“የጭን መነባንብ” እንደትኩስ ድንች

Wednesday, 13 November 2013 12:06

በቅርቡ ለአንባቢያን ከደረሱ መፅሀፍት መካከል የደራሲና ጋዜጠኛ እቱ ገረመው ስራ የሆነው “የጭን መነባንብ” ይገኝበታል። መፅሀፉ በሶስት ክፍሎችና በተለያዩ ንዑስ አርዕስቶች ተቀንብቦ በ150 ገፅ የቀረበ፤ የጋዜጠኛዋን እውነተኛ ገጠመኞችና ትዝብት ያካተተ ስራ ነው። ጽሁፎች በአብዛኛው ጋዜጠኛዋ ትሰራ በነበረችባቸው ጋዜጣና መፅሄቶች በኩል ለህዝብ የደረሱ ቢሆንም በመፅሀፍ መልክ ተጠርዘው የቀረቡት “ተነቦ የሚጣል ታሪክ እንዳይሆንና ትውልድ የሚጠቅሳቸው እንዲሆን ወደ መፅሀፍ ለመቀየር ተግቻለሁ” (ገፅ፣7) ትለናለች።

በመፅሃፉ ውስጥ ድንበር ፈጥረው ከተቀመጡት ሶስት አብይ ርዕሶች መካከል “የጭን መነባነብ” ወደ 70 ገፅ ሲሸፍን የተቀሩት “የጉዞ ማስታወሻ” እና “መጣጥፎች” ደግሞ ለየራሳቸው ከ30 ያልበለጡ ገፆችን ወስደው ተከትበዋል። ከዚህም እንደምንረዳው መፅሐፉ በርዕሱ ጥላ ስር የወደቀና አብዛኛው የታሪኩ ክፍልም በሴተኛ አዳሪዎች ህይወት እና ገጠመኝ ዙሪያ የሚሽከረከር እንደሆነ ነው።

ጸሐፊዋ በጥቅሉ መግቢያ ብላ በሰየመችው ርዕስ ስር የሚከተለውን አስፍራለች፤ “እነዚህ ታሪኮች እንዲያስደስቱ፣ እንዲያዝናኑ ወይም ለማስተዋወቅ የተፃፉ አይደሉም፤ ይልቅ የአፍላነት እድሜ የሚፈታተናቸውን ወጣቶች አርቀው እንዲያስቡ ከባለታሪኮቹ ፀፀት እንዲማሩ እንጂ” (ገፅ፣7) ይህንን የባለታሪኮቹን ታሪክ ጋዜጠኛ እቱ ገረመውም ያቀረበችው እንደወረደ በሚመስል መልኩ ነው። ለዚህም “ሳወራቸው የተጠቀሟቸውን ቃላት የተጠቀምኩባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል” ትለናለች።

“የጭን መነባነብ” በርግጥም እንደወረደ ሊባል በሚችል ደረጃ የተፃፈና ቀላል አቀራረብን የተከተለ ከመሆኑም ባሻገር ንግግራዊ ትርክቶቹ ጉዳዩን በፈጠነ መንገድና በተዋዛ ለዛ እንድንከታተለው የሚያስችል አቀራረብ ይታይበታል።

የሴቶቹን የጭለማ ህይወት ወዝ ባለው መንገድ የምትተረከው ይህቺ ጋዜጠኛ የአንድ ሰሞን ውሎና አዳሯን ጭምር ከሴተኛ አዳሪዎቹ መንደር አድርጋም እንደነበር ትነግረናለች። ማስመሰል የሌለበት፤ እንደወረደ የሚነገር ታሪክ የበዛበት “የጭን መነባነብ” ክፍል ከስድስት ያላነሱ አዝናኝና አስገራሚ ንዑስ ርዕሶችን አካቶ ይዟል። ለምሳሌ “የሰፈር ጉረምሳ ባል ያስፈልግሻል” የምትለው ራሄል፤ የሴቶቹን ህይወት ሌላኛ አቅጣጫ ማሳየት የቻለች ሆና ቀርባለች። በቺቺኒያ ምድር የተከሰተችው ራሄል በገላ ችርቸራ መንገዷ ላይ ያጋጠሟትን አይረሴ ታሪኮች ለፀሀፊዋ ነግራታለች፡ የፀሀፊዋን ጋዜጠኛ መሆን ያወቀችው ይህቺ ሴት ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የሚከተለውን ታሪክ ስትተርክላት ታዝበናል።

