“ተዋናይ የመሆን ምኞት ኖሮኝ አያውቅም”

Wednesday, 22 October 2014 12:04

 

 

ተዋናይ ይገረም ደጀኔ

 

 

 

በርካቶች መልካም ስነ-ምግባር ያለው ተዋናይ ነው ይሉታል። በ1972 ዓ.ም አሮጌው ቄራ አካባቢ ተወልዶ ያደገው የዛሬው የመዝናኛ አምድ እንግዶችን በፊልም ደረጃ ዕጣ-ፈንታ፣መስዕዋት፣ አዲስሙሽራ፣ 70/30፣ አስክሬኑ፣ ውበት ለፈተና፣ የትሮይ ፈረስን ጨምሮ ከ30 በላይ ፊልሞችን ሰርቷል። የጀግኖች ማህደር፣ ቅድስተ-ካናዳ፣ ሜዳሊያ፣ ምዕራፍ አራት፣ የብዕር ስምን ጨምሮ በቅርቡ በሚከፈተው የደራሲ ውድነህ ክፍሌ “የደመና ዳንኪረኞች” ቴአትሮች ላይ ተውኗል። በቲቪ ድራማዎቹ ከሚጠቀሱለት መካከል ሾፌሩ፣ አንድ ዕድል፣ ያልተሄደበት መንገድ፣ ሰው ለሰው እና አሁን በቅርቡ በኢቤኤስ ቲቪ በመታየት ላይ በሚገኘው “ሞጋቾቹ” ላይ ተጫውቷል። ይህ ሲባል ግን ከ40 በላይ የሚሆኑ አጫጭር የቴቪ ድራማዎችን ሳይጨምር ነው። ይህ ሰው በሬዲዮም አለ፤ አሁን ድረስ የሚታወስባቸውን ጨምሮ ግራረ አምባ፣ የደወል ድምፆችና በሸገር ኤፍ ኤም እየተላለፈ በሚገኘው የኛ ድራማ ላይ በብቃት እየሰራ ይገኛል። ዘንድሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት የቴአትር ጥበባት ክፍል ተማሪ ከሆነው ከተዋናይ ይገረም ደጀኔ ጋር ይህን መሰል አጭር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ፤

ሰንደቅ፦ ትወናን በአማተርነት የጀመርከው ፋዘር (የክቡር ዶክተር ተስፋዬ አበበ) ጋር ነው?

ይገረምእስከ ዛሬ አውርቼው የማላውቀውን ነገር ልንገርህ፤ ሰዎች ሲሉ ብዙም የማይጥመኝ ነገር ነው። ግን ላጫውትህ. . . እኔ ብዙ ነገሮች ውስጤ አሉ፤ ፍላጎት ግን የለኝም። ለምሳሌ ህጻን እያለሁም ጭምር እናቴ ምን ትለኛለች መሰለህ ቤታችን ቴፕ የለም ነበር። የሚገርመው ግን ገና በቅጡ ነፍስ ሳላውቅ ሙዚቃ የተከፈተበት የጎረቤት ቤት ሄጄ መቀመጥ ያስደስተኝ ነበር። ከጎረቤት ቤት የሚወጣው ቴፑ ሲዘጋ ብቻ እንደነበር ትናገራለች።

ባይገርምህ ልጅነቴን በመጮኸ፣ በመዝፈን፣ በመዘመር፣ ቆርቆሮ በመደብደብ ነው ያሳለፍት። አንድ ጎረቤታችን የነበረ በጣም የምወደውና ብሔራዊ ቴአትር የባህል ቡድን ውስጥ ይሰራ የነበረ ሰው በተለይ ክረምት ላይ ወደብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ይዞኝ ይሄድና ሲሰሩ አያለሁ። ያ የትወና ተፅዕኖ ቤተክርስትያን ውስጥ ለሰንበት ተማሪዎች አጫጭር ድራማዎችን በመስራት መገለጥ የጀመረ ይመስለኛል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ተዋናይ የመሆን ምኞት ኖሮኝ አያውቅም። ይህን ተሰጥኦዬን በጣም የተገነዘበው ኩስያን አንተ ግን ለምን አትሰራም ይለኝ ነበር። በእርሱ ግፊት ነው እንጀራዬን ያገኘሁት። በኋላ ላይ “ፋዘር” ቤት ገባሁ፤ ደስ አላለኝም ነበር። ለምን እኔ የመጣሁት ከመንፈሳዊ ቦታ ነው፤ እዛ የሚሰራው ደግሞ ሌላ ነው። አቋርጨው ብወጣም አሁንም መስራት አለብህ ተብዬ በድጋሜ “ፋዘር”ጋ ሄድኩኝ። እዛ ብዙ ነገሮችን ተምሬ ነው አሁን ያለሁበት ደረጃ ደረስኩት ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፦ የመጀመሪያው በፕሮፌሽናል መድረክ የሰራኸው ስራ የትኛው ነው?

