“ሥዕል በራሱ ቋንቋ አለው”

Thursday, 03 July 2014 12:16

ሰዓሊ ዓለምፀሐይ ንባበ

 

የዛሬዋ እንግዳችን ሥዕልን ለራሷ ያስተማረችና በራሷ የቀለም ፈጠራዎች በመሳል የምትታወቅ ናት። ከአደባባይ ሰውነት ራሷን የሸሸገችው ይህች ሰዓሊ በበርካቶች ዘንድ ከእፅዋትና ከተለያዩ አለማት የምታገኛቸው አፈሮች በምትቀምማቸው ቀለሞች በምትሰራቸው የሥዕል ሥራዎቿ ትታወቃለች። በሐረር ከተማ ጋራ ሙለታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዳ ያደገችው የዛሬዋ የመዝናኛ አምድ እንግዳችን ሰዓሊ ዓለምፀሐይ ንባብ ትባላለች። በአዲስ አበባና በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የሥዕል አውደ-ርዕይዎችን ካቀረበችው እንግዳችን ጋር ስለስራዎቿና የህይወት ልምዷ ይህን መሰል ቆይታ አድርገናል፤

ሰንደቅ፡- ለመነሻ ያህል ወደ አርት-ስኩል የመግባት አጋጣሚውን አግኝተሸ ነበር? ካልሆነ የሥዕል ተሰጥኦሽን እንዴት አዳበርሽው?

ዓለምፀሐይ፡- እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ከልጅነቴ ጀምሮ ቀለማት ይማርኩኝ ነበር። ትዳር ይዤ ልጆች ከወለድኩ በኋላ ስዕሎችን በመሞነጫጨር ለእነርሱ ማሳየት ነበረብኝ። ልጆቼን የወለድኳቸው በልጅነቴ ስለነበር ለነርሱ የምስለው ሥዕል የተሰጥኦዬን አቅጣጫ የማይበት ሆኗል። ልጅ እያለሁም የቤተሰቦቻችንን ጎጆ ለማስዋብና ወላጆቻችንን ለማስደሰት ስንል ከእህቶቼ ጋር በአካባቢው ካለ ገደል ውስጥ ምርጥ የተባለ ቀለም ያለውን አፈር በመበጥበጥና የቤታችንን ቀለም በመቀባት የተለያየ ከለር መፍጠር ያኔ የጀመረኝ እንደሆነ ይሰማኛል። ከዚያ በኋላ ነው ቀስ በቀስ ቅርፅ ያላቸውን ስዕሎች መስራት የጀመርኩት እንጂ “አርት-ስኩል” ገብቼ የመማር አጋጣሚውን አላገኘሁም።

ሰንደቅ፡- ሰዓሊ መሆንሽን በአደባባይ የገለጥሽው በቅርቡ መሆኑን ሰምቻሁ፤ እስቲ ስለእሱ ትንሽ አጫውቺኝ?

ዓለምፀሐይ፡- ባይገርምህ ሥዕል እስላለሁ ወይም “ሰዓሊ” ነኝ ብዬ እስካለፈው ቅዳሜ ማታ ድረስ በፍፁም ቃሌን ሰጥቼ አላውቅም። የሴቶችን የስር ተነሳሽነት ለማስፋፋት በሚል ባህልና ቱሪዝም በተጋበዙበት “የጀበና ሙሽሮች” በሚል ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2006 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ የሥዕል አውደርዕይ ሲዘጋጅ የኔና የባልደረባዬ ድርሻ የላቀ ነበር። በዚያ መድረክ ላይ ሰዓሊ ተብዬ መጠራትን ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀበልኩት እንጂ ሥዕልን ለራሴ የምሰራው፤ ሰላም ለማግኘት ስል የማከናውነው ተግባር ነው ብዬ ስለማምን እንደሙሉ ሰዓት ሰዓሊ ራሴን መጥራት አልደፍርም ነበር።

ሰንደቅ፡- ሌሎች ሰዓሊያን የሚሰሩትን ተግባር እየፈፀምሽ ሳለ ሰዓሊ መባሉን ስለምን ሸሸሽው?

