You are here:መነሻ ገፅ»Economy»ፀጋው መላኩ - Sendek NewsPaper
ፀጋው መላኩ

ፀጋው መላኩ

ከ74 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች ከአስራሶስት ዓመታት ጥበቃ በኋላም ቤት አላገኙም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ1997 ዓ.ም የከተማዋን ነዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ተጠቃሚ ለማድረግ ምዝገባ ባካሄደበት ወቅት ከ350 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መመዝገቡ የሚታወስ ሲሆን እንደ አዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ መረጃ ከሆነ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አስራሶስት ዓመታት በ11 ዙሮች ቤቶችን ገንብቶ ማስረከብ የቻለው ለ176 ነዋሪዎች ብቻ ነው።

በ2005 ዓ.ም በተካሄደው በዳግም ምዝገባው ወቅት የፍላጎት ለውጥ ያሳዩ ነባር ተመዝጋቢዎች በአዲስ መልኩ ከአዲስ ተመዝጋቢዎች ጋር እንዲካተቱ የተደረገ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል እጣ የወጣላቸውን ጨምሮ የፍላጎት ለውጥ ያሳዩ ተመዝጋቢዎች ሲለዩ በጊዜው በነባርነት የተመዘገቡት ነባር ተመዝጋቢዎች 137 ሺህ አካባቢ ነበሩ። በጊዜው ምዝገባው ሲካሄድ 20/80 እና 40/60 የቤት ፕሮግራሞችን ጨምሮ የተመዘገበው የከተማዋ ነዋሪ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ነበር። በጊዜው በተገባውም ቃል መሰረት ነባር ተመዝጋቢዎችን በሁለት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የቤት ተጠቃሚ በማድረግ መንግስት ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደ አዲስ ተመዝጋቢዎች ያዞራል ቢባልም፤ ሁለተኛው ምዝገባ ከተካሄደ ከአምስት ዓመታት በኋላም ከ75 ሺህ ያላነሱ ነባር የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች ገና የቤት ባለቤት መሆን አለመቻላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ከሰሞኑ ከነባር ሳይቶች በተሰበሰቡ 2 ሺህ ስድስት መቶ ቤቶች ላይ እጣ ያወጣ ሲሆን አንዳንዶቹ ሳይቶች ቤቶቹ እጣ ከወጣባቸውና ነዋሪዎች መኖር ከጀመሩ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ መሆናቸው ግርምትን የሚያጭሩ ሆነዋል። እጣዎቹ በጎተራ ኮንሚኒየም፣ በልደታ፣ እና ጀሞ ኮንደሚኒየም ሳይቶች ሳይቀር መውጣታቸው ቤቶቹ ለምን ያህል ዓመታት ይዘጉ ወይንም ሌላ ሰው ሲጠቀምባቸው ይቆይ ግልፅ አይደለም። አስተዳድሩ አሁንም በሚቀጥለው 2011ዓ.ም ነባር ተመዝጋቢዎችን ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት ለማድረግ እየሰራሁ ነው ብሏል።

 

ሳንሺግ ፋርማስዮቲካል በመባል የሚታወቀው የቻይና የመድኃኒት ፋብሪካ በዱከም ኢንዱስትሪ ዞን ያስገነባውን መድሃኒት ፋብሪካ ባለፈው እሁድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት አስመርቋል። ይኸው ለምርቃት የበቃው የመድኃኒት ፋብሪካ ግንባታው 85 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የፈጀ ሲሆን በ16 ሄክታር ላይ ያረፈ ነው። ይህም የመድኃኒት ፋብሪካ የመጀመሪው ደረጃ ሲሆን ቀጣይ ሁለተኛ ዙር የማስፋፊያ ግንባታም በቅርቡ የሚከናወን መሆኑ በዕለቱ ተመልክቷል።

 

ፋብሪካው ጉሉኮስን ጨምሮ በርካታ የመድኃኒት አይነቶችን የሚያመርት ነው። የሥራ እድልንም በተመለከተ ፋብሪካው ሶስት መቶ ለሚሆኑ ሰራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን 90 በመቶ የሚሆኑትም ሰራተኞች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን በዕለቱ በተደረገው ገለፃ ተመልክቷል።

 

በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ታን ጂያን በኢትዮጵያ ያለው የቻይና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ገልፀው እ.ኤ.አ በ2015 ከነበረው በኢትዮጵያ የቻይና የኢንቨስመንት አንፃር ሲታይ በ2017 የፍሰቱ መጠን በእጥፍ የተመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የቻይና ኢንቨስትመንት ፍሰት እየተቀዛቀዘ ነው የሚለውም ጉዳይ ሀሰት መሆኑን ገልፀዋል።

