የቅዳሜን ምሽት ከለዛ ምርጦች ጋር

Saturday, 12 October 2013 15:10

መታሰቢያነቱን በቅርቡ በድንገተኛ ሞት ላጣነው ድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ያደረገው የዘንድሮው የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች የዓመቱ ምርጥ አልበም፣ የዓመቱ ምርጥ ፊልም፣ የዓመቱ ምርጥ ተዋናይትና ተዋናይ እንዲሁም የዓመቱን ምርጥ ነጠላ ዜማ አሸናፊዎች ለ3ኛ ጊዜ በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ ባሳለፍነው ቅዳሜ መስከረም 25 ቀን 2006 ዓ.ም በደማቅ ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል።

በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት በዚህ ፕሮግራም ላይ ሰዓትን ያለማክበር በአዘጋጆቹ ዘንድ በጉልህ ታይቷል። ለ12 ሰዓት የተጠራው እንግዳ የፕሮግራሙን መጀመር ያገኘው ከ1 ሰዓት በኩል በኋላ መሆኑ ብዙዎችን ቅር አሰኝቷል። ምናልባትም ይህ የጊዜ ችግር የተፈጠረው የለዛ ፕሮግራም በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የቀጥታ ስርጭት ጋር በቀጥታ ስርጭት እንዲገናኝ ታስቦ ቢሆንም፤ በዚህ መልኩ በዝግጅቱ ላይ ለመታደም የመጡትን እንግዶች ማጉላላት አልነበረበትም የሚሉ ሰዎች አልታጡም።

በዕለቱ የለዛ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው ብርሃኑ ድጋፌ በእንግዶቹ ፊት ስለ ድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ሲያወሳ እንባ ሲተናነቀው እንደነበር ታይቷል። መድረኩን ያሟሹት የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የህብር ዘማሪያን የድምፃዊውን አንድ ዘፈን ተጫውተዋል። አለባበሳቸውና መሳሪያ አልባ የሙዚቃ ስራቸውም ወጣቱንና ተወዳጁን ድምፃዊ በሚገባ ያሰበ ፕሮግራም እንደነበር ያሳያል። በጊታር የታጀበው የቀረበው የኢዮብ ሙዚቃ፤

ነገን ላየው እጓጓለሁ

በል ሂድ ዛሬ ጠግቤያለሁ

ከእንግዲህ መቼም ላትመጣ

ደህና ሁን በል ሌላ መጣ

በል ሸኘኝ በሰላም ልሂድ

ልጀምር የነገን መንገድ። (የሚለው ነበር)

የሽልማት መድረኩን ከሐዘን ስሜት ያወጣውና በቅርቡ አዲስ አልበሙን ለህዝብ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀው ድምፃዊ አብነት አጐናፍር በጊታር የታጀበ ምርጥ ሙዚቃ አቀንቅኗል። ዘፈኑ ለ“አላዳንኩሽም” ፊልም ማጀቢያነት ያቀነቀነው እንደሆነ ይታወሳል።

የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጥ ተሸላሚ ሆነው በመጀመሪያ በነጠላ ዜማ ዕጩ ከሆኑት መካከል በ“አደራ” መሐሙድ አህመድና ጐሳዬ ተስፋዬ፤ በ“አቤት እዚህ ቤት” የኛዎች፣ በ“መላ” ብዙአየሁ ደምሴ፣ በ“ድል ዜማ” ዘላለም ካሳሁን እና በ“ሰላ በይ” ጃኪ ጆሲ የተመረጡ ሲሆን፤ በዚህ ዘርፍ አሸናፊ የሆነው ነጠላ ዜማ የእኛዎች “አቤት እዚህ ቤት” የተሰኘ ሆኖ ተመርጧል።

በዚህ የአድማጮች ምርጫ ተሸላሚ ምርጥ የዓመቱ ነጠላ ዜማ ላይ እንደብዙ የሽልማት ፕሮግራሞች ሁሉ ጉርምርምታ የተሰማበት ሲሆን፤ በተለይም አሸናፊውን ነጠላ ዜማ ለአድማጭ፤ ተመልካቹ ይፋ ለማድረግ ወደመድረክ የወጡት የሙዚቃ ባለሙያው አርቲስት ዳዊት ይፍሩ ውጤቱን ከማሳወቃቸው በፊት “ውጤቱ አሸናፊ ይሆናል ብለን ከገመትነው ያልገመትነው ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ማለታቸው ታዳሚውን የአግራሞት ሳቅ ውስጥ የነከረ ሆኗል። በዚህ ውድድር አሸናፊ ለሆኑት ድምፃዊያን ሽልማቱን የሰጠው ደግሞ ከሀገርና ከመድረክ ከራቀ 49 ዓመታትን እንዳስቆጠረ የነገረን ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ ነበር። የናፈቀንን ሰው በዚህ መሰል መድረክ ላይ ማግኘት በራሱ ለፕሮግራሙ ሌላ ድመቀት ፈጥሯል።

