አዲስ መንገድ፤ “ከሠላምታ ጋር” ቴአትር

Wednesday, 23 July 2014 17:05

ባሎች አልበረከትልሽ ያሏትና የትዳር ያለህ የምትልን ሴት ታሪክ ተንተርሶ በድንቅ አቀራረብ የሚተርክ ሰሞነኛ ቴአትር ነው።

ቀላል የመድረክ ግንባታን ድንቅ ዝግጅት፣ ታሪኩን የሚያዋዛ የዳንስ ቅንጅትና ምርጥ የትወና ብቃት የታየበት ሥራም ነው፤ በመዓዛ ወርቁ ተፅፎ የተዘጋጀውና በሳምንት ለሁለት ቀናት በጣይቱ ጃዝ አንባ አዳራሽ፣ በዓለም ሲኒማ መድረኮች በመታየት ላይ የሚገኘው “ከሠላምታ ጋር” ቴአትር። ቴአትሩን ፕሮዲዩስ ያደረገው ኪባ መልቲ ሚዲያ ነው።

ወንድ አልበረክትልሽ እያላት፤ የቋጠረችው የትዳር ውል ሁሉ በግትር አቋሟ ምክንያት ጉም የመጨበጥ ያህል ሲሆንባት የምናያት ማርታ (ኤልሳቤጥ መላኩ) አራተኛውንና በእናቷ “አዳኝነት” ተፈልጎ የተገኘላት ሁለት ሚስቶች የሞቱበትና ስድስት ልጆች ያሉትን ሰው በማግባትና ባለማግባት የሃሳብ ፔንዱለም መካከል እንደዋለለች ነው ቴአትሩ የሚጀምረው።

ቀላል ከሆነው መድረክ አገነባቡ ጀምሮ በቴክኒካል ቅንብሩ እጅግ የተዋጣለት “ከሰላምታ ጋር” ቴአትር ተጀምሮ የሚያልቀው በገፀ-ባህሪዋ መኝታ ቤት ውስጥ ነው። ይህን እንድል ያስደፈረኝ በመድረኩ ላይ የምናየው ገፀ- ባህሪዋ ከራሷ ጋር የምታወራበትና የዕድሜዋን መግፋት የምትመለከትበት የሚመስለንን ማሳያ (መስታወት፣ በነገራችን ላይ መስታወቱ ተመልካችንም የሚያሳይ ነው) እና አንድ አልጋ ብቻ መኖሩን ልብ ስንል ነው።

አብዛኛውን ጊዜውን የዋናዋን ገጸ-ባህሪይ የምልስት ታሪክና የሃሳብ ውጣ ውረድ በጉልህ የሚያሳየው ይህ ቴአትር፤ የገፀ ባህሪዋን የቃላት ጦርነት ለመቀነስና ለማዋዛት ሲልም በዳንስና በሶስቱ ቧሎቿ ምልልስ ይተረክልናል። እዚህ ላይ የኤልሳቤጥ መላኩን ያለአንዳች እረፍት በመድረኩ ላይ በብቃት መተወን ሳናደንቅ ማለፍ ፅሁፉን ጎደሎ ያደርገዋል።

“ከሠላምታ ጋር” ቴአትር አጥብቃ የምትሻውን ትዳር ባለማግኘቷ ሰላሟን ያጣችና የመጨረሻዬ ይሆናል ብላ የምታስበውን፤ ዳሩ በአካል አይታው የማታውቀውን ሰው ለማግባት የምትወጥንን ሴት ታሪክ ከመተረኩ ባሻገር ቴአትሩ ለበርካታ ትርጉሞች የተጋለጠና ጥልቅ ማህበራዊ ጉድለቶቻችንን የሚጠቁመን ነው ማለት ይቻላል።

በቴአትሩ ውስጥ አንድም ሶስትም ሆኖ አስገራሚ የትወና ብቃቱን ያሳየን ፈለቀ የማርውሃ አበበን መመልከት ተገቢ ነው። አንድነቱ ለሴትየዋ ወይም ለማርታ ባል ሆነው የመጡትን ሶስት ሰዎች ወክሎ መጫወቱ ሲሆን፤ ሶስትነቱ ደግሞ የተለያዩ ባህሪያትን ማሳየቱ ላይ ነው። ይህ ከወጪና ከተዋናይ ቅነሳው ባሻገር በግልጽ የሚታይ ጥበባዊ ውህደትን በማርታ አማካኝነት ማሳየት የቻለ ነው። ሶስቱም ለማርታ ባሎች ነበሩ፤ ሶስቱም የተለያየ ፀባይ ያላቸው ሰዎች ነበሩ።

