የ“፮ቱ ፋና ወጊዎች” መፅሐፍ ከፍና ዝቅ

Wednesday, 30 July 2014 12:16

“ሰው ሁለቴ ይፈጠራል። መጀመሪያ በእናቱ ማህጸን ውስጥ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ወደዚህ አለም ከመጣ በኋላ። ለዚህም ነው የስነ- ልቦና ምሁራን የሰው ልጅ ስብዕና የተፈጥሮና የአካባቢ ተፅዕኖዎች ድምር ውጤት ነው የሚሉት። የሰው ልጅ ከወላጆቹ ከሚወርሰው ዘረመላዊ ተፅዕኖ ቀጥሎ ከህጻንነቱ አንስቶ የሚቀላቀለው ማህበረሰብና አካባቢው ተፅዕኖ ያሳድሩበታል። በተናጠልም ሆነ በጋራ እኚህ ሥርወ-ምክንያቶች ወሳኝ መሆናቸውንና ግለ-ሰቦች የራሳቸውና የአካባቢያቸው መሃንዲሶች መሆናቸውንም ሳንዘነጋ፤ አንድ ማህበረሰብ በአንድ ወቅት ወይም በሌላ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ፤ የአንድን ትውልድ አቋም በመቅረፅ ረገድ የሚኖረው ድርሻ እጅግ የላቀ ነው። “(ከመፅሐፉ መግቢያ ተቀንጭቦ ተወሰደ)

“፮ቱ ፋና ወጊዎች” መፅሐፍ በውስጡ ታሪካቸውን ለዚህና ለመጪው ትውልድ ማስተማሪያነት የመረጣቸው ስድስት ጎምቱ ሰዎች በእውነቱም በየመስካቸው የተሳካላቸውና ፋና ወጊዎች ሊባሉ የሚችላቸው ናቸው።

መጽሐፉ ከወራት በፊት ታትሞ ለገበያ የዋለ ሲሆን የመረጣቸውን ባለታሪኮችና ስራቸውን ለዚህ ትውልድ ያለው አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልሆነ ይታሰባል። እነሆ ጊዜው ክረምት ከመሆኑና በርካታ ሰዎችም ለንባብ የሚታትሩበት ወቅት ከመሆኑ አንጻር በተለይ ወጣቶች ይህን መፅሐፍ የማንበብ አጋጣሚውን ቢያገኙ በፋናወጊዎቹ ታሪክ ውስጥ የራሳቸውን ተስፋ፣ እቅድና መድረሻ ለመተለም ይረዳቸዋል። በመሆኑም መፅሐፉ የቀረበበት መንፈስ ከመረጃና ትምህርት ሰጪነቱ ባሻገር አዝናኝ መሆኑ “ከነገሩ አነጋገሩን” እንድናስተውል ያደርገናል።

በሚዲያውና በመዝናኛው አለም ስሟ የገነነውን ኦፕራ ዊንፍሬን፤ አገራችን ካፈራቻቸው ምጡቅ የጥበብ ሰዎች መካከል አንጋፋው እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን፤ ከመንፈሳዊ አባትነታቸው ባሻገር በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው የሚታወቁትን ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን፤ በተቃራኒው ደግሞ እድሜውን በዱር በገደል በትግል የጨረሰውን አገር አልባውን “አለማቀፋዊ” ጀግና ቼ ጉቬራን እንዲሁም የኮምፒዩተር አብዮተኛውንና ቢሊየነሩ ቢል ጌትስን ጨምሮ ባለምጡቅ አእምሮውንና የአንጻራዊነት ንድፈ ሃሳብ ቀማሪውን አልበርት አንስታይንን ህይወት በመጠኑ ሊያስቃኘን የሞከረ መፅሐፍ ነው።

መፅሐፉ እነዚህን ጎምቱና ህይወታቸውን በጥረታቸው በመለወጥ ስማቸውን ለአለም ህዝቦች ያዳረሱ ሰዎች ማተቱ ምን አዲስ ነገር አለው? ሊያስብለን ይችላል፤ ነገር ግን ፀሐፊው ፀሐዬ አለማ ከዚህ ቀደም በመፅሐፉ ምረቃም ወቅት እንደተናገሩት፣ “ጀግኖችን ደጋግሞ ማስታወስ የራሱ መልካም ጎን የመኖሩን ያህል በመፅሐፍ መልክ ሲቀርቡም በብዙ ንባብ ያገኘኋቸውንና አዲስ የመሰሉኝን መረጃዎች ለማካተት ሞክሬያለሁ” ይሉናል።

