You are here:መነሻ ገፅ»ኢንተርቴይመንት

 

·        ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ለተሸላሚዎቹ ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቷል


የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻቸውን በመጠቀም ትክክለኛ፣ ወቅታዊ፣ ማህበራዊና ትርፍ ያላቸውን አዝናኝ መረጃዎች በመስጠት፤ የአገራችንን ብሎም የአማራ ክልልን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና ለነበራቸው ግለሰቦችና ተቋማት ባሳለፍነው ጳጉሜ 2 ቀን 2009 ዓ.ም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ዘመራ መልቲ ሚዲያና ፕሮሞሽን እንዲሁም በላመርጌር ህትመትና ሚዲያ ፕሮዳክሽን የተሰኙ ተቋማት በጋራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አንደኛው የጣና ማህበራዊ ሚዲያ ሽልማት ለአስር የተለያዩ ዘርፎችና ለአንድ ልዩ ተሸላሚ የዕውቅና ምስክር ወረቀትና የፌስ ቡክ “ላይክ”ን አመላካች የያዘ የዋንጫ ሽልማትን እንካችሁ ብሎ አስተዋውቋቸዋል።

የጣና ማህበራዊ ሚዲያ አስር የመወዳደሪያ ዘርፎች ተብለው የተጠቀሱት በፈጣን ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃ፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በኪነ-ጥበብ፣ በበጎ አድራጎትና አካባቢ ልማት፣ በጤና መረጃ፣ በአስደማሚ ምስሎችና ትርከቶች፣ በትምህርት ምርምርና ማህበራዊ አገልግሎት፣  በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች እንዲሁም በስፖርት መረጃ እና በታሪክ ዘርፎች ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል። ለውድድሩ የቀረቡት ተወዳዳሪዎች በየዘርፉ የተመደቡበትን አካሄድ በተመለከተ የፕሮግራሙ አዘጋጆች አቶ ደምስ አያሌው እና አቶ ሰለሞን ምህረት መረጃዎችን አስተላልፈዋል። በዚህም በማህበራዊ ሚዲያ በኩል የተከፈተውን ገፅ ተከትሎ ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሠረት በ10 ዘርፎችና በአንድ ልዩ ተሸላሚ በአጠቃላይ 36 ግለሰቦችና ድርጅቶች የመጨረሻ እጩ ሆነው ቀርበዋል። ከቀረቡት ዕጩዎችም መካከል በጓደኛና በተከታይ ብዛት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተወዳዳሪዎች የተመረጡ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ የውድድሩ የመጨረሻ ውጤት የተገኘውም ከተሳታፊዎች 30 በመቶ ድምፅ እንዲሁም ከዳኞች 80 በመቶ የተወሰደውን ድምጽ በመቀመር መሆኑም ተገልጿል። ባሳለፍነው ሐሙስ ባህርዳር ከተማ በሚገኘው ብሉ ናይል ሪዞርትና ሆቴል አዳራሽ በተካሄደው የሽልማት ፕሮግራም ላይ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ለአሸናፊዎቹ ሽልማትና የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በዕለቱ በግሽ አባይ የባህል ቡድን የተሟሸው የሽልማት መድረኩ፤ በባህል ሙዚቃ ተጫዋቹ በዋኘው አሸናፊም ደምቋል። በመድረኩ የክብር እንግዳ ሆነው የታደሙት የባህርዳር ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ክብረት መሀመድ ሲሆኑ በክልሉ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ አንጋፋና ወጣት የኪነ-ጥበብ ሰዎችም መታደማቸውን ተመልክተናል።

የምሽቱ የጣና ማህበራዊ ሚዲያ የሽልማት ፕሮግራም የጀመረው በአስደማሚ ምስሎችና ትርከቶች ዘርፍ የቀረቡትን ዕጩዎች በማስተዋወቅ ነው። በዚህ ዘርፍ ህይወት ጌታቸው፣ ሲሳይ ጉዛይ እና እያዩ ገነት የመጨረሻ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፤ አሸናፊው በፎቶግራፍ ጋዜጠኝነቱ የሚታወቀው ሲሳይ ጉዛይ ሆኗል። የዘርፉን ሽልማት ያበረከተው ደግሞ በተለይም በአማራ ክልል ዕውቅ ከያኒነቱ የሚወደደው አርቲስት ስለሽ አምባው ነበር።

በመቀጠልም በበጎ አድራጎትና በአካባቢ ልማት ዘርፍ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ ጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማህበር፣ እኛ ለእኛ የበጎ ፈቃደኞች ማህበር እንዲሁም ተቀባ ተባበል በግል የመጨረሻ ዕጩ ሆነው ቀርበዋል። በዚህ ዘርፍ የተቋማት፣ የቡድኖችና የግለሰቦች ስብጥሩ ሚዛናዊነቱን የተፈታተነው ነበር ማለት ይቻላል። የዚህ ዘርፍ የዕለቱ ተሸላሚ የሆነው “እኛ ለእኛ የበጎ ፈቃደኞች ማህበር” ሲሆን፤ ሽልማታቸውን ከሕዝብ አምባ ከተወከሉት አቶ ማሩ ደስታ እጅ ተቀብለዋል።

በጤና መረጃ ዘርፍ ውስጥ የመጨረሻ ዕጩዎች ሆነው የቀረቡት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የምስራቅ ጎጃም ጤና መምሪያ እና ጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማህበር ሲሆኑ፤ አሸናፊው ደግሞ የጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማህበር በመሆን ከዶ/ር መኮንን አይችሉም እጅ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

በበርካቶች ዘንድ ትኩረትን የሳበውና በርካታ ተወዳዳሪዎም በመጨረሻ ዕጩነት የቀረቡበት የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ነው። በዚህ ዘርፍ በርካታ ተከታይ ያላቸው በቃሉ ሙሉ፣ ሸጋው ሙሉማር፣ ደረጀ ምንላርግህ፣ ሐብታሙ አዱኛ፣ ከፍያለው እሸቴ፣ ሐ/ማርያም መንግስቴ እንዲሁም በላይ በቀለ ወያ እና ውብሸት ታደለ ቀርበዋል። የዘርፉ አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው ወጣቱ ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ሲሆን፣ ሽልማቱን ከአንጋፋው አርቲስት በምናቡ ከበደ እጅ ተቀብሏል።

በመቀጠል በፈጣን ሚዛናዊና ወቅታዊ መረጃ ዘርፍ ሽልማት ተበርክቷል። በዚህ ዘርፍ የመጨረሻ ዕጩዎች ሆነው የቀረቡት ጌጡ ተመስገን እና የሺሀሳብ አበራ ናቸው። አሸናፊ ሆኖ የዕውቅና ምስክር ወረቀቱንና ዋንጫውን የወሰደው ደግሞ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ሲሆን፤ ሽልማቱን ያበረከተው ጋዜጠኛ ኃይሌ አበራ ነው።

በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የቀረቡት የመጨረሻ ዕጩዎች በዘርፉ በርካታ ስራዎችን በመስራት የሚታወቁ ግለሰቦች ናቸው። በዚህ ዘርፍ ጌትነት ተመስገን፣ ዘላለም መራዊ፣ ሄኖክ ስዩም እና ተሾመ ባላገሩ ነበሩ። አሸናፊ የሆነው በሚያቀርባቸው ባህልና ቱሪዝም ተኮር ፅሁፎቹ የሚታወቀው “ተጓዡ ጋዜጠኛ” ሄኖክ ስዩም ሆኗል። በስፍራው ያልተገኘው ሄኖክ በዘላለም መራዊ በኩል ሽልማቱን ከአርቲስት ጊዮን አለምሰገድ እጅ ተረክቧል።

አገራዊ ታሪኮቻችንን በመፈተሽና ሚዛናዊ የሆኑ ምንጭ ጠቀስ ፅሁፎችን በማስነበብ የሚታወቀው ፀሐፍት በታሪክ ዘርፍ ለውድድር ቀርበዋል። በዚህ ዘርፍ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ሁለት ተወዳዳሪዎች ብቻ ሲሆኑ፤ የሺሀሳብ አበራ እና ጌትነት ተመስገን ናቸው። የዕለቱ አሸናፊ የሆነው የሺሀሳብ አበራ ሲሆን ሽልማቱን የተቀበለው ደግሞ ከባህርዳር ከተማ የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ከአቶ በሰላም ይመኑ እጅ ነው። የሺሀሳብ አበራ በሌላም በኩል በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዘርፍም ዕጩ ሆኖ በመቅረብ የአሸናፊነቱን አክሊል ለሁለተኛ ጊዜ በመድረኩ ደፍቷል። በዚህ ዘርፍ ስር ዕጩ ሆነው የቀረቡት ደግሞ ቤተልሄም ሐብቴ፣ የዕውቀት ማዕድ፣ መላኩ አላምረው፣ ጌጡ ተመስገን፣ ዳግማዊ ዳግማዊ እና የሺሀሳብ አበራ ነበሩ።

በስፖርት መረጃ ዘርፍ የመጨረሻ ዕጩ ሆነው የቀረቡት አራት ተወዳዳሪዎች ናቸው። እነሱም ብርሃን ስፖርት፣ የአፄዎቹ ገጽ፣ ባህርዳር ከነማ እና እንዳለው ሙሉ ናቸው። በዚህም ገፅ ግለሰብ ከቡድን ጋር የተወዳደረበት አጋጣሚ መኖሩን እንደስህተት የሚጠቅሱት አልጠፉም። በዚህ ዘርፍ አሸናፊው በታዳጊ ወጣቶች የተገነባውና ስፖርታዊ መረጃዎችን በፍጥነት በመስጠት የሚታወቀው ብርሃን ስፖርት ሆኗል። በመድረኩ ተገኝተው ሽልማቱን ያበረከቱት ደግሞ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ክብረት መሀመድ ናቸው።

በምሽቱ ድምቀት ከፈጠሩት ተቋማዊ የከባድ ሚዛን በማህበራዊ ሚዲያ የትምህርት ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የንባብን ባህል ለማሳደግ አላማው አድርጎ የተቋቋመው ቡክ ፎር ኦል (Book fore all) እና አንጋፋው ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ናቸው። በዚህ መስክ አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሲሆን፤ የዩኒቨርስቲው መምህር ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ ሽልማቱን ለተቋሙ ተወካይ አበርክተዋል። በዝግጅቱ ሂደትም እንደድንገቴ የደስታ ዜና አንዳች ብስራት ከዩኒቨርስቲው ተሰምቷል። ይህውም ለዕለቱ አሸናፊዎችና ተሸላሚዎች በሙሉ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ በ2011 ዓ.ም 70 ሺህ ብር የሚገመት ነፃ የትምህርት ዕድል ማመቻቸቱም ተሰምቷል። ይህ ይበል የሚያሰኝና በቀጣይም ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸውን ለመልካም ነገር እንዲጠቀሙበት ከማስቻል አንፃር አበረታች ነው ማለት ይቻላል።

በዕለቱ የልዩ ተሸላሚነት ማዕረግን ለማግኘት በክልሉ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኪነጥበባዊና ስፖርታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ መረጃ ከመስጠት ባለፈ አርአያ መሆን የሚችሉ ግለሰቦች በዕጩነት ቀርበው ተሸልመዋል። በዚህ መልኩ ሔኖክ የኖላዊ ኃር ልጅ፣ ሰጡ ብርሃን እና መንግስቱ ዘገየ ሲቀርቡ ተሸላሚ የሆነው መንግስቱ ዘገየ ከአቶ መስፍን አድማሱ እጅ ሽልማቱን ተረክቧል።

በቀጣይ ጣና የማህበራዊ ሚዲያ ሽልማት ላዘጋጀባቸው የሚገቡ ጥቆማዎች

እንደመጀመሪያ በዘመራ መልቲ ሚዲያና ፕሮሞሽን እና በላመርጌር ህትመትና ሚዲያ ፕሮዳክሽን የተሰናዳው “ጣና የማህበራዊ ሚዲያ ሽልማት” ዝግጅት በብዙ ይበል፤ ዓመቱን ጠብቆ ደጋግሞ ይምጣ የሚያሰኝ ነው። ሆኖም ግን ሊታረሙና አስቀድሞ ዝግጅት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጥቃቅን ክፍተቶችም ታይተዋልና ለአዘጋጆቹ በቀናነት ማስታወስ እንወዳለን።

ቀዳሚውና በበርካቶች ዘንድ የምሽቱን የሽልማት አካሄድ እንዲደበዝዝ አድርጎታል የተባለለት ጉዳይ የዋንጫው ዘግይቶ መምጣት ነው። አሸናፊዎቹ ተጠርተው ወደመድረክ ሲወጡ ከምስክር ወረቀቱ ባለፈ የሽልማት ዋንጫው መሰጠት ሲገባው ዘግይቶ በስተመጨረሻ እንደገና ተጠርተው እንዲወስዱ መደረጉ ዝግጅቱን ከማደብዘዙም ባለፈ ድምቀቱን በእጅጉ አሳጥቶታል የሚሉ በርካታ ታዳሚያን አጋጥመውናል። ይህ በቀጣዮቹ ዓመታት እንደማይደገም ተስፋ አለን።

በሌላ በኩል የዕጩዎች በቁጥርና በአቅም አለመመጣጠን ጉዳይ ነው። ግለሰቦችን ከተቋማት፤ ማህበራት ከግለሰቦች ጋር በአንድ የውድድር ዘርፍ ውስጥ መቅረባቸው የሚዛኑና መጠን የሚያዛባ ይመስላል። ከዚህም ሌላ በየዘርፎቹ በዕጩነት የሚቀርቡት ተወዳዳሪዎች ቁጥር ተቀራራቢ ቢሆን መልካም ነበር። በአንዳንድ ዘርፎች እስከ ስምንት ዕጩዎች ሲቀርቡ በሌላ በኩል ደግሞ ሁለት ተወዳዳሪዎች የቀረቡበት ዘርፍ ብቻ መኖሩ የውድድሩን ስፋት ያጠበበ ይሆናል። እናም በቀጣይ ተቋማት ከተቋማት፤ ግለሰቦች ከግለሰቦች በእኩል ቁጥር ተወዳዳሪ ሆነው ቢቀርቡ መልካም ይሆናል የሚል ሃሳብ አለን።

መጠቆም የሚገባን ሌላው ነገር የልዩ ተሸላሚዎች ጉዳይ ነው። በልዩ ተሸላሚዎች ዘርፍ ምንም አይነት የዕጩ ጋጋታ ባይኖር ይመረጣል። ለፕሮግራሙም ድምቀት በሚል በሚስጥር የተመረጠ አንድ ሰው ብቻ የዕለቱ ልዩ ተሸላሚ ሆኖ ይፋ ቢደረግ የተሻለ ነውና፤ ልዩ ተሸላሚዎች ከውድድር ውጪ ቢሆኑ ይመከራል።

የመጨረሻው ሊታረም የሚገባው ጉዳይ የመድረክ አመራሩ ነው። መድረክ መሪዎች በተወዳዳሪዎቹ ዙሪያ በቂ መረጃ ያላቸው ቢሆኑ ይመረጣል። በቀጣይ የሚቻል ቢሆን አሸናፊዎች ዋንጫቸውን ከተረከቡ በኋላ አጭር ንግግር የሚያደርጉበት ዕድል ቢሰጣቸው መልካም ነው። በጣና የሚዲያ ሽልማት ምሽትም ይህ ነገር ጉራማይሌነት ባለው መልኩ የታየ ቢሆንም በቀጣይ ግን ወጥነት ባለው መልኩ ቢሰራበት ለመድረኩ ድምቀት እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም።

የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችን ሰዎች ለመልካም ነገሮች ሲጠቀሙባቸውና ለውጥም ሲያመጡባቸው መመልከት ይበል የሚያሰኝ ከመሆኑ አንፃር፤ መሰል ማበረታቻና ሽልማትም ሊሰጥባቸው የሚገባ ይገባል። ይህንን ኃላፊነት የወሰዱት የጣና የማህበራዊ ሚዲያ ሽልማት አዘጋጆች በጠቅላላ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።  

                   

ባለታሪኩና የመፅሐፉ ደራሲ - ካሊድ አደም

 

“በሀገሬ ኢትዮጵያ ኋላቀር መሆኑን በመገንዘብና እጅግ በጣም ከፍተኛ ርብርብ ተደርጐ እንዲቀር የተደረገው የሴት ልጅ ግርዛት ከአስራ አንድ ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ለልጄስ እመኛለሁ? ለመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ [ወንድ] አባት ሴት ልጁን መግረዝ ባህል ነውን? ባላንጣዬና በጥላቻ የተሞላችው የቀድሞ ባለቤቴ በዚህ በመሠረተችው የሀሰት ክስ በጭፍን አምነው የተቀበሉት የአገሪቷ ሃያል የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት የሴት መብት ተከራካሪዎች ከሳሽ እናቷ ከሁለት ዓመታት በኋላ የልጇን መገረዝ አወኩኝ ስትል አእምሯቸው በየትኛው ፍትሐዊ ህሊና ተቀበለ? ፍርዱን ለአንባቢያን እተዋለሁ።” (ገፅ፣ 21)

