“አንዳንድ ፕሮዲዩሰሮች ያታልላሉ”

Wednesday, 17 September 2014 13:24

አርቲስት ፍቃዱ ከበደ

የ2007 ዓ.ም የመጀመሪያው የመዝናኛ አምድ እንግዳችን አርቲስት ፍቃዱ ከበደ ነው። ፍቃዱ በቴአትር፣ በፊልም፣ በሬዲዮና በቲቪ ድራማዎቹ የሚታወቅ በወጣትነቱ የአንጋፎቹን ያህል ስሙ የሚጠራ ተዋናይ ነው። ከቴአትር ባቢሎን በሳሎን፣ የብዕር ስም፣ ህንደኬ፣ ሜዳሊያ፣ ትዳር ሲታጠን፣ ማበዴ ነው እና ሌሎችንም ተጫውቷል። በፊልም ደግሞ 70/30፣ የትሮይ ፈረስ፣ በዚህ ሳምነት፣ ሰርግ ከአሜሪካ፣ ሚዜዎቹ ደላሎቹ ይጠቀሳሉ። በአርቲስቱ ሥራና ህይወት ዙሪያ ጥቂት ተጨዋውተናል።

ሰንደቅቄራ፣ አዲሱ ዓመትና ልጅነት ለፍቃዱ ምን ትውስታ አላቸው?

ፍቃዱበጣም ደስ ይላል። የልጅነት ጊዜዬን ደስተኛ ሆኜ ያሳለፍኩትን ያሳለፍኩት በቄራ ነው። ጥበብን የጀመርኩት፤ በልጅነት አሉ የሚባሉ ጨዋታዎችን የተጫወትኩትና እዚህ የደረስኩበት ሰፈር ነው ቄራ። ልጅነትን በተመለከተ ሁሉን ነገር አድርጌ ስላደኩም በጣም ደስ የሚል ትውስታ አለኝ። በዓል በመጣ ቁጥር ልጅነቴን ሳስታውሰው በጣም ነው ደስ የሚለኝ። በተለይ ደግሞ እንቁጣጣሽ ላይ የአበባ ሉክ (ወረቀት) ነገር የማይረሳ ነው። በኛ ጊዜ እንደአሁኑ አይደለም፤ የመላዕክትን ስዕል ስለን ለቅርብ ሰዎች እንሰጣለን አንድ ብርም፤ ሁለት ብርም ስናገኝ ሜዳ ሄደን በኳስ ጨዋታ (በፍፁም ቅጣትምት) ነው የምናጠፋው።

ሰንደቅእዚህ'ጋ ስለኳስ ጨዋታ ካነሳህ ተዋናይ ባይሆን ኖሮ እግር ኳስ ተጫዋች ይሆን ነበር የሚሉ ሰዎች፤ አሉ አንተ ምን ትላለህ?

ፍቃዱቄራ ሁለት አይረሴ ሜዳዎች አሉ። አልማዝዬ እና አመድ ሜዳ ይባላሉ። እኛ አለማዝዬ ሜዳ ላይ ተጫውተን ነው ያደግነው። እውነቱን ለመናገር ተዋናይ ባልሆን እግር ኳስ ተጫዋች ነገር የምሆነው። በቀደም እንደውም አይተህ ከሆነ የአባይ ግድብ ሶስተኛ አመትን ምክንያት በማድረግ በተካሄደ ግጥሚያ በባለስልጣናት ቡድን ላይ ሃይለኛ ጎል ያገባሁት እኔ ነኝ። በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነበርኩ። ከእኔ'ጋር ይጫወቱ የነበሩት እነ ሀብታሙ ባርጌቾ፣ እነረዘነ በርሄ፣ እነዳንኤል ተሰማ፣ እነ አስናቀ ደጀኔ ኧረ ብዙዎች አሉ ለብሔራዊ ቡድን ጭምር የተጫወቱ ጓደኞቼ ናቸው። የሚገርም ነገር ቀጫጫ ነኝ ነገር ግን ኳስ በፍፁም አይቀሙኝም ነበር። እንደውም “ኤልፓ ሲ” ቡድን ሁሉ ሞክሬ ነበር። በኳስ አያያዜና በአጨዋወቴ ወደውኝ ግን ቀጫጫ ስለነበርኩ አቅም የለውም ብለው ነው ያስቀሩኝ። ደግሞም እውነት ነው እግር ኳስ ጉልበትም ይጠይቃል። የሚገርመው ነገር ኳስ እንደዛ እየተጫወትኩም ትምህርት ቤት ደግሞ ግጥሞች፣ ሥነ-ፅሑፎችን እየሞካከርኩ አቀርብ ነበር። የመጀመሪያው አድናቂዬ ወንድ አያቴ ነበሩ። ትምህርት ቤት ውስጥ ስነ-ፅሁፍ ሳቀርብ ይሰሙ ስለነበር በጣም ነበር የሚያበረታቱኝ። ይህው በደመነፍሴ ያደገው ነገር አሁን ላይ ገዝቶኛል።

