“አዘጋጅ የሚፈተነው በገፀ-ባህሪይ ግንባታ ላይ ነው”

Wednesday, 27 August 2014 11:02

 

ተዋናይ መኮንን ላዕከ

 

“ጨርቆስ ተወልጄ ያደኩ የአራዳ ልጅ ነኝ” የሚለው የዛሬው የመዝናኛ አምድ እንግዳችን ብዙዎች ሳይናገር ሳቅ የሚቀናቸው፤ ሰርቶ የሚማርካቸው አይነት ተዋናይ ነው። በርካታ ቴአትሮችን በመስራት የጀመረው ይህ ተዋናይ አሁን- የፊልሞች ቅመም ያህል ሆኗል። ሰርቷቸው ከተወደደለት ቴአትሮች መካከል የሲኦል ነፍሳት፣ “የምሽት ፍቅረኞች” እና “መስተፋቅር” ሲጠቀስለት፣ በፊልሙ ዘርፍ ደግሞ ከብዙዎቹ አፋጀችን፣ ማርኩሽ፣ ባዶ ነበር፣ የጎደለኝ ፣ ቦምቡ ፍቅርሽ፣ የትሮይ ፈረስ “ድፍረት” እና በቅርቡ በተለየ የሚጠቀስለት “ጥቁር እንግዳ” ፊልሞች ላይ ሰርቷል። ከተዋናይ መኮንን ላዕከ ጋር አሸናፊ ደምሴ አጭር ቆይታ አድርጓል።

ሰንደቅ፡- አሁን-አሁን በብዙ ፊልሞች ላይ ትታያለህ፤ ቴአትርን ትተኸው ነው?

መኮንን፡- እኔ ትወናን ስጀምር በቴአትር ነው የጀመርኩት። የመጀመሪያ ስራዬም “የሲኦል ነፍሳት” የሚል ነበር፤ ቀጥዬ “የመቃብር ቁልፎች” እና “አንድ ቃል” የተሰኙ ቴአትሮችን በማዘጋጃ መድረክ ላይ ተጫውቻለሁ። ሌላው “የምሽት ፍቅረኞች” የሚል ቴአትር ሲሆን የማዘጋጃ ስራ ሆኖ እኔ ግን ክፍለ ሀገር ነው የሰራሁት። ከዚያም ወደቅርብ ጊዜ “መስተፋቅር”ን በሀገር ፍቅር ሰራሁ። አሁን- አሁን ቴአትር የሚያሰራ ጠፍቶ ፊልም ላይ በረከትኩ እንጂ ስራዬን የጀመርኩት በቴአትሮች ነው። አሁንም ድረስ ከፊልም ይልቅ ቴአትርን ብሰራ ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- ብዙ ፊልሞችን ሰርተሃል መርጠህና ወደህ ነው የምትሰራቸው?

መኮንን፡- አዎ ብዙዎቹን ሃሳባቸው ጥሩ ስለሆነ ነው የምሰራቸው። ለምሳሌ “ሜድ ኢን ቻይናን” ተመልከት “አፋጀሽኝ” አለ፤ “የትሮይ ፈረስ”፤ “ህይወት በደረጃ”ም እንዲሁ አብዛኞቹ ማህበራዊ ህይወታችንን ውጣ ውረድ የሚያሳዩ ስራዎች ናቸው። በቅርቡም እየታዩ ካሉት “የጎደለኝ” እና “ጥቁር እንግዳ” ሃሳባቸውን ወድጄ የሰራኋቸው ፊልሞች ናቸው።

ሰንደቅ፡- አንተ የተለያዩ ገፀ-ባህሪያትን መስራት እንደምትችል ብትናገርም፤ አብዛኞቹ ፊልሞች ላይ ተመሳሳይነት ያላቸው ገፀ-ባህሪያት ነው የተጫወትከው ለምንድነው?

