“ከመጀመሪያ አልበሜ ያገኘሁት ክፍያ ዋንጫ ብቻ ነው”

Wednesday, 03 September 2014 13:33

የባህል ሙዚቀኛው ስማቸው ካሳ

በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር፤ ደብረ ማርቆስ ከተማ የጁቤ የምትባል አካባቢ ተወልዶ ያደገ ከያኒ ነው። ገና በልጅነት ዕድሜው በትምህርት ቤት መድረኮች የድምፅ አቅሙን ማሳየት እንደጀመረ የሚናገረው ይህ የባህል ሙዚቃ ተጫዋች፤ በ1988 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ኮልፌ ፖሊስ ማሰልጣኛ በመግባት ፖሊሳዊ አገልግሎት ከመስጠቱም በተጨማሪ በፖሊስ የሙዚቃ ባንድ ውስጥም በድምፃዊነት አገልግሏል። በአሁን ወቅት በግል በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ድምፃዊ ስማቸው ካሳ፤ ሦስት የሙዚቃ አልበሞች ያሉት ሲሆን፤ ቃለመጠይቅ ለማድረግ የተገናኘነው በሰቆጣ ከተማ ለሻደይ በአል በተገኘበትና የሙዚቃ ክሊፖችን በቀረፀበት ወቅት ነው።

ሰንደቅየሰራሃቸውን አልበሞች ለአንባቢያን በማስታወስ እንጀምር?

ስማቸውበ1994 ዓ.ም “እማ” የሚል አልበም ሰርቻለሁ። ይህ “እማ” የተሰሠኘው ዘፈኔ ብዙ ጊዜ በኢትዮጰያ ቴሌቪዥን ይታይ ነበር። ይህ አልበም የኔው አካሉ የተሰኘ ባለሙያ ነው ግጥምና ዜማ የሰራልኝ። ይህ የመጀመሪያ ስራዬ ሲሆን፤ በመቀጠል ደግሞ በአምባሰል ሙዚቃ ቤት አማካኝነት በ1996 ዓ.ም “ጎጃም ና በይኝ”የተሰኘ አልበም ሰራሁ። የዚህን አልበም በሙሉ ግጥምና ዜማ ራሴ ነበርኩ የሰራሁት። ቀጥሎ የሠራሁት ሦስተኛ አልበሜ “እየሩሳሌም” ይሠኛል፤ በ98 መጨረሻ አካባቢ ነው የሠራሁት።

ሰንደቅጠቅልለህ ወደሙዚቃስራ ከመግባትህ በፊት የፖሊስ አባልእንደነበርክ ሰምቻለሁ፤ እስቲ ስለሁኔታው አጫውተኘ?  

ስማቸው ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት በ1988 ዓ.ም ነው። ስመጣ አካባቢ አዲስ አበባ ፖሊስ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር። የኔ ፍላጎት ሙዚቃ መስራት በመሆኑ የፖሊስ ኦርኬስትራውም ብዙም የሚራራቅ ስላልመሰለኝ ተመዘገብኩ። ስልጠና ጨርሼ አንድ ሁለት ሦስት አመት ቆይታ በኃላ ማለትም በ1992 ዓ.ም በኋላ ወደ ፖሊስ ኦሪኬስትራ ተዛውሬ በሙያው ቢሠራ ጥሩ ነው ተብዬ የሙዚቃ ስራ መስራት ጀመርኩ።

