“ክፍያን በተመለከተ ብዙ የሚያስተዛዝቡ ነገሮች ይገጥማሉ”

Wednesday, 29 October 2014 14:34

ኮሜዲያን - ወንደሰን አውራሪስ

 

በርካቶች በተለይ የሚያስታውሱት በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ በጽሁፍና በድምፅ በሚያቀርባቸው ጭውውቶቹ ነው። የዛሬው እንግዳችን ኮሜዲያን ወንደሰን አውራሪስ፤ በርካታ የሬዲዮና የቲቪ ጭውውቶችን በመተወንና በመፃፍ ይታወቃል። በቪሲዲ ከውጪ የኮሜዲ ስራዎቹ መካከል ከሀብቴና ደረጄ ጋር “ሀ” ብሎ የጀመረበትን ጨምሮ አሁንም ድረስ ሲታዩ ፈገግታን የሚያጭሩ የኮሜዲ ስራዎችን ያበረከተ ባለሙያ ነው። በፊቸር ፊልም ዘርፍም እንዲሁ ይቅርታ እና አዲስ ፍቅር በቅርቡ በሲኒማ ቤት እየታየ የሚገኘውን “ባንከሩ”ን ማስታወሱ በቂ ነው። የነበረንን አዝናኝ ቆይታ እነሆ በአጭሩ፤

ሰንደቅ፡- በርካቶች አንተን የሚያስታውሱህ በቅዳሜ መዝናኛ የሬዲዮ ስራዎችህ ነው፤ አንተስ ስለቅዳሜ መዝናኛ ምን ትውስታ አለህ?

ወንደሰን፡- አጀማመሬን ላስታውስህ፤ እኔ ወደሬዲዮ ከመቅረቤ በፊት ደረጄና ሀብቴን ነበር የምቀርበው። ገና ልጅ እያለሁ ለእነርሱ የሚሆን የኮሜዲ ጽሁፎችን አቀርብላቸው ነበር። ድርሰቱን ሳዘጋጅም በገፀባህሪ ስም አልጠቀምም። ለሀብቴ ከሆነ - ለሀብቴ ብዬ ነው የምፅፈው። ለደረጄ ከሆነም ደረጃ ብዬ ነው እጽፍላቸው የነበረው። ለብዙ ጊዜያት በጽሁፎቼ ብቻ ነበር የምንተዋወቀው። ታዲያ አንድ ጊዜ ሰው ይፈልጋችኋል ተብለው በር ላይ ሲወጡ እነርሱ የጠበቁት ትልቅ ሰው ነበር። እኔ ግን ጩጨ ነኝ፤ በዛ ላይ በቁምጣ ነበር የመጣሁት። “አንቺ ነሽ እንዴ?” ብለውኝ ተዋውቀን ይዤላቸው የመጣሁትን ሥራ ሰጥቻቸው ሰሩት፤ እነርሱ አበረታተውኝ ነው እዚህ የደረስኩት። በመሆኑም የቅዳሜ መዝናኛ ላይ ከጽሁፍ ወደድራማውና ጭውውቱ ተሳትፎ የገባሁበት መንገድ ሁሌ አይረሳኝም። ሀብቴ ነፍሱን ይማረው፤ ደረጄ በህይወት አለ ሁለቱንም ግን አሁንም ድረስ በጣም ነው የማመሰግናቸው።

ሰንደቅ፡- ለደረጄና ሀብቴ የሰጠሀቸው የመጀመሪያ ሥራ ምን የሚለው ነው? ክፍያውስ?

