“መስፍን” የነገሰበት ወግ

Wednesday, 20 August 2014 13:13

እሁድ ነሐሴ 11 ቀን 2006 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፀሐፍት አዳራሽ ሚውዚክ ሜይዴይ፤ መታሰቢያነቱን በቅርቡ በሞት በተለየንና ለአንጋፋው ወግ ፀሐፊ መስፍን ሃ/ማርያም ያደረገ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር። የፃፋቸውን ወጎች ማንበብ ብቻ ሳይሆን “ሰውዬውን” ራሱን ማስታወሱ ዘና የሚያደርግ መንፈስን እንደሚያጭር የመሰከሩለት የመድረኩ ታዳሚዎች በሥራዎቹና በህይወቱ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። በዕለቱ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ ለውይይት የሚሆን ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን፤ እንደመነሻም ስለመስፍን ሃ/ማርያም “እንደአዲስ” መናገር የቱን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን በሚከተለው መልኩ በማስረዳት ጀምሯል።

“ስለመስፍን ሃ/ማርያም ንግግር ላደርግ ስዘጋጅ አንድ የፒካሶ ቃለ ምልልስ ናት የተባለች ነገር ትዝ አለችኝ። ቃለ-ምልልሱ ላይ ፒካሶን፤ “ለአንድ ሰዓሊ በጣም ቃላሉ ነገር ምን መሳል ነው? ብለው ሲጠይቁት ምን ብሎ መለሰ፣ “ሰይጣን” አለ። ምክንያቱም ሰይጣን “አብስትራክት” ነው። ሃሳባዊ በመሆኑ እንደፈለግነው ቀንድ አውጥተንለትና አበለሻሽተነው ብንሰራው እንኳን “ሰይጣን ነው ካልን” እንታመናለን። ነገር ግን “በጣም የሚከብደውስ?” ብለው ሲጠይቁት የፒካሶ መልስ የነበረው “ሁሉም የሚያውቃትን እርግብ መሳል ነው” አለ። ዛሬም ስለ መስፍን እኔ ላወራ ስዘጋጅ እርግብ ነው የሆነው፤ ምክንያቱም ሁላችሁም ታውቁታላችሁና በማለት ሁሉም ታዳሚ ስለሚያውቀው ሰው መናገር የቱን ያህል እንደሚከብድ በማስታወስ ንግግሩን በወግ ጀምሯል።

ሞት ቀመስ ትውስታዎች

“አንድ ደራሲ ሞተ ሲባል እንደማንኛውም ሰው ተቀብሮ የሚረሳ አይደለም” በማለት ሃሳቡን የቀጠለው ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ የጋሽ መስፍን ሃ/ማርያምን ሞት በሰማበት ወቅት ስለታየው ነገር ያወሳል፤ ጋሽ መስፍን ከኛ ተነጥሎ ቢያልፍም ከእነ ስብሃት፣ ከነሎሬት ፀጋዬ እና ከእነከበደ ሚካኤል ጨምሮ ከተቀሩትም ሟች ደራሲያን ጋር በደስታ የተገናኘ ይመስለኛል በማለት የደራሲ አዳም ረታን ሃሳብ ተውሶ ያብራራል።

የወግ መስፍኑን በሚያስበው በዚህ መድረክ ላይ ወዝ ያላቸው ወጎችም ተሰምተዋል። ከእነዚህም መካከል ደራሲና ሃያሲው አለማየሁ ገላጋይ ከጋሽ መስፍን ጋር ትሄድልኛለች ያላትንና አንዲት ወግ ተርኳል። “ሰውየው ይሞትና ወደገሀነም ከመግባታችን በፊት ገነትን እንጎበኛለን፤ መኖሪያችን ሲኦል ከሆነ ገነትን አይተን የቀረብንን እንድናውቅ እንደረጋለን። ገነት የምንገባ ከሆነ ደግሞ ገሃነምን ሃይተን ከምን አይነት ጉድ እንዳመለጥን እናያለን” በማለት ታሪኩን ያንደረድራ።