የኋላ ታሪኳን ባልተለመደ የመድረክ አተራረክ በምልሰት የምታሳየን ማርታ (ኤልሳቤጥ መላኩ) ስለመጀመሪያ ባሏ ሽብሩ (ፈለቀ የማርወሃ አበበ) ስትተርክ ቅናታምነቱና ሰካራምነቱ አሰልችቷት የቋጠረችው ትዳር ሲፈታ ታሳየናለች። ይህ ሽብሩ የተባው ገጸ ባህሪይ ሚስቱ ከርሱ በፊት ትወደው የነበረውን ሰውዬ እያሰበ በንዴት የሚጠጣና በቅናት የሚያስጨንቃት አይነት ሆና ተስሎ ቀርቧል።

ከዚህም በላይ ለሽብሩ ሞት ቀላል ይመስል የማርታን የቀድሞ ጓደኛ (የመጀመሪያ ምርጫዋ የሆነውን ሰው) አድራሻ ይጠይቃል። ለምን ሲባል? በምድር ቤት የነበረውን አድራሻውን በሰማይ ቤት ላድርግለት የሚል ነበር ምላሹ። ይህ ሰው ቅናተኛ ከመሆኑ የተነሳ ነዝናዛና ፀብያለሽ በዳቦ ስለነበረ ፈታሁት ትለናለች፤ ገፀባሪዋ።

ማርታ (ኤልሳቤጥ መላኩ) ሁል ጊዜ የሚሰማት የሰው ሃሜትና የወላጅ እናቷ ቆመሽ ቀረሽ አይደል? የሚለው ወቀሳ እንደሆነ ትነግረናለች። ስለራሷም ስትገልጽ፣ “እኔ ማለት ብቸኛ ሴት፤ ላጤ ሴት፤ ፈት ሴት፤ ተስፋ የቆረጥኩና እርጅና በሬ ላይ የቆመ ሴት ነኝ ሳሳዝን!” ትለናለች። እውነትም የሚታዘንለት አይነት ገፀ-ባህሪይ ናት።የመጀመሪዋ ባሏን ፈታ የመጀመሪያ ምርጫዬ ነው ያለችውን ወንድ ስታገባ ትዳር እንደአውቶቡስ በፈለጉት ፌርማታ ገብተው በፈለጉበት ፌርማታ መውረድ የሚቻልበት እንዳልሆነ ትጠቁማለች።

የመጀመሪያ ትዳሩን ፈቶ ወደመጀመሪያ ምርጫው የተመለሰው ዮሐንስ (ፈለቀ የማርውሃ አበበ) ድንገት እህል ውሃችን አልቋልና ፍቺ እፈልጋሁ ይላል። “የኔ ሳትሆኚ አመልክሸ ነበር፤ ሳገኝሽ ግን እንጥፍጣፊ ፍቅር የለኝም” ሲል የፍቺ ሃሳቡን ያፀናው ዮሐንስ፤ ትዳሩን የመሰረተው ለበቀል ይሁን የመጀመሪያ ሚስቱን ለመርሻነት በውል ሳይነግረን ሳቅን በሚያጭር መልኩ ማርታን ሲሰናበታት መመልከቱ ግርምታን የሚፈጥር ነው።

ፍቺ ዕጣ-ክፍሏ ይመስል፤ “ዮሐንስ ጥሎኝ ሲሄድ ሰማይ ድፍት የሚልብኝ መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን ሰማዩም እዛው ነው፤ እኔም በህይወት አለሁ” የምትለው ማርታ ድጋሚ ባለተራውን ስታጠምድ እንመለከታለን።

ሶስተኛው የማርታ ባል ሚሊዮን (ፈለቀ የማርውሃ አበበ) ሲሆን፤ ይህም ሰው ከደሃ ቤተሰብ የተገኘና በቁጠባና በስራ እራሱን ቱጃር ለማድረግ የሚታትር አይነት ሰው ሆኖ ተስሏል። የዚህ ሰው አስቸጋሪነት የትገባሽ የትወጣሽ ሳይሆን “ምን በላሽ፣ ምን፣ጠጣሽ፣ ምን ሸመትሽ?” የሚል እና ለነገሮች ሁሉ የሂሳብ ማወራረጃ ደረሰኝን የሚፈልግ ከቆጣቢነት ወደ ቀብቃባነት ያደገ መሆኑ ነው።

