ከነዳጅ ሀብቱ መገኘት ባሻገር

Wednesday, 04 July 2018 12:27

 

ኢትዮጵያ ካለፈው ሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት የምትጀምር መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከተገለፀ በኋላ በዕለቱ ይሄንኑ የነዳጅ አወጣጥ ሂደት የሚያሳይ የተሌቭዥን ምስል ተለቋል። ይህንንም የዜና ብስራት ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በስፋት ተቀባብለው ዘግበውታል። ይህ ምርትም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አዲስ እሴትን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

 

በኢትዮጵያ የነዳጅና የጋዝ ምርት ፍለጋ አንድ ምዕተ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ዓመታት ቢቀሩትም በተጨባጭ ውጤት መገኘት የጀመረው ግን ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ነው። አሁን የተገኘው የነዳጅ ሀብት ሀገሪቱ በአንድ መልኩ ሀገሪቱ የነዳጅ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀር ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኝ ነው። እነዚህና ሌሎች በርካታ ጥቅሞች እንደተጠበቁ ሆነው ከዚሁ ሀብት ባሻገር የሚታዩ ሥጋቶችና እድሎችም አሉ።

 

የፀጥታና ደህንነት ሥጋት

ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ የመገኘቱን ያህል ከዚሁ ጋር ተያይዘው ሊነሱ የሚችሉ አደጋዎችም በስጋትነት የሚታዩ ናቸው። ሥጋቶቹ በዋነኝነት አሁን ነዳጅ ተገኘ የተባለበት የኦጋዴን አካባቢ ከመሃል አገር የራቀ ከመሆኑ ባሻገር ብዙም ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት በሌላት ሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ መሆኑ። ይህ ብቻ ሳይሆን አካባቢው ከዚህ ቀደም አማፀያን ኃይሎች የሚንቀሳቀሱበት መሆኑና ቀደም ብሎም ከጋዝ ፍለጋው ጋር በተያያዘ ጥቃት የተፈፀመበት ታሪክ ያለ መሆኑ ስጋቱን ያንረዋል።

 

በዚህ በኩል እንደዋና ሥጋትነት የሚታየው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ነው። ኦብነግ በሶማሌ ከልል አካባቢ የረዥም ጊዜ ትጥቅ ትግል ታሪክ ያለው ሲሆን አንድ ጊዜ ሲጠናከር ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲዳከም እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ ኃይል ነው። ይህ ታጣቂ ኃይል ባለፉት ዓመታት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ቀላል የማይባል ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶችን አድርሷል። የኢትዮጵያ መንግስትም ታጣቂ ቡድኑን ከኦነግና ከግንቦት ሰባት ጋር በአንድ ላይ አካቶ በህግ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ ካደረገ በኋላ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎችም እንዲዳከም የማድረግን ሥራንም ሲሰራ ቆይቷል።

 

በዚህ መሃል የኦብነግ እንቅስቃሴ ከመዳከም ባለፈ የመከፋፈልን አዝማሚያንም እስከ ማሳየት ደርሷል። የኢትዮጵያ መንግስት ካፈነገጠው አንደኛው የኦብነግ አንጃ ጋር በሚስጥር የተያዘ ድርድርን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲያደርግ ቆይቷል። ይህ ድርድር በኬኒያ ናይሮቢ ሳይቀር የተካሄደ ሲሆን የውይይቱ ጭብጥና የደረሰበት ደረጃም እስከዛሬ ድረስ ግልፅ አይደለም።

 

ቡድኑ ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ ስሙ እንዲፋቅ ሰሞኑን ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን፤ ይሁንና የነዳጁና የተፈጥሮ ጋዙ መገኘቱን ተከትሎ ሁኔታውን በመቃወም ጥቃቱን አፋፍሞ የሚቀጥል መሆኑን ሌላኛው አንጃ ከሰሞኑ አስታውቋል። አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም የኦብነግ ኃይሎች ችግሮቻቸውን በድርድር ለመፍታት ዝግጁነቱ የሚታይባቸው ከሆነ በአካባቢው ሊኖር የሚችለው ስጋት ከተራ ሽፍትነት የዘለለ ባይሆንም በዚህ ዙሪያ ያሉ ሥጋቶችን እስከመጨረሻው መቀረፍ ካልቻተቻለ ግን የቡድኑ እንቅስቃሴ በነዳጅ ሀብቱ ሥጋትነት ጭምር የሚታይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