ሰንደቅቄራ ያንተ የአማተር ከያኒነት መጀመሪያ ነው። ካንተ ጋር ደግሞ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ)፣ ሰለሞን ቦጋለና ቢኒያም ወርቁ ይጠቀሳሉ። እስቲ ስለመጀመሪያው ጊዜ አስታውሰኝ?

ፍቃዱበጣም ጥሩ፤ እዚህ'ጋ አንድ ነገር ልንገርህ። ከቤተሰብ ሁሉ እናቴ ነፍሷን ይማረውና “የኔ ልጅ ወደፊት ድራማ ሰሪ ነው የሚሆነው” ትል ነበር። ለምን መሰለህ እኛ ቤት የሚመጡ ትልልቅ ሰዎችን ሁሉ አስመስዬ ስናገር እናቴ ትገረም ትስቅም ነበር። አሁን እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱን እናቴ ባለማየቷ ይቆጨኛል። በአማተርነት ጊዜ 8ኛ ክፍል አፄ ዘረያቆብ ትምህርት ቤት ስንማር አሁን ጋዜጠኛ ነው አብርሃም ሞገስ ይባላል፤ እሱ ይፅፋል ሌሎቻችን እንተውናለን። በትምህርት ቤቱ ውስጥ በጣም ታዋቂዎች ነበርን። መምህራኖችን ስክሪብቶና ደብተር ይሸልሙን ነበር። ከዚህያ ወደሃይስኩል አልፈን ንፋስ ስልክ ት/ቤት ገባን። በዛ መሀል ከምወደው ኳስ የተለያየሁት ከፍተኛ ጉዳት ደረሰብኝ። እግሬ ተሰበረ። ሁለት ዓመት ያህል ታመምኩኝ። በዚህ ጊዜ ተሰብሬ እቤት ስቀመጥ ብዙ ነገሬን ወደማንበብ አደላሁ። ያኔ ነው በጣም ማንበብ የጀመርኩት። ደግሞም በጣም ጠቅሞኛል።

ሰንደቅየቴአትር ስልጠናም ወስደህ ነበር?