በመፅሐፍ ውስጥ ከተጠቀሱትና ለዛሬ ከመዝናኛ አምድ ጋር ይሄዳሉ ያልኳቸውን ሃሳቦች በጥቂቱ በማንሳት ቀሪውን እንድታነቡት ልጋብዝ። አርጄንቲናዊው ዶክተር ቼ ጉቬራ ራሱን ለጭቁን ህዝቦች አሳልፎ በመስጠት ከሀገሩ አልፎ በጎረቤት አገሮችም በነበረው የትግል አስተዋፅዖ ይጠቀሳል። ቼ ስለህይወት ትዝታው ሲናገር፤ “ያለፈ ህይወቴን ዞር ብዬ ስቃኘው ለአብዮታዊ ድል ብቁ በሆኑ መተባበርና ትጋት እንደሰራሁ አስባለሁ” ይላል (ገፅ ፡39)። ይህ ድንበር የለሽ የጭቁኖች ታጋይ አዘውትሮ የሚታወስበት አንድ አባባል አለው “ለጠላት ተንበርካኪ ከመሆን ታግሎ መሞት ይሻላል” ይለናል (ገፅ ፡46)

በአሁኑ ወቅት በዓለም መገናኛና የመዝናኛ መንደሮች ስሟቸው በክብር ማኖር ከቻሉ ጥቂት እንስቶች አንዷ ናት፤ ጥቁር አሜሪካዊቷ ኦፕራ ዊንፍሬ። በበርካታ ውጣ ውረዶችና በመደፈር አደጋ ውስጥ ያለፈችው ኦፕራ አሁን የደረሰችበት ህይወት ለበርካታ ወጣት ሴቶች ተምሳሌት መሆን የሚያስችላት ነው። ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ዝነኛ የመሆን ምኞት ይዛ ነበር። ይህቺ ወጣት ፍቅርና እንክብካቤ ከሌለው ቤተሰብ ብትገኝም፤ የመደፈር አጋጣሚው ቢጎበኛትም ዳሩ ግን በትምህርቷ በመግፋት ያለመችውን ለማሳካት አላገዳትም። ለዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪ ሳለች በቁንጅና ውድድር አንደኛ ከወጣች በኋላ የህይወቷ መንገድ ሲቀየር እንመለከታለን፤ “እዚያው ናሽቪል ከሚገኘው የሲ.ቢ.ኤስ ከባቢያዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ በምሽት ዜና አቅራቢነት እንድትሰራ የተሰጣትን እድል በፀጋ በመቀበል የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን ከሁለቱ ብዙሃን መገናኛዎች ሥራ ጋር አጣጥማ ማስኬዷን ተያያዘችው። በዚህም በናሽቪል በእድሜ ከሁሉም ያነሰችና የመጀመሪያዋ አፍሮ- አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ለመሆን በቃች፡ (ገፅ-54) ይለናል፤ የረጅም የስኬት ህይወት ጅማሬዋን ሲነግረን።

ሌላኛው ሰው ብዙዎች ገና ከመጀመሪያው ሳይንቲስት ሆኖ የተወለደ ሰው ነው ይሉታል፤ አልበርት እንስታይንን፡፤ “እጅግ ወሳኙ ጉዳይ ያለማቋረጥ ጠያቂ ሆኖ መገኘት ነው” የሚለው ይህ ሰው፤ ሙሉ በሙሉ ታዛዥ መሆንን በሚጠይቁት የትምህርት ቤቱ ደንቦች ደስተኛ ያልነበረ ሲሆን የካርቶን ቤቶችን ለመስራትና ቤቱ ውስጥም ከእህቱ ማሪያ ጋር መጫወትን ይመርጥ ነበር” ተብሎለታል። (ገፅ-63) የአንስታይን ሊቅነት ከጠያቂነቱ የመነጨ ሲሆን እንደማሳያ የሚከተለው በመፅሐፉ ውስጥ ሰፍሯል፤ “አንስታይን በተፃራሪነት ላይ የተመሰረተ የመጠየቅ ባህልን ያዳበረ ነበር። ይህም በጣም ከሚደንቁት የአንስታይን ባህሪያት አንዱና ዋንኛው መሆኑ ግልጽ ነው። በዚህ ረገድ አንድ የአንስታይንን ባህሪይ የሚጋራ የቻይናውያን አባባል መጥቀስ ይቻላል። የሚጠይቅ ሰው ለአምስት ደቂቃ ያህል ሞኝ እንደሆነ ሊቆጠር ይችላል፤ የማይጠይቅ ሰው ደግሞ በህይወት ዘመኑ ሁሉ ሞኝ ሆኖ ይቀራል። እውነተኛ ትምህርት ጥያቄ በመጠየቅ ላይ የሚመሰረት ነው።” (ገፅ፡72)

