የውጭ ምንዛሪው ፈተና

Wednesday, 16 May 2018 13:13

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ከተመታ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ እየተባባሰ ሂዶ በአሁኑ ሰዓት ያለው የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ከ 3 ቢሊዮን ዶላር በታች አሽቆልቁሏል። ችግሩ በብዙ መልኩ የተተበተበ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያሉትን መሰረታዊ ችግሮች በሚከተለው መልኩ ዳሰናቸዋል።

 

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ መልሶ ኤክስፖርቱን ሲጎዳው

 

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ተፅዕኖ እያደረሰ ያለው በኤክስፖርት ገቢውም ጭምር ነው። ወደ ውጪ የሚላኩ የኢትዮጵያ ምርቶች ከማምረቻ ማሽኖች ጀምሮ እስከ ከፊል ያለቀላቸው ምርቶች ድረስ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ከውጪ በመሆኑ የውጪ ምንዛሪ እጥረቱ ኤክስፖርትን በማዳከም ሌላ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የሚፈጥርበት ሁኔታም አለ። በሌላ አነጋጋር የውጭ ምንዛሪ ችግሩ በራሱ ሌላ የውጭ ምንዛሪ ችግርን ይወልዳል ማለት ነው። እየሆነ ያለውም ይህ ነው።


በተለያዩ የኤክስፖርት ምርት ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከተከተሰው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ምርት አምርተው በኤክስፖርቱ ገበያ መሳተፍ አልቻሉም። በውጪ ገበያ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከተቀባይ ደንበኞቻቸው ጋር በገቡት ውል መሰረት ምርቶቻቸውን በአግባቡና በጊዜ ማቅረብ ካልቻሉ ደግሞ ከገበያ እየወጡ የሚሄዱበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው። ይህም በጊዜ ሂደት የሀገሪቱን የኤክስፖርት ገቢ የበለጠ እየጎዳው የሚሄድ ይሆናል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ

 

የውጭ ባለሀብቶች በአንድ ሀገር መዋዕለ ነዋያቸውን ሲያፈሱ ትርፍ ለመሰብሰብ ነው። በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ የውጭ ባለሀብቶች ኢንቬስት ኢንዲያደርጉ የሚፈቀድላቸው በዶላር ነው። ለዚህም የተቀመጠላቸው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን አለ። አንድ የውጭ ባለሀብት በዶላር ኢንቬስት የማድረግ ግዴታ ቢኖርበትም ከምርት በኋላ ትርፉን በውጭ ምንዛሪ መንዝሮ የመውሰድ መብቱ ግን የተጠበቀ ነው።


ሆኖም በኢትዮጵያ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ መዋዕለ ነዋቸውን ያፈሰሱ የውጭ ባለሀብቶች የሚያገኙትን ትርፍ በውጭ ምንዛሪ ቀይረው ወደ ሀገራቸው መውሰድ የቻሉበት ሁኔታ የለም። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የውጭ ባለሀብቶች በተደጋጋሚ ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ የቆዩበት ሁኔታም ነበር።


ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ኢንቬስት ያደረጉ የአውሮፓ ባለሀብቶች ህብረት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በባለሀብቶቹ በኩል ከተነሱት ጥያቄዎች መካከለም አንዱ ይሄው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጉዳይ ነው። ባለሀብቶቹ ትርፋቸውን በዶላር መንዝረው ለመውሰድ ለብሄራዊ ባንክ ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በተገቢው ሁኔታ እየተስተናገዱ አለመሆኑን የገለፁበት ሁኔታ ነበር። በጊዜው ለባለሀበቶቹ የተሰጣቸው ምላሽ በሁለት አቅጣጫ የተመለከተ ነበር። አንደኛው ባለሀብቶቹ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እስኪቃለል ለጥቂት ጊዜ ትዕግስት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ሲሆን ሌላኛው የቀረበው አማራጭ ደግሞ ባለሀብቶቹ በኤክስፖርት ሥራም በመሰማርተው የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ የሚያመነጩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ።