 

አምባሳደሩ ጨምረውም በቀጣይም ይህ የኢንቨስትመንት ፍሰት መጠን ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው መንግስት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እየሄደበት ያለውን ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥልበት መሆኑን አስታውቋል።

 

የፋብሪካው ሁለተኛ የማስፋፊያ ምዕራፍም ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚጀምር መሆኑ ታውቋል። ኢትዮጵያ ለተለያዩ መድሃኒት ግዢዎች በየዓመቱ እስከ 5 መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ወጪ የምታደርግ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን የአሁኑና የሌሎች መድሃኒት ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባት ግን ሀገሪቱ በመድሃኒት ምርት ራሷን እንድትችል ከማድረግ ባለፈ በኤክስፖረቱም ዘርፍ በመሳተፍ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ያስችላታል ተብሏል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት የመድኃኒት ኢምፖርትን ከማስቀረትና ምርቶቹን ወደ ውጪ ከመላክ ባሻገር የመጨረሻው ግቡ ሀገሪቱን በዘርፉ የአፍሪካ የመድኃኒት ማምረቻ ማዕከል (Africa’s Pharmaceutical Manufacturing Hub) ማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

 

ይህንንም እቅድ እውን ለማድረግ ቀደም ብሎ ሲሰሩ የነበሩ ሥራዎች መኖራቸውን አመልክተው ከእነዚህም ሥራዎች መካከለም ለዘርፉ ራሱን የቻለ የኢንዱስትሪ ፓርክን መገንባት መሆኑን በመግለፅ ለማሳያም የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጠቅሰዋል። ሳንሺግ ግሩፕ በፋርማሲዮቲካል ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በሥራ ላይ ያለ መሆኑን የኩባንያው ታሪክ ያመለክታል።

 

የሲንጋፖር አየር መንገድ የዓለምን ረዥሙን የአየር በረራ ሊጀምር መሆኑን አስታውቋል። በረራው ከሲንጋፖር ሻንጋይ ኤርፖርት አሜሪካ ኒውዮርክ የሚደረግ መሆኑን ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አስታውቋል። ይህም ያለማቋረጥ የሚደረግ የ19 ሰዓት በረራ መሆኑን ዘገባዎቹ ጨምረው አመልክተዋል። ይህም ረዥም በረራ 16 ሺኅ 7 መቶ ኪሎ ሜትሮችን ይሸፍናል ተብሏል።

 

እንደ ትራቭለር ድረገፅ ዘገባ ከሆነ በመጪው ጥቅምት ወር አዲሱ በረራ የሚጀመረው በኤር ባስ A-350-900 ULR አውሮፕላን ነው። ሲንጋፖር 21 ይህ አይነት አውሮፕላን ያላት መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

 

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ እስከ ዛሬ ረዥሙ የማያቋርጥ የመንገደኞች አውሮፕላን በረራ ሪከርድ የተያዘ ሲሆን 17 ነጥብ 5 ሰዓታትን የሚፈጅ በረራ ነው። ይህም በረራ ከዶሃ እስከ እስከ ኦክላንድ የሚካሄድ ነው። አሁን ግን በአዲሱ የዓለማችን የመንገደኞች አውሮፕላን ሪከርዱ ተሻሽሏል።

 

ፋም አቢሲኒያ የትራንስፖርትና ቱሪዝም ፐብልኬሽን አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ጋር በመተባበር የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት መገናኛ ብዙኃን በሚኖራቸው ሚና ዙሪያ የግማሽ ቀን አውደ ጥናት አካሂዷል። በዚሁ ግንቦት 30 ቀን 2010 በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በተካሄደው አውደ ጥናት ጋዜጠኞች፣ የቱሪዝሙ ዘርፍ ባለሙያዎች የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የተለያዩ አካላት ተገኝተዋል።

 

 

