You are here:መነሻ ገፅ»Economy»ፀጋው መላኩ - Sendek NewsPaper
ፀጋው መላኩ

ፀጋው መላኩ

 

በ2009 ዓ.ም ተጀምሮ ተስፋፍቶ የቀጠለውን ግጭት ተከትሎ በመንግስት በኩል ተደርሶባቸዋል ከተባሉት የችግሩ ምንጮች መካከል አንደኛው በሀገሪቱ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች መኖራቸው ነው። ይህንንም ድምዳሜ ተከትሎ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በ2009 የሁለቱ ምክርቤቶች መክፋቻ ስበሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር መንግስት ወጣቶችን ወደ ሥራ ሊያስገባ የሚያስችል የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ዝግጁ ያደረገ መሆኑን በመግለፅ ይህም የገንዘብ በየክልሉ በድርሻ የሚከፋፈል መሆኑን አመለከቱ። የፕሬዝዳንቱ የመስከረም ወር መጨረሻ 2009 ንግግርን ተከትሎ ይህንን የወጣቶች የስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድን የሚመለከተው አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ  በዚያው ዓመት አጋማሽ ላይ ነበር። በዚህ አዋጅ መሰረትም በሀገሪቱ የሚገኙና እድሚያቸው ከ18 እስከ 34 ያሉ ወጣቶች የፈንዱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተደንግጓል።

 

ይህንንም የፈንድ አዋጅ መፅደቁን ተከትሎ በየክልሉ የሚገኙ በአዋጁ የተመለከቱትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ወጣቶች እንዲመዘገቡ ተደርጓል። በዚህም ከሶስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የተዘዋዋሪ ፈንዱ ተጠቃሚ ለመሆን በየክልሉ በገጠርና በከተሞች የተመዘገቡ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በወቅቱ ይህ ገንዘብ ከፌደራሉ መንግስት የሚለቀቅ መሆኑ ሲገለፅ ከወራት በፊት ለፓርላማው በቀረበቀው በጀት ውስጥ ተካቶ የፀደቀ ግን አልነበረም።

 

 ይህም በመሆኑ በመጨረሻ ወደ አፈፃፀም ሲገባ ለክልሎች የሚለቀቀው የገንዘብ መጠን በተመደበላቸው የክፍፍል መጠን ሆኖ አልተገኘም። ለምሳሌ የቤኒሻንጉል ክልል የተመደበለትና የተለቀቀለት የገንዘብ መጠን ሊመጣጠን ባለመቻሉ ለስራ ፈጠራ የመዘገባቸውን ወጣቶች ለማስተናገድ የተገደደው  ከመደበኛ በጀቱ በመቀነስ ነበር። ለአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የተመደበው የገንዘብ መጠን ወደ 419 ሚሊዮን ብር ሲሆን በዚህም ወጣቶች እንዲጠቀሙ የተደረገው 17 ሚሊዮን ብሩን ብቻ ነበር። በአጠቃላይ ሲታይ በመንግስት የተገባው ቃልና በመጨረሻ ወደ አፈፃፀም ሲወረድ የታየው እወነታ ፈፅሞ የሚገናኝ ሆኖ አልታየም።

 

የመንግስት የፋይናስ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ከማደጉ ባሻገር የገቢው መጠን ደግሞ በዚያው መጠን አሽቆልቁሏል። በዚህ በኩል በተለይ በውጭ ምንዛሪ የታየው ማሽቆልቆል ከዓመት ዓመት እየከፋ ሄዷል። ከዚህም በተጨማሪ ሀገሪቱ በተደጋጋሚ ያለፈችብት ህዝባዊ ዓመፅም ኢኮኖሚውን ክፉኛ ጎድቶታል። ይህ ብቻ ሳይሆን የደመወዝተኛው የደመወዝ ግብር ዝቅ እንዲል መደረጉ ለመንግስት ገቢ መውረድ አንዱ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀስ ነው። መንግስት የደመወዝ ግብርን ሲቀንስ ይሄንኑ ያጣውን ገቢ የሚያተካኩ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን ታሳቢ በማድረግ ነበር። ከእነዚህም ታሳቢ የገቢ ምንጮች መካከል አንዱ ተደርጎ የተወሰደው በአዲስ መልኩ የተሻሻለውን የገቢ ግብር አዋጅ ተከትሎ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ የታክስ ጭማሪ ማድረግን ነበር።

 

 መንግስት የቀን ገቢ ግምቶችን ማሻሻያ የሚያደርገው በየስድስት ዓመቱ ሲሆን በተሻሻለው አዋጅ መሰረት የቀን ገቢ ግምት በየሶስት ዓመቱ እንዲሆን ተደንግጓል።  በሳላፍነው ዓመት የመንግስት የቀን ገቢ ግምት ማሻሻያ ወቅት ስለነበር የተደረገውን ማሻሻያ ተከትሎ የተካሄደው ግምት የማወጣት ስራ በርካታ የንግዱን ማህበረሰብ አስቆጥቷል። ይህም ጉዳይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲያወዛግብ ከመቆየቱም ባሻገር በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልል የንግድ ስራን እስከማቆም የዘለቀ አድማ እንዲካሄድ አድርጓል። የመንግስት የገቢ ፍላጎት ንረት ገቢውን ለመሻሻል ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር የወጪ መጠኑንም ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።

 

 በዚህም አላስፈላጊ ወጪዎችን ለመቀነስ የሚያስችል መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ይህም መመሪያ ተግባራዊ የሚሆን ከሆን የመንግስትን ወጪ በመቀነስ በገቢውና በወጪው መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ አይነቱ አካሄድ ከኢህአዴግ መንግስት ቀደም ካለ ታሪክ አንፃር ሲታይ ከወጪ አኳያ የመጀመሪያው እርምጃ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው። መንግስት ገቢውን ከፍ እንዲያደርግ የሚያስገድዱ በርካታ ነባራዊ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