“ጋዜጠኛ እንዴት መሰለሽ የሚደብረኝ”

“ለምን?” አሳቀቀችኝ።

“አይ ወንዶቹን ማለቴ ነው” አለች መሳቀቄ ገባት መሰለኝ ከአፌ ቀበል አድርጋ።

“ብታይ ወይ አይከፍሉሽ ወይ አይለቁሽ፣ ወሬ እየመጠመጡ ሙድ መያዝ ነው የሚፈልጉት”

“የሚከፍሉሽ ለምታወሪያቸው ወሬ ነው ወይስ. . .?” አላስጨረሰችኝም ከት ብላ ሳቀች። ሙዚቃውን አልፎ ቤቱን ድብልቅልቅ የሚያደርግ ድምፅ ያለው ሳቅ ነበር አሳሳቋ . . .” ይህ አጋጣሚ ሴቶች ጋር የሚሄዱትን ወንዶች አይነትና ስራም ጭምር የሚጠቁም ነው። እንደአብዛኞቹ ሴቶች ሁሉ ሰሚ ቢያገኙ ቁም ነገር መሆን የሚችሉ ጉዳዮች እንደምትሰነዝር ለማስታወስ ለጋዜጠኛዋ ጥያቄዎች የምትሰጣቸውን መልስ በተመለከተ “ከእያንዳንዱ መልሷ ውስጥ የለበጣ ቢመስልም ቁም ነገር ይመዘዝበታል” ተብለናል።

በእነዚህ ሴቶች ህይወት ውስጥ እንደባልም እንደጠባቂም ሆኖ የሚያገለግል ወንድ መኖሩ ይነገራል። የሚገዛቸው ወንድ ሲያጡ የሚያስተዳድራቸውና የሚሸኛቸው ወንድ መሆኑ ነው። ይህንንም ፀሐፊዋ በገጽ ፣14 ላይ እንደሚከተለው ተሰፍረዋለች።

“[ከባልሽ’ጋ] አብራችሁ ነው የምትኖሩት?”

“አይ እሱ ቤተሰቦቹ ጋር ነው የሚኖረው አንዳንዴ አብሮኝ ይሆናል”

“አሁን ቢዝነስ ብታገኚ ጥለሽው ትሄጃለሽ?”

“አዎና፤ ካገኘሁ ወደቤቱ ይሄዳል፣ ካላገኘሁ ወደቤቴ ይሸኘኛል፤ አለዚያም አብረን እናድራለን፤ ደግሞ ታውቂያለሽ መከበሪያም ነው። እያንዳንዷ ሸርሙጣ ባል አላት። የሰፈር ጎረምሳ ካልያዝሽ ብዙ ሰው ነው የሚተናኮልሽ”።

ከዚህ አስከፊ ህይወት ስለመውጣትና ኑሮን ስለመቀየር እሩቅ የሚመስልም ቢሆን ተስፋ ያላት ራሄል በሴተኛ አዳሪነት ስራዋ እስከመቼ እንደምትቀጥል ስትጠየቅ የሰጠችው መልስ “ውበት ሲረግፍ፤ ቁንጅና ሲያልቅ ልበልሽ?” ትላለች (ገጽ21)

ሴቶች በውሎና አዳራቸው የሚገጥሟቸውን ምስቅልቅል ክስተቶች ከሞላ ጎደል ለመተረክ የሚሞክረው ይህ የመጽሐፉ ክፍል “እንደወረደ” በሚል ሰበብ አፈንጋጭና አስደንጋጭ ቃላትን ሁሉ ይዟል። በርግጥ ፀሀፊዋ በመግቢያዋ የሴተኛ አዳሪዎቹን ህይወት ገፅ በገፅ የማሳየት ፍላጎት እንዳላትና የንግግራቸውንም ተዋረድ ባለማፋለስ ህያውነቱን ላለማሳጣት እንደምትታትር ነግራናለች። ሆኖም የቃላቱ ግልፅነትና ግልብነት የቱን ያህል የተዋጣለት እንደሆነ አንባቢ የሚመዝነው ይሆናል። ለጋዜጠኛ እቱ ገረመውም ይህ ነገር ሸክም ሳይሆንባት እንዳልቀረ ከሚከተለው ጽሁፍ መረዳት እንችላለን።

