የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ የውጭ ዕዳ ጫና፤ ቀጣይ ፈተናዎች እና ዕድሎች በፀጋው መላኩ

Wednesday, 20 June 2018 12:38

 

ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ውስጥ ናት። ችግሩ አሁን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይድረስ እንጂ ፈተናው እየተባባሰ የሄደው ከዓመታት በፊት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የወጪና የገቢ ከፍተት ይበልጥኑ እየሰፋ ሄዶ ያለበት ደረጃ በአሰራዎቹ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠረውን የአሃዝ ምዕራፍ ለማለፍ ዳዴ እያለ ነው። ይህ እየሆነ ያለው የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በታች በሆነበት ሁኔታ ነው። ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አኳያ ሲታይ አሁን ያለው የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ገቢ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆን ነበረበት። ሆኖም በየትኛውም የኤክስፖርት ያለው አፈፃፀም ዳካማነት በስተመጨረሻ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል።

 

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እየተባባሰ ሄዶ ምርቶች ሳይቀር ከየመደብሩ እየጠፉ በነበረበት ሁኔታ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደሌለ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል። በስተመጨረሻ እውነታው እያፈጠጠ ሄዶ መንግስት አሉኝ የሚላቸውን የመጨረሻ ጥሪቶች በሽያጭ ለግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ ግድ ብሎታል። ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ እያነሰ መሄዱ ብቻ ሳይሆን ከዚያው ላይም ተቀንሶ ለውጭ ዕዳ ክፍያ የሚውል መሆኑም አንዱ ፈተና ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ባለፈው ሰኞ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ያለባት የውጭ ዕዳ መጠን ከ24 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

 

ኢትዮጵያ ከኤክስፖርቱ ዘርፍ ባሻገር በተለያየ መልኩ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝባቸው ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህም የውጭ ምንዛሪ ምንጮች መካከል አንዱ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት (Foreign Direct Investment) አንዱ ነው። የውጭ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን ሲያፈሱ በውጭ ምንዛሪ እንዲያፈሱ፤ እንደዚሁም ትርፋቸውንም በውጭ ምንዛሪ የሚሰበሰቡበት አካሄድ ነው ያለው። ይህ ማለት አንድ የውጭ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገባ አዲስ ካፒታል ይዞ ከመምጣት ባሻገር ዶላር ይዞ ይገባል ማለት ነው።

 

ይሁንና ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ይህንን የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጉዳቱ በተመሳሳይ መልኩ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ይገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ እንዲወርድ አድርጎታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ባለፈው ሰኞ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት በ2010 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ገቢ በ7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር የቀነሰ መሆኑን አስታውቀዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ያለው የውጭ ምንዛሪ የወረደ መሆኑንም አስታውቀዋል።

 

የብድር ጫና እና የውጭ ምንዛሪው ቀጣይ ፈተና

አንድ ሀገር ከመበደር አልፎ በከፍተኛ የውጭ ብድር ጫና ውስጥ ሲወድቅ ሁለት መሰረታዊ ፈተናዎች ይከሰታሉ። የመጀመሪያው ሀገር በተለያየ ዘርፍ የሚያገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለልማት ከማዋል ይልቅ ለዕዳ ክፍያ እንዲያውል መገደዱ ሲሆን በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ያ ሀገር በዕዳ ጫና ውስጥ ከወደቀ ተጨማሪ የውጭ ብድር የማግኘት እድሉ የጠበበ መሆኑ ነው።

 

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት አነስተኛ የውጭ ዕዳ ካለባቸው ሀገራት ተርታ ውስጥ ትመደብ እንደነበር ዓለም አቀፍ የብድር ግምገማ የሚያካሂዱ ኤጀንሲዎች ያወጡት የቀደመ ሪፖርት ያመለክታል። በዚህም በገምጋሜ ኤጀንሲዎች ደረጃ አሰጣጥ መሰረት ኢትዮጵያ የ“B” ደረጃን ያገኘችበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም በሰኞው የፓርላማ ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ተርታ ከተሰለፉት ሀገራት ውስጥ ገብታለች። ሀገራት በእንደዚህ አይነት የዕዳ ጫና አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ ከሚወስዷቸው እርምጃዎች መካከል አንደኛው ከአበዳሪዎች ጋር መደራደር ነው። ድርድሩ የዕዳ ክፍያ ጊዜን ከማራዘም ጀምሮ እስከ ዕዳ ስረዛ የሚዘልቅ ነው።

 

ኢትዮጵያ ከሩስያ ወይንም ከቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በደርግ ዘመን የተበደረችው ከፍተኛ ዕዳ በኢህአዴግ ዘመን የተሰረዘው በሁለትዮሽ ድርድር ነው። በዕዳ ስረዛው ረገድ ኢትዮጰያ አዲስ አይደለችም። ይሁንና ዕዳ ስረዛዎች ከሀገራት እንደዚሁም ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት የሚወሰደውን የብድር የሚመለከት እንጂ በተቋማት ሥም የገባን ብድር እንደዚሁም ከንግድ አበዳሪ ተቋማት የተወሰደን ብድር የሚመለከት አይደለም። በኢትዮጵያ መንግስት ዋስትና በኢትዮ ቴሌኮምና በሌሎች ተቋማት የተወሰዱ ብድሮች በቀጥታ ከንግድ ብድር ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው በእንደዚህ አይነት የዕዳ ስረዛ ይጠቃለላሉ ተብሎ አይጠበቅም።

