ከላሊበላ በ500 ዓመታት የቀደመው “ውቅር መስቀለ ክርስቶስ”

Wednesday, 24 September 2014 11:43

 

የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 17 ቀን 2007 ዓ.ም የሚከበረውን የመስቀል በዓል ምክንያት በማድረግ በዚህ ሳምንት ለመንፈስም ሆነ ለአካል መዝናኛን ይቸራል ያልነውን “ውቅር መስቀለ ክርስቶስ” ቤተ-ክርስትያንን እናስጎበናችኋለን። ውቅር መስቀለ-ክርስቶስ በአማራ ክልል፤ በዋግኽምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ቤተ-ክርስትያን ነው። የብራና መፅሐፍት፤ የወርቅና የብር መስቀሎችንና የተለያዩ ነዋየ-ቅዱሳትን ጨምሮ አስራሶስት የሚጠጉ ጥንታዊ ቅርሶችን በውስጡ ይዟል።

“ውቅር መስቀለ ክርስቶስ” በአፄ ካሌብ ዘመነ-መንግሥት ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራ ሲሆን፤ ዘመኑም አፄው ግዛታቸውን በአስተዳደሩበት ከ515 እስከ 529 ዓ.ም ሊሆን እንደሚችል የደብሩ ካህንና አስተዳዳሪ አባ መልዓከ ሰላም መርሃ ጥበብ በየነ ይናገራሉ። አፄ ካሌብ ንጉስም ቅዱስም ስለነበሩ በራዕይ ታይቷቸው ይህን ፍልፍል ቤተክርስቲያን ገንብተዋል የሚል ትውፊት በፅኑ የሚታመን ሲሆን፤ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያንም በ500 ዓመት የላቀ እድሜ እንዳለው ተነግሯል። ቤተክርስትያኗ በአሁኑ ወቅት ሶስት መምህራን፣ አስር ቀሳውስትና በአጠቃላይ 28 ዲያቆናት እያገለገሉባት ይገኛሉ። ያም ሆኖ ከአፄ ካሌብ ይልቅ በላሊበላ ዘመነ መንግስት ተገንብቷል ሲሉ የሚከራከሩም ሰዎች አሉ።

የቤተክርስትያኗን የተለያዩ ክፍሎች ለመጎብኘት የታደልን ሲሆን በአጠቃላይም የውስጥ ገፅታው በሰባት ክፍሎች የታነፀ እንደሆነ ተነግሮናል። በዚህም እንደአባ መላዕከ ሰላም ገለጻ፤ የመጀመሪያ ሆኖ ያገኘነው “ቅኔ ማህሌት” የሚባለውን ነው። ይህ ቦታ አባቶች በዝማሬና በሽብሸባ ማህሌት ቆመው ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ሥፍራ ነው።

በቅዱሳን ምስሎችና በመጋረጃ የታጠረው ሁለተኛው ሥፍራ ደግሞ “ቅድስት” ተብሎ ይጠራል። ይህ ስፍራ ቅዳሴና ፀሎት የሚከወንበት ነው። በዚህም ውስጥ አስደናቂ በሆነ ጥበብ የተሰሩ መስቀሎች ሲኖሩ፤ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከሚገኙት አምስት ቋሚ አምዶች መካከል አንዱ ይገኝበታል።

“ውቅር መስቀለ ክርስቶስ” በውስጡ ሰባት ለተለያዩ ተግባራት የሚውሉ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ በስርዓተ-ቤተክርስትያን መሰረት ሶስት በሮችም አሉት። አንደኛው የሴቶች መግቢያ፤ ሁለተኛው የወንዶች መግቢያ ሲሆን ሶስተኛውና በምስራቃዊው በር በኩል ደግሞ የካህናት መግቢያ ሆኖ ተሰርቷል።

ይህቺ ቤተክርስቲያን በወቅቱ ከምትሰጠው አምልኳዊ ተግባር በተጨማሪ የተለያዩ የአገራችን ነገስታት ያረፉባትና በርካታ ደብዳቤዎችን የተላላኩበት እንደነበር አስጎብኚያችን አባ መላዕከ ሰላም መርሀ-ጥበብ በየነ ተናግረዋል። ለዚህም እንደማሳያ ከአፄ ቴዎድሮስ ሞት በኋላ ኢትዮጵያን ለጥቂት ዓመታት የገዙት የቀድሞው ዋግሹም ጎበዜ በኋላም በንግስና ስማቸው አፄ ተ/ጊዮርጊስ አፅም አርፎ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስከ አፄ ኃ/ስላሴ ድረስ ዋግን ያስተዳደሩ የነበሩ ነገስታት አፅማቸው በክብር ተቀምጦ የሚገኘው በዚሁ በውቅር መስቀለ ክርስቶስ ነው። ለዚህም አፅማቸው ሳይፈርስ እስካሁን መቆየት በርካታ ትውፊታዊ መላምቶች ይቀርባሉ።

