አወይ! “ኑሮ እና አዲስ አበባ”

Thursday, 16 October 2014 14:14

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን ላይ የሚያጠነጥኑ በርካታ የወግ መጽሐፍት ለንባብ በቅተዋል። በርግጥም ለአፍታ ቆይታ የሚነበቡ አጫጭር ወጐች፤ ረጅምና ወጥ ሥራዎችን ማንበብ ለሚያታክተው አይነት አንባቢ ብርቱ መነሻዎች ከመሆናቸውም ባሻገር የመዝናኛና የመረጃ ምንጮች እየሆኑ መጥተዋል ማለት ይቻላል። ዳሩ ግን አብዛኞቹን የማኅበራዊ ወጐች መጽሐፍት በደምሳሳው ስንገመግማቸው በእጅጉ የሚያመሳስሏቸው ሁለት ነገሮች ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው መቼታቸው ወይም የጉዳያቸው ማጠንጠኛ ጊዜና ቦታ አዲስ አበባን ያማከለ መሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የሚበዙት ከጋዜጣና ከመጽሔት ተሰባስበው የቀረቡ መሆናቸው ነው።

ከአለፍ ገደም የእነዚህ መጽሐፍት ወዳጆችና አንባቢያን የሚያቀርቧቸው ቅሬታዎችና ይሁንታዎችም በዚህ አጋጣሚ ቢጠቀሱ መልካም ነው። አንዳንዶቹ የጽሁፎቹ ትኩረት አዲስ አበባ ብቻ መሆኑ የፀሐፊው ልምድና ገጠመኝን መሰረት ያደረገ መሆኑን ቢሰማውም ጽሁፎቹ በብዛት ከጋዜጦችና መጽሔቶች ተጠራቅመው በመጽሐፍ መልክ ስለመቅረባቸው ግን “የፈጠራ ንጥፈት ነው” ይላሉ። በአንፃሩ ደግሞ ሁሉም ሰው ጋዜጦችና መጽሔቶችን በየጊዜው ሊያገኝ አይችልምና በዚህ መልክ ሰብሰብ ብለው ማግኘቱ ጠቀሜታው የጐላ ነው ባዮች አሉ።

ለዛሬ መዝናኛችን ላይ የምንቆይበትና ዳሰሳ የምናደርግባት መጽሐፍ ባሳለፍነው 2006 ዓ.ም መጨረሻ ለንባብ የበቃው የሄኖክ ግርማ፤ “ኑሮ እና አዲስ አበባ” ነው። ደራሲው ከዚህ ቀደም “ስልክሽን ልያዘው?” እና “ፊት ለፊት ስንኞች” የተሰኙ ሁለት መጽሐፍትን በአንድ መድብል አቅርቧል። ይህ በርካታ ስራዎችን በአንድ የማቅረቡ ትጋት ነው መሰል፤ “ኑሮ እና አዲስ አበባ” በተሰኘው በዚህ መጽሐፉም በርካታ ጉዳዮችን አንስቷል። በመጽሐፉ ውስጥ ሃያ አምስት የሚደርሱ አዝናኝና ቁምነገር አዘል ስራዎቹን አካቶ አቅርቧል። ስራዎቹንም ማኅበራዊ ወጐች፣ ትዝብታዊ ጨዋታዎች፣ እውነተኛ ታሪኮችና ሐተታ ጽሁፎች ናቸው ሲል ያስተዋወቃቸዋል። ይህም ፀሐፊው በአንድ ዘውግ ስር የሚቀነበቡ ሥራዎችን ለማቅረብ ምን ያህል እንዳስቸገረው የሚያሳይ ነው።

በመጽሐፉ “ከዘሪሁን ህንፃ እስከ ቺቺንያ አትላስ” በሚሰኘው ረጅም ርዕስ ይጀምራል። በዚህ ስራው ውስጥ ፀሐፊው ውሎና አዳሩን ሳይቀር በቺቺኒያና አካባቢው አድርጐ አይቻቸዋለሁ ያላቸውን “ጉድ!” የሚያሰኙ ታሪኮች ይተርክልናል። ስለአካባቢው ሲገልጽም፤ “ይሄ ሰፈር እንደ እነ አራት ኪሎ፣ ውቤ በረሃ፣ ሰራተኛ ሠፈር ወይም ደግሞ ገዳም ሠፈር ዛሬ በትዝታ የሚወራለት የዳጎሰ ታሪክ ያጠራቀመ ሠፈር አይደለም። ይልቁንም ሠፈሩ በአሁኑ ወቅት ለነገ ትዝታ መሆን የሚችል ታሪክ እየተሰራበት ያለ የሠፈር ክልል ነው” ይለናል። (ገፅ፤11)

