“የአዲሱ ትውልድ መምህራን ነን!”

Wednesday, 13 August 2014 13:29

ይህ ተወዳጅ አርቲስት ከ20 በላይ የሙሉ ጊዜ ቴአትሮችን ተጫውቷል። የቅርቦቹን ለመጥቀስ ያህልም ጣይቱ፣ ሕንደኬ፣ የሚስት ያለህ፣ ቶፓዝ እና በበርካቶች ዘንድ አዲስ አሰራርን እንደተከተለ በተነገረለት “ከሰላምታ ጋር” በተሰኙ ቴአትሮቹ የትወና ብቃቱን አሳይቷል። ብዙ ፊልሞችን ከሰሩ ባለሙያዎች በላይ ስለፊልም የተሻለ እውቀት ያለው አርቲስቱ በጣት የሚቆጠሩ፤ ነገር ግን ስኬታማ የሆነባቸውን እንደ፣ “የእግር እጣ”፣ “የመጨረሻዋ ቀሚስ” እና “ኒሻን” የመሣሠሉት ፊልሞች ተወዳጅ ስራዎቹ ናቸው። ከአርቲስት ፈለቀ የማርውሃ አበበ ጋር ገርጂ በሚገኘው በመፅሐፍና በስዕል ስብስቦች በተሞላው ቤቱ ውስጥ ተገናኝተን አውግተናል።

ሰንደቅ፡- በቴአትር፣ በፊልምና በሬዲዮ ድራማዎች ብዙዎች ያውቁሃል ሥራዎችህን ለአንባቢው በማስተዋወቅ ብንጀምርስ ደስ ይለኛል?

ፈለቀ፡- ከ20 ቴአትሮች በላይ ሰርቻለሁ። ከህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት በስተቀር አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ ቴአትር ቤቶች በሙሉ ሰርቻለሁ። ይህ ማለት የኤድናሞልና የአለም ሲኒማ መድረኮችን ጨምሮ ማለቴ ነው። የቲቪ ድራማዎች በተለይ በልጅነት በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያ ሬዲዮና ሸገር አልፎ አልፎም በፅሁፍ የታገዘ በርካታ ትረካዎችን ሰርቻለሁ። ፊልምን በተመለከተ ጥቂት ናቸው። ድሮ “አጋቹ” የተሰኘ ፊልም ሠርቼ ነበር፤ ከዚያን በኋላ በዲጂታሉ ዘመን ሶስት ናቸው። “የእግር ዕጣ”፣ “የመጨረሻ ቀሚስ” ና “ኒሻን” የተሰኙ ተወዳጅ ፊልሞች ተሰርተዋል።

ሰንደቅ፡- በአገሪቱ ውስጥ “የአርት” ኮሌጆች ገብተህ አልተማርክም፤ ነገር ግን ራስህን አንቱ የሚባል ደረጃ አምጥተሃል። ራስህን እንዴት አስተማርከው?

ፈለቀ፡- መልሱ አጭር ነው፤ በማንበብ። እውነቱን ለመናገር አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ዩኒቨርስቲ ብገባ ኖሮ ይሄን ያህል ላነብ እችል ነበር? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። እናም አልደረስኩም ብለህ ባሰብክ ቁጥር ማንበብህ ይጨምራል። አሁን ደግሞ ቅርብ ጊዜ አካባቢ ያነበብኳቸውን ፅሁፎች ለሌላ ሰው ማስነበብ ስጀምር የበለጠ አቅም ለመፍጠር አነባለሁ። ልክ አንድ መኪና ነዳጅ እንደሚያስፈልገው ሁሉ በጥበብ ስራ ውስጥ ስትሆን በሁሉም ዘርፍ ማንበብ ያስፈልጋል። የህክምና ጠበብቶች እንደሚሉት ስንፈጠር ቀለምን የመለየት፤ ምልክትን የመለየት ተሰጥኦ አብሮን ይኖራል እንጂ ማንበብ በተሰጥኦ የሚገኝ አይደለም ይላሉ። ስለዚህ ማንበብን ልምድህ ስታደርግ የኑሮህ አንድ አካል ይሆናል። ያም ሆኖ አሁን ቢሆን በንባቡ ብዙ ይቀረኛል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሰንደቅ፡- በርካታ የአጫጭር ልቦለዶችና ድራማዎች ተርጉመሃል፤ ሃሳቦቹን ስትመርጥና ለታዳሚው ለማድረስ ስትነሳ መመዘኛህ ምንድነው?