1994 ዓ.ም የመጀመሪያ አልበሜን ስሰራ በፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥም እሰራ ነበር። ከዚያ በኋላ መስሪያ ቤቱ ለሁለት ዓመት የIT ትምህርት እያስተማረኝ ነበር። ያንን ተምሬ እስክጨርስ ድረስ ከሙዚቃ ራቅ ብዬ ነበር። 1996 ዓ.ም ላይ እዛው እያለሁ ሁለተኛ አልበሜን ሰራሁ። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ስራዎቼ ወጡ እንጂ እኔ አልወጣሁም። ምክንያቱም ስራዬን መስራት ነበረብኝ። በተማርኩት መሰረት በፌዴራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ በኮምፒዩተር ጥገና ክፍል ውስጥ ተመድቤ እሰራ ስለነበር ምንም ጊዜ ሊበቃኝ አልቻለም። ከዚያ በኋላ ግን ሙዚቃን የሙሉ ጊዜ ስራዬ ለማድረግ ከፖሊስ ለቅቄ መውጣት እንዳለብኝ አሰብኩ። የሚገርምህ በ1997 ዓ.ም ነው ከፖሊስ ለቅቄ የወጣሁት። ከፖሊስ ህዳር ወር ላይ ለመውጣት መልቀቂያ ደብዳቤ ሳስገባ ለአንድ ወር የምከፍለው የቤት ኪራይ ገንዘብ ራሱ አልነበረኝም። ይህ ሁሉ የሙዚቃ ፈተና ነው። ፈተናውን ለመውጣት ደግሞ መስዋትነት መክፈል ግድ ነው። ለሶስት ወር ስራ አላገኘሁም፤ አከራዮቼም በጣም ጥሩዎች ስለነበሩ እንደምንም ጊዜው አለፈ።

ሰንደቅምንም ሳይኖርህ ድንገት ከወጣህ በኋላ ምን አጋጠመህ?

ስማቸው አጋጣሚ ሆኖ ከፖሊስ ከወጣሁ በኋላ ወራት እንዳለፈ “አልማ 97” በጎንደርና በባህርዳር ከተሞች የባዛር ዝግጅት ይዞ ነበር። በዛ ውስጥ የ19 ቀናት የሙዚቃ ኮንሰርትም ነበረ። ያን ኮንሰርት ተወዳድሬ በማሸነፍ ከባንዱ ጋር ለ18 ቀን ትርኢት አሳየሁ። በዚያ ገንዘብ ትንሽ ቀና አልኩ ማለት ነው። ጥር አካባቢ ግማሽ ተብሎ በህይወት ዘመኔ ለመጀመሪያ ጊዜ 32ሺህ ብር ያዝኩኝ። ብሩ ብዙ ሆኖኝ ባንክም ሳላስገባ፣ ሌሊቱን ሙሉ ታቅፌው አደርኩ (ሳቅ). . . ብዙ ብር አይቼ ካለማወቄ የተነሳ ምን እንደሆንኩ ታውቃለህ? ጎንደር ሄጄ ለሙዚቀኞች አበላቸውን በቀን እከፍላለሁ ታዲያ አንድ ጊዜ 5ሺህ ብር በአንድ የጎን ኪስ ውስጥ ተረሳ። ያን ብር ከወራት በኋላ ያገኘሁት ጃኬቱን ለክረምት ብርድ ብዬ ልለብሰው ሳነሳ ነው ብሩን ያገኘሁት። ይሄ እንግዲህ የገቢያ እና ወጪ አያያዜ ምን ያህል ችግር እንደነበረበት የሚያሳይ ነው።

ሰንደቅእስቲ ደግሞ መለስ እንበልና የሙዚቃ አልበምህ ሲሰሙ ከአድማጭ ይደርስህ የነበረው ምላሽና ይሰማህ የነበረው ስሜት ምን ይመስላል?

ስማቸው ባይገርምህ እኔ ከሀገር ቤት ስመጣ ግጥምና ዜማ ብዬ ሰበሰብኳቸውና እዚህ ከባለሙያዎች ጋር ስገናኝ ምንም ሆኑብኝ። የመጀመሪያ አልበሜን የሰራው የኔው አካሉ ስራዎቼን አየና እንደመነሻ ይዟቸው ሙሉ ስራውን እራሱ ጥሩ አድርጎ ሰራልኝ። በ1994 ዓ.ም የመጀመሪያ አልበሜ ስወጣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ጥሩ ውጤት አግኝቶ ነበርና ለእኔ ልዩ ትዝታ ነበረው። ታዲያ ሙዚቃው ያወጣው ሙዚቃ ቤት ጎጃም በረንዳ አካባቢ ነበርና እንደምታውቀው ቦታው ግርግር የበዛበትና በተለይም የስሜኑ ሰው የሚበዙበት ነው። ዘፈኔ ተከፍቶ ሰዎች ተሰብስበው ሲጨፍሩ ሳይ ከሰው መካከል ቆሜ እመለከት ነበር። በጣም ደስ ከመሰኘቴ የነተሳ ቤቴ መገናኛ ሆኖ ጎጃም በረንዳ ላይ መሸብኝ። (ሳቅ) ደስታው የተለየ ነበር። ያም ሆኖ ቅጂ በጣም የተስፋፋበት ሰሞን በመሆኑ ተጠቃሚ አልሆንኩም። በመጀመሪያ አልበሜ ያገኘሁት ክፍያ ዋንጫ ብቻ ነው። ያም ዋንጫ ወጣት ብሔራዊ ቡድናችን ያገኘው ነው። ሌላ ምንም ያገኘሁት ጥቅም የለም።