 

የኢትዮጵያ መንግስት ወጪው በከፍተኛ ደረጃ እየናረ መሄዱን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ገቢውን ለማሳደግና ወጪውን ለመቀነስ ጥረት እያደረገ ነው። ከውጪ አንፃር ባለፉት ጊዜያት ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቀላል የማይባል ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የድርቁ ሁኔታ ቀላል የማይባል ገንዘብን መጠየቁም አንዱ ፈተና ነበር። እነዚህና ሌሎች የኢኮኖሚው ተግዳሮቶች መንግስት ለወጣቶች የስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ ያፀደቀውን የ10 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንኳን በተፈለገው መጠን እንዳይለቅ አድርጎታል።

·        ከካርድ ውጪ የሞባይል ሂሳብ የሚሞላበት አሰራር ተጀምሯል

 

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሞባይል ካርድ እጥረት የተከሰተ ሲሆን ኢትዮቴሌኮም በበኩሉ ችግሩ የተፈጠረው ከውጭ ለኩባንያው ካርድን ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለሰንደቅ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮ ቴሌኮም የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ  ካርዱ በውጭ ሀገራት ታትሞ ሀገር ውስጥ የሚገባ መሆኑን ገልፀው፤ ይሁንና ካርዱን የሚያቀርቡት የውጭ ኩባንያዎች ኤርፖርት ድረስ ካደረሱ በኋላ ማሟላት የሚገቧቸውን አንዳንድ መስፈርቶች ማሟላት ባለመቻላቸው የታተሙት ካርዶች ወደ ገበያው መግባት ያልቻሉ መሆኑን አመልክተዋል። ይህም መዘግየት የተፈጠረው ባለፈው ሳምንት መሆኑን ገልፀው፤ ይሁንና ችግሩ በመፈታቱ በአሁኑ ሰዓት ሀገር ውስጥ የገባው ካርድ ለአከፋፋዮች መሰራጨት በመጀመሩ  ችግሩም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚቀረፍ መሆኑን ገልፀዋል።

እጥረቱ ከ15 ብር በላይ ዋጋ ባላቸው ካርዶች ላይ የተከሰተ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ በሁለት መሰረታዊ መፍትሄዎች እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። እነዚህም መፍትሄ ተብለው የተወሰዱት በአንድ መልኩ ካርዱ ሀገር ውስጥ እንዲታተም ማድረግ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ደንበኞች ካርድ መፋቅ ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ ገንዘብ መሙያ ማሽኖችን በመጠቀም ካርድ የሚሞሉበት ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ነው።

ለዚህም ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠት በአንዳንድ የኢትዮቴሌኮም ማዕከላት በሙከራ ደረጃ ይህ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተመልክቷል። ሆኖም አሁን ካርዶቹ የሚሞሉባቸው ውስን ማሽኖች በቀጣይ ለሁሉም ህብረተሰብ በቀላሉ ተደራሽ በሚሆኑበት መልኩ በየአካባቢው እንዲገኙ ይደረጋል ተብሏል። የኢትዮቴሌኮም የካርድ ስርጭት እጥረት በሀገሪቱ በስፋት የታየ ሲሆን በተለይ ከአዲስ አበባ ባሉ አካባቢዎች በስፋት የታየ መሆኑን ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። የካርዱ ዋጋ እየጨመረ ሲመጣ ከአንድ ካርድ የሚገኘው የትርፍ ህዳግም ጭምር በዚያው መጠን እያደገ የሚሄድ መሆኑን የገለፁልን አንዳንድ የሱቅ ባለቤቶች ይሁንና ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ከ15 ብር በላይ ያሉት ካርዶች በመጥፋታቸው ከካርድ ሽያጭ የሚያገኙት ገቢ አነስተኛ እንዲሆን ስላደረገው የሞባይል ካርዶች መያዝ ወደ መተው አዝማሚያ እየሄዱ መሆኑን ገልፀውልናል።

ተጠቃሚዎች በበኩላቸው አነስተኛ ዋጋ ያለውን ካርድ መሙላትና  ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ካርዶች በአንድ ጊዜ መሙላት ያለው የአየር ሰዓት የተለያየ በመሆኑ ከተፈጠረው የካርድ እጥረት ጋር በተያያዘ አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን ካርዶች ለመግዛት በመገደዳቸው ብዙ ብር ለማውጣት የተገደዱ መሆኑን ገልፀውልናል። ኢትዮቴሌኮም ግን ችግሩ ተፈትቶ ካርዶቹ በሀገር ውስጥ አከፋፋዮች እጅ እንዲገቡ እየተደረጉ በመሆኑ ደንበኞች በትግስት እንዲጠባበቁ ጠይቀዋል።¾

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቀናጀ የበረራ ስርዓት እንዲኖረው የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ለማግኘት ሴበር ከተባለ አንድ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ። በዚህ ስምምነትም መሰረት ኩባንያው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማቅረብ ይጠበቅበታል። እንደ ኢትዮጵያ የአየር መንገድ አለም አቀፍ አገልግሎቶች ማኔጂግ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ወልደማርያም ገለፃ ከሆነ አየር መንገዱና ሴበር ላለፉት አስራአንድ ዓመታት በጋራ የሰሩ ሲሆን፤ አሁን በታደሰው የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት ሴበር ኩባንያ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኦንላይን ትኬት ጀምሮ በርካታ አገልግሎቶችን በዘመናዊ ኢንፎርሜሽን በተደገፈ መልኩ እንዲያገኝ የሚያደርግ ይሆናል።

