የአዲሱ መንግስት ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችና የሚጠበቁ ተስፋዎች

Wednesday, 27 June 2018 12:33

 

ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊ ቁመና አንፃር ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልጋት ቢሆንም ፈጣን የሆነ ውጤትን ማምጣት የሚቻልበት ሁኔታ ግን አይኖርም። ለውጭ ምንዛሪው ግኝት ዋነኛ የጀርባ አጥንት የሆነው የኤክስፖርቱ ዘርፍ እየታየበት ነው ከሚባለው የአቅም ውስንነት ባሻገር በብዙ የሙስና መረብ የተተበተበ መሆኑን ቀደም ሲል በተለያየ መልኩ ሲወጡ የነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለምሳሌ ምርቶቹን ኤክስፖርት በማድረግ ያገኙትን የውጭ ምንዛሪ በተቀመጠው ህግና አሰራር መሰረት ወደ መንግስት ቋት የማያስገቡ ላኪዎች መኖራቸውን ቀደም ያሉ የፌዴራልና ሥና ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥናቶች ያመለክታሉ።

 

ይህ ብቻ ሳይሆን ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ ተብለው ልዩ ድጋፍ የሚደረግላቸው በልዩ ልዩ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ድጋፉን ቢገባ ቢያገኙም ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡበት ሁኔታ መኖሩም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል። ይሁንና በተለይ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የስልጣን ቆይታ ዘመን በዚሁ ዙሪያ ጥናቶች ተደርገው በእንዲህ አይነት ድርጊት የተሰማሩ ባለሀብቶች የተየሉበት ሁኔታ ቢኖርም እነዚህ ባለሀብቶች ላይ ምንም አይት እርምጃ ሲወሰድባቸው አልታየም።

 

በመሆኑም “አምርተን ኤክስፖርት እናደርጋለን” በማለት ለኤክስፖርት ማበረታቻ የሚሰጠውን ማሽንን እና የግብዓት ምርቶችን የመሳሰሉ ከቀረጥ ነፃ ከማስገባት ጀምሮ ለተወሰኑ ዓመታት የግብር የእፎይታ ጊዜን የሚያገኙበት ሁኔታም አለ። ሆኖም ነጋዴዎች እነዚህን ጥቅማ ጥቅሞች በሚገባ ካገኙ በኋላ ኤክስፖርት አድርገው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት ይልቅ፤ ምርቶቻቸውን በሀገር ውስጥ ገበያ መሸጣቸው ሁለት መሰረታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን የሚያስከትሉ ሆነው ይታያሉ።

 

የመጀመሪያው ለውጭ ገበያ በሚቀርቡት ምርቶች ሊገኝ ይችል የነበረውን የውጭ ምንዛሪ የሚያሳጣ መሆኑ ሲሆን በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በኤክስፖርት ማበረታቻ ስም ሰፊ ድጋፍ ካገኙ በኋላ ሀገር ውስጥ ሽያጭን ማከናወኑ ሌሎች በሀገር ውስጥ ገበያ ውስጥ ብቻ ተሰማርተው ከሚሰሩ ባለሀብቶች ጋር የሚኖረውን የገበያ ውድድር ያልተገባና በኢፍትሃዊነት የተሞላ ያደርገዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ መንግስት ከፖለቲካው ወደ ኢኮኖሚው ዘርፍ ፊቱን ሲያዞር በመሰረታዊነት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ችግር መቅረፍ ካለበት በዚህ አቅጣጫ ያለውን የተወሳሰበ ችግሮ አንጥሮ መፍታትን ይጠይቀዋል።

 

ኤክስፖርቱ ከአቅም ውስንነት ጀምሮ በመሰል ውስብስብ የሙስና መረብ ውስጥ የተዘፈቀ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ በሚል በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም አማካኝነት በራሳቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥተኛ ክትትል የሚደረግበት የኤክስፖርት ክትትል ምክርቤት እስከ መቋቋም ደርሶ ነበር። ይሁንና ወደ ተግባር ሲገባ ይህ ነው የሚባል ለውጥን ያመጣበት ሁኔታ አልታየም። ኤክስፖርቱ ዘርፍ መጨመር ይቅርና ከነረበት እንኳን ወደኃላ እንዳይንራሸተት መታደግ አልቻለም። ከህጉና ከተቋም ግንባታው ባለፈ ዋነኛ ችግሩ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱም ጉዳይ ነበር።