ሰንደቅእንደዚህ የሞራል ውድቀት እያለብህ ወደሁለተኛ አልበም ስራህ እንዴት ገባህ?

ስማቸው ገንዘብ ባለማግኘቴ ምንም ሳይመስለኝ ነው ወደሁለተኛው አልበም ስራዬ የገባሁት። ያኔ ገንዘብ የማገኘው ከፖሊስ፤ ከአንዳንድ መድረኮችና የሚያውቁኝ ሰዎች ለሰርግ ስራ እየጋበዘኝ እሰራ ነበር። ሁለተኛ አልበሜን ራሴው ነኝ ግጥምና ዜማውን የሰራሁት፤ ከዚያ በኋላ አምባሰል ሙዚቃ ቤት ሲገዛኝ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ብዙ ብር አገኘሁ። ብሩ የብዙ ስለመሰለኝ “በቪሲዲ፣ ምናምን ብሰራው አትቃወምም አይደል?” ሲለኝ! ኧረ እኔንም አፍርሰህ ብትሰራኝ አልቃወምህም ብዬው ባለቤቱን አሳኩት። (ሳቅ)

ሰንደቅየሶስተኛ አልበምህስ ውጤት ምን ይመስላል?

ስማቸው በሶስተኛ አልበሜ “እየሩሳሌም” ይሰኛል። ውስጡ “እንቁጣጣሽ” የተሰኘ ቆንጆ ስራ ነበረው ኢቲቪም ደጋግሞ በራሱ ቅንብር ያሳየዋል። ጥሩ ተሰሚነት ነበረው። “ወሎ መገናዋ” እና “ጎጃሜ ናት ልጅቷ” በጣም ተወዳጅ ስራዎቼ ነበሩ። እነዚህን በክሊፕም ሰርቻቸዋለሁ። በዚህም ብዙ ሰዎች ነጠላ ዜማዎቼ እንጂ ሙሉ አልበም የሰራሁ ሁሉ አይመስለውም ነበር።

ሰንደቅበኮንሰርት ምክንያት ከክልል ከተሞች ሌላ ውጪ ሀገር የሰራህባቸው አሉ?

ስማቸው ውጪ ሀገር ሰርቼ አላውቅም። እዚሁ ጎረቤት በር ላይ ማለት ይቻላል፤ ሱዳን ሰርቻለሁ። እሱንም በስደት ሄጄ ነው።

ሰንደቅበምን ምክንያት ተሰደድኩ?

ስማቸው ከ2000 ሚሊኒየም በኋላ አንድ “ኑ!” የሚል ነጠላ ዜማ ሰራሁ። እርሱም በብዙ ሚዲያዎች ይሄድ ነበር። ከዚያ በኋላ በቤተሰብም ለኢኮኖሚም ከባድ ችግር ገጠመኝ። ከዚያም የአንድ ወር የጉብኝት ቪዛ አስመትቼ ወደሱዳን ሄድኩ። እዚህ አዲስ አበባ የማውቀው ልጅ ሱዳን ነበር። እርሱ እንደሚቀበለኝ ሲነግረኝ ተነስቼ ሄድኩ። የሚገርመው ግን እዛ ስደርስ ስልኩን አጥፍቶ ተደበቀኝ። ባይገርምህ የሄድኩት በመኪና ነው። ከአዲስ አበባ መተማ፤ ከመተማ ገላባት፤ ከገለባት ካርቱም ከሌሊቱ 7 ሰዓት ገባን። ልጁ ስልኩን አጥፍቷል። እኔ ምንም፤ ማንንም አላውቅም።

ሰንደቅበማታውቀው ሀገር ለስደት ስትገባ፤ የሚቀበልህ አጥተህ ወዴት ሄድክ?