ፍቃዱበ1990 ዓ.ም ክልል 14 የቴአትር ስልጠና ይሰጥ ነበር። ከ3000 ምናምን ተማሪዎች ጥቂቶች ነበርን የማለፍ እድሉን የምናገኘው በዚህ መሀል አባቴ ስራ እንድሰራ ፈልጎ መንገድ ትራንስፖርት ውስጥ ሥራ እንድገባ በሚያውቃቸው ሰዎች በኩል ተገኘልኝ። ወዲያው ሥራ መጀመር እንደምችል ሲነገረኝ በጣም ነበር ያዘንኩት። ነገር ግን ክልል 14 ላይ በቴአትር ዘርፍ ተፈትነን መጨረሻ ላይ 90 ልጆች ቀረን። ከዚያ ደግሞ አለፍኩ ስል ፍቃዱ ከበደና በፍቃዱ ከበደ የምንባል ሰዎች ስማችን አምታታ፤ እኔም አልፌያለሁ ስል ሌላም ልጅ መጥቶ እኔ አልፌያለሁ አለ። ከፈታኞቻችን መካከል አቶ ንጉሴ ታፈሰ የሚባሉ የማዘጋጃ ቤት ሰው ነበሩ፤ ሲያዩኝ አላማርኳቸውም፤ ኮሰስኩባቸው መሰለኝ እሱ ነው ያለፈው አንተ ሂድ አለኝ። እኔ አለቀስኩ ምክንያቱም የፈተኑኝ ሰዎች በጣም ተደስተውብኝ ተስፋ አርገውብኝ ነበር። ያኛውን ልጅ የፈተኑትም ሰዎች ልጁ በጣም ጎበዝ ነው አሏቸው። ይሄኔ ጋሽ ንጉሴ ፊታቸውን ወደዛኛው ልጅ አዙረው በል አንተ ሂድ መልክህን አሳምረህ አሳሳትከኝ አሉት (ሳቅ) በጣም እልህ ስለያዘኝ ምን እንዳልኩ ታውቃለህ፤ እኔ አይደለም ከዚህ ልጅ ከፈታኞቹም ጋር ብወዳደር አልወድቅም ብዬ ፎከርኩ።(ሳቅ) ድጋሚ ሁለታችንም ተፈተንን ሁለታችንም በሚገርም ሁኔታ አለፍን። ባይገርም አሪፍ ወዳጆች ሆነን እሱ ሲያገባ ሚዜው ሁሉ ነበርኩ።

ሰንደቅከዚህ ስልጠና በኋላ ነው ቄራ አካባቢ የተሰባሰባችሁት?

ፍቃዱየሚገርምህን ነገር ልንገርህ አሪፍ ስልጠና ነበር የወስድነው። መምህራኖቻችን ደበበ እሸቱ፣ አስታጥቃቸው ይሁን፣ እና ስዩም ተፈራ ሁሉ ነበሩ። እድለኛ መሆኔ የምታውቀው ደግሞ ከሶስቱም ጋር የመታውን አጋጣሚውን አግኝቻለሁ። ከማከብራቸው ሰዎች ጋር አብሬ መተወኔ ለኔ ትልቅ ኩራት ነው። ከስዩም ጋር “ይፈለጋል”ን፤ ከአስታጥቃቸው ይሁን ጋር “ዋናው ተቆጣጣሪ” ቴአትርን፤ ከጋሽ ደቤ ጋር ደግሞ “70/30” ፊልምን አብሬው ሰርቻለሁ። ከዚያ በኋላ ግን ምን ሆነ መሰለህ ቢኒያም ወርቁ ጎረቤቴ ነው። የሆነ ቀን “እስቲ 42 ቀበሌ አዳራሽ ና” አለኝ። እኔ ግን ቀረሁ ለምን? ከተመረቅነው ልጆች ጋር “ነጫጭ ሰይጣኖች” የሚል ቴአትር ሰርተን የቴአትር ቤት መድረክ እየጠበቅን ነበር። በኋላ ላይ እስቲ ልያቸው ብዬ ስሄድ ቢኒያም ወዲው የምተውነውን የቴአትር ፅሑፍ ሰጠኝ። ራሴን ገፀ-ባህሪይ “ዲያሎግ” ለመገልበጥ ወስጄ ፅሁፍ እንዴት ይነበብልኝ፤ የቢኒያምን ፅሁፍ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው የሚያነቡት፤ እኔ ማንበብ ባለመቻሌ በነጋታው ሄጄ “አትምጣ ማለት ስትችል ይሄን ፅሁፍ እንዴት ትሰጠኛለህ?” ብዬ ስመልስለት በሳቅ ሞተ። ከዚያ ሌሎች ልጆች ገልብጠው እንዲነበብ አድርገው ስጡኝ ማጥናት ጀመርን። በነገራችን ላይ ለኔም፣ ሊያሬድም፣ ለሰለሞንና ለሳምሶንም ጭምር ቢኒያም በጣም መሰረት ጥሎልናል ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅከብዙ ልፋት በኋላ ፕሮፌሽናል መድረክ እንዴት አገኛችሁ?