“እንደዚሁ ‘ዠለጠኝ፣ ወጠረኝ፣ አጫወተኝ፣ ተከለ፣ ጠመደ፣ ደፈቀ. . .’ የሚሉ ቃላት የገቡባቸው ንግግሮች ካዳመጡ ተጠቃሚዎቻቸው ይለያይ እንጂ ትርጉማቸው አንድ ሲሆን ‘ወሲባዊ ግንኙነት አደረገ’ ወይም የመፀሀፍ ቅዱሱን ‘አወቃት’ ተካተው የሚያገለግሉ ናቸው።” (ገጽ፣23) ትለናለች።

የቺቺኒያዋ ፌቨን ከምትናገራቸው ዋዘኛ ቁም ነገሮች መካከል ሴተኛ አዳሪዎች በየዕለቱ ስለሚጎነጩት መጠጥና ምክንያቱ ያስረዳል። በየቀኑ የምትጠጣበትን ምክንያት ፌቨን ስታስረዳ እንዲህ ትላለች፤ “[እኛ ሴተኛ አዳሪዎች] ለሶስት ምክንያቶች እንጠጣለን። አንደኛው ወጪ እንዲያወጣ የምንፈልገው ሰው ሲሆን፣ ሁለተኛ እንደዚህ እንደዛሬው ደስ ሲለን፣ ሶስተኛውና ዋነኛው የሚወስደን ወንድ እንዳይደብረን፤ ስራችንን ሰርተን እንድንመጣ እንጂ የመጠጥ ሱስ ኖሮብን እንዳይመስልህ” ትላለች። (ገፅ፣26)

ጸሐፊዋ የአፍላ ወጣቶቹን ህይወት አቅም ባጣ ርህራሄ ስትቃኘው፣ ከወጣቶቹ ጋር ለመቅበጥ የሚጋልቡትን ወንዶች ደግሞ በቃላት ጦር ትጠቀጥቃቸዋለች። ይህንን ለማስተዋል ስል “ወንድ ሸርሙጣዎች” ርዕስ ስር ያሰፈረችውን መመልከት ይቻላል። በነገራችን ላይ የወንዶችን ሽርሙጥና የምትተርከው “ሊሊ” የተባለች ወጣት ናት። ሊሊ የወደደችው ወንድ ከሀብታም ሴት የሚያመጣውን ገንዘብ እንደሚሰጣት እና ከእርሷም ጋር እንደሚወጣ ትናገራለች። “. . . ቁመናው፣ ወጣትነቱና መልኩ እንዴት መሰለሽ የሚያምረው? ለዚህ ቁመናውና ወጣትነቱ እኮ ነው እየተከፈለው ከዚያች ማያ የመሰለች አሮጊት ጋር የሚሞዳሞደው። ስለዚህ ከኔ በምን ይለያል? እዚያ ይከፈለዋል። እዚህ ይከፍላል” ባይ ናት።

የሴቶቹንና የደንበኞቻቸውን ሁኔታ በንፅፅር የምታስነብበን ፀሃፊዋ፤ “ለአይን እንኳን ምራቋን ዋጥ ያደረገች አላየሁም። ምራቁን ዋጥ ያደረገ አዳሜ ግን ከተማው እዚህ ነው” በሚል በንፅፅርና በትችት መነፅር ትገልጸዋለች።

“የሀበሻ ባል ሚስቱን አስቀምጦ በሸርሙጣ ይቀናል” የምትለው የኮንኮርዷ ናርዶስ፤ በለጋ ውበቷና በአይነ ግቡነቷ የተነሳ ፋታ ከሌላቸው የወሲብ ፔንዱለሞች መካከል አንዷ ስለመሆኗ ይነገረናል። ዕጣ ፈንታዋ ወደዚህ ህይወት የጎተታት ናርዶስ ኑሮን ለማሸነፍ ብዙ የታተረች፤ የአረብ አገር ግርድናን የቀመሰች፤ በፍቅር እፍ -ክንፍ ያለች ወጣት ነበረች። ያሰበችው ሁሉ ሳይሆን ቀርቶ ቡና ቤት ምሽጓ ሆኖ ብዙዎችን አስተናግዳለች።

