“ለዛ” ያላቸው ምርጦች

Wednesday, 08 October 2014 12:29

 

ባሳለፍነው ቅዳሜ መስከረም 24 ቀን 2007 ዓ.ም ለጣሊያን የባህል ማዕከል አንድ ዓመታዊ የሽልማት ፕሮግራም ተካሂዶ ነበር። በሸገር ኤፍ ኤም የለዛ ፕሮግራም አሰናጅነት ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ የተካሄደው ይህ የዓመቱ ምርጦችን የመሸለም ሥነ-ሥርዓት በብዙዎች ዘንድ ደማቅ እንደነበር ተነግሮለታል። በእውነትም ካለፈው ዓመት በተሻለ የሚታይ ለውጥ ያመጣ ፕሮግራም ሆኖ ተጠናቋል።

በዓመቱ ውስጥ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በትወና፣ በምርጥ አልበምና በምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍን ጨምሮ በልዩ ተሸላሚነት ተመርጠው ለወጡ ባለሙያዎች በዝግጅቱ ላይ ዕውቅና የሚሰጥ ሽልማት መሰጠቱን ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ ተናግሯል። የዕጩዎቹ የመጨረሻ ውጤት ይፋ የሚሆነው 40 በመቶ ለዘርፉ ቅርበት ካላቸው ባለሙያዎች ሲሆን፤ ቀሪው 60 በመቶ ደግሞ የአድማጮቹን ድምፅ መሠረት ያደረገ ነው። ይህም ከአምናና ካቻምናው ጋር ሲነፃፀር ለውድድር የቀረቡትን ሥራዎች ከስሜት ውጪ ሙያዊ ይዘታቸውን የሚመዝን የባለሙያ ዳኝነት መኖሩ ይበል የሚያሰኘው ነው።

በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአድማጮች ምርጫ ሆነው በመጨረሻዎቹ የዕጩዎች ዝርዝር ስር የገቡ ባለሙያዎች በጣሊያን የባህል ማዕከል ሲገኙ፤ መድረኩ በሙዚቃ ትርኢት ደምቆ ነበር።

የሽልማት ፕሮግራሙን ለሰንደቅ አንባቢያን እንዲመች አድርገን ስናቀርበው የዓመቱ ምርጥ ተብለው በዕጩነት የቀረቡት ተዋንያን፣ የተመረጡት አልበሞች፤ የተመረጡት ነጠላ ዜማዎች፤ የተመረጡት የሙዚቃ ቪዲዮዎች፤ የተመረጡት ፊልሞችና የተመረጡት አዲስ ድምፃዊያን ዕጩዎች ዝርዝር በአዳራሹ ለታደሙ ሰዎች እንዲተዋወቁ ተደርጓል።

በዚህም መሠረት ከሰባቱ የዕጩነት ዘርፍ መለያዎች ውጪ የሆኑና በየዓመቱ በተለየ መልኩ ሳይታሰብ የሚበረከቱ ሽልማቶች ይፋ ሆነዋል። ባለፈው 2006 ዓ.ም በተካሄደው የሸገር ሬዲዮ የለዛ ፕሮግራም አድማጮች ምርጥ ሽልማት ሲደረግ ታዋቂውና አንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ የህይወት ዘመን ምርጥ ድምፃዊነት ክብርን ማግኘቱ ይታወሳል። በዚያን ወቅት በመድረኩ ተገኝተው ሽልማት እንዲሰጡ ከተጋበዙት የክብር እንግዶች መካከል አንዱ የነበረው ድምፃዊ መሐመድ አህመድ በዘንድሮው የለዛ የህይወት ዘመን ድምፃዊ ተሸላሚ ሆኗል። ሆኖም መሐመድ አህመድ በውጪ ሀገር በመሆኑ ምክንያት እንደ አምናው በመድረኩ አለመገኘቱ ቁጭትን ፈጥሯል።

ሌላው በተመሳሳይ የተካሄደው የልዩ ሽልማት ሥነ-ስርዓት ታዋቂውን የሙዚቃ ሰው አየለ ማሞን ያስታወሰና ክብርም ያሰጠ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም የህይወት ዘመን ሙዚቀኛ ክብር ተሸላማሚ ሆነው ሽልማቱ እንዲበረከትላቸው ሆኗል።