ፍቃዱቴአትሮችን እንሰራለን ባለሙያዎች በግምገማ ይጥሉታል። አሁንም እንሰራለን፤ ይወድቃል። ከሰላሳ በላይ ቴአትሮችን ሰርተን ወድቀውብናል ማለት እችላለሁ። ግን ተስፋ አልቆረጥንም። ከዚያ በኋላ በስንት ልፋት “የአልማዝ ቀለበት” እና “ዲቪ” የተሰኙ ሁለት ቴአትሮችን አለፉ። ብዙ ቲአትሮች መውደቃቸው ለኛ ብዙ እንድንሰራ ምክንያት ሆኖናል። ሁለቱ ያለፉት ቲአትሮች “ዲቪ” ኮሜዲ ሲሆን፤ “የአልማዝ ቀለበት” ደግሞ ትራጄዲ ነው። ሁለቱም ለብሔራዊ ቴአትር መድረክ አለፉልን ማለት ነው። በነገራችን ላይ “የአልማዝ ቀለበት” ቴአትር የቢኒያም አብይ ሥራ (ማስተር ፒስ) ነው ማለት ይቻላል። ይሄኔ ታዲያ ፕሮፌሽናል መድረክ መርገጥ ሊጀምር ነው ማለት ነው። በዚህ መሀል ሀገር ፍቅር “ነጫጭ ሰይጣኖች” መድረክ ሲያገኝ እዛም መስራት ጀመርኩ።

ሰንደቅጥሩ የንባብ አቅም እንዳለህ በመፅሔቶችና በጋዜጦች ላይ በምታወጣቸው ፅሁፎች ማወቅ ይቻላል። ቴአትርና ፊልም ለምን እስካሁን አልፃፍክም?

ፍቃዱድርሰትን በተመለከተ አንድም ስንፍና አንድም የጊዜ እጥረት አለብኝ ብዬ መመለስ እችላለሁ። እውነቱን ለመናገር በአሁኑ ጊዜ ብዙ የማሳልፈው በትወና ላይ ነው። ብዙ ወጎችን ፅፌያለሁ። በ2007 ዓ.ም ካሉኝ እቅዶች አንዱ ወጎቹን በመፅሐፍ ደረጃ አውጥቼ ህዝብ እንዲፈርድ ማሳየት ነው። ሌላው ግን የፃፍኳቸው የመድረክም ሆነ የፊልም ፅሁፎች (ስክሪብቶች) አሉኝ። እንደምንም ብዬ ሰው እንዲያያቸው ለማድረግ የዚህ ዓመት ሌላኛው እቅዴ ነው።

ሰንደቅቅርብ ጊዜ አካባቢ በሳምንት ከሰባት በላይ ቴአትሮችን ትሰራ ነበር። ውጥረቱ ምን ይመስላል፤ እንዴት ተቋቋምከው?