 

“ፍትህ ያጣ ዕንባ” ከወጣትነት እስከጐልማሳነት ኑሮውን በአሜሪካን ሀገር ያደረገውና በመሠረተውም ትዳር የአንዲት ሴት ልጅ አባት የሆነው አቶ ካሊድ አደም ያጋጠመውን ኢ-ፍትሐዊ ፍርድ በተመለከተ በቅርቡ ለንባብ ያበቃው በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ መፅሐፉ ነው። በመፅሐፉ የመግቢያ ምዕራፎች ውስጥ “ፍትሕ ምንድነው?” ሲል የሚጠይቀው ባለታሪኩና የመፅሐፉ ፀሐፊ አቶ ካሊድ እንዲህ የሚል ሀሳብ አስፍሮ እንመለከታለን፣ “… የሰው ፍጡር ከፍተኛ ጉዳትን የመቋቋም ኃይል ውስጡ አለውና፤ ተርቦ ረሃቡን ይችላል። የሚደርስበትን ተፈጥሯዊ አደጋና ሐዘንም ይችላል። ነገር ግን የሰው ነፍስ ኢ-ፍትሐዊነትን መቋቋም አይችልም።” (ገፅ፤ 26)

 

“በፍፁም አስቤ በማላውቀው ጉዳይ ሴት ልጅህን ገርዘሃል ተብዬ፤ በተቀነባበረ ክስ ለአስር ዓመታት ታስሬያለሁ” የሚለው ካሊድ ከመነሻ እስከመድረሻ ያለ ህይወቱን ፊልም በሚመስል መልኩ በቅፅ አንድ ባቀረበው ታሪኩ እንካችሁ የህይወቴን ገጾች ብሎ ያስነብበናል።

 

የመፅሐፉን ምርቃት ተከትሎ ከፀሐፊው ጋር በርከት ያሉ የመገናኛ ብዙሃን የመገናኘት ዕድሉን አግኝተዋል። የዚህ ሰው ታሪክ አሁን ላይ በአማርኛ በተፃፈው መፅሐፍ ሳቢያ በአገር ውስጥ መነጋገሪያ መሆኑን ይቀጥል እንጂ፤ ቀደም ባለው ጊዜ የበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ስቦ እንደነበር ተገልጿል። “መፅሐፉን የፃፍኩት ሐቁን ለማስረዳት ነው” የሚለው ካሊድ፤ ክፍል አንድ ብሎ በጠቀሰው በዚህ መፅሐፍ ውስጥ አስተዳደጉን፣ የመኖሪያና የትምህርት አካባቢውንና የወጣትነት ህይወቱንና የስደት መንገዱን ሁሉ ይተርካል። ከዚያም በሀሰት ተቀነባብሮብኛል ያለውን የክስ ሂደት በዝርዝር በማስረዳት በአስራ አራት ምዕራፎች ከፋፍሎ በ455 ገጾች ይተርክልናል።

 

ለተቀነባበረው የሀሰት ክስ መነሻው ከቀድሞ ባለቤቱ ፎርቹኔት ዱቤ ጋር የነበረው ትዳር በፍቺ የመጠናቀቅ ዳር-ዳርታ እንደጀመረ በብስጭትና በበቀል ልቦና ተመስርቶ መሆኑን ያስታውሳል። የንብረት ክፍፍልና የልጅ ማሳደግ ጥያቄን በተመለከተ በፍርድ ቤት የሙግት ሂደት ላይ በነበረበት ወቅት [የቀድሞ ባለቤቱ] በጥላቻ የተሞላ ሀሰተኛ ክስ ለማቀነባበር ከቤተሰቦቿ ጋር በማበር መንቀሳቀሷንም ይገልፃል። በክርክር ሂደቱ ህፃን ልጁን በፍፁም ስላለመግረዙ በቂ ነው የሚላቸውን መረጃዎች ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ ቢችልም፤ ተሰሚነት ማግኘት አለመቻሉን የሚናገረው ካሊድ፤ “የኔን ክስ በጣም ልዩ የሚያደርገው በክሱ ላይ የሚቀርቡት መረጃዎች ሁሉ በምን አይነት ሁኔታ ተንደው እንዲወደቁ መደረጋቸውን ስትመለከቱ ትረዳላችሁ።” ይላል። ከዚህም ባለፈ በሰበር ሰሚ ችሎቱ ወቅት ጠበቆቹ የአሜሪካንን ሕገ-መንግስት ስድስተኛው አንቀፅ ሙሉ በሙሉ ተወርውሮ የነበረበት ሁኔታ እንደነበር በግልፅ ታይቷል ሲል ይገልፃል።

 

በወቅቱ በፍርድ ቤት ይካሄድ የነበረውን ክርክር የሚያስታውሰው ካሊድ፤ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘትም አለው ብለው የሚያምኑ ወገኖች እንደነበሩም ያስታውሳል። ይህንንም አስተሳሰብ የሚጋራው እንደሆነ ይናገራል። ገርዘሃታል የተባለችው ልጁ አሚራ ካሊድ እንደምትባል አስታውሶ፤ አሁን ላይ እድሜዋ 17 ዓመት እንደሆናትም በናፍቆት ተሞልቶ ይናገራል። ከልጁ ከተለየ 10 ዓመታትን ያሳለፈው ካሊድ፤ የሀሰት ክሱ የተመሠረተበት ልጁ የሦስት ዓመት ከስድስት ወር ህፃን ሳለች መሆኑንም ሲቃ እየተናነቀው አስረድቷል።

 

“ፍርድ ቤቱ በፃፈው አምስት ገፅ ወረቀት ብቻ ሀብት ንብረቴን አጥቼ ለከሳሽ እንዲሰጥ ከማድረጉም ባለፈ ልጄን እስከማጣት ደረጃ አድርሶኛል” ሲል በቁጭት ተናግሯል። ከምንም በላይ አስፈሪ በነበረው የአሜሪካን እስር ቤት ቆይታው እንደሚያዝን የገለፀው ካሊድ፤ ዛሬ ለደረሰበት ቀንና ፅናት ያበቃውና ምስጢር ሲገልፅም “ከምንም በላይ የመኖር ፍላጐቴ እና ይህንን የተደበቀ ሐቅ የመናገር ጉጉቴ ሁሉን ነገር ችዬ አሁን ድረስ እንድኖር አስችሎኛል” ብሏል። በእስር ቤት ቆይታው የነበረውን ፈተና በተመለከተ “ጉነት ካውንቲ የእስር ማቆያ ክፍል” (Gwinnet County Court’s Holding Cell) በተሰኘው አምስተኛ ምዕራፍ ውስጥ የተገለፀውን አንቀፅ እንመልከት። “… ሳይኮሎጂስቷ በእርጋታ እንዳስብ በተቻለኝ መጠን እረፍት ማድረግ እንዳለብኝ፣ ከዓይኔም ድካም እንዳዩ ነገሩኝ። እኔ በሁኔታው ግራ ስለተጋባሁ በዚህ ዓይነት ክፍል ውስጥ ምን አይነት እረፍት ማድረግ አንደምችል ጠየኩ።” “ክፍሉ ይቀዘቅዛል፤ ብርድልብስ የለውም በዚህ አይነት ለመተኛት ስለማልችል የምለብሰውን ብርድልብስ እንኳን ቢሰጡኝ?” ሳይኮሎጂስቷ ለጥያቄዬ መልስ በመስጠት፤ “ይህ ክፍል የራስን ማጥፋት ለመከላከል (Suicide watch) ክፍል ስለሆነ ብርድልብስ አይፈቀድም። ባይሆን የእንቅልፍ መድሐኒት ላዝልህ እችላለሁ።” (ገፅ፤ 217) ሲል አስከፊውን ጊዜ በመፅሐፉ ገልጿል።

 

ከክሱ በፊት ለአስራ አራት ዓመታት በአሜሪካ በነፃነት ይኖር የነበረው ካሊድ አደም፤ የአሜሪካንን መሬት ሲረግጥ የ16 ዓመት ጐረምሳ እንደነበርም ያስታውሳል። የኮሌጅ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም በተለያዩ መስኮች በርካታ ስራዎችን መስራቱንም ይናገራል።

 

“ልጄን እጅግ በጣም ነው የማፈቅራት፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንደምመለከታት ጐበዝና ቆንጆ ልጅ ሆናለች። ገና በአራት ዓመቷ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ብንለያይም ሁልጊዜ ግን ስለእሷ አስባለሁ” የሚለው የ“ፍትህ ያጣ ዕንባ” መፅሐፍ ደራሲው ካሊድ፤ ልጁ በተጠና ሁኔታ በአባቷ ላይ ጥላቻ እንዲያድርባት መደረጉንም በጠበቆቹ አማካኝነት በማስረጃ ለፍርድ ቤት ማቅረቡንም ይገልፃል። “ምናልባትም ከአመት በኋላ ማለትም አስራ ስምንት ዓመት ከሞላት አባቷን የመፈለግ ሙሉ መብትና ነፃነት ስለሚኖራት፤ አንድ ቀን እንገናኛለን የሚል ተስፋ አለኝ” ይላል።

 

በአሜሪካ ኑሮው ብዙ ቢያሳልፍም ከመኖሪያ ፍቃድ ውጪ የዜግነት ጥያቄ አቅርቦ እንደማያውቅ የሚገልፀው ካሊድ፤ ምናልባትም ይሄ ነገር “የቀድሞ ባለቤቱ አሜሪካዊት” በመሆኗ ጭምር ክሱን ሳያከፋበት እንዳልቀረ ይገምታል። በሌላ በኩል ደግሞ እንኳንም ዜግነት አልጠየኩ የሚለው ካሊድ፤ ምናልባትም ከእስር ከወጣው በኋላ አሜሪካዊ ሆኜ ቢሆን ኖሮ አሁንም ለአገሬ ምድር አልበቃም ነበር ሲል ቀሪዎቹን አምስት የቁም እስር ዘመናት በሀገረ አሜሪካ የማሳለፍ ግዴታ እንደነበረበት ይጠቁማል። አሁን ላይ አሜሪካንን ስታስብ ምን ይሰማሃል? ተብሎ የተጠየቀው ካሊድ፤ “አሜካንን ሳስብ እስር ቤት ነው ትዝ የሚለኝ” ሲል ከቤተሰቡ ከሀገሩና ከወገኑ ርቆ በጭለማ ክፍል ውስጥ ያሳለፋቸው መራር አመታት በቀላሉ ከህሊናው እንደማይጠፋ ይገልፃል። የአስር ዓመታቱ የእስር ጊዜ ከባድ እንደነበር ደጋግሞ የሚገልፀው ካሊድ አዕምሮውን በስራ ለመወጠር ብዙ ስራዎችን ይሠራ እንደነበር፤ ቀደም ብሎ ይማር የነበረውን ትምህርት በተልዕኮ በመቀጠል ከሉዚያና ስቴት ዩኒቨርስቲ  እና ከካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ በአካውንቲንግ እና በማኔጀመንት ሁለት ዲግሪዎችን በእስር ቤት ቆይታው ተምሮ ስለማጠናቀቁ ይገልፃል። ከዚህም ባለፈ ክፉውን የእስር ጊዜ ለመርሳት ሲል በርካታ መፅሐፍትን የማንበብ አጋጣሚውን እንደተጠቀመበት ካሊድ ያስረዳል። “ካነበብኳቸው መፅሐፍት ጥንካሬን፣ የሰዎችን ልምድ፣ በማግኘቴ ፅናት አግኝቼባቸዋልሁ” ይላል።

 

“ፍትህ ያጣ ዕንባ” የተሰኘውን መፅሐፍ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የመተርጐም ሃሳቡ አለህ ወይ? ተብሎ የተጠየቀው ካሊድ ሲመልስ፣ “የመፅሐፉ የተፃፈበት ዋናው አላማ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነቱን እንዲያውቅ ነው። በኔ ክስ ምክንያት ብዙ ኢትዮጵያውያን አብረውኝ ወጥተው ወርደዋል፤ ለፍተዋል። እነሱን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐቁን እንዲያውቅ የፃፍኩት ነው። በጅምላ የጠፋውን የኢትዮጵያውያን ስም እንዲታደስና ሐቁ እንዲወጣ በማሰብ፤ አይዟችሁ ለማለት ነው የፃፍኩት። ወደፊት ሁኔታውን አይተን በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ለአሜሪካ ህዝብ ሊቀርብ ይችላል” ብሏል።

 

“መፅሐፉ የበርካቶችን ጥያቄዎች እነደሚመልስ ተስፋ አለኝ” የሚለው ካሊድ፤ በስልክና በኢ-ሜይል ለሚደርሱት ጥያቄዎች በመረጃና በማስረጃ የተደገፈውን “ፍትሕ ያጣ ዕንባ” መፅሐፍ በመፃፍ የታላቋን አገር አሜሪካንን የፍትህ ጉድለቶች ሚዛን ላይ አስቀምጦልናል። ይህን መፅሐፍ በእስር ላይ እያለ ማሰናዳት መጀመሩን የሚያስታውሰው ካሊድ፤ ነገር ግን ጠበቆቹ ጉዳዩን የበለጠ “ውስብስብ ያደርግብሃል” በሚል እንዳያዘገዩትም አስረድቷል።

 

“ፍትህ ያጣ ዕንባ” መፅሐፍ የተሰናዳው ሐቁን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስረዳት ነው የሚለው ካሊድ፤ ወደፊትም የኔ እውነት ሲገለጥ ካሳ ሳይሆን የፍትህን የበላይነት ማሳየት ትልቁ አላማዬ ነው ብሏል። በህይወቱ ሙሉ መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀበት ጉዳይ መሆኑን በማስረዳት፤ ሐቁ ይፋ ወጥቶ የህሊና እረፍት የሚያገኝለትን ቀን በመናፈቅ ላይ እንደሚገኝ በአፅንኦት ይናገራል።

ካሊድ አደም በእስር ላይ በነበረበት ወቅት በአገረ-አሜሪካ በእርሱ ህይወት ላይ የተመሠረተና “Mutilated kalid” (ካሊድን መበጣጠስ) በሚል ርዕስ ስር የጆርጂያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ቻርለስ መፅሐፍ አሰናድተው ነበር። በ2003 (እ.ኤ.አ) በአማዞን የመፅሐፍት የድረ-ገፅ ሽያጭ የቀረበው ይህ መፅሐፍ፤ የካሊድን የችሎት ሂደት ተንተርሶ በአመዛኙ ፖለቲካዊ እንድምታውንና ሕጉን በመፈተሽ ላይ አተኩሮ የተዘጋጀ ስራ እንደነበርም ካሊድ ተናግሯል።

 

“ብዙ መፅሐፍትን ከማንበብ ባለፈ ደራሲ ነኝ ማለት አልችልም” የሚለው ካሊድ፤ ብዙ የማንበብ ልምዴ ነው ይህንን መፅሐፍ ለማዘጋጀት የረዳኝ ሲል ስለመፅሐፉ አዘገጃጀት ተናግሯል። አክሎም “ከሁሉም በላይ አንድ ሰው ፍትህ አጥቶ ሲንገበገብ እውነቱን በፅሁፍ ቢገልፀው ይሻላል በሚል ፅፌዋለሁ” ብሏል። እናም ሥነ-ጽሁፋዊ ይዘቱን ለባለሙያዎቹ መተውን አስረድቷል።

 

ከዚህ ሁሉ የፍትህ እጦትና የእስር ስቃይ በኋላ አሁን ላይ “ነፃ ነህ፤ የተፈፀመብህ ሁሉ ስህተት ነው” ብትባል ምን ይሰማሃል ተብሎ የተጠየቀው ካሊድ፤ “ደግሞ የተፈጠርኩ ያህል ይሰማኛል” ብሏል። አሁን ላይ “ፍትህ ያጣ እንባ” የተሰኘ መፅሐፉ ለንባብ ካበቃ በኋላ ባስተካክለው ብለህ የምትቆጭበት ነገር ይኖር ይሆን በሚል ለቀረበለት ጥያቄም፤ “ይህ መፅሐፍ ክፍል አንድ ነው። ሙሉ ታሪኬ ተተርኮ አላለቀም። ይህ ስራ በመጀመሪያዎቹ ሰባት የእስሬ ዓመታት የፃፍኩት ነው። ነገር ግን ቀጣዩ መፅሐፍ የበለጠ ሙሉ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ። አሁን ግን በፍፁም ቀረ ብዬ የምቆጭበት ሀሳብ የለም” ብሏል።