የቡና ቤት ሴቶች ወንዶችን፤ ባለትዳሮችን ባለሀብቶችን፣ ባለስልጣኖችን፣ ዝነኞችንና አዋቂዎችን ጭምር ሁሉ በቅርበት ማግኘትና መታዘብ የሚችሉ የጭለማ ውስጥ ካሜራዎች ናቸው። በህሊናቸው ቀርፀው የሚያስቀምጧትና ቢተርኩ የሚችሉት አይነት ታሪክ አላቸውና። ለዚህም ነው መሰል ታሪኮች በተለያዩ ፀሀፍትና መፅሀፍት ታጭቀው የሚነበቡት። የሰው ልጅ የሰውን ገመና ለማወቅ ሲጣጣር ከሚገላልጣችው መፀሀፍት መካከል የቡና ቤት ሴቶችን መዝገብ ማገላበጡ እየተለመደ የመጣ ይመስላል።

በመፅሃፉ ውስጥ የሴቶቹን የመግለፅ አቅም ደጋግመን መመልከት እንችላለን። አንዳንዶቹ ንግግሮችም በንዑስ ርዕስነት ተሰይመው ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፤ “ጭን ፍሬቻ ነው” የምትለው ሄለን፤ ብርድ በነገሰበት ክረምት ጭን አስጎብኚ ቀሚስ ለብሳ ስትታይ ለፀሐፊዋ የመለሰችው መልስ፣ “የእኔ እመቤት ጭን እና ልጅ አይበርደውም” (ገጽ፣71) የሚል ነበር። ይህም ብቻ አይደለም ሴቶቹ ተፈላጊው ነገር ባላቸው እንጂ ልብሳቸው እንዳልሆነ ለማስረዳት ወንዱ ወደቡና ቤት የሚመጣው ልብስ ፍለጋ ሳይሆን ሴት ፍለጋ ነው የሚል አገላለፅን ትጠቀማለች።

ጋዜጠኛ እቱ ገረመው በ “ጭን መነባነብ” መፅሃፏ ውስጥ ብዙ ታሪኮችን አስነብባናለች። ምንም እንኳን ለመዝናነትና ለማስተዋወቅ የተፃፉ አይደሉም ብትለንም አንበበን ግን ብዙ የሚያዝናኑና የሚያስተምሩም ነገሮች ይዟል። እዚህ’ጋ ሳይነገር መታለፍ ያለበት ነገር ቢኖር የ“ወሲብ ቀስቃሽ” ፊልሞችን ለልጆች መልካም አስተዳደግና ሥነ-ምግባር ስንል እደምንሸሽገው ሁሉ ይህንንም መፅሀፍ ልጆች በማይደርሱበት ቦታ ብናኖው ይመከራል። አለበለዚያ ግን ጭን ተኮር የቃላት ጨዋታና ምርምር ውስጥ ከቶ በጥሬው የተነገረን እውነት ለመመንዘር የሚሯሯጡ ልጆችን ልናፈራ እንችላለን። በመፅሃፉ ውስጥም የብዙዎች ሴቶች ህይወት ቀላል በሚመስሉ ምክንያቶች ወደከባዱና አስከፊው የሴተኛ አዳሪነት ህይወት እንዴት እንደሚያመራ በጉልህ ተፅፏልና።

ከዚህ መለስ ግን ጋዜጠኛዋ የተጓዘችበትን በጉዞ ማስታወሻ መልክ የታዘበችውን ደግሞ በመጣጥፍ መልክ አድርሳናለች። የፀሀፊዋን ወግ ስናጣጥም ባህር ዳርን እና አርባ ምንጭን ከህዝቡና ከአኗኗሩ ጋር እንዲሁም ዋዛና ቁም ነገር የተከሉባቸውን ወጎች እንካችሁ ብላናለች።

“የጭን መነባንብ” በክረምት መካከል እንደተገኘ ትኩስ ድንች የሚፋጅና የሚያጓጓ መጸሐፍ ነው። የፀሀፊዋን ልፋትና የባታሪኮቹን ድፍረት ጭምር የምናይበት ይህ ስራ ለሌሎች የምናብ ፈጠራዎች መነሻ መሆን የሚችሉ ሀሳቦችንም ደርቦ የያዘ ነው ማለት ይቻላል።

Last modified on Tuesday, 28 January 2014 13:29
ይምረጡ
(27 ሰዎች መርጠዋል)
24781 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us