ይገረምበመሰረቱ እኔ የጀመርኩት በቲቪ የሚቀርቡ አጫጭር የባህል ድራማዎችን በመስራት ነው። ነገር ግን ቴአትር ካልከኝ “ፋዘር” ቤት ሁልጊዜ የቴያትር ልምምድ ስላለ፤ ምናልባት አምስት ቴአትሮች እየተሰሩ ከሆነ በአምስቱም ውስጥ ሚና ሊኖርህ ይችላል። ለእኔ የመጀመሪያው በቴአትር ህዝብ ፊት የቀረብኩበት የተስፋዬ አበበ ድርሰት የሆነው “ከጀግኖች ማህደር” ነው። የራስ መስፍንን ገፀ-ባህሪይ ወክዬ ነበር በብሔራዊ ቴአትር የተጫወትኩት።

ሰንደቅ፦ ላንተ የመጀመሪያው የአደባባይ ስራ (በመድረክ ላይ) ከመሆኑ የተነሳ የፈጠርብህ ስሜት ምን ነበር?

ይገረምየሚገርምህ ቴአትሩ በጣም በወኔ የተሞላ ነበር። በዚያ ላይ በአዳራሹ ውስጥ አርበኞች ተገኝተው እያዩት ነበር። በታሪኩ ውስጥ አብዲሳ አጋ፣ ራስ መስፍን እና አርበኞች ይታዩበታል። ታዲያ አንድ ንግግር በተነገረ ቁጥር በአዳራሽ ያለው ተመልካች በጭብጨባ ያደነቁርሃል።

በተለይ አርበኞቹ ወኔያቸው እየተቀሰቀሰ ነገሩ ሁሉ ዛሬ ዛሬ የተፈፀመ ያህል ነበር የሚሆኑት፤ የተመልካቹ ምላሽ በጣም ደስ ይል ነበር። ከዚያ ውጪ ደግሞ “ፋዘር ቤት” ቴአትር ከተሰራ በኋላ እንገማገማለን። በዚያም ላይ አብሬያቸው የሰራሁት ልጆች በሙሉ ስለኔ ጥሩ-ጥሩ አስተያየት ሲሰጡ ስሰማ ደስታው ለየት ይላል። ያ አጋጣሚ ነው እንግዲህ ለበርካታ ስራዎች ዕድል የከፈተልኝ ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፦ ተዋናይነት እንደሙያ አለማዊ ነው። አንተ ደግሞ መዝሙር ዘምረሃል፤ ዘፈን ቢሳካልህ ትሰራ ነበር?

ይገረምየልጅነት ታሪኬን አስታውስ። ልጅ ሆኜ በሰንበት ት/ቤት ነው የማሳልፈው፤ ወደቤት ስመጣ ደግሞ ቤታችን መጠጥ ቤት ነው። ወደድኩም ጠላሁም ሙዚቃና መዝሙር እያዳመጥኩ ማደጌ ግድ ነው። ነፍስ አውቄ ቤታችን መጠጥ ቤት መሆኑን ሲያቆም ግን ሙሉ ለሙሉ ወደአገልግሎቱ ነው የመጣሁት። ሲለኝ እዘምራለሁ፤ ካልሆነም እዘፍናለሁ። ያለማንጎራጎር ስራ የለኝም ነበር፤ ጎረቤቶቼ እስኪታዘቡኝ ድረስ ማለት ነው። አሁን አንተ ላልከው ነገር ትወናን እንደስራ ሰርቼ ይከፈለኛል፤ ነገር ግን ውስጤ ሁሌም ዝማሬና ምስጋና እንዳቀርብ ነው የሚገፋፋኝ። ስለዚህ ዘፈንን ለእውቅናም ለገንዘብም ቢሆን አልጓጓለትም።

ሰንደቅ፦ ከመዝሙርህ የተገኘው ገቢ ለበጎ አድራጎት ድርጅትና ለገብርኤል ቤተክርስቲያን እንዲውል አድርገሃል። ይህ የጋስነት መንፈስ ከምን የመጣ ነው?