ዓለምፀሐይ፡- እውነት ነው ስራዎቼ ብዙ መናገር ይችላሉ። ነገር ግን ስሙን ያልደፈርኩበት ምክንያት አንደኛ ራሴን መስቀል (ከፍ ማድረግ) ስላልፈለኩ ነው፤ ታዋቂነትን አልፈልግም። ይሄ የኔ ችግር ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ሰዎች አንዴ ይሰቅሉህና በሚቀጥለው ደግሞ ሊያወርዱህ ይችላሉ። ስለዚህ በነበርኩበት ተረጋግቼ ስራዬን መስራት ነው የምፈልገው።

ሰንደቅ፡- ተደብቀሽ መሳል የምትመርጪ ከሆነ ሥዕል ላንቺ ምንድነው ፋይዳው?

ዓለምፀሐይ፡- ሥዕል ሁለት ነገር ነው ለኔ፤ አንደኛ ሰላም የሚሰጠኝ ነገር ነው። ሃሳብ ሲበዛብኝ የሚያስጨንቁና የሚያሳዝኑ ሁኔታዎች ሲገጥሙኝ ነፃ የምሆንበት ነገር ነው። ሁለተኛው ደግሞ በውስጤ ያከማቸሁትንና ለሌሎች ይጠቅማሉ የምላቸውን ሃሳቦች በሙሉ የምገልፅበት መሳሪያ ነው ማለት እችላለሁ። በአፌ መናገር የማልፈልገውንም ነገር ጭምር በሥዕል ማሳየት ይቀናኛል። ሥዕል የራሱ ቋንቋ አለው፤ ሀሳቤን በደንብ ነው የምገልጽበት።

ሰንደቅ፡- ከአገራችን ሰዓሊያን ጋር የመገናኘቱ አጋጣሚው ነበረሽ? በሕይወት ካሉትም ሆነ ከሌሎት እነማንን ታደንቂያለሽ?

ዓለምፀሐይ፡- እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ሥራዎች አደንቃሁ። ባሉበት ቦታ ይቅርታ ያርጉልኝና ለእርሳቸው ካለኝ ፍቅርና አክብሮት የተነሳ አንድ ስዕላቸውን ድጋሜ ሰርቼዋለሁ። እያየሁት የሰራሁት ስራ ስለሆነ ፎቶ ነው ያነሳሁት ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- ያንቺ የሥዕል ስራዎች የሚለዩት ራስሽ በምትቀምሚያቸው ከእፅዋትና ከአፈር በተገኙ ቀለሞች የሚሰሩ ስራዎች መሆናቸው ነው፤ እስቲ ስለአፈርና ቀለም ያለሽን ምልከታ ንገሪኝ?

ዓለምፀሐይ፡- በመጀመሪያ ደረጃ አፈር በአፈርነቱ ይሄ ነው ብዬ ገልጬ መጨረስ አልችልም። ምክንያቱም አፈረ ይሸከመናል፣ ያበላናል፣ ያጠጣናል፣ ያኖረናል መልሶ ደግሞ ወደራሱ ይወስደናል። ይሄ አንዱና ትልቁ የተፈጥሮ ፀጋ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ስለቀለም ሳስብ ከአፈር ድብልቅ የሚፈልገውን አይነት ቀለም ማግኘት መቻሉ በጣም ነው የሚያስደስተኝ። ሁልጊዜ የማስበው ነገር በቂ ጊዜ ኖሮኝ ከአፈር ቆፋሪዎች ጋር፤ ከማዕድን ቆፋሪዎች ጋር ብዙ ጊዜዬን ማሳለፍ ብችልና የምድራችንን አፈር ወደውስጥ በጥልቀት ማየት ብችል የተለየ አፈር የማገኝ ይመስለኛል። ላለፉት 22 ዓመታት በተለያዩ አገሮች የተለያየ ቀለም ያላቸውን አፈሮች ሳስባስብ ቆይቻለሁ። ራሴ በቀመምኳቸው የእፅዋትና የአፈር ቀለሞች ነው የሥዕል ስራዎቼን የምሰራው። በዚህም በጣም የተለዩና የሚያምሩ ስራዎችን ሰርቻለሁ።

ሰንደቅ፡- ቀደም ባሉት ጊዜያት በፋብሪካ ቀለሞች ውህድ የሥዕል ስራዎችን ለመስራት አልሞከርሽም?