ፈለቀ፡- ይሄ በጣም አሪፍ ጥያቄ ነው። ለምንድነው አሁን አንተ እንዳልከው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አጫጭር ልቦለዶች ይቀርባሉ። ጋዜጣው ከ10 ዓመት በላይ ምርጥ ምርጥ ስራዎች ሲያስነብብ የቆየ ጋዜጣ ከመሆኑ አንፃር ልትደግም ሁሉ ትችላለህ። አንድ አጭር ልቦለድ ፅፈህ ስትሄድ፤ “ኦ! ይሄኮ ከአምስት ዓመት በፊት ተነቧል” ሊልህ ይችላል አዘጋጁ። በመሆኑም አዲስ ነገር ይዘህ ለመምጣት መጣር እንዳለ ሆኖ አንድ አጭር ልቦለድ ለማውጣት 50 አጫጭር ልቦለዶችን ማንበብ ይጠበቅብሃል። ከነዚያ ውስጥ በጣም ደስ ያለችህንና ይህቺ ነገር እኔ ብቻ አንብቤያት ከምትቀር በሚል መርጠህ ነው ወደህዝብ የምትመጣው። እኔን ደስ ያሰኘኝን ለማድረስ ነው የምጽፈው ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ከ20 በላይ ቴአትሮችን ስትጫወት የማትረሳ ገፀባህሪይ የቱ ነው? አሁን ድረስ የምታስታውሰውስ?

ፈለቀ፡- ያው ከጣቶቸህ መካከል እንደማማረጥ ነው። በተለይ እንደኔ ሲሆን ምክንያቱም መርጬ ስለምጫወት ሳልወደው እንድተውን የሚያስገድደኝ ነገር ስለሌለ፤ በቀላል ቋንቋ ተቀጣሪ ስላሆንኩ፤ ቴአትር ተጋብዤ ነው የምጫወተው። ስለዚህ ካልወደድኩት አልወደድኩትም የማለት መብት አለኝ ማለት ነው። ብዙውን ወድጃቸው ነው የምጫወታቸው። ደግሞም እድለኛ ነኝ፤ አዘጋጆቹ ሲጠሩኝ ትንሽ ለየት ያለ ነገር ሲኖር ነው። ግን እንዳልከው ደግሞ መምረጥ ካለብኝ ሶስት ቴአትሮችን እንጥራ፤ የመጀመሪያ ቴአትር “ሮሚዮና ዡሌየት” ነው። ባሴ ሀብቴ ተርጉሞት ስዩም ተፈራ ያዘጋጀው ሥራ ነበር። እዛ ላይ የሮሚዮ ጓደኛ ሜርኩቺዬ የሚባለውን ገጸ ባህሪይ ነበር የተጫወትኩት። በጣም ቀልደኛ “ካራክተር” ነበር። የማይረሳኝ ነገሩ ምንድነው፤ ሲሞት ጓደኞቹ እንዳያዝኑ ምንም አልሆንኩም እያለና እያሳሳቃቸው ነው የሚሞተው። እናም ተመልካቹም እየሳቀ ነበር የሚያለቅሰው። በዚህ አልረሳውም። ሁለተኛው ቴአትር ተስፋዬ ገ/ማርያም ያዘጋጀው የበላይነህ አቡኔ “ተውኔቱ” የተሰኘ ትርጉም ስራ ነበር። ይህ ቴአትር በቴአትር ውስጥ ያለ ቴአትር ነው። እዛ ላይ ጋሽ ጌች የሚባሉ ሽማግሌ ገፀ-ባህሪይ አሉ። በጣም አውቃለሁ የሚሉ ነገር ግን ቴዎድሮስ ሲገልፃቸው “በጣም ያረፍዳሉ” የሚባሉ አይነት ናቸው (ሳቅ). . . ትንሽ ዘብረቅ ያሉ አይነት ሰው ስለሆኑ ወጣ ብለህ ነው የምትጫወተው። አስበው መነፅራቸው ዓይናቸው ላይ ሆኖ መነፅር የሚፈልጉ አይነት ሰው ናቸው። ሌላኛው ቴአትር የጌትነት እንየው እቴጌ ጣይቱ ላይ ያለው ተራኪ ይመስለኛል። የ3ሺህ ዓመት ታሪክ የሚናገር ነው። ተራኪው ተውኔቱን የተሸከመው በመሆኑ አሁን ድረስ አልረሳውም።