 

አሁን ወደአገሬ በሰላም በመመለሴ ቤተሰቦቼንና ወገኖቼን በመገናኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ የሚለው ካሊድ፤ በወገኖቼ መሀል ስረማመድ መንፈሴ በእጅጉ እየታደሰ እንዳለም ይሰማኛል ባይ ነው። የ“ፍትህ ያጣ ዕንባ” መፅሐፍ ደራሲና ባለታሪክ ካሊድ አደም የስኬት ህይወት እንዲገጥመው እኛም በዝግጅት ክፍላችን ስም እንመኝለታለን።

* ይህ መፅሐፍ ፍትህን እስከ ሲኦልም ቢሆን ለመፈለግ ቆርጦ የተነሳን ሰው ታሪክ የሚተርክ ዳጐስ ያለ ስራ ነው።

 

እነሆ ከዘመናት በኋላ በተለየ መልኩ የኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ (ድርሰትና ደራሲንን) ከፍ የሚያደርግ የሽልማት ፕሮግራም ተካሄደ። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ “ሀ”ብሎ የተጀመረው ይህ የሽልማት ፕሮግራም “ሆሄ” የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል። ከመድረኩም ሲነገር እንደሰማነው “ሆሄ” ማለት በአለቃ ኪዳነ- ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ- ሰዋስው ወግዕዝ መዝገበ ቃላት” መሠረት “ሆሄ” ማለት ስመ - ፊደል፣ የፊደል መልክ፣ የዕውቀት መጀመሪያ፣ የዕውቀት ምንጭ፣ የዕውቀት መነሻ፣ ወደሰፊው ዕውቀት የሚያስገባ በር በማለት ይተረጉመዋል” ሲል መድረክ መሪው አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ምሽቱን አሟሽቶታል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ከትናንት በስቲያ (ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም) በተካሄደውን የሽልማት ፕሮግራም በድምቀት የከፈተው የፌዴራል ፖሊስ የማርሽ ባንድ ነው። ባንዱ አስቀድሞ የአንጋፋውን አርቲስት ጥላሁን ገሠሠን “ኢትዮጵያ -የኛ መመኪያ” እነሆ በረከት ያለን ሲሆን፤ አስከትሎ ደግሞ በተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የመጨረሻ አልበም መጠሪያ የሆነውን “ኢትዮጵያ” የተሰኘ  ሙዚቃ ተጫውቷል። ከበርካታ ተመልካቶችም በአዳራሹ ሞቅ ያለ አድናቆትን ያተረፈ አቀራረብ እንደነበር አይዘነጋም። በማስከተልም ገጣሚ፣ ተርጓሚና ሃያሲው ነብይ መኮንን ነው። ነብይ በግጥሙ የወዳጅ ጠላትን እና የጠላት ወዳጅን እየገማመደ እንዲህ ሲል አሳርጓል።

ኢጣሊያም መጣ - ሄደ ተመለሰ

ፈረንሳይም መጣ - ሄደ ተመለሰ

እንግሊዝም መጣ - ሄደ ተመለሰ

ሚናስ ብቻ ቀረ ቤት እያፈረሰ

የሚለው ግጥማችን እስከዚህ ደረሰ።

በአገራችን የንባብ ባህል እንዲዳብርና እንዲስፋፋ ለማድረግ አልሞ ጸሐፍትን በማጉላትና ትኩረት እንዲያገኙም ለማስቻል፤ መሠል የዕውቅናና የሽልማት መድረክ አስፈላጊ መሆኑም በምሽቱ ተወስቷል። በርካታ አንጋፋ ደራሲያን፣ የሥነ-ጽሁፍ ባለሙያዎችና የኪነ-ጥበብ ቤተሰቦች በታደሙበት በዚህ ደማቅ ምሽት በ2008 ዓ.ም ለንባብ በቅተው በአንባቢያን እና በዳኞች መስፈርት መሠረት የተመረጡ የሥነ -ፅሁፍ ስራዎች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

እንደመጀመሪያ በሶስት ዘርፎች ብቻ (ማለትም በረጅም ልቦለድ ዘርፍ 23 መጽሐፍት፤ በግጥም መድብል 39 መጽሐፍት እንዲሁም በህፃናት መፅሐፍት ዘርፍ 12 ስራዎች) በአጠቃላይም 74 ስራዎች ለውድድር ቀርበው ነበር። ሆሄ የሥነ-ጽሁፍ የሽልማት ድርጅት 14 አባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴዎችን ያቀፈ ሲሆን፤ በሶስቱም ዘርፎች ስር 80 በመቶ ድምጽ መስጠት የሚችሉ ሶስት -ሶስት ዳኞች ተሰይመዋል። ቀሪው የአንባቢው የድምጽ መጠን ደግሞ 20 በመቶ እንደነበር ከመድረኩ ለትውስታ ተጠቁሟል።

በዚህም መሠረት አሸናፊ ሆነው ወደመድረክ ለወጡት የዘንድሮ ባለወግ ተራዎች በአንጋፋው አርቲስት ታደሰ መስፍን የተቀረፀውን የሆሄ ዋንጫ ከክብር እንግዶች እጅ እንዲረከቡ ተደርጓል። በ2008 ዓ.ም ለንባብ ከበቁት ወጥ የህጻናት መፅሐፍት መካከል ለመጨረሻ ዙር የቀረቡት ሶስት ስራዎች ናቸው። እነሱም “የቤዛ ቡችላ” - በአስረስ በቀለ፤ “የአይጦችና የድመቶች ሰርግ” ታለጌታ ይመር እንዲሁም “ዋናተኛዋ ሶሊያና” በድጋሚ አስረስ በቀለ ለሽልማት የታጩ ሲሆን፤ አሸናፊው ስራ የአስረስ በቀለ “የቤዛ ቡችላ” የተሰኘው ሆኗል። ይህን ሽልማት ለአስረስ ያበረከቱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋና ሥነ-ፅሁፍ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ ገብሬ ናቸው። “ይህን ሽልማት አባባ ተስፋዬ በህይወት ኖረው ቢያዩልኝ ደስ ይለኝ  ነበር” ያለው አስረስ፤ ልጆችን ማገልገል የበለጠ ተመራጭ ያደርጋል ሲልም ምስጋናውን አቅርቧል።

በግጥም መድብል ዘርፍ የ2008 ዓ.ም ምርጥ የግጥም መፅሐፍ ለመባል የመጨረሻ ዕጩ ሆነው ለሽልማት የተዘረዘሩት “ኑ ግድግዳ እናፍርስ” - በኤፍሬም ስዩም፣ “የጎደሉ ገፆች” በትዕግስት ማሞ፣ “የተስፋ ክትባት” በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፤ “ፍርድ እና እርድ” በአበራ አያሌው እንዲሁም “እንቅልፍ እና ሴት” በበላይ በቀለ ወያ ሆነዋል። የምሽቱ አሸናፊ የሆነው ስራ “ፍርድ እና እርድ” ሲሆን፤ ለገጣሚው ሽልማቱን ያበረከተው ደግሞ ደራሲ፤ ገጣሚና ፀሐፊ ተውኔት አያልነህ መላቱ ናቸው። የሽልማት ስሜቱን በሚገባ መግለፅ የከበደው ገጣሚ አበረ አያሌው በአጭሩ፣ “ያልጠበኩት ነው። በመጀመሪያ ስራ መሸለም በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በጣም አመሠግናለሁ” ሲል የተሰማውን ተንፍሷል።

የምሽቱ የከባድ ሚዛን ተሸላሚ ከሆኑት የረጅም ልቦለድ ዘርፍ እጩዎች እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል። “ዝጎራ” በዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ “የስንብት ቀለማት” በአዳም ረታ፣ “መፅሐፉ” በሰብለወንጌል ነጋ፣ “ውስብሳቤ” በያለው አክሊሉ እንዲሁም “የሱፍ አበባ” በሃብታሙ አለባቸው የመጨረሻዎቹ ሆነው ቀርበዋል። በዚህ ዘርፍ እንደሚገመተው ሁሉ አሸናፊው የአንጋፋው ደራሲ አዳም ረታ ስራ የሆነው “የስንብት ቀለማት” ሆኗል። በአዳራሹ መገኘት ያልቻለው አዳም፤ በወንድሙ በለጠ ረታ በኩል ሽልማቱ እንዲደርሰው ሆኗል። ሽልማቱን ያበረከቱት ደግሞ አንጋፋው ፀሐፊና ተርጓሚ ሳህለ ስላሴ ብርሃነ ማርያም ናቸው።

በሆሄ የሥነ-ጽሁፍ የሽልማት ምሽት ተወዳድረው ካሸነፉት ባልተናነሰ፤ በተለየ መልኩ ለኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አንጋፋ ሰዎችና ተቋማት የዕውቅና ሽልማትም ተበርክቷል። “የሥነ-ፅሁፋችን ባለውለታዎች” ተብለው ከተሸለሙት መካከልም በቅደም ተከተላቸው፤ በሚዲያ ተቋም ዘርፍ የሥነ ፅሁፍ የላቀ ባለውለታ ተብሎ የተሸለመው ሸገር ኤፍ. ኤም 102.1 ሲሆን፤ ሽልማቱንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ- ጥበባት መምህር፣ ሰዓሊና ገጣሚ አገኘሁ አዳነ ድልነሳው እጅ ተቀብሏል፡ ይህም ተቋሙ ለድርሰትና ደራሲያን መነቃቃት እያበረከተ ላለው ጉልህ አስተዋፅኦ የተበረከተ እንደሆነ ከመድረኩ ተወስቷል።

ለረጅም ዘመን የትምህርት መስፋፋት የላቀ ባለውለታ በመሆን የሆሄ ተሸላሚ ሆነው የተመረጡት አቶ ማሞ ከበደ ሸንቁጥ ናቸው። ትምህርትን ለማስፋፋት ውጣውረድ የበዛበት ረጅም ጉዞን የተጓዙት እኚህ ባለውለታ፤ በትምህርት ዘርፍ ከአንደኛ ደረጃ እስከመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት አገልግለዋል። ሽልማታቸውንም ከዶ/ር ደመቀ አቺሶ ተቀብለዋል። ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላም የተሰማቸውን ስሜት ሲገልጹ፤ “እኔ ሸምግያለሁ ነገር ግን እኔ በሰራሁት ስራ እንዲህ ያለ ሽልማት ሳገኝ ሌሎች ደግሞ እንደዚህ አይነት ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት ያደርጋሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ዛሬ በተሰጠኝ ሽልማት እጅግ በጣም እኮራለሁ - አመሰግናለሁ” ብለዋል።

ሌላው በምሽቱ የዕውቅና ሽልማት የተበረከተላት ተቋም “አዲስ ህይወት የዓይነ -ስውራን ማዕከል” ሲሆን፤ ለዓይነ -ስውራን መፅሐፍትን ተደራሽ በማድረግ ባበረከተው አስተዋፅኦ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል። ማዕከሉ ሽልማቱን ከዜማ ብዕር ሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት ከደራሲ የዝና ወርቁ እጅ ተቀብሏል። የማዕከሉ ተወካይ ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት፣ “በአቅማችን የከፈትናትን ትንሽ ቤተመጽሐፍት ተመልክቶ ሆሄ የሥነ ፅሁፍ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ አድርጎ ስለጠራን ከልባችን እናመሠግናለን” ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል።

በረጅም ጊዜ የጋዜጠኝነትና የስነ-ፅሁፍ አገልግሎት የላቀ ባለውለታ ተሸላሚ ሆኖ የተመረጠው፤  በተለይም በኢትዮጵያ ሬድዮ “ከመፅሐፍት ዓለም” ፕሮግራም አቅራቢነቱ በእጅጉ የሚታወቀውና የሚደነቀው ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን ሲሆን፤ ሽልማቱን ለማበርከት በክብር እንግድነት  ወደመድረክ የተጠሩት ደግሞ አንጋፋው ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ናቸው። ሆኖም በዚህ ዘርፍ ተሸላሚ የሆነው ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን ባለመኖሩ በተወካይ አማካኝት ዋንጫው እንዲደርሰው ተደርጓል።    

በረጅም ጊዜ ሃያሲያን የሥነ- ፅሁፍ የላቀ ባለውለታ ተሸላሚ የሆኑት ደግሞ ደራሲና ሃያሲ ጋሽ አስፋው ዳምጤ ናቸው። እርሳቸውም በአዳራሹ ያልተገኙ ሲሆን፤ ደራሲ ሃይለመለኮት መዕዋል ተወካያቸው ሆኖ ሽልማታቸውን ወስዷል። ሽልማቱን ያበረከቱት ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሐፍት ኤጀንሲ ተወካይ ወ/ሮ እስከዳር ግሩም ናቸው።

የመጨረሻው የላቀ ባለውለታ የተሸለመበት ዘርፍ የህይወት ዘመን የሥነ-ፅሁፍ የላቀ ባለውለታ ተሰኝቷል። ተሸላሚው አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ሆነው ተመርጠዋል። ይህን ሽልማት በመድረኩ ተወካይ በመሆን የተቀበለው ጋዜጠኛ ሔኖክ ያሬድ ነው። የክብር እንግዳ በመሆን ሽልማቱን የሰጡት ደግሞ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ ናቸው። የአለቃ ኪዳነ ወልድን ስም በአያሌው ከሚያስጠሩት ስራዎቻቸው መካከል “መፅሐፈ ሰዋሰው ወግዕዝ መዝገበ ቃላት አዲስ” እንደሚሰኝም በመድረኩ ተጠቅሷል። ጋዜጠኛ ሔኖክ በበኩሉ ስለአለቃ ዘርዘር ያለሀሳብ ከመናገር ባለፈ ሽልማቱ “የሶስቱ - አናብስት” ሲል ለጠራቸው ማለትም የአለቃ ኪዳነ ወልድ፣ መምህራቸው ክፍለ ጊዮርጊስ እና ደቀመዝሙራቸው ደስታ ተ/ወልድ ጥረትና ስራን ይገልፅልኛል ብዬ አስባለው ሲል ሽልማቱ ለአንድ ሰው ብቻ የሚሰጥ እንዳልሆነ ከታላቅ ምስጋና ጋር አትቷል።

 

እንደማጠቃለያም እንደማሳሰቢያም እሆነ፡-

ሆሄ የሥነ -ፅሁፍ የሽልማት ዝግጅት እንደመጀመሪያ ይበል የሚያሰኝ ነው። ዓመታትንም ተሻግሮ የአገራችንን ሥነ -ፅሁፍ ከማሳደግና ከማበረታታት አንጻር ትልቅ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አለን። ከመጀመሪያው ዝግጅት በመነሳት ግን መስተካከል የሚገባቸውን ክፍተቶችን መጠቆሙ ደግ ይሆናል። የመጀመሪያው ጥቆማ አዘጋጆቹን ይመለከታል። ኢትዮጵዊ ቀለም ያለውን ሥነ ፅሁፋዊ የሽልማት ፕሮግራም እያዘጋጃችሁ “ኖዝ ኢስት ኤቨንትስ” የተሰኘ ስም መጠቀማችሁ እርስ -በእርስ የሚቃረን መስሎ ይታያል።

ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ደግሞ በአንድ የውድድር ዘርፍ ውስጥ አማራጭ ካልጠፋ በስተቀር አንድ ፀሐፊ ተደጋግሞ ባይመረጥ መልካም ነው። ለምሳሌ አስረስ በቀለ በሁለት የህጻናት መጽሐፍት ዕጩ ሆኖ መቅረቡ ቢያንስ የሌሎች ስም ከመሸለም ወዲህ ከመድረክ እንዳይጠራ አድርጓል። እርግጥ ነው የሽልማት ስራ እንደፅዋ ዕጩነት ሁሉም ጋር መዳረስ አለብ ባይባልም ቢያንስ ግን በመድረክ ስማቸው የሚነሳ ደራሲያንና ድርሰቶች በዓይነት ቢበዙ መልካም ነውና ቢታሰብባት ለማለት ነው።