ስለአካባቢው ሰዎችና አኗኗር ሲገልፅ ደግሞ፤ “በዚህ ከዘሪሁን ህንፃ ቺቺንያ አትላስ ባልኩህ ሠፈር ውስጥ ሚሊዮን ብር ያሉት ሰው አለ፤ ሺህ ብሮች ያሉት ሰው አለ፤ አንድ ብር የሚቀፍል ሰው አለ፤ ሠራተኛ አለ፤ ጡረተኛ አለ፤ ስራ ፈት አለ፤ እንዲሁም ደግሞ ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ የመጣ ሰው አለ፤ ከዓረብ ወይም ከክልል የመጣም አለ፤ እንዳትፈራ እንጂ በዚህ ሰፈር አደገኛ ማጅራት መቺም አለ” ሲል ይዘረዝራል። (ገጽ፤ 13)

የሰፈሩን ጓዳ ጐድጓዳ ሁሉ ከቀን እስከ ሌሊት በእግረ-ፊደል የሚያስጉዘን ፀሐፊው ቺቺኒያን ዘና በሚያደርግ መንገድ ሲገልፃት፤ “ቺቺንያ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ድብልቅልቅ ነው የሚለው። እነዚያ ስፋታቸው በሀብታም ሰው ቁምሳጥን ልክ የሚገመተው መጠጥ መሸጫ ቤቶች ከጂፓስ ወይም ከሲዲ ማጫወቻ የሚወጣውን ሙዚቃ ከፍ ባለ ድምጽ እያሰሙ፤ እያንዳንዳቸው በትንሹ አራት እና አምስት ገላቸው ለገበያ ያቀረቡ ሴቶችን በራቸው ላይ ኮልኩለው ይታያሉ” (ገጽ፤ 23)

በመጽሐፉ ውስጥ ትኩረትን ከሚስቡ ንዑስ ርዕሶች መካከል “ሴቶች እና ቦርጭ” የሚለው ይጠቀሳል። በተዋዛና ፈገግ በሚያሰኝ መንገድ የሚጀምረው ይህ ጽሁፍ፤ ቦርጭ የቱን ያህል የሴቶች አንገብጋቢ ችግር እንደሆነ ያትታል። “ያለማጋነን ነው የምነግርህ ቦርጭ ለሴት ልጅ የለየለት ጠላቷ ነው! ሴትን ልጅ ቦርጭ ሲቆራኛት ያበሳጫታል፤ ይረብሻታል፤ ሰላሟንም ይነሳታል ብዬ የምልህ ዋሸሁ ብዬ ጭራሽ ሳልሸማቀቅ ነው” ይለናል። (ገጽ፤ 31)

ፀሐፊው በዚህ አጭር ጽሁፍ በድርብቡም ቢሆን፤ ስለቦርጭ ምንነት፣ መንስኤና መፍትሄ አገኘኋቸው ከሚላቸው ጥናቶች በመነሻት ይዘረዝራል። ሴቶችም እርስ በእርሳቸው መረጃን ተለዋውጠው ከቦርጭ ሀሜት ይድኑ ዘንድ አጥብቆ ይመክራል። ከዚህ ጽሁፍ ለመውጣት ከማኮብኮባችን በፊት ግን የምትከተለዋን አንቀጽ እንካችሁ፤ “አንቺ ቦርጫም! መባል ደግሞ በሴት ልጅ ላይ የሚፈጥረው ‘ኢ-ልማታዊ’ ስሜት ገምተው። አንድ ጊዜ አንድ በርቀት የማውቀው ሰው በፌስ ቡክ ገፁ ምን ሲል ሰማሁት መሰለህ፤ ‘ሴቶች ቦርጭን የሚፈሩትን ያህል ፈጣሪያቸውን ቢፈሩ ገነትን በወረሱ  ነበር’ ” (ገጽ፤ 35)

በቀጣዩ ርዕስ ስር የሚዘረዘረው ዘመነኛ ነን ባይ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን በሰላ ትችት የሚጐነትል ነው። “ቅንጥብጣቢ ምልከታዎች እና ወጋ ወጋዎች” በተሰኘው በዚህ ጽሁፍ ርዕስ ስር፤ በተመሳሳይ ልዝዝ ዜማ እና በተመሳሳይ የጾታ ፍቅር ላይ ባተኮሩ ግጥሞች ስለሚያቀነቅኑ ድምፃውያን የትችት መአቱን ያወርዳል። ከናፈቅሺኝ/ከኝ፤ ከቀረሽብኝ/ህብኝ”፤ ከአበድኩልሽና ከሞትኩልህ አይነት ግጥሞች ወጥታችሁ ሀገራዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸውን ጠንካራ ግጥሞች በዘፈኖቻችሁ መካከል ካላበዛችሁ ዋጋም የላችሁም ነው የሚላቸው።