ሰንደቅ፡- ብዙ በማንበብ ሂደት የኢትዮጵያ ታሪክ የማወቅ አጋጣሚው ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ተራኪው ለኔ የሚገባኝና የምታወቀውን ታሪክ እንደመናገር አይነት ስሜት ይሰማሃል?

ፈለቀ፡- እንደሱ አይነት ነገር አይጠፋም። ወደድንም ጠላንም የአዲሱ ትውልድ መምህራን ነን። ይህቺ ሀገር ደግሞ በ3ሺህ ዓመታት ታሪኳ ያለፈችው ብዙ ነገር አለ። ሁላችንም በገባን መጠን ለትውልድ ማቀበል አለብን። ጌትነት ፅፎ የመጣው እውነታውን ነው። ያ እውነት እኔም ውስጥ አለ፤ አንተም ውስጥ አለ። ስለዚህ ተራኪውን ሆኖ መቆም እንደዚያ ሊያሰኝ ይችላል። ጌትነት፤ ከማወቀው በላይ ነገርም ፅፎ ቢመጣ ያ ነገር የአገሬ ታሪክ ነው።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ወደፊልም እንመለስ፤ ስለፊልም የምታውቀውን ነገር በጋዜጦች ላይ ፅፈህ አካፍለሃል። አሁን ደግሞ ካለፈው አስር አመታት ወዲህ ፊልሞች እየበዙ ነው። እንደባለሙያ ኢትዮጵያን ፊልም አካሄድ እንዴት ትመለከተዋለህ?

ፈለቀ፡- ፊልም ላይ ከኔ የበለጠ የፃፉ ወንድሞች አሉ። ማስረሻ ማሞ፤ ፈቃዱ ልመንህ (የአቡጀዲ ግርግር) እና ብርሃኑ ሽብሩን የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። እኔ ጋዜጣ ላይ ብዙ ፅፌያለሁ ብዬ አላስብም። ለልጄ አንደኛ ዓመት የልደት በዓል “ፊልሙ” የተሰኘ መፅሐፍ አሳትሜ ነበር። ስለሆሊውድ፤ ቦሊውድና ኢትዮውድ የሚያትት መፅሐፍ ነው። አልፎ- አልፎ እጽፋለሁ። አሁን ለመጨረሻ ጊዜም አድማስ ላይ “የፊልማችን አገራዊ ፋይዳ” በሚል ፅፌ ነበር።

አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ፊልም ከገቢ ማግኘቱ ባሻገር ትልቅ ተፅዕኖ (Impact) አለው። የሙያው ጠበብቶች ከስነ ልቦና ሁሉ ጋር ያገናኙታል። “ፊልምን የማያዩ ሰዎች፤ ፊልምን ከሚመለከቱ ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ የመሞት እድላቸው በአራት እጥፍ የተፋጠነ ነው” የሚል ጥናት ሰሞኑን አንብቤያለሁ። እኔ እንግዲህ ፊልምን የማየው አንድ የተሳሳተ መፈክር ፅፌ ግድግዳ ላይ እንደማይለጠፈው ሁሉ፤ አንድን ትክክል ያልሆነ ሃሳብ “ስክሪን” ላይ አትለጥፍም። በነገራችን ላይ እንደቡናና ጫት ሁሉ ፊልምም “ያነቃቃል” ይባላል። ፊልሙ በመጥፎ ከሆነ የምትነቃቃው በመጥፎ ይሆናል፤ በጥሩ ከሆነ ደግሞ እንዲሁ ጥሩ ይሆናል ማለት ነው። አንድ ሰው ምን ብሎ ፃፈ መሰላህ፤ ፊልም ማለት ህፃን ልጅን የመመገብ ያህል ነው ልትፈውሰው ወይም ልትመርዘው ሁሉ ትችላለህ። ይህ ማለት ግን ተመልካቹ ምንም አያቅም ወይም አያመዛዝንም ማለት አይደለም።

ሰንደቅ፡- የአገራችን ፊልም ሰሪዎች ይህንን ተገንዝበው እየሰሩ ነው ብለህ ታስባለህ?

ፈለቀ፡- በደምሳው ዳኝነት መስጠት ከባድ ነው። “Every generalization is wrong even this one” የሚባል ነገር አለ። አንደኛ አሁን ፊልም የሚሰሩት ሰዎች እነማናቸው? ከላይ በትምህርትና ስልጠና የታገዙ ጥቂቶች ባለሙያዎች ነበሩ። ከነርሱም መካከል እንደብርሃኑ ሽብሩ አይነት ሰዎች ጥቂቶች ናቸው እውቀታቸውን ያካፈሉት። በዩኒቨርስቲ ደረጃ እንኳን በቅርብ ነው ሊጀመር ነው የተባለው። የቴአትሩን እውቀት ይዘን ነው ፊልም ለመስራት የገባነው። አሁን ፊልምን ከቴአትር የሚለየው ደግሞ ገንዘብ ይወጣበታል። ስለዚህ ገንዘቡን ያወጣው ሰው ምንም ስራ ተሰርቶ ገንዘቡ ትርፋማ እንዲሆን ይፈልጋል። በዚህ ላይ ልንደራደር እንችልም። ግን ከሳንሱር መልስ ይህ ፊልም ሲወጣ ለህብረተሰቡ የሚሰጠው ፋይዳ ምንድነው? ብለው የሚያዩ ወገኖች መቋቋም አለባቸው። አሁን ባለው ደረጃ ፊልሞች የሚገመገሙት የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የብሔር ግጭት እንዳይነሳ ብቻ ይሆናል። ግን ከዚያም ባሻገር ሄዶ ስነ ልቦናዊ ጉዳዮችም ቢጤኑ መልካም ይመስለኛል። በተረፈ ግን ፊልም የሚሰሩት ልጆች ያለምንም ስልጠና በራሳችሁ ጥረት እንደዚህ ብዙ ፊልም በመሰራታቸው አደንቃቸዋለሁ። ግን ደግሞ በመንግሥትም በኩል ለዘርፉ ትኩረት ቢሰጠው ጥሩ ገቢ ማግኛ ይመስለኛል። እንደውም ፕሮዲዮሰሮች በአደራሽ እጦት እየተሰቃዩ እንዲህ መስራታቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል ባይ ነኝ።

ሰንደቅ፡- ከፊልም ጋር በተያያዘ ማንሳት ያለብኝ ሌላው ጥያቄ፣ በፊልም ጉዳይ ወደውጪ ሀገሮች ሄደሃል። ለምን ነበር? ምንስ ተምረህ መጣህ?