የቴክኖሎጂ እድገትን ያፋጠነ ሰው ነው ይባላል፤ የማይክሮ ሶፍት መስራቹና ባለቤት ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ። በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ በሁለተኛ አመቱ ጥሎ የወጣው ቢል ጌትስ ታሪክ ሲቀጥል “ቢል ጌትስ ዩኒቨርስቲውን ጥሎ በወጣ በ10 ዓመቱ ውስጥ ሚሊየነር፤ ከዚያም በ31 ዓመት እድሜው ቢሊየነር ለመሆን በቅቷል “(ገፅ፡83)። ይህ የሰው ልጅ ውስጡን ማዳመጥ ከቻለና ፈጠራዎቹንም መተግበር ከቻለ ስኬት በእጁ እንደሆነችም የሚያሳይ ታሪክ አለው። “ህይወት ሚዛናዊ አይደለችም በሚገባ ተጋፈጣት” የሚለው ቢልጌትስ ራሱን ተፍጨርጭሮ ለትልቅ ደረጃ ያደረሰ ተምሳሌት ነው።

“ታሪክን ራሱ ለማንበርከክ የቻሉት ታላቅ ሰው” ይሏቸዋል። እኚህ ሰው ፊት ለፊት በጥይት መትቶ ለመግደል አስቦ ያቆሰላቸውን ሰው ከልባቸው ይቅርታ አድርገውለታል። በዚህም “ይቅር ባዩ አባት” ተሰኝተዋል፤ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ። በታይም መፅሔት ከ15 ጊዜ በላይ በፊት ገፅ መቅረባቸውም ከጵጵስናቸው ባሻገር በአለም ላይ የነበራቸውን የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝነት ማሳያ አድርገው የሚወስዱት በርካቶች ናቸው። ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የነበራቸውን አለማቀፋዊ ተፅዕኖ በተመለከተ የሶቬየት መሪ የነበሩት ሚካኤል ጉርቫቾቭ በ1992 (እ.ኤ.አ.) ባሳተሙት መፅሐፍ ውስጥ እንደሚከተለው ገልፀዋቸዋል። “ባለፉት ጥቂት ዓመታት በምስራቅ አውሮፓ ውስጥ ሲከሰት የታየው ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ጆንፓል ዳግማዊ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በፖለቲካውም ጭምር የተጫወቷቸውን ወሳኝ ሚናዎች ባይታከሉበት ኖሮ ይሆን ነበር ተብሎ በጭራሽ ሊታሰብ የማይችል ነው” ሲሉ መስክረውላቸዋል (ገፅ፡102)

በሥራቸውና አለም ባደነቀላቸው የስዕል ሥራዎቻቸው “የሎሬትነት” ማዕረግን አግኝተዋል፤ “የማይሞተው ጠቢብ” የተሰኙት እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ። የአእምሯቸውን ምጥቀት በሥዕል ሥራ ላይ ለዓለም ማሳየት ከመቸላቸውም ባሻገር በተለያዩ ታላላቅ የአለም አገራት ለትምህርት ሄደው ዘመናቸውን በአገራቸው ለመጨረስ የታደሉ ጥበበኛም ነበሩ። የሥራቸው ፍሬዎችም እውቅናና ክብርን ያጎናፀፋቸው የሀገራችን አይረሴ ባለተሰጥኦ ናቸው። “የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ “አፈወርቅ ተክሌ በተማሪነታቸው ዘመን ብቻ ከእስር በላይ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከእነሱም ውስጥ በስነ-ጥበብ መስክ ላበረከቱት አስተዋፅኦ በንጉሱ በክብር የተበረከተላቸው ሽልማት ይገኝበታል።” (ገፅ፡120)

የመጽሐፉ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች

“፮ቱ ፋና ወጊዎች” መፅሐፍ ሊነበብ የሚችልና አዳዲስ የሚባሉ መረጃዎችን የያዘ ስለመሆኑ አይካድም። መፅሐፉ ብዙ ልፋትና ድክመት፤ ጊዜና ሀብትን ወስዶ የተሰራም ስለመሆኑ መገመት ይቻላል። ነገር ግን መፅሐፉ ውስጥ ተመርጠው የተካተቱት ሰዎች ስብጥርና የተምሳሌትነት ደረጃ የቱንም ያህል ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ቢሆን የራሱ ህፀፆችንም እንደያዘ ማስታወሱ ለአንባቢያን ግንዛቤን ከማስጨበጡ ይረዳል።