 

ይህ ኃይል ከዚህ ቀደም በአካባቢው ነዳጅ ፍላጋ ላይ በተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን እና ቻይናዊያን ላይ ባደረሰው ጥቃት ዘጠኝ ቻይናዊያን እንደዚሁም ከ60 በላይ ኢትዮጵያዊያን መገደላቸው የሚታወስ ነው። ይህ ድርጊትም በአካባቢው ያለው የነዳጅ ምርመራ ሥራ ለተወሰኑ ጊዜያት እንዲራዘም አድርጎት ቆይቷል። ቡድኑ በቅርቡም ተመሳሳይ ዛቻን ያሰማ ሲሆን በአካባቢው ያለፈውን ጊዜ ስህተት ላለመድገም ከፍተኛ የሆነ ጥበቃን የሚጠይቅ እንደዚሁም በዘለቄታነት ደግሞ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታትን የሚያስገድድ ይሆናል።

 

የሙስና ሥጋት

ከነዳጅ መገኘት ጋር በተያያዘ የሚፈጠረው ሌላኛው ፈተና ሙስና ነው። በዚህ ረገድ በአፍሪካም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ ችግሩ ስር የሰደደ ነው። ናይጄሪያ በዓለም ስድስተኛ ነዳጅ አምራች ሀገር ብትሆንም ዛሬም ቀላል የማይባለው ህዝቧ በከፍተኛ የድህነት አዘቅት ውስጥ ይገኛል። ናይጄሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሙስና ደረጃን እንድትይዝ ያደረጋት ነዳጅ ነው። ሀገሪቱ ባላት ረዥም ዓመት ነዳጅን የማውጣት ታሪክ የነዳጅ ድፍድፍን ወደ ውጪ ከመላክ ባለፈ የነዳጅ ማጣሪያን እንኳን መትከል አልቻለችም። ዛሬ ናይጄሪያ ድፍድፍ ነዳጅን ኤክስፖርት በማድረግ እንደ ማንኛውም ሀገር የተጣራ ነዳጅን ከውጭ የምትገዛ ሀገር ናት። ይህ እንዲሆን ያደረገው በሀገሪቱ የተንሰራፋው ከነዳጅ ጋር የተያያዘ ሙስና ነው።

 

በተመሳሳይ መልኩ ደቡብ ሱዳንን ወደ ውስብስብ የእርስ በእርስ ጦርነት የማገደው አሁንም ይህ የነዳጅ ሀብት ነው። ሀገሪቱ ወደለየለት ጦርነት ከመግባቷ በፊት በስተመጨረሻ የስልጣን ባላንጣ ሆነው በተፃራሪ ወገን ቆመው የተገኙት ሀይሎች ከፍተኛ በሆነ የነዳጅ ሀብት ሙስና የተዘፈቁ መሆናቸው ተረጋግጧል። ችግሩንም ከምንጩ ለመፍታት አሜሪካንን ጨምሮ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በደቡብ ሱዳን የነዳጅ ምርት ላይ ማዕቀብ እስከመጣል ደርሷል። ከብዙ እልቂት በኋላ መጠኛ የሰላም ጭላንጭል መታየት የጀመረው በቅርቡ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በኢትዮጵያ በኦፊሴል የነዳጅ ማውጣት ሂደት የሚጀመር መሆኑን ባበሰሩበት ንግግራቸው በዚህ በኩል ያላቸውን ሥጋት ከስግብግብነት ጋር አያይዘው ገልፀውታል።

 

አደጋውንም በማመላከት ጥንቃቄ እንዲደረግም ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። ከዚህ ውጪ ግን የተወሰኑ ሀገራት ታሪክ ከነዳጅ ሀብት ጋር በተያያዘ የመበላሸቱን ያህል ሀብቱን በሚገባ ተጠቅመው ያደጉበትም ሀገራት በርካቶች ናቸው።

 

 

