53 ሚሊዮን ብር የፈጀው የአዳማ ማስተር ፕላን ይፋ ሆነ

Wednesday, 25 July 2018 13:26


“የከተሞቻችን እድገት የሕንፃ ዋሻ እየሆኑ ነው”

አቶ መስፍን አሰፋ

የአዳማ ከንቲባ

 

ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዳራሽ 53 ሚሊዮን ብር የፈጀው ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት የሚቆየው የአዳማ ከተማ ማስተር ፕላን ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህ ዝግጅት ለማስተር ፕላኑ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ባለሐብቶች እና ተቋማት ከአስተዳደሩ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ያገኘናቸውን የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋን ስለ ማስተር ፕላኑ እና ስለ አዳማ ከተማ ጉዳዩች በተመለከተ ቃለ-ምልልስ አድርገንላቸዋል፡፡

አቶ መስፍን አሰፋ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ናቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በከተማ አስተዳደር ሰርተዋል። ለሶስተኛ ዲግሪያቸውን የመመረቂያ ጽሁፋቸውን እየሰሩ ይገኛሉ።

አሜሪካን ሀገር በሚገኝ ዓለም ዓቀፍ የሳይንስ ጆርናል ሁለት ጽሁፎች አሳትመዋል። አንደኛው፣ የከተማ ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፤ ሁለተኛው፣ ‘city resilience’ በተመለከተ በለገጣፎና በአዲስ አበባ ላይ ሰርተው፤ አሳትመዋል።

አቶ መስፍን ሃያ አራት ዓመት የስራ ልምድ አላቸው። ይኸውም፤ በአዲስ አበባ አስተዳደር ከተማ የንግድ ቢሮ ኃላፊ፤ የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፤ የለገጣፎ ለገዳዲ ከንቲባ፤ በኦሮሚያ ፀጥታና አስተዳደር ውስጥ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ የኃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ኃላፊ፤ የሱልልታ ከተማ ምክትል ከንቲባ፤ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።

ሰንደቅ፡-ለቀጣይ አስር ዓመታት የተነደፈው ማስተር ፕላን ይዘት ምን ይመስላል? ምንስ አዲስ ነገር አለው?

አቶ መስፍን አሰፋ፡-ለከተማው ትልቅ ትርጉም ያለው ማስተር ፕላን። በቀጣይ አሰር ዓመታት ውስጥ በአዳማ ከተማ ምን ሊሰራ ይችላል? ከተማውስ ምን ዓይነት ቅርጽና ይዘት ይኖረዋል? የሚለውን ከወዲሁ ለማየት ያስቻለን በበርካታ ጥናቶች ላይ የተመሰረተ ዕቅድ ነው። ምን ምን መካተት እንዳለበት በጥናቱ ታይቷል። ይህም ሲባል የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥናቶች ተካተውበታል። አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ የሚያርፈው ምንድን ነው? ለመኖሪያ ነው? ለሪል እስቴት ነው? ለኢንዱስትሪ ዞን ነው? ለፋብሪካ ግንባታ ነው? ለአረንጓዴ ቦታ ነው? እንዲሁም የከተማው መሰረተ ልማት ምን ይመስላል? መንገዶች እንዴት ነው የሚሰሩት? በየትኛው ቦታዎች ላይ ነው መሰረተ ልማቶች የሚዘረጉት? የሚለውን ሁሉ ያቀፈ ማስተር ፕላን ነው።

በዚህ መዋቅራዊ ፕላን ውስጥ ለየት የሚለው ጉዳይ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለመገንባት አቅደናል። በዓለም ላይ የሚገኙ ተመሳሳይ የአየር ፀባይ ያላቸው ሀገሮች በከተማቸው ሰው ሰራሽ ሐይቅ በመገንባት ከተማቸውን ውብ ከማድረግ ባለፈ፤ ነፋሻ አየር በከተማ ውስጥ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። የአዳማ ከተማ አየር ፀባይ እንደሚታወቀው ወደ ቆላ የአየር ፀባይ የሚያደላ ነው። በከተማችን ውስጥ ነፋሻ አየር መፍጠር የሚያስችል የተፈጥሮ ወንዝ ወይም ሀይቅ የለም። በአቅራቢያችን የሚገኘው የአዋሽ ወንዝ ብቻ ነው። ሰባት ኪሎ ሜትር ከከተማችን ይርቃል። ይህንን የአዋሽ ወንዝ ጠልፈን ወደ ከተማችን በመሳብ ሰው፣ ሰራሽ ሐይቅ እንፈጥራለን። ይህንን ስናደርግ የተዋበች ነፋሻማ የስምጥ ሸለቆ ውብ ከተማ እናደርጋታለን።