ወንደሰን፡- (ሣቅ) የዛን ጊዜ ለእኔ ትልቁ ክፍያ የነበረው እነርሱን ማግኘቴና ድርሰቴን ሲሰሩት ማየቴ ነበር። በሄድኩ ቁጥር የተሻለ እንድሰራ ይመክሩኛል፤ ይንከባከቡኛል። ነገር ግን ስለክፍያ አንድም ቀን አስቤው አላውቅም። የመጀመሪያ ስራዬ የነበረው፤ አንድ የማራቶን ተወዳዳሪን ዘግይቶ መግባት የሚያሳይ ሥራ ነው። ሀብቴ ከብዙ ሯጮች ጋር በማራቶን ውድድር ይሳተፍና በየመንገዱ ሰው ሰላም ሲል ሲበላ ሲዝናና ቆይቶ ስታዲየም ሲደርስ መሽቶ ሰው ሁሉ የለም። እና ዘበኛው (ደረጄ ነበር) “ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ምን ታደርጋለህ?” ሲለው ሀብቴም - “መምጣቴን ንገሩልኝ ለማለት ነው” የምትለዋ የመጀመሪያ ስራዬ ናት ከእነርሱ ጋር ማለቴ ነው።

ሰንደቅ፡- ለስራዎችህ መነሻ ሀሳብ የምታገኘው ከየት ነው?

ወንደሰን፡- እኛ ቤተሰብም ሆነ አካባቢ በጣም ቀልድ ይበዛል። ሁሉም ጨዋታ አዋቂዎች ናቸው ማለት ይቻላል። በዚህ ላይ የቀደምት ኮሜዲያንን ሥራ በደንብ ነው የማየው። የእነ አለባቸው፣ የእነልመንህ፣ የእነተስፋዬ ካሣ፣ የእነአብርሃም አስመላሽን ሥራዎች ሳይ ስለኮሜዲ እንዳውቅ ረድቶኛል። ነገር ግን በብዛት ባየሁትና በሰማሁት ነገር ላይ ተንተርሼ ቀልድ መፍጠር እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ከደረጄና ሀብቴ ጋር በፊልም የወጣህበት የራስህ ድርሰት የቱ ነው?

ወንደሰን፡- ለደረጄና ሀብቴ ሥራዎቼን ብቻ ነበር የምሰጠው። በኋላ ላይ እንድሳተፍ ሲጋብዙኝ በወጣ አንድ የኮሜዲ ካሴት ውስጥ “የአያቴ አያት”፣ “ለመድሃኒዓለም መጠት ነው” (የሚለው በእውነተኛ ገጠመኝ ላይ ተንተርሼ የሰራሁት ሥራ ነው) ለመጀመሪያ በቴሌቪዥን መስኮት ራሴን ያየሁት ከሀብቴና ደረጄ ጋር ነው። ከዚያ በመቀጠል ግን የቀድሞው ኢቲቪ ላይ ከአስረስ በቀለ ጋር መስራት ጀምሬያለሁ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- በፊቸር ፊልምስ የሰራሃቸው የትኞቹ ናቸው?

ወንደሰን፡- የመጀመሪያ ፊልሜ ከዮናታን ወርቁ ጋር ነው የሰራሁት። “ይቅርታ” ይሰኛል። በርግጥ ከዚህ ፊልም በፊትም የሰራሁት ሥራ ነበር ግን አልወጣም። ከዚያ በመቀጠል “አዲስ ፍቅር” ይሰኛል። ሌላው በቴክኒክ ችግሮች ምክንያት ብዙም ወደተመልካች ያልደረሰው “የማልተኛው” የሚል ፊልም ነበረ። በቅርቡ “ባዶ ነበር” ፊልም ላይ ተሳትፌያለሁ። የመጨረሻው ስራዬ “ባንከሩ” እየታየ ይገኛል። በቅርቡ ደግሞ ሰርቼ የጨረስኩትና የሚወጣ ፊልም አለ።

ሰንደቅ፡- አንዳንድ ተመልካቾች አንተን በሬዲዮ፣ በቲቪና በፊልም ይታይ እንጂ በመድረክ ስራ (በቴአትር) ግን አቅሙን ማሳየት አልቻለም ይሉሃል፤ ችግሩ ምንድነው?