መኮንን፡- ይሄን መመለስ የሚችሉት ዳይሬክተሮቹ ናቸው። እኔ ግን በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ። ይሄ የአዘጋጆቹ ምርጫ ነው። ሌላም ገፀ ባህሪይ መጫወት እንደምችል ተናግሬያለሁ፤ መናገር ብቻም አይደለም በተግባርም አሳይቻለሁ። እኔ ሽማግሌ አይደለሁም፤ ጎልማሳ የምባል ነኝ። ግን የእነርሱ ምርጫ ሸምግልና ላይ ብቻ ያተኮረ ሆነ። እንግዲህ ይሄነገር ከአዘጋጆቹ አቅም ይሁን ወይም ሽምግልናዬን ስለሚወዱት አላውቅም። ነገር ግን አንድ የማረጋግጠው ነገር እኔ ብዙ መጫወት እችላለሁ፤ ይህን ደግሞ አዘጋጆቹም በእርግጠኝነት ያውቃሉ። እውነቱን ለመናገር አንድ አዘጋጅ የሚፈተነው ገፀ-ባህሪይ ግንባታ ላይ በሚሰራው አዲስ ነገር ነው ብዬ አምናለሁ። የዚህ ጥያቄ መልስ እነሱ'ጋ ነው ያለው።፡ እኔ የተሰጠኝን ገፀ ባህሪይ ሁሉ መስራት እችላለሁ። ይህንንም በ “አማረኝ” ፊልም አሳይቻለሁ።

ሰንደቅ፡- በሬዲዮና በቲቪ ድራማዎች ላይ ያለህ ተሳትፎ ምን ይመስላል?

መኮንን፡- ሬዲዮ ላይ ፓፕሌሺን ሚዲያ ሴንተር በሚያሰራው ድራማ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ሰርቻለሁ። በቲቪ ደግሞ “ገመና” ሲጀምር ነበርኩ። አስር ክፍሎችን ከሄደ በኋላ ገፀ-ባህሪው ወጥቷል፤ መውጣትም ነበረበት። በአጠቃላይ ግን በቴአትርም በሬዲዮም ሆነ በቲቪ ድራማዎች ላይ ከጋበዙኝ እሰራለሁ። ነገር ግን አሰሩኝ ብዬ አልዞርም። አስፈላጊ ሆኜ ስገኝና መጥተው ሲያነጋግሩኝ ከመስራት ወደኋላ አልልም።

ሰንደቅ፡- ትወናን ለራሱ ያስተማረ ሰው ነው የሚሉህ ወዳጆች አሉ። እስቲ ስለአጀማመርህ ንገረኝ?

መኮንን፡- ስጀመር አላማዬ የነበረው ድርሰት መፃፍ ነው። ይህንን ተመስገን መላኩ የሚባል ወዳጄ ያውቃል። ያም ሆኖ ግን ያን ጊዜ “ሀ-ሁ በስድስት ወር” የተሰኘ ቴአትር እየተጠና ነበር። እነሱ ሲሰሩ ለማየት ወስዶኝ ስመለከት ደስ አለኝ። አብሬያቸው መብራት አካባቢ ማገዝ ጀመርኩ። ከዚያ ሳምሶን ወርቁ ፍላጎቴን አይቶ “የሲኦል ነፍሳት” የተሰኘ ቴአትር ላይ እንድተውን ዕድሉን ስጠኝ። ይህ የመጀመሪያ መድረኬ ነበር። አሪፍ አድርጌ እጫወት ስለነበር እዛ ላይ ያዩኝ ሰዎች የተለያዩ ስራዎች ላይ እየጠሩኝ አብሬያቸው መስራት ጀመርኩ ማለት ነው። ደራሲ እሆናለሁ ያልኩት ሰውዬ ሳላውቀው ወደትወና ገብቼ ቀረሁ። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- የፅሁፍ ነገር አሁን ድረስ እንደተዳፈነ ነው?

መኮንን፡- ያዘጋጀኋቸው ፅሁፎች አሉኝ። አሁን በቅርቡ ወደስራ አመጣቸዋለሁ ብዬ እየጠበኩ ነው። ጊዜ እየጠበኩ እንጂ የፊልምም የመድረክም ድርሰቶች አሉኝ።

ሰንደቅ፡- በበርካታ ፊልሞች ላይ የሚያዩህ ሰዎች ዋጋው አነስ ያለ ስለሆነ ነው ይሉሃል። ከአማርኛ ፊልሞች መብዛትና ካንተ አስተዋፅኦ ጋር ጠቅለል አድርገህ ንገረኝ?