ታዲያ የሞተው ሰውዬ መጀመሪያ የሚሄደው ወደ ሲኦል ይሆናል። ፀድቋል ማለት ነው። በጉብኝቱ ወቅት የእሳት ዛፍ ይመለከታል። እዛም ስር አንድ ደራሲ በእሳት ወረቀት ላይ በእሳት እስክሪብቶ ይፅፋል። ብዙ መፃፉን የተመለከተው እንግዳው ታዲያ “ወይ የደራሲ ነገር! በምድር ሳለ እንዲያ ሲፅፍ- ሲፅፍ ቆየ፤ አሁን እንኳን ተኮንኖም አያርፍም?”እያለ ተገርሞ ያልፋል። የሲኦል ጉብኝቱን ጨርሶ ገነትም ሲገባ እንደዛው የሚያጓጓ ፍሬ የተንዠረገገበትና የወተት ወንዝ የሚፈስበት፤ ልምላሜው ያማረ ቦታ አንድ ደራሲ ቁጭ ብሎ ይፅፋል። ይሄኔም ሰውዬው በጣም ተገርሞ “ይሄ ደራሲ ደግሞ ከፀደቀስ በኋላ ለምን ይፅፋል? ከዚህ የበለጠ ነገር ምን አለ?”ይላል። በነገሩ እጅግ ተገርሞ ያስጎበኘው የነበረውን መለአክ ቀረብ በማለት፣ “ለመሆኑ ገሃነም የገባውም ፣ ገነት የገባውም ደራሲ ይፅፋል ታዲያ የገነትና የገሀነም መግባት ልዩነቱ ምንድነው?” ሲል ይጠይቃል። መልዓኩም፣ “ገሀነም ያሉት አይታተምላቸውም። ገነት ያሉት ግን ይታተምላቸዋል” ሲል ታዳሚውን የሚያስፈግግ ተረክ ተናግሮ ሲያበቃ፤ አንድ ደራሲ የሚቀጣው ስራው ሳይታተም ሲቀር ነው የምትል እንድምታ ያላት ሃሳብ ጣል አድርጎ አልፏል።

ወግ እና ጋሽ መስፍን

ወግ ከመስፍን ሃ/ማርያም በፊትም እንደነበር በመናገር ይህን ሃሳብ ማስፋት የጀመረው ደራሲና ሃያሲው አለማየሁ ገላጋይ፤ ዳሩ ግን እዚህ አለም ላይ ወግ የሚባል ነገር ሊኖርም አሁን ባለው ዘመናዊ መልኩ ከመስፍን ቀድሞ በኢትዮጵያ እንዳልተከሰተ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ዘመናዊ የወግ አፃፃፍ በፈረንሳይና በእንግሊዝ አካባቢዎች እንደተጀመረና ለመጀመሪያ ጊዜም ሚካኤል ዴ ሞንታኝ ለዚህ ዓለም ዘመናዊውን ወግ እንዳስተዋወቀ ተጠቅሷል። ከ1530 እስከ 1592 ዓ.ም የኖረው ይህ ደራሲ 100 ያህል ወጎችን (ኢሲዎችን) በመፃፍ በሶስት መድብሎች ያሳተመ ሲሆን፤ ኢሴይ የሚለውን ስያሜም ያወጣው ይህ ደራሲ እንደሆነ ጠቁሟል። በእንግሊዝም ፍራክ ቤኮን ጀማሪ ሆኖ ሲጠቀስ፤ ይህም ሰው ወደ58 የሚደርሱ ወጎችን ፅፏል።