የፋም አቢሲኒያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው አበበ በዕለቱ ኩባንያው ከተመሰረተ ገና የአንድ ዓመት ተኩል እድሜ ያስቆጠረ መሆኑን ገልፀው፤ የድርጅቱም መነሻ ራዕይ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ የራሱን አዎንታዊ አሻራ ማሳረፍ መሆኑን አመልክተዋል። ዋና ሥራ አስኪያጁ መንግስት የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማሳደግ የወሰዳቸውን በርካታ እርምጃዎች ጠቅሰው ይሁንና የሀገር ውስጥ የቱሪዝሙ ዘርፍ ግን ሊያገኝ የሚገባውን ያህል በቂ ትኩረት ያላገኘ መሆኑን አመልክተዋል። መንግስት ባለፉት ዓመታትም ዘርፉን ለመለወጥ በወሰዳቸው እርምጃዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራና የተለያዩ አካላትን ያቀፈ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽናል ምክር ቤት መመስረቱ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ራሱን ችሎ መቋቋሙና ቱሪዝም ቦርድን እውን መሆኑ በማሳያነት አመልክተዋል።

 

“በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ ወጣቶቻችን አሜሪካና አውሮፓን ለማወቅ የሚጥሩትን ሽራፊ ያህል ጊዜ አገራቸውን ለማወቅ አለማዋላቸው ለኢትዮጵያዊያን ወላጆች፣አሳዳጊዎች ራስ ምታት ሲሆን እንደ አገር እጅግ አሳሳቢ አደጋ ከፊታችን መደቀኑን የሚጠቁም ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ፤ ሌሎች አለማትን ማወቅ መልካም ቢሆንም አገርን መዘንጋት ራስን ከመዘንጋት ጋር እኩል መሆኑን አለመረዳት በራሱ ስህተት መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል።

 

 

በዕለቱ በሀገር በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ዙሪያ ዳሰሳዊ ጥናቶቻቸውን አቅርበዋል። በዚህ ዳሰሳም የዓለም የቱሪዝም ታሪክ፣ የኢትዮጵያ ንፅፅራዊ የቱሪስት ፍሰት፣ የገቢ ሁኔታ፣ የሀገር ውስጡ የቱሪዝም ኢንዱስትሪና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ተዳሰዋል። ከዳሰሳ ጥናት አቅራቢዎቹ መካከል በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ረዥም ዕድሜን ያሳለፉት ዶክተር አያሌው ሲሳይ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ዙሪያ አጠር ያለ ጥናትን አቅርበዋል። በሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ዙሪያ የዜጎች የጉብኝት ባህል አለመኖር፣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣የግንዛቤ እጥረት፣የሁኔታዎች ምቹ አለመሆንና የመሳሰሉት በእንቅፋትነት ተነስተዋል። የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ መጎልበት ለእርስ በእርስ ትውውቅ፣ለባህል ልውውጥ፣ ለስራ እድል መስፋትና ለመሳሰሉት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢሆንም የተሰጠው ትኩረት ግን አነስተኛ በመሆኑ ተገቢው ውጤት እየተገኘበት አለመሆኑ በአውደ ጥናቱ የተሳታፊዎች ውይይት ተመልክቷል። በዚህ ዙሪያም ዘርፉን ለማሳደግ ፋም አቢሲኒያ የትራንስፖርትና ቱሪዝም ፐብልኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑ ተመልክቷል። በዚህም ዜጎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን መጎብኘት እንዲችሉ ኩባንያው የተለያዩ የጉብኝት ፓኬጆችን በተመጣጣኝ ዋጋ ያዘጋጀ መሆኑም ተመልክቷል።

 

አውደ ጥናቱ እውን እንዲሆንም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶክተር አረጋ ይርዳው፣ የሬይንቦ መኪና ኪራይና አስጎብኚ ድርጅት እና ትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ እንደዚሁም ሳማንታ አስጎብኚና የመኪና ኪራይ ድርጅት የፋይናስና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል።

 

የዓለም ስኳር ድርጅት በኢትዮጵያ ሊያካሂድ ነው። ይህ ጉባኤ ለ53ኛ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል። ጉባኤው የሚካሄደው “Ethiopian Sugar Development - A way to Structural Transformation” በሚል መሪ ቃል መሆኑ ታውቋል። ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች፣ በስኳር ሥራ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ የሚዲያ አካላት የዚሁ ጉባኤ አካል መሆናቸውን ከስኳር ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

ይሄው ጉባኤ ከሰኔ 19 እስከ 21 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።

 