የመጀመሪያውን የውጭ ሀገር ባለሀብቶችን ጥያቄ በአግባቡ ለማሳካት በጊዜው ከነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ችግር መሆኑ ተገልፆ ችግሩ በሂደት የሚፈታ በመሆኑ ባለሀብቶቹ እንዲታገሱ የተጠየቀበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም ከዚያ በኋላ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ መፍትሄ ከማግኘት ይልቅ የበለጠ እየተባባሰ ነበር የሄደው። ሁለተኛው አማራጭ ባለሀብቶቹ ኤክስፖርት በማድረግ የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር የሚለው ነው። ይህ ምላሽ በጊዜው በበርካታ የውጭ ባለሀብቶች በኩል ቅሬታን የፈጠረበት ሁኔታ ነበር። አንድ የሀገር ውስጥ ወይም የውጭ ባለሀብት መዋዕለ ነዋዩን ሲያፈስ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ኤክስፖርት እንዲያደርግ የሚገደድባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም ሁሉም ባለሀብት በዚህ ግዳጅ ውስጥ የሚገባባት አሰራር ግን የለም። ባለሀብቶች ገና ከመጀመሪያው ወደ ኢንቬስትመንት ዘርፉ ሲሰማሩ፤ ዘርፉ ለኤክስፖርት ዘርፍ የተለየ በመሆኑ ሙሉ ምርቶቻቸውን ለኤክስፖርት ገበያ እንዲያውሉ የሚገደዱበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው በርካታ ማበረታቻዎች ከተደረገላቸው በኋላ ነው።


የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋና አላማ የኤክስፖርት ዘርፉን ማሳደግ በመሆኑ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የገቡ ባለሀብቶች ከሆኑ መቶ ፐርሰንት ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ የመላክ ግዴታ አለባቸው። እነዚህ ባለሀብቶች ወደዚህ ሥራ ሲገቡ ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት ለማድረግ ቃል ገብተውና ፊርማቸውን አኑረው ነው። በመሆኑም እነዚህ ባለሀብቶች ምርቶቻቸውን ልከው የውጭ ምንዛሪ ያስገባሉ፤ከዚህ ገቢ ውስጥም የድርሻቸውን ይወስዳሉ። ሆኖም ከዚህ ውጪ ያሉ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ዘርፉ በተለየ ሁኔታ አስገዳጅ ካላደረገውና፤ ባለሀብቱም በውጭ ገበያ የመሳታፍ ፍላጎት ከሌለው በስተቀር በህጉ መሰረት በዶላር ኢንቬስት አድርጎ ትርፉን በዚያው ምንዛሪ የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ ነው።


ይሁንና ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጋር በተያያዘ ከተገባው ስምምነትና ከህጉ ውጪ ሁሉም የውጭ ባለሀቶችን ኤክስፖርት አድርጉና ትርፋችሁን በውጭ ምንዛሪ ውሰዱ የሚለው አካሄድ ባለሀብቶች ተጨማሪ የኢንቬስትመንት ሥራን እንዳያከናውኑ የሚያደርግ ከመሆኑም ባለፈ ሌሎች የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱ የሚያደርግ ይሆናል። ይህም ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሀገሪቱን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቬስመንት ፍስት የሚጎዳውም ይሆናል።

 

የኤክስፖርት ማበረታቻውና የውጭ ምንዛሪው ስንክሳር

 

በግብርናውም ሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሰማርተው በኤክስፖርቱ ዘርፍ ለመስራት የተስማሙ ባለሀብቶች በህጉ መሰረት በርካታ ማበረታቻ ይደረግላቸዋል። ከማበረታቻዎቹ መካከልም የግብር እፎይታ፣ ከውጭ ለሚያሰገቧቸው ማሽኖችና ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ መብቶች ተጠቃሚነት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። ባለሀብቶቹ ከሌሎች ባለሀብቶች በተለየ ሁኔታ እነዚህ ማበረታቻዎች ሲደረግላቸው ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት አድርገው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ነው።


ሆኖም በርካታ ባለሀብቶች እነዚህን ማበረታቻዎች ከወሰዱ በኋላ ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት አድርጎ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ይልቅ የሀገር ውስጥ ገበያን የሚጠቀሙበት ሁኔታ አለ። ይህ ጉዳይ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደዚሁም በንግድ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች በኩል በተደጋጋሚ የሚነሳ ቅሬታ ቢሆንም እስከዛሬም ድረስ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ተሰጥቶት አይታይም።

 

የዲያስፖራው ፖለቲካና የውጭ የውጭ ምንዛሪው ፈተና

 