ፈለቀ፡- የመጀመሪያው ጉዞዬ ብርኪናፋሶ ዋጋዱጉ ነበር፤ “የኢትዮጵያ ፊልም ኢኒሼቲቭ” ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር አምባሳደር መሀመድ ድሪር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በነበሩ ወቅት ነው። ስድስት ወጣቶች ዋጋዱጉ ሄደን፤ የፊልም ስልጠና ወስደን ነበር። እዛ “ፎስፓኮም” የሚዘጋጅበት ወቅት ነበር። ይህ ትልቁ የአፍሪካውያን ፊልም ፌስቲቫል ነው። ጠቃሚ የሆነ የፊልም ስራ እውቀትን ከታወቀ ባለሙያ “Imagen film institute” ውስጥ ለሁለት ወራት በዝግ ነው የተማርነው። በስልጠናው መጨረሻ ላይ መላው አፍሪካ የፊልም ማህበር መስርተን ነበር። ሁለተኛው ጉዞዬ የነበረው ደግሞ ኢትዮጵያን ወክዬ “አፍሪካን ሙቪ አካዳሚ አዋርድ” ናይጄሪያ ሄጄያለሁ። ኢትዮጵያውያንን በጣም ነው የሚያከብሩት። በዚያ አጋጣሚ ከእነፎረስት ዊቴኮር ና ዳኒግሎቨር ጋር የመገናኘትም እድል አግኝቻለሁ። ጥሩ-ጥሩ አጋጣሚዎች ነበሩ ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- በዲጂታል ከሰራሃቸው ሶስት ፊልሞች መካከል በሁለቱ ተሸልመሃል። ብዙ ፊልም ያልሰራኸው ለምንድነው? ስክሪፕት ትመርጣለህ? ዋጋህ ውድ ነው? ወይስ አሰሪዎች ባህሪይ አይመችም?

ፈለቀ፡- አሪፍ ነው፤ ሶስቱንም ምክንያቶች እንያቸው። የመጀመሪያው ስክሪፕት ትመርጣለህ ወይ? ላልከው አዎ እመርጣለሁ። ቴአትርም ሆነ አጭር ልቦለድ ለማንበብም እመርጣለሁ። ፊልምም ሆነ ሌላ ስራ ስሰራ መምረጤ ግድ ነው። ምክንያቱም እኔ እዚህ ሞያ ውስጥ የገባሁት ገንዘብ ለማግኘት ሳይሆን ይሄ ሙያ የኔ ሙያ ነው ብዬ ነው። ሁለተኛው ብዙ ገንዘብ ትጠይቃለህ ወይ? እውነት ለመናገር ብዙ ሰዎች እርሱ ብዙ ገንዘብ ነው የሚጠይቀው የሚሉ አሉ። ይሄ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። እንደተባለው ብዙ ገንዘብ የምፈልግ ቢሆን እኮ በዓመት አንድ አስር ፊልሞችን ማምረት ይቻል ነበር። ግን ደግሞ ለባለሙያው ተገቢው ክፍያ ሊከፈለው ይገባል የሚል አቋም አለኝ። ሶስተኛው ባህሪው ነው የሚባለው ነገር ይሄ ሰውን አጠቃሎ መፈረጅና ስም የማጥፋት ነገር በጥበብ ማህበረሰብ ውስጥ ባህል የሆነ ነው። አንዱ ስለሌላው ጥሩ ነገር አያወራም። ይሄ ሊቀረፍ የሚገባውና የሚያሳፍርም ነው። በዚህ አጋጣሚ ከውጪ ያለው ሰው ሊያፍሩብን እንደሚችሉ መረዳት አለብን። ለአንባቢ ፍርዱን እንተወው. . .

ሰንደቅ፡- ግን ደግሞ ሳትግባባ ቀርተህ የተውካቸው ስራዎች አሉ?