ኢትዮጵያ በዚህ ጉባኤ በዘርፉ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ አቅም በማሳየት የተለያዩ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ትጠቀምበታለች ተብሏል። በዚሁ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከዓለም ስኳር ድርጅት 87 ተሳታፊዎች እንደዚሁም 4 መቶ እንግዶች ከሀገር ውስጥ የሚሳተፉ መሆኑን መረጃው ያመለክታል። ኢትዮጵያ በስኳሩ ዘርፍ ከዓመታት በፊት ብዙ አቅዳ ይህ ነው የሚባል አመርቂ ውጤትን ያላሰመዘገበች ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም ስኳርን ከውጪ ከማስገባት ባለፈ ምርቱ በገበያው ውስጥ እንደ ልብ የሚገኝበት ሁኔታ የለም። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በ2002 ይፋ ሲደረግ በእቅዱ አጋማሽ ማለትም በ2004 በጀት ዓመት አካባቢ ሀገሪቱ በስኳሩ ዘርፍ ራሷን በመቻል ወደ ኤክስፖርት ትንደረደራለች የሚል ሀሳብ ቢኖርም ይህ እቅድ በሁለተኛው ትራንስፎርሜሽንም እቅድም ሊሳካ አልቻለም።

 

ከተንዳሆ እስከ ኩራዝ እንደዚሁም ከወልቃይት እስከ ጣና በለስ ያሉት ስኳር ፋብሪካዎች አንዳቸውም ወደ ማምረት ሥራ የገቡበት ሁኔታ የለም። ይህ ብቻ ሳይሆን በፕሮጀክቶቹ የወጣው ገንዘብም ሀገሪቱን በከፍተኛ የውጭ እዳ ውስጥ እንድትዘፈቅ ያደረጋት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።


የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት መፅሐፍ

 

በቅርቡ በኢትዮጵያ አኮኖሚ ዙሪያ የሚያጠነጥን አንድ መፅሀፍ ለገበያ በቅቷል። መፅሀፉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን ፀሀፊው አቶ ጌታቸው አሰፋ የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው። መፅሀፉ በ387 ገፆች ተቀናብሮ የተዘጋጀ ሲሆን በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንም በውስጡ ዳሷል።

ፀሐፊው አቶ ጌታቸው አስፋው በሙያው ረዥም ዓመታትን የሰሩ ሲሆኑ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው የብሄራዊ ኢኮኖሚ እቅድ ባለሙያ ሲሆኑ በቀድሞው በኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ወይም በአሁኑ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በሙያቸው አገልግለዋል።

     ቀደም ብሎም በአሥመራ ዩኒቨርስቲ ለሶስት ዓመታት በገጠር ልማትና በታዳጊ ሀገራት የመልማት ችግሮች ዙሪያ በመምህርነት ሙያ ሰርተዋል። ባለፉት ሶስት ዓመታትም በሪፖርተር ጋዜጣና በውይይት መፅሄት ላይ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የዳሰሱ ፅሁፎችን ለአንባቢያን ሲያደርሱ የቆዩ መሆናቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል። አቶ ጌታቸው ይህንን ሙያዊ መፅሃፋቸውን ባሳለፍነው ቅዳሜ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አስመርቀዋል። በዕለቱም በመፅሀፉ አጠቃላይ ጭብጥና ይዘት ዙሪያ የተለያዩ ምሁራን የየራሳቸውን አስተያየቶች ሰጥተውበታል።

 

በሀገራችን አሁን ካለው የፖለቲካ፣ ልብወለድ፣ ታሪክና የወግ ፅሁፎች ባለፈ በዚህ ደረጃ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ የተፃፈ መፅሀፍ የለም ብሎ መናገር ይቻላል። ቢኖሩም በተቋም ደረጃ የተፃፉ ወይንም ደግሞ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እገዛ ለህትመት የበቁ ናቸው። እነዚህም ጥናቶች ቢሆኑ ታትመው በገበያው ላይ ለህዝብ የሚቀርቡ ሳይሆኑ ይመለከታቸዋል ተብለው ለሚታሰቡ ተቋማት የሚበተኑ በመሆናቸው በማንኛውም አንባቢ እጅ የሚገቡ አይደሉም። በዚህ በኩል ሲታይ አቶ ጌታቸው የተለየ ሥራን ሰርተዋል ያስብላል።

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት? እንደገፁ ብዛት በይዘቱ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ዳስሷል። ከዳሰሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ በዚህ ወቅት አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው የዋጋ ንረት ይገኝበታል። አቶ ጌታቸው በዚሁ መፅሀፋቸው ለዋጋ ንረት መፈጠር ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች መኖራቸውን በሚከተለው መልኩ በመግለፅ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያዛምዱታል።

 

“የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በዋናነት በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መብዛት እንደሆነ ካወቅን ዘንዳ ይህ የጥሬ ገንዘብ መብዛት ዋጋን እንዴት እንደሚያንር እንመልከት። የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በሁለት መንገድ ነው። አንዱ የሸማቹ የመግዛት አቅሙ አድጎ ለመሸመት ውድድር ውስጥ ሲገባና ወድ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ሲሆን ነው። ሁለተኛው የዋጋ ንረት ምክንያት በአምራቹ ላይ ግብር ወይንም የሰራተኛ ደመወዝ ወይም ጥሬ ዕቃ ዋጋ ጨምሮበት ምርቱን ሲያስወድድ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የዋጋ ንረት የተፈጠረው በሁለቱም መንገድ ነው” ፀሀፊው ከዚሁ የዋጋ ንረት ጋር ምክንያት ጋር በተያያዘ ሀሳባቸውን በሰፊው በማብራራት ለዋጋ ንረት ምክንያት ነው ያሉትን ሃሳብ በሚከተለው መልኩ ትንታኔ ሰጥተውበታል። “በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጨመር የፍላጎት ስበት የዋጋ ንረት ምክንያት እና በውጭ ምንዛሪ ተመን የብር ዋጋ መርከስ፣ በንግድ ትርፍ ግብር መጨመር፣ በጥሬ ዕቃ መወደድ በሚፈጠሩ የማምረቻ ወጪ ግፊት የዋጋ ንረት ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እንደሚጨምር ይገመታል።

 

የዋጋ ንረት የመንግሥት ዓላማ ማስፈፀሚያ ነው?

አቶ ጌታቸው በዚሁ መፅሀፋቸው የዋጋ ንረት የኢኮኖሚ መሳሪያ በመሆን አንዳንድ ጊዜ መንግስት የሚጠቀምበት መንገድ መሆኑንም አብራርተዋል።

ባለሙያው “የዋጋ ንረት የመንግስት ዓላማ ማስፈፀሚያ መሳሪያም ነው። የዋጋ ንረት ሀብታሙ ከደሃው ጥሬ ገንዘብ የሚነጥቅበት፤ ከነጠቀውም ውስጥ ለመንግስት የሚገባውን ግብር የሚሰጥበት ስለሆነ መንግስት ከሀብታሙ የሚሰበስበውን ግብር መጠን ከፍ ማድረግ ሲፈልግም ሆን ብሎ ጥሬ ገንዘብ ወደገበያው በመርጨት የዋጋ ንረት ይፈጥራል።

 

አቶ ጌታቸው ከዚህ ባለፈ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመግዛት አቅሙ እያሽቆለቆለ ሥላለው የብር መግዛት አቅም ሁኔታም በበርካታ ዓመታት ድምር ውስጥ ብር ዋጋውን በምን ያህል ደረጃ ዋጋውን እንዳጣ ከህዝቡ በተለይም ከደመወዝተኛው ኑሮ አንፃር በሚገባ ትንታኔ ሰጥተውበታል። ከኤክስፖርቱም ዘርፍ መዳከም ጋር በተያያዘ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎችንና ብዙም ውጤት እያመጡ አለመሆኑ በማስረጃ በተደገፈ መልኩ በሰፊው ተዳሷል። መፅሀፉ በአጠቃላይ ይዘቱ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በስፋት ዳሷል። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ከታሪክና ከዓለም አቀፉ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ጭብት አኳያም አያይዞ ሰፋ ያለ ትንታኔን ሰጥቶበታል።

 

ግብፅ ለወታደርና ለፖሊስ ጡረተኞች የ15 በመቶ የጡረታ ጭማሪ ያደረገች መሆኗን የአህራም ኦን ላይን ዘገባ አመልክቷል። በዚህም ጭማሪ መሠረት ዝቅተኛው የገንዘብ መጠን 125 የግብፅ ፓውንድ መሆኑ ታውቋል።

 

በግብፅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ከሄደው የዋጋ የኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በተለይ የጡረተኞች የኑሮ ሁኔታ እየከፋ መሄዱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ህጉ ተግባራዊ እንዲሆን ከፓርላማው ማፅደቅ በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱ ፊርማቸውን ማኖር የሚጠበቅባቸው ይሆናል። ሆኖም አንዳንዶች ጭማሪው ብዙም አይደለም በማለት መንግስት አሁንም የተሻሻለ ማሻሻያ እንዲያደርግ እየጠየቁ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

