የፍቅር ምንዛሬ የታየበት “ፍቅር ሲመዘር”

Wednesday, 09 July 2014 13:21

ከዚህ ቀደም በስራቸው “አማላዩ” እና “ሼፉ” በተሰኙት ፊልሞቹ የምናውቀው ካም ግሎባል ፒክቸርስ በተለየ መልኩ ሶስተኛ ስራው የሆነውን “ፍቅር ሲመነዘር” የተሰኘ የፍቅር ኮሜዲ ፊልም ለዕይታ አቅርቧል። ይህ ፊልም በፈረንሳዊው ዳይሬክተር ፒፌ ሳይቫደሪ ተፅፎ በዩኒቨርሳል ፒክቸር ተሰራጭቶ ለዕይታ የበቃው እ.ኤ.አ በ2006 ሲሆን፤ ጋድ ኤልማሌህ እና አድሬይ ታውቱ በብቃት የተወኑበት ፈረንሳይኛ ፊልም ነው። በ “Hers de-prix” ፊልም ላይ ተመስርቶ የተሰራው “ፍቅር ሲመዘነር” (priceless) ተብሎ ለአሜሪካ ተመልካቾችም ስለመቅረቡና ለበርካታ የአለማችን ፊልም ተመልካቾች ዘንድ ተወዳጅነት ያገኘ እንደነበር ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

በአንተነህ ግርማ ተፅፎ፤ በኩሩቤል አስፋው ዳይሬክት የተደረገው “ፍቅር ሲመዘር” ፊልም የሰለሞን ቦጋለን ተለምዷዊ የትወና ብቃትና የወጣቷን ተዋናይት የትናየት ታምራት ጥረትም በእጅጉ አዋህዶ የቀረበ አስቂኝ የፍቅር ፊልም ነው ማለት ይቻላል።

“ፍቅር ሲመነዘር” ከልጅነቷ ጀምሮ ፈጣንና ጎበዝ የነበረች ወጣት ሴት፤ ሀብታሞችን በማሳደድ የተሳካ ህይወትን ለመኖር የምትታትር ወጣት የህይወት ገጠመኝና ድንገት የተዋወቃትን የቡናቤት አስተናጋጅ (ባር ማን) የፍቅር ህይወት በአስቂኝ መልኩ የሚያሳይ ፊልም ነው። “ውሃ ሲወስድ አሳስቆ” እንዲሉ፤ እንደድንገት የተጨመረው ለሁሉም “ወዳጅ” የመሆንና የብልጭልጭ ጉጉት፤ እያደር አድጎ መውጫ ያሳጣት ማክዳ (የትናየት ታምራት) ቤይሩት ሀገር በአሰሪዎቿ አደጋ የደረሰባት እህቷን የህክምና ወጪ ለመሸፈን በምታደርገው ጥረትና በምታገኘው ገቢ መካከል ያለውን ክፍተት በዕድሜ እኩዮቿ ካልሆኑ ሽማግሌ ባለሀብቶች (ሹገር ዳዲስ) ጋር የፍቅር ጥምረት ለመመስረት ስትገደድና በፈተናዎች መካከል ስታልፍ በአስቂኝ መልኩ ይተርካል።

በአንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ የባር ማንነት (የአስተናጋጅነት) ሚና ተሰጥቶት የሚሰራው ብሩክ (ሰለሞን ቦጋለ) “ድሃ ድህነቱን ይረሳ ዘንድ” በሚል የተጋበዘውን ወይን በመጠጣቱ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖበት በተኛበት የዘመን መለወጫ ምሽት ብቻውን ያገኛትን ማክዳን ወደሆቴሉ የመጣ እንግዳ ባለሀብት መስሎ ቢተዋወቃትም፤ ፍቅሩ ከዕለት ዕለት እየጨመረ ሲመጣ ግን ቀድሞ ድንገት የፈጠረውን ውሸት ሰንሰለት ሆኖበት ሲያደነቃቅፈው በሚከፍለው የየዋህ ፍቅሩ መስዋዕትነት ውስጥ ሳቅን ያጭራል።

ፊልሙ ከፈረንሳይ ፊልም ላይ ተደግፎ የመሰራቱን ያህል የወጣቷን ወጣ ያለ ባህሪና የፍቅር ግንኙነት ከመሳሳም ባለፈ አለማሳየቱ ኢትዮጵያዊ ወግ ይዞት እንጂ ከዚያም በላይ የሚያስኬድ ጉልበት የነበረው ነው። ያም ቢሆን ዳይሬክተሩና ተዋናዮቹ ለመነሻ ታሪኩ በተቻለ ሁሉ ታማኝ ለመሆን ያሳዩትን ፅናትና ጥረት ማድነቅ ተገቢ ይሆናል።

ከተለያዩ ሀብታም ወንዶች ጋር በመገናኘትና ፍቅርን በማስጀመር ራሷን በስጦታ ዕቃዎችና በጌጣጌጥ ማድመቅም ስራዋ የሆነው ማክዳ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ፍቅርን ወደገንዘብ ስትመነዝረው ማየቱ በፊልሙ ውስጥ ጎልቶ ወጥቷል። በአንፃሩ ደግሞ ከማክዳ (የትናየት ታምራት) ተቃራኒ ባህሪን የተላበሰው ብሩክ (ሰለሞን ቦጋለ) ይሉኝታ የሚያጠቃው ስብዕናውን ለገንዘብ ሲል በመሸጥ ከሚያገኘው የጌጥ ጥቅም ይልቅ ለማንነቱ ትልቅ ቦታ እንዲሰጥ የሚመርጠው ወጣት በፍቅር መውደቅ “በሬ ካራጁ ይውላል” አይነት ነው።

