“ፊልም የቴአትርን ያህል ጥራት የለውም”

Wednesday, 06 August 2014 14:00

አርቲስት ሽመልስ አበራ (ጆሮ)    

በርካቶች አብረውት መስራት የሚመኙትና በትወናውም አንቱ የተሰኘ ጐምቱ ተዋናይ ነው። ከ40 በላይ የሙሉ ጊዜ ቴአትሮችን፤ ከሬዲዮ ድራማም ወደሀብት ጉዞ፣ የማዕበል ዋናተኞችና የቀን ቅኝት የሚታወሱለት ሲሆን፤ በቲቪ ድራማ አሁን ድረስ በበርካቶች ልብ ውስጥ የቀረውን “የህሊና ዕዳ” እና አሁን በመታየት ላይ ያለው “ዳና” ይጠቀሳሉ። በፊልምም ቢሆን ጥቂት ሠርቶ በብዙ የገነነ ተዋናይ ነው።

ከሰራቸው ፊልሞች መካከልም ቀዝቃዛ ወላፈን፣ ሲኦል፣ ቃል ኪዳን፣ ዙምራ፣ ትንቢት፣ ሃኒሙን እና ኮንደሚኒየሙ ጐልቶ ወጥቶባቸዋል። የዛሬው እንግዳችን ተዋናይ ብቻም አይደለም በዝግጅትም እየሰራ ያለ ባለሙያ ነው። የአባቱን የትወና ፈለግ የተከተለው ይህ ሰው፤ አርቲስት ሽመልስ አበራ (ጆሮ) ነው። ከአርቲስቱ ጋር ባልደረባችን አሸናፊ ደምሴ ይህን የመሰለ አዝናኝ ቆይታ አድርጓል።      

 

ሰንደቅ፡- በፋዘር ቤት (ተስፋዬ አበበ) ትወናን ከመጀመርህ በፊት በድምፃዊነት ነበር የተነሳኸው፤ በኋላ ቀይረህ ተዋናይ ሆንክ። ተዋናይ ባትሆንስ ኖሮ? ከሚለው ጥያቄ እንጀምር።

ሽመልስ፡- ሌላ ምንም ልሆን አልችልም። ተዋናይ ባልሆንም መልሼ ተዋናይ የምሆን ነው የሚመስለኝ (ሣቅ)

ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት በአገራችን በየዕለቱ በርካታ ፊልሞች ይመረታሉ፤ አንተ ግን እንደ አጀማመርህ ሳይሆን በጣት የሚቆጠሩ ሥራዎችን ነው የሠራኸው። ለምንድነው?

ሽመልስ፡- እውነቱን ለመናገር እኔ ፊልም ስሰራ እመርጣለሁ። የሰራኋቸው ፊልሞችም ተመስገን በሚያስብል ደረጃ ስኬታማ ናቸው። ስለዚህ ብዙ ያልሰራሁት በራሴ ምርጫ ነው ማለት ነው። እጅግ በጣም በርካታ ፊልሞችን አልሰራም ብዬ መልሻለሁ። አሁንም በእጄ ላይ እያየኋቸው ያሉ አራት የፊልም ጽሁፎች አሉ። ሁለቱን ተስማምቼ ወደስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ስሆን፤ ቀሪ ሁለቱን ግን አንደኛው ደራሲው ያነሳው ኀሳብ ለእኔ ትልቅ ስላልመሰለኝ ትቼዋለሁ። ሁለተኛው ደግሞ በጣም የወረደ ስለሆነ ለሳንቲም ብዬ አልሰራም በሚል ትቼዋለሁ። እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን እኔ የሳንቲም ችግር የለብኝም። ስለዚህ ጥቂት ፊልሞችን የሰራሁት በምርጫዬ ነው ለማለት ነው።

ሰንደቅ፡- የሰራሃቸው ፊልሞች በአንተ ዕይታ እጅግ የተዋጣላቸው ነበሩ እያልከኝ ነው?