ይገረምእኔ ከሁለት አንፃር አየዋለሁ። መጀመሪያ ውስጤን ፈተነኝ መስጠቴ ባይታወቅስ ብዬ አስቤ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ምን አሉኝ አንተ ትንሽ ገንዘብ ይሆናል የምትሰጠው። ነገር ግን አንተን የሚያውቁህ፤ አንተን ተከትለው ብዙ ሊሰጡ ይችላሉና በግልፅ አድርገው የሚል ሃሳብ መጣ። ተስማምቼ ነው በይፋ ስጦታውን ያበረከትኩት። ሌላው ግን በጣም መታወቅ ያለበት በአገራችን ብዙ ሊረዱ የሚገባቸው ወገኖች አሉ። እነዚህን የእኛን ሸክሞች ሰብስበው እየረዳልን ያሉ የበጎ አድራጎት ተቋማትን በእንደዚህ መልኩ መርዳት ካልቻልን ትልቅ ውድቀት ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ እርስ በእርሳችን መሰጣጠት ካልቻልን ህይወት በጣም ይከብዳል ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፦ ዝነኝነት ላንተ የጨመረብህ ኃላፊነት፤ ያሳጣህ ነፃነትና ያመጣልህ እድል ምንድነው?

ይገረምበሁለት መንገድ ማየት ይቻላል። ዝና ጥቅም አለው። ክብር አለው፤ ብዙ ሰዎች ያውቁሃል፤ ከብዙ ሰዎች ጋር ቤተሰብ ሆነህ መኖር ትችላለህ። ያ ደስተኛ ያደርግሃል። ከዚህ ሁሉ ባሻገር ግን እንደተራ ሰው መኖርን ልታጣው ትችላለህ። ይቅርታ አርግልኝና እኔ ይህ ነገር አስጨንቆኝ አያውቅም። የትም ቢሆን ነፃ ነኝ። ተወልጄ ያደኩት ቄራ በመሆኑና ድህነትን አጣጥሜ የኖርኩ በመሆኑ (ሳቅ) ዝቅ ያለው ህይወት ምንም አይከብደኝም። እንደውም ትልልቅ ሆቴሎችና ፕሮቶኮል የበዛባቸው ቦታዎች ያስጨንቁኛል። አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰለህ። ሻይ እንጠጣ ተባብለን እኔ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ጥበቡ ወርቅዬና ትግስት ግርማ ሆነን ሂልተን ገባን። የሆነ ነገር ጭንቅ ሲለኝ፣” የሆነ ቤት ገብተን የሆነች ነገር ጎረስ- ጎረስ አድርገን ብንወጣ አይሻለንም አልኳቸው። ሁሉም ወዲያው ነው የተስማሙት። ለካ ተፋፍረን ነው እንጂ ሁላችንም ነፃነቱን እንፈልገው ነበር። ስለዚህ ሁሌ ነፃ መሆን ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፦ ባለቤትህን በገዳማይቷ ፊልም ላይ እንዳገኘሃት ሰምቻለሁ። እስቲ ለመሆኑ ወደዚያ ፊልም ስራ እንዴት ተመረጥክ?

ይገረምአዎ!. . . ይገርምሃል ፕሮዲዩሰሩ አብይ ይባላል። እርሱ ነበር የመረጠኝ። እውነቱን ለመናገር ፊልሙን ለመስራት አልፈለኩም ነበር። የአጋጣሚ ሆኖ የአሁኗ ባለቤቴ የፕሮዲዩሰሩ ዘመድ በመሆኗ በፊልሙ ውስጥ አንድ ሚና ተሰጥቷት ነበር። አብረን የምንሰራው ቦታ ስለነበር እያጠናን ፊልሙን መስራት እንዳልወደድኩት ነገርኳት። እርሷ ደግሞ ይሉኝታ ያላት፤ በጣም ለሰው የምትጨነቅ አይነት ሰው ስለነበረች። አይሆንም ብላ ወጥራ ይዛኝ አለቀሰች። ቀስ በቀስ ተቀራርበን፤ ጓደኛሞች ሆንን። ስለእውነት ለመናገር በፊልሙ ደስተኛ ባልሆንም ሚስት ስላገኘሁበት ግን ዕድለኛ ነኝ።

ሰንደቅ፦ አንዳንድ ሰዎች በፊልሙ ላይ ያለው መሳሳም አይተው። ይገረም በዳይሬክተሩ ላይ ጫና ፈጥሮ ያገኘው ነው ይሉሃል፤ ትስማማለህ?