ፍቃዱ በነገራችን ላይ ለምትሰራው ነገር ፍቅር ካለህ እንደዚህ አይነቱ ውጥረት በጣም ደስ ይላል። በወቅቱ እሰራቸው የነበሩት ቴአትሮች ገፀ-ባህሪያት የተለያዩ ናቸው። ለምሳሌ ማክሰኞ በማዘጋጃ ቴአትር ቤት “የብዕር ስም”ን ተጫውቼ፤ ረቡዕ ደግሞ ድንገት ሸዋፈራው ደሳለኝ ታሞ “ጓደኛሞቹን” እጫወታለሁ፤ (በዚህ አጋጣሚ ሰው የተጫወተውን ተውኔት መጫወት ብታጣ ፈታኝ ነው። ለምሳሌ እኔ ሸዋፈራሁ ሰቅሎ የተጫወተውን እኔ ልሰራው ስነሳ በጣም ነበር የከበደኝ። ግን አዘጋጇ ገነት አጥላውም ረድታኝ ተወጥቼዋሁ) ሐሙስ ደግሞ “ትዳር ሲታጠን” አለ ሀገር ፍቅር ቴአትር፤ አርብ ብሔራዊ ላይ “ባብሎን በሳሎን” አለ። ቅዳሜ “ሜዳሊያ” አለ፤ እሁድ ደግሞ “ህንደኬ” አለ። በዛኑ ቀን በብሔራዊ ማታ “ማበዴ ነው” ቴአትርን ምሽት ላይ እሰራ ነበር። በጣም የሚገርምህ እሁድ “ህንደኬ” ላይ ያለውን የጦር አዛዥ ሰርተህ። ወዲያው ደግሞ “ማበዴ ነው” ላይ ያለውን አስተናጋጅ መስራት በጣም ይከብድ ነበር። ሌላ ጊዜ ደግሞ ህንደኬን ሰርተህ ማዘጋጃ ቤት የብዕር ስምን መስራት በጣም ፈታኝ ነበር። ግን ቅድም እንዳልኩህ የምትወደው ነገር ከሆነ በፍቅር ትወጣዋለህ ማለት ነው።

ሰንደቅበተመልካች ዘንድ ንግግራቸው የማይረሳ ገፀ-ባህሪያትን ተጫውተሃል። ለምሳሌ ትዳር ሲታጠን ላይ “ኧረ ባካችሁ!” ይላሉ፤ ባቢሎን በሳሎን ላይ “እየመጣኤ!” የሚለው ይታወሳል። በሜዳሊያ ቴአትርህ ደግሞ የአትሌቱ የንግግር ዘዬ አይረሴ ነው። ላንተ የቱ የተለየ ነበር?

ፍቃዱበጣም የሚገርም ነው። ብዙ ሰዎች መንገድ ላይ ንግግሬን እየጠቀሱ ሰላም ይሉኛል። አንድ ቁም ነገር ልንገርህ ቢኒየም ወርቁ “ሜዳሊያ” ቴአትርን ስንሰራ አትሌቶቹን እስቲ አንዴ ሄደህ እያቸው ነበር ያለኝ። እኔ ግን ለብዙ ጊዜ አብሬያቸው እየሮጥኩ ነበር አነጋግራቸውን ያጠናሁት። በአለም አንደኛ አድካሚ ስራ ሩጫ ነው ብዬ ያመንኩት ያኔ ነው። ማናቸውም እስከ ቴአትሩ ምረቃ ዕለት ተዋናይ መሆኔን አያውቁም ስለነበር አብሬያቸው ስሮጥ ያበረታቱኝ ነበር። ይሄ ለሜዳሊያ ቴአትር ነው። ለባብሎን በሳሎን ስል ደግሞ የሃይለመለኮት መዕዋል “ጉንጉን” መፅሐፍን ደጋግሜ አንብቤያለሁ። የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ”ን ማንበቤ በጣም ነው የጠቀመኝ።

ሰንደቅዝነኝነት ያሳጣህ ነፃነት አለ?

ፍቃዱ በጣም አለ እንጂ፤ ለምሳሌ አሁን ፓስቲ ቤት መግባት አልችልም። እንደርጉዝ ሴት ቢያምረኝ እንኳን ውጬ ዝም ነው (ሳቅ)። መንገድ ላይ ጠቃ-ጠቆ ሙዝ ስታይ እንዴት ብለህ ትበላለህ? አትበላም። መንገድ ላይ የሆነች ቆንጆ ልጅ አይተህ ውበቷን ለማድነቅና ለመልከፍ ራሱ እያማረህ የሚቀር ነገር ሆኗል (ሳቅ). . . በሌላ በኩል ግን እኔ እግረኛ ነኝ። በታክሲ ስሄድ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ናቸው የሚከፍሉልኝ በዚህ ደግሞ የታደልኩ ነኝ።

ሰንደቅበመንገድ ሰዎች አግኝተህ የማትረሳውን ነገር ምን ተናግረውሃል?

