የዝነኞች ገፅታ- በፖርትሬት ካርቱን

Thursday, 06 November 2014 08:55

“ፖርትሬት ካርቱን ብለን የምንጠራው የካርቱን ዘርፍ ሲሆን ከሌሎች የካርቱን ዘርፎች በተወሰነ ደረጃ የሚለይና ልዩ ጥንቃቄን የሚፈልግ ነው። ሌሎቹ ዘርፎች በጥሩ ሀሳብና በጥሩ አቀራረብ ላይ ጥንቃቄ ሲፈልጉ፤ ይህኛው ዘርፍ ደግሞ በምስል (መልክ) እና ልዩነት (ግነት) ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል” ሲል ስለፖርትሬት ካርቱን መለያ ባህሪያት ያሰፈረው አርቲስት ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲማን) ዘርፉ የዝነኞችን የፊት ገፅታ መሰረት አድርጎ ልዩ ነገራቸውን የማጉላት አቅም እንደሚጠይቅም ያትታል። ይህን የሚያስረዳው በቅርቡ “ETHIO GLOBAL” አለማቀፋዊ ልዩ የፖርትሬት ካርቱን ፌስቲቫል ሲል በሰየመው የታዋቂ ሰዎችን ምስል የያዘች አዝናኝ እትም ላይ ነው።

ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ በካፒታል ሆቴል የታየው የፖርትሬት ካርቱን አውደ-ርዕይ ላይ በርካታ ተመልካቾች ተገኝተው ባዩት ምስል መዝናናታቸውን የገለፁ ሲሆን፤ አርቲስቱም የቀረቡት ስራዎች ተመልካቹን በማዝናናትና አዲስ እይታን ለማስተዋወቅ ያሰበ ስለመሆኑ ይናገራል።

በአራት ሺህ ኮፒ ታትሞ በአውደርዕይው ፕሮግራሙ ላይ የተዋወቀው የአርቲስት ቴዎድሮስን ስራዎችና የፀሐፊውን መልእክቶች ያካተተው መፅሐፍት በቀጣዩ ወር በቶሞካ አርት ጋለሪ የፓርትሬት ካርቱን አውደ-ርዕይ መክፈቻ ወቅት ለሽያጭ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል።

መፅሐፉ በአጠቃላይ ሰላሳ ሶስት የታዋቂና አንጋፋ ሰዎችን የፊት ምስል የያዘ ሲሆን፤ 24 የውጪ ሰዎችንና 9 የሚደርሱ የአገራችን ሰዎችን አካቶ አቅርቧል።

ከውጪዎቹ የፊት ገጽታቸው በአዝናኝ መልኩ ከተሰራባቸው ሰዎች መካከል 16ኛው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን፣ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ፣ የፊዚክስ ሊቁ አልበርት አንስታይን፣ 44ኛው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፣ የሬጌው የሙዚቃ ንጉስ ቦብ ማርሌይ፣ ተዋናዩና የማርሻል አርቲስቱ ጃኪ ቻን፣ የሰብዓዊ መብት ታጋዩ ማሃተመ ጋንዲ እና የደቡብ አፍሪካው አባት ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ ሌሎችም ተካተው ቀርበዋል።

 

                                      ባራክ ኦባማ   የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ

 

ከሀገር ውስጥ የፊት ገፅታቸው የፖርትሬት ካርቱን በመፅሃፉ ከተከታተላቸው ሰዎች መካከል ደግሞ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (በነገራችን ላይ 302ኛው የኢትዮጵያ መሪ ናቸው የሚል ማስታወሻ አብሮ ቀርቧል) ፣ ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ፣ ቢሊየነሩና በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ የሚታወቁት ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን፣ የሶል ሬብልስ መስራችና ባለቤት ቤተልሄም ጥላሁን፣ ድምጻዊት አስቴር አወቀ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጨምሮ ሌሎች ዝነኞችም አዝናኝ ምስላቸው ተካቶበታል።