ትዳሩ ሲጀመር “ካገቡ አይቀር እንዲህ አይነቱን ባለዕራይ ነው” ብላ የጀመረችው ማርታ፣ “ከምንበላው እየቀነስን እንቆጥባለን- እንቆጥባለን- እንቆጥባለን” ስትል የሰውየውን አስተሳሰብ ታስረዳለች። ይህ ለዘንድሮውን ቆጣቢ ተመልካች በእጅጉ ሳቅ መፍጠር የሚችል ክፍል ነው።

“ከሰላምታ ጋር” ቴአትር በዳንስ የታጀበ ስራ ነው። የዳንስ እንቅስቃሴውና ሙዚቃው ሙሉ በሙሉ ታሪኩን የሚያፋስስ እንጂ የሚያፋልስ ሆኖ አይታይም። ዳንሱን በመድረክ የሚቀምሩት ወጣቶች የገፀ-ባህሪያቱን ሃሳብ በጉልህ የሚያሳዩን ሆነው ታይተዋል። ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ማርታ (ኤልሳቤጥ መላኩ) ብቸኝነትና ምስቅልቅል ያለ ሃሳብ በተሰማት ጊዜ በዳንስ የምታጅባት ወጣት (ገነት ደምሴ) ብቸኝነቷንና ምስቅልቅል ያለ ሃሳቧን ስልት ባለው እንቅስቃሴ ልታሳያት ትሞክራለች።

በሌላም በኩል የማርታ ሁለተኛ ትዳር ሲፈፀምና ማርታ ከዮሐንስ ጋር ስትጋባ የነበራትን ደስታ ለማሳየት ሁለቱ ዳንሰኞች በጋራ በቬሎ አልባስ የታገዘ ድንቅ ውዝዋዜን አሳይተውናል። የመጨረሻውና የዳንሱ ግብዓት የገፀ-ባህሪያቱን ሃሳብ የሚተርክ መሆኑን በጉልህ የሚያሳየን “ሚሊዮን” የተባለው ገፀ-ባህሪይ የውጪ ደረሰኞችን ሲያወራርድ በነበረበት ጊዜ፣ ሲተኛም ሲነሳም ያለሂሳብ ሃሳብ እንደሌለው ወጣቱ ዳንሰኛ (ምንተስኖት ጌታቸው) በጉልህ ያሳየናል።

አኗኗራችንን፣ ጉርብትናችንን፣ ቅናታችንን፣ ፍቅራችን፣ ትዳራችንን በአጠቃላይ የህይወት ውጣ ውረዳችንን በ1፡30 ጊዜ ውስጥ የማርታን ታሪክ ተንተርሶ የሚተርክልን “ከሰላምታ ጋር” ቴአትር፤ በቴክኒክ በእጅጉ የበለፀገና ለሌሎች ባለሙያዎችና ተማሪዎችም ማሳያ ሆኖ መቅረብ የሚችል ድንቅ ቴአትር ነው። “ከሠላምታ ጋር” የተሰኘው የመዓዛ ወርቁ ስራ፤ ቴአትርን በቴክኒክና በታሪክ ፍሰት እረገድ እንዲሁም በትወናውና በዝግጅት አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው ለማለት ይቻላል። ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከመድረክ ያላጣናትን የማርታን (ኤልሳቤጥ መላኩ) ገፀ-ባህሪይ ሰላም ማጣት እያሳየን “ከሰላምታ ጋር” የሚለን ይህ ቴአትር፤ የትዳር መልቀቂያ ደብዳቤ አይነት የሚመስል ስላቅን ይዟል።

“ከሠላምታ ጋር” በመድረክ ያላየናቸውን የማርታን ጎረቤቶችና እናቷን ጭምር በጉልህ ስሎ ማሳየት የቻለና በሁለት ተዋንያን የበርካቶችን ጉልበት የተመለከትንበት ስራ ነው። በስራው ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች ሁሉ ይህን መሰል ግሩም ጥበብ ስላሳዩን ምስጋናችንን “ከሰላምታ ጋር” ይድረሳቸው ማለት እንወዳለን።    

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16018 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us