የብሔራዊ ባንክና የንግዱ ማህበረሰብ የፊት ለፊት ውይይት

Wednesday, 25 July 2018 13:19

 

የንግዱ ማህበረሰብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጋር ቀደም ሲል ባደረገው ውይይት በርካታ ችግሮች መነሳታቸው ይታወሳል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በንግዱ ማህበረሰብ በኩል በርካታ ቅሬታዎችና ጥቆማዎች ቀርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ጥያቄዎችም የቀረቡበት ሁኔታ ነበር። የተነሱትን ጥያቄዎች ተከትሎም ጥያቄዎቹ በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲሰጥባቸው በማሰብ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት አስተባባሪነት ባለፈው ሀሙስ ሀምሌ12 ቀን 2010 ዓ.ም የንግዱ ማህበረሰብ አካላትና የብሄራዊ የሥራ ኃላፊዎች ውይይት አድርገዋል።

በዚሁ ውይይት ላይ የብሕሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ዋና ዋናዎቹ የውይይቱ ርዕሰ ጉዳዮች የነበሩት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና ፍትሃዊ የውጭ ምንዛሪ ክፍፍል እንደዚሁም ከብድር አቅርቦትና አመላለስ ጋር ነበሩ። ከዚሁ ውይይት ጋር በተያያዘ የተነሱትን ሀሳቦችና የተሰጠባቸውን ምላሾች እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

 

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ህግ መሰረት አንድ የውጭ ባለሀብት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ የሚጠበቅበት በዶላርና በሀገሪቱ ተቀባይነት ባላቸው ሌሎች የውጭ ምንዛሪ ገንዘቦች ነው። ባለሀብቶቹ በውጭ ምንዛሪ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የመገደዳቸውን ያህል ምርቶቻቸውን አምርተው በሀገር ውስጥ በብር ከሸጡ በኋላ በባንክ አሰራር መሰረት በውጭ ምንዛሪ ቀይረው ትርፎቻቸውን የመሰብሰብ መብቱም አላቸው።

 

ሆኖም አንድ ሀገር የውጭ ምንዛሪ የማመንጨት አቅሙ እየተዳከመ በሚሄድበት ወቅት ይህንን ሀገራዊ ግዴታ የመወጣት አቅሙን የሚያጣበት ሁኔታ ይኖራል። በዚህም ወቅት ተጨማሪ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት የሚዳከምበት ሁኔታ ይኖራል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሰሱ የውጭ ባለሀብቶች ትርፎቻቸውን መንዝረው ለመውሰድ እንደዚሁም ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለማከናወን ከመንግስት በኩል በቂ የውጭ ምንዛሪ እየቀረበላቸው አለመሆኑን በመግለፅ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ ለጊዜው ያለባቸውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚያቃልሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር በመፍትሄ ሀሳብነት ሲያቀርብ ቆይቷል። አንዳንዶቹ ኩባንያዎች ከመነሻው ለኤክስፖርት ምርት የገቡ በመሆናቸው በዚህ ረገድ ቅሬታው የለባቸውም። ሆኖም ከዚህ ውጭ ያሉት ግን ከመነሻው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ሲሰማሩ ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት የማድረግ ግዴታ ውስጥ ያልገቡ በመሆናቸው “የራሳችሁን የውጭ ምንዛሪ ወጪ ለመሸፈን ምርቶቻችሁን ኤክስፖርት ማድረግ አለባችሁ” ተብለው ሊገደዱ የሚችሉበት አሰራር አይኖርም።

 

መንግስት የውጭ ባለሀብቶቹ በቻሉት መልኩ ኤክስፖርት በማድረግ የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ ወጪ እንዲሸፍኑ የተለያዩ ጫናዎችን ከማሳደር ባሻገር በምንዛሪው አቅርቦት በኩልም ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በተሻለ ለውጭ ባለሀብቶች ሲሰጥ ቆይቷል። የውጭ ምንዛሪው ለኢቨስትመንት ማስፋፊያ፣ለግብዓት ጥሬ ዕቃ እንደዚሁም ለትርፍና ለሌሎች ወጪዎች የሚያገለግል ሲሆን በዚህ ረገድ የሚታየው ለውጭ ባለሀብቶች ቅድሚያ የመስጠቱ ጉዳይ በሀገር ውስጥ በኩል ቅሬታ የፈጠረ መሆኑን በዚሁ መድረክ ላይ በስፋት ተነስቷል። ባለሀብቶቹ ጥሪታቸውን አሟጠውና ከባንክ ተበድረው የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ውስጥ ከገቡ በኋላ የግብዓት ምርቶችንና የመለዋወጫ መሳሪያዎችን ከውጭ ለማስመጣት የውጭ ምንዛሪ በሚጠይቁበት ወቅት በመንግስት በኩል ቅድሚያ የሚሰጠው ለውጭ ባለሀብቶች በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ አፈቃቀዱ ፍትሀዊነት የሚጎለው መሆኑን በማመልከት ሊሰተካከል የሚገባው መሆኑን ገልፀዋል። ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘም ኢንዱስትሪዎቻቸው በተገቢው የማምረት አቅማቸው ማምረት ባለመቻላቸው ለኪሳራ ከመዳረግ ባለፈ የባንክ ብድሮቻቸውን ሳይቀር መክፈል እየተሳናቸው የሄደበት ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ በሀገሪቱ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ ችግርን ከመሰረቱ ሊታይ የሚገባ መሆኑን በመግለፅ ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚገኝበትን አካሄድንም ጠቁመዋል። እንደሳቸው ገለፃ መንግስት አሁን ካለው ውስን የውጭ ምንዛሪ አቅም ጋር በተያያዘ እየተሰራ ያለው ያንኑ ውስን ሀብት የማቃመስ ሥራ ነው። እንደ እሳቸው ገለፃ አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር በቀጥታ የሚያያዘው ከግብርናው፣ከኢንዱስትሪው እንደዚሁም ከአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ ካለመሆን ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