በአንድ ቀን ምሽት ድንገታዊ ግንኙነት በማክዳ ፍቅር እፍ-ክንፍ ያለው ብሩክ በአስተናጋጅነት በሚያገለግልበት ሆቴል ውስጥ ተስተናጋጅ መስሎ ያልተያዘ ባዶ መኝታ ክፍል ውስጥ ሲቀብጥ የደረሰበት አለቃው (ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን) ከስራ መባረሩን ተከትሎ በውሸት የገነባው ማንነቱ ተጋልጦና በሚወዳት ሴት ፊትም ተዋርዶ ሜዳ ላይ ሲቀር ፍቅሩ ግን ጥልቅ ነበርና “አለኝ የምለው ገንዘብ እስኪያልቅ አብረን መኖር እንችላለን” ማለቱ የፍቅሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ከማትወደው ሴት ጋር በፍቅር የወደቀው ይህ ወጣት መጨረሻው ምን ይሆን ብለን እንድንጓጓ “ፍቅር ሲመነዘር” ያሳየናል።

በሰው ምርጫ ተወጥራ የነበረችው ማክዳ፤ ብሩክ ጋር አምሽታ ስትመለስ ሊያገባት ሶስት ወራት ብቻ በቀረው ሽማግሌ እጮኛዋ እምነቱን ስላጎደለችበት “ተዋርደሽ አዋርደሽኝ” በሚል ምክንያት ትቷት በመሄዱ፤ ያሰበችው ሁሉ የእምቧይ ካብ ሲሆንባት እንመለከታለን። ይባስብሎም በፍቅር የያዛትን ብሩክ ያለውን ገንዘብ እስኪጨርስ አብራው ከመቆየት በዘለለ፤ በሆቴል ዕዳ ተይዞ ሳለ የተዋወቃትን በሰል ያለች ሴት ሀብት እንዴት መቀራመት እንደሚችል የማማለል ጥበብ አበክራ ስታስተምረው ማየት የፊልሙን የሳቅ አድማስ የሚያሰፋ ይሆናል።

“የወደደና ያበደ አንድ ነው” ብለን እንለፈው እንጂ “ብትተውኝ እኮ ይሄኔ ሁሉ ዘመን ብርጭቆ አጥበህ ያጠራቀምከውን ገንዘብ አትጨርስም ነበር” የምትለውን ሴት የሚከተለው ብሩክ፤ በስተመጨረሻ ወደቀልቡ እስኪመለስ ድረስ ከአዲሷ ወዳጁ ሊያ (እሌኒ ምትኩ) በስጦታ የተበረከተለትን ሰዓት ሽጦና በቃኝ ብሎ ፍቅሩን እንዳረገኝ ያርገኝ ሲል ባላየነው ነበር።

“ፍቅር ሲመዘነር” በትወናው አዳዲስ ፊቶችንና አዳዲስ ባለተሰጥኦችን ያሳየን ፊልም ነው። በፊልሙ ውስጥ ፍቅር በሁለት መልኩ ሲመነዘር እናስተውላለን። ከመልከ መልካሙዋ ወጣት ክፉኛ በፍቅር የወደቀው አስተናጋጁ ብሩክ (ሰለሞን ቦጋለ) ለእውነተኛ ፍቅሩ ሲል፤ በየዋህነት ያልሆነውን መስሎ እርሷን ለማስደሰት ትዕግስትን ሲመነዝር፣ ይቅርታን ሲመነዝር፣ መስጠትን ሲመዝር፣ መቻልን ሲመነዝር እንታዘበዋለን። በአንጻሩ ደግሞ በአፍቅሮተ ነዋይ የተሸፈነችው ማክዳ (የትናየት ታምራት) ፍቅርን ወደጥቅም፣ ፍቅርን ወደጌጣጌጥ፣ ፍቅርን ወደአስመሳይነት እና ፍቅርን ወደገንዘብ ማሽንነት ቁልቁል እየገፈተረች ስትመነዝረው ተመልክተናል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ይህቺ ገፀ-ባህሪይ የምትጠቁመን አንድ ቁምነገር አለ። ያላቸውን በሃብት የናጠጡ ሀብታም ዕድሜ ጠገቦች ለሰብዓዊ ተግባራትና ለደግነት ከሚያበረከትት አስተዋፅኦ ይልቅ የወጣት ሴቶችን ገላ ለመግዛት የሚመነዝሩት ብር ቅንጣት ታክል የማይቆጫቸው ከመሆኑም በላይ፤ ኑሮ የከበዳቸው ሰቶች ባለሀብቶች በሚያቀርቡት ገንዘብልባቸውን እንዳሸፈተው በምሬት እንድናስተውለው አድርጋናለች።

     ለ“ፍቅር ሲመዘር” ፊልም የኤዲቲጉ አቅሙ ከፍታ በጣም ጎልቶ ይታያል። በተለይም ፊልሙ ሲጀምር በኦኒሜሽን መልክ ታሪኩ የሚጠቆምበት መንገድ እጅግ የተዋጣለት ነው ማለት ይቻላል። ከዚያም ባለፈ በባዕድ አገር ቋንቋና ባህል ተሰርቶ በርካታ ተመልካቾችን ያገኘን ፊልም ወደራስ ቋንቋና ለማህበረሰባችን ቅርብ በሆነ መንገድ መሰራት መቻሉ በጣም የሚያስመሰግን ተግባር ነው ማለት ይቻላል። “ፍቅር ሲመነዘር” ለበርካታ ቀጣይ ስራዎች ምንዛሪ ማሳያ መሆን የሚችል “ፊልም” ነው።

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
20550 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us