ስማቸውበዚህ አጋጣሚ በጣም የማመሰግነውን ሰው ፈጣሪ አስተዋውቆኛል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ አንድ የጅማ ልጅ እህቱን ካርቱም ለማግኘት አብሮኝ በመኪና ውስጥ ተዋወቀን ነበር። እህቱ ስትመጣ የገጠመኝን ነገራት “የሀገራችንን ልጅማ ጥለነው አንሄድም” ብላ ከእነርሱ ጋር አብራ ወሰደችኝ። ባይገርምህ እነርሱ ሙስሊሞች እኔ ደግሞ ክርስቲያን ነኝ። በአንድ ቤት ውስጥ ስምንት ዘጠኝ ሆነው ነበር በአንድ ላይ የሚኖሩት። ከተለያዩ ቦታ የመጡ ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ እዛ ቤት ውስጥ ትንሿን ኢትዮጵያ አየኋት ማለት እችላለሁ። ከአስራአምስት ቀናት በላይ እነርሱ ጋር ቆየሁ። ከዚያም ሱዳን ውስጥ ኃይለስላሴ ያስገነቡትና ከ60 ዓመት በላይ ያስቆጠረ “መድሃኒያለም” የሚባል ቤተክርስትያን አለ። ከቤተመንግስቱ ፊት ለፊት ነው። አጋጣሚ ለጥምቀት በዓል እዛ ደርሼ ነበር። የጥምቀት ዕለት እንደአዲስ አበባ ነበር የሚከበረው። ይህን ሳይ በጣም አለቀስኩ። አንድ ልጅ አይታኝ መጣችና “አንተ ልጅ አዲስ አበባ አውቅሃለሁ፣ ካሴትም አለህ፤ ዘፋኝ ነህ አይደል?” አለችኝ። የገረመኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘፋኝ የሚለኝ ሰው ሳገኝ፤ እንዴት መጣህ? አለችን ያጋጠመኝን ነገርኳት በጣም አዘነች።

ሰንደቅከዚህ ሁሉ በኋላ ምን እየሰራህ በሱዳን ከአንድ ዓመት በላይ ቆየህ?

ስማቸው እዛው ሱዳናዊ ባለሀብት እየከፈላቸው ሙዚቃ የሚያሰራቸውን ልጆች አገኘሁ። አንድ በጣም ኢትዮጵያዊን የሚወድ ወገን በስልክ አፈላልገው አገናኙኝ። በቃ እኔ ቤት ነው የምወስድህ አንድ ክፍል እሰጥሃለሁ ምንም ችግር የለም አለኝ። ከዚያ ከሙዚቀኞቹ ጋር ስገናኝ እነርሱን የቀጠራቸው ባለሀብት እኔንም በዶላር ቀጠረኝ። በወር 300 ዶላር እየተከፈለኝ እዛው ቤት መስራት ጀመርኩ። ባይገርምህ ለሱዳኖች ሰርግ ሳይቀር እኛ ነበርን የምንሰራው፤ የአማርኛ ባህላዊ ዘፈን እዛ በጣም ነው የሚወደደው።

ሰንደቅበዓመት ውስጥ ምን ያህል ሱዳናውያንን ዘፍነህ አጋባህ?

ስማቸው ኧረ በጣም ብዙ ነው። በሳምንት ቢያንስ ሶስት የምንሰራበት ጊዜ ሁሉ ነበር። የሰርግ ፕሮግራሞችን ብቻ ሳይሆን የልጆች ልደትንም የምርቃትንም ሁሉ በባንድ ነው የሚያሰሩት የነበረው።

ሰንደቅወደኢትዮጵያ እንዴት ተመለስክ?