ባለፈው ግንቦት 23 በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል የተከፈተው ኢድ ኤክስፖ በመካሄድ ላይ ነው። ዝግጅቱም እስከ ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ኤክስፖ ላይ በርካታ ድርጅቶች ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን ይዘው የቀረቡ ሲሆን ከህንድ ከሶሪያና ከፓኪስታን የመጡ ተሳታፊዎችም የተገኙበት መሆኑ ታውቋል።

 

ይሄው በየዓመቱ በኢድ አልፈጥር ፆም ወቅት የሚካሄደው ኤክስፖ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር በየጊዜው ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሚሰራ ሲሆን በዚህ ዓመትም ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመት ጋር በጋራ በመሆን በትራፊክ አደጋ አስከፊነት ዙሪያ ለጎብኚዎች ግንዛቤ የሚሰጥበትን ሁኔታ ያመቻቸ መሆኑ ታውቋል።

በኤክስፖው ላይ፣አልባሳት የሃይማኖት መፃህፍት፣ የቤት እቃዎች፣ ጌጣጌጦችና የመሳሰሉት ምርቶች በስፋት ቀርበው ተመልክተናል። የዚሁ ዝግጅት አዘጋጅ የሆነው ሀላል ፕሮሞሽን በቀጣይ ኤክስፖውን በዓመት ሁለት ጊዜ ለማድረግ እቅድ ያለው መሆኑ በመክፈቻው ዕለት በተሰጠው ማብራሪያ ተገልጿል።

 

 

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከሰሞኑ የታክሲ ትራንስፖርት ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን ተገልጋዮች የአሁኑ ማሻሻያ የተጋነነ መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡ የታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት በአንፃሩ የታክሲ ታሪፍ ጭማሪው አነስተኛ መሆኑን ነው የገለፁልን፡፡


እስከዛሬ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪው ሲካሄድ የነበረው ከዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ ይሁንና የታክሲ ማህበራቱ ከነዳጅ ዋጋ ባለፈ የአንድ ተሽከርካሪ ግብዓቶች በርካታ በመሆናቸው የእነዚህም ግብዓቶች ዋጋ ታሳቢ ተደርገው የታክሲ ታሪፉ ጭማሪ ማሻሻያ ይደረግ የሚል የቆየ አቋም ነበራቸው፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ጥናቶች ሲደረጉ የቆዩ ቢሆኑም ይህ ነው የሚባል ጭማሪ ሳይደረግ የቆየ መሆኑን የታክሲ ማህበራት ይግፃሉ፡፡


የብሌን ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር አቶ ኑረዲን ዲታሞ እንደገለፁልን የታክሲ ከሰሞኑ አሁን ያለው ጭማሪ ሲታይ በአማካይ በአንድ ኪሎ ሜትር 60 ሳንቲም መሆኑን በመግለፅ ለታክሲ ትራንስፖርት አዋጪ የታሪፍ በአንድ ኪሎ ሜትር በአማካይ አንድ ብር ጭማሪ ቢሆን ነበር ሲሉ አመልክተዋል፡፡ በጭማሪው የጥናት ሂደት ላይም ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ውጪ የታክሲ ማህበራት ያልተሳተፉ መሆኑን በመግለፅ ሂደቱ ፍትሃዊነት ይጎድለዋል ብለዋል፡፡


አቶ ኑሪድን ጨምረውም ከወተት እስከ እንቁላል ብሎም እስከ አልባሳትና የተለያዩ ምርቶች በየዘርፋቸው በብዙ እጥፍ እንዲጨምሩ ሲደረግ የታክሲ ትራንስፖርት ዘርፍ ግን በመንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት በመሆኑ ይህ ነው የሚባል የታሪፍ ለውጥ ያልታየበት መሆኑን በመግለፅ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ያለውን የጋራዥ ጥገና ዋጋ፣የቅባት፣ የጎማና የመሳሰሉትን ዋጋ መናር ለማሳያነት ተጠቅመዋል፡፡ በአሁኑ የታሪፍ ጭማሪም ቢሆን ከረዥም ጉዞ ውጪ በአጭሩ ጉዞ ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ያልተደረገ መሆኑን በመግለፅ የተወሰነ ለውጥ የሚታየው በረዥም የጉዞ ርቀት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

 

ማይንድ ሴት ኮንሰልት በመባል የሚታወቀው ድርጅት ባሳለፍነው ቅዳሜ ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም ሰዎችን ለተለያዩ ሥራዎች የሚያነቃቃ ፕሮግራም በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። “እኔ ነኝ አዲሷ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ፕሮግራም በርካታ ታዋቂ ወጣቶችና ታዋቂ ሰዎችን አሳትፏል።

 