ወንደሰን፡- እውነቱን ለመናገር ቴአትር ትልቅ አቅም የሚጠይቅ ዘርፍ ነው። ከዚህ በፊት አንድ ሁለት ቴአትሮችን ከጓደኞቼ ጋር ለመስራት ሞክረን ነበር። ግን አጥንተን - አጥንተን ሳይወጣ ይቀራል። ልፋቱ ይበዛል። እሰለቻለሁ መሰለኝ ተውኩት። ነገር ግን አሁንም የመድረክ ሥራ መስራት የምመኘውና የምወደው ነው። ወደፊትም የመስራት ዕድሉ ከተገኘ አቅሜን ለማሳየት ዝግጁ ነኝ።

ሰንደቅ፡- ከብዙ አንጋፋና ወጣት ኮሜዲያን ጋር እንደመስራትህ ማንኛቸውን በተለየ መልኩ ታስታውሳቸዋለህ?

ወንደሰን፡- አሁንም ድረስ ሳስበው የደረጄ የፊት ገጽታ መለዋወጥ ያስቀኛል። የሚገርም ችሎታ ነው ያለው። በመቀጠል ተስፋዬ ካሣ ደግሞ በድምፁ የፈለገውን ነገር መግለፅ መቻሉ ይገርመኛል። በተረፈ ግን ሁሉም አሪፎች ናቸው። ሁሉንም የማስታውስበት የራሳቸው ብቃት አላቸው። ደረጄ እና ተስፋዬ ግን በድምፅና በፊት ገጽታ በተለየ አስታውሳቸዋለሁ።

ሰንደቅ፡- በብዛት የሰራኸው ኮሜዲ ስራዎችን እንደመሆኑ ከካሜራ በፊትም ቢሆን ሣቅ ያጋጥማል። እስቲ በስራ ላይ የምታስታውሰው ነገር ካለ አጫውተን?

ወንደሰን፡- በጣም የሚገርም ነገር ልንገርህ፤ “አዲስ ፍቅር” የተሰኘ ፊልም እየቀረጽን ነው። ካሜራ የሚሰራውና መብራት የሚይዘው ልጅ ወንድማማቾች ናቸው። ስራው ተጀምሮ እኔ ምንም ላውራ እነሱ ሣቅ-በሣቅ ይሆናሉ። የሚገርመው ያንን ፊልም ስንሰራ በተዋንያኑና በዝግጅቱ ከሚቋረጠው ይልቅ በእነሱ ሣቅ ምክንያት የሚቋረጥበት ጊዜ ብዙ እንደነበር አስታወሳለሁ። በፊልሙ ውስጥ ኬክ ይዤ የምታይበት ትዕይንት አለ። በልምምድ ላይ ያልነበረ ነገር አደረኩ። ምንድነው መሰለህ? ኬኩን እንደ ደብተር ብብቴ ስር ይዤው መፈለግ ጀመርኩ። ይሄኔ አንደኛው ልጅ ሣቅ-በሣቅ ሆነው “ኧረ ብብትህ ስር ነው” ሲሉኝ የባሰ ሁሉም ሣቁና ስራው ተቋረጠ።

ሰንደቅ፡- ፊልም ሥራን በተመለከተ ታሪክ ትመርጣለህ ወይስ ክፍያህ ውድ ነው?

ወንደሰን፡- ለመጡልኝ ስራዎች በተቻለ አቅም ሁሉ ታሪክ እመርጣለሁ። ደስ የሚል ፊልም ብሰራ ለራሴም ደስ ይለኛል። ነገር ግን ግማሹ ታሪኩ ጥሩ ይሆንና ክፍያው የወረደ ይሆናል። አንዳንዴ ስለ ክፍያም የሚያወሩ ይገጥሙሃል። አብረን እናድጋለን የሚባል ነገር አለ። አንዴ ምን ገጠመኝ መሰለህ፤ አንድ ሰው የፊልም ጽሁፉን ሰጠኝ፤ ሳነበው በጣም አሪፍ ነው። ደወልኩለትና በጣም ጥሩ ሥራ ነው ተባብለን ከተነጋገርን በኋላ ክፍያው ላይ ስንደርስ የሆነ ቁጥር ጠራሁለት፤ ወዲያው ስልኩ ተዘጋ (ሣቅ) ቆይቶ - ቆይቶ ደወለልኝና “ምነው በደልኩህ ወንዴ ለፊልሙ ብዬ የያዝኩትን በጀት የሚያክል ገንዘብ የምትጠይቀኝ” ብሎኝ እርፍ - ትንሽ እኮ ነው። ክፍያን በተመለከተ ብዙ የሚያስተዛዝቡ ነገሮች ይገጥማሉ። በነገራችን ላይ ግን የ“ባንከሩ” ፕሮዲዩሰሮችን በዚህ አጋጣሚ ማመስገን ይኖርብኛል። በተዋዋልነው መሰረት ነው ወዲያው የከፈሉኝ።

ሰንደቅ፡- ከነማን ጋር መተወን ትመኛለህ?

