የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ምንዛሪ ችግር መፍትሄ

Wednesday, 18 July 2018 15:56

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሰኞ ለሶስት ቀናት የሥራ ጉብኝት የቆዩት የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂን ሸኝተው ሲመለሱ በዚያው በአየር መንገዱ ቪአይፒ ሳሎን መግለጫ በሰጡበት ወቅት አንደኛው የመግለጫቸው ርዕሰ ጉዳይ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ነው።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማሳሰቢያ አዘል መልዕክታቸው የውጭ ምንዛሪ በግላቸው ያከማቹ ግለሰቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ባንክ ሄደው እንዲመነዝሩ አለበለዚያም በቅርቡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሀገሪቱ ውስጥ ስለሚገባ ክስረት እንዳይደርስባቸው አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርቡም የኦፕሬሽን ሥራ የሚጀመር መሆኑንም አመልክተዋል። ሆኖም የኦፕሬሽኑ አይነት ምን እንደሆነ ግን አላብራሩም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሄድ የጥቁር ገበያውን አቅም ለማዳከም በሀይል ማሳደድ ከሆነ ችግሩ ከጊዜያዊ መፍትሄ ያለፈ እንደማይሆን በቅርቡ በሱዳን የታየው እርምጃና ውጤት በቂ ማሳያ ነው። ሱዳን የመገበያያ ገንዘቧን ምንዛሪ እየወደቀ መሄዱን ተከትሎ ህግ ጭምር በማውጣት በጥቁር ገበያ ያለውን እንቅስቃሴ በትሞክርም ይህ ሂደት የሰራው ለጥቂት ወራት ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ ግን እጅግ ሚስጥራዊ በሆነ ሁኔታ የጥቁር ገበያው ሥራ ቀጥሏል። ለጊዜው መፍትሄ ያስገኘ የመሰለው ቁጥጥር በመጨረሻ የባሰ የሱዳን ፓውንድን መውደቅ አስከትሏል።

 

በዚህ በዘላቂ የውጭ ምንዛሪ ችግር መፍትሄው ዙሪያ የኢኮኖሚ ባለሙያውን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ አናግረን የሚከተለውን ጠቅለል ያለ ሀሳብ አጋርተውናል።

 

 

***        ***        ***

 

አሁን መንግስት ያለበትን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት። ይህንን ችግር ከሚወሰዱት እርምጃዎች መካከል በሌሎች አካላት በቀጥታ የሚሰጥ የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ ነው። ይህ ድጋፍ በቅርቡ በተባበሩት አረብ ኤሜሬት በኩል ታይቷል። ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ ተደርጓል። የዓለም ባንክና ሌሎች አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ሀገራት በመሰል ችግር ውስጥ ሲገቡ መፍትሄ የሚያፈላልጉባቸው የአሰራር ዘዴዎች አሏቸው። በመሆኑም ቀጥተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ አንዱ ችግሩን በጊዜያዊነት ማቃለያ መንገድ ነው።

 

ሆኖም ችግሩን በዘለቄታዊነት ለመፍታት ከወዲሁ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች አሉ። ከእነዚህም እርምጃዎች መካከልም የመጀመሪያው ቀደም ሲል የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ቀዝቀዝ ማድረግ መቻል ነው። ምክንያቱም ፕሮጀክቶቹ ግዙፎችና ብዛትም ስላላቸው የሚጠይቁትም የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ነው። 19 ግድብን በአንድ ጊዜ መገንባት አይቻልም። በመሆኑም አሁንም በፕሮጀክቶች የልማት ቅደም ተከተል ዙሪያ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል።

 