ዓለምፀሐይ፡- የፋብሪካ ውጤት በሆኑ ቀለማት ሥዕል ስዬ አላውቅም። አሁንም ድረስ በዚያ መንገድ መስራት አልችልም። ስዕሎቼ ሁሉ በአፈርና በእፅዋት ድብልቅ ቀለማት የተሰሩ ናቸው። የምለየውም በዚህ ዓይነት አሳሳሌ ነው።

ሰንደቅ፡- በተለያዩ አገራት በመዘዋወርሽ ምክንያት የተለየ ቀለም ያለው አፈር አጋጥሞኛል ብለሽ የምትጠቅሺው አገር ይኖራል?

ዓለምፀሐይ፡- ማርቲኒክ የምትባል ደሴት አለች። ይህቺ ደሴት በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከተያዙ ደሴቶች አንዷ ናት። እዛ ብዙ አይነት ቀለም ያለው አፈር አይቻለሁ። ነገር ግን አንድ ነገር የምነግርህ ሁሉም አገራት የራሳቸው የሆነ የተለየ “ከለር” ያላቸው ናቸው። ኢትዮጵያንም ሙሉ በሙሉ የማየት አጋጣሚውን አላገኘውም እንጂ የተለየ ቀለም ያለው አፈር እንደሚኖር ተስፋ አለኝ። እንደሰው መልክ መለያየት ብዙ ዓይነት ቀለሞች በአፈር ውስጥ አሉ።

ሰንደቅ፡- እስካሁን ምን ያህል አውደ-ርዕዮችን አዘጋጅተሻል? በቁጥር የሚታወስ ከሆነም ምን ያህል ስዕሎችን ሰርተሻል?

ዓለምፀሐይ፡- አሉኝ የምላቸው ስራዎች የሰራኋቸውን ሁሉ ሳይሆን ሰርቻቸው የረካሁባቸውን ብቻ ነው። ብዙ ስራዎች አሉኝ ግን ለኔ ትንሽ ስህተት ያለው ከመሰለኝ ለሰዎች አላቀርባቸውም። ስለዚህ ቢኖሩም እንዳሉ አይቆጠሩም። ሌላው የኔ ደካማ ጎን የሚመስለኝ አንድን ሥዕል ጀምሮ በአንድ ሌሊት መጨረስ ካልቻልኩ ደግሜ አልሰራውም ስለዚህ በጅምር የቀረም ብዙ ስራዎች አሉኝ ማለት ነው። ስለዚህ አሁን አሉኝ የምልህ አፌን ሞልቼ የምናገርባቸው ከ300 እስከ 400 ስዕሎች አሉኝ ማለት እችላለሁ። ኤግዚቪዥንን በተመለከተ ላለፉት ስምንት አመታት አካባቢ ቢያንስ በዓመት ሁለቴና ሶስቴ አዘጋጃለሁ። በግሌም ሆነ ከተለያዩ ሰዓሊያን ጋር እናሳያለን።

ሰንደቅ፡- ከሌሎቹ ሰዓሊያን በተለየ ያንቺ ሥዕል በአፈር የተቀለመ በመሆኑ ሰዎች ምን አስተያየት ይሰጡሻል?

ዓለምፀሐይ፡- ባይገርመህ አብዛኞቹ ጓደኞቼ (በሥዕል ውስጥ ያሉት) ለምን ወደሥዕል ትምህርት ቤት ለምን አትገቢም ይላሉ፤ ከትምህርት በኋላም ደግሞ ለምን አታስተምሪም ነው የሚሉኝ። እኔ ግን ምናልባት ሰው ቢያስተምረኝ የሚገባኝ አይመስለኝም። እኔ በራሴ መንፈስ የቻልኩትን ነገር መስራት እንጂ የተማርኩትን ነገር ደግሞ መስራት ተሰጥኦዬን የሚሸፍንብኝ ይመስለኛል። ነገር ግን ትምህርት ቤት ገብቼ ባልማርም የማውቀውን ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ ነኝ።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ በብሔራዊ ቴአትር በተካሄደው ዝግጅት ላይ ሰዓሊ መባልሽን ተቀብለሽዋል፤አሁን ሥዕል የሙሉ ጊዜ ስራሽ ነው? ማለቴ እንጀራሽ ነው?