በሁለቱ ፀሃፍት መካከል ግን የአፃፃፍ ልዩነት መኖሩ ይጠቀሳል ሲል ልዩነቱን ማስረዳት የጀመረው አለማየሁ፤ ሞንታኝ የሚፅፈው “ኢሴይ” ኢ-መደበኛ ሲሆን የቤከን ደግሞ መደበኛ የሚለውን እንደሆነ ዘርዝሯል። ስለሁለቱ የአፃፃፍ ስልቶች ልዩነት ለማስረዳትም ከእኛ ሀገር ፀሐፊያን እንደ በዕውቀቱ ስዩም ያሉ ሰዎች ከራሳቸው ልምድ ተነስተው የሚፅፉበት ፅሑፍ ኢ-መደብኛ ተብሎ ሲጠቀስ፤ ፍራንሲስ ቤከን የጀመረው መደበኛ ወግ ደግሞ ሳይንሳዊ ምርምር ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ተወስቷል። ያም ሆኖ ከእነዚህ ሁለቱ ቀደምት ፀሐፍትም በፊት የብሉይ ወጎች አሉ ሲል የሚያትተው አለማየሁ፤ ወግን ወደዚህች አለም ያመጡት ሌሎች ፀሐፊዎች ናቸው ተብሎ ይታመናል ሲል የግሪካዊው ፀሐፊ ሥራዎች ይጠቃቅሳል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የወግ ጀማሪዎች ተበራክተውና አሻሚ ሆነው ቢቀርቡም “በአገራችን በተለይም ለአማርኛ ስነ-ፅሁፍ ወግን ያስተዋወቀው ግን መሰፍን ሃ/ማርያም ነው” ይለናል። ለዚህም እንደማሳያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፃፈው ወግ በየካቲት መጽሔት መስከረም 1975 ዓ.ም “የቡና ቤት ስዕሎች” በሚል ርዕስ እንደታተመ ተወስቷል። ከቆይታ በኋላም ጋሽ መስፍን ሌሎች ፅሁፎችን ጨማምሮ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት እንዲታተምለት ቢያቀርብም ስራው ስያሚ የሌለውና ወግ የማይታወቅ ከመሆኑም የተነሳ አሳታሚ ድርጅቱ ፅሁፎቹን “ምን ብዬ ላሳትመው?” እስከማለት ደርሶ እንደነበር ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ ያስታውሳል። ለስራውም ስም ያወጡለት ዘንድ ሥነ-ፅሁፍ ያውቃሉ የተባሉ ሶስት ሰዎች ኮሚቴ መሰረተ። ከነዚህም ውስጥ ደበበ ሰይፉ፣ ጋሽ አስፋው ዳምጤና ሌላ ሰው ተጨምሮ “ስም አፈላላጊ ኮሚቴ” ሆነዋል ይለናል። ኮሚቴው ለጊዜውም ቢሆን “ድርሰት” በሚለው የተስማማ ሲሆን፤ ዳሩ ግን ለ “የቡና ቤት ስዕሎች” መፀሐፍ መግቢያ እንዲፅፍ ኃላፊነት የተሰጠው ደበበ ሰይፉ ከሳምንት በኋላ ሲመጣ ስራው “ወግ” መባል ይችላል ማለቱን ያትታል። ይህም ሃሳብ አሁን ድረስ በበረካቶች ተቀባይነት አግኝቶ ቀጥሏል።

ጋሽ መስፍን ወግን ከማስተዋወቁም ባሻገር የአፃፃፍ ስርዓቱንና ድንጋጌውን ጭምር ማሳየት የቻለ ሰውም እንደነበር ከመድረኩ ተነግሯል። ለዚህም ከደበበ ሰይፉ ሃሳብ በኋላ፤ በ “ዓውደ አመት” እና “የሌሊት ድምፆች” የወግ ሥራዎቹ የተብራራ ሃሳብ ለማቅረብ እንደሞከረም መጥቀስ ተችሏል። በዚያም አንድ ወግ ፀሐፊ ያለምንም ማፈር፤ ያለምንም ማመንታትና ያለምንም ክብሬ ተነካ፤ ስሜ ጠፋ ሳይል ከታች ከእስከ ላይ ድረስ እየተንፏቀቀ ደርሶም ቢሆን የሆነ ነገር ይዞ መምጣት አለበት” ማለቱን ውይይት መሪው አትቷል። ይህ ሃሳብ የመስፍን ሃ/ማርያም ብቻ ሳይሆን የፈረንሳዊው ወግ ፀሐፊ የሞንታኝም ስለመሆኑ በማስታወስ የሚከተለውን ይጠቅሳል። “ሞንታኝ እኔን አያችሁኝ” ይላል፤ ስለዚህም መፅሐፌንም መንገድ ላይ ብታገኟት እኔን ቁርጥ ሆና ታገኟታላችሁ” ይላል በሚል የወግ ፀሐፊዎች ህይወት በሥራዎቻቸው ውስጥ በአደባባይ የተሰጠ እንደሆነ ይጠቁማል።