ይህ አይነቱ አነቃቂ ኮንፍረንስ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የተለመደ ነው።ዋና አላማውም ሰዎች በነገሮች በጎና የተነቃቃ አዕምሮ ኖሯቸው በማህበራዊና በኢኮኖሚዊ ስራዎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። በሀገራችን እንደዚህ አይነት ጅምሮች በተለያዩ አቅጣጫዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች የዜጎችን አስተሳሰብ በማነቃቃት ለስራ ፈጠራ ብሎም ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ እንደሆነ ይታመናል።

 

በዚህ ዙሪያ በሀገራችን ከሚንቀሳቀሱት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ዶክተር ምህረት ደበበ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድም ወደ ሀገር መሪነት ሥልጣን ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል የነበሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

የኮንፍረንሱ ምልከታ

የአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሰፊ ቢሆንም በወጣቶች ተሞልቷል። የአዳራሹ ስፋት የመድረኩን ክንውን ሰው በሚገባ ስለማያሳይ በርካቶች ፕሮግራሙን የሚታደሙት በዚያው በአዳራሽ ውስጥ በተሰቀሉት ግዙፍ ስክሪኖች ጭምር ነው። በዕለቱ ግጥሞች፣ ወጎችና የተለያዩ የሥነፅሁፍ ሥራዎችም ለታዳሚው ቀርበዋል። ከፕሮግራሙ ግዝፈት አንፃር ሲታይ መድረኩን ይመጥናሉ ተብለው የማይታሰቡ ሥራዎችም ሲቀርቡበት ታይቷል። ለወጣቶች ተሞክሮ ይሆናሉ ተብለው የቀረቡት ስራዎችና ልምድን የማካፈል ንግግሮች እያንዳንዳቸው በይዘታቸው ሰፊ ጊዜን የወሰዱ በመሆናቸው በታዳሚው ዘንድ መሰላቸትን ሲፈጥሩ ታይቷል።

 

በፕሮግራሙ መገባደጃ አካባቢ የማነቃቂያ ስብከት መሰል ንግግር ያደረጉት ዶክተር ምህረት ደበበ በሃሳብ ዙሪያ ሰፋ ያለ ፅንሰ ሀሳብ ለማስጨበጥ ጥረት አድርገዋል። በርካቶችም በጥሞና አድምጠዋቸዋል። ሆኖም ዶክተር ምህረት ብዙዎቹ የንግግር ጭብጦቻቸውን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያቀረቧቸው በመሆኑ ብዙም አዲስ ነገር አልነበራቸውም ብሎ መናገር ይቻላል።

 

ፕሮግራሙ ዘግይቶ የተጀመረ በመሆኑ እያንዳንዱ የመድረክ ዝግጅት አቅራቢ በመድረክ አስተባባሪ “ይብቃህ” እየተባለ በጆሮው ሹክ ይባለውም ነበር። ዶክተር ምህረትም ቢሆን ይህ እጣ ገጥሟቸዋል። በዚህ በኩል ሲታይ መድረኩ የቅንጅት ችግር የሚታይበትም ይመስላል። በመድረኩ የሙዚቃ ስራዎቸቸውን ያቀረቡት አርቲስቶች በሙያቸው ብቃትም ሆነ የታዳሚውን ጆሮ በመያዝ በኩል የተዋጣላቸው ነበሩ። ሰዓቱ እየገፋ መሄዱን ተከትሎ በከተማዋ ካለው የትራንስፖርት እጥረት ጋር በተያያዘ በርካቶች ፕሮግራሙን አቋርጠው ለመውጣት ተገደዋል። በተለይ በመጨረሻ በነበረው የፕሮግራሙ የሙዚቃ መሸጋገሪያ ወቅት ፕሮግራሙ የተጠናቀቀ እስኪመስል ድረስ በርካታ ታዳሚዎች በጥድፊያ ሲወጡ ታይቷል።

 

