአብዛኛው ከፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ነው። ቻይና ለኢትዮጵያ የለቀቀቸው የብድር መጠን መንገድን፣ የኤሌትሪክ ኃይልን፣ ባቡርን እና ከመሳሰሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዘ ነው።

 

አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡሩ ግንባታ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ ቻይና ናት። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት 475 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የጠየቀ መሆኑን መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆኑ ከዚህም አጠቃላይ ወጪ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ከቻይና የተገኘ ነው። በአሁኑ ሰዓት በግንባታ ላይ ያለው የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ተርሚናል ማስፋፋያ ፕሮጀክት 345 ሚሊዮን ዶላር የጠየቀ ሲሆን የዚህ ፕሮጀክት ወጪ የተሸፈነው የቻይናው ኤግዚም ባንክ በብድር መልኩ በለቀቀው ገንዘብ ነው።

 

በሀገሪቱ የመንገድ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው የአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ 8 ቢሊዮን ብርን ወጪ የጠየቀ ሲሆን ከዚህም አጠቃላይ ወጪ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነውን የወጪ መጠን የተሸፈነው የቻይናው ኤግዚም ባንክ በብድር መልኩ በለቀቀው ገንዘብ ነው። ቻይና በኢትዮጵያ የፋይናስ ፍሰት ውስጥ ያላት ሚና እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ይታያል። አንዳንዶች እንደውም ኢትዮጵያ ለቻይና የአፍሪካ መገቢያ በር (Gateway to Africa) ሆና እያገለገለች መሆኗን ማሳያ ነው ይሉታል።

 

ቻይና በኢትዮጵያ ከብድር ባለፈ በቀጥታ ኢንቨስትመንት ያላት ድርሻም ከፍተኛ ነው። የኢንቨስትመንት ፍስቱ ከተናጠል የባለሀብቶች እንቅስቃሴ ባለፈ በቻይናዊያን የኢንዱስትሪ መንደር ሳይቀር በሰፊው እየተሰራበት ያለ ነው። በቻይናዊያን ባለሀብቶች ተገንብቶ በአብዝሃኛው ቻይናዊያን ባለሀብቶችን እያስተናገደ ያለው የዱከም ኢስት ኢንዱስትሪ ዞን በዚህ ረገድ በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችል ነው። ቻይናዊያን ባለሀብቶች ከዚህም ባለፈ በአማራ ክልል ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዋ የሰሜን ሸዋ ከተማዋ አረርቲ ላይ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ በመገንባት ላይ ናቸው። ፓርኩ በዋነኝነት የግንባታ ቁሳቁሶችን እንደዚሁም የቤትና የቢሮ እቃዎችን የሚያመርት ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቅ ነው።

 

ቻይና ከዚህም ባለፈ አሁን ካለው ከፍተኛ የተከማቸ ካፒታል ጋር በተያያዘ በርካታ ኢንዱስትሪዎቿ ወደ አፍሪካ ምድር ፈልሰው እንዲሰሩ የተለያዩ የቅስቀሳና የማበረታቻ ስራዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች። የቻይና የንግድ ሳምንት የንግድ ትርዒት አዘጋጅ ፕራና ኢቬንትስ ማኔጂግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ ከአፍሪካ ለዚህ የቻይናዊያን ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍስት የተመረጡት ሀገራት ሶስት መሆናቸውን ገልፀውልናል። እነዚህም ሀገራት ኢትዮጵያ፣ናይጄሪያና ግብፅ ናቸው። ቻይና ለኢትዮጵያ እየለቀቀችው ካለው ከፍተኛ የብድር መጠን፣ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰትና የበርካታ ፕሮጀክቶች ሥራ አኳያ በእርግጥም ኢትዮጵያ የቻይና የአፍሪካ መግቢያ በር ናት የሚለውን ሃሳብ ያጠናክራል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
555 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 928 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us