የበርካታ የአገው መሳፍንቶች አፅም በቤተ-ክርስትያኑ የሚገኝ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል ዋግ ሥዩም ክንፈ ሚካኤል ይገኙበታል። በዘመናቸው ለቤተክርስቲያኗ ትልቅ መሰዋዕት በመክፈላቸውም ይታወቃሉ። ከፈፀሟቸው አብይ ተግባራት መካከልም ለቤተክርስቲያኗ በርካታ የብራና መፅሐፍትና መስቀሎች እንዲበረከቱ አድርገዋል የሚለው ይገኝበታል።

ሌላኛው ደግሞ ደጃች ፓሪስ ናቸው። ደጃች ፓሪስ በቆቦ ይኖሩ የነበሩና አፅማቸው በክብር በቤተክርስቲያኗ ያረፉ ናቸው። ቀጥሎ ያየነው የዋግ ስዩም አርአያ ክርስቶስ ሲሆን እሳቸውም ስዕልን ጨምሮ በዘመናቸው በርካታ የክብር ዕቃዎችን ለቤተ-ክርስትያኒቱ አበርክተዋል ተብሎ ይታመናል። የዋግ ሥዩም ወሰን እና የእመቤት ላቀችም አፅም ያረፈው በዚሁ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው። እመቤት ላቀች፤ የዋግ ሥዩም ገ/መድህን ልጅ ሲሆኑ የምስራቅ ጎጃም አስተዳዳሪ የነበሩት የንጉስ ተ/ሃይማኖት ባለቤትና የአፄ ተ/ጊዮርጊስም እህት እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል። አባታቸው ዋግ ሥዩም ገ/መድህን ለቤተክርስትያን ወርቀ-ወንጌል መፅሐፍን በማበርከታቸውም እንደሚታወቁም ተነግሯል።

በውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተክርስትያን ውስጥ ከሚታዩት አስደናቂ ነገሮች አንዱና ሌላኛው ደግሞ የመሬት ውስጥ ለውስጥ መንገድና ዋሻ ነው። “ይህ መንገድ በመሬት ውስጥ ላሊበላ ውቅር ቤተክርስትያን እንደሚያደርስ ይታመናል” ያሉት አባ መላዕከሰላም መርሃ-ጥበብ በየነ፤ ከአባቶች ውግዘትና ከአየር እጥረት ጋር በተያያዘ ማንም ወደ ውስጥ ዘልቆ እንደማይገባ ተነግሯል። መንገዱ በሁለት (ወደሰሜን እና ወደደቡብ) የተከፈለ ሲሆን ወደላሊበላና ወደ አክሱም የሚወስድም እንደሆነ ይታመናል። ይህ መንገድ ውስጥ ለውስጥ ተፈልፍሎ የተሰራውም ቅዱሳን አባቶች አለማውያን ባለመሆናቸውና የተሰወሩ በመሆናቸው በስውር የሚጓዙበት ነው ተብሎ እንደሚታመንም አስጎብኚያችን ያስረዳሉ።

በአባ መልዓከሰላም አቅም ወደውስጥ አምስት ሜትር ያህል ብቻ መሄድ እንደተቻለና ከዚያም በኋላ የተዘጋ በር ስለመኖሩ እንዲሁም ከ30 የሚያንሱ የራስ ቅሎችን መቁጠራቸውን እማኝነት ሰጥተውናል። ሌላው የዋሻው መሰራት ምክንያት ተደርጎ የሚታመነው አፄ ካሌብ የከበሩ ንብረቶችን ያስቀመጡበት ነው ተብሎም እንደሚገመት ይነገራል።