ፈለቀ፡- ሁለት ምሳሌዎችን ላስቀምጥልህ፤ ፊልም ለመስራት ወደሐመር ሄድን። ከዚያ በኋላ እኔ በሬ ዘለልኩኝ፤ እንደአጋጣሚ ፊልሙ “ኮፒ ፔስት” የሚመስል ነው “Danecs with olives” ከሚባል የኮቨን ኮስትነር ፊልም ጋር ይመሳሰላል። እዛ ፊልም ላይ ወደሬድ ኢንዲያን የገባች ልጅ ወደማህበረሰቧ ስትቀላቀል ያሳያል። በዛኛው ፊልም ልክ ነው። በእኛ ፊልም ደግሞ አንዲት የሐመር ወጣት ወደአዲስ አበባ አምጥቶ ማሰልጠን ነው። የኔ ጥያቄ የነበረው እኛ ማን ሆነን ነው? አንድን ማህበረሰብ አንተ ከኛ ያልተሻልክ ነህ በሚል ወጣቷን አዲስ አበባ አምጥተን እናሻሽላለን የምንለው? የሚል ጥያቄ አነሳሁ። ከዚያም ሰዎቹ አስቸጋሪ ሰው ነው አሉኝ። ከሆንኩኝ ልሁን ነገር ግን ይሄ የ “አንትሮፖሎጂ” ጥያቄ ነው። ሁለተኛ ሰሞኑን አንድ ፊልም እየተጫወትኩ ነበር። ነገር ግን ፕሮዲዩሰሩ በፊልሙ ውስጥ ለፊልሙ የማይጠቅም ነገር ተቀምጦ ይቀረፅ የሚል ሃሳብ አቀረበ፤ እኔ ደግሞ ከዳይሬክተሩ ጋር ተነጋግሬ እንዲነሳ አስደረኩ።ከዚያ በዚህም ፀብ ተፈጠረ። አሁንም በዚህ ሁኔታ አስቸጋሪ ከሆንኩ ልሁን። በዚህ ሁኔታ እኔ ፊልም ከምሰራ ሳልሰራ ብሞት ይሻለኛል።

ሰንደቅ፡- ሐመር አካባቢ ስለተሰራው “ላሎምቤ” ፊልም ካነሳህ አይቀር በዛ አጭር ቆይታህ ከማህበረሰቡ ጋር ምን አሳለፍክ?

ፈለቀ፡- ብዙ የማይረሱ ነገሮች ነበሩት። በሬ ልዘል እንደሆነ ሲያውቁ አንድ ከነሱ ማህበረሰብ የወጣ ነገር ግን እዚህ ዩኒቨርስቲ የተማረ “ቆፀ” የሚባል ልጅ ነበር። ቤተሰቡን ሰጠኝ፤ እህቶቹ ሊገርፉልኝ ሆነ። ፍየል ወግተው በደም አጠመቁኝ። ከዚያም “ኢኪሊ” ሆነህ በሬዎቹን ስትዘል እንደባህሉ እርቃንህን መሆን ይጠበቅብሃል። እኔም ለፊልሙ ሲባል በፓንት እንድዘል ቢነገረኝም ዳይሬክተሩን አሳምኜ፤ ይህቺን አጋጣሚ ልጠቀም ስለው ፈቀደልኝ። በዚህ ላይ ከኔ በፊት አንድ አውስትራሊያዊና ጃፓናዊ እርቃናቸውን እንደዘለሉ ስሰማ አስቲ እውነት እናድርገው አልኩኝ። ራቁቴን በሬ ዘለልኩ።

ሰንደቅ፡- ያህንን ፊልም ባመስራት አሁን ይቆጭሃል?

ፈለቀ፡- ፊልሙ እኮ መነሻው አሪፍ ነው ውስጡ ያለው ሃሳብ ነው ያላስማማን። አሁን ፊልሙ ውጤታማም ሆኗል። አሜሪካን ሀገር ታይቶ ተወዷል አሁንም ዳይሬክተሩ አብርሃም ፀጋዬ ተጋብዞ እዛው ነው ያለው። ፊልሙን ባለመስራቴ አሁንም ቢሆን አይቆጨኝም። ምክንያቱም በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሟል ብዬ ስለማምን።

ሰንደቅ፡- እስቲ ወደቴአትር እንመለስ፤ በአሁኑ ወቅት በመታየት ላይ ያለውንና ትናንት ማክሰኞ የተመረቀው “ከሰላምታ ጋር” ቴአትር እጅህ ገብቶ ስታነብም ምን ስሜት ሰጠህ?

