“ፊልሞች በብዛት መሠራታቸው ጥሩ ነው”

Wednesday, 16 July 2014 11:53

በሳልሳ ዳንስ ውዘዋዜዋና አሰልጣኝነቷ ትታወቃለች። በአሁኑ ወቅት ሳምንታዊ “ዳንኪራ” የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ በአስተዋዋቂነት እየሰራች ያለች ሲሆን፤ በቅርቡ ለመድረክ ይበቃል ተብሎ የሚጠበቀውን “የጠለቀች ጀንበር” ቴአትር ላይ ድርሻ ያላት ወጣት ባለሙያ ናት። ከፊልም ሥራዎቿ መካከልም የተሰበረ፤ የዜግነት ክብር፤ ሹገር ማሚ፤ አብሮ አበድ እና ተወዳጅን ጨምሮ በርካታ ፊልሞችን ሰርታለች። በቅርቡም ከደራሲ ስብሃት ገ/እግዚያብሔር ጋር የሰራችው “የልጅቷ ማስታወሻ” የተሰኘ ፊልም-ለዕይታ ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከተዋናይት ኤደን በሪሁን ጋር የነበረን የመዝናኛ ቆይታ የሚከተለውን ይመስላል።

ሰንደቅ፡- ገና ወጣት ነሽ፤ የሙያ ዘርፎችሽ ግን በዝተዋል እንዴት እያስኬድሽው ነው ከሚለው እንጀምር?

ኤደን፡- እውነት ነው ሥራዎቼ በርከት ያሉ ናቸው። ሳልሳ ዳንዱ ከበፊትም ጀምሮ የምሰራው ነው። በሂደት በዕድሜ መግፋት እስከማቆመው ድረስ ከጎን-ከጎን መስራቴ ይቀጥላል። ነገር ግን “በአርቱ” በተለይም በትወናው ላይ እስከመጨረሻው የምቀጥልበት ይመስለኛል። ወደፊት ከትወናውና መድረክ ከመምራቱ በተጨማሪ ፕሮዲዮስ የማድረግም ሃሳብ አለኝ።

ሰንደቅ፡- ወደኪነ-ጥበቡ የገባሽው ገና ተማሪ እያለሽ እንደነበር ሰምቻለሁ፤ እስቲ ስለአጀማመርሽ ንገሪኝ?

ኤደን፡- አዎ! እኔ የተማርኩት አፍሪካ አንድነት የሚባል ትምህርት ቤት ነው። ያኔ ከአንደኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል እየተማርኩ ሳለ እዛው “እነፋዘር” (ተስፋዬ አበበ) ጋር ልጆች ሲሰለጥኑ እናይ ነበር። ያኔ በጣም ነበር አብሬ መስራትና መሰልጠንን የምመኘው ፍላጎቴን የማስተነፍስ የነበረውም “ሚኒ ሚዲያ” ላይ በመስራት እንደነበር አስታውሳለሁ።

ሰንደቅ፡- ራስሽን ወደመድረክ ያመጣሽው በምን መልኩ ነው ታዲያ?

ኤደን፡-“የሃይስኩል” ትምህርቴን አደይ አበባ መማር ስጀምር አርቲስት ሃይሉ ፀጋዬ የቴአትር “ኮርስ” ይሰጥ ነበር። ስልጠናውን እንድካፈል ስለፈቀደልኝ ገብቼ ሰለጠንኩ። ያኔ ብዙ ልጆችን አውቄ፤ ትወና እንዴት እንደሆነ በተግባር መስራት ጀመርኩ። ፑሽኪን አዳራሽ ውስጥ ስራዎችን እናቀርብ ነበር። ከዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሮፌሽናል መድረክ ላይ “ሞት በቀጠሮ” የተሰኘውን የአንዱአለም አባተን ስራ በራስ ቴአትር መድረክ ላይ ይዘን ቀረብን። ከዚያ በኋላ የመስራት አጋጣሚዎቼ እየሰፉ መጡ ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- እንደጀማሪ ከተመልካች ጋር ስትገናኚ የነበረው ስሜት ምን ይመስላል? ምናልባትም ስሜቱ በቴአትርና በፊልም ስራዎች ውስጥ እንዴት ሊገለፅ ይችላል?