ዓለምፀሐይ፡- እውነቱን ለመናገር እንጀራ አልበላበትም። ነገር ግን ሥዕል ስሰራ እድሜዬ ይረዝማል። ሌሎችንም ሰዎች አስደስትበታለሁ። በአሁኑ ጊዜ ጥሩ የሥዕል ተመልካች አለ። ስራህን አይቶና አድንቆ የሚሰጥህ አስተያየት እጅግ ደስ የሚያሰኝ የመንፈስ ምግብ ነው። በአፈር የቀመምኩትን ቀለም አድንቆና ጠይቆ የሚሄድ ተመልካች ማግኘቱ በራሱ ያስደስታል። እውነቱን ለመናገር እኔ በሀገሬና በህዝቤ እኮራለሁ። ይበልጥ ብዙ መስራት እንዳለብኝ የገባኝ ቅዳሜ ዕለት በብሔራዊ ቴአትር ከተካሄደው አውደ-ርዕይ በኋላ ያገኘዋቸው አስተያየቶች ለኔ እጅግ በጣም አበረታች መሆናቸውን ስረዳ ነው። ቦታው ጠባብ ነበር፤ ብዙ ማስታወቂያ አልሰራንም፤ በዚህ ሁሉ መሀል መጥቶ ሥዕል ማየት የሚወድ ተመልካች ማግኘት በጣም ደስ ይላል። መተዳደሪያዬ ግን ሥዕል ሳይሆን ሌላ ስራ አለኝ የገቢ ምንጬ ከሥዕል ውጪ ነው።

ሰንደቅ፡- የሥዕል ገበያ በአገራችን የሚታይ ለውጥ አለው ብለሽ ታስብያለሽ?

ዓለምፀሐይ፡- በርግጥ ከሰው የኑሮ ደረጃ አንፃር ያን ያህል ነው ሊባል ይችል ይሆናል እንጂ ሥዕል የሚገዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ከመቶ ሁለትና ሶስት ሊሆኑ ይችላሉ። አቅሙ ያላቸው ናቸው። ሌላው ግን ካየሁት ተነስቼ መናገር የምችለው ስዕሎቹን የሚጎበኙ ሰዎች አቅም ቢኖራቸው መግዛት የሚፈልጉ ናቸው ማለት ይቻላል። አንድ ሰዓሊ ሥዕል ሰርቶ መኖር የሚችልበት ደረጃ ተደርሷል ብዬ አምናለሁ። ከሥዕል ሽያጩ በተጨማሪ ልጆችን ማስተማር ቢቻል ጥበቡ ያኖራል የሚል እምነት አለኝ።

ሰንደቅ፡- ከሥዕል በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየሰራሽ ነው?

ዓለምፀሐይ፡- የተጎዱ ወገኖቼን እረዳለሁ። ወላጅ አልባ የማሳድጋቸው ህፃናት አሉኝ። የምደግፋቸው ሴቶች አሉኝ። ለእነርሱ የስራ ሁኔታዎችን አመቻቻለሁ በዓመት አንዴ፣ ሁለቴ እየመጣሁ እጎበኛቸዋለሁ። ነገር ግን ኑሮዬ በፈረንሳይ ሀገር ነው። ስራዬን ለማሳየትና ወገኖቼን ለመጎብኘት እመጣለሁ።

ሰንደቅ፡- ቡናን በተመለከተ የተለየ ግንዛቤ እንዳለሽ ሰምቻለሁ እስቲ ስለቡና አጫውቺኝ?