ሽመልስ፡- እኔ የሰራሁባቸውንም ጨምሮ ኢንደስትሪው እየተስፋፋ ቢመጣም ፊልም በጥራት እየተሰሩ ነው ብዬ አላምንም። ፊልም የቴአትርን ያህል ጥራት የለውም። ያለህ ዕድል ምንድነው መሰለህ፤ አንድ እንዳትጠፋ ትሰራበታለህ። ሁለተኛ ደግሞ ኢንደስትሪውን (ዘርፉን) እየለመድከውና እያወከው መሄድ ስለሚያስፈልግ ከደከሙት ትንሽ ሻል ያሉትን ሰርቻለሁ እንጂ እኔ የሰረኋቸው ሁሉ ፍፁም ናቸው እያልኩህ አይደለም። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ሁለት ቆንጆ ፊልሞች ናቸው ብዬ አፌን ሞልቼ የምናገርባቸውን “ስክሪብቶች” አግኝቻለሁ፤ እንደዚህ የሚመረጡ ሰራዎችን ሳገኝ እሰራለሁ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- አንተን ጨምሮ ለበርካታ ታላላቅ ተዋንያን ቴአትር ተቀዳሚ ምርጫ ነው። ከፊልምና ከቲቪ ድራማ የቱን ትመርጣለህ ብልህስ ምርጫህ የቱ ይሆናል?

ሽመልስ፡-እውነት ነው ቴአትር ከምንም ጋር አይወዳደርም። ከፊልምና ከቲቪ ድራማ ካልከኝ ግን ሁለቱን በጥቂቱም ቢሆን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። ነገር ግን ገንዘብ ባይኖረውም የቲቪ ድራማ ጥሩ ነው። የተሻለ ተመልካች ታገኛለህ፣ በአንዴ ብዙ ቦታ ላይ ትደርሳለህ፤ ትተዋወቅበታለህ፤ ይህ የቲቪ ድራማ ጥቅም ነው። ፊልም ግን አንዴ ትሰራለህ በከተማው ባሉ ጥቂት ሲኒማ ቤቶች ያውም ታግለህ ትገባለህ፤ አሳይተህ ትወጣለህ። እርግጥ ፊልም ክፍያው ጥሩ ነው። ቢሆንም ግን ድራማው ይሻላል።

ሰንደቅ፡- በአንድ ወቅት “ፍቅር የተራበ”፣ “ለእረፍት የመጣ ፍቅር” እና “የሚስት ያለህ” ቴአትሮች ላይ የሰራሃቸው ገፀ-ባህሪያት ፈታኝ እንደሆኑ ተናግረሃል። ከምን ተነስተህ ነው እንደዛ ያልከው?

ሽመልስ፡- “ፍቅር የተራበ” ትንሽ ጊዜው ቢርቅም አሁንም ድረስ ከውስጤ የሚወጣ ድራማ አይደለም። “ፍቅር የተራበ” ላይ ያለው “ካራክተር” የቤተሰብ፣ የፍቅረኛ እና የማኅበረሰብ ፍቅርን ያጣና የተጐዳ ገፀ-ባህሪይ ነው። ማፍቀር እየፈለገ ፍቅርን የተነፈገ አይነት ሰው ነው። ይህ “ካራክተር” በጣም የሚያሳዝነኝ “ካራክተር” ነው። ይህ ሰው ስሜቱን አንዴ በደስታ አንዴ በሐዘን የሚገልፅ ነው። ይህንን ተለዋዋጭ ስሜት ለተመልካቹ ማሳየት ትንሽ ከባድ ነበር።

“ለእረፍት የመጣ ፍቅር” ቴአትርን በተመለከተ፤ ብዙ ጊዜ በመድረክ ላይ ማኅበረሰቡ ዘገምተኛ የሚላቸውን ገፀ-ባህሪያት ተጫውተህ ማሳመን ትንሽ ከባድ ነበር። በዚህ ላይ ባህሪው የጅልነት ነገር ስለነበረው ብዙ ነገሩ ከእኔ የራቀ ነበር። ድምፁ የእኔ አይደለም፤ አካሄዱም ሆነ ድርጊቱ የእኔ አልነበረም ወይም ለእኔ አዲስ የሚባል ገፀ-ባህሪይ ነበር ማለት እችላለሁ።