በጉብኝታችን ወቅት በቤተክርስትያኑ የሚገኙት ቅርሶች ከላሊበላ ጋር መመሳሰላቸውና በእድሜም ቢሆን ከላሊበላ በ500 ዓመት ቀድመው የውስጥ ለውስጥ ዋሻ (መንገድ) መሰራቱን በተመለከተ ተጨባጭ የሆነ ምላሽ ስለመኖሩ ጥያቄ አንስተን ነበር። በተለይም ውቅር መስቀል ክርስቶስ ቤ-ክርስቲያን ከላሊበላ ውቅር አብያተክርስትያን በ500 ዓመት የሚቀድም ከሆነ የዋሻው መንገድ እንዴት ቀድሞ ተሰራ? የሚል ጥያቄ ብናነሳም፤ አባ መላዕከሰላም ግን መልሶች ሁሉ በትውፊት ላይ የተመሰረቱና ከአባቶች በተገኘ ታሪካዊ ምላሽ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ለዚህም “ለቅዱሳን የሚሰወር ምስጢር የለም” በሚል ጥቅል መልስ የተሰጠበት ሆኗል።

ትኩረትን ከሚስቡት የቤተክርስቲያኗ ቅርሶች አንዱና ዋንኛው አፄ ካሌብ ቤተክርስትያኑን አንጸው እንደጨረሱ አገልግሎት ላይ የዋለው የመጀመሪያው ተአምረ ማርያም በዚያ መገኘቱ ነው፡ ተዓምረ ማርያም ሌሎቹ ብራናዎች ተፅፈው አገልግሎት ላይ እስኪውሉ ድረስ በብቸኝነት ለቅዳሴና ለስብከት መዋሉን አባ መላዕከሰላም ያስረዳሉ። የመፅሐፉ እድሜም ከ1ሺ400 ዓመት በላይ እንደሆነ ይገመታል ብለውናል። በአሁኑ ወቅት ቤተክርስቲያኗ የወረቀት መፅሐፍትን ስላገኘች ተዘውትሮ ይህ የመጀመሪያ የተባለው ተአምረ-ማርያም አገልግሎት ላይ እንደማይውል ሲነገር፤ ነገር ግን በዓመት ለስቅለት በዓል እንደሚወጣም ተጠቁሟል።

ከዚህ መፅሐፍ በተጨማሪ ወርቀ-ወንጌልም ይገኛል። ይህ መፅሐፍ በተለየ መልኩ የቅዱሳን ስምና እግዚያብሔር፣ ክርስቶስና ማርያም የሚሉ ስሞች በወርቅ የተፃፉ ሆነው ይታያሉ። ይህን መፅሐፍ እመቤት ላቀች ያበረከተችው እንደሆነ ሲታመን፤ የሉቃስ፣ የማርቆስ፣ የማቲዎስና የዮሐንስ ወንጌሎች ተካተው የቀረቡበት ነው። ፅሁፉም በግዕዝ ቋንቋ የተፃፈ ነው። ከብደቱ በእጅጉ ከፍ ያለ ከመሆኑም የተነሳ ቀሳውስት ሊያነቡት ሲሉ ከሁለት በላይ ዲያቆናት ደግፈውት መያዝ ይጠበቅባቸዋል። ሌላው በዚህ ቤተክርስቲን የሚገኘው ጥንታዊ መፅሐፍ ተአምረ-ኢየሱስ ነው። ይህም ጌታ ኢየሱስ ከልጅነቱ እስከ እውቀቱ የፈፀማቸውን ተዓምራት የሚያስረዳ መፅሐፍ ነው።

“በውቅር መስቀለ-ክርስቶስ” ውስጥ ከሚገኙት ጥንታዊ ቅርሶች መካከል የግሪክ ቤተክርስትያን ያበረከተችው የወርቅ መስቀል በይበልጥ ይታወቃል። አርአያ ክርስቶስ በ15 ክፍለ ዘመን አበርክተዋል ተብሎ የሚታመነው ይህ መስቀል በልዩ መስህብነት በቤቱ ይገኛል።

    ብዙም እውቅናን ያልተቸራት “ውቅር-መስቀል ክርስቶስ” ቤተክርስቲያን በይበልጥ ታውቃ፣ ጎብኚዎችን በመሳብ የአካልና የመንፈስ ማረፊያ ትሆን ዘንድ ከፌዴራል መንግስት ጋር ጭምር ተባብሮ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተስፋ ይጣልበታል ያሉት የደብሩ አስተዳዳሪ አባ መልዓከ ሰላም መርሃ-ጥበብ በየነ፤ ትኩረት ብታገኝ ለዞኑም፣ ለክልሉም ሆነ ለአገር የሚኖረው ፋይዳ ቀላል አለመሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
12189 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us