 

ሰሞኑን ኢትዮጵያ አንድ ምሁር አጥታለች። ይህ ምሁር ዶክተር ወልዳይ አምሀ ይባላሉ። ባለሙያው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በበርካታ የሙያው ዘርፎች ውስጥ ሰፊ ሥራዎችን ሰርተዋል። ይሁንና ከሰሞኑ ሞጆ አካባቢ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ህይወታቸው አልፏል።

  ምሁሩ በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በሀላፊነት ከመምራት ባሻገር በዩኒቨርስቲ መምህርነት ብሎም በአማካሪነት  ጭምር ያገለገሉ ናቸው። የኢኮኖሚ ባለሙያው ህይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ የኢትዮጵያ ማይክሮ ፋይናስ ተቋማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ።

 

ምሁሩ ከዚያ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል። በቀድሞው ግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥም በአማካሪነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

 

 የበርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ስብስብ የሆነውንና በኢትዮጵያም ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዙሪያ ጥልቅ ጥናቶችን የሚያደርገውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበርን በፕሬዝዳንትነት ከመሩት ምሁራን መካከል አንዱ ዶክተር ወልዳይ ነበሩ። ዶክተር ወልዳይ ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመምህርነት አገልግለዋል።

 

 ህይወታቸው ከማለፉ ከቀናት በፊት በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄድ ሀገር አቀፍ የፋይናስ ተቋማት ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ማይክሮ ፋይናስ ተቋማት ተግዳሮት ዙሪያ አንድ ጥናት አቅርበው ነበር።

 

የኬኒያ አየር መንገድ በቀጥታ በረራ አሜሪካ መግባት የሚያስችለውን ፈቃድ አግኝቷል። አየር መንገዱ በቀጥታ በረራ አሜሪካ መብረር ይችል ዘንድ አንዳንድ የምዘና ጥናቶች ሲካሄዱበት ቆይተዋል። የአሜሪካ የትራንስፖርት ዲፓርትመንት የኬኒያን የበረራ መሰረተ ልማትና መሰል የደህንነት ስራዎች በሚገባ ሲፈትሽ ከቆየ በኋላ በስተመጨረሻ ለተወሰኑ ቀናት የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተቃውሞ ሀሳብ ካላቸው ሀሳባቸውን እንዲያሰፍሩ የ61 ቀናት ቀነ ገደብ አስቀምጦ ቆይቷል።

 

በሀገሪቱ ህግ መሰረት የተቀመጠው የተቃውሞ ማሰሚያ ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ አየር መንገዱ አሜሪካ ቀጥታ መብረር የሚያስችለውን ፈቃድ በእጁ አስገብቷል። በዚህም ፈቃድ መሰረት የኬኒያ አየር መንገድ የመንገደኞችም ሆነ የጭነት አውሮፕላን ወደ አሜሪካ የቀጥታ በረራ ማድረግ የሚችል መሆኑን የ ሲቲዝን ዘገባ ያመለክታል።

 

 

በያዝነው 2009 ዓ.ም እና ከዚያ በፊት የነበሩ በርካታ የኢኮኖሚ ፈተናዎች በቀጣዩ አዲስ ዓመት 2010ም ጭምር የሚቀጥሉ ይመስላል። ባለፉት ዓመታት ከነበሩት በርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱት የመሰረታዊ ፍጆታዎች አቅርቦት መፍትሄ አለማግኘት፣ ድርቅና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዋነኝነት ሊታዩ የሚችሉ ናቸው።

 

መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች

መንግስት እጥረት የሚታይባቸውን እንደ ስኳርና ዘይትና ዱቄት የመሳሰሉት መሰረታዊ ሸቀጦች በራሱ በመንግስት አቅራቢነት በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል እንዲቀርቡ ማድረግ ከጀመረ ከአምስት ያላነሱ ዓመታት አልፈዋል።

 

በእርግጥ ከዘይትና የስንዴ ዱቄት ምርት ጋር በተያያዘ በተለያዩ የሸቀጥ መደብሮች ያሉ ቢሆንም የስኳር ጉዳይ ግን አሁንም በመንግስት ጥብቅ የቁጥጥር ስርዓት ውስጥ ያለ ነው። በእርግጥ ነው የመጀመሪያው አምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲቀረፅ የስኳሩ ዘርፍ ፕሮጀክቶች በእቅዱ አጋማሽ ተጠናቀው የሀገር ውስጥ ፍጆታን ሙሉ በሙሉ ከመሸፈን ባለፈ በኤክስፖርት ግብይት በሚያስገኙት ገቢ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፋይናንስ ይደግፋሉ የሚል ሀሳብ ነበር። ሆኖም አሁን ባለንበት የሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን አጋማሽ ወይንም ከመጀመሪያው እቅድ ሰባት ዓመታት በኋላ ሀገሪቱ ስኳርን ኤክስፖርት ማድረግ ይቅርና ከውጪ በማስገባት ላይ ትገኛለች። ዛሬም ድረስ ዜጎች የስኳር ፍጆታቸውን የሚያገኙት በኮታ ነው። ይህ አሁን ልንሰናበተው ቀናት በቀሩት 2009ኝም ጭምር እየታየ ያለ በመሆኑ በመጪው 2010ም የሚቀጥል መሆኑ ጥርጥር የለውም። ከዓመታት በፊት በሀገሪቱ የተለያየ አቅጣጫ የተጀመሩት የስኳር ፕሮጀክቶች ዛሬም ተጠናቀው የስኳር የኮታ እደላን መታደግ አልቻሉም።

 