የመጨረሻው አስተያየት የዝግጅቱን የመድረክ አጋፋሪነት ምርጫና ዝግጅት ይመለከታል። በተለይ በዕለቱ መድረኩን የመራው አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ግሩም እንደነበር መመስከር ይቻላል። ነገር ግን የክብር እንግዶችን ወደመድረክ ሲጠራና ሲያስተዋውቅ ልዩነታቸውን በእጅጉ አጉልቷል። በተለይም ገጣሚና ፀሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱን ለማስተዋወቅ የሄደበት እርቀትና አንጋፋውን ደራሲና ተርጓሚ ሳህለስላሴ ብርሃነማርያምን ለማስተዋወቅ የተንፋቀቀበት አካሄድ ለተመልካች አይመችም። ቢያንስ እንኳን ጋሽ ሳህለስላሴ ከሰሯቸው ስራዎች አንድ ሁለቱን በስም በመጥቀስ ማስታወሱ ማንን ገደለ?. . . በተረፈ ግን በቀጣይ በእጥፍ አድጋችሁ በጉጉት የምንጠብቀው ዓመታዊ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት ፕሮግራም ሆኖ እንደሚቀጥል ተስፋችን ነው። 

 

ከመዝናኛ ፕሮግራሞች ባለፈ በርካታ የሰብዓዊነት ተግባራት ላይ በመሳተፍና በማስተባበር የሚታወቅ ወጣት ነው። ይህን ተግባሩን በመመልከትም ይመስላል በአሜሪካን ሜሪላንድ ግዛት የሚገኘውና በሰብዓዊ ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላትን የሚሸልመው “DDEA - Humanitarian Award” የተሰኘ ተቋም በመስከረም ወር ለሚያካሂደው የሽልማት ፕሮግራም ከአገራችን ዕጩ አድርጎ የመረጠው።

“ታላቅነት ለሰብዓዊነት” በሚል ለሁለተኛ ጊዜ በአገራችን የተሰናዳው የምሥጋና እና የሽልማት ፕሮግራም የሃሳብ ጥንስሱን ያመጣው ወጣት መሳይ ሽፋ ይባላል። ይህ ወጣት ከዚህ ቀደም መሳይ ፕሮሞሽን (Mesay Promotion) በሚል ባቋቋመው ድርጅት ስር የፊልምና የሙዚቃ ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን እንዳከናወነ ይናገራል። ከተግባራቱም መካከል አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈው የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ አንዱ እንደነበር ያስታውሳል። በዚህም ሥራ ላይ የቀድሞ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሔር ተሳትፈውበት ጥሩ የሚባል ውጤት የተገኘበት እንደነበር ይናገራል። በሌላም በኩል ለሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት የተለያዩ ኩባንያዎች ያላቸውን ድጋፍ በማድረግ የገና ስጦታ እንዲያበረክቱ መድረክ በማመቻቸት ተቋሙ እንዲደገፍ ሰርቷል።

በቅርቡም ከወጣቶች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ “መጤ ባህልን በማስወገድ ትኩረት ለኤች.አይ. ቪ/ ኤድስ እንስጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ሥር ከአዲስ አበባ ኤች. አይ ቪ/ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ጋር በጋራ በመሆን በሀገራችን የሚገኙ ታዋቂና ዝነኛ ሰዎች የተሳተፉበት ወጣቱን የማንቃት ሥራ በመስራቱ ከተለያዩ አካላት ምስጋና ስለማግኘቱም ይጠቅሳል።

ከመሰል የበጎ አድራጎት ተግባራት በተጨማሪ አሁን ላይ ለተከታታይ ዓመታት ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እና ከብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ጋር በመተባበር የደም ልገሳን በተመለከተ በአዲስ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም አቶ መሳይ አስረድቷል። “ታላቅነት ለሰብዓዊነት” በተሰኘው የምሥጋናና የሽልማት ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡ ሰዎች ለህዝባቸውና ለሀገራቸው በማንኛውም መስክ ታላቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሰዎች ምስጋና የምናቀርብበት ነው ያለው አቶ መሳይ፤ በተያያዘም በእነዚህ አንጋፋ ሰዎች ስም ህብረተሰቡ የደም ልገሳ እንዲያደርግ እንቀሰቅሳለን ይላል።

“ሰዎች በብዙ ጥረትና ልፋት ከበሬታና አንቱታን ሊያተርፉ ይችላሉ። ያንን ታላቅነታቸውን ደግሞ ለማህበረሰባዊ ችግራችን መፍቻ እንዲሆነ ብንጠቀምበት የተሻለ ውጤት ማግኘት እንችላለን፤ በሚል መንፈስ የጀመርነው ፕሮግራም ነው” የሚለው አቶ መሳይ፤ ከጅማሮውም የተሳካ መሆኑን ስለማረጋገጣቸው ያስረዳል። የመጀመሪያው “ታላቅነት ለሰብዓዊነት” ዘርፍ የክብር አምባሳደር ሆነው እውቅናና ሽልማት የተበረከተላቸው ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚያብሔር ነበሩ። በእሳቸውም ስም ህዝቡ የደም ልገሳ ፕሮግራም እንዲያደርግ ተጋብዞ የተሳካ ውጤት አግኝተናል ይላል።

በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው “ታላቅነት ለሰብዓዊነት” የምስጋናና የሽልማት ፕሮግራም ደግሞ አምባሳደር ሆነው የተመረጡት የሚሊኒየሙ የትውልዱ አምባሳደር እና አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ናቸው። በእሳቸው ስም በተለያዩ የክልል ከተሞች በመዘዋወር የደም ልገሳ ፕሮግራም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከማስቻል ባለፈ በመገናኛ ብዙሃን ሊተላለፍ የሚችል የ30 ሰከንድ ደም ልገሳን የሚያስታውስ ማስታወቂያ ግጥምና ዜማ በመስራት ጋሽ ውብሸት ለፕሮግራሙ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ይናገራል። ከዚህም በተጨማሪ በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነ ነው የተባለለትን የእናቶች የእግር ጉዞ በመምራት “ልጄን ወልጄ መሣም እፈልጋሁ ደም ለግሱ” በሚል ሃሳብ በአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ መሪነት በዘጠኙም ክልሎች በመዘዋወር መስራታቸውን ያስታውሳል። በዚህም እንቅስቃሴ ታላቅነትን በማክበር ማህበረሰቡ በደም ልገሳው ላይ ተረባርቧል ባይ ነው።

በያዝነው ወር መጨረሻ በሞዛይክ ሆቴል ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን” 2ኛው ታላቅነት ለሰብዓዊነት” የተሰኘ ፕሮግራም አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የመጀመሪያው ተሸላሚ የክብር አምባሳደሩ ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሔር ተገኝተው ነበር። “ታላቅነት ለሰብዓዊነት” የሚለው አባባል እውነትም የታላቅነትን ምንነት በሚገባ የሚገልፅ ነው” ያሉ ሲሆን፤ ታላቅነት ለሰብዓዊነት ሳይሆን ለግል ጥቅም ብቻ ከሆነ ዘለቄታዊ ጊዜያዊ እንደሆነም ምሳሌ በመጥቀስ ጭምር አስረድተዋል። “ሰው የገደለ ሽፍታም ታላቅ ነኝ ብሎ ጉራውን ሊነፋ ይችላል” ያሉት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን፤ የደም ልገሳን አስፈላጊነት በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ማስተማር አስፈላጊ እንደሆነ በዝርዝር አስረድተዋል። አክለውም የመጀመሪያው “የታላቅነት ለሰብዓዊነት” አምባሳደር በመሆናቸው የተሰማቸውን ሲገልፁ፤ “የዚህ በጎ ተግባር አምባሳደር መሆን ከክብርም በላይ ነው፤ ምክንያቱም ተግባሩ በጣም አስፈላጊ ነውና” ሲሉ የራሳቸውን ገጠመኝ በማከል ተናግረዋል። በአንድ ወቅት በደርግ ዘመን መጨረሻ ገደማ በጥይት የመመታት አደጋ አጋጥሟቸው እንደነበር አስታውሰው፤ ህይወታቸውን ከሞት ያተረፈው የሚተካ ደም በማግኘታቸው እንደነበር አስታውሰዋል። “ደምን መለገስ የሰብዓዊነት ትልቁ መለያ ነው” ያሉት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ህብረተሰቡም የታላላቆቹን ፈለግ እንዲከተል ምክራቸውን ለግሰዋል።

በአሜሪካን አገር የሚገኘው የመዝናኛ እና የሰብዓዊ ተግባራት ላይ ያተኮሩ ሽልማቶችን የሚሰጥ ተቋም የመሳይ ፕሮሞሽን ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆነውን ወጣትመሳይ ሽፋን ዕጩ አድርጎ መርጦታል። ስለመመረጡ የተሰማውን ስሜት እንዲያጋራን በጠየቅነው ጊዜ፣ “በእርግጥ መታጨት ደስ ይላል። ሽልማት ሲባል ልፋትህን በቅርበት የሚያይልህ እዚሁ በአገራችን ያለ ድርጅት ቢሆን የበለጠ ደስ ይለኝ ነበር። ምክንያቱም የምትሰራው ለሀገርህ ስለሆነ። ዕውቅናውም ከሀገር ቤት ቀድሞ ቢገኝ ጥሩ ነበር” ሲል ይገልጸዋል። በውጪ ሀገር የሚንቀሳቀሱ እንዲህ አይነት ሸላሚ ድርጅቶች የአንድን ሰው በጎ ተግባር እንደሀገር ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ይመለከቱታል የሚለው መሳይ፤ ዕጩ ሆነው መቅረባቸውን ካወቁ በኋላ አስፈላጊ ናቸው ብለው የተፈለጉ መረጃዎችንም በመስጠት የሽልማቱን ቀን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ይላል።

በተለያዩ ሰብዓዊ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ታዋቂ አርቲስቶችና ግለሰቦች ቢኖሩም “ታላቅነት ለሰብዓዊነት” የተሰኘው ፕሮግራም ግን አንጋፋዎቹ ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ለምን ሆነ? በሚል ላቀረብንለት ጥያቄ አቶ መሳይ ምላሽ ሲሰጥ፣ “አንጋፋዎቹን የመረጥንበት ዋነኛው ምክንያት ታላቅነታቸውንና ታዋቂነታቸውን ለሰብዓዊ አላማ ከመጠቀም ባለፈ እግረ መንገዳችንንም ምስጋናችንን ለመግለፅ እንዲያመቸን በሚል ነው” ይላል። ይህንንም ሲያብራራ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች “የክብር ዶክትሬት” ሲሰጥ የሚመረጡት ሰዎች በሙያቸው ከ20 እስከ 25 ዓመታት ያገለገሉ መሆን እንደሚገባቸው አውቃለሁ ሲል ምሳሌ ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ በአገራችን በአንድ ነጠላ ዜማም ታዋቂ የሆኑ አርቲስቶች ይኖራሉ የሚለው መሳይ፤ ደም ከመሰባሰቡ ባለፈ ታላላቅ የምንላቸውን ሰዎች ስብዕናም ለአዲሱ ትውልድ ማጋባት (ማሸጋገር) ፍላጎታችን ነው ሲል የአመራረጡን ሂደትና ምክንያት ያስረዳል።

በቀጣይ ስለሚኖረው “የታላቅነት ለሰብዓዊነት” የምስጋናና የሽልማት ፕሮግራም ከወዲሁ የተሻለ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሚናገረው መሳይ፤ የሽልማትና የምስጋና ፕሮግራሙ ከአንድ ወደ ወደአምስት ሰዎች በማሳደግ ይከናወናል ብሏል። ከቴአትር ጥበባት፣ ከአካዳሚክ ዘርፍ፣ ከሙዚቃ ዘርፍ፣ ከስፖርት ዘርፍና ከበጎ አድራጎት/ሰብዓዊነት ዘርፍ የተመረጡ ሰዎች በስማቸው የደም ልገሳና ችግረኛ የሆኑ ህፃናት ግልፅ በሆነ መስፈርት ተለይተው ዓመታዊ የትምህርት ወጪያቸው እንዲሸፈንላቸው እናደርጋለን ብሏል።

ይህን ፕሮግራም እዚህ ደረጃ ለማድረስ ያገዙትን አካላት በተለይም፤ የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት እና አምባሳደርነታቸውን በደስታና በክብር ተቀብለው ወደሰብዓዊነት ለቀየሩት አንጋፋ ባለውለታዎቻችን ምስጋናውን አቅርቧል። አክሎም ተባባሪ ድርጅቶችና በታላቅነት ጥላ ስር ሰብዓዊነትን ላሳዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ አብሮነታቸውም እንዳይለየው ጠይቋል።

 

የበገና መምህርና ዘማሪት የትምወርቅ ሙላት

 

በጥረቷና በፍላጎቷ ከፍ ያደረገችውን የበገና አጨዋወት አሁን ላይ ለበርካቶች በማስተማር ላይ ትገኛለች። “ደጋግሜ በመጣርና አብረውኝ የሚሰሩ የዜማ አዋቂዎችን በመጠየቅ ነው ለዚህ የበቃሁት” የምትለው የዛሬዋ እንግዳችን የበገና የከበሮና የዋሽንት ስልጠናዎችን ቤት- ለቤት ጭምር በማስተማር አንቱታን ያተረፈች ዘማሪ ናት።

ገና በልጅነት ዕድሜዋ በጆሮዋ የሚንቆረቆረውን የበገና ዝማሬ በተመስጦ ታደምጥ እንደነበር የምትናገረው የዛሬዋ እንግዳች፤ አሁን ላይ በገናን ይዞ በመቃኘት በከተማችን ከሚጠቀሱ የበገና ተጫዋቾች ውስጥ አንዷ ለመሆን በቅታለች። በቅርቡም “አየሁት በዓይኔ ጎሎጎታን” የተሰኘ የበገና መዝሙር ለአድማጭ አድርሳለች። እንዲህ እንደሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማኒያን ዘንድ የፆም ወቅት ሲሆን የበገና መዝሙሮች ተዘውትረው እንደሚደመጡም የትምወርቅ ትናገራለች።

በገናን ለመማር ፅኑ ፍላጎት የነበራት የትምወርቅ ምሳሌ የምታደርጋትን ሴት በአንድ መድረክ ላይ የበገና ቅኝትን ስትደረድር እንደተመለከተች ታስታውሳለች። ሶስና ገ/ኢየሱስ የተባለችው የመጀመሪያ መምህሯ የምትፈልገውን ሁሉ ለማሳየትና ለማሰልጠን ፍቃደኛም በመሆኗ ራሷን እንደእድለኛ ትቆጥራለች።

በዕምነቱ ተከታዮች ዘንድ በገና ከሙዚቃ መሳሪያነትም በዘለለ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን የምታስረዳው የትምወርቅ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደአውደ-ምህረት ስትቀርብ በእጅጉ ፈርታም እንደነበር ታስታውሳለች። በመንፈሳዊ የዝማሬ ሥራዎች ላይ በከበሮና በዋሽንት የማጀብ ተግባርን ትፈፅም እንደነበር የምታስታውሰው የትምወርቅ፤ የመጀመሪያ የመዝሙር ስራዋ “የችግረኛን ጨኸት እግዚአብሔር ሰማ” የተሰኘ እንደነበር ገልፃለች። ያም ሆኖ ብዙ ሰው ዘንድ አለመድረሱንም አትረሳም።

በተለያዩ መድረኮች እና መንፈሳዊ ጉዞዎች ላይ በመታደም የበገና ሥራዎቿን ከማቅረብ ባለፈ ከዓመት በፊት በተካሄደው የአለም አብያተ ክርስትያናት ጉባኤም ላይ ተጋብዛ ሥራዎቿን በአፍሪካ ኮሚሽን አዳራሽ ውስጥ አቅርባ እንደነበር ትናገራለች። ይህ ጉልህ እንቅስቃሴዋ በሌሎች ወጣት ተማሪዎችም የትኩረት ምንጭ እንዳደረጋት መረዳት ይቻላል። ለዚያም ይመስላል፤ በተለያዩ ቦታዎች በገናን የምታስተምራቸው ሰዎች ከጊዜ ወደጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ስለመምጣቱ በአግርሞት የምትናገረው።

ወደእርሷ በገናን ለመማር የሚመጡትን ሰዎች ሁሉ በተመሳሳይ የምትጠይቃቸው ጥያቄ፤ “በገናን መማር የፈለጋችሁት ለምንድነው?” የሚል እንደሆነ ታስታውሳለች። ይህም በገና ያለውን የተለየ ቦታና ክብር እንዲረዱት ለማድረግ ተማሪዎቿን የበለጠ ለማዘጋጀት እንደሚረዳት ትናገራለች። አብዛኞቹ ተማሪዎች በገናን መማር የሚፈልጉት ራሳቸውን ለማረጋጋት፣ መንፈሳቸውን ዘና ለማድረግና ለፀሎት ጊዜ የፅሞና መዘመሪያ ነው ብለው ከማሰብ የመነጨ እንደሆነም ካጋጠሟት መልሶች በመነሳት ትናገራለች። ከተማሪዎቿ አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውንም ጠቆም አድርጋለች። ትምህርት ቤት ለቤትም ሆነ በእርሷ የማስተማሪያ ቦታ እንደሚሰጥም የትምወርቅ ታስረዳለች።