ኤደን፡- የመጀመሪያ ትልቁ ቴአትር ለኔ “ሞት በቀጠሮ” ነበር፤ ከፊልም የመጀመሪያ ስራዬ ሊባል የሚችለው ደግሞ “የተሰበረ” ይሰኛል። በመድረክም ሆነ በስክሪን መስራት ትንሽ ያስፈራል። ነገር ግን አብሬያቸው ቴአትሩን እሰራበት የነበሩት ልጆች በጣም ጥሩዎችና እንዳልፈራ የሚያበረታቱኝ ነበሩ። በዚህ አጋጣሚ ካሌብ ዋለልኝን በጣም ማመስገን እወዳለሁ። ገና በፈተና ስገባ ፈርቼ ስለነበር እርሱ ነው ያበረታታኝ። ድምፄ ሁሉ ያን ያህል አይሰማም ነበር። ከመፍራቴ የተነሳ ማለት ነው። ቀስ በቀስ ግን ድፍረቱን እያገኘሁ ፈተናውንም አልፌ ነው ቴአትሩን ለመስራት የቻልኩት። ከዚያ ቴአትር ብዙ ልምድ አግኝቼበታለሁ። እንዳልከው ወደመድረክ ከመውጣቴ በፊት ፍርሃት ይሰማኛል፤ ነገር ግን ልክ መድረኩን ስረግጥ ሁሉን ነገር ረስቼ ነው ገፀ ባህሪዋን እጫወት የነበረው። ከተመልካቹም ይገኝ የነበረው ምላሸ በጣም አሪፍ ነበር ማለት እችላለሁ። ነገር ግን በቴአትሩ ራሴን ስለማላየው ይሻለኛል እንጂ በፊልም ስክሪን ላይ ራስን ማየት በጣም ነው የሚያስፈራኝ። ከመጓጓትህ የተነሳ ትፈራለህ። አንዳንዴ እንደውም እኔ ፊልም ሰርቼ ከመውጣቱ በፊት ገና በኢዲቲንግ ላይ እያለ አሳዩኝ ብዬ እጠይቃለሁ፤ እንዲህ- ቢሆን ኖሮ ብዬ ከምቆጭ ቀድሜ ማየትን እመርጣለሁ።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ ከደራሲ ስብሃት ገ/እግዚያብሄር ጋር የሰራሽውና “የልጅቷ ማስታወሻ” የተሰኘ ፊልም ለተመልካች ይበቃል፤ እንዴት ነበር ስራው ?

ኤደን፡- እውነቱን ለመናገር “የልጅቷ ማስታወሻ” ላይ ያለችውን ገፀ-ባህሪይ የምወጣት አልመሰለኝም ነበር። በዚህ ላይ ገፀ-ባህሪዋ ሴተኛ አዳሪ በመሆኗ ሌሊት ላይ አጭር ቀሚስ አድርገን በብርድ ነበር የምንሰራው። ገፀ-ባህሪዋን በደንብ ለመስራት እጥር ነበር። በዚህ ላይ ጋሽ ስብሃት እንዳለበት ስሰማ በጣም ነበር የበረታሁት። ጋሽ ስብሃት በጣም የምወደውና ደራሲ ነው። ከእርሱ ጋረ ስትሰራ ነፃና ደስተኛ ሆነህ ነው። በአጠቃላይ የፊልሙ ቡድን አባላት በጣም ደስተኞች ነበርን። በነገራችን ላይ ከፊልሙ አባላት ጋር በጣም ጓደኞች ከመሆናችን የተነሳ አሁን ድረስ እንጠያየቃለን።

ሰንደቅ፡- ስብሃት እንደደራሲነቱና እንደተዋናይ እንዴት ትገልጪዋለሽ?

ኤደን፡- ሁላችንም እንደምናውቀው ስብሃት ምርጥ ፀሐፊ ነበር። በትወናውም ቢሆን አሪፍ ተዋናይ እንደሆነ አብሬው በሰራሁበት ጊዜ ለማወቅ ችያለሁ። ዘና ብሎ ከመተወኑ የተነሳ ገፀባህሪን ተላብሶ ሳይሆን ኑሮውን እየሰራው ሁሉ ነው የሚመስልህ። አንዳንዴ ሳስበው የሚቆጨኝ የፃፈውን ያህል ምናለ ብዙ ፊልም በሰራ ሁሉ ብዬ እመኝ ነበር።

ሰንደቅ፡- እስካሁን ከሰራሻቸው ገፀ ባህሪያት የትኛዋ ትመስጥሻለች?