ዶክተር ምህረት የማነቃቂያ ንግግራቸውን እያደረጉ እያለ በፍጥነት እንዲያጠናቅቁ ከመድረክ አስተባባሪው በኩል ተነገራቸው። እሳቸውም ንግግራቸውን በፍጥነት አጠናቀው መድረኩን እንደተሰናበቱ፤ ማንም ባልጠበቀው መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አንድ እጃቸውን ከፍ አድርገው ለታዳሚው ሰላምታ እየሰጡ ወደ ንግግር ማድረጊያው ተጠጉ። ታዳሚው ከመቀመጫው በመነሳት በጩኸትና በፉጨት ተቀበላቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ የሚሊኒየሙ ፕሮግራም ከአምስት ወራት በፊት እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆኑ የተያዘ እንደነበር አስታውሰው የመድረክ ንግግራቸውንም የሚያደርጉት ቀድሞ ፕሮግራሙ ሲያዝ በነበራቸው ማንነት ሳይሆን በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ማንነታቸው መሆኑን በመግለፅ በቀጥታ ወደ ንግግራቸው ገቡ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳቸው በፊት ከነበሩት ተናጋሪዎች በላይ እጅግ በላቀ ሁኔታ የታዳሚዎቸቸውን ቀልብ ገዝተው ንግግራቸውን በስፋት ቀጠሉ። የንግሮቻቸው ጭብጥም በአንድነት፣ በይቅርታ፣ በአብሮነትና በመቻቻል ላይ ያተኮረ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ፕሮግራሙ የገቡት የሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ በመሆኑ እግረ መንገዳቸውንም በዚሁ ጉብኝት አላማና ስኬት ዙሪያ ስለነበሩ አንዳንድ ጉዳዮችም ማብራሪያ ሰጥተዋል። በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸው ወቅት ይዘዋቸው ከሄዷቸው አስር ጥያቄዎች ከአንዱ በቀር ዘጠኙ የተመለሱ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

“ሳዑዲ አረቢያ ሄደን ምን ትፈልጋላችሁ ተብለን ስንጠየቅ ገንዘብ ሳይሆን ዜጎቻችንን ፍቱልን ነው ያልናቸው። የሚገርመው ነገር ለዜጎቻችን ክብር መስጠት ስንጀምር ያልጠየቅናው ነገር ሁሉ ይሰጠናል።” በማለት ታዳሚውን በጭብጨባ ግለት ውስጥ ከተቱት።

 

ንግግራቸውንም ቀጠል በማድረግ “ዝርዝሩን ለዲሲፒሊን ብዬ መናገር ቢያስቸግረኝም፤ እጅግ ስኬታማ የሚባል የዲፕሎማቲክ ቆይታ ነበረን። በቆይታችን ከአንድ ጥያቄ በስተቀር የጠየቅናቸው ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ አግኝቷል። አንደኛው ጥያቄ ሺህ ሙሀመድ አሊ አልአሙዲንን ማምጣት ነበር። እሳቸውን በሚመለከት ከክራውን ፕሪንሱ ጋር መቶ በመቶ ተግባብተናል። አንድ ሺህ እስረኞችን ሳዑዲ ለቃለች። መፍታት ብቻ ሳይሆን ዛሬ ምሽት ከፊሉ መግባት ይጀምራል። ሼኽ አልአሙዲንን በሚመለከት እንደ ሀገር ያለንን ፅኑ አቋም አመላክተናል። ለእኛ ሀብታምም ደሃም ዜጋ ነው።

 

ሼህ ሙሐመድ ሄሴን አሊ አልአሙዲ የማንፈልጋቸው ሰዎች ያለን እንደሆነ ሲመጡ እንነግራቸዋለን እንጂ በባይተዋር ሰዎች ሲታሰሩ የሚጨክን ልብ የለንም። ይህ ጠንካራ አቋማችንን የተረዱት ክራውን ፕሪንሱ አሳዛኝ ቢሆንም ማታ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ላይ ተግባብተን ጠዋት ሊለቁ ከወሰኑ በኋላ ቤተሰቦቻቸው ባደረጉባቸው ከፍተኛ ጫና አሁን ከእኛ ጋር ሊመጡ አልቻሉም።

 

ከእሳቸው በሰተቀር አስር ጥያቄ ነበረን? ዘጠኙን መልሰውልን ለአስረኛው ጥያቄ ግን ጥቂት ጊዜ ስጡን ብለዋል። የሼኽ አልአሙዲ መታሰር በዓለም ላይ ያሉ ዲያስፖራዎች ሁሉ አጀንዳ መሆን አለበት። ምክንያቱን ኢትዮጵያ አንተ አንቺ ከሆንሽ፣ አንድ ኢትዮጵያ ታስራለችና ኢትዮጵያ ስትታሰር ዝም ማለት የሚያስችለው ሌላ ኢትዮጵያዊ መኖር የለበትም። የጀመርነውን ዲፕሎማቲክ ጫና በማስቀጠል ጊዜውን መናገር ብቸገርም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ።” በማለት በዚህ ዙሪያ የነበራቸውን ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

Page 1 of 68

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us