በትምህርት አሰጣጧ ወቅት እንደተግዳሮት የሚጠቀሰው የበገና መሣሪያን ተማሪዎቹ በግላቸው እንዲያመጡ መደረጉ መሆኑን የገለፀች ሲሆን፤ “በገና ከቦታ ቦታ በቀላሉ የማይንቀሳቀስ ከመሆኑ አንፃር ሁሉም የራሱን እንዲገዛ ተማሪዎቼን እነግራቸዋለሁ። በዚህም በትንሹ እስከ ሶስት ሺህ ብር ለግዥ ያወጣሉ” ትላለች።

“በገና ልታስታምመው የሚገባ የዜማ መሣሪያ ነው” የምትለው የትምወርቅ፤ በተረበሸችበት ስሜት ውስጥ ሆኖ በገናን በምትጫወትበት ጊዜ የሚያረጋጋት የሚያፅናናት እንደሆነም አልደበቀችም። ስለበገና አሰራር ሳይቀር የቀረበ ዕውቀት እንዳላት የምትናገረው የትምወርቅ፤ “በገና ከእንሳትና ከእፅዋት” ውህድ እንደሚሰራም ታስረዳለች። ከእንስሳት የሚወሰደው ቆዳና የበግ አንጀት (በተለይም ለአስሩ አውታሮች) የተለየ ዜማ እንዲወጣው አስፈላጊ ነው የምትለው የትምወርቅ፤ በእፅዋት በኩል ደግሞ ግዙፉን በገና የምናቆምበትና የምንቃኝባቸው የዛፍ ውጤቶች እንደሆኑ ታስታውሳለች። “የበገና አሰራሩ በርካቶችን ያስገርማቸዋል” የምትለው ዘማሪ የትምወርቅ፤ በተለይም” አስሩን አውታራት” በመደነቅ የሚመለከቱ ሰዎች ስለአሰራሩና ስለተምሳሌታዊነቱ ስታስረዳ፣ “አስሩ አውታሮች በመፅሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰውን የአስርቱ ትዕዛዛት ተምሳሌት ነው” ትላለች።

ቆየት ባለው ጊዜ የበገና ዜማዎች በፆም ጊዜ ብቻ የሚደመጥ እንደነበር እያስታወሰች፤ አሁን ላይ ግን በገናን በተለያየ ጊዜ የመጠቀም ሁኔታ እየታየ መሆኑን ትናገራለች። “ያም ሆኖ በገና የምስጋና መሣሪያ መሆኑ መረሳት የለበትም” ስትል በአፅንኦት ትናገራለች።

በቅርቡ የምናከብረው የቡሄ (የደብረ-ታቦር) በዓል ምንም እንኳን የወንዶች ቢሆንም፤ በበዓል አከባበሩ ወቅት በገናን ለምስጋና የምንጠቀምበት አጋጣሚ አለም ባይነች። በርካቶችን በበገና በማጀብና የበርካቶችን መንፈስም በበገና በማረጋጋት ስራ የተጠመደችው ዘማሪ፤ የሌሎ መንፈስ ከማደስና ከማዝናናት ባለፈ ለራሷስ ምን የተለየ ጊዜ ይኖራት ይሆን? ብለን ጠይቀናል። “ብቻዬን በፅሞና መቆየት መንፈሴን ያረጋጋኛል። ያዝናናኛልም። የብቸኝነት ጊዜዬ ውስጥ ዜማና ግጥም እፈጥራለሁ” ስትል ብቸኝነቷ ከመዝናናት ባለፈ ለፈጠራ ስራዎቿ መዳበር ፋይዳው ትልቅ እንደሆነም ትገልጻለች።  

በተለያዩ አገራት በመጓዝ በገናን በማስተዋወቅና በመጫወት የራሷን አሻራ በመተው ላይ የምትገኘው ዘማሪት የትምወርቅ ሙላት፤ በቀጣይም በገናን በተመለከተ ሰፊ ሰራዎችን ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ትገልፃለች። ከተለያዩ ሰዎች ከሚነሱላት ጥያቄዎች በመንተራስ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ “በገና ትናንትና እና ዛሬ” በሚል ርዕስ የመድረክ ስራ ለማሳየት ተሰናድታለች። ይህም የበገናን አጀማመርና ቀደምት አመጣጡን በማስተዋወቅ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ከራሷ ስራዎች ጋር በማቀናጀት ለማቅረብ እየተዘጋጀች ነው። በስራዋማ የኢትዮጵያን ቅኝቶች አንባሰልን፣ አንቺሆዬን እና በትዝታ ቅኝቶች ውስጥ በገናን የመጫወት እቅዷን ይዛ በመዘጋጀት ላይ ትገኛለች። ይህንንም ስራዋን ለህዝብ በመድረክ ለማቅረብ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን ምላሽ በማፈላለግ ላይ እንደምትገኝም ጠቁማለች። “በገናን የበለጠ ለማስተዋወቅ እፈልጋሁ” የምትለው እንግዳችን፤ በጥረቷ እዚህ እንድትደርስ የረዷትን ባለሙያዎች ሁሉ ታመሰግናለች።

እንደማስታወሻ

ሐምሌ 29 ቀን 2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ማህበረ-ቅዱሳን ስር የሚገኘው የአቡነ -ጎርጎሪዎስ ስልጠና ማዕከል በበገናና በመዝሙራት ዙሪያ የጥናት ፅሁፎችን በማቅረብ ውይይት አካሂዷል፡፡ በመድረኩም በመጥፋት ላይ ባሉት የበገናና የመዝሙራት ጉዳዮች ላይ ሊቃውንት አባቶች፣ የአቡነ-ጎርጎሪዎስ የዜማ መሣሪያዎችና የልሳነ-ግዕዝ ተመራማሪዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ግብአት የሚሆኑ ሀሳቦች አንስተው ተነጋግረዋል፡፡

 

አቶ ኤፍሬም ብርሃኑ

የሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት ፕሮግራም ኃላፊ

 

“አንብበው የወደዱትን መፅሐፍ ያሸልሙ!” ይህ ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሚካሄደው “ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” አብይ መልዕክት ነው። ኖርዝ ኢስት ኤቨንትስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፅሐፍት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ያሰናዳው “ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” ለአገራችን ሥነ-ፅሁፍ እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ ከማበርከት ባለፈ፤ ለፀሐፍቱም ሆነ ለአንባቢያኑ መስታወት መሆን የሚችል ፕሮግራም እንደሚሆን በርካቶች ከወዲሁ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። አቶ ኤፍሬም ብርሃኑ የፕሮግራሙ ኃላፊ ሲሆኑ፤ በወጣቶች ጤናና ልማት ዘርፍ በርካታ ሥራዎችንም ሰርተዋል። ዛሬ የመዝናኛ አምድ እንግዳ አድርገን ስናቀርባቸው በ“ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” ዙሪያ የሚከተሉትን ሀሳቦች አንስተን ተጨዋውተናል። መልካም ንባብ….

 

ሰንደቅ፡- “ሆሄ” የሚለው የሽልማት ድርጅቱ መጠሪያ በምን መልኩ ሊመረጥ ቻለ?

አቶ ኤፍሬም፡- ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ጥንታዊ ሀብቶቿ መካከል አንዱ የራሷ የሆነ ፊደል ያላት መሆኗ ነው። ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ የሥነ-ፅሁፍ ታሪክም በዓለም ካሉት እጅግ በጣም ቀደምት ነው። እናም የራሳችን ፊደል ባለቤቶች መሆናችንን ለማመልከት ታስቦ ነው “ሆሄ” የሚለው የተመረጠው። የሥነ-ፅሁፍ የሽልማት ፕሮግራም እንደመሆኑ ደግሞ ከፊደል ውጪ አይታሰብምና ዞሮ-ዞሮ ማንነታችን ላይ ከማተኮር የመነጨ ነው ስያሜን ለመጠቀም አስበን ነው “ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” ስንል የሰየምነው።

 

ሰንደቅ፡- ከመነሻው ይህ የሽልማት ፕሮግራም እንዴት ታሰበ? ለአገራችን ሥነ-ፅሁፍስ የሚያበረክተው ፋይዳ ምንድነው?

አቶ ኤፍሬም፡- በዋናነት መነሻ ያደረግነው የንባብ ባህልን ለማነቃቃትና የሥነ-ፅሁፍን ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚል ነው። ሥነ-ፅሁፋችንን ለማበረታታት ምን ይደረግ ስንባባል ሥነ-ፅሁፋችን ላይ ያተኮረ የሽልማት ፕሮግራም ማዘጋጀቱን ተስማማን። መሰል ፕሮግራሞች በተለይ በሥነ-ፅሁፍ ዙሪያ ቀጣይነት ባለው መልኩ ባለመኖሩ ምክንያት እኛ በየዓመቱ የሚወጡትን መፅሐፍት በተቻለ አቅም በዳኞችና በአንባቢያን ፍተሻ ላይ ተመርኩዘን ብንሸልም፤ በአንድ በኩል ሥነ-ፅሁፍን ለማበረታታት ይረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ አንባቢያንን በማነቃቃት የንባብ አቅማችንን ማጐልበት እንችላለን በሚል ነው የጀመርነው።

 

ሰንደቅ፡- “ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” ፕሮግራም መፅሐፍትን አወዳድሮ መሸለም ብቻ ነው ዓላማው?

አቶ ኤፍሬም፡- ዓላማችን  መሸለም ብቻ አይደለም። ለምሳሌ በቀጣዩ ዓመት ከፈረንሳይ የባህል ማዕከል ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ የመፅሐፍት ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ለማካሄድ በሚያዚያ ወር ዕቅድ ይዘናል። በሌላም በኩል ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመነጋገር ቀጣይነት ያለው ሥነ-ጽሁፍ ተኮር የውይይት መድረክ እንዲኖር እየሠራን ነው። የህፃናት የመፅሐፍት ሳምንትም እናዘጋጃለን ብለናል። ስለዚህ ከሽልማት ፕሮግራሙ ጐን-ለጐን ዓመቱን በሙሉ የምንሰራቸው ሥራዎች ይኖራሉ ማለት ነው።

 

ሰንደቅ፡- በግልህ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን እንዳገኘህ አውቃለሁ። መሰል ፕሮግራም በእኛ አገር ሲካሄድ ከሌሎቹ አገራት የወሰድናቸው ልምዶች ይኖሩ ይሆን?

አቶ ኤፍሬም፡- ይህንን የሽልማት ፕሮግራም ስናዘጋጅ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፍ የተመለከትናቸው ቀደምት ተመሳሳይነት ያላቸው ፕሮግራሞች አሉ። ለምሳሌ ከቀደሙት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የሽልማት ድርጅት አንዱ እና በጉልህ ተጠቃሹ ነው። እንደሚታወቀው ይህ ፕሮግራም የተደራጀ ነበር ማለት ይቻላል። እርግጥ እንደ እኛ ሥነ-ፅሁፍ ላይ ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ ዘርፎች ላይ ነው የሚያተኩረው። ከዚያም ሌላ ከቅርብ ጊዜው የመገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት የሚባል ተቋቁሞ እንደነበር እናስታውሳለን። ከውጪም የተመለከትናቸው አሉ። በተለይ በመፅሐፍት ዙሪያ በርካታ ፕሮግራሞች ይሰራሉ። ለዛም የሕትመት ኢንዱስትሪው ጠንካራ መሆኑ ማሳያ ነው። ለምሳሌ ከአፍሪካ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካና ጋና በመፅሐፍት ዙሪያ አነቃቂ ሥራዎችን ከሚሰሩ ግንባር ቀደምት አገሮች ተርታ የሚመደቡ ናቸው። ወደ እኛ ፕሮግራም ስንመጣ እንግዲህ ደረጃውን ጠብቆ እንዲቀጥል፤ በዋናነትም በዘርፉ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች (ማለትም ፀሐፊያኑ፣ አንባቢያኑ፣ አሳታሚዎቹና በመፅሐፍት ዙሪያ የሚሰሩ ሰዎች በሙሉ) የሚሳተፉበት ለማድረግ እየሰራን ነው። እንደመጀመሪያ እስካሁን ያለው እንቅስቃሴያችን ጥሩ ነው።

 

ሰንደቅ፡- በርካታ ባለሙያዎችን ባቀፈ ኮሚቴ የሚመራ የሽልማት ፕሮግራም አዘጋጅታችሁ፤ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኙ ይታወቃል። ምን ያህል ስራዎችን ገምግማችሁ ለመጨረሻ ዙር ዕጩ አደረጋችሁ?

አቶ ኤፍሬም፡- በ2008 ዓ.ም የታተሙ መፅሐፍትን ነው አወዳድረን ለመሸለም የተቀበልነው። እንዳልከው ይህን ፕሮግራም የማያስተባብሩ አስራ አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን እየሰራ ይገኛል። በረጅም ልቦለድ ዘርፍ ወደሃያ ሦስት መፅሐፍትን ነው ያገኘነው፤ ከዚህም ውስጥ ‘ዝጎራ’፣ ‘የስንብት ቀለማት’፣ ‘መፅሐፉ’፣ ‘ውስብሳቤ’ እና ‘የሱፍ አበባ’ የተሰኙ መፅሐፍት ለመጨረሻው ዙር ቀርበዋል። በግጥም ዘርፍ ደግሞ ወደ ሰላሳ ዘጠኝ የሚደርሱ ሥራዎችን ተመልክተናል፡ ከእነዚህም ውስጥ፤ ‘ኑ ግድግዳ እናፍርስ’፣ ‘የጎደሉ ገጾች’፣ ‘የተስፋ ክትባት’፣ ‘ፍርድ እና እርድ’፣ እንዲሁም ‘እንቅልፍና ሴት’ የተሰኙ ሥራዎች ለመጨረሻው ዙር ቀርበዋል። ሌላው ዘርፍ የልጆች መፅሐፍት የሚል ነው። ከዚህ ዘርፍ ወደ አስራ ሁለት የሚደርሱ መፅሐፍትን አግኝተናል፤ ነገር ግን ለመጨረሻው ዙር የቀረቡት ‘የቤዛ ቡችላ’፣ ‘የአይጦችና የድመቶች ሰርግ’ እና ‘ዋናተኛዋ ሶሊያና’ የተሰኙ ሦስት መፅሐፍት ናቸው። በዋነኛነት ለውድድር የቀረቡት መፅሐፍት በሙሉ በኢትዮጵያውያን ፀሐፍት የተፃፉና ወጥ ታሪኮችን የያዙ በሚል ነው የመረጥናቸው። በመሆኑም በተለይ የልጆች መፅሐፍት አብዛኞቹ ትርጉም ስራዎች ሆነው ስለመጡልን ሳንቀበላቸው ቀርተናል።

 

ሰንደቅ፡- የመወዳደሪያ ዘርፎች ለምን አነሱ?... በኢትዮጵያ የሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ የትርጉም ሥራዎችም የራሳቸው ድርሻ አላቸው የሚሉ ባለሙያዎች አሉና ወደፊት ዘርፎቹን በማስፋት እንዲካተቱ የማድረግ ሀሳብስ ይኖራል?

አቶ ኤፍሬም፡- እውነት ነው። እንግዲህ በዚህ ዓመት በሦስቱ ዘርፎች በመጀመር በቀጣይ እያሳደግን ለመምጣት ሀሳቡ አለን። በቀጣይ ዓመት እናካትታለን ብለን ካሰብናቸው መካከል የአጫጭር ልቦለድ ሥራዎችን፤ የትርጉም ሥራዎችን፤ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያሳትማቸውን የምርምር ሥራዎችንም የሚዳሰሱበትና የሚተዋወቁበትን መንገድ እንፈልጋለን ብለናል። ስለዚህ ዘርፎቹ በቀጣይ ሰፋ ማለታቸው አይቀርም።

 

ሰንደቅ፡- ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ለሚካሄደው የሽልማት ፕሮግራም ከዳኞች በተጨማሪ የአንባቢያን ድምፅ በምን መልኩ ይካተታል?