 

ህጉም ሆነ ተቋማቱ ዛሬም አሉ። ሆኖም ችግሩን ከመሰረቱ ፈቶ በማስተካከሉ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ መንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ሊያንሰው ይችላል የሚል አንዳች ጥርጣሬ የለም። ይህም በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ያለው የጥቅም ትስስር ቀስ በቀስ እየተበጣጠሰ እስኪሄድ ግን የአዲሱ መንግስት ፈተና ሆኖ መቀጠሉ ግን አይቀርም።

 

ችግሩን የበለጠ ፈታኝ የሚያደርገው ደግሞ የኤክስፖርቱ ዘርፍ የጥቅም ትስስር በባህሪው በርካታ ተቋማትን የሚያዳርስ መሆኑ ነው። ትስስሩ ከብሄራዊ ባንክ እስከ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ብሎም ከንግድ ሚኒስቴር እስከ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ሌሎች መሰል ተቋማት ይዘልቃል። ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ተቋማቱን በአዲስ የሰው ኃይል ከመተካት ጀምሮ ተቋማዊ ሪፎርም እስከማድረግ ሊደርስ ይችላል። ይህ በራሱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ መንግስት የአጭር ጊዜ መፍትሄ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።

 

አንዳንዶቹ እርምጃዎች በዚህ ውስብስብ ኤክስፖርትን የማዳከም ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በህግ እስከመጠየቅ የሚያደርስ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ዘርፉን በመታደግ ኤክስፖርቱን ካለበት ችግር ለማውጣት የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ጥብቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካልታከለበት በስተቀር ችግሩ ከቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተለየ ውጤት ሊያገኝ አይችልም።

 

ተጨማሪ ብድር የማግኘት ፈተና

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር ጫና ውስጥ ከወደቁ ሀገራት መመደቧ ታውቋል። ይህ የብድር ጫና የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መንግስት በሀለት መልኩ የተፈለገውን ያህል ተጨማሪ ብድሮችን እንዳያገኝ የሚያደርግ ይሆናል። በአንድ መልኩ አበዳሪ አካላት ሀገሪቱ የብድር ጫና ውስጥ ከመውደቋ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ብድርን ለማቅረብ ብዙም ፈቃደኝነት የማይታይባቸው መሆኑ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በብድር ተቀባዩ መንግስት በኩልም ቢሆን ተጨማሪ የብድር ጫና ውስጥ ላለመግባት ተጨማሪ ብድር ውስጥ ላለመግባት የሚደረጉ ቁጥብነቶችም ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል። እነዚህ ሁኔታዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ መንግስት ቀጣዩ ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም መንግስት አሁን ባለው አካሄድ የፖለቲካ ውጥረቱን እያረገበና የመጫወቻ ሜዳውን እያሰፋ ከሄደ የዲሞክራሲውን ሂደት የሚደግፉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ ሀገራት የሚኖራቸውን ኢኮኖሚያዊ ከፍ የሚያደርገው በመሆኑ በዚህ በኩል የተወሰኑ የገንዘብ ድጋፎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

የቢሮክራሲ አሻጥሮች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለአዲስ ለውጥ የመነሳታቸውን ያህል ቀላል በማይባል መልኩ አዲሱን የለውጥ ሂደት ወደኋላ ለመመለስ የሚጥሩም መኖራቸው ግልፅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያው የፓርላማ ሪፖርታቸው ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን በሪፖርታቸው ላይ በግልፅ አስቀምጠዋል። እነዚህ አሻጥሮች ከአገልግሎት እስከ ምርት ያለውን የኢኮኖሚውን ዘርፍ የሚያዳክሙት ይሆናል። በዚህ ረገድ የዶክተር አቢይ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ብዙ የመዋቅራዊ ፍተሻዎችን ማድረግ የሚጠበቅበት ይሆናል። እነዚህ ሁኔታዎች በሥጋትነት የሚታዩ ሲሆን የሚካሄደው መዋቅራዊ ፍተሻና ማስተካከያ ደግሞ በአዎንታዊ ለውጥነት ሊታዩ የሚችሉ ተስፋዎች ናቸው።