ይገረም(ሳቅ) አይ አጋጣሚ ነበረው። ይልቅ መቀራረባችንና ጓደኛሞች መሆናችን ስራውን አቀለለው ማለት ይቻላል። ልምምድ ሁለት ሶስት ወር የወሰደ በመሆኑ እኛ በጣም ተግባብተን ነበር። አዘጋጁ በስሱ እንደምንሳሳም ሲነግረን እኔና እርሷ በመሆናችን ብዙም አልከበደንም፤ እንጂ እኛ ከፊልሙ ፅሁፍ ውጪ የግድ ይጨመርልን አላልንም።

ሰንደቅ፦ ፊልሞች በብዛት እየተሰሩ ነው። አንተም ጥቂት በማይባሉ ፊልሞች ላይ ተሳትፈሃል። ዕድገቱን እንዴት ታየዋለህ?

ይገረምእንደተመልካች ሆኜ ከ80ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በካሴት የሚወጡ ፊልሞችን በደንብ አይ ነበር። እነሰናይት፣ ስውር ችሎት፣ የሳት እራት፣ ፍለጋ፣ መዘዝ በቪዲዮ የሚታዩ ፊልሞችን በደንብ እከታተል ነበር። የሚገርምህ ነገር እነዚያ ፊልሞች አሁን ባለው ቴክኖሎጂ ተደግመው ቢሰሩ የመታየት አቅም አላቸው ብዬ አምናለሁ። ለምን ብትል በታሪክ ሚዛናዊ የነበሩ ሥራዎች ነበሩ። ከዚያም በኋላ ጥሩ-ጥሩ ፊልሞች ተሰርተዋል። ከ1999 ዓ.ም በኋላ የመጡ ፊልሞች ግን ከመቅለላቸው ብዛት “የምንስቅባቸው እንጂ ቁም ነገር የምንነጋገርባቸው ፊልሞች እያነሱ መጥተዋል። እርግጥ ውስጥ ስላለን እኛም አንዱ ነው። የተሻለ ስራ ለመስራት በፈተና ውስጥ ነን፤ ለውጡ እስኪመጣ ግን ውጪ ከመሆን ብለን አብረን እየታገልን እንገኛለን።

ሰንደቅ፦ ይገረም አንድ ፊልም ለመስራት እስክሪብቱ ነው የሚያጓጓህ ወይስ ክፍያው ነው?

ይገረምእውነቱን ለመናገር መጀመሪያ የምመርጠው ታሪኩን ነው። ያን ስልህ ግን ክፍያ አልደራደርም ማለቴ አይደለም። ችግሩ ግን ምን መሰለህ ቴአትር ስትሰራ ዛሬ ብትሳሳት እንደምንም ብለህ ታስተካክለዋለህ፤ በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ የበለጠ አሪፍ ይሆናል። ፊልም ግን አንዴ ሰርተህ ከተመረቀ በኋላ ምናልባት ድምፁ ጥሩ ካልሆነ ተመልካቹ የድምፅ ባለሙያውን ሳይሆን አንተን ወይም ተዋናዩን ነው የሚወቅስህ። ይገረም የፊልም ተዋናይ እንጂ የድምፅ ባለሙያ አይደለም። ይህን የማይረዳ ሰው ይኖራል።

ሰንደቅ፦ የሚገባኝን ክፍያ አግኝቻለሁ ብለህ ታስባለህ?

ይገረምበክፍያ እረክቼ አላውቅም። ነገር ግን የለፋሁበትን ነገር ቢቆይም ዘመን ይከፍለኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ሰንደቅ፦ ከቴአትር ተመልካች እና ከፊልም ካሜራዎች የቱን ትፈራለህ?