አቶ ኤፍሬም፡- ስንጀምር ምንድነው ያደረግነው፤ የተለያዩ የሽልማት ፕሮግራሞችን ተሞክሮ በመውሰድ ሦስት-ሦስት ዳኞችን በእያንዳንዱ ዘርፍ እንዲኖሩ አድርገናል። እነዚህ ዳኞች በስፋት በሥነ-ፅሁፍ ዙሪያ የሚታወቁ ደራሲያን፣ የሥነ-ፅሁፍ ተመራማሪዎች እና የሚታመኑ ባለሙያዎች የተካተቱባቸው ናቸው። ከዳኞቹ ባሻገር አሁን የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ታውቀዋል። እኛ የምንሸልመው አንደኛ የወጡትን ሥራዎች ነው። ይህ የተሳካ እንዲሆንም አንባቢያን የራሳቸውን ድምፅ እንዲሰጡ በተለያዩ መንገዶች መፅሐፍቱን በማስተዋወቅ እንዲመርጧቸው ከሐምሌ 20 እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ እያስተዋወቅን እንገኛለን። በነገራችን ላይ የአንባቢው ድምፅ ከአጠቃላዩ 20 በመቶ የሚሆነውን ይይዛል። የዳኞቹ 80 በመቶ ሲሆን፤ የድምር ውጤቱ በሽልማቱ ዕለት ይታወቃል። ስለሆነም አንባቢያን አንብበው የወደዱትን መፅሐፍ ለመሸለም በስልክ 0988-12 12 12 በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ወይም ደግሞ በፌስ ቡክ እና በሽልማቱ የትዊተር አድራሻ በኩል ለመጨረሻዎቹ ዕጩ መፅሐፍት ደረጃ መስጠት ይችላሉ ማለት ነው።

 

ሰንደቅ፡- ከሽልማትና ከዕውቅናው ባለፈ ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማትን ያሸነፉ ደራሲያን ምን የተለየ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል?

አቶ ኤፍሬም፡- በዋናነት ከመነሻው ያሰብነው የምንሰጠው ሽልማት እንዳለ ሆኖ የሚያገኙት ዕውቅና ትልቅ እንዲሆን ለማድረግ ነው። የሽልማቱ ነገር በዕለቱ በአዳራሽ ውስጥ ብቻ የሚያልቅ አይደለም። ለምሳሌ አንድ ጥሩ ነገር ያደረግነው ከፈረንሳይ የባህል ተቋም ጋር በመነጋገር ከሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት አሸናፊ የሆኑትን መፅሐፍት ወደ ውጪ ቋንቋ በመተርጐም በፈረንሳይ አገር እንዲታተም ለማድረግ እየሠራን ነው። ይህም አሸናፊዎቹ መፅሐፍት ተተርጉመው ዓለም አቀፍ አንባቢያን ዘንድ እንዲደርሱ ለማድረግ እየሠራን ነው። ከዚያም ባሻገር በተለያዩ አገራት አጫጭር ሥልጠናዎችን የሚያገኙበት መንገድ ይመቻቻል። በውጪ ሀገር የሚካሄዱ መሰል የመፅሐፍት ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እስከማመቻቸት የሚደርስ ሥራ ለመሥራት እየተዘጋጀን እንገኛለን።

 

ሰንደቅ፡- እስካሁን በሄዳችሁበት ሂደት እንደተግዳሮት የሚጠቀሱ ነገሮች አሉ?

አቶ ኤፍሬም፡- በዋናነት መፅሐፍቱን የማግኘት ፈተና ገጥሞን ነበር። በተለይም የቤተ-መዛግብት እና ቤተ-መፅሐፍት ኤጀንሲ በአገሪቱ ውስጥ የሚታተሙ ሕትመቶች በሙሉ ይኖሩታል ተብሎ ስለሚታሰብ በአንድ ላይ ይገኛሉ የሚል ሀሳብ ነበረን። ነገር ግን በ2008 ዓ.ም የወጡትን መፅሐፍት በሙሉ ማግኘት አልተቻለም። በዓመቱ ለሕትመት የበቁ መፅሐፍትን ለማግኘት ሁለት ሦስት መንገዶችን ተጠቅመናል። ከዛም ባሻገር የሚጠቀስ ጉልህ ችግር የለም። ግን ይሄ የመጀመሪያ ሥራችን እንደመሆኑ ለቀጣይ መማሪያችንም ጭምር ሆኖ አልፏል።

 

ሰንደቅ፡- አሸናፊዎቹ የሚያገኙት ሽልማት ምን-ምን ያካትታል?

አቶ ኤፍሬም፡- ለአሸናፊዎቹ የሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት ዓርማ ያለበትን ሽልማት ከማበርከት ባለፈ፤ የገንዘብ ሽልማት እንዲኖረው አስበናል። ከዚያ ውጪ ግን በዚህ የሽልማት ፕሮግራም “ሒደት” ውስጥ ያለፉ መፅሐፍትን እንዴት ነው በትልቁ የምናስተዋውቃቸው የሚለው ነገር በጥልቀት አስበን እየሰራንበት ነው። ከተቻለም መፅሐፍቱን ወደፊልም የመቀየር ሀሳብም ይዘናል።

 

“ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” ይህ እንደዘበት ተደጋግሞ የሚነገርና ትልቅ ትርጉም ያለው አባባል ነው። ያነበበ ሰው ሙሉ መረጃ ያለው፤ የጠለቀ ዕውቀት ያለው፤ ዓለምን በሚገባ የተረዳና ደስተኛ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ማንበብ ምን ያህል መንፈስን እንደሚያድስ በመግለፅ ሲፈልጉ ቻይናዊያን እንዲህ ይላሉ፤ “መፅሐፍ በኪስ የሚያዝ፤ መንፈስን የሚያድስ የአትክልት ስፍራ ነው”። ለዛም ሳይሆን አይቀርም “መጽሐፍት ዓለምን በሞላ ህያው አድርገው የሚያሳዩ የመንፈስ ምግቦች ናቸው” የምንለው።

እነሆ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ሶስተኛው “ንባብ ለህይወት” የመጽሐፍት አውደ-ርዕይ ከሐምሌ 21 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል ተሰናድቷል። ከሆድ በተረፈ ለመንፈስ የሚሰነቅበት ይህ የመፅሐፍት አውደ-ርዕይ ስለመጽሀፍትና ስለፀሀፍቱ ብዙ የሚባልበት፤ ጥናትና ምርምር የሚቀርብበት ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል። ታዲያ ስለመፅሐፍትና ስለንባብ ካነሳን አይቀር ከወር በፊት የተካሄደ አንድ የውይይት መድረክ ትዝ ይለኛል። “ሀገራዊ እሴትና ንባብ ለሰላም -በኢትዮጵያ” በሚል አብይ ርዕስ ስር ህዝባዊ ገለፃ ተካሂዶ ነበር። የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሀፍት ኤጀንሲ ከዓለም እርቅና ሰላም ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በተሰናዳው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ በርካታ ንባብና መፅሐፍት ተኮር ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል።

የጥናት ፅሁፍን ያቀረበው ጋዜጠኛ ሚካኤል አለማየሁ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሀሳቦችን አቅርቧል። የማህበሰብ ጤና ባለሙያው ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ በአወያይነት በተሠየሙበት መድረክ ላይ ሀገራዊ እሴትና ንባብን የሚመለከቱ ሃሳቦች ውይይት ተደርጎባቸዋል። ሰላምን በተመለከተ ቀደምት አባቶቻችን በርካታ ተግባራትን ይፈፅሙ እንደነበር ያስታወሰው ጋዜጠኛ ሚካኤል፤ አሁን ድረስ የአብሮነትና የሰላም እርሾ የሆኑ ሃሳቦችን ከአባቶቻችን አግኝተናል በማለት ይጀምራል። አሁን ላይ እሴቶቻችንን ለማጉላትና ለማስተዋወቅ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይቀር በአንድ ማህበረሰብ ባህላዊ እሴት ላይ ያተኮረውን “ፎብሎር” የተሰኘ ትምህርት ዘርፍ በመሰጠት ላይ ይገኛል ብሏል።

ህዝባዊ ክንውን ጥበባት ላይ የሚያተኩረው “ፎክሎር” የአንድን ማህበረሰብ ሥነ-ቃላዊ ሀብት በእጅጉ እንደሚመረምር በማስታወስ የዶ/ር ፍቃደ አዘዘን ሃሳብ ለማጠናከሪያነት ይጠቅሳል። ማህበረሰባችን በፎክሎር ውስጥ ሲታይ ወደስድስት የሚቆጠሩ እሴቶችን አጠቃሎ ይይዛል ያለው ሃሳብ አቅራቢው ሥነ-ቃልን፣ ሀገረሰባዊ ልማድን፣ ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባትን፣ ቁሳዊ ባህልን፣ ሀገረ ሰባዊ ህክምናን እና ማህበረሰባዊ የፖለቲካ ተቋማትን በዝርዝር አቅርቧል።

እነዚህን የእሴት ማጠንጠኛዎች በመፈተሽና በማወቅ አንድ ማህበረሰብ ከራሱ ጋር፣ ከፈጣሪው ጋር፣ ከተፈጥሮና ከመሪው ጋር ተግባብቶ እንዲኖር ለማስቻል የፎክሎር ጥናት አስፈላጊ መሆኑ ተወስቷል። “የረጅም ጊዜ ባህልና ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን ስንል፤ ህልውናችንን ማስቀጠል የሚያስችሉ እሴቶች ባለቤት ነን ማለት ነው” ያለው ሀሳብ አቅራቢው ጋዜጠኛ ሚካኤል፤ አለበለዚያ ግን እንጠፋ ነበር ሲል አፅንኦት በመስጠት ይገልጸዋል።

በአገራችን ለምንፈልገው ሰላም “ፍቅር-ሰብ” ትልቁ መልስ ነው የሚለው ጋዜጠኛ ሚካኤል፤ “ፍቅረ-ሳብ” ደግሞ ዕድሜን፣ ፆታን፣ ሃይማኖትን መሠረት ያላደረገ ነገር ግን ሰውነትን ብቻ የሚመለከት ጥልቅ አስተሳሰብ ነው ሲል ያስረዳል። የሩቅ አገር ስደተኞችን እና እንግዳ ተቀባይነታችን፣ ሆቴል ባልነበረበት ወቅት እንግዳ አሳዳሪነታችንን በማስታወስ ጨዋነትና መልካም ስብዕና ለሠላም ያለውን ፋይዳ አመላክቷል። አሁን ላይ በዘመናዊ አኗኗር ዘይቤ ውስጥ ፍቅረ-ነዋይ እየገዘፈ መምጣቱን ያመለከተው ሃሳብ አቅራቢው፤ ይህ እየበረታ ከሄደ ደግሞ ልጓሙ እንዳያጥረን እሰጋለሁ ባይ ነው።

መልካም የሆኑ እሴቶቻችንን ጠብቆ ለማቆየት ንባብ ያስፈልገናል የሚለው ሚካኤል፤ ዘመን የተሻገሩ እሴቶቻችንን በተለይም ሥነ-ቃላዊዎቹን ወደፅሁፍ ማምጣት ግድ ነው ይላል። “በቃል ያለ ይረሳል በፅሁፍ ያለ ይወረሳል” የሚለውን ሀገራዊ አበባል በማስታወስ የፅሁፍን አስፈላጊነት አብራርተዋል። ንባብን በተመለከተ “ጳውሎዊነት” ያስፈልገናል የሚለው ሀሳብ አቅራቢው፤ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ህዝባዊ የታሪክ ፀሐፊውን ጋሽ ጳውሎስ ኞኞን እንደምሳሌ አስቀምጧል። ጳውሎስ ትምህርቱን ያቋረጠው ከአራተኛ ክፍል ቢሆንም ብዙ በማንበብ የነበረበትን ክፍተት መሙላቱን ይናገራል። ይህ ሰው ከማንበቡም በላይ አስራ አምስት መፅሐፍት ለንባብ ከማብቃቱ ባሻገር፤ ስድስት ስራዎቹ የህትመትን ብርሃን እየተጠባበቁ ነው ሲል እማኝ እየጠቀሰ ያስረዳል።

ጳውሎስ ኞኞ ጽፏቸው ካልታተሙት ስድስት መፅሐፍት መካከል አንዱ “የኢትዮጵያ ኢንሳይኮሎፒዲያ” ነው ያለው ጋዜጠኛ ሚካኤል፤ ሰውዬው ምን ያህል በግል ንባቡ ተመራማሪና አዋቂ እንደነበር ያስረዳል። በቅርቡም ይህን መፅሐፍ ጀርመኖች ሰርተውት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንደሚገኝ እግረመንገዱን ጠቁሟል። ለዚህም “ጳውሎሳዊነት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲያትት፤ “ራስን በንባብ ወደአዋቂነት ማምጣት ነው” ሲል ይዘረዝራል። ንባባችንን ከጳውሎሳዊነት አንጻር የቃኘው ሀሳብ አቅራቢው፤ “የትምህርት ደረጃችን ዲፕሎማም ይሁን፣ ዲግሪም ይሁን ሁለተኛ ዲግሪም ይሁን ንባብ ካልተጨመረበት ዋጋ የለውም” ሲል ይደመድማል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ውስጥ ንባብን መሠረት ያደረገ የትምህርት አሰጣጥ አለመኖሩ ትልቁ ችግር ነው የተባለ ሲሆን፤ ነገር ግን በራሳችን ፈቅደን ልናዳብረው የሚገባውን አንባቢነት ካለማዳበራችን አንጻር ከተወቃሽነት ነፃ አያስብለንም ሲል ይተቻል። “ንባብ ለሰላምም ለእድገትም ሆነ ለልማት መሠረታዊ ነገር ነው” ሲል የሚሞግተው ሃሳብ አቅራቢው፤ “ነገር ግን ምን አይነት ንባብ ነው ማንበብ ያለብን?” ሲልም ይጠይቃል። በተለይም አሁን ላይ ከሉዑላዊነትና ከቴክኖሎጂ ተጽዕኖ አንጻር በመዘርዘር፤ ቀደም ያለው ትውልድ ለቴክኖሎጂ ቀዳዳ ያልተዳረገ በመሆኑ መፅሐፍትን በተሻለ የማንበብ ዕድሉን (ወዶም ይሁን ተገዶ) አግኝቷል ሲል ያትታል። አሁን ግን እኛ አንፈልግም ብንል እንኳን የሚፈታተነን ብዙ የቴክኖሎጂ ማማለሎች በዙሪያችን አንዣበዋል ሲል የዘመኑን ዕድልና ፈተና በጥምረት ያሳየናል።

አሁን ባለንበት አለምና የቴክኖሎጂ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ስለጠንካራ አንባቢነት ስናስብ “ጳውሎሳዊነትን” ማስታወስ ይገባናል። ግንቦት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ከተለየን 25ኛ ዓመቱን የያዘው ጋሽ ጳውሎስ ኞኞ በስሙ ለመታሰቢያነት የሚውል ተቋም አለመኖሩ በራሱ አሳሳቢ መሆኑን የተናገረው ሃሳብ አቅራቢው፤ በአንዳንድ ወጣቶችና ማህበራት የሚሰራውን ስራ ግን ሳያደንቅ አላለፈም። “ጳውሎን የሚዘክር ነገር ማቆም አንባቢነትን ማበረታታት” እንደሆነም ያስታውሳል።

ንባብን ከአፀደ እስከ ህፃናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ በማስፋፋት ባህል እንደሆን መሠራት አለበት የሚለው ሚካኤል፤ ይህ እንዴት ይሳካል ለሚለው ጥያቄ እሴቶቻችንን በመመርመር ይመለሳል ባይ ነው። ለዚህም ነው፤ በመግቢያችን ላይ “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” የሚለውን የተደጋገመ አባባል መጥቀስ ያስፈለገን።

አንድ ሰው ጥሩ አንባቢ ነው የሚባለው ስለህይወት፣ ስለሀገሩና አለም ታሪክ፣ ስለተፈጥሮና ማህበረሰቡ በሚገባ እንዲያውቅ በጥልቀት መመርመር ሲችል ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የውይይት ሀሳብ አቅራቢው እንደጠቀሰው በዚህ ዘመን “ጳውሎሳዊነት” ጎልቶ መውጣት ይኖርበታል። ለዚህም ይሆን ዘንድ ምቹ የመፅሐፍት አውደ-ርዕይዎችና በርካታ የህትመት ውጤቶች አሉንና ልንጠቀምባቸው ይገባል እንላለን። በመጨረሻም እንዲህ እንላለን፣ “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል፤ ጳውሎሳዊነት ይለምልም!!!”