ተምሳሌት የሚሆኑት ግለሰቦች በተመለከተ በጥቂቱም ቢሆን ያልተሰሙ የመሰሉ ሃሳቦች መካተታቸው፤ የፋና ወጊዎቹ የህይወት መንገድና ዓላማ የተለያዩ (ስብጥር) የታየበት መሆኑ (ማለትም ከተመራማሪዎቸ፣ ከቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች፣ ከነፃነት ተፋላሚዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሚዲያ እና ከኪነጥበብ ሰዎች የተካተቱት መሆኑ) እንዲሁም ቀላልና አንባቢን አዝናንቶ መዝለቅ በሚያስችል መልኩ መፃፉ የመፅሐፉ ጠንካራ ጎኖች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

በአንፃሩ ደግሞ መፅሐፉን ሳነበው “ቢሆን ኖሮ” ብዬ ያሰብኳቸውን ጉድለቶች ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛል። የመጀመሪያው ዋነኛው የመፅሐፉ ድክመት አገራችን ካፈራቻቸው በርካታ ፋና ወጊዎች መካከል አንዱን ብቻ ማቅረቡ ነው። እርግጥ ነው ፀሐፊውን ጨምሮ አንዳንዶች “ጀግና” አገር የለውም፤ እነዚህ ሰዎች ከአገራቸው አልፈው የኛም አለም ሰዎች ሆነዋል። የሚል መከራከሪያ ሊያነሱ ይችላሉ። ዳሩ ግን እነዚህን ተምሳሌቶች ለማግኘት የድረ-ገፆች ድካም ቀናሽነት ፀሐፊው ብዙ መድከምን ሸሽታውታል ያሰኛል።

የፀሐፊው ልፋት በእጅጉ የቀነሱና በተለያዩ ድረ-ገፆች ታትመው የወጡትን ፅሁፎችን መተርጎሙ ቀላል ስለሆነ ይህ መንገድ ተመርጦ ይሆናል። ነገር ግን በተገላቢጦሽ ሆኖ ኢትዮጵያን “አንቱ” የተባሉ ተምሳሌቶችን ለማውጣት የበለጠ ጊዜን፣ ገንዘብንና ምርምርን የሚጠይቁ መሆናቸውን ፀሐፊው ሳይሸሹት እንዳልቀረ እጠራጠራለሁ።

ሌላኛው እንደድክመት የሚነሳው ነገር ጸሐፊው የመረጧቸው ሰዎች እያንዳንዳቸው ራሳቸውን የቻለ አንድ ሙሉ መፅሐፍ መሆን የሚችል ታሪክ የያዙ ከመሆናቸው አንፃር በእጅጉ የታሪክ ጥበትን ጥድፊያ ታይቶበታል። እነዚህን ስድስት ተምሳሌቶች ለመፃፍ መነሳት በራሱ ጥንካሬን የሚጠይቅ ሲሆን በ158 ገፆች ቀንብቦ ለማቅረብ መሞከር ያውም(የፀሐፊውን ማስታወሻ በምዕራፍ አንድ ስር የተዘረዘሩትን የ24 ገፆች ሀተታ ጨምሮ) በጣም ጠባብና ቁንፅልነትን እንዲበዛ አድርጎታል። እዚህ'ጋ ፀሐፊው በምዕራፍ አንድ “የፋና ወጊዎች መረጣ ጅምር መንገድ” በተሰኘ ንዑስ ርዕስ ስር ያሰፈሩት ግለ-ታሪክ በአጭሩ መቅረብ ሲገባው ወይም በመግቢያው ውስጥ መካተት ሲችል ያን ሁሉ መውሰዱ ዋጋዎቹን ባለጉዳዮች ማደብዘዝ ይሆናል።

በዚህ አጋጣሚ በአማካኝ አሥር ገፅ በሚደርስ ፅሁፍ የስድስቱን ሰዎች ታሪክ ለማካተት መሞከር በጣም ድክመት ሲሆን፤ በተለይም “የኛው” እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መካተት ምስጋናን ቢያስገኝም ከሌሎች ባነሱና በአምስት ገፆች ብቻ በአጭር እንዲቀርብ መደረጉ ፀሐፊው መረጃ አልዳሰሱም ወይ? ሊያስብል ይችላል።

    መፅሐፉ በስተመጨረሻ ማለትም በገፅ 128-157 ባሉት ገፆች ውስጥ ፋና ወጊዎቹን ተንተርሶ ወጣቱን በመልዕክት ማጨናነቁ የጨቅጫቃ አባላት ምክር ይመስላል። ይልቁንም ወጣቱ ትውልድ ከተጠቀሱት ተምሳሌቶች እንዲማር በባለታሪኮቹ ታሪክ ውስጥ የሚታዩ ነገሮችን አጉልቶ ማሳየት እንጂ፤ እነርሱን አልፎ ፀሐፊው የራሱን ምክርና ተግሳጽ ማስተላለፍ መሞከራቸው የመፅሐፉን መጨረሻ ገጾች አሰልቺ አድርጎታል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
9602 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us