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ተደርገው ከሚወሰዱት ምንጮች መካከል አንዱ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚላከው የውጭ ምንዛሪ (remittance) አንዱ ነው። ከንግድ ሚኒስቴርም ሆነ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ከውጭ የሚላከው የውጭ ምንዛሪ መጠን ኢትዮጵያ በኤክስፖርት ምርት ከምታገኘው ገቢ መብለጥ ችሏል። ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ እየጦዘ ከመጣው የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት ጋር በተያያዘ የመንግስት የፋይናስ ጉልበት ለማዳከም በሚል የተከፈተ ዘመቻም አለ። ይህ ዘመቻ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የውጭ ምንዛሪ ማዕቀብን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እንዲጥሉ የሚያሳስብ ነው። እንቅስቃሴው በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀንሱ ወይንም መንግስት ኪስ እንዳይገባ ከባንክ ሥርዓት ውጪ ያለውን የመላኪያ ዘዴ እንዲጠቀሙ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ተሰምቷል። ይህ ጥሪ ምን ያህል ግቡን እንደመታ በግልፅ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ይሁንና ምንም አይነት ተፅዕኖን አያመጣም ብሎ መደምደም ግን አይቻልም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ይሄንኑ ጉዳይ አስመለክተው በቅርቡ በአንድ መድረክ የሚከተለውን ምላሽ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።


“መንግስትን ለማስደንገጥ የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት ትክክለኛ መፍትሄ አይደለም። ልጅ ሲያጠፋ የምንቀጣው ራት እየከለከልን አይደለም። እያበላን በድሮው ከሆነ እንቆነጥጣለን በአሁኑ ከሆነ ደግሞ Time out ነው የምንለው። ዲያስፖራ መንግስት ለመቆንጠጥ ዶላር አንልክም ሲሉ። ማነው እየተጎዳ ያለው ሲባል ዝቅተኛ ዶላር የማመንጨት አቅም ያላቸው ነጋዴዎች ናቸው።”

መደበኛ ያልሆነው የንግድ አካሄድና የውጭ ምንዛሬው

 

መንግስት በቂ የውጭ ምንዛሪን ማቅረብ ባልቻለ ቁጥር ነገሮች መደበኛ ያልሆነ አካሄድን መከተላቸው እሙን ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በተለይ የጥቁር ገበያ መጠናከር አንዱ መደበኛ ያልሆነው ገበያ ሥርዓት መጠናከር ማሳያ ነው። ከዚህም ባለፈ ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ ከላኩ በኋላ በመደበኛው የባንክ ሥርዓት የውጭ ምንዛሪን የማያስገቡ ባለሀብቶችም መኖራቸው ይታወቃል።


በብሄራዊ ባንክ ያለው የውጭ ምንዛንረ ወረፋ የሰለቻቸው እንደዚሁም በቂ ከዚህም በኋላ ቢሆን በቂ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት ያልቻሉ አስመጪዎች ያላቸው አማራጭ ፊታቸውን ወደ ጥቁር ገበያው በማዞር የዶላር ሸመታን ማካሄድ ነው። ይህም ሁኔታ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ በኩል ያለውን የምንዛሪ ልዩነት የበለጠ እያሰፋው የሚሄድ ይሆናል። ለዚህ ብቸኛው መፍትሄ መንግስት በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሪን ማቅረብ መቻል ብቻ ነው።


ከዚህ ባለፈ በአንድ ሀገር ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ሀብት በሚኖርበት ወቅት በባለሀብቶቹ በኩል በራስ መተማመን ስለማይኖር በብር የሚገኘውን ገቢ በውጭ ምንዛሪ ቀይሮ በውጭ ባንክ የማስቀመጥ ሁኔታም ይከሰታል። በሙስና ተጎጂ የሆኑ ሀገራት አንዱ የውጭ ምንዛሪ ድርቀት ይህ ነው። ይህ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ሀብት በዘረፋ ከመገኘቱ ባለፈ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ቋሚ ሀብቱ ለሀገር ተጨማሪ ጉዳትን የሚያስከትለው በገንዘብ ማሸሻነት የሚያገለግል መሆኑ ነው። ይህ ጉዳይ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው እነዚህ የገንዘብ ማሸሺያ የሆኑ የንግድ ተቋማት አንዳች አይነት እርምጃ ሲወሰድባቸው ብቻ ነው።


በአጠቃላይ ሲታይ በአንድ ሀገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲከሰት የሚያስከትላቸው ችግሮች ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ናቸው። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢንቨስትመንትን ይጎዳል፣ የንግድ ሚዛንን ያዛባል፣በውጭ እዳ ክፍያ ላይ የራሱን የሆነ ተፀዕኖን ያሳድራል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ መንግስት ፈተናዎች መካከልም ይሄው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጉዳይ አንዱ ነው። ዶክተር አቢይ በቅርቡ እንደተናገሩት የፈተናው መፍትሄ ዓመታትን የሚፈጅ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1386 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1035 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us