ዓለምፀሐይ፡- ቡናችን መለኪያ የሌለው ተክል ነው። ቡና ለኢትዮጵያውያን በድሮ ጊዜ ከስልክ በላይ ለመረጃ ልውውጥ የሚያገለግል ነው። የአካባቢ ሰው ቡና ላይ ነው የተፈጠሩ ሁኔታዎችን በመረጃ መልክ የሚለዋወጠው። ከዚያም በላይ ሰዎች ሲቆስሉ ተቆልቶ የተወቀጠ ቡናን በቁስሉ ላይ በማድረግ እንደመድሃኒትም ያገለግላል። ሌላው ደግሞ ቡና ይሸጣል፤ የኢኮኖሚያችን ዋልታ ነው። ስለዚህ ቡና ለሁላችንም ብዙ ነገር ነው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- ቡናን በማስተዋወቅ ደረጃ ምን ስራ ሰርተሻል?

ዓለምፀሐይ፡- በፈረንሳይ ሀገር ለኔ እንግዶች የማዘጋው ተቀዳሚ ግብዣ ቡና ነው። በኢትዮጵያዊ የአፈላል ስነስርዓት የሀገር ልብሴን ለብሼ ቆንጆ ቡና አፈላላቸዋለሁ። ባይገርምህ በፈረንሳይ የምኖርበት ቤት ውስጥ አንድ ሰፊ ክፍል አለኝ፤ ያ ክፍል ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊ ቁሳቁሶች የተሞላ ነው። ዓመት በዓል ሲመጣ እዛ ነው የምናከብረው ያኔ ሀገሬ የተመለስኩ ያህል ይሰማኛል።

ሰንደቅ፡- ሥዕል ለመሳል የሚያነቃቃሽ ምንድነው?

ዓለምፀሐይ፡- እኔ ሥዕል የምሰራው ሳዝን ነው፤ ስጨነቅ ነው፤ ሃሳቤ ሳይቋጭልኝ ሲቀር ነው የምሰራው። ሥዕል ስሰራ ነፃና ደስተኛ እሆናለሁ። በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ልንገርህ በጣም የምወደው ቃለአብ ገዛህኝ የሚባል ልጅ አለኝ። ሥዕል የመሳል መንፈሴ ሲመጣ ለወርም ሆነ ለሁለት ወር በጣም ነው የሚንከባከበኝ ቡና ያፈላልኛል፤ የምበላውንም ሆነ የምጠጣውን ያዘጋልኛል። በሥዕል ስራዬ በጣም ነው የሚደሰተው። እኔም በጣም የምወደው ልጅ ነው። በርግጥ ሌሎቹን ልጆቼን አልወዳቸውም ማለት እንዳይመስልብኝ የርሱ ከስራዬ ጋር በተገናኘ የተለየ ነው ለማለት ፈልጌ ነው።

ሰንደቅ፡- ሰዓሊ ዓለምፀሐይ በምን ትዝናናለች?

ዓለምፀሐይ፡- የተሳካልኝ ጊዜ የከፋቸውን ሰዎች ማፅናናት ስችል ዘና እላለሁ። ብዙ ጊዜ እኔ የሚያዝናናኝን ሰው ሳይሆን የማዝናናውን ሰው ነው የምፈልገው። ሰዎች በኔ ዘና ሲሉ ነው እኔ የምዝናናው። ከሰዎች ጋር ሀሳብን መካፈል ያዝናናኛል። ሰው ከሚናፍቃቸው ወገኖች ጋር ጊዜዬን ሳሳልፍ ነው የምዝናናው ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ምን ለመስራት ሃሳብ አለሽ?

ዓለምፀሐይ፡- ሰው ብዙ ያስባል። በተለይም በስዕሉ ዙሪያ ብዙ ልሰራቸው ያሰብኳቸው ነገሮች አሉ። በፈረንሳይ በቅርቡ “በአንድ ቋንቋ እንናገር” የተሰኘ ፌስቲቫል አዘጋጅተናል። ለርሱ እየተዘጋጀው ነው። በቀጣይም ወደኢትዮጵያ ተመልሼ ስራዎቼን የማሳየት ሃሳቡ አለኝ። በተጨማሪ ግን ልረዳቸው አስቤ የሰበሰብኳቸው ልጆችና ሴቶች አሉ እነርሱን ጥሩ ደረጃ ማድረስ ትልቅ አላማዬ ነው ከእግዚአብሔር ጋር።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11296 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us