ኤደን፡- እኔ አሁን ድረስ የማልረሳት ገፀ-ባህሪይ ብትኖር “የልጅቷ ማስታወሻ” ላይ ያለችውን ገፀባህሪይ ነው። ለምን አስታውሳታለሁ መሰለህ፤ በጣም ታሳዝነኛለች። ሴተኛ አዳሪ ናት፤ ነገር ግን ትዳርን በእጅጉ የምትፈልግ ሴት ናት። በጣም የሚገርመኝ ብዙዎቻችን ልጅ ሆነን ዶክተር፣ ፓይለት፤ ምናምን እንመኛለን አይደል? እርሷ ግን ልጅ ሆና እንኳን ትመኝ ነበረው የቤት እመቤት መሆን እንደነበረ ስትተርክ በጣም ነው የምታሳዝነኝ። ሁሌ ራሷን ደብቃ ደስተኛ መስላ የምትኖር ገፀ ባህሪይ ናት። እናም አሁን ድረስ በውስጤ የቀረች ሴት ናት።

ሰንደቅ፡- አንድ ጥያቄ ላንሳ እስካሁን ከሰራሻቸው ገፀ-ባህሪያት ውስጥ የአንዷን ህይወት ኤደን መኖር አለባት ቢባል የትኛዋን የገፀ-ባህሪይ ህይወት ትመርጫለሽ?

ኤደን፡- (ሳቅ) “ተወዳጅ” የተሰኘው ፊልም ላይ የሰራኋትን ገፀ-ባህሪይ ህይወት ብኖር እመርጣለሁ። እዛ ላይ ያለችው ልጅ ሙሉ ጊዜዋን በስራ ያሳለፈች ናት። ቤተሰቦቿ ባወረሷት ሃብት የምትኖር ሆና ድንገት ከጎዳና ልክ ጋር ፍቅር ይይዛታል። ይህቺ ገፀ-ባህሪይ ደስ ትለኛለች። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ቴአትር ላይ ብዙ የለሽም፤ ስለሚከብድ ነው?

ኤደን፡- እውነቱን ለመናገር ከፊልምና ከቴአትር፤ ቴአትርን ነው የምመርጠው። እንዳልከውም ቴአትር መስራት ይከብዳል። እኔ ራስ ቴአትር መድረክ ላይ “የሞት ቀጠሮንን ከሰራሁ በኋላ አሁን በቅርቡ ደግሞ “የጠለቀች ጀንበር”ን በብሔራዊ ቴአትር ለማሳየት እየሰራን ነው። ብዙ ባለሙያዎች እንደሚያውቁት ፊልም ብዙ አያደክምም ቴክኒኩ ከገባህ እንዴ ሰርተህ ዞር ትላለህ። ቴአትር ግን ገና በልምምድ ብቻ አምስትና ስድስት ወር ያውም ደስ እያለህና እየተማረክበት የምትሰራው ስራ ይመስለኛል። ለምሳሌ አሁን ላይ “የጠለቀች ጀንበር” ቴአትርን ስሰራ ሽመልስ አበራ (ጆሮ) ጨምሮ እነሱራፌል፣ እነገነት፣ እነተስፋዬ፣ እነመለስ ያሉበት ስራ ነው። ከእነሱ ደግሞ ብዙ የምማረው ነገር ይኖራል። አብሬያቸው በመስራቴ በጣም እድለኛ ነኝ ብዬም አስባለሁ። እናም ቴአትር እድሉም ጠባብ ነው ይከብዳልም። ግን እኔ መስራት ሳልፈልግ ቀርቼ አይደለም ወደፊልሙ ያዘለነበልኩት፤ አጋጣሚ ነው።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በኋላ ብስራት ብለሽ የምትመኛት ምን አይነት ገፀባህሪ ናት?

ኤደን፡- ወጣ ያለችና አይረሴ ገፀ ባህሪይን ብሰራ ደስ ይለኛል። ለምሳሌ “አብሮአበድ”ን ስንሰራ ብዙ ልጆች ሆነን ስንፈተን እብድ ሆኖ ለመስራት ፍቃደኛ አልነበረም። እንደውም በግልፅ እኔና ማህሌት ሹመቴ ብቻ ነን የመረጥነው። ብዙዎቹ የእብዷን እህት መስራት ነበር የፈለጉት፤ እንደ አጋጣሚ ግን እኔ የእብዷን እህት ነው የሰራሁት። ነገር ግን እንዲህ የምትፈትን ወጣ ያለች ገፀ-ባህሪይን መስራት እናፍቃለሁ።

ሰንደቅ፡- በፊልም ትወና ውስጥ በተለይ አብሬያቸው ብሰራ ብለሽ የምትመኛቸው ወንድና ሴት ተዋንያንን ጥቀሺልን?