ወንደሰን፡- ከጋሽ ፍቃዱ ተ/ማርያም ጋር ትንሽም ቢሆን ሰርቻለሁ አሁንም ግን በደንብ ብሰራ ደስ ይለኛል፡፡ ሌላው ከሙሉአለም ታደሰ ጋር መስራት እፈልጋለሁ። በጣም ነው የማደንቃት።

ሰንደቅ፡- ዝነኝነትና ማኅበራዊ ግንኙነት እንዴት ነው?

ወንደሰን፡- በፊት - በፊት መታየትና መታወቅ በጣም ያጓጓሃል። በደንብ ከታወክ በኋላ ግን ሙሉ ነፃነት አይኖርህም። በርግጥ ብዙ ሰው ሲያውቅህ ቅድሚያ ይሰጥሃል፤ ሰው ይወድሃል ያከብርሃልም። ደግሞ ሁሉም ሰው ያውቀኛል ማለት አትችልም። ለምሳሌ አንዳንድ ቢሮዎች’ጋ ስትሄድ ዋናው ስራ አስኪያጅና ፀሐፊው እያወቁህ በር ላይ የቆመው ጠባቂ ምንድነህ? ወደየት ነህ? ሊልህ ይችላል። “እነ እገሌ እኮ ናቸው” ሊባሉ እኛ የት እናውቃቸዋለን ይሉሃል። እውነታቸውን ነው እነዚህ ሰዎች ቲቪ ካላዩ በምን በኩል ሊያውቁን ይችላሉ።

ሰንደቅ፡- ለቅሶና ሠርግ ላይ ያለህ ማኅበራዊ ሁኔታስ?

ወንደሰን፡- በጣም ጐበዝ ነኝ ብዬ አስባለሁ። አንድ ጊዜ ግን የጓደኛዬ ወንድም ሞቶ ለቅሶ ሄድኩኝና ሰው ሁሉ ሲያለቅስ እኔም አልቻልኩም። ታዲያ እያለቀስኩ ሳለ ወንድምዬው መጣና “አንተም እያለቀስክ ነው?” አለኝ። “አዎ” አልኩት ገርሞኝ፤ ወንድሜ እኮ እንዲህ ነበር እያለ ታሪኩን እየተረከልኝ የባሰ ማልቀሱን ቀጠለ ማለት ነው። አንዳንዴ ለቅሶህንም የሚያጠፋብህ ሰው አታጣም።

ሰንደቅ፡- ከወዳጆቼ ጋር ስለአንተ ሳወራ ወንዴ ብዙ ሴቶች የሚጠብሱት ሰው ነው፤ ነገር ግን እርሱም አደገኛ ነው ብለውሃል፤ ምን ትላለህ?

ወንደሰን፡- (ሣቅ) እንደ እውነቱ ከሆነ ሴቶች እየጠበሱኝ ሳይሆን እያደነቁኝ ነው። ሌላ ነገር የለም። በመንገድ ላይ አንዳንድ ሴቶች “በጣም እንወድሃለው” እንጂ፤ እስካሁን “አፈቅርሃለሁ” ያለችኝ ሴት አላጋጠመችኝም (ሣቅ) …. እኔም እንደ አቅሜ ድፍት ብዬ ነው የማመሰግናቸው። እኔን ይጠብሳል የሚሉኝ ካሉ፤ አዎ እጠብሳለሁ! እኔ የምጠብሰው ግን ኑሮዬን እንደሆነ ንገርልኝ። (ሣቅ) በጣም የሚገርምህ አሁን - አሁን ከመንገድ ወደ ፌስ ቡክ ተቀይረዋል። እዛ ላይ ሲያገኙህ ሁሉም ሰው “እንወድሃለው” ይሉሃል ይሄ መታደል አይደለም?