ከዚህም በተጨማሪ የነበሩና ወቅታዊ ችግሮችን መፍታት በሚያስችለን ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ፕላን ነው። ቀጣዩን የከተማችን እድገትና ለውጥን ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ ፍላጎቶችን ታሳቢ አድርገን ነው፣ ማስተር ፕላኑን የቀረጽ ነው። ከተማችን ለነዋሪዎቿ አመቺ፣ ዘመናዊ፣ ከዓለም ከተሞች ደረጃዋን የጠበቀች ተወዳዳሪ ከተማ እንድትሆን ከተፈለገ፤ ይህንን መዋቅራዊ ፕላን በጥብቅ የሥራ ዲሲፒሊን ማስፈጸም ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ የታሰበውን መዋቅራዊ የአዳማ ከተማን ማስተር ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ፤ የሚታሰብ አይደለም። ስለዚህም፣ የከተማው አስተዳደር፣ ካቢኔዎች እንዲሁም እስከታችኛው የማስፈጸሚያ አካላት ድረስ የተቀናጀና ቁርጠኝነት የተላበሰ አመራር በመስጠትና የማስፈጸሚያ ስልቶችን በመንደፍ ተግባራዊ ለማድረግ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል።

ሰንደቅ፡-ለዚህ መዋቅራዊ ማስተርፕላን እገዛ ያደረጉላችሁ ተቋማት እነማን ናቸው?

አቶ መስፍን አሰፋ፡-በዚህ ጥናት ውስጥ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ትልቅ ሥራዎች ሰርቶልናል፤ ከፍተኛ ድርሻም አለው። እንዲሁም በአሮሚያ ከተማዎች ፕላን ኢንስቲትዩት ማሕራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥናቶች እገዛ ተደርጐልናል። በዚሁ አጋጣሚ ለስራችን መቃናት እገዛ ላደረጉልን ባለድርሻ አካላት በሙሉ በአስተዳደሩ ስም አመሰግናለሁ።

ሰንደቅ፡-የከተማው ማስተር ፕላን የዲጂታል ዳታዎችን ያካተተ ነው?

አቶ መስፍን አሰፋ፡-አዎ፣ ሁሉንም ያካተተ ነው። ኦርቶፎቶ አለው። በጂአይኤስ የታገዘ ነው። መሬት ላይ ያለውን እያንዳንዱ ነገር ለቅሞ መሬት ላይ ለማዋል “local development plan” የተወሰነውን ተሰርቷል። ቦታዎችን ሸንሽነን ለይተን በቀላሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲነበቡ ለማድረግ እየሰራን ነው። የተወሰነውንም አውትሶሰርስ አድርገን ለማጠናቀቅ እቅድ ይዘናል።

ወደዲጂታል ሲስተም በመግባታችንም በቀጣይ በከተማችን ውስጥ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎት ለማስቀረትና ለመግታት መሬታችን መዝግበን፤ በካዳስተር ለመያዝ እየሰራን ነው። ከንክኪ ነፃ የሆነ የከተማ መሬት አጠቃቀምና አያያዝ በቅርቡ ይኖረናል።

ሰንደቅ፡-በዚህ የአዳማ ማስተር ፕላን የባለሃብቶች ተሳትፎ እንዴት የሚገለጽ ነው?