የጠባቂነት ፈተና

ሌላኛው የነዳጅ ምርት ፈተና ዜጎች ሙሉ በሙሉ የዚህ ሀብት ጥገኛ መሆናቸው ነው። ይህም የሀገራትንና የዜጎቻቸውን ፈጠራ የሚያዳክም፣ለትምህርት ያላቸውን ፍላጎት የሚቀንስና በካሽ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ብቻ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። በበርካታ ነዳጅ አምራች የአረብ ሀገራት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በእነዚህ ሀገራት ሰፊ የሆነ የመሀይምነት መንሰራፋት ሁኔታዎች ይታያሉ።

 

ዜጎች ትምህርትን እንደ ጭንቀት ስለሚያዩት በስተመጨረሻ የሁሉም ነገር ጥገኛ ለመሆን ተገደዋል። በተማረ የሰው ሀይል ሀብት የሚገኙበት ደረጃ የዓለም ግርጌ ነው። ይህም በመሆኑ ሀገራቱ ከተራ ሠራተኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ምሁራን ድረስ የሚጠቀሙት የሰው ኃይል የሌሎች ሀገራት የሰው ኃይል ነው። እንደኳታር ያሉ ሀገራት የውጭ ዜጋው ቁጥር ከሀገሬው ዜጋ የሚበልጥበት ሁኔታ አለ።

 

ሀገራቱ በተገቢው መንገድ ታክስን የማይሰበስቡ፣ ዜጎችም ቢሆኑ የታክስ ግዴታን እንኳን በቅጡ የማይገነዘቡ ናቸው። ዜጎች ሁሉም ነገር በመንግስት እንዲደረግላቸው የሚጠብቁ ናቸው። ሳዑዲ የተጨማሪ እሴት ታክስን ወደ ሥራ ያስገባቸው በቅርቡ ነው። እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ሲታዩ ሀገራቱ ከመንግስት እስከ ህዝብ የነዳጅ ሀብት ጥገኛ ሆነው ይታያሉ።

 

ሆኖም የበርካታ ሀገራት የነዳጅ ክምችት እየወረደ መሄዱን ተከትሎ ሀገራቱ አማራጭ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለማማተር ተገደዋል። ይህም በመሆኑ በርካታ በነዳጅ የበለፀጉ ሀገራት በነዳጅ ሽያጭ ያገኙትን ገንዘብ በሌሎች ሀገራት ኢንቨስት በማድረግ ሀብቱን ለትውልድ የማስቀጠል ሥራን በመስራት ላይ ናቸው። ይህ ኢንቨስትመንት ከግብርና እስከ ሪል ስቴት ብሎም እሰከ ግዙፍ የአገልግሎት መስጫ ኩባንያዎች ድረስ የሚዘልቅ ነው።

 

በሌላ አቅጣጫ የነዳጅ ሀብት ያላቸው እንደ ሩስያ፣ አሜሪካ፣ ካናዳና ቤልጂየም ያሉ ሀገራት የነዳጅ መኖር ወይንም መገኘት እንደ አረብ ሀገራቱ የዚህ ሀብት ጥገኛ እንዲሆኑ አላደረጋቸውም። በሀገራቱ ቀድሞ የነበረው ምርምር፣ትምህርትና የሌላው ኢኮኖሚ ዘርፍ እንቅስቃሴ በስፋት እንደቀጠለ ነው።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ከዚሁ ጋር የሰጡት ማሳሰቢያ በዚህ ዙሪያ ሊታዩ የሚችሉ ሥጋቶችን ያመላከተ ነው። እሳቸው በዚሁ ንግግራቸው ነዳጅ ተጨማሪ ሀብት መሆኑን አመልክተው፤ከዚህ ውጪ ያሉት እንደ ግብርና፣ኢንዱስትሪና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ማመልከታቸው የሚታወስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ሀሳብ ያነሱት በሌሎች ሀገራት ከታየው የጠባቂነት አስተሳሰብ በመነሳት ነው።

 

ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን የመሳብ እድል

ፖሊ-ጂሲኤል ኩባንያ በኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋና ምርመራን ብሎም የምርት ሥራን ለመስራት ከኢትዮጵያ ጋር የሥምምነት ውልን የፈረመው እ.ኤ.አ በ2013 ነው። ኩባንያው ውሉን ከፈረመ በኋላ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ በመግባት ከሌሎች ቀደምት ኩባንያዎች በተሻለ መልኩ ውጤትን ማስመዝገብ ችሏል።

 

 