 

እንደ ዶክተር ይናገር ገለፃ ሀገሪቱ ልታመርታቸው የምትችላቸው እንደ ስንዴ፣ስኳርና ዘይትን የመሳሰሉ የፍጆታ ምርቶች በስፋት በውጭ ምንዛሪ እየተገዙ ሀገር ውስጥ መግባታቸው በውጭ ምንዛሪ ወጪው ላይ የራሱን ጫና አሳድሯል። እንደሳቸው ገለፃ በተለይ የስኳር ምርትን በተመለከተ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ምርቱ ለውጭ ገበያ ቀርቦ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪን እንዲያመጣ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ይቅርና በሁለተኛውም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሳይቀር ሀገሪቱ የስኳር ምርትን ከውጭ እያስገባች መሆኗን አመልክተዋል።

 

ከዚህ ውጭም የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመፍታትና አዲስ ካፒታልን በሀገሪቱ ለመፍጠር ከሀገር ውስጥ ባንኮች በተጨማሪ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ቢደረግ የተሻለ ይሆናል የሚል ሀሳብም በተሰብሳቢዎች በኩል ቀርቧል። ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ ዶክተር ይናገር በሰጡት ምላሽ ሀገሪቱ ከቀሪው የዓለም ክፍል ተገልላ ልትኖር የማትችል መሆኗን አመልክተው በዚህ በኩል ቀጣይ የሚኖረውን አካሄድ በተመለከተ ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።

 

በተለይ አሁን ባለው የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠና ሥምምነት እንደዚሁም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገችው ባለው ጥረት ገበያን እየከፈቱ መሄድ ግድ መሆኑም ተመልክቷል። ከዚህም በተጨማሪ በሚበዛው የዓለም ክፍል የሚዘወተረው የአክስዮን ገበያን ለማስጀመር ሰፊ ጥናት የተደረገ መሆኑን በዶክተር ይናገር በኩል ተመልክቷል።

 

ሌላኛው የውይይቱ አጀንዳ የነበረው በብሄራዊ ባንክ ስለሚወጡት መመሪያዎች ነው። አንዳንዶቹ መመሪያዎች በጥልቀት የንግዱ ማህበረሰብ ሳይመክርባቸው የሚወጡ በመሆናቸው ትግበራ ላይ ችግር የሚገጥማቸው መሆኑም ተመልክቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን መመሪያዎቹ የወቅቱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እየታዩ እንዲሻሻሉ የሚደረግበት ሁኔታ አለመኖሩም እንደ አንድ የንግዱ ዘርፍ ተግዳሮት ተደርጎ ተመልክቷል። አንዳንድ መመሪያዎች ደግሞ በየጊዜው የሚቀያየሩና ከዚሁ ጋር በተያያዘም ለአሰራ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ መሆኑም በተሰብሳቢዎች በኩል በቅሬታነት ተነስቷል።

 

ለዚሁ ቅሬታ ዶክተር ይናገር በሰጡት ምላሽ “ አሁን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ የማይገልፁ መመሪያዎች አሉ” ካሉ በኋላ፤ እነዚህንም መመሪያዎች እንዲሻሻሉ ለማድረግም ይሄንን ጉዳይ የሚመለከት ኮሚቴ የተቋቋመ መሆኑን ጠቆም አድርገዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን መመሪያዎቹ ረዥም እድሜ በስራ ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ የግድ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ጥልቀወ ውይይት ሊደረግባው የሚገባ መሆኑንም ጭምረው አመልክተዋል።

 

ከክስረት ጋር በተያያዘ በስፋት የሚነሱ “የብድር ይራዘምልን” ጥያቄዎች መኖራቸውን ያመለከቱት ዶክተር ይናገር፤ ይህ ጉዳይ በንግዱ ማህበረሰብ በኩል በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባ መሆኑን ገልፀዋል። ባንኮች ለነጋዴው የሚያበድሩት ገንዘብ ከህብተረሰቡ በቁጠባ መልክ የተሰበሰበውን ገንዘብ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፤ ባንኮች የብድር ሁኔታን በአግባቡ መቆጣጠር ካልቻሉ ሊያስከትል የሚችለው ውጤት ከባድ መሆኑን ገልፀዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1081 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 969 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us