በበርካቶች ዘንድ የኢትዮጵያውያኑ ዝነኛ ቁጥር አንሶ መታየቱ ምነው? ያስባለ ቢሆንም፤ አርቲስት ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲማን) “ግን፣ ስራዎቹ ከሀገር ውጪ በሚካሄድ በርካታ የስዕል አውደ ርዕይዎች ላይ መታየታቸው የማይቀር በመሆኑ አለማቀፋዊ ተመልካቾችንም ትኩረት እንዲስብ በማሰብ የሰራሁት ነው” ይላል። እዚህ'ጋ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የተፅዕኖ ፈጣሪዎች የፖርትሬት ካርቱን ስራዎች ላይ አርቲስት ሀረገወይን አሰፋ ለቴዲማን የፃፈችውን ማስታወሻ መመልከቱ ብቻ ይበቃል። “ሌላ አይነት ሐረገወይን አየሁኝ በጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ተፈልፍላ የተሰራች። ትንሽ ልጅ መሰለኝ ያየሁት። ራሴን ቅርፃ ቅርፅ ሆና ሳያት ደስ ብሎኛል፡ ሌላ ከእኛ በላይ ተፅዕኖ የፈጠሩ ኢትዮጵያውያንም ካርቱን ቢሰራ ጥሩ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ” ብላለች።

የአስተያየቶቹ ነገር ከተነሳ በመፅሐፉ በራሳቸው እጅ ፅሁፍ ቀርበው አዝናኝ ይዘት ካላቸው መልዕክቶች መካከል የሚከተሉትን መጠቃቀስ ይቻላል። አትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴ የራሱን የፖርትሬት ካርቱን ምስል ከተመለከተ በኋላ ባሰፈረው ማስታወሻ፣ “ፎቶዬን በካርቱን ስዕል አይቼው ስለማላውቅ አሁን በቴዲማን የተሰራው ስራ በደንብ አርጎ ስላስቀመጠኝ በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ” ብሏል።

የኢትዮፒካሊንክ ሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው ብርሃኔ ንጉሴ በበኩሉ ቀጣዩን አዝናኝ አስተያየት አስፍሮ ይነበባል። “አርቲስት ቴዲ ማን በታዋቂ ሰዎች ፊት አዝናኝ የሆነ የካርቱን ፖርትሬት ስዕሎችን ለአገራችን አስተዋውቋል። በዚህ ዘርፍም ፈር ቀዳጅ ሆኗል። ለዚህ ታሪካዊ ስራ ፊቴን ስለመረጠ አመሰግነዋለሁ። ወደፊትም ለተመሳሳይ ስራ ፊቴን እንደፈለገው እንዲጠቀምበት (እንዲጫወትበት) ፈቃዴ ነው። (ሳቅ)” የሚል ሃሳብ አስፍሯል።

አንጋፋው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በበኩሉ፣ “በስለጠኑትና በሌሎች አገሮች እንደምናውቀው ይህን አይነት የጥበብ ዘርፍ በፖለቲካዊም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ሁኔታዎች ከሰዎች አስገራሚ የመልክ አቀራረፅ ጋር የማቅረቡ ጥበብ እጅጉን የጎላ እና ጉልህ ቦታ ተሰጥቶት የሚደነቅ ነው። በአገራችንም እንደቴዲ ያሉ ባለሙያዎች ሊደነቁና በእጅጉ ሊበረታቱ ይገባል። ስለዚህ ቴዲ በርታ እላለሁ!!” ብሏል።

    መፅሐፉ በውስጣችን ያኖርናቸውን ዝነኞች በተለየ ገፅ እንድንመለከት ከማስቻሉም በተጨማሪ አዝናኝነቱ የጎላ ነው። የአርቲስቱን ጥበባዊ ነፃነት እያከበርንና እያደነቅን በሰራቸው የፖርትሬት ካርቱን ምስሎችም መገረምና መሳቅ የግላችን ይሆናል። የተመልካቹን የማስታወስና የማስተዋል አቅም ለመለካትም ከፖርትሬት ካርቱኑ በተጨማሪ የዝነኞቹ ምስል በፎቶግራፍም ተደግፎ ቀርቧል። ይህም በምስል ግምትና በምናየው ገጽታ መካከል ባለው የጎላ ልዩነት መዝናናት መፈጠሩ አይቀሬ ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15722 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 146 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us