ሰንደቅ፡- ብዙ ጊዜ በኅብረት የሚሰሩ አጫጭር የኮሜዲ ስራዎች ከባህል ባፈነገጠ መልኩ በተለይም ጾታን መሠረት አድርገው ልቅ ቀልድ ይቀልዳሉ የሚባል አስተያየት አለ፤ አንተ ምን ትላለህ?

ወንደሰን፡- እውነቱን ለመናገር ኢ-ስነምግባራዊ ኀሳቦችን እያነሱ የሚሰሩ ስራዎች አሪፍ ናቸው ብዬ አልገምትም። እንደዚህ ዓይነት ሥራ የብዙዎችን ስሜት ሊጐዳ ስለሚችል አይመከርም። ስም እየጠቀሱና የብልግና ቃላትን እየተጠቀሙ ለማሣቅ መሞከር አሪፍነት አይደለም። ለእኔ ሥራ መፍታት ነው የሚመስለኝ። መጀመሪያ አካባቢ ስህተት ሊኖር ይችላል። ግን ከአንዳችን ስህተት ሌሎቻችን መማር አለብን ብዬ ነው የማስበው።

ሰንደቅ፡- በሲኒማ ቤቶች በመታየት ላይ ካሉት ፊልሞች መካከል አብዛኞቹ ኮሜዲ ናቸው፤ ለምን የበዙ ይመስሉሃል?

ወንደሰን፡- ብዙዎች መሣቅን ፈልገው ሰልፎች በበዙ ቁጥር ፊልም ሰሪዎችም ወደ ኮሜዲ ስራዎች ያደሉ ይመስለኛል። ይህ የእኔ አመለካከት ነው። ሰው ከስራና ከኑሮ ጭንቀቱ ለመዳን በሣቅ ራሱን ማዝናናት የሚወድ ሰው ይበዛል ብዬ ነው የምገምተው። እንጂ ተመልካቹ መምረጥ ሳይፈለግ ቀርቶ አይመስለኝም። የተለያዩ ዘውግ ያላቸውን ፊልሞች ለማየት የሚፈልገው ሰው ቁጥር ግን ጥቂት ነው መሰለኝ።

ሰንደቅ፡- በመንገድ ላይ ያገኙህ ሰዎች እስቲ አስቀን ብለውህ አያውቁም?

ወንደሰን፡- በጣም ብዙ ጊዜ ያግጥምሃል። አንዳንዴ ከጓደኞችህ ጋር ቁጭ ብለህ እየተዝናናህ ድንገት አንድ ሰው መጥቶ እስቲ እኔንም አስቀኝ ይልሃል። አሁን-አሁን ደግሞ ፌስቡክ ላይም አስቀኝ የሚሉ መጥተዋል (ሣቅ) በጣም ይገርሙሃል።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ የራስህን ድርሰት በፊልም ይዞ የመምጣት ሀሳብ አለህ?

ወንደሰን፡- አዎ! በቅርቡ መሟላት ያለባቸውን ነገሮች ጨርሼ ቀረፃ እጀምራለሁ። ፊልሙ ተጽፎ አልቋል፤ ተዋንያኑን አነጋግሬያለሁ። በዚህ ዓመት አንድ ስራ ይዤ የመምጣት ሀሳቡ አለኝ።

ሰንደቅ፡- በስተመጨረሻ ማመስገን የምትፈልገው ሰው ካለ?

ወንደሰን፡- አብረውኝ ለሰሩ ጓደኞቼ በሞራል ላገዙኝ ቤተሰቦቼ እንዲሁም ስራዎቼን ተመልክቶ አስተያየት ለሚሰጡኝ ተመልካቾች በጣም አመሰግናለሁ። በተለይ ደግሞ አሁን የራሴን ፊልም ለመስራት ስነሳ እያገዘኝ ለሚገኘው ሳሙኤል ኃይሉ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
12199 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us