እዚህ’ጋ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ሁለት ዕንግዶችን ወደመድረክ ጋብዘው አሸናፊውን እንዲያሳውቁና ሽልማት እንዲያበረክቱ ማድረጋቸው መልካም ቢሆንም፤ ነገር ግን ቀጥሎ በመጣው የዓመቱ ምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ላይ የተከሰተውን አይነት ምስቅልቅል መፍጠር አልነበረባቸውም የሚሉ ድምጾች ከበርካታ ታዳሚያን ተሰምታዋል።

በለዛ ፕሮግራም የዓመቱ ምርጥ ተዋናይት ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡት ተዋንያን መካከል ኤልሳቤጥ መላኩ በሎሚ ሽታ ፊልም፣ ብርቱካን በፍቃዱ በኒሻን ፊልም፣ ማህደር አሰፋ በአምራን ፊልም፣ ሄለን በድሉ በከመጠን በላይ ፊልም እና ሳያት ደምሴ በስሜት ወይስ ስሌት ፊልም ናቸው።

በዚህ የዓመቱ ምርጥ የተዋናይት ዘርፍ አሸናፊዋን ለመሸለም በአዘጋጆቹ ወደመድረክ የተጠራችው የአምናዋ አሸናፊ እና ዘንድሮም በዕጩነት ስሟ የተካተተው ማህደር አሰፋ ስትሆን፤ ብዙዎች እንደገመቱት እርሷ ከአሸናፊነቱ ውጪ ትሆናለች ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ይህንን ስሜት አብዛኛው ታዳሚ ብቻ ሳይሆን ራሷ ማህደር አሰፋም ብትሆን ያንፀባረቀችው ነው ለማለት ያስደፍራል። ያም ሆኖ አሸናፊውን ዕጩ እንድታስተዋውቅ በተጠራችበት መድረክ ላይ ራሷን ተሸላሚ ሆና ማግኘት አዘጋጆቹ ሊፈጥሩ ያሰቡት ድንገተኛ ደስታ (ሰርፕራይዝ) አወዛጋቢና አነጋጋሪ ሆኖ አምሽቷል። ይህም ሆኖ ምናልባትም የሽልማት አሰጣጡን ከተለምዶአዊው አካሄዱ ፈቀቅ ለማድረግ ያለመ ነው ቢባል እንኳን መንገዱ የሚያዘልቅ አለመሆኑን ከተመልካቹ የተሰነዘሩትን ኀሳቦች ማጤን ቢቻል ለቀጣይ መልካም ይሆናል። በነጠላ ዜማው ዘርፍ ሽልማት እንዲሰጡ ሁለት ታዋቂ ግለሰቦችን የመጋበዛቸውን ያህል በፊልሙም ዘርፍ ቢሆን ሊሸልሙ የሚችሉ በርካታ ባለሙያዎች እያሉ ይህን ማድረጋቸው ሽልማቱን ለዛ አሳጥቶታል። ለዚህም ነው አብዛኞቹ ድፍረትም ድክመትም የተንፀባረቀበት ሽልማት ሲሉ የምርጥ ተዋናይት ዘርፉን የወረፉት።

ቀጥሎ በመጣው የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡት አለማየሁ ታደሰ በያ ቀን ፊልም፤ ሳምሶን ታደሰ በአምራን ፊልም፣ ነፃነት ወርቅነህ በ3ኛ ወገንና ፈለቀ አበበ በኒሻን ፊልም ናቸው። የዚህን ዘርፍ አሸናፊ ሽልማት እንዲያበረክቱ ወደመድረክ የተጠሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር መምህር ሆነው ለረጅም ዓመታት ያገለገሉትንና በበርካታ ጥበባዊ ስራዎቻቸው የሚታወቁት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ነበሩ። በዘርፉ አሸናፊ የሆነው ምርጥ ተዋናይም ተወዳጁ ተዋናይ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) ነበር። በዚህ ዘርፍ አራት ዕጩዎች ብቻ መቅረባቸው ከሌሎቹ ዘርፎች በአንድ ዕጩ ለምን አነሰ አሰኝቷል።

የ2005 ዓ.ም ምርጥ የሙዚቃ አልበም ሆነው በዕጩነት ለመጨረሻው ዙር የቀረቡት አምስት አልበሞች የሚካኤል በላይነት “ናፍቆትና ፍቅር”፣ የሸዋንዳኝ ኃይሉ “ስጦታሽ”፣ የአበባ ደሳለኝ “የለሁበትም”፣ የፀጋዬ እሸቱ “ስብስብ ዘፋኖች” እና የጃኖ ባንድ ስራ የሆነው “ኤርታሌ” ሆነው ቀርበዋል። በመጨረሻም ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ በናፍቆትና ፍቅር አልበሙ የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጥ አልበም ሆኖ በማሸነፉ ሽልማቱን ከአርቲስት መሐሙድ አህመድ እጅ ተቀብሏል።