ፈለቀ፡- በመጀመሪያ በእንግሊዝኛ ነው ያነበብኩት። “Desperate to Fight” ብላ ነው መዓዛ ወርቁ የፃፈችው። ሳነበው በጣም ደስታ ነው የተሰማኝ፤ ምክንያቱም እንዲህ አይነት ዘር ኢትዮጵያ ውስጥ መምጣቱ ደስ ይልሃል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረለትን ተውኔት አንዲት ኢትዮጵያዊት መስራቷ በጣም አስደምሞኛል። ፅሁፉን ስታስነብበኝ የራሷ ስራ የሆነውን “ዝነኞቹ”ን እየተጫወትኩ ነበር። ከዚያ ሴቷን የሚጫወት ሰው እየፈለግን በአማርኛ እየተተረጎመ ነበር። መጀመሪያ የገባኝ 4 ሰዎች እንደሚጫወቱት ነበር። በኋላ እኔ አንድም ሶስትም ሆኜ እንደምሰራ ሚናው ሲነገረኝ ሌላ መደነቅ ፈጠረብኝ። ወዲያው ወደስራ ገባን፤ አሪፍ ስራ ሲሆን ገንዘብ አትጠይቅም። የሚገርምህ አሁን ድረስ የውል ወረቀት ሰጥተውኛል ግን አልተፈራረምንም። ቴአትሩን በነፃም ስራው ብባል እሰራዋለሁ። ያም ሆኖ ግን አሁንም ብዙ ክፍያ ነው የሚከፍሉኝ።

ሰንደቅ፡- የተመልካቹ ምላሽ እንደጠበቃችሁት ነበር?

ፈለቀ፡- ይሄን ጥያቄ ደራሲና ዳይሬክተሯ ወይም ፕሮዲዩሰሩ ነበር መጠየቅ የነበረበት። ነገር ግን ከተለመደው አፃፃፍ ወጣ ያለ በመሆኑ ሰው አይረዳው ይሆን የሚያስብል ፍርሃት ነበረን። አሁን ግን የሚደጋግሙትም አሉ። ይህም ቀምሰውት እንደጣፈጣቸው ምግብ ሆኖባቸው ይመስለኛል። በዚህ ላይ ብቻቸው ሳይሆን ሰው ይዘው ነው የሚመጡት ይህ ማለት ያልወደድከውን ምግብ ሰው አትጋብዝም ብዬ አስባለሁ። ብዙ አስተያየቶች ይደርሱኛል በአመዛኙ ግን ያልተለመደ አይነት ስራ መሆኑን ሰዎች ወደውታል።

ሰንደቅ፡- ከፍቺ ጋር በተያያዘ “ከሰላምታ ጋር” ቴአትር ውስጥ ከሰራሃቸው ሶስት ገፀ-ባህሪያት መካከል የትኛው ይመስልሃል ትክክለኛ ምክንያት ያለው?

ፈለቀ፡- ለኔ ሶስቱም ያው ናቸው። ሶስቱም ሙሉ ናቸው። ይሄን የምለው ሶስቱም አዲስ ልምድ ስለሆኑኝ ነው። ላገቡም ላላገቡም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ቴአትር ነው። ፍቺን በተመለከተ ከባድ ጥያቄ ነው። ነገር ግን አብሮ መኖር ካልተቻለ መፍታት ሰላም ነው።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

ፈለቀ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፤ በዚህ አጋጣሚ ቤተሰቦቼን ባለቤቴ አበባ ወልዴ፣ ልጆቼ በረከት እና ወዳሴኤለ በጣም አመሰግናለሁ። በተረፈ ወደውጪ በተጓዝኩ ወቅት ለረዱኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አማረ አረጋዊ፣ ለፍቃዱ ከበደ በላይነህ፣ እንዲሁም ሴፍ ዌይ ሱፐርማርኬት እና ሁሉም አድናቂዎቼን እወዳችኋለሁ፣ በልልኝ እናንተንም አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
12159 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us