ይገረምለእኔ እውነቱን ለመናገር ካሜራ ያስፈራኛል። ቴአትር ላይ እኮ ተመልካቹን የምትፈራው መድረኩን እስክትረግጠው ነው። ይህ ደግሞ ለምን 40 ዓመት ወይም 50 ዓመት በትወና አታሳልፍም፤ አንድ ተዋናይ መድረክን እስኪረግጥ ድረስ መፍራቱ የተለመደ ነው። ወደፊልሙ ወይም ወደቲቪ ድራማው ስንመጣ ደግሞ “አንድ ካሜራ የ80 ሚሊዮን ህዝብ አይን ማለት ይችላል። ሌላው ግን ቴአትር ይከብዳል፤ ፊልም ይቀላል የሚባለው ነገር አይመቸኝም። ሁለቱም የራሳቸው “ኳሊቲ” አሏቸው። ቴአትር ጎበዝ የሆነ ነገር ግን ፊልም የማይችል ተዋናይ አለ። በአንጻሩ የተገላቢጦሽም ቴአትር የማይችል ነገር ግን ፊልም ላይ ጎበዝ የሆነም ሰው አለ።

ሰንደቅ፦ ከሰራሃቸው በርካታ ፊልሞች በተለይ ሁኔታ የማትረሳው?

ይገረምበነገራችን ላይ ከሰራኃቸው 32 ፊልሞች መካከል 28ቱ ፊልሞች በቪሲዲ ወጥተዋል። ቤቴ ሆኜ አያቸዋለሁ። ሁሉንም እንደመፅሐፍ ደርድሬ ሳያቸው የአስራ ምናምን ዓመታት ተሞክሮዎቼ ናቸው እላለሁ። ደስ የሚለኝንም ሆነ የተፀፀትኩበትንም ፊልም ቢሆን እኩል ነው የማያቸውን ምክንያቱም የታሪኬ አንድ አካል ሆነዋልና። ሁሉም በህይወቴ ትዝታ አላቸው። ነገር ግን አንተ ለጠየከኝ ጥያቄ መልስ ለመስጠት “ፊደል አዳኝ” የተሰኘውን ፊልም አልረሳውም። የተጫወትኩት ገፀ-ባህሪይ ለየት ከማለቱም ባሻገር የተሸለምኩበት በመሆኑ ልዩ ትዝታ አለኝ። ገፀ-ባህሪው ከእኔ የግል ባህሪይ በፍፁም የራቀ ስለሆነም ይመስለኛል። ሌላው “ዕጣ- ፈንታ” ንም አስታወሰዋለሁ። ከቢኒያም ወርቁ ጋር የሰራሁት፤ “አዲስ ሙሽራም” እንዲሁ የተለየ ነው። ሌላው ከማልረሳቸው ልዩ ስራዎች ውስጥ “7ኛው ሰው” ነው፤ የተለየ ሃሳብ የተነሳበት ስራ ነው። በርግጥ ተመልካቹ አልወደደውም፤ ነገር ግን በአምስተኛው የፊልም ፌስቲቫል ላይ በምርጥ ድርሰት ተሸላሚ የሆነ ስራ ነበር። በባለሙያዎች አይን ጥሩ ስራ ነበር።

ሰንደቅ፦ እስቲ ደግሞ ስለ “ሰው ለሰው” ድራማ የማትረሳውን ነገር አጫውተኝ። በተለይ ያንተን ገፀ-ባህሪይ በተመለከተ?

ይገረም በእርግጥ እንደሰው የኔ “ካራክተር” ይጎረብጠኛል። አንዳንዴ እንደተመልካች እንዴት ይቅር ይላቸዋል እላለሁ፤ ነገር ግን የደራሲው ነፃነት የተጠበቀ ነው። የኪነ-ጥበብ ዋነኛ አላማው ማስተማር ነው፤ ማዝናናትም አብሮት አለ። ስለዚህ ደራሲው እኔ በምሰራው ገፀ-ባህሪይ በኩል ይቅር ባይነትን ለማሳየት የሞከረ ይመስለኛል። በርግጥ ብዙ ተመልካቾች እንዴት ይቅር ይላታል ይላሉ። ከሁሉም ግን ብዙ ጫና ያለበትን ተከታታይ የቲቪ ድራማ ሰርተን መጨረሻችን በራሱ አሪፍ ልምድና ብቃት ይመስለኛል።

ሰንደቅ፦ በስተመጨረሻ የምታመሰግናቸው ሰዎች ካሉ እድሉን ልስጥህ?

ይገረምሁሌም ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ። ባለቤቴ ፅዮን ዮሴፍንና ልጆቼን ማለትም አቤሜሌክ፣ አስቴርና ሃና ይገርም አመሰግናቸዋለሁ። እንዲሁም አጠቃላይ በሙያው ውስጥ ያሉ ሰዎችንና ተመልካቾቼን አመስግናለሁ። በመጨረሻም ይህን ዕድል ስለሰጣችሁኝ እናንተንም አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11857 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us