የድርቅ ፈተና እና መጪው ዓመት

 ድርቅ የኢትዮጵያ ፈተና መሆን ከጀመረ ዓመታት ተቆረዋል። የክረምቱ የዝናብ ስርጭት ሁኔታ የተሻለ መሆኑ ቢነገርም አሁንም ቢሆን በሀገሪቱ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ዘጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የቅርብ መረጃዎች ያመለክታሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቱ ከገጠማት የድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ልዩ ልዩ ድጋፎችን ሲያገኝ ቢቆይም፤ የተገኘው ድጋፍ ግን ከችግሩ ስፋት አንፃር ሲታይ በቂ ሊባል የሚችል አልነበረም።

 

ይህም በመሆኑ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት መንግስት እስከ 7 መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ተገዷል። ይህም በልማት ፕሮጀክቶች ላይ፤ እንደዚሁም በአጠቃላይ አኮኖሚው ላይ የፈጠረው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ኢትዮጵያ በድርቅ በምትጠቃባቸው ጊዜያት ሁሉ ለድርቅ ተጠቂዎች ከፍተኛ እርዳታ በማቅረብ የምትታወቀው አሜሪካ ቀደም ሲል የነበራትን ቁርጠኝነት ማሳየት አልቻለችም።

 

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ሀገሪቱ ቀላል የማይባል የእርዳታና የእገዛ ገንዘብን ለመቀነስ እንቅሳቀሴ ከጀመረች ዋል አደር ብላለች። ኢትዮጵያ “ፊድ ዘ ፊውቸር” ተብሎ በሚጠራው የአሜሪካ የእርዳታ ፕሮግራም ታቅፋ ሰፊ ድጋፍ ስታገኝ ብትቆይም የትራምፕ አስተዳደር ለዚህ ፕሮግራም ይመደብ የነበረውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር በጀት በግማሽ እንዲወርድ ያደረገው መሆኑን የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ያመለክታል። ኢትዮጵያ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የነበራት የ78 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታ ፈንድ ድርሻም የዚሁ ቅነሳ ሰለባ እንደሚሆን ይሄው ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።

 

ይህ ብቻ ሳይሆን የትራምፕ አስተዳደር ለታዳጊ ሀገራት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርገውን የዩ.ኤስ.ኤይድ በጀትንም የሚቀንስ መሆኑ በመታወቁ ድርቁ በመጪው አዲስ አመትም ጭምር የሚቀጥል ከሆነ ዜጎችን በመታደጉ በኩል ከኢትዮጵያ መንግስት ብዙ የሚጠበቅ ይሆናል።

 የዩ.ኤስ.ኤይድ አዲሱ ኃላፊ ሚስተር ማርክ ግሪን በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በተገናኙበት ወቅትም የድርቅ ተጠቂ ዜጎችን ህይወት በመታደጉ በኩል ከኢትዮጵያ መንግስት ብዙ የሚጠበቅ መሆኑ እንደገለፁላቸው የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።

 

 ኃላፊው ለዚሁ የረድኤት ስራ የኢትዮጵያ መንግስት እስከ ዛሬ ከነበረው የገንዘብ መጠን የተሻለ በጀት እንዲመደብ የጠየቁ መሆኑን ይሄው ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል። አሁን ባለው ሁኔታ ቀደም ሲል በድርቅ የተጠቁትን ወገኖች ለማገዝ ተጨማሪ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን በመጪው 2010 ዓ.ም ደግሞ ምን አይነት ሁኔታ እንደሚኖር አይታወቅም።

 

ሆኖም አሁን ካለው አጠቃላይ ሁኔታ ሲታይ የድርቁ ሁኔታ የቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መንግስት ፈተና ሆኖ ይቀጥላል። ከረድኤት ድርጅቶች ምላሽ አናሳነት ጋር በተያያዘም ከኢትዮጵያ መንግስት ብዙ የሚጠበቅ በመሆኑ መንግስት የተወሰነ በጀቱን ለእርዳታ በማዋል የሚቀጥል ከሆነ የልማት በጀት ወደ ፍጆታነት የሚቀየር በመሆኑ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት ብቸኛ አማራጭ የግብርናውን ዘርፍ ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የመስኖ ስራን ማስፋፋት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቢቆይም ይህ ጉዳይ እስካሁን ድረስ መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም።

 

የውጭ ምንዛሪው ፈተና

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ አሁንም በችግርነት ተንከባለው ወደ ሚቀጥለው ዓመት መሸጋገራቸው አይቀሬ ከሆኑት ፈተናዎች ውስጥ ሌላኛው አንኳር ችግር የውጭ ምንዛሬው እጥረት ነው። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለኢትዮጵያ አዲስ ባይሆንም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ከፋይናስ ጋር በተያያዘ በተባባሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ የተካሄደው ስብሰባ ያመለክታል። የዚህ ችግር ዋነኛ መንስኤም የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እያሽቆለቆለ መሄዱ ነው።

በሀገሪቱ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በተለይ ከቱሪዝም ይገኛል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተፈለገው መጠን እንዳይሄድ አድርጎታል። ምንም እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም አሁንም ቢሆን እዚህ እና እዚያ የሚታዩት አለመረጋጋቶች ወደ ቀጣዩ ዓመት የሚሸጋገሩ ከሆነ የሚጠበቀው የቱሪስት ቁጥር በተፈለገው ደረጃ እንዳይገኝ የሚያደርገው ይሆናል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በሀገሪቱ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በባንኮችና በጥቁር ገበያው ያለው የዶላር ምንዛሪ ክፍተት እየሰፋ ነው።

 

 

አንድነት ኢንተርናሽናል ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በዲግሪ እንደዚሁም በቴክኒክና ሙያ ዘርፎች በዲፕሎማ ያስተማራቸውን 95 ተማሪዎች ባለፈው ዕሁድ በትምህርት ተቋሙ ቅጥር ጊቢ አስመርቋል። የትምህርት ተቋሙ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች በመደበኛና በማታው መሀርሃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።