መኮንን፡- ክፍያን በተመለከተ እስካሁን የሚገባኝን አግኝቻለሁ ብዬ አላስብም። ይኸው እንደምታየኝ በእግሬ ሯጭ ነኝ። የሚገርምህ ክፍያው በቂ ሳይሆን እንኳን የተነጋገርከውን የማይከፍልህም አለ። በጭቅጭቅና በሽምግልና የሚከፍልህም አለ። ይህን ስልህ ደግሞ ጥሩዎችም መኖራቸው መዘንጋት የለበትም።

የአማርኛ ፊልሞች መብዛትን በተመለከተ ለሁለት ከፍዬ ነው የማየው። የመጀመሪያው ፅሁፍ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የፊልሙ አባላት (መብራት፣ ካሜራ፣ ኤዲቲንግ) ከፊልም ፅሁፍ አንጻር ብዙ ደካማ ስራዎች አጋጥመውኛል። ይህን መደባበቅ አይቻልም። እኔ በግሌ ያስተካከልኳቸው ስራዎች አሉ። አንድ ፊልም የያዘው ጭብጥ ምንድነው የሚለው ዋና ጉዳይ ነው። የሚያዋጣ ከሆነ ትሰራለህ፤ ካልሆነ ደግሞ ዴሞክራት አዘጋጅ ካለ ተነጋግረህ እንደሚሆን ታስተካክለዋለህ።

ሰንደቅ፡- አሁን ድረስ የምትወደውና የማትረሳው ገፀ-ባህሪይ የትኛው ነው? ለምን?

መኮንን፡- እኔ ሁሉንም ስራዎቼን በተለያየ አንግል ነው የማያቸው። ለተመልካቹ ምን ይሰጣሉ ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ “ማርኩሽ” የተሰኘውን ፊልም ብትወስድ ፍርድ ቤት ነፃ ያለውን ሰው ማህበረሰቡ “ሙሰኛ” እያለ ሲጠራው ታያለህ፤ በህግና በሰዎች ፍርድ መካከል የወደቀ “ካራክተር” በመሆኑ ደስ ይለኛል። ሁለተኛው “ሜዲኢንቻይና” ፊልም አለ፤ የማህበረሰባችንን ነጭ አምላከነት በጉልህ ያሳየ ስራ ነው፤ እኔ እንደውም አንዳንዴ “ቀኝ አልተገዛንም እንዴ?” ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። ለፈረንጅ ቅድሚያ የምንሰጠው ከአክብሮት ከሆነ እሰየው፤ ነገር ግን ከአጎብዳክንት ከሆነ በጣም አሳፋሪ ነው። በፊልሙ ውስጥ ካለው ቻይናዊ ይልቅ እኔ የምጫወታቸው አዛውንት መከበር እያለባቸው፤ ተገላቢጦሽ በመሆኑ ሃሳቡ ደስ ይለኛል። ሌላው “የጎደለኝ” የተሰኘው ፊልም ነው፤ ምን ያህሉ ቤተሰብ ነው ያን የመሰለ መቀራረብ ያለው የሚለውን ስጠይቅ በፊልሙ ላይ ያለው አባት በጣም ነው ደስ የሚለኝ። የቅርቡ ደግሞ “ጥቁር እንግዳ” ፊልም ላይ ያሉት ባሻ ማጣት ምን ያህል ስብዕናን እንደሚያሸጥ ያሳዩ ገፀ-ባህሪይ ስለሆኑ በጣም ደስ ይሉኛል።

ሰንደቅ፡- ስለ“ጥቁር እንግዳ” ፊልም ካነሳህ አይቀር ባሻን እንዴት ትገልፃቸዋለህ?

መኮንን፡- ባሻ የሚገርሙ ሰው ናቸው። የመስማት ችግር አለባቸው። የኢኮኖሚ ችግር ስላለባቸው ብቻ ያልወለዷትን ልጅ ለገንዘብ ሲሉ ልጄ ናት እስከማለት ደርሰዋል። በርግጥ መወለድ ቋንቋ መሆኑን ልጅቷ ስላሳየቻቸው በስተመጨረሻ ተለሳለሱ እንጂ ባሻ የሚገርሙ “ካራክተር” ናቸው። እስካሁን ከሰራኋቸው የሽማግሌ ገፀ-ባህሪያት በጣም የተለዩ ናቸው ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ምን አይነት ገፀ-ባህሪን መጫወት ትፈልጋለህ?