የጋሽ መስፍን ልጅነት

በሞጆ ከተማ ለቤተሰቡ ስምንተኛ ልጅ ሆኖ በ1935 ዓ.ም እንደተወለደ በአንድ ወቅት በፈርጥ መፅሔት እራሱ አስፍሮት ከተገኘ ፅሁፍ ያጣቀሰው ደራሲና ሃያሲው አለማየሁ ገላጋይ፤ በተለይም ስምንተኛ ልጅ ሆኖ በርከት ያሉ የቤት ስሞች እንደነበሩት በመዘርዘር ታዳሚውን ፈገግ አሰኝቷል። ጋሽ መስፍን፤ ከተጠራባቸው ስሞች መካከልም፡- የትነበርክ፣ ሲሳይ፣ እንግዳወርቅ፣ የኋላሸትና በትውልድ ሀገሩም ስም የሞጆ ወርቅ ሁሉ ይባል እንደነበር ተወስቷል። ይህ ሁሉ ጋሽ መስፍን ለቤተሰቡ የቱን ያህል ብርቅ እንደነበር የሚያሳይ ነው ይላል።

ስለግል የልጅነት ባህሪው ሲነገርም “ሞኛሞኝና እልኸኛ እንዲሁም አንዴ ከመቱኝ ቀኑን ሙሉ ሳለቅስ የምውል ነኝ” ማለቱን ሃሳብ አቅራቢው ለታዳሚያኑ ያስታውሳሉ።

በ1947 ዓ.ም ልዑል መኮንን ኃ/ስላሴ ሞጆ አካባቢ በመኪና አደጋ ሲሞቱ የሀዘን መግለጫ ግጥም ከአየር ተበትኖ ያገኘውና ያነበበው የ12 ዓመቱ መስፍን በጣም ማዘኑን ይነግረናል። ከዚያም አንድ ግጥም በመፃፍ ወደስነ-ፅሁፍ ልክፍቱ እንዴት እንደተንደረደረ ያስታውሰናል። ከመጀመሪያ ግጥሙ የሚያስታውሰው ስንኝም፤

ያ ልዑል መኮንን፤ የደሆች በረንዳ፤

ተለይቶን ሄደ፣ ጥሎን ዱብ ዕዳ

ታዲያ በዚህ ወቅት ታዳጊው መስፍን ከሄሊኮፍተር የበተነውን ግጥም ብቻ ሳይሆን የራሱንም ግጥም አንብቦ ሌላ ግማሽ ቀን ሲያለቅስ መዋሉን እራሱ በፃፈው ማስታወሻ ላይ ጠቅሶታል።

“ይህ የደራሲው የሞኛሞኝነትና የእልህኝነት ባህሪይ እስከዩኒቨርስቲ ስለመቀጠሉ በሥራዎቹ አይቻለሁ” የሚለው ደራሲና ሃያሲው አለማየሁ ገላጋይ ጋሽ መስፍን ፅፏቸው “በኮሌጅ ቀን ግጥሞች” መድብል የተካተቱትን ሁለት ሥራዎች አስታውሷል። “ፍለጋ” እና “ስሞታ” የተሰኙት እነዚህ ግጥሞቹ (በ1960 ዓ.ም የተፃፉ ናቸው) ያኔ መስፍን ሃ/ማርያም የ20 ዓመት ወጣት ነበር።

ጋሽ መስፍንና ሥራዎቹ

የወግ ደራሲው መስፍን ሃ/ማርያም “የቡና ቤት ስዕሎች እና ሌሎች”፣ አዜብ (የአጫጭር ልቦለዶች መድብል)፣ “ዓውደአመት” እና ሌሎችም ወጎች” እና “የሌሊት ድምፆች እና ሌሎች” የተሰኙ አራት ሥራዎች ለአንባቢያን አበርክቷል። ደራሲው ወግን በመፃፍ ከፍተኛ ተፅዕኖ የነበረው እንደሆነ የሚናገረው ደራሲና ሃያሲው አለማየሁ ገላጋይ፤ የመስፍን የፅሁፍ ሃይል ሥራዎቹን አንብቤ ድንገት አንድምግብ ቤት (ዘውዲቱ ሆቴል) የፃፈባቸው ስዕሎችን ስመለከት እየደገምኩ ትን እስኪለኝ ድረስ እስቃለሁ” ይለናል። ለዚህም የመስፍን አፃፃፍ ጉልበት ስለነበረው እንጂ ነገሮች ሁሉ ሊረሱ ይችሉ ነበር ሲል የገለፀና የቋንቋውን ጉልበት ያትታል።