“የሚስት ያለህ” ደግሞ ለእኔ ፈታኝ የነበረው እረፍት አልባ መሆኑ ነው። በእኛ ሀገር ተውኔቶች ሲፃፉ መድረክን የረገጠ ተዋናይ ትንሽ የሚያርፍበት መውጫ ታሪክ ይሰራለታል። “የሚስት ያለህ” ቴአትር ግን ከመነሻው እስከ ፍፃሜው ምንም አይነት እረፍት የለውም። እንደውም አዘጋጇ ትንሽ ውሃ ለመጠጫና አየር ለመውሰጃ እንዲሆነኝ ወደመኝታ ቤት ገብቼ ፎጣ ነገር እንዳመጣ አድርጋኛለች። የሚገርመው ግን ይህ ገፀ-ባህሪይ በጣም የሚያብድ ሚስቱን ገድሎ አልገደልኩም በሚል ተመልካቹን የማሳመን ደረጃ የደረሰ ነው። እናም ለእኔ እነዚህ ቴአትሮች ትንሽ ፈታኝ ነበሩ። ለእኔ እስካሁን ታሪኬ የሰራኋቸው ቴአትሮች በቂና ችሎታዬን ያሳዩ ናቸው ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ከብዙዎች ጋር እንደምስማማው፤ በመጀመሪያዎቹ ስራዎችህ ስኬታማ ስለሆንክ ዕድለኛ ነህ። በቲቪ የመጀመሪያ ስራህ “የህሊና ዕዳ” ተወዶልሃል። ከሬዲዮ የማዕበል ዋናተኞችን ብዙዎች ባይረሱትም የመጀመሪያ ስራህ “ወደ ሀብት ጉዞ” ነው፤ ይህም ድራማ ተወዶልሃል። ከፊልምም ሲኒማ እንዲህ ከመስፋፋቱ በፊት “ቀዝቃዛ ወላፈን” የመጀመሪያ ስራህ ሆኖ ተወዷል፤ ምንድነው ምስጢሩ?

ሽመልስ፡- በመጀመሪያ ዕድለኛ መሆኔን ከአንተም በመስማቴ በጣም አመሰግናለሁ። አዎ እድለኛ ነኝ። አሁን ለምሳሌ “የህሊና ዕዳ” 16 ክፍል በተከታታይ የታየ የቲቪ ድራማ ነው። በአሁኑ ሰዓት “ሰው ለሰው”፣ “ገመና” እና “ዳና” ድራማዎች ረጃጅም ጊዜ የታዩ ድራማዎች ናቸው። የሚገርመው ግን 16 ክፍሎች የታየው “የህሊና ዕዳ” ድራማ አሁንም ድረስ ከህዝብ ልብ አልወጣም፤ የሚገርምህ ነገር ሽመልስ የሚለውን ስም መቀየር ስላቃተኝ እንጂ ብዙዎች “ብሩክ” በሚባለው የገፀ-ባህሪይ ስሜ ነው የሚያውቁኝ። ይሄን ያህል ስኬታማ ስራ ነበር። ስራው ይበልጥ የተወደደው ደግሞ ከደርግ ዘመን የፕሮፓጋንዳ ድራማዎች ወጣ ባለ መልኩ 1985 ዓ.ም አካባቢ ነው፤ አሪፍ የፍቅር ታሪክ ነበር የሰራነው። ታሪኩ በረጅሙ መቀጠል የሚችል ነበር፤ ነገር ግን አንድ ግለሰብ ከሬዲዮ መጥቶ የቲቪ ኃላፊ ሲሆን በእርሱ ጫና ነው ስራው ቶሎ እንዲያልቅ የተደረገው። “የህሊና ዕዳ” በየሳምንቱ የሚፃፍ ድራማ ሳይሆን እንደ መጽሐፍ ተጽፎ ያለቀ ታሪክ ነበር። በወቅቱ ብዙ ተመልካቾች አይተውት የተወደደ ስራ ነበር።