አቶ መስፍን አሰፋ፡-የአዳማ ባለሃብቶች በመቶ ሚሊዮን ብር በሚቆጠር ድጋፍና መዋጮ ከተማውን ያለሙ ናቸው። በዚህ መድረክም እውቅና የተሰጣቸው አሉ። የባለሃብቶቹ ድጋፍ፤ በገንዘብ፣ በሙያ፣ በጉልበት ሁሉንም የሚያካትቱ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ባለሃብቶቹ በልማቱ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ከፍተኛ አመራር የሰጡም የቀድሞ የከተማው አስተዳደር ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደለም።

በተለይ ከሶማሌ ክልል አለሃጢያታቸው ተፈናቅለው የመጡ ከ6ሺ በላይ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች (አባት፣ እናትና ልጆች) በከተማችን ውስጥ አሉ። ይህንን ያህል መጠን ያለው የሕብረተሰብ ክፍል በአንድ ጊዜ በከተማችን ውስጥ ተፈናቅሎ ሲመጣ፣ ምን ማለት እንደሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚገነዘበው ነው። መንግስት ብቻውን ሊወጣው የማይችለው እዳ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አልነበረም። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአዳማ ባለሃብቶችና ነዋሪዎች ያደረጉት ድጋፍ መቼም የሚዘነጋ አይደለም። ከተፈናቀሉ ዜጎች ጎን በመቆም፤ ምግብ በማቅረብ፣ ልብስ በመስጠት፣ እንዲሁም የሞራል የማቴሪያል ድጋፎችን በማቅረብ፣ ከጎናቸው መሆናቸውን በመግለጽ ጭምር ወገንተኝነታቸውን ሕዝባዊነታቸውን አሳይተዋል።

የከተማችን ባለሃብቶች ላደረጉት ከፍተኛ ተሳትፎም ሽልማትና እውቅን በከተማ መስተዳድሩ ሰጥተናቸዋል። በቀጣይም ከጎናችን በመሆን ልማቱን እንደሚያግዙ ያለን ተስፋ ከፍተኛ ነው።    

ሰንደቅ፡-በፀደቀው ማስተር ፕላን፣ ለሕፃናትና ለወጣቶች የሚሆኑ የመዝናኛ ቦታዎች በተለይ የእግር ኳስና የኪነጥበብ ማዘውተሪያ ቦታዎች ተካተውበታል?

አቶ መስፍን አሰፋ፡-ይህ ጥያቄ በጣም ተገቢ ነው። ምክንያቱም የከተሞቻችን እድገት ሲታይ የሕንፃ ዋሻዎች እየሆነ መምጣታቸውን የሚካድ አይደለም። የሚገርመው በአብዛኛው የሚሰሩ ማስተር ፕላኖች ላይ ለልጆች መጫወቻ ቦታዎችና ለአካባቢ አረንጓዴ ቦታዎች ተካተው ነው የሚሰሩት። ሆኖም ግን አንዳንድ ኃላፊነት የሚጎድላቸው የሥራ መሪዎችና ሰግብግብ ነጋዴዎች በመመሳጠር ላልተገባ ግንባታ ያውሏቸዋል። አንዳንድ የከተማ ውሃ መውረጃ ቦታዎችን ደፍነው ለቤቶች ግንባታ የሚያውሉ አሉ። ይህም በመሆኑ ከተሞች በዝናብ ወቅት በጎርፍ እንዲጠቁና ጉዳት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናሉ።

ለምሳሌ በአዳማ በርካታ ቦታዎች ተዘግተው ከተማው ውስጥ ውሃ መፍሰሻ ጠፍቶ የጎርፍ ችግር አለ። በውሃ መፍሰሻ ቦታዎች ቤቶች ተገንብተዋል። ማስተር ፕላኑ ስንመለከተው ለቤት ግንባታ ባልተፈቀደ ቦታ ተገንብተው እናገኛለን። ለሕፃናት፣ ለወጣቶች፣ ለአዛውንቶች መዝናኛ የተሰጡ ቦታዎች ላልተገባ ስራ ውለው በከተማችን እናያለን። የከተማ መለኪያው በፎቅ ወይም በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ብዛት አይደለም። በሰለጠነው ዓለም የከተማ መለኪያ ለሕፃናትና ወጣቶች መዝናኛ በሚሰጠው ሥፍራ፤ ለአዛውንቶች አየር ማውጫ የሚሆኑ ቦታዎች በመተው፤ ለአረንጓዴ ልማት በየሚሰጡት ቦታ ነው።