ሰፊ የቆዳ ሥፋት ባላቸው የገናሌ እንደዚሁም የካሉብና ሂላላ አካባቢዎች ያለውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ምርመራ አጠናቆ የራሱን የሆነ የአዋጭነት ሥራ ለመስራት እስከዛሬ በኢትዮጵያ መሰል ሥራን ሲያከናውኑት እንደነበሩት በዘርፉ የተሰማሩት ኩባንያዎች በርካታ ዓመታትን አልፈጀበትም። ኩባንያው በተለይ ከፍተኛ መጠን ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ማግኘቱን ካሰበ በኋላ ቀጣይ እቅዱ የነበረው ምርቱን በምን መልኩ ለኤክስፖርት ማብቃት ነው።

 

ለዚህ ደግሞ ያለው አማራጭ በጂቡቲ ወደብ በኩል በጋዝና ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ አማካኝነት ምርቱን በማሻገር የምርቱን ድፍድፍ እዚያው ጂቡቲ በሚተከል ማጣሪያ ሂደቱን ጨርሶ በመርከብ በቀጥታ ወደ ቻይና ኤክስፖርት ማድረግ ነው። ይህ ሂደት በኩባንያው እንደዚሁም በኢትዮጵያና በጂቡቲ መንግስታት መካከል ሰፊ በሆነ ዝርዝር ጥናት ላይ ተደግፎ የሶስትዮሽ ውይይት ማካሄድን ጠይቋል። በስተመጨረሻ ድርድሩ በስኬት ተጠናቆ ሰባት መቶ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ ዝርጋታ እውን የሚሆንበት ሂደት ተጀምሯል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ጂቡቲ ኢትዮጵያ ኤክስፖርት የምታደርገውን የነዳጅና የጋዝ ምርትን ማስተናገድ የሚያስችላትን ልዩ የወደብ አገልግሎት መስጫ ግንባታን ስታከናውን ቆይታለች። እነዚህ ኢንቨስትመንቶች በተጨማሪ ኢንቨስትመንት ሊታዩ የሚችሉ ናቸው።

 

በኢትዮጵያ ከነዳጅ ሀብት ጋር በተያያዘ በተደረገ ጥናት አምስት ነዳጅ ሊገኝባቸው ይችላል ተብለው የተለዩ አካባቢዎች አሉ። እነዚህም አካባቢዎች ኦጋዴን፣ደቡብ ኦሞ፣ ጋምቤላ፣ የአባይ ሸለቆና ትግራይ አካባቢ ናቸው። በተለይ በኬኒያና በደቡብ ሱዳን የተገኘው የነዳጅ ሀብት በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ መሆኑ ከኦጋዴን በተጨማሪ የደቡብ ኦሞን እና የጋምቤላን አካባቢ የዚህ ሀብት መገኛ መሆንን የበለጠ ያሰፋዋል። አሁን በኦጋዴን ተረጋግጦ ወደ ምርት ሥራ የተገባበት የነዳጅ ሀብት ሌሎቹን የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች እንዲፈተሹ የሚያደርግ ይሆናል።

 

የኃይል ሚዛን ለውጥ

ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የሚታዩት በአፍሪካ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ግኝት እየጨመረ ሄዷል። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በአፍሪካ ናይጄሪያ፣ሊቢያ፣ አንጎላ፣ አልጄሪያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቻድ፣ ጋቦን፣ቱኒዚያ፣ ግብፅ፣ ካሜሮን፣ አይቮሪኮስትና ሞሪታኒያ በነዳጅ አምራችነት የተመዘገቡ ሀገራት ሲሆኑ በቅርቡም ኢትዮጵያና ኬኒያ ይሄንን ምድብ ተቀላቅለዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአፍሪካ ያሉ ነዳጅ አምራች ሀገራት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። አዳዲስ የነዳጅ ባለሀብት አፍሪካዊ ሀገራት እየተገኙ ያሉት ደግሞ የነባሮቹ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የነዳጅ ክምችት መጠን እያሽቆለቆለ መሄድ ጀምሯል የሚሉ ጥናቶች እየወጡ ባለበት ሁኔታ ነው። ይህም መጪው ጊዜ የአፍሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የሀይል ሚዛን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የተሻለ እየሆነ እንደሚሄድ ማሳያ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
155 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 420 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us