ወደፊልም ስንመጣ “ቀዝቃዛ ወላፈን” ነው፤ በነገራችን ላይ ይህ ፊልም ቀረፃው ወደ ሦስት ዓመት ፈጅቶ ነበር። ሲቋረጥ ሲቀጥል፤ ቴዲ ስቱዲዮም የምር ለፍቶበት የተሰራ አድካሚ ፊልም ነበር። አንድ ጊዜ እንደውም በቃ ይሄ ፊልም ቢቀርስ ሁሉ እስከማለት ደርሰን ነበር። ግን በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ ውስጥ ሜጋ አንፊ ቴአትር እና ሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ውስጥ ፊልሙን ለማየት የነበረው ሰልፍ ጉድ የሚያሰኝ ነበር። እንደውም ትዝ ይለኛል፤ እዚህ ብሔራዊ አንድ ቴአትር ሰርቼ ስወጣ የሜጋው ሰልፍ ፖስታ ቤት ደርሶ ነበር፤ ምንድነው ሰልፉ? ብዬ ስጠይቅ “የቀዝቃዛ ወላፈን” ፊልም ሰልፍ ነው ተባልኩ። በጣም የሚገርምህ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አስቤውም አላውቅም። በሀገር ፍቅርም ቢሆን በቀን ሁለቴ ሦስቴ እስከመታየት የደረሰ ፊልም ነበር።

በሬድዮ ድራማ ዘርፍ “ከማዕበል ዋናተኞች” በፊት “ወደ ሀብት ጉዞ”ን ነበር የሰራሁት፤ ይሄም ትልቁ የኃይሉ ፀጋዬ ስራ ይመስለኛል። ህዝቡ ውስጥ በሬዲዮ ድራማ የገባሁት ከዚያ ስራ ጀምሮ ነው። ከዚያ በኋላ ነው “የማዕበል ዋናተኞች” እና “የቀን ቅኝት” የመጡት። ከመድረክ ስራዬ ደግሞ ራስ ቴአትር “ዲዳይት ወይዘሮ”ን ስጫወት የ19 ዓመት ወጣት ሆኜ የ62 ዓመት አዛውንት በመሆን ተጫውቻለሁ። ይህ ስራ ብዙ የለፋሁበት ነገር ግን ያልታየልን ነው ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ስለባልደረባህ አዜብ ወርቁ እናንሳ፤ በቲቪ “ዳና”ን፤ በቴአትር “የሚስት ያለህን” በፊልም ደግሞ “ኮንደሚኒየሙን” ስትጽፍ አብረሃት ሰርተሃል። ጓደኝነታችሁ እንዴት ይገለፃል?

ሽመልስ፡- አዜብ ለእኔ በኪነጥበቡ ዙሪያ የሴት ጀግና ከምላቸው ባለሙያዎች ቀዳሚዋ ናት። ከአቅሟ በላይ እየሰራች ያለችና በጣም ቅን ስብዕና ያላት ሰው ናት። ስለአዜብ ብዙ ብናገር አንባቢዎችህ የተጋነነ ሊመስላቸው ይችላል። ግን አንድ ነገር ስለ አዜብ ማለት እችላለሁ፤ እርሷ መልካምና የኪነት ፀጋዋን በትክክል እንድትጠቀም የተፈጠረች ሴት ናት። በአጠቃላይ “አርቱ” የሚፈልገውን በሙሉ ያሟላች ሴት ናት። እኔ ምንም ነገር ከአዜብ ጋር ብሰራ በጣም ደስተኛ ነኝ። በነገራችን ላይ “ኮንደሚኒየሙ” ፊልም በስክሪፕት ደረጃ በጣም አሪፍ ስራ ነው። በደንብ ተሰርቷል ብዬ ግን አላምንም። የዝግጅትና የፕሮዳክሽን ድክመት ይኖረዋል፤ በጽሁፉ ግን አዜብ ጽፋ ስታመጣው በጣም አሪፍ ስራ ነው።

ሰንደቅ፡- እዚህጋ “ኮንደሚኒየሙ” በደንብ አልተሰራም ስትል፤ በቲቪ እየተላለፈ ያለውን “ዳና” ድራማንም ለተመለከተ በአንድ ወቅት፤ ብዙ መሠራት እየተቻለ ያልተሰራ ድራማ ነው ብለሃል። ምን ለማለት እንደፈለክ እስቲ ግልጽ አድርገው?