ፍቃዱለምሳሌ በጣም ብዙ አይነት ሰው አለ። አንዳንዱ የታክሲ ሂሳብ ይከፍልልህና እስቲ እንደው ከቴአትርህ ላይ አንዷን በልልኝ ሊልህ ይችላል። እሱን ማስረዳት ያንተ ድርሻ ነው። አንድ ሃኪም እዚህ መኪና ውስጥ እንደማያክም (መርፌ እንደማይወጋ) ሁሉ ቴአትርም ሙያ ነው መድረክ ላይ ነው የሚሰራው ትለዋለህ። ማስረዳት ይጠበቅብሃል።

ሰንደቅከፊልም ሥራዎችህ እስካሁን የተከፈለህ ትልቁ ክፍያ ስንት ነው?

ፍቃዱአብዛኞቹ ፕሮዲዩሰሮች ቀጥሎ የምናገረውን አስበው ራሳቸውንም ታዝበው ቅር እንዲላቸው እፈልጋለሁ። ብዙዎቹ ያታልሉሃል፤ ገንዘብህን አይሰጡህም። አንዳንድ የፊልሞች ፕሮዲዩሰሮች አልቅሰው ያሰሩህና አስለቅሰውህ ሳንቲምህን ይሰጡሃል። አንዳንዶቹ እንዲያውም በፖስተር ላይ ሳይቀር ስምህን መፃፍና “ክሬዲት” መናገር አይፈልጉም። ሌሎቹ ደግሞ ገንዘብህን ቆራርጠው ይሰጡሃል። እውነቴን ነው የምልህ ብሬን ያስቀሩብኝ ፕሮዲዩሰሮች በዚህ ሰዓት ቢከፍሉኝ የ300 ሺህ ብር አሪፍ መኪና እገዛ ነበር። በዚህ አጋጣሚ ግን ለኔ አሪፍ ከፋይ ቢኒያም ወርቁ ነው፤ ቢያንስ ጊዜህን በአግባቡ እንድትጠቀም ያደርግሃል። ሌሎቹ ግን ጊዜህንም ገንዘብህንም ይበሉታል።

ሰንደቅብሰራው ብለህ የምትመኘው አይነት ገፀ-ባህሪይ አለ?

ፍቃዱ እንደአጋጣሚ ሆኖ የሰራኋቸው ሥራዎች ሳቅ የሚያጭሩ ገፀ-ባህሪያት ይበዛቸዋል። ከዚህ በኋላ ግን በተለየ መልኩ “ሲሪየስ” ነገሮችን መተወን እፈልጋሁ። ለምን መሰለህ አቅሜን ማሳየት ስለምፈልግ ነው። ይህን ማድረግ የሚችሉ ፕሮዲዩሰሮች ካጣሁ በራሴ ድርሰቶች አማካኝነት ለየት ያለ ገፀ- ባህሪይን ይዤ እመጣለሁ።

ሰንደቅበመጨረሻ ማመስገን የምትፈልጋቸው ሰዎች ካሉ እድሉን ልስጥህ ?

ፍቃዱ በአርቱ ዙሪያ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ላደረጉኝ ጓደኞቼ በጣም አመሰግናለሁ። ከዚህ ውጪ ግን በተለይ ለወንድሞቼና ለእህቶቼ ለመሰረት አሰፋ፣ ለአዜብ ሽፈራው፤ ለዳንኤል አሰፋ በጣም ነው የማመሰግናቸው። ሌላው ደግሞ በአርት ሙያ እንድገፋ ሳይሰስት ይረዳኝ ለነበረው ፍሰሐ በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ። በመጨረሻም አድናቂዎቼን በሙሉ አመሰግናለሁ። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15915 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us