ስማቸውአንድ ዓመት ከምናምን ከሰራሁ በኋላ ሳየው ሳንቲም አገኛለሁ፤ ነገር ግን ለሙያዩ በሀገሬ መኖሬ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተረዳሁ። ከዚህ ቀደምም ብዙ ታዋቂ ድምፃውያን ሱዳን ገብተው ሰርተው ተመልሰዋል። እውነቱን ለመናገር ሱዳን ሰርተህ መኖር ትችላለህ። ነገር ግን አዳዲስ ስራዎችን ለመስራትና ለመፍጠር ስትነሳ አይሳካልህም። ምክንያቱም የባህል ዘፈን ባህሉን በሚያውቅ ማህበረሰብ ውስጥ ሆነህ የምትሰራው መሆን አለበት። አለበለዚያ ከባህር የወጣ አሳ መሆን ነው። ከዚያ መጥቼ ከተለያዩ ባንዶች ጋር የተለያዩ ዝግጅቶችን በመስራትና አራተኛ አልበሜንም አጠናቅቄ እየጠበኩ ነው። እዚህ ከመጣሁ በኋላ ባዛሮች፣ የባህል ኮንሰርቶች፣ ሰርጎችና የሆቴል ምርቃቶችንም እየሰራሁ ነው።

ሰንደቅየባህል ሙዚቀኞች በዓላትን አስታኮ ካልሆነ ብዙም አይታወቁም፤ ከአዲስ አበባ ይልቅ በክልል ይታወቃሉ ይህ ለምን ይመስልሃል?

ስማቸው አንደኛው ብዙ የማስተዋወቅ አቅም አለመዳበሩ ይመስለኛል። ደጋግመህ የምታየውን የምትሰማውን ሰው የማታውቅበት ምንም ምክንያት የለም። አሁን አሁን እንደውም ሙዚቃ ቤቶች ራሳቸው ጠፍተዋል። ባህርዳር ባለፈው ሄጄ አንድ ሙዚቃ ቤት የለም። ምክንያቱ ኪሳራ ፍራቻ ነው። “ኮፒ ራይት” ሰውን ማሰራት አልቻለም። አዲስ አበባም ቢሆን ከሙዚቃ ቤት ይልቅ አዟሪዎ ናቸው የሚያዞሩት። ያ ደግሞ የማይሆን ነገር ነው። ብዙ ሰዎች በኮፒ ራይት ሰበብ ይያዛሉ ይፈታሉ፤ ይሄ ደግሞ መፍትሄ አይደለም። ዋናው ነገር ግንዛቤ መፍጠር ነው። መንግስትም ሚዲያውም የራሱን ሚና ሲጫወት ነው።

ሰንደቅበምንድነው የምትዝናናው?

ስማቸው እኔ እንደዚህ ጩኸት የበዛበት ቦታ ላይ መገኘት አይመቸኝም። ሙዚቃ ሲጮህ አይመቸኝም። እኔ ስዘፍን እንጂ ሲዘፈንብኝ ደስ አይለኝም (ሳቅ) ፀጥ ያለ ጫካ ውስጥ እና ውሃ ዳር ስቆይ መንፈሴ ዘና ይላል።

ሰንደቅወደፊት ምን ለመስራት አስበሃል?

ስማቸው ወደፊት እንግዲህ ከሱዳን ያመጣኋትን ጥሪት ለቀጣዩ አልበም አውያታለሁ። አልበሜን ሰርቼ ጨርሻለሁ፤ ነገር ግን ሙዚቃ ቤቶች ስለጠፉ ስፖንሰር ማግኘት የሚቻል ከሆነ ለማውጣት እየፈለኩ ነው። አለበለዚያ ግን አንድ ሁለት ሶስት ክሊፖችን እየሰራሁ ነው። እነሱን ለቅቄ ለአድማጭ ተመልካቹ በሚዲያ በኩል ማድረስ ነው።

ሰንደቅቤተሰብ አለህ?

    ስማቸውአዎ! ባለትዳር ነኝ። ባለቤቴ ጥሩ ወርቅ አበበ ትባላለች። እዮብ ስማቸውና ሚካኤል ስማቸው የተባሉ ሁለት ልጆች አሉኝ። ጥሩ ቤተሰብ አለኝ፤ ደስተኛ ነኝ። በተረፈ በዙሪያዩ ያሉትን ሰዎች ሁሉ አመሰግናለሁ። እናንተም ይህን እድል ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11407 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us