ሽመልስ፡- ምን ለማለት ፈልጌ መሰለህ? የፕሮዲዩሰሩ ይሁን የፀሐፊዋ (የአዜብ) ግልፅ አልሆነልኝም፤ ግን ለሁለቱም ተናግሬያለሁ። ስለ “ዳና” ድራማ ሰምተህ ከሆነ “ማድሪድ” ነው የሚባለው (የኮከብ ተዋንያን ስብስብ በዝቶበታል እንደማለት) ነገር ግን ብዙ ስራ አልተሰራበትም። ይህም በመሆኑ በድራማው ላይ ለሁለቱም ተናግሬ አቋርጫለሁ። ለሰዎቹ ጥላቻ ኖሮኝ ሳይሆን ስራው የሚገባውን ያህል ባለመሠራቱ ነው ያቋረጥኩት። ቅያሜ የለኝም ለጥላሁንም ለአዜብም ነግሬያቸዋለሁ። አዜብ ልትታገዝ ይገባታል። የቲቪ ተከታታይ ድራማ ለብቻ መፃፍ ቀላል አይደለም። በጣም አድካሚ ነው። አዜብ በተቻላት ሁሉ እዚህ ደረጃ ማድረሷን አደንቃለሁ። ግን “ዳና” ከዚህ በላይ መሠራት አለበት ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ይመስለኛል የታሰበውን ያህል ህዝብ ልብ ውሰጥ ያልገባው።

ሰንደቅ፡- ከዚህ ቀደም ከብዙ ተዋንያን ጋር ቃለ-ምልልስ ሳደርግ ብዙዎቹ አብረውህ መስራትን እንደሚመኙ ነግረውኛል። አንተስ ከማን ጋር ብሰራ ብለህ ትመኛለህ?

ሽመልስ፡- እኔም ከብዙዎች ጋር መስራትን እመኛለሁ። ለምሳሌ ከፍቃዱ ተ/ማርያም ጋር፣ ከኤልሳቤጥ መላኩ ጋር አንድ ሁለቴ ተገናኝተናል። ከጌትነት እንየው ጋር “አንቲገን” ላይ ትንሽ ተገናኝተናል፤ ግን አልረካሁም። በነገራችን ላይ እኔ ከክርስቶስ በታች የማከብራቸው ፍቃዱና ጌትነት ናቸው። ከሙያቸውም ውጪ በግል ስብዕናቸውም ጭምር ይማርኩኛል። በጣም አክብሮት አለኝ። ከተፈሪ አለሙ ጋር ብሰራም በጣም ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- በ“ቅጥልጥል ኮከቦች” ቴአትር ላይ የጋዜጠኛ ገፀ-ባህሪይ ትጫወታለህ። ገፀ-ባህሪው በአንተ ዕይታ ምን አይነት ጋዜጠኛ ነው?

ሽመልስ፡- ጋዜጠኛ እኛ ሀገር በብዙ ይከፈላል። ለሆዳቸው የሚያድሩ ጋዜጠኞች አሉ። ሰውን በመሳደብና በማዋረድ ገንዘብ የሚሰበስቡ ጋዜጠኞች አሉ። በአንፃሩ ደግሞ ስለ እውነት ብለው የሚገረፉና በእስር ቤትም የተጣሉ ጋዜጠኞች አሉ። እዚህም ሆነው እውነትን በማውጣት በህይወታቸው ያን ያህል የሚባልን ኑሮ የሚገፉ ጋዜጠኞች አሉ። የማኅበረሰቡን ህይወት የሚቀይሩ ጋዜጠኞችም አሉ። በ“ቅጥልጥል ኮከቦች” ውስጥ ያለው ጋዜጠኛ በዚህም አገር ያሉና በስም የማልጠራቸው፤ ነገር ግን የማደንቃቸውን ጋዜጠኞች የሚወክል ገፀ-ባህሪይ ይመስለኛል። ፍቅርን ይፈልጋል፤ ፍቅር ግን ለእርሱ ከእውነት በላይ አይደለም፤ ቤተሰብ ይፈልጋል ዳሩ ግን ቤተሰብ ለእርሱ ከእውነት በላይ አይደለም። እውነት ከሁሉም በላይ የሆነበት ጋዜጠኛ ነው። አገር ውስጥ ያሉትን ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የሚያጋልጡ ብዙ ጋዜጠኞች አሉ፤ የእነሱ ተምሳሌት ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ቴአትሩ ተመልካችን እስኪያስጨንቅ የምትደክምበት ከመሆኑ የተነሳ ምን ምላሽ አገኘህ? የተመልካቹ አስተያየት እንዳለ ሆኖ በተለይ ከባለቤትህ ከሪታ ወጋየሁ ምን አስተያየት አገኘህ?