 

ተመራቂዎቹ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአካውንቲግና በጀት ሰርቪስ፣በሀርድዌርና ኔትወርኪንግ ሰርቪስ የሙያ ዘርፎች ነው። ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ በቀጣይ በአርክቴክቸር፣ በስራ ፈጠራ እንደዚሁም በአነስተኛ የንግድ ሥራ አመራር በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን ተመልክቷል።ከዚህም በተጨማሪ በማስተርስ ዲግሪ በቢዝነስ አድምንስትሬሽን፣ በአካውንቲግና ፋይናንስ እንደዚሁም በርቀት ትምህርት ስልጠናዎችን ለመስጠት ያቀደ መሆኑ ተመልክቷል። ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ተማሪዎችን ያስመረቀው ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

 

ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ በአሁኑ ሰዓት ትምህርት እየሰጠ ያለው ከህፃናት መዋያ ጀምሮ እስከ ሀይስኩል ድረስ ነው። የትምህርት ተቋሙ 27 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ያረፈ ሲሆን፤ በ43 በኢትዮጵያና አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያን በአክስዮን የተቋቋመ ተቋም ነው።

 

ትምህርት ቤቱ በ1998 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ከዚያ በኋላ በ2000 ዓ.ም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምነት ያደገ መሆኑን ከኃላፊዎቹ ገለፃ መረዳት ችለናል። ከትምህርት ተቋሙ መስራቾች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር  ዘውድነህ በየነ እንደገለፁልን ከስር ጀምሮ የትምህርት ጥራትን ጠብቆ ለማስኬድ በማሰብ የትምህርት ተቋሙ ከመዋዕለ ህፃነናት ጀምሮ እስከ ሀይስስኩል ብሎም እስከ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ድረስ ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል።

 

 በዚህ ዓመት በትምህርት ቤቱ 12ኛ ክፍልን ካጠናቀቁ ተማሪዎች መካከል 30 የሚሆኑት በአሜሪካን ሀገር በሚገኙ ታዋቂ ዩኒቨርስቲዎች ተቀባይነትን አግኝተው በዚያው ሀገር ለመማር ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ መሆኑን ዶክተር በየነ ጨምረው አመልክተዋል። እነዚህም ተማሪዎች ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ስኮላርሽፕ ያገኙ መሆኑን ዶክተር ዘውድነህ ጨምረው ገልፀዋል። ተማሪዎቹን በቦታው በመገኘት በክብር እንግድነት የመረቀው አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ነው።

 

በናይጄሪያ ግዙፍ አየር መንገድ መሆኑ የሚነገርለት አሪክ ኤይር አየር መንገድ ከገጠሙት በርካታ ችግሮች ለመውጣት ኩባንያውን በኮንትራት ማኔጅመንት የሚያስተዳደርለት አካል እያፈላለገ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድም ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፍ አገልግሎቶች ማኔጂግ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ኢሳያስ ወልደማርያምን ዋቢ ያደረገው ይሄው ዘገባ አየር መንገዱ አሪክ ኤይርን በማኔጅመንት ኮንትራት ለማስተዳደር ፍላጎት ያለው መሆኑን አመልክቷል። አሪክ ኤይር ከዚህ ቀደም በገጠመው ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ የናይጄሪያ መንግስት የመታደጊያ ገንዘብን በመልቀቅ ከውድቀት ያዳነው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማፈላለግ አማራጭ ሆኖ የተገኘው ሙሉ የአየር መንገዱን ማኔጅመንት በሌላ ኩባንያ እንዲተዳደር ማድረግ ነው።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኦፊሴላዊ ጥያቄውን ያቀረበ ሲሆን ምላሹንም ከናይጄሪያ መንግስት እየጠበቀ መሆኑን አቶ ኢሳያስ ጨምረው አመልክተዋል። “አየር መንገዱን ለማስተዳደር ብቃቱ አለን” ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ የአየር መንገዱን ማኔጅመነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢረከብ በምን መልኩ ሊያሰተዳድረው እንደሚችል ፍንጭ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

 

 የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ አየር መንገዶችና በዚሁ ዙሪያ ልምድ ያላቸው በርካታ ኩባንያዎች ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮንትራት ማኔጅመንቱን የሚያሸንፍ ከሆነ፤ በቀላል ውድድር ይወጣዋል ተብሎ አይጠበቅም። ከዚህ ቀደም የአሪክ ኤይርን ማኔጅመንት ሙሉ በሙሉ ሲያስተዳደር የነበረው “አሴት ማኔጅመንት ኮርፖሬሽን ኦፍ ናይጄሪያ” የተባለ መንግስታዊ ድርጅት ነበር።

ሆኖም በስራው ብዙም ውጤታማ መሆን ሳይችል በመቅረቱ አየር መንገዱም የተፈለገውን ስኬት ማስመዝገብ ሳይችል ቀርቷል። አየር መንገዱ ከናይጄሪያ መንግስት ካዝና የተለቀቀለት ከ 8 መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ ያለበት በመሆኑ ይህ ጉዳይ መፍትሄ ካላገኘ ቀጣይ ለሚኖረው የኮንትራት አስተዳደር አንዱ ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከበረራ አገልግሎት ባለፈ ዓለም አቀፋዊ አድማሱን በማስፋት የማሊ አየር መንገድን 49 በመቶ፤ እንደዚሁም የቶጎ አስኪ አየር መንገድን 40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻን ይዟል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ወቅት መንገደኞች የሚጠቀሙበትን የዋይፋይ አገልግሎትን ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን የአየር መንገዱ አለም አቀፍ አገልግሎቶች ማኔጂግ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ወልደማርያም አመልክተዋል።