 

የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ቅርስና ኪነ-ጥበብን ከማስተዋወቅ ባለፈ ታላቋን ሀገር በአንድ ግቢ ውስጥ የማሳየት አቅም ያለው ማዕከል ነው። ይህ የነገስታትን ታሪክ፤ የታሪካዊ ቦታዎችን፣ ባህላዊ እሴቶችን እና ዕደ-ጥበቦችን በምስል አስደግፎ በማስተዋወቅና የጎብኚዎችን ቀልብ በመግዛት ለበርካታ ዓመታት በመቆየት ዕውቅናን ያተረፈው ስፍራ “ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከል” ይሰኛል። የዚህ ማዕከል እናት ድርጅት ደግሞ “The Other face of Ethiopia` ሲባል፤ የተመሠረተውም ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በፔሩ ርዕሰ ከተማ ሊማ መሆኑን ከመስራችና ባለቤቷ ወ/ሮ ሳቤላ በላይነሽ አባይ ለመረዳት ችለናል።

የኢትዮጵያን በጎ ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች ለመላው አለም ለማስተዋወቅ በርካታ ስራዎችን የሰራው ይህ ማዕከል በላቲን አሜሪካ፣ በፔሩ ዋና ከተማ ሊማ የተፀነሰ ሲሆን፤ በእናት ድርጅቱም “The Other face  of Ethiopia” ጥላ ስር ሆኖ ዋንኛ አላማውም በውጪ ዓለም በረሃብና በእርስ በእርስ ጦርነት ብቻ በተዛባ መልኩ የተቀረፀውን የኢትዮጵያን ገፅታ ለመላው አለም በተሻለና ብሩህ በሆነ መልኩ ለማስተዋወቅ ያለመ ነው። ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ የመጀመሪያ የግል ማዕከል ሆኖ የተቋቋመው “ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከል” የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን አበይት መገለጫ የሆኑት ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴቶችን በስፋት ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ጎብኚዎች (ቱሪስቶች) ሲያስተዋውቅ ቆይቷል። በተለምዶ በጎብኚዎች ዘንድ “ትንሿ ኢትዮጵያ” በመባል የሚታወቀው ይህ የባህል ማዕከል በበርካቶች ዘንድ እውቅና የተሰጠው ነው።   

በአገራችን የመጀመሪያ የግል የባህል ማዕከል ተብሎ ዕውቅናን ያገኘውና ከሜክሲኮ ወደቄራ በሚወስደው መንገድ ላይ ቡልጋሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆመው ማዕከሉ አሁን ላይ የመፍረስ ስጋት አጋጥሞታል። ከአምስት ዓመታት በላይ በክርክር የቆየው የዚህ ማዕከል ጉዳይ አሁን ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ የሚናገሩት የማዕከሉ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሳቤላ፤ “ይህ ቤት ኢትዮጵያን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ጎብኚዎች የሚያስተዋውቅ  ማዕከል እንጂ እንደማንኛውም የግለሰብ መኖሪያ ይፍረስ ተብሎ የሚገለፅ አይደለም። እኔም የአገሪቱን ልማት የማደናቀፍ ተደርጎ መተርጎም የለበትም” ሲሉ ባሳለፍነው አርብ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙሃን የቅሬታ ሃሳባቸውን ገልፀዋል።

ማዕከሉን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ በሚያስችል መልኩ ከከተማዋ ከንቲባ ጋር ጭምር በመነጋገር አንድ ኮሚቴ መቋቋሙን የሚገልፁት ደግሞ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገ/ፃድቅ ሀጎስ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት ሁኔታውን በማጣራት ላይ እንገኛለን፤ ይህ ማዕከል በግለሰብ ተነሳሽነት የተቋቋመ ከመሆኑ አንፃር ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው፤ ከከንቲባው ጽ/ቤት ጋር በመነጋገር ማዕከሉን ከመፍረስ ስጋት ለመታደግ እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። “ምንም እንኳን መንገድ ልማት ቢሆንም ከልማት በላይ ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ስለሆነ በጋራ ተነጋግረን ችግሩን እንፈታዋለን የሚል ተስፋ አለ” ብለዋል። አሁን ላይ የተቋቋመው ኮሚቴ በእርሳቸው አነሳሽነት መቋቋሙን ያመለከቱት አቶ ገ/ጻድቅ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ማዕከሉን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ማዕከሉ የአገራችንን ባህልና ቱሪዝም ከማነቃቃት አንፃር ያበረከተውን አስተዋፅኦ በሚመለከት የዕውቅና እና የምስጋና የምስክር ወረቀት ማግኘቱን ያስታወሱት ወ/ሮ ሳቤላ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቋሙን ዋጋ የሚያሳጡ ክስተቶች ገፍተው መምጣታቸው አሳዝነውኛል ሲሉ ተናግረዋል። ለቅሬታው መባባስ ምክንያት የሆነው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደርና ከተማ ማደስ ጽ/ቤት ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም በማዕከሉ በር ላይ ለጥፎት የሄደው ማስታወቂያ ነው። በማስታወቂያም የቤቱን ልኬት ለመውሰድ በተደረገ ጥረት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የልማት እንቅፋት መሆናቸውን ከመግለፁም ባለፈ፤ ይህ ደብዳቤ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ የስራ ቀናት ወደመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽ/ቤት ቀርበው ሪፖርት ካላደረጉ እርምጃ እንደሚወስዱ ያሳስባል። ሆኖም ግን ወ/ሮ ሳቤላ ልኬቱ ተለክቶ መስመርም ተሰምሮ እንደነበር አስታውሰው ይህ አግባብነት የሌለው ማስታወቂያ ነው ሲሉ ተችተዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዮናስ ደስታ በበኩላቸው፤ ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከልን በተመለከተ የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸው፤ ነገር ግን ከዚህ በፊት ማዕከሉን በሚመለከት መንገድ የሚሰራው አካል በዲዛይኑ ላይ በጥብቅ እንዲያስብበት አስገንዝበን ነበር ብለዋል። “ማዕከሉ የኔ የሚባል ሳይሆን የኛ የምንላቸውን ባህሎችና ታሪኮች የሚያስተዋውቅ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከልማት ጋር በተገናኘ መፍረስ ካለበት እንኳን በቅድሚያ አሉ የምንላቸው አማራጮች መፈተሸ ይኖባቸዋል ብለዋል። ይህም ካልሆነ ሌላ ምትክ የሚሆን ቦታ በመፈለግ በተመሳሳይ ማዕከሉ እንዲቆም ቢደረግ ለሀገርም ለትውልድም የሚሆን ይዘት አለው ይላሉ።

የባህል ማዕከሉን በተመለከተ የውሳኔ ሃሳብ መስጠታቸውን ያመለከቱት የብሔራዊ ባህል ማዕከል ኃላፊ ዶ/ር እልፍነሽ ኃይሉ፤ የማዕከሉን አስፈላጊነት በሚመለከት ሃሳብ የሰጡ ቢሆንም ከልማት ጋር በተገናኘ ያለውን ጉዳይ ግን መወሰን አንችልም ብለዋል። ማዕከሉ ባለበት ሁኔታ በሩ ቢፈርስ የሚያሳያቸው የታሪክ ቅርሶች የሆኑ ምልክቶችም አብረው ሊፈርሱ ስለሚችሉ የሚመለከተው አካል ጥንቃቄ እንዲያደርግ የብሔራዊ ባህል ማዕከሉ ሃሳቡን አስቀምጧል።

ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከልን በተመለከተ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊው አቶ ገ/ጻዲቅ ሐጎስ ሲናገሩ፤ “የተወራው ነገር በራስ ተነሳሽነት ከመሆኑም ባለፈ የብሄር ብሄረሰቦችን ታሪክና ማንነት የሚያሳይ ነው። ጥሩ ስራ እንደተሰራም አስባለሁ” ይህ ማዕከል በዜጎች ቢጎበኝ ጥቅም ያለው ስለሆነ አተኩረን እየሰራን ነው” ብለዋል።  

ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከሉ ከአፄ ቴዎድሮስ አንስቶ እስከ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ድረስ ኢትዮጵያን በመምራት የታሪክ አሻራ የነበራቸውን ሰዎች፤ የሥነ-ስዕል ጥበብ በሚታይባቸው ምስሎች በማስደገፍ በግቢው ለጎብኚዎች ያሳያል። የማዕከሉ መስራችና ባለቤት ወ/ሮ ሳቤላ እደሚያስረዱት ወደማዕከሉ የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች አንድ ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ በሚወስድ ጊዜ ውስጥ በርካታ ነገሮችን እንዲያውቁ ይደረጋል ብለዋል። ማዕከሉ የኢትዮጵያን ታሪክና ቅርሶች በአምሳያ ምስሎች ከማሳየቱም ባለፈ ባህላዊ የምግብና የመጠጥ አሰራሮችንና ሀገር በቀል የዕደ-ጥበብ ስራዎች እንዴት እደሚሰሩ ጭምር በተግባር የሚያሳይ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ተብሎለታል።

የመፍረስ ስጋት ያጋጠመው ይህ “ትንሿ ኢትዮጵያ” የተሰኘው ማዕከል ለመንገድ ስራ በሚል የሚያጣው የ5 ሜትር ስፋቱ ማዕከሉ ሊያመለክታቸው የቆማቸውን የድሬዳዋ፣ የሀረር፣ የአክስምና የጎንደር ምልክት የሆኑ ጥበባዊ ስራዎችም አብረው የሚፈርስበት በመሆኑ ከዚያ በኋላ እንደማዕከል የመቀጠሉ ነገር የማይታሰብ መሆኑንም ወ/ሮ ሳቤላ በላይነሽ አባይ በአፅንኦት ተናግረዋል። የዚህን ማዕከል መቆም የሚደግፉ አካላት ያሏቸውን ተቋማት እና ግለሰቦች ያመሰገኑት ወ/ሮ ሳቤላ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት፣ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ለባህል ማዕከሉ በቀናነት ላሳዩት ድጋፍ ምስጋናቸውን ቸረዋል። አሁን ላይ “ትንሿን ኢትዮጵያ” ከመፍረስ ስጋት ሊታደጋት የሚችለው ቀናነትና ማስተዋል እንደሆነ የጠቆሙት ወ/ሮ ሳቤላ፤ ይህንንም የሚመለከታቸው አካላት ተገንዝበው የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚሰጧቸው ተስፋ አድርገው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።  

 

የፊልሙ ርዕስ                - “እንደቀልድ”

ደራሲ                  - ማርታ አበበ

ዳይሬክተርና ፊልም ጽሁፍ    - ብዙአየሁ እሸቱ

ፕሮዳክሽን  ማኔጀር       - መስፍን ገ/ሔር

ካሜራና ኤዲቲንግ        - ሀሰን ሰይድ

ተዋንያን                - ታሪኩ ብርሃኑ፣ ብርክቲ አበበ፣ ዮሐንስ ተፈራ፣  ሺመላሽ ለጋስ፣ አላዛር ሳለልኝ፣ ሃና አሰፋና ሌሎች

በኪነ ፒከቸርስ ተዘጋጅቶ በቤተልሄም ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “እንደቀልድ” ፊልም ለሲኒማ ከበቃ ሰንበትበት ብሏል። ፍቅር፣ ጓደኝነት፣ እምነትና ፅናት ተፈራርቆ የሚታዩበት ፊልም ነው። እንደቀልድ የሚጀመሩ ግንኙነቶች በሚፈጥሩት ታሪክ ተንተርሶ ተመልካችን በሳቅና በአግራሞት ማዕበል ውስጥ ያንቦራጭቃል፤ የፍቅር ኮሜዲ ዘውግ ያለው “እንደቀልድ” የተሰኘው ይህ ፊልም።

የዚህ ፊልም ዳይሬክተር እና የፊልሙ ፅሁፍ አዘጋጅ ብዙአየሁ እሸቱ ከዚህ ቀደም “ታስጨርሺኛለሽ” በዳይሬክቲንግ እንዲሁም የ“ወፌ ቆመች” ደራሲና ዳይሬክተር ሆኖ በመስራቱ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል። በዚህ ፊልም ውስጥም በስክሪን የምናውቃቸውን ተዋንያን እና አዳዲስ ልጆችን ይዞ በመምጣት በፊልሙ አለም ተጨማሪ አሻራውን አሳርፏል ማለት ይቻላል።

የፍቅርንና የጓደኝነትን ታሪክ “እንደቀልድ” በስክሪን ላይ የሚተርከው ይህ ፊልም እንዲህ ይቀጥላል። ገጠር ያሉ ቤተሰቦቹን ተሰናብቶና ትምህርቱን በደረጃ አጠናቆ አዲስ አበባ መኖር የጀመረው ምንተስኖት (ታሪኩ ብርሃኑ)፤ ስራ አግኝቻለሁ በሚል ሰበብ ከአጎቱ ቤት በመውጣት እንደቀልድ በአይናለም መጠጥ ቤት ውስጥ በአስተናጋጅነት መስራት ይጀምራል።

በጓደኝነት አብሮት የቆየው ዳንኤል (ዮሐንስ ተፈራ) ደጋግሞ የሚጎበኘውን መጠጥ ቤት ባለቤት የሆነችው አይናለም (ብርክቲ አበበ) እንደቀልድ ይወዳታል። በፊልሙ ውስጥ የምር የሚወዳት ምንተስኖት ቢሆንም፤ ፍቅሩ መግለፅ ባለመቻሉ በርካታ ሴቶችን ሲያማግጥ የምናየው ዳንኤል አይናለምንም በእጁ ሲያስገባት እንመለከታለን። ይህ በፍቅርና በክብር መካከል የሚጠነሰስ ግጭት ፊልሙን እስከመጨረሻ ይዞት ሲሄድ እናያለን።

የ“እንደቀልድ” ፊልም የመረረ ቀልድ የሚጀምረው ምንተስኖት ቤተሰቦቹን ጥየቃ ወደክፍለ ሀገር በሄደበት ወቅት ነው። እናትዬው እንደቀልድ አንተ ካላገባህ ህመሜ ብሶብኝ መሞቴ አይቀርም በሚል በፈጠሩት ታሪክ ውስጥ ምንተስኖት ሊያገባት ያዘጋጃት ሴት እንዳለችው በሚል ኦፋ- እንዳመጣለት ይናገራል። ይህም ንግግሩ ለማጽናናት ብሎ የሰነዘረው ቢሆንም የቤተሰቡን ደስታ ከመጠን በላይ አድርጎት ጭራሽ ከእርሱ ፈቃድ ውጪ የሰርግ ፕሮግራም ይታቀዳል።

የዳንኤልና የአይናለም መዋደድም ቢሆን እንደቀልድ የተጀመረ ለመሆኑ ምንተስኖት ከቤተሰቦቹ ቤት ሲመለስ ባየው ነገር አረጋግጠናል። የእሱ ሃሳብና የቤተሰቡ ሃሳብ በእጅጉ የተራራቀበት ምንተስኖት በቤተሰቡ ክብር እና በሚወዳት ልጅ ፍቅር መካከል ሆኖ ግራ ሲገባው እንታዘባለን።

በሰው ላይ ተንጠልጥሎ ራሱን ክፉ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የሌለው ገፀ- ባህሪይ ተደርጎ የተሳለው ዳንኤል፤ እንደቀልድ በፍቅር ያጠመዳትን ልጅ አስቀምጦ አሜሪካ ትወስደኛለች ያላትን ወጣት ሲያጫውት አይተናል። ዳሩ ግን “ሁሌ ፋሲካ የለምና” ይህቺ አሜሪካ ትወስደኛለች ብሎ የተማመነባት ሴት፤ በፌስ ቡክ ከተዋወቃት እህቷ ጋር ጭምር ይወጣ እንደነበር በመረዳቷ እንዴት እንደምትቀጣው ስታውጠነጥን ተመልክተናል።

በፍቅረኞች ቀን ምሽት የቀጠራትን አይናለም ረስቶ፤ ውጪ ትወስደኛለች ካላት ሴት ጋር ያመሸው ዳንኤል፣ “አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፣ የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል” እንዲሉ የውሸት መንገዱ ሲጋለጥበት ይበረግጋል። ይህ አጋጣሚ ለምንተስኖት ዕድል ነው ብሎ ለሚጠብቀው ተመልካች እንደቀልድ ሌላ አስገራሚ ታሪክ እንዲመለከት ይደረጋል።

በተቀጣጠሩበት ቦታ በብቸኝነት የተቀመጠችው አይናለምን ለማፅናናት አበባ ይዞ ወደሆቴሉ የመጣው ምንተስኖት፤ ማርፈድ የሚያስከፍለውን ዋጋ እየጠቀሰ በቁጭትና በምሬት ሲናገር ይስተዋላል። በሆቴሉ በነበረው የፍቅረኞች ቀን ዝግጅት ላይ በወጣላቸው ዕጣ መሠረት የአንድ ቀን የእራት የመጠጥና የአልጋ ዕድል ቢገጥማቸውም፤ ምንተስኖት ያዘጋጀውን ዳንኤል ሲበላው የፊልሙ ታሪክ እንደቀልድ ያሳየናል። እዚህች’ጋ “የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ፤ ከኋላ ተነስቶ ቀድሞ በመድረሱ” የምትለዋን ስንኝ እንድናስታውስ ያስገድደናል።