በመቀጠል በተያያዘ ሊነሳ የሚገባው የምርጥ አዲስ ድምፃዊ ዘርፍ ነው። የፕሮግራሙ መስራችና ባለቤት ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ ስለ አዳዲስ ሙዚቀኞች በዚህ ዓመት በተለየ መልኩ መቅረብ መጀመሩን አስፈላጊነት ሲያስረዳ፤ “አዳዲሶቹ ድምፃውያን በአንጋፋዎቹ እንዳይዋጡ እና እንዲበረታቱም ሲባል የተጀመረ ዘርፍ ነው” ይላል።

በዚህ “የአዲስ ድምፃዊ” ዕጩ ዝርዝር ውስጥ የተቀመጡት፤ ዳንኤል ፍስሃዬ፣ አሳየኝ አለሙ፣ እመቤት ነጋሲ፣ ተመስገን ገ/እግዚአብሔርና ሚካኤል ለማ ሲሆኑ፤ በዘርፉ የአድማጮችና የባለሙያዎች ምርጥ ሆኖ ሽልማቱን ያገኘው፤ ባሳለፍነው ዓመት “ደስ ብላኛለች” የተሰኘ አልበም ያወጣው ድምፃዊ ሚካኤል ለማ ደምሰው ሆኗል።

ከሙዚቃው ዘርፍ አንጋፋዎቹን አካቶ በአዳዲስ ስራቸው ውድድሩን ያካሄደው ምርጥ አልበም ዝርዝር ውስጥ ስለሺ ደምሴ - ያምራል ሀገሬ፤ ብዙአየሁ ደምሴ - ሳላይሽ፤ አስቴር አወቀ - እወድሃለሁ፤ ሚካኤለ ለማ - ደስ ብላኛለች፤ አብርሃም ገ/መድህን - ማቻይስማኒሎ፤ ተመስገን ገ/እግዚአብሔር - ኮራሁብሽ የተሰኙ ናቸው። በዚህ ዘርፍ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) በያምራል ሀገሬ አልበሙ ተሸላሚ ሆኗል።

በለዛ ፕሮግራም የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ የእኛዎቹና አስቴር - ጣይቱ፤ አቤል ሙሉጌታ - ልብ በ40 ዓመት፤ ዘሪቱ ከበደ - የወንድ ቆንጆ፤ ጃኪ ጐሲ - ፊያሜታ፤ በኃይሉ አጐናፍር - አዩ እሹሩሩ እንዲሁም አሸፊው የግርማ ተፈራ - መቼ ትመጫለሽ ሆኗል።

በምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍ በለዛ አድማጮችና በባለሙያዎቹ አሸናፊ የሆነው የጃኪ ጐሲ - ፊያሜታ ሲሆን፤ በዘርፉ ዕጩ ሆነው የቀረቡት የተመስገን ገ/እግዚአብሔር - ኮራሁብሽ፤ የናቲ ማን - ጭፈራዬ፤ በኃይሉ አጐናፍር - አዩ እሹሩሩ፤ አስቴር አወቀና የእኛዎቹ ጣይቱ ነበሩ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢንዱስትሪው እየጐለበተ መጥቷል፤ ፊልም። በፊልም ዙሪያ ደራሲው፣ ተዋናይ፣ ፀሐፊው፣ ዳይሬክተሩ፣ የሙዚቃና የቀረፃ ባለሙያዎቹ እንዳሉ ሆነው ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ ተመልካች የዚህ ዘርፍ አንዱ አካል ነውና በለዛ የአድማጮች የዓመቱ ምርጥ ፊልምን ለማወቅ ያልጓጓ አልነበረም። በዕጩነት የቀረቡት ፊልሞች ደግሞ ረቡኒ፣ በጭስ ተደብቄ፣ ትመጣለህ ብዬ፣ ህይወትና ሣቅ፣ አይራቅ ነበሩ። ዳሩ ግን እንደተጠበቀው “ረቡኒ” ፊልም አሸናፊ ሆኗል። እዚህ’ጋ እንደተጠበቀው ያለነው ከሽልማቱ በፊትም ቢሆን ይህ ፊልም በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅና አነጋጋሪ ሆኖ የሲኒማ ቤቶችን ደጃፍ በሰልፍ ያጨናነቀ ከመሆኑ አንፃር ነው። ዳይሬክተሯና ፀሐፊዋ ቅድስት ይልማ ከዚህ አንፃር በሚገባ ተሳክቶላታልና ሽልማቱ ይገባታል ማለት ይቻላል።