ሥራዎቹ በጣም የሚቆጠሩ ቢሆኑም ጋሽ መስፍን ሃ/ማርያም እንደደራሲ ነፍሱ በአንባቢዎቹ ዘንድ እስከመጪው ትውልድ እንዳይረሳ ሆኖ ቀርቷል። ይህ ብዙዎች የሚስማሙበት ሃሳብ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ለወጣት ደራሲያን የነበረው ፍቅርና አክብሮት በበርካታ እውቅ ደራሲያን ላይ ጭምር ተፅዕኖን እስከመፍጠር ደርሷል።

መስፍን ከሰራቸው ወጎቹ መካከል የሚበዙት በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸው የውይይት ሃሳብ አቅራቢው ይናገራል። ለዚህም አብይ ምክንያቱ ወግ በማህበራዊ ህይወት ላይ እንዲያተኩር ግድ ስለሚለው ነው በሚል በጥናት ያገኛቸውን ቁጥሮች ይጠቅሳል። እንደማሳያም ጋሽ መስፍን ካሳተማቸው ሶስት የወግ ሥራዎቹ መካከል 49 ወጎች ቀርበዋል። ከነዚህም 26 ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ሲያተኩሩ፤ በስነፅሁፍ አውድ አካባቢ ወደ ስድስት ወጎች ቀርበዋል። ቀሪዎቹ አምስት ሥራዎቹ ሥነ-ልቦናዊ ትርክቶች ሆነው የቀረቡ ናቸው።

ከእነዚህ ሥራዎቹ ጋር የመስፍን ሃ/ማርያም ጠንካራ ጎን ተብሎ መነሳት ካለበት ነገር ሌላው ከኢ-መደበኛ ወግ ለመለስ በምርምር ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን መስራቱ እንደሆነ ተጠቁሟል። ለዚህም “አይጥ የሰይጣን ግልገል” በሚል ሥራው ውስጥ የግል ልምዱን ከጥናት ጠቀሶ ተጨባጭ እውነቶች ጋር አዛምዶ አቅራቧል። ይህም መደበኛ ፅሁፎችን ኢ-መደበኛ በሚለው መካከል አማካኝ አለ ወይ? እንድንል ያደረገ ነው ሲል ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ ጥያቄ ይሰነዝራል። ከዚህም ሌላ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ እና መስፍን ኃ/ማርያም በውጪ የትምህርት ቆይታቸው “በክሬቴቪ ራይት” የፈጠራ ፅሁፍን የተማሩ ብቸኛ ባለሙያዎች ናቸው። ነገር ግን በሚገባ አልተጠቀምንባቸውም አልተንከባከብናቸውም የሚል ሃሳብ አንስቷል። ጋሽ መስፍን ኃ/ማርያም በስተመጨረሻ በሰራቸው ሥራዎችም ለመኖር ብሎ መፃፍ መጀመሩ የወግ ሥራዎቹ ጥረት እንዲጎላቸው መሆኑን አፅንዖት ሰጥቶ፤ ማህበረሰባዊ የንባብ ጉዟችን ወቅሷል።

በእሁድ የሚውዚክ ሜይዴይ የውይይት መድረክ ወቅት ደራሲው ብዙ መፀሐፍት ስለአለመፃፉ፤ ስለቀደምት ስራዎቹ፣ ስለወግ ስያሜ ፣ ወግ ፀሐፊ ማነው? እና ሌሎችም የውይይት ሃሳቦች ከተሳታፊዎች ተነስቶ ጠቅላላ ምላሾች ተሰጥቶባቸዋል።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
12163 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us