“የዋጋ ንረት የመንግሥት ዓላማ ማስፈፀሚያ ነው?”

Wednesday, 06 June 2018 13:50


የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት መፅሐፍ

 

በቅርቡ በኢትዮጵያ አኮኖሚ ዙሪያ የሚያጠነጥን አንድ መፅሀፍ ለገበያ በቅቷል። መፅሀፉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን ፀሀፊው አቶ ጌታቸው አሰፋ የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው። መፅሀፉ በ387 ገፆች ተቀናብሮ የተዘጋጀ ሲሆን በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንም በውስጡ ዳሷል።

ፀሐፊው አቶ ጌታቸው አስፋው በሙያው ረዥም ዓመታትን የሰሩ ሲሆኑ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው የብሄራዊ ኢኮኖሚ እቅድ ባለሙያ ሲሆኑ በቀድሞው በኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ወይም በአሁኑ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በሙያቸው አገልግለዋል።

     ቀደም ብሎም በአሥመራ ዩኒቨርስቲ ለሶስት ዓመታት በገጠር ልማትና በታዳጊ ሀገራት የመልማት ችግሮች ዙሪያ በመምህርነት ሙያ ሰርተዋል። ባለፉት ሶስት ዓመታትም በሪፖርተር ጋዜጣና በውይይት መፅሄት ላይ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የዳሰሱ ፅሁፎችን ለአንባቢያን ሲያደርሱ የቆዩ መሆናቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል። አቶ ጌታቸው ይህንን ሙያዊ መፅሃፋቸውን ባሳለፍነው ቅዳሜ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አስመርቀዋል። በዕለቱም በመፅሀፉ አጠቃላይ ጭብጥና ይዘት ዙሪያ የተለያዩ ምሁራን የየራሳቸውን አስተያየቶች ሰጥተውበታል።

 

በሀገራችን አሁን ካለው የፖለቲካ፣ ልብወለድ፣ ታሪክና የወግ ፅሁፎች ባለፈ በዚህ ደረጃ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ የተፃፈ መፅሀፍ የለም ብሎ መናገር ይቻላል። ቢኖሩም በተቋም ደረጃ የተፃፉ ወይንም ደግሞ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እገዛ ለህትመት የበቁ ናቸው። እነዚህም ጥናቶች ቢሆኑ ታትመው በገበያው ላይ ለህዝብ የሚቀርቡ ሳይሆኑ ይመለከታቸዋል ተብለው ለሚታሰቡ ተቋማት የሚበተኑ በመሆናቸው በማንኛውም አንባቢ እጅ የሚገቡ አይደሉም። በዚህ በኩል ሲታይ አቶ ጌታቸው የተለየ ሥራን ሰርተዋል ያስብላል።

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት? እንደገፁ ብዛት በይዘቱ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ዳስሷል። ከዳሰሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ በዚህ ወቅት አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው የዋጋ ንረት ይገኝበታል። አቶ ጌታቸው በዚሁ መፅሀፋቸው ለዋጋ ንረት መፈጠር ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች መኖራቸውን በሚከተለው መልኩ በመግለፅ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያዛምዱታል።

 

“የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በዋናነት በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መብዛት እንደሆነ ካወቅን ዘንዳ ይህ የጥሬ ገንዘብ መብዛት ዋጋን እንዴት እንደሚያንር እንመልከት። የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በሁለት መንገድ ነው። አንዱ የሸማቹ የመግዛት አቅሙ አድጎ ለመሸመት ውድድር ውስጥ ሲገባና ወድ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ሲሆን ነው። ሁለተኛው የዋጋ ንረት ምክንያት በአምራቹ ላይ ግብር ወይንም የሰራተኛ ደመወዝ ወይም ጥሬ ዕቃ ዋጋ ጨምሮበት ምርቱን ሲያስወድድ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የዋጋ ንረት የተፈጠረው በሁለቱም መንገድ ነው” ፀሀፊው ከዚሁ የዋጋ ንረት ጋር ምክንያት ጋር በተያያዘ ሀሳባቸውን በሰፊው በማብራራት ለዋጋ ንረት ምክንያት ነው ያሉትን ሃሳብ በሚከተለው መልኩ ትንታኔ ሰጥተውበታል። “በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጨመር የፍላጎት ስበት የዋጋ ንረት ምክንያት እና በውጭ ምንዛሪ ተመን የብር ዋጋ መርከስ፣ በንግድ ትርፍ ግብር መጨመር፣ በጥሬ ዕቃ መወደድ በሚፈጠሩ የማምረቻ ወጪ ግፊት የዋጋ ንረት ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እንደሚጨምር ይገመታል።

 

የዋጋ ንረት የመንግሥት ዓላማ ማስፈፀሚያ ነው?

አቶ ጌታቸው በዚሁ መፅሀፋቸው የዋጋ ንረት የኢኮኖሚ መሳሪያ በመሆን አንዳንድ ጊዜ መንግስት የሚጠቀምበት መንገድ መሆኑንም አብራርተዋል።

ባለሙያው “የዋጋ ንረት የመንግስት ዓላማ ማስፈፀሚያ መሳሪያም ነው። የዋጋ ንረት ሀብታሙ ከደሃው ጥሬ ገንዘብ የሚነጥቅበት፤ ከነጠቀውም ውስጥ ለመንግስት የሚገባውን ግብር የሚሰጥበት ስለሆነ መንግስት ከሀብታሙ የሚሰበስበውን ግብር መጠን ከፍ ማድረግ ሲፈልግም ሆን ብሎ ጥሬ ገንዘብ ወደገበያው በመርጨት የዋጋ ንረት ይፈጥራል።

 

አቶ ጌታቸው ከዚህ ባለፈ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመግዛት አቅሙ እያሽቆለቆለ ሥላለው የብር መግዛት አቅም ሁኔታም በበርካታ ዓመታት ድምር ውስጥ ብር ዋጋውን በምን ያህል ደረጃ ዋጋውን እንዳጣ ከህዝቡ በተለይም ከደመወዝተኛው ኑሮ አንፃር በሚገባ ትንታኔ ሰጥተውበታል። ከኤክስፖርቱም ዘርፍ መዳከም ጋር በተያያዘ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎችንና ብዙም ውጤት እያመጡ አለመሆኑ በማስረጃ በተደገፈ መልኩ በሰፊው ተዳሷል። መፅሀፉ በአጠቃላይ ይዘቱ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በስፋት ዳሷል። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ከታሪክና ከዓለም አቀፉ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ጭብት አኳያም አያይዞ ሰፋ ያለ ትንታኔን ሰጥቶበታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1354 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 47 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us