 

በውጭ ባሉ ኢትዮጵያዊያን የሚላክ የውጭ ምንዛሪ (Remittance) ማዕቀብና መልካም ጅማሮ

በውጪ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ለቤሰቦቻቸው የሚላከው የውጭ ገንዘብ ለሀገሪቱ በውጪ ምንዛሪ ገቢነት ያገለግላል። በዚህ በኩል የኤክስፖርት ገቢው እየተዳከመ መሄዱን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት ከውጪ የሚላከው ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሪ ያለው ብልጫ ከፍ እያለ መሄድ ችሏል። ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ እየተከሰተ የሄደውን የፖለቲካ ውጥረት ተከትሎ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የራሳቸውን ግብረ ኃይል በማቋቋም በኢትዮጵያዊያንና በትውልደ ኢትዮጵያዊያን በኩል ወደ ሀገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ የመንግስት ካዝና እንዳይገባ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል።

 

ኢትዮጵያዊያኑ በዚሁ ዘመቻቸው ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የሚፈልጉ ሰዎች ገንዘባቸውን በመንግስት የፋይናስ ስርዓት ውስጥ በማሳለፍ ሳይሆን መደበኛ ባልሆነ የመላኪያ ዘዴ በመጠቀም መንግስት በዚህ በኩል የሚያገኘውን ገቢ ለማሳጣት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይህ ማዕቀብ በመንግስት ላይ ምን ያህል አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳደረሰ በግልፅ አይታወቅም። ሆኖም ይህ ማዕቀብ እንዲጣል ያደረገው ግብረ ኃይል የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ መንግስት እያሳየ ያለውን አዎንታዊ የፖለቲካ ለውጥ ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ ማዕቀቡ እንዲነሳ ጥሪውን አስተላፏል።

 

እንደውም ለውጡን የማይፈልጉ የውስጥ ኃይሎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይን መንግስት በኢኮኖሚ አሻጥር ለማዳከም ስለሚፈልጉ መንግስት ከዲያስፖራው ሊያገኝ የሚገባውን በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት አለበት ሲሉም መግለጫ አውጥተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ወደ 3 ሚሊዮን ይደርሳል። ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኃይል በሀገሪቱ በተፈጠረው አግላይ ፖለቲካ ቀላል የማይባለው ኃይል በሀገሪቱ የልማት ሥራ ውስጥ ተሳታፊ ሳይሆን ቆይቷል። ሆኖም አሁን እየታየ ያለው መቀራረብ ለዶክተር አቢይ መንግስት ከፈተናው ጀርባ ያለ ተስፋ ነው።

 

ይህ አሁን በመንግስትና በውጪ ባሉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል እየታየ ያለው መቀራረብ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና የሰፋ የሚያደርገው ይሆናል። መንግስት ከዚህ ቀደም የህዳሴው ግድብ ግንባታ ማስኬጃ ገንዘብን ከውጪ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ለማሰባሰብ ያደረገው ጥረት ብዙም ያለመሳካቱ ሚስጥር ይሄው የፖለቲካ ልዩነትና አለመግባባት ነው። መንግስት ከያዘው እቅድ አንፃር የተሻለው የተባለውን ገቢ ማሰባሰብ የቻለው በመካከለኛው ምስራቅ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ነው።

 

በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ይህ ብቻ ሳይሆን የግድቡ ገንዘብ እንዳይሰባሰብ ከፍተኛ የማደናቀፍ ስራም ሲሰራም ነበር። እንደዚህ አይነቶቹ የፖለቲካ እልህ መጋባቶች በሌላ አቅጣጫ ኢኮኖሚውን ክፉኛ ሲጎዱት ቆይተዋል። ይሁንና አሁን እየታየ ያለው ፖለቲካዊ ለውጥ በዚሁና በስፋትም የሚቀጥል ከሆነ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ለውጥ ላይ የሚኖረው አዎንታዊ ድርሻ ከፍተኛ ነው ተብሎ ይጠበቃል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
141 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 443 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us