 

የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ አቅም ያላቸው መንግስታት ወይንም ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ መንግስት ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ (Cash Injection) እንዲያደርጉ መማፀን ነው። ግብፅ ከአረብ አብዮት በኋላ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቋቋም ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬት በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የቀጥታ ድጋፍ አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ በኢንቨስትመንት ሥም ቢሊዮን ዶላሮች የግብፅ ኢኮኖሚ ውስጥ በማፍሰስ ላይ ናቸው።

 

ይህ ጅምር በኢትዮጵያም ተጀምሯል። ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ የተገኙት የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ልዑል ሞሀመድ ቢን ዛይድ አልናሂያን ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተወሰነ ደረጃ መቋቋም ትችል ዘንድ የአንድ ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ ካሽ ድጋፍ እንደዚሁም የሁለት ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ሀገራቸው የምታደርግ መሆኗን ገልፀዋል።

 

ይህ አይነቱ የመታደጊያ ገንዘብ (Bail out Money) የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከድርቀት የሚታደገው ይሆናል። መንግስት ለሽያጭ ያቀረባቸው ድርጅቶች ሽያጭ ገቢ አሁን በፍጥነት ለሚያስፈልገው ገንዘብ ሊያገለግል የሚችል ባለመሆኑ ብቸኛው አማራጭ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቀጥታ የውጭ ምንዛሪ ሊታደግ የሚችልን ሀገር ወይንም ድርጅት መፈለግ ብቻ ነው። የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬት ተግባር አንዱ ጅምር ሲሆን ጉዳዩ የሌሎችን ሀገራት ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ መንግስት ሌላ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ያስፈልገዋል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አሁን እያካሄዱት ካለው የፖለቲካ ለውጥ አንፃር በዚህ በኩል ድጋፍ ያጣሉ ተብሎ አይጠበቅም። ከአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት በኋላ በእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒሰትር ቴሬሳ ሜይ በኩል የተሰማው የድጋፍ ተስፋም ይሄንን የሚያመላክት ነው። ሁለተኛውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣል የተቃወመችው አሜሪካም ብትሆን ለዶክተር አቢይ የለውጥ ሂደት ድጋፏን የምትሰጥ መሆኗን ገልፃለች። ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ሁኔታ መቀበሏን ማስታወቋ በራሱ አንዱ ከፖለቲካ ድጋፍ ባለፈ የፋይናንስ ድጋፍን ጭምር የሚያስከትል ነው ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢኮኖሚውን መበላሸት የፖለቲካው መበላሸትም ነፀብራቅ ነው። ይህም በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ መንግስት አሁን እየሄደበት ያለው መንገድ በሚገባ የሚሰምር ከሆነ አዎንታዊ የኢኮኖሚ ለውጥም ይመዘገብበታል ተብሎ የሚጠበቅ ይሆናል። የፖለቲካ መረጋጋቱ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር ያደርገዋል። ግልፅነትና ተጠያቂነት የሚሰፍን ከሆነ በተለይ በኤክስፖርቱ ዘርፍ ያለው ሥር የሰደደ ሙስና ከሥሩ የሚነቀል በመሆኑ የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ በከፍተኛ ደረጃ የሚያድግ መሆኑ ጥርጥ የለውም። ይህ ብቻ ሳይሆን ሙስናና ብልሹ አሰራር የህዝብ ገንዘብን በውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ የሚያሸሽ በመሆኑ የፖለቲካው መልክ መያዝ እንደዚህ አይነት ቀዳዳዎች እንዲዘጉ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮ-ቴሌኮም የውጭ ገቢ ጥሪ ከሙስና ጋር በተያያዘ ምን ያህል እንደወረደ በዚሁ በፓርላማ ቆይታቸው አመልክተዋል። ይህ ችግር በቀጥታ ከፖለቲካው መበላሸትና ከተደራጀ ሙስና ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ሆኖ ይታያል። ይህ አይነት ኢኮኖሚያዊ ፈተናን ሊያስከትል ችግር ከመሰረቱ ሊፈታ የሚችለው የተደራጀ ሙስናን በፖለቲካ ለውጥ እርቃኑን ማስቀረት ሲቻል ብቻ ነው።

 

በአጠቃላይ ሲታይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ መንግስት በኢኮኖሚው ዘርፍ የአጭር ጊዜ ፈተና የሚገጥመው ይሁን እንጂ በሂደት ሲታይ ግን ከነበረው በብዙ እጥፍ የሚሻል ለውጥ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ መንግስት የጀመረውን ለውጥ ዘርፈ ብዙ በሆነ መልኩ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ማድረስ ካለቻለ ግን የፖለቲካው ውድቀት የኢኮኖሚ መንኮታኮትን ጭምር የሚያስከትል ይሆናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
179 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 541 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us