በአዳማ ለመጪው አስር ዓመታት የተነደፈው ማስተር ፕላን ለአረንጓዴ ልማት፣ ለሕፃናት፣ ለወጣቶች እና ለአዛውንቶች ከፍተኛ ሥፍራ የሰጠ ነው፤ ብዙ ቦታዎች ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል። ሆኖም ግን ቦታ መሰጠቱ ብቻ በቂ አይደለም፤ እስከመጨረሻው ድረስ ተከታትሎ ማስፈጸም ከአስተዳደሩም ከነዋሪዎችም የሚጠበቅ ነው።

ሰንደቅ፡-ማስተር ፕላኑን ወደመሬት ለማውረድ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቅ ለመረዳት ከባድ አይደለም። ለመፈጸም የገንዘብ ምንጫቹ ምንድን ነው? በከተማ አስተዳደሩ ብቻ የሚሸፈን ነው?

አቶ መስፍን አሰፋ፡-ከፍተኛ ካፒታል እንደሚፈልግ አሻሚ አይደለም። ከሕብረተሰቡ ተሳትፎ ውጪ የሚታሰብ ማስተር ፕላን አይደለም። ሕብረተሰቡ አንደኛ አጋራችን እና የካፒታል ምንጫችን ነው፡ ሁለተኛው፤ ከተማ አስተዳደሩ የሚያስገባቸው የተለያዩ ገቢዎች አሉ። ከኪራይ፣ ከንግድ እንቅስቃሴዎች የሚያገኛቸው ገቢዎችም አሉ። እንዲሁም ከክልል መንግስት የምናገኘው ድጎማም አለ። መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ ድርሻም ይኖራቸዋል።

ሰንደቅ፡-በአዳማ ያለውን የውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ብዙ ርቀት መሄዳችሁ ቢታወቅም፣ አሁንም የውኃ እጥረት እንዳለ ቅሬታ የሚያቀርቡ ነዋሪዎች አሉ። የከተማዋ የቴሌኮሚኒኬሽን አቅርቦት ከከተማዋ እድገት ጋር ተመጣጣኝ አይደለም ይባላል። በእነዚህ ቅሬታዎች ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

አቶ መስፍን አሰፋ፡-የውኃ አቅርቦት እንደተባለው ትኩረት የሚፈልግ ነው። ለከተማው የሚቀርበው የውሃ መጠን ከሃያ ዓመት በፊት ታሳቢ የተደረገው የከተማው ነዋሪዎች ሕዝብ ቁጥር መጠን፤ በአራት በመቶ በየዓመቱ እያደገ ነው የመጣው። እንዲሁም ከተማው በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው። ከገጠር ወደ ከተማ የሚመጣው የሕዝብ ቁጥሩ መጠን ከፍተኛ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ተደረምረው፣ የከተማው የውሃ ፍላጎት በከፍተኛ መጠን አድጓል። ይህም ሆኖ ግን በከተማችን ውስጥ ያለው የውሃ መጠን ተደራሽነቱ በጣም የከፋ ነው የሚባል አይደለም። በአንፃራዊነት ከተወሰደም ከሌሎች ከተማ የተሻለ የውሃ አቅርቦት በከተማችን ውስጥ አለ።

በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ቁጥርና ከከተማው እድገት ጋር የሚጣጣም የውሃ አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠብቀን እናውቃለን። በቀጣይም ይህንን ፍላጎት ለማሟላት የሚገጥሙን ተግዳሮቶች በመፍታት የተሻላ የውሃ አቅርቦት በከተማችን እንዲኖር እንሰራለን።

ከመብራትና ከቴሌ ጋር የተነሱት ችግሮች አሁንም አሉ። ችግሮቹ መፈታት እንዳለባቸው እናምናለን። ከሚመለከታው ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ችግሮቹን እንፈታለን ብለን እናስባለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1088 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1030 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us