 እንደ አቶ ኢያሳያስ ገለፃ አውሮፕላኖቹ ከመጀመሪያው ሲሰሩ መሰል ቴክኖሎጂን መጠቀም በሚያስችላቸው ደረጃ የተሰሩ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም በቀጣይ አገልግሎቱን በቀላሉ ለማስጀመር ያስችላል ብለዋል።

 ይህም አየር መንገዱን ይህንን አገልግሎት ከሚሰጡ ሌሎች አየር መንገዶች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርገው ይሆናል ተብሏል። ይህ ብቻም ሳይሆን ተጓዦች በአውሮፕላን ውስጥ ካሉት ሌሎች መዝናኛዎች በተጨማሪ የዋይፋይ አገልግሎቱም ተጨማሪ መዝናኛና መረጃ መለዋወጫም ከመሆን ባሻገር የቢዝነስ ተጓዦች በየትኛውም ቦታ ሆነው በጉዞ ላይ እያሉ ሥራቸውን ለመስራት የሚያመቻቸው መሆኑን አቶ ኢሳያስ ጨምረው አመልክተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቴክኖሎጂውን ከሚያቀርብ ኩባንያ ጋር ውይይትና ድርድር እየተካሄደ ነው ተብሏል። በዚህም ሁሉም የአየር መንገዱ አውሮፕላኖች በቀጣይ የዋይፋይ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል።¾

 

ባሳለፍነው ሳምንት ማጠናቀቂያ በነበሩት ሁለት ቀናት ፋይናስ ለሀገራዊ ኢንዱስትሪ ልማት በሚል አንድ ሀገራዊ ኮንፍረንስ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሂዷል። የዚህ ኮንፍረንስ ዋነኛ አላማም የሀገሪቱ የፋይናስ ዘርፍ ከኢንዱስትሪው ጋር ሊኖረው በሚገባው ተመጋጋቢነትና ትስስር ዙሪያ ትኩረት አድርጎ መስራት ላይ ነው። ኮንፍረንሱ የፋይናሱ ዘርፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን፣የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንና የልማት ባንክን ጨምሮ የግል ንግድ ባንኮችንና የኢንሹራንስ ከፍተኛ ሀላፊዎችን አሳትፏል። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት እንደዚሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ የኩባንያ ኃላፊዎችና ባለሀብቶችም የዚሁ ኮንፍረንስ ተሳታፊዎች ነበሩ።

 

በዚህ ኮንፍረንስ በርካታ ከፋይናስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ተነስተዋል። ከብድር አሰጣጥ እንደዚሁም ከውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከመሳሰሉት ጋር ተያያዥነት ያላቸው የተለያዩ ሀሳቦች በመድረኩ ላይ ተንሸራሽረው ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የልማት ባንክ ሀላፊዎች የየባንኮቻቸውን የሥራ እንቅስቃሴና አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተም በመጠነኛ ዳሰሳ ለተሰብሳቢው አቅርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የፋይናሱን ዘርፍና ኢንዱስትሪውን በማስተሳሰሩ ረገድ የሌሎች ሀገራት አሰራርና ተሞክሮም ምን እንደሚመስል አጠር ያለ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አጠቃላይ እንቅስቃሴን በተመለከተ አጠር ያለ ጥናት ያቀረቡት የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተሾመ አለማየሁ ናቸው።

 

 አቶ ተሾመ የባንኩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የዳሰሱበት ፅሁፍ Development Bank of Ethiopia (DBE): Industrial Projects Financing Prospects and Challenges. በሚል ርዕስ የቀረበ ነው። አቶ ተሾመ በዚሁ ጥናታቸው የሀገሪቱን የልማት አጀንዳዎችና እቅዶች እውን ለማድረግ ባንኩ በማስያዣ ሳይሆን በፕሮጀክት ብድር ላይ መሰረት አድርጎ ኢንዱስትሪውን የሚያግዝ ባንክ መሆኑን  አመልክተዋል። በዚህም ባንኩ የእፎይታ ጊዜን ጨምሮ የብድር ቆይታ ጊዜው እስከ 20 ዓመት የሚዘልቅ የረዥም ጊዜ ብድርን የሚፈቀድበት ሁኔታ መኖሩንም አመልክተዋል።

 

ባንኩ የብድር አመላለስ ስጋትን ለመቀነስ ብሎም የተሻለ የፋይናስ አቅርቦት እንዲኖረው ለማድረግ ከሌሎች የሀገር ውስጥና የውጭ የፋይናስ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሰራ መሆኑም ተመልክቷል። ባንኩ አሁን ኢንዱስትሪውን በፋይናስ በመደገፉ ረገድ እየሰራባቸው ካሉት ስራዎች መካከል አንዱ የሊዝ ፋይናሲግ ስርዓት መሆኑን ያመለከቱት አቶ ተሾመ፤ በዚህም አንድ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሰማራት አዋጪ የሆነ ፕሮጀክትን ማቅረብ የቻለ ባለሀብት ምንም አይነት ማስያዣያ ሳይጠየቅ ማሽኖቹ በባንኩ ተገዝተው የሚቀርቡለት መሆኑን አመልክተዋል። ባንኩ ማሽኖቹን ገዝቶ ከማቅረብ ባለፈ በባለሙያ እስከማስተከል የሚደርስ ኃላፊነትንም ጭምር ይወጣል ተብሏል። ሆኖም የማሽኖቹ ግዢ የሚፈፀመው በባንኩ ስም በመሆኑ ባለቤትነቱ የባንኩ መሆኑ ተመልክቷል። በዚህ አይነቱ የብድር አሰጣጥ ሂደት ከባለሀብቱ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች መሟላት ይጠበቅባቸዋል።