የዓይናለምን መቸገር ማየት የማይፈልገው ምንተስኖት ድንገት የከፋ ጉድ ይገጥመዋል። አባትዬው (ሺመላሽ ለጋስ) ከገጠር በመምጣት አገባታለሁ ብሎ በፎቶ ያሳያቸውን ልጅ በሽማግሌ ለመጠየቅ መዘጋጀታቸውን ይነግሩታል። “ለማግባት ዝግጁ አይደለሁም ቢልም ሰሚ አላገኘም። ለዚህም “ሀገር ከመምራት ሚስትን መምራት ይከብዳል” ሲል ሙግት ቢገጥምም አባትዬው ግን፤ “ትዳር እና ሀገር ምን አገናኛቸው?” ሲሉ ያጣጥሉበታል።

ይህን ጊዜ እንደቀልድ ለማስመሰል ለማለፍ በድብቅ የሚስማሙት ምንተስኖትና ዓይናለም የውሸት ባልና ሚስት ሆነው አባትዬውን ያስተናግዳሉ። ይህ ነገር በሌላ በኩል ዳንኤልን በቅናት ያንገበግበዋል። ሁሉ ነገር እንደቀልድ ተጀምሮ በእየአንዳንዱ ትዕይነት እየመረረና እየከረረ ሲሄድ ቀጥሎ የሚመጣውን ተመልካችን ያጓጓል።

“እንደቀልድ” ፊልም ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ክብር፣ ኩራትና ፅኑ ፍቅር በአንድ ላይ ተገምደው ይታዩበታል። በፊልሙ ውስጥ የዳንኤልን አስመሳይነትና ዋሾነት ዘግይታ የምትረዳው ዓይናለም የተባለችው ገፀ ባህሪይ የፍቅር ስሜቷን ለይቶ ለመናገር የሚከብድ ነው። ሲጀመር ምንተስኖትን ትወደዋለች እንዳንል፤ ከዳንኤል ጋር ስትሆን ተመችቷታል። የለም ዳንኤልን ብቻ ነው የምትወደው እንዳንል ደግሞ ምንተስኖት ሲናፍቃት እናያለን።

“እንደቀልድ” የክብር እና የፍቅር ሞተር የሚዘውረው በሳቅና በትዝብት ተውጠን የምንመለከተው የፍቅር ኮሜዲ ፊልም ነው። የክብርና የፍቅርን ሰንሰለት የሚያጠነክረው ምንተስኖት በሚናገራት አንዲት ሀረግ ውስጥ በእጅጉ ተቆላልፋ እንሰማታለን። “እየኖርኩም እየሞትኩም ከልቤ እወድሻለሁ” ይህ ተደጋግሞ የተሰማ ጽኑ ቃል ነው።

በፊልሙ ውስጥ ምንም እንከን የለም ለማለት አያስደፍርም። እንዲያው ግን በጥቂቱ ለመጠቋቆም ያክል የሚከተሉትን ማንሳቱ አይከፋም። የመጀመሪያው ነገር የብርሃን እና የቀለም አጠቃቀሙ ነው። የተዋንያኑን የፊት ገፅ የፈረንጅ እስኪያስመስለው ድረስ ያልተመጠነ የቀለምና የብርሃን እርጭት ተደጋግሞ ታይቷል። ይህ ደግሞ በኤዲቲንግ መስተካከል የሚችል ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው።

እዚህ’ጋ ሳይጠቀስ የማይታለፈው የብርሃን ልልነት ነው። በተለይም አባትዬው ባደሩበት ምሽት የተቀረፀው የምሽት ትዕይንት (ሲን) በመስኮት የሚገባን የጨረቃ ብርሃን አስመስሎ ማሳየት ቢቻል ጥሩ ነበር። ሌላው በፊልሙ ውስጥ ተመልካችን እስኪያሰለች ድረስ ተደጋግሞ እንድናየው የተደረገው የቡና ቤቱ ስም ነው። ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ይመስል የሆቴሉ (የመጠጥ ቤቱ) ማስታወቂያ እጅግ በዝቷል ለማለት ያስደፍራል። በተረፈ ግን ፊልሙን ስንመለከት በወጣቶች ፍቅር እና በቤተሰብ ክብር መካከል ያለውን ክፍተት እንዲህ በቀላሉ የምንሞላው እንዳልሆነ እንገነዘባለን።

“እንደቀልድ” ፊልም በህይወታችን ውስጥ እንደቀላል የምናሳልፋቸውና የምንናገራቸው ነገሮች እየከረሩ ሲመጡ የሚያመጡትን አንዳች ተዓምር “እንደቀልድ” ያሳየን ፊልም ነው። እንደቀልድ የተጀመሩ ብዙ ነገሮች የት ሊደርሱ እንደሚችሉ በህይወታችን እንደናስተውል ያደርገናል። “እንደቀልድ” ፊልም እንደቀልድ የተጀመሩ ነገሮች የምር ሲሆኑ የሚያሳይና ለአንዳችን ቀላል የመሰለን ነገር ሌላችን ምን ያህል ፈተና እንደሚሆን አጉልቶ በፍቅርና በክብር ውጥረት ውስጥ አስተሳስሮ ማሳየት የቻለ ስራ ነው ማለት ይቻላል።

 

የቴአትሩ ርዕስ - “የእግዜር ጣት”

ድርሰት - ጌትነት እንየው

ዝግጅት - ሉሌ አሻጋሪና በተዋንያን ህብረት

ዝግጅት አስተባባሪ - ስናፍቅሽ ተስፋዬ

የመድረክ ገፅ ቅብ - ታፈሰ ለማ

መብራት -  ቅጣው ክፍሌ እና ዘይድን አማን

ድምጽ - ባለኝ ሽብሩ እና ውብሸት

ተዋንያን - ካሌብ ዋለልኝ፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ዋሲሁን በላይ፣ ህንፀተ ታደሰ እና   የማታወርቅ ታደሰ

የሰው ልጅ በፍፁም ከዕጣ -ፈንታው ሊያመልጥ አይችልም። “የእግዜር ጣት እንደው መስመሩ ረቂቅ ነው። እሱ (ፈጣሪ) የነደፈውን ማን ያጠፋዋል?” ይህን የሚሉት የቹቹዬ አባት አቶ ሰይፉ ደበላ (ዋሲሁን በላይ) ናቸው። አንጋፋው ደራሲ፣ ገጣሚና ተዋናይ ጌትነት እንየው ከዓመታት በፊት ለመድረክ ያበቃው “የእግዜር ጣት” ቴአትር ተመልሶ በመታየት ላይ ይገኛል። ለመሆኑ አሁን ተመልሶ ወደመድረክ መምጣቱ ለምን አሰፈለገ? ለዚህ ምላሽ የምትሰጠን የቴአትሩ ዝግጅት አስተባባሪ ተዋናይት ስናፍቅሽ ተስፋዬ ናት። “የአዳዲስ ስራዎች ወደመድረክ መምጣት ሲቀንስ፤ ከዚህ ቀደም ተሰርተው አሪፍ የነበሩ ቴአትሮች እንዲመጡ አስተዳደራዊ ፈቃድ ሲሰጠን ያን ተጠቅመን ነው የእግዜር ጣትን መርጠን ያቀረብነው” ትላለች።

“የእግዜር ጣት” ቴአትር ቀደም ብሎ ሲሰራም በርካታ ተመልካች አይቶት ሳይጠግበው እንደወረደ የምታስታውሰው ስናፍቅሽ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የአዳራሽ እድሳት ጋር ተያይዞ ቴአትሩ ሲቋረጥ ያኔ ያላገኘውን ተመልካች ለማስደሰት ስንል አሁን ይዘነው መጥተናል፤ ለውጤቱም ተሳክቶልናል ትላለች።

ከአስር ዓመታት በፊት ቴአትሩ ወደመድረክ ሲመጣ ተስፋዬ ገ/ሃና፣ አለማየሁ ታደሰ፣ ሱራፌል ወንድሙ፣ ህንፀተ ታደሰ እና ስናፍቅሽ ተስፋዬ የተወኑበት ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን ሶስት አዳዲስ ተዋንያንን ተተክተው እየተሰራ መሆኑን ስናፍቅሽ ተስፋዬ ታስረዳለች።

መቼቱን ከዘመናት በፊት በነበረችው ጅማ ከተማ ላይ ያደረገው “የእግዜር ጣት” ቴአትር የሁለት ወጣቶችን ፍቅር ተንተርሶ የዕጣ-ፈንታን አይቀሬነት እና ወጥመድነት ይተርካል። መልካሙ (ካሌብ ዋለልኝ) በተከራይነት አንዲት ክፍል ቤት ውስጥ ድንገት ከአከራዩ ልጅ ጋር ከፍቅር ያለፈ ነገር ሲፈጠር በማሳየት ይጀምራል። በአባቷ ቤት ተቀማጥላ ያደገችው ቹቹ (ስናፍቅሽ ተስፋዬ) በቤታቸው ተከራይቶ መኖር ከጀመረ አራት ወራትን ካስቆጠረው መልካሙ ጋር እፍ-ክንፍ ወዳለ ፍቅር መግባቷን እንመለከታለን። ነገር ግን ፍቅራቸው እንደተቦረቦረ አገዳ ክፍተቱ ሲገልጽ ቹቹ ግን ክፍተታቸውን በግድ የሚሞላ ፅንስ በሆዷ መያዟን ትነግረዋለች። አልፈልግም ባዩ መልካሙ ግንኙነታቸው እንደማይቀጥል ይናገራል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት መልካሙ ከቀድሞ ፍቅረኛው ትሩፋት ጋር የነበረው የፍቅር ቃልኪዳን መላልሶ ስለሚያስታውሰው ነው።

ለዚህም ይመስላል በቴአትሩ ውስጥ ከመነሻው ጀምሮ ገኖ የሚሰማው የተፈራ ካሳ፤

“ባሳብ ካንቺ ጋር ነኝ፤ በእውነት ነው ያጣሁሽ፤

እሩቅ ስለሆንሽ፣ መቼ ትመጫለሽ ለሊት በህልሜ አየሁሽ?”

ዘፈን መምጣቱ። ልቡ ወዲያ ወዲህ የሚዋልልበት መልካሙ፤ የእንጋባ ጥያቄ የምታቀርብለት ቹቹን “እኔና አንቺ እንኳንስ ልንጋባ ልንግባባ አንችልም” ይላታል። ነገር ግን የሚሰጠው ምላሽ ይበልጥ ተመልካች ዘንድ ሳቅን የሚያጭር ነው። “ከተጋባን በኋላ ቀስ ብለን እንግባባለን” የቹቹ መልስ ነው።

ይህቺን ገፀ ባህሪይ ተላብሳ የምትጫወተው ስናፍቅሽ ተስፋዬ ስለባህሪዋ እንዲህ ትላለች “ቹቹዬ ተሞላቃ ያደገች፤ ግልጽና የዋህ ገፀ-ባህሪይ ናት”  . . የቴአትሩ ርዕስ የሆነውን “የእግዜር ጣት” በተመለከተ ደግሞ፣ “ብዙ ጊዜ በህይወታችን የሚገጥመን ነገር ነው። ብዙ ሰው የወደደውን ብቻ አያገባም። በዕጣ-ፈንታችን የተጻፈልን ነገር ነው የምንኖረው” ስትል የቴአትሩ ሃሳብ በእውን በግልጽ እንደሚታይ ታስረዳለች።

በአባቷ ቤት ተቀማጥላ ያደገችው ቹቹ፤ ምንም እንኳን እናቷን ድንገት በወሊድ ምክንያት ያጣች ብትሆንም ያ ታሪክ በእርሷም እንዳይደገም የምትሄድበት ርቀት የታሪኩ ጠንካራ ማሳያ ነው። ሰው ከዕጣ ፈንታው እንደማያመልጥ በአፅንኦት የሚገለፅበት ሌላው መንገድ የወንዶች በደልና ዋሾነት ለማጋነን የምትሞክረው ቹቹ ደጋግማ “ወይ ወንዶች! ግን ይሄን ሁሉ ነገር እያደረጉን ለምን እንወዳቸዋለን?” ስትል ትጠይቃለች።

በአንፃሩ ከወጣትነታቸው ጀምሮ በእግር ኳስ ፍቅር ያበዱት አባቷ አቶ ሰይፉ፤ የመስማት ችሎታቸው በእጅጉ ከመውረዱ ጋር ተያይዞ ለሚጠየቁት ጥያቄ የሚሰጡት የማይገጥም ምላሽ በተመልካቹ ዘንድ የሳቅ ማሟሟቂያ ሆኖ ቀርቧል ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚያደርገውን የእግር ኳስ ጨዋታ በተመለከተ ከቴአትሩ ባለታሪኮች ግጭት ጋር አብሮ እንዲሄድ መደረጉ ውበት ሰጥቶታል። እዚህች’ጋ የአባትየውን የጆሮ ድክመት ተንተርሶ መልካሙ የተባለው ገፀ-ባህሪይ የሚሰጣት ሽሙጥ አዘል አስተያየት ተመልካቹን በሳቅ ፍርስ የምታደርግ ናት። አቶ ሰይፉ፣ “ከጓደኛዬ ጋር ስጫወት አምሽቼ መጣሁ” ከማለታቸው መልካሙ፣ “በየትኛው ጆሯቸው ነው የሚጫወቱት” ይላል።

በሁለት ገቢሮች (በቤት ውስጥ እና በአዊቱ መናፈሻ ቦታ) እንዲሁም በአምስት ትዕይንቶች የሚቀርበው “የእግዜር ጣት” ቴአትር ሰው ምን ያህል የዕጣ ፈንታው እስረኛ መሆኑን በበቂ ማስረዳት የቻለ ነው ማለት ይቻላል።

ከሀዋሳ ወደ ጅማ ከተማ ለስራ ተመድቦ የመጣው ደንበል (የማታወርቅ ታደሰ) ዕጮኛው ትሩፋትን (ህንፀተ ታደሰ) ይዞ በመናፈሻው ይገኛል። እዚህ’ጋ ሆን ተብሎ በሚመስል መልኩ ሰው ሁሉ ከቤቱ ወጥቶ በመናፈሻው የተገኘው ግንኙነቱን ለማጠናከር አስመስሎታል። ለምን ቢባል? ገፀ ባህሪያቱ መናፈሻ ውስጥ ባይሆን የመገናኘታቸው ነገር እጅግ አናሳ በመሆኑ ያን ክፍተት ለማጥበብ ይመስላል። (እግረ መንገዱንም “የእግዜር ጣት” የትም ቢሆን እንደሚያገናኝ እንድናምን ተፈልጎ ሳይሆን አይቀርም) ቴአትሩ የኢትዮጵያን የአኗኗራችንና የስብጥር ሁኔታ በጥቂቱም ያመላከተ ነው። (ጅማ ከተማ የተገናኙት ገፀ- ባህሪያት ከደብረሲና ከሀዋሳና ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ መሆናቸውን ልብ ይሉዋል)

ኩራቱና አጉል መቀናጣቱ በተመልካቹ ዘንድ ሳቅ የሚፈጥረው ደንበል፤ ቹቹን ገና እንዳያት ቢወዳትም በመልካሙ ፊት እንደዛ መሆኑና የመልካሙም የትግስቱ መጠን መብዛቱ እጅግ የተጋነነ ይመስላል። “በእጅ ያለ ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል” እንዲሉ ቹቹ፤ በእጇ የያዘችውን “አይስከሬም” በደንበል ወሬ ተመስጣ መጣሏን ስንመለከት የግኝኙነታቸውን እድሜ እንድንገምት አድርጎናል።

በቴአትሩ ውስጥ የፍቅርና የፆታ ትንቅንቅም ተቀምጧል። ሴቶቹ፣ “ወንድና ፈረስ እስኪገሩ ድረስ ነው እምቡር እምቡር የሚሉት” ሲሉ፤ ወንዶቹ በበኩላቸው “ሴቶች እንደወደድካቸው ካወቁ በግ ነው የሚያደርጉህ” ሲሉ እንሰማለን።”

“የእግዜር ጣት” በተለይም በመጨረሻው ትዕይንት ላይ የሚደረገው የቡድን ንግግር፤ ከአባትየው የሬዲዮ ዘገባ ጋር ተዳምሮ ጥምረቱ ውበት ነበረው ማለት ይቻላል። እዚህ’ጋ የመብራት አጠቃቀሙንም ሳናደንቅ አናልፍም። በተለይም የእግር ኳሱ “ፍፁም ቅጣትምት” ጉጉትና የባለታሪኮቹ የውሳኔ ጫፍ መገናኘቱ የቴአትሩን ህይወት እንደዋንጫ ጨዋታ ውጤት በጉጉት እንድንመለከተው አድርጎናል። እናም ምን ለማለት ነው? በስተመጨረሻ ምንም ሰው ከዕጣ ፈንታው (ከእግዜር ጣት) አያመልጥም።  

Page 1 of 13

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us