ሽመልስ፡- አንድ ነገር ልንገርህ፤ ይሄን “ቴአትር” አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም መጥቶ አየውና ካለቀ በኋላ ከመድረክ ጀርባ ተገናኘን። “ተንበርክኬ ልሳምህ” አለኝ። ፍቃዱ እኔን ተንበርክኮ መሳም አይገባውም። እኔ ተንበርክኬ የእርሱን እግር ልስም እንጂ፤ ይሄ ግን ለእኔ ምን ይነግረኛል መሰለህ? የማያልቅብኝ የምግብ ጐተራ እየሰራሁ እንደሆነ ይሰማኛል። በርካታ ተመልካቾችም በድካሜ ቢጨነቁም ስራውን ወደውታል፤ ሌላው ይቅርና ከዚህ ቀደም ከተጣሉኝ ሰዎች ጋር ሁሉ አስታርቆኛል። በዚህ አጋጣሚ የባለቤቴን አስተያየት ስትጠይቀኝ ገና ዛሬ ነው ልታየው የመጣችው (አንባቢያን ቃለ-ምልልሱ የተካሄደው ባሳለፍነው እሁድ ሐምሌ 27 ቀን 2006 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ግቢ ውስጥ ነው) ሪታ ብዙ ስራዎቼን በማገዝ፤ በድካሜ ሁሉ ከጐኔ በመሆን፤ የጥቃቴ መላሽ ሚስቴም እናቴም የምላት ሴት ናት። እንግዲህ ዛሬ ብዙ ሰዎች “ቅጥልጥል ኮከቦችን” አየሽው? ሲሏት ነበርና በጉጉት ነው ለማየት የመጣችው፤ ዛሬ እርሷም ተመልካች መሀል በመኖሯ ተጨማሪ ድንጋጤ ነው ለእኔ። ምክንያቱም ብዙ ሰዎች አጉልተው ስለቴአትሩ ስላወሯት ባሰበችው ደረጃ ለመስራት ለእኔ ፈተና ነው።

ሰንደቅ፡- በትወና ብቃትህ ብዙዎች እናውቅሃለን። በዝግጅትና በድርሰቱ ግን አልወጣህም፤ ለምን?

ሽመልስ፡- በነገራችን ላይ በዝግጅት ከዚህ ቀደም “የስልጣን ማደጐ” እና “ለእረፍት የመጣ ፍቅር” በድጋሚ ሲመጣ እኔ ነኝ ያዘጋጀሁት። አሁን በቅርቡ ደግሞ የውድነህ ክፍሌ ድርሰት የሆነውን “ደጋግ ሰይጣኖች” መሪ ተዋናይም አዘጋጅም ሆኜ ለተመልካች ላደርስ ነው። በተጨማሪም “የጠለቀች ጀንበር” የተሰኘውን ቀደምት ቴአትር በድጋሚ በዝግጅትም በትወናም እየሰራሁት እገኛለሁ። በድርሰት ግን ፀጋው አልተሰጠኝም ብዬ አስባለሁ። ነገ እግዚአብሔር ካለ ከንግግር በላይ እንድጽፍ ሊያደርግ ይችላል። ግን ሁለት ሦስት አጫጭር የቲቪ ድራማዎችን ጽፌ አሳይቻለሁ። “ሰኔዎቹ” የሚል የሙስናና የበጀት መዝጊያን የሚያሳይ ድራማ ሰርቻለሁ። ሌላው ደግሞ “ቢዚ ነን” የሚል ድራማ አለኝ። ቢሮ ተቀምጠው በመዋላቸው ብቻ በአግባቡ አገልግሎት የማይሰጡ ሰዎችን በተመለከተ የፃፍኳት ድርሰት አለች።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

ሽመልስ፡- እኔም በጣም ነው የማመሰግነው። ጊዜ ሳይመቻችልን አንድ ሁለቴ ቀጠሮዎችን አፈራርሰናል። ለዛ በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ። በተረፈ ግን ብዙዎች ሊያጣጥሉኝ ሲፈልጉ የናንተን ጋዜጣ ጨምሮ ጥቂቶች ማለትም ሬዲዮ ፋና፣ ቁምነገር መጽሔትና አርሂቡ መጽሔት ስለእኔ ሚዛናዊ ዘገባ በማውጣት ሰርታችኋልና በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16250 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us