የሚሊኒየም አዳራሽ ቆይታዩና ጠቅላይ ሚኒስትሩ

Wednesday, 23 May 2018 14:15

 

ማይንድ ሴት ኮንሰልት በመባል የሚታወቀው ድርጅት ባሳለፍነው ቅዳሜ ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም ሰዎችን ለተለያዩ ሥራዎች የሚያነቃቃ ፕሮግራም በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። “እኔ ነኝ አዲሷ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ፕሮግራም በርካታ ታዋቂ ወጣቶችና ታዋቂ ሰዎችን አሳትፏል።

 

ይህ አይነቱ አነቃቂ ኮንፍረንስ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የተለመደ ነው።ዋና አላማውም ሰዎች በነገሮች በጎና የተነቃቃ አዕምሮ ኖሯቸው በማህበራዊና በኢኮኖሚዊ ስራዎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። በሀገራችን እንደዚህ አይነት ጅምሮች በተለያዩ አቅጣጫዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች የዜጎችን አስተሳሰብ በማነቃቃት ለስራ ፈጠራ ብሎም ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ እንደሆነ ይታመናል።

 

በዚህ ዙሪያ በሀገራችን ከሚንቀሳቀሱት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ዶክተር ምህረት ደበበ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድም ወደ ሀገር መሪነት ሥልጣን ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል የነበሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

የኮንፍረንሱ ምልከታ

የአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሰፊ ቢሆንም በወጣቶች ተሞልቷል። የአዳራሹ ስፋት የመድረኩን ክንውን ሰው በሚገባ ስለማያሳይ በርካቶች ፕሮግራሙን የሚታደሙት በዚያው በአዳራሽ ውስጥ በተሰቀሉት ግዙፍ ስክሪኖች ጭምር ነው። በዕለቱ ግጥሞች፣ ወጎችና የተለያዩ የሥነፅሁፍ ሥራዎችም ለታዳሚው ቀርበዋል። ከፕሮግራሙ ግዝፈት አንፃር ሲታይ መድረኩን ይመጥናሉ ተብለው የማይታሰቡ ሥራዎችም ሲቀርቡበት ታይቷል። ለወጣቶች ተሞክሮ ይሆናሉ ተብለው የቀረቡት ስራዎችና ልምድን የማካፈል ንግግሮች እያንዳንዳቸው በይዘታቸው ሰፊ ጊዜን የወሰዱ በመሆናቸው በታዳሚው ዘንድ መሰላቸትን ሲፈጥሩ ታይቷል።

 

በፕሮግራሙ መገባደጃ አካባቢ የማነቃቂያ ስብከት መሰል ንግግር ያደረጉት ዶክተር ምህረት ደበበ በሃሳብ ዙሪያ ሰፋ ያለ ፅንሰ ሀሳብ ለማስጨበጥ ጥረት አድርገዋል። በርካቶችም በጥሞና አድምጠዋቸዋል። ሆኖም ዶክተር ምህረት ብዙዎቹ የንግግር ጭብጦቻቸውን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያቀረቧቸው በመሆኑ ብዙም አዲስ ነገር አልነበራቸውም ብሎ መናገር ይቻላል።

 

ፕሮግራሙ ዘግይቶ የተጀመረ በመሆኑ እያንዳንዱ የመድረክ ዝግጅት አቅራቢ በመድረክ አስተባባሪ “ይብቃህ” እየተባለ በጆሮው ሹክ ይባለውም ነበር። ዶክተር ምህረትም ቢሆን ይህ እጣ ገጥሟቸዋል። በዚህ በኩል ሲታይ መድረኩ የቅንጅት ችግር የሚታይበትም ይመስላል። በመድረኩ የሙዚቃ ስራዎቸቸውን ያቀረቡት አርቲስቶች በሙያቸው ብቃትም ሆነ የታዳሚውን ጆሮ በመያዝ በኩል የተዋጣላቸው ነበሩ። ሰዓቱ እየገፋ መሄዱን ተከትሎ በከተማዋ ካለው የትራንስፖርት እጥረት ጋር በተያያዘ በርካቶች ፕሮግራሙን አቋርጠው ለመውጣት ተገደዋል። በተለይ በመጨረሻ በነበረው የፕሮግራሙ የሙዚቃ መሸጋገሪያ ወቅት ፕሮግራሙ የተጠናቀቀ እስኪመስል ድረስ በርካታ ታዳሚዎች በጥድፊያ ሲወጡ ታይቷል።

 