ከዘፈኖቹ ባልተናነሰ መልኩ ፊልሞቻችንም የዚሁ ተወራራሽነትና የአንድ ዜማ ረገጣ አለቀቃቸውም የሚለን ፀሐፊው፤ “ብዙዎቹ ያየኋቸው ፊልሞች ላይ አጠቃላይ የፊልሙ ታሪክ በእነሱ ዙሪያ የሚያጠነጥንባቸው ውብ የሆኑ ሴቶች አሉ፤ የቅንጡ ኢትዮጵያውያን ኑሮ ፊልሙ ላይ ተፈልጐ አይታጣም፤ የፊልሙ ዲያሎግ አስቂኝ ቃላትን እንዲይዝ ይደረጋል፤ የፊልሙ ሰሪዎች በመጽሔት ላይ ቃለ-መጠይቅ ሲደረግላቸው ፊልሙን ለመስራት ብዙ መቶ ሺህ ብር እንደወጣበት ይናገራሉ” (ገጽ፤ 42) ሲል በስላቅ ያሽሟጥጣቸዋል። እናም የአዲስ ታሪክ እጥረት በእጅጉ እንደሚታይባቸው በመጥቀስ ይተቻል።

በዚሁ ቅንጥብጣቢ ብሎ በሰየመው ምልከታ ውስጥ ንባብን በተመለከተ እንደሚከተለው ያለ ቁምነገር ያትታል። “የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ ባለበት ቦታ ሆኖ ማወቅ ለፈለገ ሰው ግን ማንበብ ዋነኛ አማራጩ ነው። የሚያነብ ሰው ቤቱ ተቀምጦ ስለተለያዩ አገራት ታሪክ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የስልጣኔ መጠን ለማወቅ ይችላል” ይለናል (ገጽ፤ 44)። በዚሁ ርዕሱ ስር ግን አንድ አስገራሚ “መረጃ” አመልክቶን ያልፋል። የመጽሐፍት አንባቢን ቁጥር ማነስና የመጽሐፍት ሕትመትን ጉዳይ አትቶ ሲያበቃ፤ “በአሁኑ ጊዜ ባለው እውነታ አንድ መጽሐፍ ከአንድ ሺህ ኮፒ እስከ ሦስት ሺህ ኮፒ ድረስ ታትሞ ተሸጦ ለማለቅ አምስትና ስድስት ዓመት ይፈጅበታል” (ገጽ፤ 46) ይላል። ይህ የፀሐፊው ምልከታ ቢሆንም ውጤቱ እውነት ከሆነ ግን ምን ያህል የንባብ ባህላችን የቁልቁለት መንገድ ላይ እንደሚሄድ የሚያሳይ ነው።

“ኑሮ እና አዲስ አበባ” በተሰኘው የመጽሐፉ አብይ ርዕስ ስር ፀሐፊው በርካታ አዲስ አበባን የሚመለከቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን እያነሳ ይዳስሳል። “ኑሮ የትም ቦታ ላይ ይኖራል” ሲል የሚንደረደረው ፀሐፊው በአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል የሰማይና የምድር ያህል ያለውን የኑሮ ልዩነት በሚነካና በሚዳስስ ነገር እያመላከተ “ወይ ጉድ!” ያሰኘናል። የሚበሉትና የሚተኙበት አጥተው በችግር የሚማቅቁ ዜጐች ቁጥር የትየለሌ በሆኑባት አዲስ አበባ አውሮፓን በሚያስንቅ ኑሮ የሚንደላቀቅም “ባለሀብት” ስለመኖሩ ይተርካል። “መንግስት ቢፈቅድላቸው ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን እንኳን ቁርሳቸውን ናይሮቢ በሚገኝ ዘናጭ ሬስቶራንት ተመግበው እራታቸውን አዲስ አበባ መመገብ የሚችሉ ሀብታሞች ተፈጥረዋል” (ገጽ፤ 47) ባይ ነው።