ሌላው የውጭ ተቋራጮችን ይመለከታል። አንዳንድ የውጭ ኩባንያዎች የግንባታ ጨረታ የሚያሸንፉት በሀገር ውስጥ ገንዘብ ሥራቸውን ለማከናወን ነው። ሆኖም እነዚህ ኩባንያዎች ሥራቸውን በብር አከናወኑ ቢባልም በመጨረሻ ትርፋቸውን መንዝረው የሚወስዱት በዶላር ነው። ከመንግስት ጋር የገቡት ውል ስለሌላቸው ባንክ ምንዛሬውን አይሰጣቸውም። ይህም በመሆኑ እነዚህ ባለሀብቶች ምንዛሬውን ለማግኘት ወደ ጥቁር ገበያው ነው የሚሄዱት። ይህ ሁኔታ ደግሞ በጥቁር ገበያውና በህጋዊው የምንዛሪ ገበያ መካከል ያለውን ክፍተት እያሰፋው የሚሄድ ይሆናል። በመሆኑም ይህ ጉዳይ በሚገባ ሊፈተሸ ይገባል።

 

ሌላው ሊታይ የሚገባው ጉዳይ አስመጪዎች ኤል ሲ ለመክፈት በባንክ በኩል የሚወስድባቸው ረዥም ሂደትና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትም ጉዳይ ነው። ቢሮክራሲው ሲበዛ ባለሃብቱ በቀጥታ ወደ ጥቁር ገበያው ነው የሚያመራው። በመሆኑም የኤል ሲው ቢሮክራሲ ጉዳይ በሚገባ መፈተሸ አለበት።

 

ከዚህ ውጪ ያለው ወሳኝ ጉዳይ በዚች ሀገር ውስጥ የውጭ ባንኮች ገብተው እንዲሰሩ ማድረግ ነው። የውጭ ባንኮች አዲስ ካፒታልና የውጭ ምንዛሪ ይዘው ስለሚመጡ የሚኖራቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እነዚህ ባንኮች በጥርጣሪ ውስጥ እንዲወድቁ ያደረጋቸው ከሰሩ በኋላ ሀብቱ ይዘው ይሄዳሉ በሚል ነው። እውነታው ግን ይህ አይደለም። አብዛኞቹ የውጭ ባንኮች መሰረታቸው አውሮፓና አሜሪካ ነው። የእነዚህ ሀገራት ኢኮኖሚ ደግሞ ለዘመናት በከፍተኛ እድገት ውስጥ ካለፈ በኋላ የማዝገም ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። ይህ አይነቱ ኢኮኖሚ ብዙም ለባንኮች አይመችም። በመሆኑም አብዛኞቹ ባንኮች ከአውሮፓና አሜሪካ ይልቅ ወደ ሩቅ ምስራቅና ሌሎች የእስያ ሀገራት መስፋፋትን መርጠዋል። ለእነዚህ ሀገራትም እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ሀብታቸውን ከዚያ አሽሽተው መሄድ ይቅርና እንደውም የበለጠ እየደረጁ ነው የሄዱት። ዋናው የሀገሪቱ የፖሊና የአሰራር ምቹነት ነው።

 

ሌላው በሀገሪቱ ወሳኝ መፍትሄ የሚሆነው በቅርቡ ወደ ግሉ ዘርፍ ይዘዋወራሉ የተባሉት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ የልማት ድርጅቶች ለውጭ ኩባንያዎች አክስዮን ሲሸጡ የውጭ ምንዛሪም እያስገኙ ይሄዳሉ። ይህም ሁኔታ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አቅም እያሳደገው የሚሄድበት ሁኔታ ይፈጠራል።

 

ከሁሉም በላይ ወሳኙ ሥራ ኤክስፖርትን ማሳደግ ነው። ለውጭ ምንዛሪ አስተማማኝ ግኝት ኤክስፖርትን ማጠናከርና ማሳደግ ብቻ ነው። ይህንን ማድረግ ግድ ይላል።

 

ከዚህ ውጪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የውጭ ምንዛሪ በስፋት ይገባል ያሉትን በተመለከተ በዝርዝር የተነገረ ነገር ስለሌለ ይህ ነው ብሎ መናገር ያስቸግራል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
139 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 70 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us