ዶክተር ምህረት የማነቃቂያ ንግግራቸውን እያደረጉ እያለ በፍጥነት እንዲያጠናቅቁ ከመድረክ አስተባባሪው በኩል ተነገራቸው። እሳቸውም ንግግራቸውን በፍጥነት አጠናቀው መድረኩን እንደተሰናበቱ፤ ማንም ባልጠበቀው መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አንድ እጃቸውን ከፍ አድርገው ለታዳሚው ሰላምታ እየሰጡ ወደ ንግግር ማድረጊያው ተጠጉ። ታዳሚው ከመቀመጫው በመነሳት በጩኸትና በፉጨት ተቀበላቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ የሚሊኒየሙ ፕሮግራም ከአምስት ወራት በፊት እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆኑ የተያዘ እንደነበር አስታውሰው የመድረክ ንግግራቸውንም የሚያደርጉት ቀድሞ ፕሮግራሙ ሲያዝ በነበራቸው ማንነት ሳይሆን በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ማንነታቸው መሆኑን በመግለፅ በቀጥታ ወደ ንግግራቸው ገቡ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳቸው በፊት ከነበሩት ተናጋሪዎች በላይ እጅግ በላቀ ሁኔታ የታዳሚዎቸቸውን ቀልብ ገዝተው ንግግራቸውን በስፋት ቀጠሉ። የንግሮቻቸው ጭብጥም በአንድነት፣ በይቅርታ፣ በአብሮነትና በመቻቻል ላይ ያተኮረ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ፕሮግራሙ የገቡት የሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ በመሆኑ እግረ መንገዳቸውንም በዚሁ ጉብኝት አላማና ስኬት ዙሪያ ስለነበሩ አንዳንድ ጉዳዮችም ማብራሪያ ሰጥተዋል። በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸው ወቅት ይዘዋቸው ከሄዷቸው አስር ጥያቄዎች ከአንዱ በቀር ዘጠኙ የተመለሱ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

“ሳዑዲ አረቢያ ሄደን ምን ትፈልጋላችሁ ተብለን ስንጠየቅ ገንዘብ ሳይሆን ዜጎቻችንን ፍቱልን ነው ያልናቸው። የሚገርመው ነገር ለዜጎቻችን ክብር መስጠት ስንጀምር ያልጠየቅናው ነገር ሁሉ ይሰጠናል።” በማለት ታዳሚውን በጭብጨባ ግለት ውስጥ ከተቱት።

 

ንግግራቸውንም ቀጠል በማድረግ “ዝርዝሩን ለዲሲፒሊን ብዬ መናገር ቢያስቸግረኝም፤ እጅግ ስኬታማ የሚባል የዲፕሎማቲክ ቆይታ ነበረን። በቆይታችን ከአንድ ጥያቄ በስተቀር የጠየቅናቸው ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ አግኝቷል። አንደኛው ጥያቄ ሺህ ሙሀመድ አሊ አልአሙዲንን ማምጣት ነበር። እሳቸውን በሚመለከት ከክራውን ፕሪንሱ ጋር መቶ በመቶ ተግባብተናል። አንድ ሺህ እስረኞችን ሳዑዲ ለቃለች። መፍታት ብቻ ሳይሆን ዛሬ ምሽት ከፊሉ መግባት ይጀምራል። ሼኽ አልአሙዲንን በሚመለከት እንደ ሀገር ያለንን ፅኑ አቋም አመላክተናል። ለእኛ ሀብታምም ደሃም ዜጋ ነው።

 

ሼህ ሙሐመድ ሄሴን አሊ አልአሙዲ የማንፈልጋቸው ሰዎች ያለን እንደሆነ ሲመጡ እንነግራቸዋለን እንጂ በባይተዋር ሰዎች ሲታሰሩ የሚጨክን ልብ የለንም። ይህ ጠንካራ አቋማችንን የተረዱት ክራውን ፕሪንሱ አሳዛኝ ቢሆንም ማታ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ላይ ተግባብተን ጠዋት ሊለቁ ከወሰኑ በኋላ ቤተሰቦቻቸው ባደረጉባቸው ከፍተኛ ጫና አሁን ከእኛ ጋር ሊመጡ አልቻሉም።

 

ከእሳቸው በሰተቀር አስር ጥያቄ ነበረን? ዘጠኙን መልሰውልን ለአስረኛው ጥያቄ ግን ጥቂት ጊዜ ስጡን ብለዋል። የሼኽ አልአሙዲ መታሰር በዓለም ላይ ያሉ ዲያስፖራዎች ሁሉ አጀንዳ መሆን አለበት። ምክንያቱን ኢትዮጵያ አንተ አንቺ ከሆንሽ፣ አንድ ኢትዮጵያ ታስራለችና ኢትዮጵያ ስትታሰር ዝም ማለት የሚያስችለው ሌላ ኢትዮጵያዊ መኖር የለበትም። የጀመርነውን ዲፕሎማቲክ ጫና በማስቀጠል ጊዜውን መናገር ብቸገርም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ።” በማለት በዚህ ዙሪያ የነበራቸውን ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2396 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 48 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us