በዚህ አጋጣሚ ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ የሽልማት ፕሮግራሙን ከማድነቁም ባሻገር ብዙ ጊዜ መሰል የሽልማት ታሪኮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መበራከታቸው መልካም ቢሆንም፤ “ምነው ያኔ ቢሆን” የሚያሰኝ ቁጭት እንደፈጠረበትም መናገሩን ተከትሎ ተሸላሚው ድምፃዊና የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ብርሃኑ ደጋፌ “ሁሌም በልባችን ውስጥ አለህ” ሲሉ የልብ የሚያደርስ መልስ ሰጥተዋል።

የመጨረሻው የሽልማት ፕሮግራም የሆነው የዓመቱ ምርጥ ፊልም ሲሆን፤ የመጀመሪያውን ባለ 35 ሚሊ ሜትር “አስቴር” የተሰኘ ፊልም ሰርተዋል። በምዕራብ አውሮፓ ጀርመን የፓን አፍሪካ ፊልም ሰሪዎች ተወካይም ነበሩ፤ በዚሁም ተቋም የክፍለ አህጉሩ ተመራጭ በመሆን የምስራቅ አፍሪካ ዋና ፀሐፊ ሆነው ሰርተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በመምህርነት እያገለገሉ የሚገኙት መምህር ሰለሞን ወያን ሽልማት እንዲያበረክቱ ወደመድረክ ተጋብዘዋል።

በዚህ የምርጥ ፊልሞች ዘርፍ ውስጥ የተካተቱት አምስቱ የ2005 ዓ.ም የፊልም ስራዎች ላ-ቦረና፣ ሎሚሽታ፣ ኒሻን፣ አምራን እና ጥቁርና ነጭ የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ሆነው ቀርበዋል። ከእነዚህ ስራዎች ውስጥ በምርጥ ስራነቱ አጠያያቂ የልሆነው “የሎሚ ሽታ” እንዲገኝ ቢደረግም በ2005 ዓ.ም ከወጡት ፊልሞች ጋር ተደምሮ ለውድድር መቅረቡ ግን የጊዜ ገደብ የለውም እንዴ? የሚያሰኝ ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም።

የዓመቱ ምርጥ ፊልም በመሆን ሽልማቱን ያገኘው “አምራን” ፊልም ሲሆን የፊልሙ ፕሮዲዩሰር አቶ ፍቅረየሱስ ድንበሩ በመድረክ ተገኝቶ ሽልማቱን ተረክበዋል።

በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጥ ለ3ኛ ጊዜ በዚህ መልኩ መካሄዱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ ፕሮግራሙ በግለሰብ ደረጃ እየተካሄደ መቀጠሉ ሩቅ እንዳይሄድ መሰናክል እንዳይሆንበት ስጋት የገባቸው ሰዎች መኖራቸው አልቀረም።

ያም ቢሆን አብዛኛው ታዳሚ መሰል ፕሮግራሞች ተበራክተው ቢቀጥሉ ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ የተሻለ ብርታትን ለመፍጠር ካለው ጉልበት አንፃር አድናቆት የሚቸረው እንደሆነ ይስማማል።

የዕለቱ ተሸላሚዎችም በአንድ ቃል የሚስማሙም በዚሁ ነው። በመድረክ ተገኝተው ምስጋናቸውን ያቀረቡት ተሸላሚዎች በሙሉ የፕሮግራሙን አዘጋጆች፣ ስራቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲሰሩ የረዷቸውን ግለሰቦችና ድምፅ የሰጣቸውን አድማጭ እና ተመልካች ሁሉ አመስግነዋል።

በለዛ የሬዲዮ ፕሮግራም የዓመቱ ምርጥ የሽልማት ሥነ-ስርዓት በቀጣይም የማናጣው እንደሆነ የበርካቶች ምኞት ሲሆን፤ በዚህ አጋጣሚ በፕሮግራሙ ላይ አሸናፊ የሚሆኑ ድምፃውያን ዘፈኖቻቸውን የሚያቀነቅኑበት አጋጣሚ ቢመቻች፤ ለሁሉም ፊልሞችም ሆነ ነጠላ ዜማዎች በስክሪኑ እኩል የመደመጥና የመታየት (ከቴክኒክ ችግር ውጪ) አጋጣሚን መፍጠር ቢቻልና ሰፋ ያለ ጊዜ የተሻለ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለዘንድሮዎቹ የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጥ ተሸላሚዎች ግን እንኳን ደስ ያላችሁ ማለትን አንዘነጋም።

Last modified on Tuesday, 28 January 2014 13:30
ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
13028 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us