መኮንን፡- እንደተዋናይ እኔ የመጣውን እጫወታለሁ። ምናልባትም አራስ ልጅ ሁን ካልተባልኩ በስተቀር የመጣውን እሰራለሁ ብዬ አስባለሁ። አራስ መሆን ግን አልችልም። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- አብረውህ የሰሩ ሰዎች እኛ የሰጠነውን ገፀ-ባህሪይ በይልጥ አዋዝቶ ማቅረብ ይችልበታል ይሉሃል፤ እስቲ ስለዚህ ነገር አጫውተኝ?

መኮንን፡- ብዙዎቹ እንደዛ ይሉኛል። አንድ ገፀ -ባህሪይን በደረቁ መጫወት አልወድም፤ ወዝ እቀባዋለሁ። የኔን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም እቀባለሁ። ምን መሰለህ እስክሪብቱን በደንብ አነበዋለሁ፤ ቀጥዬ የምሰራው ገፀ-ባህሪይ ምን አይነት እንደሆነ አጠናዋለሁ። ከዚያ በኋላ ነው የምሰራው እንጂ የተሰጠኝን ሁሉ ተቀብዬ አላነበንብም።

ሰንደቅ፡- በአመት ምን ያህል ፊልሞችን ትሰራለህ?

መኮንን፡- ምን አለ መሰለህ፤ አሁን ብዙ ፊልሞች ላይ ሰው ሲያየኝ በምን ሰዓት ሰራው ሊል ይችላል። ነገር ግን አንዳንዶቹ ፊልሞች ከወራት ከዓመታትም በፊት የሰራኋቸው ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኛውን ከረሳሁት በኋላ ነው ለዕይታ የሚቀርበው ያም ሆኖ ግን ብዙ ስራዎች ይመጡልኛል።

ሰንደቅ፡- አብረሃቸው ለመስራት የምትመኛቸው አንጋፋ ወይም ወጣት ተዋንያን አሉ?

መኮንን፡- እኔ እንዲህ አይነት ምኞት የለኝም። ከመጣው ጋር መስራት ነው። እስካሁንም ከመጣው ጋር ነው የሰራሁት፤ የእንጀራ ጉዳይ ካገጣጠመን ከማናቸውም ጋር ብሰራ ደስ ይለኛል እንጂ እገሌ ብዬ የምመርጠው ሰው የለኝም።

ሰንደቅ፡- በምንድነው የምትዝናናው?

መኮንን፡- ከጓደኞቼ ጋር ስብስብ ብዬ በአንድ ጉዳይ ላይ ስንወያይ በጣም እዝናናለሁ።

ሰንደቅ፡- ዝነኝነት የፈጠረብህ ተፅዕኖ አለ?

መኮንን፡- አስቤው አላውቅም። ለኔ ትወና እንደማንኛውም ስራ ስራ ነው። በርግጥ የኛ ስራ ለህዝብ የተጋለጠ ነው። ያም ሆኖ ስለዝነኛነት አስቤ አላውቅም።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ምን ለመስራት እያሰብክ ነው?

መኮንን፡- እኔ እንደማስበው ትወናው ላይ ምናልባት ለአጭር ጊዜ እሰራ ይሆናል፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ወደጽሁፍ ፊቴን የማዞር ሃሳቡ አለኝ። የራሴን አንድ ፊልም ለመስራት አስቤያለሁ፤ የተለየ ስራ ከመጣ እሰራለሁ ግን አሁን- አሁን መጻፍ ነው የምፈልገው። ትወናን በጣም እወደዋለሁ ግን ያን ያህል አልጓጓለትም። አሁን መፃፍ እፈልጋለሁ።

ሰንደቅ፡- በጣም አመሰግናለሁ።

መኮንን፡- እኔም አመሰግናለሁ። አብረውኝ ትወናን ለጀመሩ፤ አይዞህ በርታ ላሉኝና እዚህ ላደረሱኝ ተመልካቾች ሁሉ አመሰግናለሁ። በተረፈ ግን በትወናም መተካካት ስላለ ለአዲሶቹ መንገዱን በቅንነት ማሳየት ይገባናል እላለሁ። ዘመኑ በአእምሮ የምንወዳደርበት ስለሆነ አዳዲሶቹ ልጆች ጋር መተባበር አለብን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
9883 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us