 

 አንደኛው አዋጪ የሆነ ዝርዝር የቢዝነስ ፕሮጀክት ፕላን ማቅረብ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ባንኩ የሚጠይቀውን የተወሰነ የፕሮጀክቱን የፋይናስ መጠን ማዋጣት መቻል ነው። በዚህም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ካቀረቡት አጠቃላይ የፕሮጀክት ኢንቨሰትመንት ካፒታል ውስጥ 25 በመቶውን ድርሻ ማቅረብ ሲጠበቅባቸው ለውጭ ባለሀብቶች ደግሞ ይህ የድርሻ መጠን ወደ 50 በመቶ ከፍ ይላል።

 

ባንኩ በሚፈቅደው ብድር እንደየሁኔታው የእፎይታ ጊዜ ያለው መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ለብድሩ የሚጠይቀው የወለድ መጠንም እንደየፕሮጀክቱ ዘርፍ የሚለያይ መሆኑ ተገልጿል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በሊዝ ፋይናሲግ ለሚሰጥ  ብድር የሚጠየቀው የወለድ መጠን ፣ኤክስፖርት ለሚያደርጉ ባለሀብቶችና ለመሳሰሉት ብድር ጠያቂዎች የተቀመጠው የወለድ መጠን ልዩነት የሚታይበት መሆኑን የቀረበው ጥናት ያመለክታል። ከሁሉም ዘርፎች ቀለል ያለው የብድር የወለድ ምጣኔ የተጣለባቸው የመጀመሪያ ደረጃ ኤክስፖርተሮች (First Grade Exporters) የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ባለሀብቶች ናቸው። ባንኩ በብድር አሰጣጡና አመላለሱ ሂደት ላይ ያሉበት ተግዳሮቶችም ተመልክተዋል። በብድር አፈቃቀዱ ሂደት ላይ ተበዳሪዎች በእነሱ በኩል እንዲያሟሉ የሚጠየቁትን የብድር መጠየቂያ ድርሻን መወጣት አለመቻል። እንደዚሁም አምራቾች የባንክ ብድር ከወሰዱ በኋላ በሚገጥማቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በታቀደው ጊዜ ወደ ምርት ስራ ገብቶ ብድሩን በጊዜ መክፈል አለመጀመር በዋነኝነት በተግዳሮነት የተነሱ ጉዳዮች ናቸው። ያም ሆኖ የባንኩ የአምስት ዓመት የብድር አሰጣጥ ሂደት እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ በ2012/2013 ከነበረበት 4 ነጥብ 9 በመቶ የብድር እድገት ምጣኔ (Growth rate) በ2016/2017 ወደ 17 በመቶ እድገት አሳይቷል።

 

ሌላኛው የቀረበው ሪፖርት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ያለው እንቅስቃሴ ነው። ንግድ ባንክ በሀገሪቱ ግዙፉን ፋይናስ  የሚያንቀሳቅስ ባንክ ነው። ባንኩ በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተጫወተ ያለውን ሚና በተመለከተ “CBE’s Role in Financing the Manufacturing Industry in Ethiopia”  በሚል ርዕስ አጠር ያለ ዳሰሳዊ ጥናት ያቀረቡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ እስክንድር አስፋው ናቸው። ኤክስፐርቱ በጥናታቸው ባንኩ በብድር አሰጣጡ በኩል  ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች በቅድም ተከተል አስቀምጠዋል። በዚህም መሰረት መሰረተ ልማት የመጀመሪያውን ሲይዝ ግብርና በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል። ኤክስፖርትና ማኑፋክቸሪግ በቅደም ተከተል የሶስተኛና የአራተኛ ደረጃን ይዘዋል። በመሰረተ ልማት ግንባታ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የብድር ገንዘብ የሚለቅ መሆኑ ተመልክቷል። ሆኖም ባንኩ ለዚህ ፕሮጀክት ሥራ በየጊዜው ምን ያህል ገንዘብ እንደሚለቅና እስከዛሬም ድረስ ምን ያህል ገንዘብ በአጠቃላይ እንደለቀቀ የተመለከተ ነገር የለም። ባንኩ እ.ኤ.አ 2010 የነበረው ተቀማጭ ገንዘብ 56 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን ይህ የተቀማጭ ገንዘብ እ.ኤ.አ በ2017 364 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር አድጓል። የብሄራዊ ባንክ መመሪያ የአንድ ባንክ የተበላሸ የብድር መጠን(NPL) ከ5 በመቶ እንዳይበለጥ የሚያስቀምጥ ሲሆን የንግድ ባንክ የ2017 የተበላሸ ብድር መጠን 2 ነጥብ 8 መሆኑ በዚሁ ጥናት ተመልክቷል።

 

ባንኩ የውጭ ምንዛሪን ለማሰባሰብ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፤ ይሁንና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ይህ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መጠን በተወሰነ ደረጃ የመቀነስ አዝማሚያ የሚታይበት መሆኑ በጥናቱ ላይ ተጠቁሟል። በዚህ መረጃ መሰረት ባንኩ እ.ኤ.አ በ2010፤ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪን ማሰባሰብ ችሏል። ይህ የገንዘብ መጠን በ2012 ወደ 7 ነጥብ 151 ቢሊዮን ዶላር ማደግ ችሎ ነበር። ሆኖም ከዚያ ዓመት በኋላ የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ የመውረድ አዝማሚያ የታየበት መሆኑን የቀረበው ጥናት ያመለክታል።

 