ይህ ፊልም ከምርጥነቱም ባሻገር በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ሩታ መንግስተአብን ተሸላሚ አድርጓታል። ሩታ በፊልሙ ውስጥ ባሳየችው ድንቅ ብቃት የተነሳ ብዙዎችን ያሳመነ ስራ ሰርታለች። በዚህም አብረዋት በዕጩነት ከቀረቡት ማህደር አሰፋ (በአይራቅ)፤ ሔለን በድሉ (በዘውድና ጐፈር)፣ ዘሪቱ ከበደ (በቀሚስ የለበስኩለት) እና ሠላማዊት ተስፋዬ (በጭስ ተደብቄ) ዝርዝር አሸናፊ ሆናለች።

በወንዶቹ ዘርፍ ምርጥ የዓመቱ ተዋናይ ሆኖ የተሸለመው መሳይ ተፈራ ሲሆን፤ ፊልሙ በምርጥ ዕጩነት ከቀረቡት መካከል አንዱ የሆነው “ትመጣለህ ብዬ” ነው። በዚህ ዘርፍ፤ ይስሃቅ ዘለቀ - ቀሚስ የለበስኩለት፣ ሚካኤል ሚሊዮን - አይራቅ፣ ታሪኩ ብርሃኑ - ህይወትና ሣቅ፣ ሰለሞን ቦጋለ - በሦስት ማዕዘን እና ግሩም ኤርሚያስ - በጭስ ተደብቄ ነበሩ።

እንዲህም እንዲያም

በአገራችን በየዓመቱ ከሚካሄዱ ኪነ-ጥበባዊ የሽልማት ሥነ-ስርዓቶች ውስጥ ጥቂቶች የዓመታትን ዳዴ ጀምረዋል። ከእነዚህ “ይበል” ከሚያሰኙ የሽልማት ፕሮግራሞች መካከል በሸገር ኤፍ ኤም የለዛ ፕሮግራም አማካኝነት የሚካሄደው የሽልማት ሥነ-ስርዓት አንዱ ነው። ካለፉት ሦስት ዓመታት ልምዶቹ በመነሳትና ትችቶችንም ሰምቶ በማረም ዘንድሮ የተሻለ ሆኖ ታይቷል።

በተለያዩ ዘርፎች ክብር ለሚገባቸው የአገራችን አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መሸለሙ መልካም ነው። ይህም የህይወት ዘመን ተሸላሚዎችን ልብ ይሏል። ነገር ግን በሙዚቃው ዘርፍ ልክ እንደ ወንድ ተዋንያኑና ድምፃውያኑ ሁሉ ሴቶቹም የራሳቸው መወዳደሪያ ቢያገኙ መልካም ነው። ለምሳሌ በምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ ዘሪቱ ከበደ እና የኛዎቹ ከአስቴር አወቀ ጋር ቀርበዋል። በአዲስ አልበም ዘርፍ ደግሞ እመቤት ነጋሲ - ስትቀርብ፤ የምርጥ አልበም እጩዎችን፣ አስቴር አወቀ ተቀላቅላለች። ነገር ግን እነዚህን በተለየ መልኩ በሴቶች ዘርፍ ማወዳደር ቢቻል ጥሩ ይሆን ነበር።

በተረፈ ግን የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጥ ተሸላሚዎች ቁጥርና ጥራት እንዲህም እንዲያም እያለ እዚህ መድረሱ መልካም ነው ለማለት እንወዳለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
12332 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us