ያም ሆኖ አዲስ አበባ የብዙዎችን ቀልብ ማሸፈት የምትችል ተወዳጅ ከተማ ናት ይላል። ኑሮ የቱንም ያህል ውድ ቢሆን፤ የቤት ኪራይ ቢያንገበግብም፣ የትራንስፖርቱና የምግቡ፣ የመዝናኛውና የመናፈሻው ነገር “ድንቄም አዲስ አበባ!” የሚያሰኝ ቢሆንም፤ አዲስ አበባ ግን አሁንም የሕዝብ ፍቅር ያላት ከተማ እንደሆነች ፀሐፊው ያምናል።

በሚቀጥለው ርዕሱ አረቄ ቤት ታውቃለህ? ሲል ጀምሮ ስለ አረቄ ጠማቂዎችና ስለ አረቄ ሱሰኞች እየተረከ ዘና አድርጐ ይዘልቃል። በዚህም የአረቄ ቤት ጨዋታዎች አይነትና ብዛት ይተርካል። ፀሐፊው ቅፈላንም ቢሆን አልረሳም “ዘመናዊ ልመና” ይለዋል። የቅፈላ አይነቶች፤ የቀፋዮች ሁኔታና አገባባቸውን ሁሉ በቅርበት ያጠና ይመስል ይተርክልናል። በዚህም ወይ አዲስ አበባ እያልን በአግራሞት እንድንዝናና ያደርገናል።

“ስለወሬ ሲወራ” የሚለው ፀሐፊው፤ “ወሬን ወሬኞች ይፈጥሩታል” ይለናል። የወሬ አፈጣጠርና ስለወሬኞች አይነት በዝርዝር ይወራል። እዚህ’ጋ ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፈው ርዕሰ-ጉዳይ የስደት ህይወትን የቃኘበትና “ልጆቹ፣ ልጆቹ” የተሰኘ ርዕስ የሰጠው ጽሁፍ ነው። ስደትን ከሀገር ቤት እስከ አዲስ አበባ፤ ምን እንደሚመስልና በተለይም የልጆችን በደል እያስቃኘ የስደተኞችን ህይወት ያሳየናል።

ደራሲ ሄኖክ ግርማ በዚህ ሁለተኛ መጽሐፉ በርካታ ጉዳዮችን አንስቷል። ለዚያም ይመስላል ርዕሶቹ በእጅጉ ሰፍተው የመረጃ እጥረት ሲጐትተው የምናየው። አብዛኞቹንም በፈጣን ንዑስ-ርዕሶች ለመቆለፍ ሲታገል አይተናል። ፀሐፊው በርካታ ጉዳዮች ወደ አንባቢያን ለማድረስ ያለውን ጥረት እያደነቅን፤ ቢሻሻሉ የምንላቸውን ችግሮችም በጥቂቱ ማስታወሱ አይከፋም።

ገና ከመነሻው የመጽሐፉ ይዘት (ዘውግ) በአንድ ጥላ ሰር አለመውደቁ ለበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች የተጋለጠ አድርጐታል። በዚህም ፀሐፊው ሲገላበጥ ይስተዋላል። የኅሳቦች ምንነት ከስረ መሠረቱ ለመተንተን መሞከር ያለበቂ ማስረጃ ሲሆን፤ አድካሚ ነው። በተለይ አንዳንዶቹ ርዕሰ-ጉዳዮች ራሳቸውን ችለው ብዙ ሊፃፍባቸው የሚችሉ ከመሆናቸው አንፃር ቢቀነሱ ያስብላሉ።

በመቀጠል መጽሐፉን አድካሚ የሚያደርገው በረጃጅም ዓረፍተ ነገሮች የተሞላ መሆኑ ነው። ይህም አንባቢ ጉዳዩን በቀላሉ እንዳይረዳው ችግር ፈጥሯል። እዚህ ላይ ዓረፍተ ነገሮቹ ብቻ ሳይሆኑ አንቀጾቹም ያለልክ መለጠጣቸው አንባቢን ያደክማሉ። ይህ የፀሐፊው ረጅም ነገር የመውደድ አባዜ በአንዳንድ ርዕሶቹም ላይ ጭምር መታየቱ ግልጽ ነው። መሰል ጽሁፎች በአጫጭር ዓረፍተ ነገሮች ቢገለፁ ለተነባቢነቱ መልካም ነው። በተረፈ ግን “ኑሮ እና አዲስ አበባ” አንባቢ ጊዜ አግኝቶ ካነበበው “ወይ ጉድ!” የሚያሰኙ በርካታ የህይወት ገጽታዎችን የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። መልካም ንባብ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
16378 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us