 የምንዛሪ ግኝቱ ከዓመት ዓመት እየወረደ ሄዶ በ2017 የተመዘገበው የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ወደ 6 ነጥብ 255 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ባንኩ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ አጥብቆ መስራት ያለበት መሆኑ በዚሁ ጥናት ምክረ ሀሳብ ላይ ቀርቧል። ንግድ ባንክ ከልማት ባንክ በተለየ ባለው የብድር አሰጣጥ፤ በመሰረታዊነት የሚለይ ሲሆን የልማት ብድር አፈቃቀድ ያለ መያዣ ፕሮጀክትን መሰረት አድርጎ የሚፈቀድ ሲሆን ንግድ ባንክ በአንፃሩ የብድር ዋሰትና መያዣን መሰረት አድርጎ ብድርን የሚለቅ የፋይናስ ተቋም ነው። ያም ሆኖ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ባንኩ በርካታ የመንግስት ልማቶችን በብድር የሚደግፍ በመሆኑ፤ የልማት ባንክን ሚና ጭምር የሚጫወት መሆኑ ነው የተመለከተው።

 

የፋይናሱ ዘርፍ አጠቃላይ ምልከታና ኢኮኖሚው

አንድ ኢኮኖሚ ሲያድግ በስፋቱም (Economic Scale) ብቻ ሳይሆን በውስብብነቱ ብሎም በአይነቱ እየተለወጠ ስለሚመጣ በዚያው መጠን ይሄንኑ ለውጥ ሊመጥን የሚችል የፋይናስ ምንጭ የሚያስፈልግ መሆኑን በዕለቱ የቀረቡት ጥናቶች ያመለክታሉ። አንድ ኢኮኖሚ ሲያድግ ሶስት ምዕራፎች የሚኖሩት መሆኑን የተመለከተ ሲሆን፤ በአንድ ባልዳበረ ኢኮኖሚ ውስጥ ግብርና የመሪነቱን ሚና ሲጫወት ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ ደግሞ ኢንዱስትሪው ከዚያም በስተመጨረሻ አገልግሎት መር ኢኮኖሚ (Service Lead Economy) የበላይነቱን የሚወስድ መሆኑን የጥናቶቹ ማብራሪያዎች ያመለክታሉ።

 

 ኢትዮጵያ “ያልዳበረ ኢኮኖሚ ነው” ከተባለለት የግብርናው ዘርፍ በመውጣት ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚን ለመገንባት በመውተርተር ላይ ያለች ሀገር ናት። ሁሉም የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጦች ከኢኮኖሚው እድገትና መዋቅራዊ ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሲሆን ይሄንንም ለውጥ ተከትሎ የፋይናስ ፍላጎቱ መጠን እየሰፋ ስለሚሄድ አቅርቦቱ ብሎም ተቋማዊ ዘመናዊነቱ በዚያው መጠን እያደገ መሄድ ያለበት መሆኑ ተመልክቷል። በበርካታ ሀገራት ለየዘርፉ የፋይናስ ፍላጎት “ልዩ የፋይናስ ተቋማት ወይንም ባንኮች” ያሉ መሆኑን በቀረቡት ጥናቶች የተመለከተ ሲሆን በዚህ ዙሪያም ቻይና እና ኮሪያን የመሰሉ ሀገራት በምሳሌነት ተጠቅሰዋል። እነዚህ ሀገራትም ልማት ባንኮች ፣ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንኮች፣የኢንዱስትሪ ባንኮችና የመሳሰሉት ልዩ ባንኮችን በየዘርፉ በማቋቋም ውጤት ያገኙበት መሆኑ ተመልክቷል።

 

 በኢትዮጵያ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ 18 ባንኮች፣ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣35 ማይክሮፋይናስ ተቋማት እና 18 ሺህ የሚሆኑ አነስተኛ የቁጠባና ብድር ተቋማት ያሉ መሆኑን ከቀረበው ጥናት መረዳት ችለናል።

 

ኢኮኖሚው እያደገና እየሰፋ ሲሄድም በዚያው መጠን የልዩ ፍላጎት ባንኮች የሚቋቋሙበትና ዘርፍ ተኮር ሆነውም የሚሰሩ መሆኑ ነው የተጠቆመው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የሚሰጠው የብድር መጠንና ለተበዳሪው የሚሰጠው የእፎይታ ጊዜም ጭምር ሳይቀር ከዚሁ የኢኮኖሚ ስፋትና ውስብስብነት ጋር አብሮ እየተለወጠ የሚሄድ መሆኑ ተመልክቷል።

 

እያደገ ካለው ኢኮኖሚ ጋር የፋይናስ ኢንዱስትሪውም በተመጣጣኝነት ሁኔታ እያደገ መሄድ ይችል ዘንድ ለውጦች የሚያስፈልጉ መሆኑን በውይይቱ ወቅት የቀረቡት ጭብቶች ያመለክታሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የፋይናሺያል መሰረተ ልማቱ እንደዚሁም የቁጥጥር አካሉም(Regulatory Body) አሰራር ጭምር አብሮ እየዘመነ መሄድ ያለበት መሆኑን ይሄው ጥናት ያመለክታል። አሁን ባለው ተጨባጭ  ሁኔታ የኢትዮጵያ የፋይናስ ተቋማት ኢንሹራንሶችን ጨምሮ ያላቸው ተወዳዳሪነት ከአፍሪካ ሀገራት አንፃር እንኳን ሲታይ ደካማ ነው ተብሏል።

 

የብድር የፋይናስ ምንጫቸውም ተቀማጭ ብቻ መሆኑን አንዳንድ ውስንነት ታይቷል። የባንኮቹ አቅም ውስንነት በብደር መጠናቸው አናሳነት፣ ብዙም የረዥም ጊዜ ብድርን የማይፈቅዱ መሆናቸውና በቴክኖሎጂ አቅማቸው ውስንነት  ተገልጿል።

Page 1 of 57

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us