ኤደን፡- አብሬያቸው ብሰራ ብዬ የምመኛቸውና ጥሩ ስራዎችን የሚሰሩ ብዙ ተዋንያኖች አሉ። ነገር ግን ከሴት አንድ፣ ከወንድ አንድ ካልከኝ ከግሩም ኤርሚያስና ከሀረገወይን አሰፋ ጋር ብሰራ ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- የፊልም ስራዎች እየተበራከቱ ነው። ነገር ግን በጥራታቸው ላይ ብዙዎች ጥያቄን ያነሳሉ፤ አንቺ በዚህ ላይ ምን ሀሳብ አለሽ?

ኤደን፡- ፊልሞች በብዛት መሰራታቸው በጣም ጥሩ ነው። ፊልሞች መብዛታቸው የጎንዮሽ ጉዳት አለው ብዬ እኔ አለምንም። ከመስራት ብዙ ጥቅምና ትምህርት እናገኛለን። ብዙ ፊልሞች መስራት ስንችል ነጥረው የሚወጡ ጥቂትም ቢሆን ተዋንያንን፣ የካሜራና የኤዲቲንግ ባለሙያዎችን እንዲሁም ዳይሬክተሮችንና ፀሐፊዎችን የማግኘት አጋጣሚው ይፈጥርልናል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ወደፊት የተጣራ ስራ እናያለን ማለት ነው። ነገር ግን አንድ አይነት ዘውግ መደጋገማችን ያሳስበኛል።

ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት በኢቲቪ-3 “ዳንኪራ” ፕሮግራም ላይ አስተዋዋቂ ሆነሽ ትሰሪያለሽ እስቲ ስለዳንኪራ ንገሪኝ?

ኤደን፡- “ዳንኪራ” በጣም አሪፍ ፕሮግራም ነው። ሲጀምር እኔ ሳልሳ ዳንስን ስለማሰለጥን ከስራዬ ጋር ይሄዳል። በመቀጠል ግን “ዳንኪራ” ወጣቱ የአገሩን ባህላዊ የውዝዋዜ ስልቶች እንዲያውቅ ከታዋቂ ሰዎች ጋር አዝናኝ በሆነ መልኩ ማቅረቡን ወድጄው ነው የምሰራበት። ብዙ ተመልካችም ያለው ፕሮግራም እንደሆነ ተረድቻለሁ።

ሰንደቅ፡- ፕሮግራሙ ከማዝናናት ባለፈ ምን ፋይዳ አለው ብለሽ ታስቢያለሽ?

ኤደን፡- እኔ ውጪ ሆኜ ሳየው አዝናኝ ብቻ ይመስለኝ ነበር። ነገር ግን ገብቼ ስሰራበት፤ የሚደወለው ስልክ በጣም የሚገርም ነው። ወጣቱ ባህላዊ ውዝዋዜዎችን ለመማርና ለማወቅ ጉጉት ስላለው የት መማር እንደሚቻል ደውለው የሚጠይቁን ብዙዎች ናቸው፡ ይህ ወጣቱን ወደሀገሩ ባህል እንዲመለከት ያደረገበት ትልቁ ፋይዳው ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- በትርፍ ጊዜሽ ምን ያዝናናሻል?

ኤደን፡- ፊልም ማየትና የእግር ጉዞ ማድረግ ያዝናናኛል። በተጨማሪም ሳልሳ መደነስና ዋና መዋኘት በጣም ነው የሚያዝናናኝ።

ሰንደቅ፡- ወደፊት ከትወናውና ከሳልሳ ዳንስ በተጨማሪ ምን ሃሳብ አለሽ?

ኤደን፡- የፊልም ሃሳቦች አሉኝ። ነገር ግን የመፃፍ ችሎው አለኝ ለማለት አልደፍርም። ባይሆን ታሪኩ ተፅፎ የማዘጋጀትና ፕሮዲዩስ የማድረግ ፍላጎቱ ስላለኝ በዚህ መልኩ ከትወናው በተጨማሪ እመጣለሁ ብዬ አስባለሁ።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
8090 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us